You are here:መነሻ ገፅ»news-sendek»ፀጋው መላኩ - Sendek NewsPaper
ፀጋው መላኩ

ፀጋው መላኩ

 

እንደ ኢትዮጵያ ባሉ ድሃ ሀገራት ሰዎች ሰርተው እንዳይለወጡ ከሚያደርጉ መሰረታዊ ምክንያቶች መካከል አንደኛው የገንዘብ እጥረት ነው። ከገንዘብ እጥረት ጋር በተያያዘ እውቀት ባላቸው የምርምር ሰዎች የተሰሩ የአዕምሮ የፈጠራ ስራዎች መሬት መንካት አልቻሉም።

 

መደበኛ ባንኮች በብድር አቅርቦት መድረስ የሚችሉት ለብድሩ በቂ ማስያዣ ማቅረብ የሚችለውን የህብረተሰብ ክፍል ብቻ በመሆኑ በኢትዮጵያ እጅግ የሚበዛው የህብረተሰብ ክፍል ከባንክ ብድር ስርዓት ውጭ መሆኑ ይታወቃል። ይህም በመሆኑ በአነስተኛ ደረጃ የሚገኙ የንግድ ተቋማት የመደበኛው ባንክ ብድርን መስፈርት ማሟላት የሚችሉበት እድል ባለመኖሩ የንግድ ሥራቸውን በተፈለገው መጠን ማስፋፋትና ማሳደግ የሚችሉበት እድል የለም። በኢትዮጵያ አሁን በሚታየው ተጨባጭ ሁኔታ የባንክ ብድር ማስያዣ የሌላቸው ግለሰቦች ተበድረው መማር፣ቢዝነሳቸውን ማካሄድም ሆነ ሌሎች ሥራዎቻቸውን ማከናወን አይችሉም። በበርካታ ያደጉ ሀገራት በአንድ መልኩ የህብረተሰቡ የገቢ አቅም፤ በሌላ አቅጣጫ ደግሞ ባንኮች ከማስያዣ ውጭ የሚያበድሩባቸው አማራጮች ሰፊ በመሆናቸው ዜጎች ከባንኮች ተበድረው የሃሳብ ውጥናቸውን እውን የማድረግ እድላቸው ሰፊ ነው።

 

ካለው አሰራርና ከዜጎች የመበደር አቅም ማነስ ጋር በተያያዘ በኢትዮጵያ የባንክ ተበዳሪነት አቅም ያላቸው ዜጎች በጣም ውስን ናቸው። ይህንን መሰረታዊ ችግር ፈቶ ዜጎች በቀላሉ ብድር አግኝተው ሀሳባቸውን እውን እንዲሆን በማድረጉ ረገድ ሰፊ ሚና የሚጫወቱት የገንዘብ ቁጠባና ብድር ህብረት ሥራ ማህበራት ናቸው። የገንዘብ ቁጠባና ብድር ህብረት ሥራ ማህበራት የባንክ ብድር ሊያገኙ የማይችሉ የህብረተሰብ ክፍሎችን ብድር እንዲያገኙ በማድረጉ ረገድ ያላቸው ሚና እጅግ ከፍተኛ ነው። የህብረት ሥራ ማህበራት በግለሰቦች ተቋቁመው ከአባሎቻቸው የቁጠባ ገንዘብን በመሰብሰብ፤ የሰበሰቡትን የቁጠባ ገንዘብ መልሰው ለአባሎቻቸው የሚያበድሩ ህጋዊ ሰውነት ያላቸው አነስተኛ የፋይናንስ ተቋማት ናቸው።

 

እነዚህ የቁጠባና የብድር የፋይናንስ ተቋማት በመስሪያ ቤት ደረጃ እንደ ኢትዮጵያ አየር መንገድ፣ መንገዶች ባለስልጣንና በመሳሰሉት እድሜ ጠገብ መንግስታዊ መስሪያ ቤቶች ረዥም እድሜን ያስቆጠሩ ናቸው። በዚህም ቀደም ባሉት ዓመታት በርካቶች ቆጥበው የከተማ ቤት ባለቤት እስከመሆን ደርሰዋል። ከኢህአዴግ መንግስት ወደ ስልጣን መምጣት በኋላ  ከመስሪያቤት ማህበራት ባለፈ ማንኛውንም ዜጋ ሊያቅፉ የሚችሉ በርካታ ማህበረሰብ አቀፍ የገንዘብ ቁጠባና ብድር ኅብረት ሥራ ማህበራት ተቋቁመው በመላ ሀገሪቱ በመስፋፋት ላይ ይገኛሉ። እነዚህን ተቋማት የሚያደራጅ፣የሚመዘግብና ድጋፍ የሚሰጥ አካል ተቋቁሞም ሰፊ ሥራን በመስራት ላይ ነው።

አነስተኛ የቁጠባና ብድር ተቋማት በአለም አቀፍ ደረጃም ረዥም ታሪክ ያላቸው ናቸው። እንደ ፌደራል ህብረት ሥራ ማህበራት ኤጀንሲ መረጃ ከሆነ በዓለም ለመጀመሪያ ጊዜ ገንዘብ ብድርና ኅብረት ሥራ ማህበራት ቁጠባ የተጀመረው እ.ኤ.አ በ1840ዎቹ መጨረሻ አካባቢ በጀርመን ሀገር ነው። ከዚያም አሰራሩ በስፋት ተቀባይነትን በማግኘቱ በሂደት በዚያው በአውሮፓ እንደዚሁም በቀሪው የዓለም ክፍል መስፋፋት ችሏል።

በኢትዮጵያም የገንዘብ ቁጠባና ብድር ኅብረት ሥራ ማህበራትን ለማጠናከር ከ1950ዎቹ ከዓፄ ኃይለ ሥላሴ ጀምሮ የተለያዩ አዋጆች ሲወጡ የቆዩ መሆኑን መረጃው ጨምሮ ያመለክታል። እንደ ፌደራል ኅብረት ሥራ ማህበራት ኤጀንሲ መረጃ ከሆነ በአሁኑ ሰዓት በሀገሪቱ ከ17 ነጥብ 1 ቢሊዮን ካፒታል ያፈሩ 15 ነጥብ 4 ሚሊዮን አባላት የያዙ እንደዚሁም 11 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር በላይ የቁጠባ ገንዘብን ማሰባሰብ የቻሉ ከ78 ሺህ በላይ መሰረታዊ የህብረት ሥራ ማህበራት፣  373 የኅብረት ሥራ ዩኒየኖች እና 4 የህብረት ሥራ ፌደሬሽኖች በኢትዮጵያ ይገኛሉ። እነዚህ የቁጠባና የብድር ተቋማት በተለይ በገጠሩ የሀገሪቱ ክፍል የሚገኘው አርሶና አርብቶ አደሩ ቆጥቦና ተበድሮ በምርት ግብይትና በግብርና ምርቶች ማቀነባበር ሥራ እንዲሰማራ የገንዘብ አቅምን እየፈጠሩ መሆኑ ታውቋል።

