ኢንጅነር ታከለ ኡማ የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባ ሆነው ተሾሙ

Wednesday, 18 July 2018 15:26

 

የተሻሻለውን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ቻርተር አዋጅ ለማሻሻል በቅርቡ ለሕዝብ ተወካዮች ምክርቤት ቀርቦ በጸደቀው አዋጅ መሠረት የአዲስ አበባ ከተማ ምክርቤት አባል ያልሆኑት ኢንጅነር ታከለ ኡማ በንቲ በትላንትናው ዕለት በምክትል ከንቲባነት ተሾሙ።

አዲሱ ተሿሚ አቶ ታከለ ኡማ በትላንትናው ዕለት በተካሄደው የአዲስ አበባ ከተማ ምክርቤት ልዩ ስብሰባ ላይ በምክትል ከንቲባነት የተሾሙ ሲሆን፤ ተሰናባቹን የቀድሞ ከንቲባ አቶ ድሪባ ኩማን ኃላፊነት ሙሉ ለሙሉ ተክተው እንደሚሰሩ ታውቋል።

በዚህ ሹመት መሠረት በቀጣይ ዓመት ምርጫ እስከሚካሄድ ድረስ ኢንጂነር ታከለ የአዲስ አበባ ከተማን በምክትል ከንቲባ ይመራሉ። የተሻሻለው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ቻርተር አዋጅን ለማሻሻል ሰሞኑን በፓርላማ የጸደቀው አዋጅ የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ ከምክርቤቱ አባላት መካከል እንደሚመረጥ የደነገገ ሲሆን ምክትል ከንቲባው ግን ከምክርቤቱ አባላት ውስጥ ወይንም ከምክርቤቱ አባላት ውጭ ሊሾም እንደሚችል መደንገጉ ይታወሳል።

ኢንጂነር ታከለ ኡማ ከሹመቱ በኋላ በግል የማሕበራዊ ድረገፃቸው እንዳሰፈሩት፣ “ሀገራችን በተስፋና በአንድነት ጉዞ ላይ ባለችበት በዚህ ወቅት የኢትዮጵያ ዋና ከተማ አዲስ አበባን ማገልገል ክብርና መታደል ነው” ብለዋል።

አያይዘውም፣ አዲስ አበባ የሁሉም ክልሎች፣ ሃይማኖቶች እና በተለያዩ ማሕበራዊ መደቦች ውስጥ የሚገኙ የሕብረተሰብ ክፍሎች ነች። እንዲሁም የተለያዩ ብሔሮች፣ እምነቶችና የኢኮኖሚ ብዝሃነት ያለባት ከተማ መሆኗን ገልጸዋል። የተለያዩ ችግሮች በከተማዋ ውስጥ እንደሚገኙም ከንቲባው አስታውሰው፤ ለከተማው ሕዝብ አብረን ከሰራን እንለውጠዋለን ሲሉ፤ ቃል ገብተዋል።

ቅርበት ካላቸው ወገኖች በተገኘ መረጃ መሠረት፤ አቶ ታከለ ኡማ የተወለዱት በምዕራብ ሸዋ አምቦ ከተማ ነው። የአንደኛና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በአምቦ ከተማ ተከታትለዋል። በሲቪል ምህንድስና ኢንጂነሪንግ የመጀመሪያና ሁለተኛ ዲግሪያቸውን ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ወስደዋል። የአዲስ አበባ ከንቲባ ከመሆናቸው በፊት በኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት የመንገድና ትራንስፖርት ቢሮ ኃላፊ እና የካቢኔ አባል በመሆን አገልግለዋል። ቀደም ባሉት ጊዜያት የሆለታ ከንቲባ እና የአምቦ መሬት አስተዳደር የቢሮ ኃላፊ ሆነው ሠርተዋል።

በተጨማሪም የአዲስ አበባ አስተዳደር ምክርቤት፤ የከተማዋ ትራንስፖርት ቢሮ ኃላፊ የነበሩትን ዶ/ር ኢንጂነር ሰለሞን ኪዳኔ እና የከተማዋ የኮምዩኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ የነበሩትን ወ/ሮ ዳግማዊት ሞገስን በምክትል ከንቲባነት ማዕረግ ሾሟል።

የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አቶ ድሪባ ኩማ እና አቶ አባተ ስጦታው በአምባሳደርነት መሾማቸው በመገናኛ ብዙሃን ሰሞኑን መነገሩ አይዘነጋም።¾

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
188 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 171 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us