ጂቡቲ በኢትዮ ኤርትራ አዲሱ ግንኙነት ደስተኛ አይደለችም

Wednesday, 25 July 2018 13:33

አዲሱ የኢትዮ ኤርትራ ግንኙነት በርካታ ሀገራትንና ዓለም አቀፍ ተቋማትን ያስደሰተ ቢሆንም ጂቡቲን ግን ያላስደሰተ መሆን የደይሊ ኔሽን ዘገባ አመልክቷል። ዘገባው በሁለቱ ሀገራት አዲስ የሰላም ግንኙነት ኬኒያን ጨምሮ በርካታ ሀገራትና የተባበሩት መንግስታት ሳይቀሩ ደስታቸውን የገለፁ መሆኑን በማመልከት በጂቡቲ በኩል ግን ይህ ሁኔታ ያልታየ መሆኑን አመልክቷል።

 

ኤርትራ ከኢትዮጰያ.ቀደም ብሎም ከየመን ከዚያም ከጂቡቲ ጋር የድንበር ውዝግብ ውስጥ በመግባት ጦር መማዘዟን ተከትሎ እንደዚሁም በሶማሊያ የውስጥ ጉዳይ ሳይቀር ጣልቃ በመግባት ከአልቃይዳ ጋር ቀጥተኛ ትስስር አለው የሚባለውን አልሸባብን ሳይቀር ትረዳለች መባሉ ለተባበሩት መንግስታት የፀጥታው ምክር ቤት ማዕቀብ ዳርጓት ቆይቷል። ሆኖም በቅርቡ ከኢትዮጵያ ጋር ሰላም ማውረዷን ተከትሎ ከአስመራ ጉብኝታቸው መልስ ከተባበሩት መንግስታት ዋና ፀሀፊ አንቶኒዮ ጉተሬዝ ጋር በአዲስ አበባ የተገናኙት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አቢይ አህመድ የመንግስታቱ ድርጅት በኤርትራ ላይ የጣለውን ማዕቀብ እንዲያነሳ መጠየቃቸው ይታወሳል።


ይሁንና እንደ ደይሊ ኔሽን ዘገባ ከሆነ ጂቡቲ ይህንን የኢትዮጵያ አቋም ክፉኛ ተቃውማለች። ከዚሁ ጋር በተያያዘ የጂቡቲ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር መሀመድ አሊ የሱፍ በሰጡት ማብራሪያ በኤርትራ ላይ የተጣለው ማዕቀብ የሚነሳ ከሆነ በሀገራቸው ላይ አሉታዊ ተፅዕኖን የሚያሳድር መሆኑን እንደገለፁ ዘገባው ጨምሮ ያመለክታል። ኤርትራ በተባበሩት መንግስታት የተጣለባት ማዕቀብ የሚያበቃው በመጪው ህዳር ወር 2011 ዓ.ም ሲሆን የጂቡቲም ስጋት ማዕቀቡ እንደተለመደው ላይራዘም ይችላል የሚል ነው።


ከሁለቱ ሀገራት የፖለቲካ ውዝግብ ባለፈ የኢትዮ ኤርትራን የድንበር ጦርነት ተከትሎ ሙሉ በሙሉ የጂቡቲ ወደብ ጥገኛ የሆነችው ኢትዮጵያ የኤርትራን ወደቦች ለመጠቀም ዝግጅት ማድረጓ ጂቡቲን ያሳሰባት መሆኑን መረጃዎች ያመለክታሉ። ጂቡቲ ባለፉት ሁለት አስርት ዓመታት በወደብ ኢንቨስትንመት ላይ ሰፊ ሥራን የሰራች ሲሆን አብዛኛው የኢትዮጵያን የወደብ ተጠቃሚነት ታሳቢ ያደረገ ነው። የኢትዮ-ኤርትራ የሰላም ግንኙነት ፍፁም ያልተጠበቀና ፈጣን መሻሻል ማሳየቱ የጂቡቲን ሰፊ ወደብ ነክ እቅዶች በተፈለገው ጊዜ ግባቸውን እንዳይመቱ የሚያደርግ ይሆናል።


ጂቡቲና ኤርትራ የተካረረ የፖለቲካ ውዝግብ ውስጥ የገቡት እ.ኤ.አ በ1990ዎቹ መጀመሪያ ራስ ዱሜራ በተባለ ግዛት የይገባኛል ጥያቄ መነሳቱን ተከተሎ ነው። ከዚሁ ጋር በተያያዘ ሁለቱ ሀገራት ጦር የተማዘዙ ሲሆን የኳታር ወታደሮች በአወዛጋቢው ክልል ለዓመታት በመስፈር ውዝግቡ ወደለየለት ጦርነት እንዳያመራ ጥረት ሲያደርጉ ቆይተዋል። የኢትዮ ኤርትራ የሰላም ስምምነት ተከትሎም ጂቡቲ የተባበሩት መንግስታት ከኤርትራ ጋር እንዲያሸማግላትና ሰላም እንዲወርድ እንዲያደርግ በይፋዊ ደብዳቤ ጥያቄ ማቅረቧ የሚታወስ ነው።

ይምረጡ
(9 ሰዎች መርጠዋል)
2507 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 1066 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us