የቁጠባና ብድር ማህበራቱ በከተማም ቢሆን ዜጎች ቆጥበው በመበደር በልዩ ልዩ የሥራ መስኮች እንዲሰማሩ በማድረግ ላይ ናቸው። በቆጣቢ አባላት ቁጥር በገጠር ያለው የአባላት እድገት ከከተማው አንፃር ሲታይ የተሻለ ለውጥ ይታይበታል። በከተማው በገንዘብ ቁጠባና ብድር ኅብረት ሥራ ማህበራት ተደራጅቶ የሚቆጥበው ዜጋ ቁጥር እድገት ከገጠሩ አንፃር ሲታይ አነስተኛ ቢሆንም፤ የከተማው የግለሰብ አማካይ የቁጠባ ዕድገት  ሲታይ ግን ከገጠሩ በእጅጉ የተሻለ ሆኖ ይታያል።  

 የፌደራል ኅብረት ሥራ ኤጀንሴ ዋና ዳይሬክተር አቶ ኡስማን ስሩር ባንኮችና የገንዘብ ቁጠባና ብድር ህብረት ሥራ ማህበራት አንድ የሚያደርጓቸው ባህሪያት እንዳሉ ሁሉ የሚለያዩባቸውም አሰራሮች መኖራቸውን ገልፀውልናል። እንደ አቶ ኡስማን ገለፃ ሁለቱም ተቋማት የቁጠባ ገንዘብን በማሰባሰቡ ረገድ አንድ ናቸው። ሆኖም የገንዘብ ቁጠባና ብድር የኅብረት ሥራ ማህበራት በቁጠባ ለማበደር የተቋቋሙ ተቋማት በመሆናቸው በቁጠባ ሥርዓት ውስጥ ለገቡ አባላቶቻቸው ብድር የሚፈቅዱ ናቸው።  አንድ ሰው የቁጠባና ብድር ማህበራቱ አባል ከሆነ በኋላ ብድር ለማግኘት ለተከታታይ ስድስት ወራት መቆጠብ ይጠበቅበታል።

አባሉ ለቆጠበው ገንዘብ ወለድ የሚያገኝ ሲሆን ለተከታታይ ስድስት ወራት ከቆጠበ በኋላ የቆጠበውን ገንዘብ ሶስት እጥፍ መበደር የሚችል መሆኑን ከአቶ ኡስማን ገለፃ መረዳት ችለናል። የገንዘብ ቁጠባና ብድር የኅብረት ሥራ ማህበራት በባንኮች ተደራሽ ሊሆን የማይችለውን የህብረተሰብ ክፍል የብድር ፍላጎት ለማሟላት የሚደረጉና ውጤትም ያመጡ ጥረቶች ቢኖሩም በዚያው መጠን በርካታ ችግሮችም ያሉ መሆኑን ከሰሞኑ በአዳማ ከረዩ ሆቴል የተካሄደው የገንዘብ ቁጠባና ብድር ኅብረት ሥራ ማህበራት አገራዊ ንቅናቄ ማቀጣጠያ መድረክ ላይ የተሰጡ አስተያየቶች ያመለክታሉ። በዘርፉ ከሚታዩት ችግሮች መካከል አንደኛው የአባላት የቁጠባ መጠን እና የተበዳሪዎች ፍላጎት መመጣጠን አለመቻል ነው። 

በዚህ በኩል በመሰረታዊነት የታየው ችግር ማህበራቱ የአባሎቻቸውን ቁጥር በማብዛት የተሻለ ቁጠባን ማሰባሰብ አለመቻል ነው። ከዚህም በተጨማሪ ከንግድ ባንኮች ጋር ትስስር መፍጠር አለመቻልም አንዱ ችግር ተደርጎ በዚሁ ጉባኤ ላይ ተመልክቷል። ባንኮች በፋይናንስ አያያዝ ብዙ ልምድና አቅም ያላቸው ናቸው። ከዚህም በተጨማሪ ብድር ላይ ያልዋለ በርካታ ተቀማጭ ገንዘብን አከማችተው የሚይይዙበት ሁኔታም አለ። ሆኖም ንግድ ባንኮች ከገንዘብ ቁጠባና ብድር ኅብረት ሥራ ማኅበራት ጋር የአሰራር ትስስር የሌላቸው በመሆኑ ለማህበራቱ ገንዘብ የሚለቁበት አሰራር የለም።

የህብረት ሥራ ማህበራቱ በአንፃሩ በራሳቸው ገንዘብ የሚያስቀምጡበት ሁኔታ ስለሌለ ከአባሎቻቸው የሰበሰቡትን የቁጠባ ገንዘብ የሚያስቀምጡት በንግድ ባንኮች ነው። ቁጠባን በማሰባሰቡ ረገድ መደበኛ ባንኮች መድረስ የማይችሉትን የገጠሩን ክፍል በቀላሉ በመድረስ ሰፊ ቁጠባን ማሰባሰብ የሚችሉት የገንዘብ ቁጠባና ብድር የኅብረት ሥራ ማህበራት ናቸው። ይህም ንግድ ባንኮች ቁጠባን ለማሰባሰብ የሚያወጡትን ገንዘብና ጊዜን የሚቆጥብ፤ ብሎም ጥረቶቻቸውን የሚያግዝ ነው። ሆኖም ንግድ ባንኮች በአንፃሩ ለማህበራቱ የሚያደርጉት ብድር የማመቻቸት ሥራም ሆነ ሙያዊ እገዛ የለም።

ይህ በገንዘብ ተቋማቱ መካከል የሚታየው የትስስር ክፍተት መፍትሄ እንዲበጅለት ማህበራቱ ጠይቀዋል። በጉባኤው ከተሰጡት አስተያየቶች መረዳት እንደተቻለው ንግድ ባንኮች ማህበራቱ ለአባሎቻቸው የሚያበድሩትን ገንዘብ በመልቀቁ ረገድ አንድ መተማመኛ የሚሆን ነገርን ይፈልጋሉ። በሁለቱ መካከል መተማመንን በመፍጠር በባንኮች ያለስራ የተቀመጠው ገንዘብ በህብረት ሥራ ማህበራቱ በኩል በብድር ለልማት መዋል እንዲችል አንድ የሆነ ሥርዓት እንዲበጅ የህብረት ሥራ ማህበራቱ ፍላጎት ነው።

