የኢትዮጵያ እና የሩሲያ ኦርቶዶክስ አብያተ ክርስቲያናት የስኮላርሽፕ ትብብራቸውን ለማጠናከር ተስማሙ

Wednesday, 23 May 2018 13:40

 

-    ፓትርያርክ አቡነ ማትያስ በሩሲያ የ6 ቀናት ጉብኝት አድርገዋል

 

ከ120 ዓመታት በላይ ያስቆጠረውን የሁለትዮሽ ግንኙነታቸውን ዳግም ለማስቀጠል የተስማሙት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንና የሩስያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን፤ በደቀ መዛሙርትና በሊቃውንት ልውውጥ የስኮላርሽፕ ትብብራቸውን ለማጠናከር ተስማሙ።

የፓትርያርኩ ልዩ ጽ/ቤት እንዳስታወቀው፤ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ፣ የሞስኮና መላው ሩሲያ ፓትርያርክ ክሪል ባደረጉላቸው ሐዋርያዊ ግብዣ መሠረት፣ ከግንቦት 7 እስከ 13 ቀን 2010 ዓ.ም ያካሔዱትን የ6 ቀናት ጉብኝት አጠናቀው የተመለሱ ሲኾን፤ የቆየውንና በመካከሉ የቀዘቀዘውን የሁለትዮሽ ግንኙነት ዳግም ለማስቀጠል፣ የተማረ የሰው ኃይልም ለማፍራት የነጻ ትምህርት ዕድሉን ለማጠናከር ከስምምነት ተደርሷል።

የፓትርያርኩ ጉብኝትና የሁለቱ አብያተ ክርስቲያናት ግንኙነት የአገራቱን ረጅም ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነትንም እንደሚያጠናክረው የጠቀሱት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ሳርጌ ላብሮብም፣ ልዩ ልዩ የሥልጠና ዕድል እንደሚሰጥ ለፓትርያርክ አቡነ ማትያስ እንደገለፁላቸው መግለጫው አስፍሯል። ለዓለም ሰላም በጋራ ከመጸለይና ከመሥራት ባሻገር በማኅበራዊ ዘርፍና በልማትም ለመተባበር ከስምምነት መደረሱን ጠቁሟል። የፓትርያርኩ ልዩ ጽ/ቤት የላከው ሙሉ መግለጫ እንደሚከተለው ቀርቧል።

  

ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት በሩሲያ ኦርቶዶክስ የሞስኮና መላው ሩሲያ ፓትርያርክ ክሪል ባደረጉላቸው ሐዋርያዊ ግብዣ የስድስት ቀናት ጉብኝት አድርገው ተመለሱ።

ቅዱስነታቸውና ልዑካኑ፣ በሞስኮ የአየር ማረፊያ ሲደርሱ፣ የሩስያ ቅዱስ ሲኖዶስና የኢትዮጵያ ፌደራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ባለሙሉ ሥልጣን አምባሳደር አቶ ግሩም አባይና የሥራ ባልደረቦቻቸው ደማቅ አቀባበል አድርገውላቸዋል።

የሞስኮና የመላው ሩሲያ ቅዱስ ፓትርያርክ ክሪል፣ ለቅዱስነታቸው በሞስኮ የመድኀኔዓለም ካቴድራል የእንኳን ደኅና መጡ ንግግር አድርገው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ታላቅ ቤተ ክርስቲያን ስትሆን በአባቶችና በእናቶች ጥንካሬ ተጠብቃ ለዓለም አርአያ ሆና የምትጠቀስ ቤተ ክርስቲያን መሆኗን ገልፀው፤ የፓትርያርኩና የልዑካኑ መምጣት ለነበረን ጠንካራ ግንኙነት ጥንካሬና ጉልበት ይሆነናል ብለዋል፤ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ፓትርያርክ ቀደም ሲል የነበረው ግንኙነት በመካከሉ የቀዘቀዘ እንደነበር ጠቅሰው አሁን ወደነበረበት የሁለትዮሽ ግንኙነት ተጠናክሮ እንዲቀጥል የተማረ የሰው ኃይልም ለማፍራት የነፃ ትምህርት ዕድልም እንዲከፈት በአጽንኦት ገልጸዋል። የሩሲያ ቤተ ክርስቲያን ፓትርያርክም፣ የነበረ ግንኙነታችን ተጠናክሮ ይቀጥላል። የነፃ የትምህርት ዕድሉም ይሰጣል በማለት የገለፁ ሲሆን፤ በምዕራባውየን እየታየ ያለውን የክርስቲያናዊ ሕይወት ፈተና በጋራ የመቋቋም የሁለቱም አብያተ ክርስቲያናት ትብብር አስፈላጊ መሆኑን ገልጸዋል።

