ሰማያዊ፣ መድረክ እና ኢዴፓ በዶ/ር አብይ አህመድ ላይ የተቃጣውን የግድያ ሙከራ አወገዙ

Wednesday, 27 June 2018 12:29

 

በይርጋ አበበ

ባሳለፍነው ቅዳሜ ሰኔ 16 ቀን 2010 ዓ.ም ረፋድ በመስቀል አደባባይ በተካሄደው ሰላማዊ ሰልፍ ላይ በተገኙት ጠ/ሚ ዶ/ር አብይ አህመድ ላይ የተቃጣውን የግድያ ሙከራ ሶስት አገር አቀፍ ፓርቲዎች እንደሚያወግዙት አስታወቁ።

“የኢትዮጵያን ሉዓላዊነትና የህዝቦቿን መፈቃቀር በጠንካራ ተቋማዊ አደረጃጀቶች ላይ መገንባት የወቅቱ ጥያቄ ነው” ሲል መግለጫ ያወጣው ሰማያዊ ፓርቲ፤ “ሰኔ 16 ቀን 2010 ዓ.ም የኢትዮጵያ ጠ/ሚ ዶ/ር አብይ አህመድ በሁለት ወራት ውስጥ የኢትዮጵያን ህዝብ በማሳረፍ አገራዊ መግባባት ለመፍጠር ያደረጉትንና እያደረጉ ያሉትን ጥረት ለመደገፍና የለውጡን ሂደት ለማበረታታት የአዲስ አበባ ህዝብ በነቂስ መስቀል አደባባይ መገኘቱ እጅግ አኩሪ ተግባር ነው” ብሏል። ፓርቲው አያይዞም ዶ/ር አብይ አህመድ በቦታው ተገኝተው ያደረጉት ንግግርም “ታሪካዊ” መሆኑን ገልፆ ሆኖም እሳቸውን ዒላማ ያደረገ የግድያ ሙከራ “የለውጥ ጅማሮ ያስበረገጋቸው አንዳንድ እኩያን ድርጊት ነው። የድርጊቱ ፈፃሚዎችም በአስቸኳይ ለፍርድ ይቅረቡ” ሲል ጠይቋል።

የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ አንድነት መድረክ (መድረክ) በበኩሉ፤ ዶ/ር አብይ ስልጣን ከያዙ በኋላ የተገኙ ድሎችን አድንቆ መግለጫውን ይጀምርና የዶ/ር አብይን የለውጥ ጅማሮ እውቅና በመስጠት በተሰለፈው ህዝብ ላይ የእጅ ቦምብ ተወርውሮ ሁለት ሰው መሞቱንና 165 መጎዳታቸውን አስታውቋል። ፓርቲው በዚሁ መግለጫው “ይህ አስፀያፊ የሆነው የፀረ- ዴሞክራሲ ኃይሎች ድርጊት ለሰብአዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች መከበር ቆርጦ የተነሳውን ህዝባችንን ከፅኑ አቋሙና ትግሉ ቅንጣት ታህል ወደኋላ እንደማይመልሰው እየገለፅን የፀረ ዲሞክራሲና የአሸባሪነት ተግባራቸውን በፅኑ እናወግዛለን” ብሏል።

ፓርቲው አያይዞም “ሰፊው የኢትዮጵያ ህዝብ በብሔርና ሌላ ልዩነት ሳይከፋፈል ለከፋፋይ ኃይሎችም አንዳች ቀዳዳ ሳይሰጥ በሰላማዊ አግባብ ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶቹን እንዲያስከብር ጥሪ እናቀርባለን” ብሏል።

“ንፁሀን ዜጎችን የጥቃት ሰለባ በማድረግ የሚገኝ የፖለቲካ ትርፍ አይኖርም” ሲል ሰኔ 18 ቀን 2010 ዓ.ም መግለጫ ያወጣው ደግሞ ኢዴፓ ነው። ፓርቲው በመግለጫውም ኢትዮጵያ ላለፉት ሶስት ዓመታት በችግር ላይ መቆየቷን ገልጾ ሆኖም አዲሱ የዶ/ር አብይ አስተዳደር ችግሩን ለመቅረፍ እየሰራ መሆኑን ገልጿል። ፓርቲው በመግለጫው “ይህንንም ጅምር የለውጥ ምልክቶች ለማበረታታትና ተጠናክሮ እንዲቀጥል በጎ ግፊት ለማሳደር የሚያስችል የድጋፍ ሰልፍ በግለሰቦች አነሳሽነት ተጠርቶ ሰኔ 16 ቀን 2010 ዓ.ም መደረጉ ይታወቃል። የሰላማዊ ሰልፉ ማጠናቀቂያ አካባቢ የተፈጠረው ኢ-ዴሞክራሲያዊና ኢ-ሰብአዊ እንዲሁም ከኢትዮጵያዊያን ባህል ውጪ የሆነ ድርጊት ፓርቲያችን በእጅጉ አሳዝኖታል” ብሏል።

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
129 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 914 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us