አቶ ሽመልስ ተክሉ በአዋሽ ባንክ የአዳማ ሪጅን ሥራ አስኪያጅ ናቸው። በዚሁ ጉባኤ ላይ የተገኙ ሲሆን በነበረው ውይይት ላይ የገንዘብ ቁጠባና ብድር ህብረት ሥራ ማህበራት በኩል ያለው የፋይናንስ አቅም ውስንነት የማህበራቱን የማበደር አቅም የተፈታተነው መሆኑን የተረዱ መሆናቸውን ገልፀውልናል። ይህም ቀጣይ የንግድ ባንኮች የቤት ሥራ ተደርጎም ሊወሰድ የሚገባው ሥራ መሆኑንም ገልፀውልናል። ከዚሁ ጋር በተያያዘም ሊፈታ የሚገባው ወሳኝ ጉዳይ ለብድር ዋስትና የሚጠየቀው ማስያዣ በመሆኑ፤ ይህንን ችግር ተፈትቶ ማህበራቱ ለአባሎቻቸው የሚሰጡትን ብድር ከንግድ ባንኮች ጭምር የሚያገኙበት አሰራር እንዲፈጠር ተከታታይ ስራዎች ሊሰሩ የሚገባ መሆኑን አቶ ሽመልስ ገልፀውልናል። ትስስሩ የጋራ ጥቅም ያለው በመሆኑ ክፍተቶቹን በመፍታት ሁለቱንም የጋራ ተጠቃሚ ማድረግ የሚያስችል መሆኑ ሀላፊው ጨምረው ገልፀውልናል።

ከፋይናንስ ድጋፍ ባለፈ የባለሙያና የስልጠና ድጋፍን ጭምር ንግድ ባንኮች የሚሰጡበት ሁኔታ መኖር ያለበት መሆኑን አቶ ሽመልስ አመልክተዋል። ሌላኛው የተነሳው ችግር የቁጠባና ብድር ህብረት ሥራ ማህበራቱ አባላትን አብዝቶ የቁጠባ ገንዘብን በማሰባሰቡ ረገድ ሰፊ ውስንነት የሚታይባቸው መሆኑ ነው። በዚህ በኩልም ሰፊ ስራ መሰራት ያለበት መሆኑ ተመልክቷል። በዚህም በሀገሪቱ ከሚሰበሰበው የቁጠባ መጠን ውስጥ የገንዘብ ቁጠባና ብድር ኅብረት ሥራ ማህበራትን ድርሻ በሁለተኛው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ማጠናቀቂያ ወደ 5 በመቶ ለማሳደግ እቅድ የተያዘ መሆኑ ታውቋል።

አቶ ዘሪሁን ሸለመ ይባላሉ የአዋጭ የገንዘብ ቁጠባና ብድር ኅብረት ሥራ ማህበር መስራችና ስራ አስኪያጅ ናቸው፡፡ በአዲስ አበባ ከተማ የየመስሪያቤቱን የቁጠባ ማህበራት ጨምሮ ከአንድ ሺህ አራት መቶ በላይ ማህበረሰብ አቀፍ የብድርና ቁጠባ ማህበራት ያሉ መሆኑን ገልፀውልናል፡፡ ማህበሩ በ41 አባላት የተጀመረ መሆኑን ያመለከቱት አቶ ዘሪሁን፤ በአሁኑ ሰዓት ከ4 ሺህ በላይ አባላትን አቅፎ የያዘ መሆኑን አመልክተዋል፡፡ ይህ ማህበር ሲጠነሰስ በ15 ሺህ 6 መቶ ብር ካፒታል የተጀመረ ሲሆን በአሁኑ ሰዓት ወደ 63 ሚሊዮን ብር ደርሷል፡፡  የህብረት ሥራ ማህበራት ቁጠባን አሰባስቦ በመደበኛ ባንኮች በማስቀመጡ በኩል ሰፊ ሚናን ስለሚጫወቱ የባንኮችን ስራ በከፍተኛ ደረጃ የሚያቀሉ መሆኑን ገልፀውልናል፡፡ እንደ አቶ ዘሪሁን ገለፃ ይህም ሁኔታ የባንኮችን የተቀማጭ ገንዘብ ከፍ በማድረግ የማበደር አቅማቸው እንዲጨምር የሚያደርግ ይሆናል፡፡¾  

 

በአዲስ አበባ ከተማ የሚታየውን የመልካም አስተዳደር ችግር ለመፍታት በከተማዋ አስተዳደር ፐብሊክ ሰርቪስና የሰው ሃብት ልማት ቢሮ አማካኝነት ከሰሞኑ አንድ ሰነድ ይፋ ሆኗል። ሰነዱ “የከተማ መልካም አስተዳደር ንቅናቄ ማቀጣጠያ ሰነድ-2” የሚል ስያሜ ተሰጥቶታል። ከዚህ ቀደም ብሎ መሰል ሁሉን አቀፍ ሰነድ ተዘጋጅቶ የነበረ መሆኑንም በማመልከት ይህ ሰነድም ሁለተኛው ሰነድ መሆኑን ያመለክታል።

ሰነዱ በከተማዋ የሚታዩ ችግሮችን በዝርዝር ያስቀምጣል። በመሬት፣ በመኖሪያ  ቤት፣ በትራንስፖርት፣ በኮንስትራክሽን፣ በጤና፣ በትምህርት፣ በፍትህና በመሳሰሉት ዙሪያ ያሉ ችግሮችን ይዳስሳል። የተለመዱት ኪራይ ሰብሳቢነት፣ የመልካም አስተዳደር ችግር፣ የህዳሴ ጉዞ፣ ልማታዊ ሰራዊት የሚሉ አገላለፆችን በስፋት ይጠቀማል። ችግሮችንም ውስጣዊና ውጫዊ አድርጎ ይገልፃቸዋል። ሰነዱ በአንድም ይሁን በሌላ መልኩ በገዢው ፓርቲ ሰነዶችም ሆኑ በተለያዩ ጊዜያት የሚዘረዘሩ ችግሮቹን እየደጋገመ ዘርዝሯል። እኛም ሰነዱን በመመልከት ሁለቱን ችግሮች ለይተን በሚከተለው መልኩ አቅርበናቸዋል።