ቅዱስነታቸው በዕለቱ ከሩሲያው ፌዴሬሽን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ሚስተር ሳርጌ ላብሮብ ጋር ውይይት አድርገዋል፤ ቅዱስነታቸው የሁለቱን አብያተ ክርስቲያናት የቆየ ግንኙነት አብራርተው፣ በሀገር ደረጃም ከ120 ዓመታት በላይ ያስቆጠረ መሆኑን፣ በመካከል ግን እየቀዘቀዘ መምጣቱን ገልፀው፣ ይህን ግንኙነት ዳግም ለማጠናከር ቤተ ክርስቲያኗ በሰፊው እየሠራች እንደሆነ ገልፀውላቸዋል፤ ለዓለም ሰላም መጸለይ የዘወትር የቤተ ክርስቲያኗ ተግባር ቢሆንም፣ በሶርያና በአንዳንድ የሰሜን የአፍሪካ ሀገራት ሰላም እንደሚያስፈልግ ገልፀው በማኅበራዊ ዘርፍ በልማት በጋራ መሥራት እንዲሁም የተቋረጠው የትምህርት ዕድል በሚቀጥልበት ሁኔታ ተወያይተዋል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ጥንታዊት፣ ታሪካዊት በተክርስቲያን መሆኗን ገልፀው፤ ከኢትዮጵያ ሕዝብ ጋር የረጅም ጊዜ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት የሩሲያ መንግሥትና የኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን እንደነበራቸው ለወደፊቱም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ልዩ ልዩ የሥልጠና ዕድልም እንደሚሰጥ አብራርተው ፓትርያርኩ ሩሲያን መጎብኘት የበለጠ የሚያጠናክረው ይሆናል በማለት ገልፀዋል።

ቅዱስነታቸው ከሩሲያን ፌደሬሽን ምክትል አፈ ጉባኤ ከሚስተር ኒኮላይ ፌዮዶሮብና ከምክር ቤቱ አባላት ጋር ውይይት አድርገዋል፤ አፈ ጉባኤውም የሁለቱ አብያተ ክርስቲያናት ግንኙነት ለሁለቱም ሀገራት ጠቃሚ መሆኑን ገልፀው፤ የቅዱስነታቸው ጉብኝት ታሪካዊ እንደሆነና የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነት መጠናከር መልካም አጋጣሚ እንደሆነ ገልፀዋል፤ ቅዱስነታቸውም በበኩላቸው፣ የዚህ ጉብኝት ዋና ዓላማም የቆየውን ግንኙነት ማጠናከር ስለ ዓለም የሰው ልጆች ደህንነት ማሳሰብና መጸለይ በልማቱም ዙሪያ ትብብር እንዲኖረን የልምድ ልውውጥ እድልም እንዲከፈት ከአሁን በፊት ተምረው የመጡ የቤተ ክርስቲያን አባቶች በከፍተኛ የቤተ ክርስቲያኒቱ የሥልጣን እርከን በማገልገል ላይ መሆናቸውን አውስተው፤ አሁንም ይህ ተግባር እንደሚቀጥል ምኞታቸውን ገልፀዋል።

በፓትርያርኩ የግራንድ ክሬሚልን ቤተ መንግሥትና ከፍተኛ የመንፈሳዊ ዩኒቨርስቲ ቲዮሎጂካል ኮሌጆች ተጎብኝተዋል።

በመጨረሻም በሩሲያ የኢትዮጵያ ባለሙሉ ሥልጣን አምባሳደርና የኤምባሲው ሠራተኞች እንዲሁም የዲያስፖራው ማኅበረሰብ የራት ግብዣ የተደረገ ሲሆን፤ ቅዱስነታቸው በግብዣው ላይ ለነበሩት ኢትዮጵያውያን፣ አሁን ሀገራችን ኢትዮጵያ እያደገች በመሆኗ፣ እናንተም ወደሀገራችሁ ተመልሳችሁ ሥራ መሥራት ይጠበቅባችኋል፤ በማለት አባታዊ ምክራቸውን ለግሰዋል። ልዑኩ በሩሲያ የነበረውን ሐዋርያዊ ጉብኝት አጠናቆ ከትናንት በስቲያ ሰኞ ጠዋት አዲስ አበባ ገብቷል።¾  

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
2423 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 137 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us