የመሬትና ግንባታ ጉዳይ

  ሰነዱ ከዳሰሳቸው የመልካም አስተዳደር ችግሮች መካከል አንደኛው  ከመሬት ጋር የተያያዘው ጉዳይ ነው። ከተጠቀሱት ችግሮች መካከልም የአገልግሎት ሰጪ ሰራተኞች የተገልጋዩን የይዞታ ማረጋገጫ ሰነድ(ካርታ) በእግድ እንዲመዘገብ ከሚመለከታቸው አካላት የተሰጠን ደብዳቤ ሆን ብሎ የመደበቅና በማህደር ላይ እንዳይታሰር ማድረግ፣ከድላላና ጉዳይ አስፈፃሚ ጋር በስልክና በአካል በመገናኘት የአገልግሎት አሰጣጥ ስርዓቱን ማበላሸትና በዚህም ያልተገባ ጥቅም ማግኘት አንዱ  ችግር ተደርጎ የሚጠቀስ መሆኑን ይሄው ሰነድ ያመለክታል።

 

ሰነዱ በሰራተኞች በኩል የሚታዩትን ጉልህ ችግሮችንም በተወሰነ ደረጃ አስቀምጧል። ከተዘረዘሩት ችግሮች መካከልም በመንግስት ቢሮና ማቴሪያል የመንግስትን የስራ ሰዓት በመጠቀም የግል ስራን መስራት እንደዚሁም መስክ ነኝ በማለት ከስራ ገበታ መቅረት በዋነኝነት ተጠቅሰዋል። አንዳንድ ሰራተኞች በአገልግሎት አሰጣጥ ሂደትም ለባለጉዳዮች “የፕላን ተቃርኖ አለው፣ መንገድ ይነካዋል፣ የድንበር ክርክር አለበት፣ ማህደሩ አልተገኘምና የመሳሰሉትን ምክንያቶችን ለባለጉዳዮች በመስጠት በማመላለስ ለድርድር የሚጋብዙበት ሁኔታ መኖሩን ሰነዱ ያትታል። የመስክ ስራን የሚሰሩ ሰራተኞች የተሸከርካሪ እጥረትን ምክንያት በማድረግ ተገልጋዮች መኪና ተከራይተው እንዲያመጡ የሚደረግበት ሁኔታ መፈጠሩን ይሄው ሰነድ ያመለክታል።

 

 የሀገሪቱ የህንፃ አዋጅ ደንብና መመሪያ አንድ ህንፃ ከተገነባ በኋላ አገልግሎት መስጠት ከመጀመሩ በፊት የመጠቀሚያ ፈቃድ ማገኝት ያለበት መሆኑን ይደነግጋል። ይህ አሰራር በህንፃ አዋጅ 624/2001 አንቀፅ 18 ቁጥር አንድ እና ሁለት፤ እንደዚሁም አዋጁን ለማስፈፀም በወጣው ደንብ ቁጥር 243/2003 አንቀፅ 16 ላይ በግልፅ ተቀምጦ ይታያል። ይሁንና የሰሞኑ ሰነድ በከተማዋ ግንባታቸው ሳይጠናቀቅ ፈቃድ ወስደው የሚያከራዩ ባለሀብቶች መኖራቸውን ያመለክታል።የመጠቀሚያ ፈቃዶቹም የሚሰጡት ከግንባታ ፈቃድ እውቅና ውጪ መሆኑን  ሰነዱ ያትታል።

 

 አንዱ መንግስት አካል ፈቃድ የሰጠበትን ሌላኛው የመንግስት አካል ወደ ማሸግ ስራ የሚገባበት አሰራር መኖሩን ሰነዱ የሚጠቁም ሲሆን ይሁንና ግንባታቸው ያልተጠናቁ ህንፃዎችን በብዛት የሚከራዩት ባንኮች በመሆናቸው ለማሸግ አስቸጋሪ ሆኖ መገኘቱን ይሄው ሰነድ ቃል በቃል ያስቀምጣል።

 

 የሀገሪቱ ህጎችም ሆኑ የህግ መርህ ግለሰቦችም ሆኑ ህጋዊ ሰውነት ያለው ማንኛውም አካል በህግ ፊት እኩል መሆኑ የህግ መርህ የሚደነግግ ቢሆንም  ይሄው የንቅናቄ “የከተማ የመልካም አስተዳደር ማቀጣጠያ ሰነድ 2” የሚል ስያሜ የተሰጠው ሰነድ ግን ግንባታቸው ሳይጠናቀቅ አገልግሎት የሚሰጡ ህንፃዎችን ለማሸግ የተቸገረበት ዋነኛ ምክንያት ያላለቁትን ህንፃዎች የሚከራዩት ባንኮች ከመሆናቸው ጋር የተያያዘ መሆኑን ይገልፃል። ችግሩንም ለመቅረፍ የተደረገውን ጥረት በተመለከተ ሰነዱ የሚከተለውን ማብራሪያ ይሰጣል

 

“ግንባታቸው ሳይጠናቀቅ ፈቃድ ወስደው የሚያከራዩና ወደ አገልግሎት የሚገቡ ባለሀብቶች በመኖራቸው በህብረተሰቡ ላይ የሚደርስ ጉዳትን ለመከላከል ቀደም ሲል ለሁሉም ባንኮች ባላለቁ ህንፃዎች ላይ እንዳይከራዩ በደብዳቤ ቢገለፅም ችግሩ ባለመቀረፉ ከሚመለከተው ፈቃድ ሰጭ እና ከፌደራል ጋር በጋራ መስራት እና የመጠቀሚያ ፈቃድ ሳይወስዱ በሚያከራዩ ህንፃዎች የእርምት እርምጃ በመውሰድ ስርዓት ማስያዝ ያስፈልጋል።”

  

የህዝብ ትራንሰፖርት ችግሮች

ሌላኛው በዚህ ሰነድ በመሰረታዊ ችግርነት ከተጠቀሱት ተግዳሮቶች መካከል አንደኛው የከተማዋ ዘርፍ ነው። በአዲስ አበባ ከተማ በህዝብ ትራንስፖርት በኩል ያለው ችግር ሰር የሰደደና እስከዛሬም ድረስ ይህ ነው የሚባል መፍትሄ ያልተገኘለት ጉዳይ ነው። በአቅርቦትና ፍላጎት ካለው ሰፊ ክፍተት ባሻገር ያለውን የትራንስፖርት አቅርቦት በሚገባ ጥቅም ላይ በማዋሉ ረገድ ከአሰራር ጀምሮ መንገድን እስከመሰሉ መሰረተልማቶች ድረስ በርካታ ችግሮች ይታያሉ።

 

የህዝብ ትራንስፖርት አቅርቦትን በተመለከተ አዲስ አበባ ሰማያዊ ሚኒባስ ታክሲዎች፣ የአንበሳ አውቶቡስ አገልግሎት ድርጅት፣ ሀይገር ባስ፣ በክልል ታርጋዎች ለከተማዋ አገልግሎት የሚሰጡ በሺ የሚቆጠሩ ሚኒባሶች፣ ቀላል የከተማ ባቡር፣ድጋፍ ሰጪ ቅጥቅጥ አውቶቡሶች፣  እንደዚሁም በመደበኛነት ለመንግስት ሰራተኞችና አልፎ አልፎም ለከተማዋ ነዋሪ የትራንስፖርት አገልግሎት እየሰጡ ያሉትና ፐብሊክ ሰርቪስ  በመባል የሚታወቁት ሰማያዊ አውቶብሶች፣ በቅርቡ ዘርፉን የተቀላቀሉት ሜትር ታክሲዎችና በተለምዶ የኮንትራት ታክሲ በመባል የሚታወቁት አነስተኛ ታክሲዎች አገልግሎት እየሰጡ ቢገኙም ዛሬ በከተማዋ በየትኛውም አቅጣጫ የሚታዩ ረዣዥም የትራንስፖርት ጥበቃ ሰልፎችን መታደግ አልቻሉም።

 

ችግሩ የበለጠ እየተባባሰ ሄዶ በስራ መውጫና መግቢያ የሚታዩት ረዣዥም ሰልፎች በአሁኑ ሰዓት ቀንም ጭምር መታየት ጀምረዋል። በአሁኑ ሰዓት በመሰረታዊነት የሚታየውን የመዲናዋን ሰፊ የትራንስፖርት ፍላጎት ክፍተት በተመለከተ ግን ሰነዱ “የህዝብ ትራንስፖርት እጥረት መኖር” በሚል አንድ አረፍተ ነገር ነው ያለፈው። ከዚህ ውጪም በማስፋፊያ አካባቢዎች የህዝብ ትራንስፖርት ተደራሽነት አለመኖር፣ የአሰራርና አደረጃጀት ችግር፣ የመለዋወጫ አቅርቦት ችግር፣ ታክሲዎች ዞናዊ ስምሪትን ጠብቀው አገልገሎት የማይሰጡበት ሁኔታ መኖር፣ የትራንስፖርት አገልግሎት የሚሠጡ አሽከርካሪዎችን በህጉ መሰረት ከመቅጣት ይልቅ ያልተገባ ጥቅም በመቀበል የጥቅሙ ተጋሪ መሆን በዘርፉ ከተዘረዘሩት ችግሮች መካከል የተጠቀሱት ናቸው።

 

ከዚህ ውጭ ከትራንስፖርት አገልግሎት ጋር በተያያዘ የአሽከርካሪ ተሸከርካሪ አገልግሎት አሰጣጡም በጥናቱ ተዳሷል። ለአሽከርካሪዎች የሚሰጠውን አገልግሎት በተመለከተ በቢሮዎች ጥራት የሌለው የመዝገብ አያያዝ፣ ሲስተም ተበላሽቷል፣እንደዚሁም “ፋይል ጠፍቷል” በማለት ደንበኞችን ማጉላላት፣ ተሸከርካሪዎች አገልግሎት ለውጥ እንደዚሁም ለቦሎ፣ ለታርጋና ሽያጭ የተሟላ መረጃ ሳይቀርብ ወይም በፎርጅድ መረጃ የሚስተናገድበት አሰራር የተስተዋለ መሆኑም በሰነዱ ላይ ተመልክቷል።

እንደዘገባው ከሆነ የሱዳንን መንግስት ለመጣል የአልሲሲ መንግስት ደቡብ ሱዳንን መጠቀም ይፈልጋል። የሱዳንና የግብፅ የቀደመ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት እንዲሻክር ካደረጉት ምክንያቶች መካከል አንዱ ተደርጎ የሚወሰደው ከህዳሴው ግድብ ጋር በተያያዘ ሱዳን ለኢትዮጵያ ድጋፏን መስጠቷ ነው። ሁለቱ ሀገራት ከዚህም በተጨማሪ የቆየ የግዛት ይገባኛል ውዝግብ ላይ ያሉ መሆናቸውም ሌላኛው የግንኙነታቸው መሻከር አንዱ ምክንያት ተደርጎ የሚጠቀስ ነው። በሰሜናዊ ሱዳን እና በደቡባዊ ግብፅ የምትገኘው ሀላይብ ግዛት የሁለቱ ሀገራት የውዝግብ መንስኤ ናት። 13 ሺህ ሰኩዌር ኪሎ ሜትር ስፋት ያላት ይህች ግዛት ቀደም ሲል በሁለቱ ሀገራት በጋራ ስትተዳደር የቆየች ሲሆን ሆኖም እ.ኤ.አ ከ2000 ጀምሮ የሱዳን የፀጥታ ኃይሎች ለቀው ለመውጣት በመገደዳቸው ሙሉ ግዛቷን ግብፅ ማስተዳደርን እስከዛሬም ድረስ ቀጥላበታለች። ከዚህ በኋላም ሱዳን የግዛት ይገባኛል ጥያቄው በዲፕሎማሲያዊ መንገድ እንዲያልቅ ጥረት ስታደርግ ብትቆይም ግብፅ ፈቃደኝነትን ባለማሳየቷ ጥረቱ ሁሉ መክኖ ቀርቷል። 

 

ሱዳን ቀደም ሲል ከሀላይብ ግዛት ይገባኛል ጥያቄ ጋር እንደዚሁም ከህዳሴው ግድብ ጋር በተያያዘ ሱዳን ለኢትዮጵያ ያሳየችው ድጋፍ ግብፅን ያስቀየማት መሆኑን ዘገባዎች ያመለክታሉ። ፕሬዝዳንት አልሲሲ ቀደም ሲል የኤርትራውን ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂን፣ የጂቡቲውን ፕሬዝዳንት እስማኤል ኦማር ጌሌ ካይሮ ጠርተው ያነጋገሩ ሲሆን ባለፈው ማከስኞ ደግሞ የደቡብ ሱዳኑ ፕሬዝዳንት ሳልቫኪየር ወደ ካይሮ አምርተዋል። የሳልቫኪየርን የካይሮ ጉብኝት አስመልክቶ ዘገባውን ያሰራጨው ሱዳን ትሪብዩን የአልሲሲ መንግስት የአልበሽርን መንግስት ለመጣል ደቡብ ሱዳን የአማፅያን ማሰልጠኛ ቦታን የሚፈልጉ መሆኑን አመልክቷል። የግብፅን የሳልቫኪየር ሚስጥራዊ ስምምነት የተቃወመው የደቡብ ሱዳን ነፃነት አርሚ ለደቡብ ሱዳን የዜና ወኪል በሰጠው ማብራሪያ የሁለቱን ሀገራት ሚስጥራዊ ስምምነት ተቃውሟል።   በግብፅ ደጋፊነት የሳልቫኪየር መንግስት መጠናከር የሀይል ሚዛኑን እንደሚያስቀይር የተረዳው ይህ ታጣቂ ሀይል ጠበቅ ያለ ተቃውሞውን አሰምቷል። “የአልሲሲና የሳልቫኪየር ግንኙነት ለግብፅ ብሔራዊ ጥቅም ነው።” ያለው ይህ ታጣቂ ሀይል ሪክ ማቻርን የመሳሰሉ ተቃማዊዎች ለማስወገድም ያለመ መሆኑን ጨምሮ አመልክቷል። አልሲሲ ከዚህ ቀደም ከኡጋንዳው ፕሬዝዳንት ጋር በነበራቸው የሁለትዮሽ ቆይታ ኡጋንዳ ለሱዳን አማፅያን የስልጠና ካምፕ እንዲሰጡ ጥያቄ ያቀረቡ መሆኑን  ዘገባዎች ያመለክታሉ። በሱዳን የእርስ በእርስ ጦርነትን ለማቀጣጠል በግብፅ የተመረጡት ሀይሎች የሰሜናዊ ሱዳን ህዝብ ነፃ ንቅናቄ (SPLM- North) እና የዳርፎር አማፅያን መሆናቸውን የሱዳን ትሪብዩን ዘገባ ያመለክታል።

 

ከሱዳን ባሻገር ግብፅ ሌላኛው ውዝግብ ውስጥ የገባችበት ጉዳይ የሳዑዲ ከአረቢያ ጋር ያላት ግንኙነት ነው። ከግብፅ አብዮት በኋላ ግብፅ ከገባችበት ኢኮኖሚያዊ ቀውስ እንድትወጣ ለማገዝ ሳዑዲ አረቢያ ሰፊ የፋይናንስ ድጋፍ ስታደርግ ቆይታለች።  ይሁንና የሁለቱ ሀገራት ግንኙነት በሁለት መሰረታዊ ጉዳዮች ውጥረት ውስጥ መግባት ግድ ብሎታል። የመጀመሪያው በቀይ ባህር አካባቢ ባሉ ደሴቶች የተነሳው የግዛት ይገባኛል ጥያቄ ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ በሶርያ የእርስ በእርስ ጦርነት የአልሲሲ መንግሰት የያዘው አቋም ነው። በሶርያ የእርስ በእርስ ጦርነት በአሜሪካ በሚመራው ጎራ በኩል ሳዑዲ አረቢያ የሶርያ አማፅያንን የምትደግፍ ሲሆን ይሁንና ግብፅ በተባበሩት መንግስታት በሩስያ ለሚደገፈው የበሽር አላሳድ መንግስት ድጋፏን መስጠቷ የሁለቱ ሀገራት ዲፕሎማሲያዊ ውዝግብ ይፋ መውጣት መነሻ ሆኖ ተመልክቷል።  በዚያው ሰሞን የሳዑዲ ከፍተኛ ልዑካን ቡድን በኢትዮጵያ በመገኘት ህዳሴውን ግድብ መጎብኘቱ በበርካታ ግብፃዊያን ባለስልጣናትና ሚዲያዎች ብዙ ጫጫታን ፈጥሮ ከርሟል። ሳዑዲ አረቢያም የኢትዮጵያን ህዳሴ ግድብ በገንዘብ ለመደገፍ አስባለች በማለትም የግብፅ ሚዲያዎች በሰፊው ሲያናፍሱ ከርመዋል።

 

በሁለቱ ሀገራት ግዛት ይገባኛል የተነሳባቸውን ሁለት የቀይ ባህር ደሴቶችን ለሳዑዲ ለመስጠት አልሲሲ ከዚህ ቀደም ወስነው የነበረ ቢሆንም ባልተጠበቀ ሁኔታ የተነሳው ህዝባዊ ተቃውሞ በውሳኔያቸው እንዳይገፉበት አድርጓቸዋል። ከሳዑዲ አረቢያ ልዑካን ቡድን የኢትዮጵያ ጉብኝት በኋላ ግን የሁለቱ ሀገራት የደሴቶቹ ይገባኛል ጥያቄ መልሶ ወደ መድረክ መጥቷል። ጉዳዩም ከአልሲሲ ካቢኔ፣እስከ ፓርላማው ብሎም እስከ ከፍተኛው ፍርድ ቤት ድረስ ዋነኛ አጀንዳ ሆኗል።

ናይጄሪያ በአፍሪካ ከፍተኛ ቁጥር ያለው ህዝብን የያዘችና ከፍተኛ የነዳጅ ሀብት ያላት ሀገር ብትሆንም የሚበዛው ህዝቧ በኤሌክትሪክ ኃይል እጥረት ችግር ውስጥ የሚገኝ መሆኑን በኤሌክትሪክ ሀይል ዙሪያ በርካታ ዘገባዎችን የሚያሰራጨው ዋይ ኤልክትሪክሲቲ ማተርስ (Why Electricty Matters) ድረገፅ አመልክቷል። ድረገፁ 80 በመቶ የሚሆነው የናይጄሪያ የኤሌክትሪክ ኃይል ምንጭ ከተፈጥሮ ጋዝ (Natural Gas) የሚገኝ መሆኑን አመልክቷል። ከዚሁ ጋር በተያያዘ “አረንጓዴ ኢኮኖሚ” በሚለው የዓለም አቀፍ አበዳሪ ድርጅቶች አንዱ መመዘኛ የናይጄሪያ የኤሌክትሪክ ኃይል ማስፋፊያ ተቀባይነት ሊያገኝ አልቻለም። ይህ ብቻ ሳይሆን በሀገሪቱ ያለው ሙስና በሀገሪቱ ወሳኝ የተባሉ መሰረተ ልማቶች እንዳይስፋፉ እንቅፋት መሆኑን ዘገባዎች ያመለክታሉ።

 

 የድረገፁ ዘገባ ናይጄሪያ ምንም እንኳን ከደቡብ አፍሪካ በሶስት እጥፍ የሚልቅ ህዝብን ብትይዝም በአሁኑ ሰዓት የምታመነጨው የኤሌክትሪክ ሀይል መጠን ግን የደቡብ አፍሪካ አንድ አስረኛ መሆኑን ዘገባው ያመለክታል። 98 ሚሊዮን የሚሆኑ ናይጄሪያዊያን ኤሌክትሪክ ኃይል የማያገኙ መሆኑን ዘገባው ጨምሮ አመልክቷል። በናይጄሪያ መሰረቱን ያደረገው የዳንጎቴ ሲሚንቶ ፋብሪካ ከኃይል እጥረት ጋር በተያያዘ ስራውን በድንጋይ ከሰል ለማከናወን እንደተገደደ በዘገባው ተመልክቷል።

 

ሀገሪቱ የተፈጥሮ ጋዝን በሀይል ምንጭነት ከመጠቀሟ ጋር በተያያዘ ለሀይል መቋረጥ ብሎም መቆራረጥ እየዳረጋት ነው። የጋዝና የነዳጅ ቱቦዎች በተለያዩ ግዛቶች ተደጋጋሚ የሽብር ጥቃት የሚደርስባቸው መሆኑና በነዳጅና ጋዝ ስርቆት የተሰማሩ ግለሰቦችና ቡድኖችም በቱቦዎች ላይ የሚያደርሷቸው ተደጋጋሚ ጉዳቶች ለሀይል መቆራረጡ አንዱ ምክንያት ተደርጎ ይጠቀሳል።

አንበሳ የከተማ አውቶቡስ አገልግሎት ድርጅት ከ277 በላይ የሆኑ አውቶብሶችን ለጨረታ ያወጣ መሆኑን ከድርጅቱ ያገኘነው መረጃ አመለከተ። ይህም የመጀመሪያ ዙር ጨረታ መሆኑ ታውቋል። ድርጅቱ ለጨረታ ያቀረባቸው የቀደሙትና ከውጭ ተገዝተው በመግባት ለረዥም ጊዜ አገልግሎት የሰጡት እንደዚሁም ከዓመታት በፊት በብረታብረት ኢንጂነሪግ ኮርፖሬሽን ተገጣጥመው ለድርጅቱ የቀረቡ አውቶብሶች መሆናቸውን ከድርጅቱ ያገኘነው መረጃ አመልክቷል። ድርጅቱ ከአንድ ሺህ በላይ አውቶብሶች ያሉት ሲሆን በአሁኑ ሰዓት በየቀኑ የሚያሰማራቸው አውቶብሶች ቁጥር 460 ያህል ብቻ ናቸው።

 

ድርጅቱ በከተማው አስተዳደር በኩል ሌሎች ተጨማሪ አውቶብሶችን ከውጭ ለማስገባት እንቅስቃሴ መጀመሩ ታውቋል። በዚህ ዓመትም አንድ መቶ አውቶብሶችን ለማስገባት እንቅስቃሴ ተጀምሯል ተብሏል። ድርጅቱን አቅሙን ለማሳደግ የመዋቅር ለውጥ፣ የሰራተኛ ምድባ እና የሠራተኞች ስልጠና እየሰጠ መሆኑ ታውቋል። አሰራሩንም ለመለወጥና የአውቶብሶችን ስምሪት ከማዕከል ለመቆጣጠር የሚያስችል ስራም ከአለም ባንክ በብድር በተገኘ ገንዘብ እየተሰራ መሆኑን የተገኘው መረጃ ያመለክታል። አዳዲስ አውቶብሶችን ለመግዛት የስራ ኃላፊዎች ውጭ ሀገራት በመሄድ የምልከታ ስራ የሰሩ መሆኑ ታውቋል። ድርጅቱ ከዚህ ቀደም በኢትዮጵያ የብረታ ብረት ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን በኩል የተገጣጠሙ ከ5 መቶ ያላነሱ አውቶብሶችን ተረክቦ ሲሰራ የቆዩ ሲሆን ባለፉት ጊዜያት ከ100 በላይ አውቶቡሶች በቴክኒክ እና የመለዋወጫ ችግር ገጥሟቸው የቆሙበት ሁኔታ ነበር።

ኤርትራ የአሰብ ወደብን ለተባበሩት አረብ ኤሜሬት አላካራየሁም በማለት አስተባበለች። ኤርትራ አሰብን ለተባበሩት አረብ ኤሜሬት የጦር ቤዝ ሆኖ እንዲያገለግል በሊዝ ሰጥታለች የሚሉ ዘገባዎች ሲሰራጩ የቆዩ ሲሆን ይህ ዘገባ ከሰሞኑም ተጠናክሮ ቀጥሏል። በቤይሩት መሰረቱን ያደረገው አልማያዲን የተባለ የአረብኛ ቴሌቭዥን ጣቢያ የተባበሩት አረብ ኤሜሬት አሰብን ለ30 ዓመታት ለወታደራዊ ቤዝነት ለመጠቀም የሊዝ ስምምነት ያደረገች መሆኗን በአዲስ መልኩ ዘግቧል። እስከዛሬ በነበሩት ዘገባዎች በኤርትራም ሆነ በተባበሩት አረብ ኤሜሬት በኩል ይህ ነው የሚባል የአዎንታና የማስተባበያ ድምፅ ያልተሰማ ሲሆን ከሰሞኑ ግን ኤርትራ መረጃው የተሳሳተ ነው በማለት ጠበቅ ያለ ማስተባበያ ሰጥታለች። በዚህ የተሌቭዥን ዘገባ ዙሪያ ጠበቅ ያለ ማስተባበያ የሰጠው የኤርትራ ማስታወቂያ ሚኒስቴር መረጃው የሀገሪቱን ገፅታ ለማጉደፍ ታስቦ መሰረት በሌለው መረጃ የተሰራጨ ነው ብሏል። ከቴሌቭዥን ጣቢያው ጋር የቃላት እሰጣ ገባ ውስጥ የገባው የኤርትራ ማስታወቂያ ሚኒስቴር ጣቢያው ከዚህ ቀደምም በተመሳሳይ መልኩ እስራኤል በቀይ ባህር ሰርጥ ባቤል ኤል ሜንዴብ ያለውን እንቅስቃሴ ለመቆጣጠር  እምባሶይራ በተባለ የኤርትራ ግዛት ግዙፍ ወታደራዊ ቤዝ እየገነባች ነው በማለት የሀሰት መረጃ አሰራጭቷል ስትል  ኤርትራ ከሳለች። የኤርትራም ባለስልጣናት ቴሌቭዥን ጣቢያው የመረጃ ምንጩን እንዲገልፅ ጥያቄ ያቀረቡ መሆኑ ታውቋል።

 

የኤርትራ መንግስት ተቃዋሚዎች በበኩላቸው የተባበሩት አረብ ኤሜሬት ለአስርተ ዓመታት የሚያገለግላትን ወታደራዊ ቤዝ በአሰብ መገንባቷን በተደጋጋሚ የሚናገሩ መሆኑን የሱዳን ትሪብዩን ዘገባ ያመለክታል። የተባበሩት መንግስታት የኤርትራ ጉዳይ ክትትል አካል ከዚህ ቀደም በለቀቀው ሪፖርት ሳዑዲ አረቢያና የተባበሩት አረብ ኤሜሬት በየመን ያሉትን የሁቲ አማፂያንን ለማጥቃት አሰብን በቤዝነት የተጠቀሙ መሆኑን አመልክቷል። ሆኖም በተደጋጋሚ ኤርትራ ለተባበሩት አረብ ኤሜሬት ወታደራዊ ቤዝን በሊዝ ሰጥታለች የሚለውን ጉዳይ ግን አላረጋገጠም። ሳዑዲ አረቢያም ሆነች የተባበሩት አረብ ኤሜሬት ከአሰብ ወታደራዊ ቤዝ ጋር በተያያዘ ከኤርትራ የሚያደርጉት እንቅስቃሴ በተመለከተ ዋጋ የሚያስከፍላቸው መሆኑን በመግለፅ ከዚህ ቀደም ኢትዮጵያ ለሁለቱ ሀገራት ጥብቅ የማስጠንቀቂያ ያስተላለፈች መሆኗን ሱዳን ትሪብዩን አመልክቷል።

 

በሀገሪቱ ከተመሰረቱት አክስዮን ማህበራት መካከል ጃካራንዳ ኢንተግሬትድ አግሮ ኢንዱስትሪ ማህበር አንዱ ነው። ማህበሩ በ2 ሺህ ዓ.ም የተመሰረተ ሲሆን ከ2 ሺህ በላይ ባለአክስዮኖችን ያቀፈ ነው። በግብርናው ዘርፍ የተሰማራው ይህ አክስዮን ማህበር ከተመሰረተ ዓመታት የተቆጠሩ ቢሆንም በመሀል በገጠሙት በርካታ ውስብስብ ችግሮች ወደ ፊት መራመድ ሳይችል ቆይቷል።

 

የድርጅቱን ችግር ፈትቶ ስራውን በተፈለገው አቅጣጫ ወደፊት ለማስኬድ በተደረገው ጥረትም ባለፈው እሁድ ታህሳስ 23 ቀን 2009 ዓ.ም በንግድ ሚኒስቴር አዳራሽ ጠቅላላ ጉባኤውን አካሂዷል። በዕለቱ የተበተነው የስብሰባ ፕሮግራም የጠቅላላ ጉባኤው ስብሰባ እንደሚጀመር የሚገልፀው እስከ ጠዋቱ 3 ሰዓት ባለው ጊዜ ቢሆንም ስብሰባው ግን የተጀመረው በ6 ሰዓት ተኩል ነበር። ለስብሰባው መጀመር መዘግየት ዋነኛ ምክንያትም የነበረው የተሰብሳቢዎች ዘግይተው በቦታው መድረስና እየተንጠባጠቡ መገኘት ነበር።

 

ከዚሁ ጋር በተያያዘም ህጉ በሚፈቅደው መሰረት ምልዓተ ጉባኤውን የተሟላ ለማድረግ ሲባል የስብሰባ መጀመሪያው ጊዜ ሰዓታትን ወስዷል። አንዳንዶችም በጥበቃው በመሰላቸት ትተው ለመሄድ ተገደዋል። ተሰብሳቢዎች ታግሰው እንዲቆዩ ለማድረግም ከመድረኩ ተደጋጋሚ ማሳሳቢያዎች ሲሰጡ ቆይቷል። መደበኛ ጠቅላላ ጉባኤውን ለማካሄድ የሚያስችለው ምልዓተ ጉባኤው መሟላቱ ተረጋግጦ ስብሰባው ከተጀመረ በኋላ የዳይሬክተሮች ቦርድ ሪፖርት ለጉባኤው ቀርቧል።

 

በምዕራብ ሸዋ ዞን በባኮ ልዩ ወረዳ የጀመረው የእርሻ ልማት ለሁለት ዓመታት ያህል ከተቋረጠ በኋላም ወደ ስራ የገባ መሆኑ በዚሁ ሪፖርት ላይ ተገልጿል። የአትክልት ምርትን በተመለከተ ለሁለት ጊዜያት ያህል ተመርቶ የተሸጠ መሆኑ ተመልክቷል። ከዚህም በተጫማሪ ከአንድ ቅባት ላኪ ኩባንያ ጋር በተደረገ ስምምነት የቦሎቄ፣ የሰናፍጭና የጥቁር አዝሙድ ዘር እንዲገባ ተደርጓል ተብሏል። ሚያዚያ ላይ ሊሰበሰብ የሚችል የአትክልት ምርት መኖሩም ተመልክቷል። የአዋሽ ቢ ሾላ የእርሻ ስራን በተመለከተም ኩባንያው በአክስዮን ማህበሩ አቅም ሊሰራ የማይችል በመሆኑ የአክስዮን ማህበሩ አባል ከሆኑ ግለሰቦች ጋር በጋራ ለመስራት እንቅስቃሴ ውስጥ የተገባ መሆኑን ሪፖርቱ ያመለክታል።

 

አክስዮኑ የርካታ ንብረቶች መጥፋትና መባከን የደረሰበት መሆኑ ተገልጿል። መጥፋታቸው ከተገለፁት ንብረቶች አንዱ የድርጅቱ የሽያጭ መመዘገቢያ ማሽን ሲሆን በተሰናባቹ ቦርድ ለጥገና በሚል ይሄንኑ አገልግሎት በሚሰጥ አንድ ኩባንያ ተልኮ የነበረ መሆኑን በመግለፅ፤ በአሁኑ ሰዓትም በፖሊስ ክትትል ስር መሆኑ ታውቋል። የድርጅቱ ሲንግል ጋቢና ፒክ አፕ መኪናም እንደዚሁ በፖሊስ ክትትል ተፈልጎ ከተገኘ በኋላ በአሁኑ ሰዓት በፖሊስ እጅ በምርመራ ላይ የሚገኝ መሆኑን ይሄው ሪፖርት አመልክቷል። ለባኮ እርሻ ልማት አገልግሎት ሲሰጥ የነበረ የመሬት መከሽከሻ መሳሪያም ተፈታቶ ከተወሰደ በኋላ በተደረገው ክትትል የመከስከሻው አካላትና ሌሎች የአክስዮን ማህበሩ እንዲመለሱ ተደርጓል ተብሏል። የድርጅቱን ሰራተኞችን በተመለከተም በአዲስ አበባ፣ በባኮና በአዋሽ ያሉና የተበተኑትን የጥበቃና የንብረት ክፍል ሰራተኞች የስምንት ወራት ያልተከፈለ ደመወዛቸው ተከፍሏቸውና ክሳቸውም በማቋረጥ  ወደ ስራ እንዲገቡ የተደረገ መሆኑ በቀረበው ሪፖርት ተመልክቷል።

 

በዚሁ ሪፖርት ከተዳሰሱት ጉዳዮች መካከል አንደኛው የድርጅቱ የቢሮ እቃዎች ሲሆን በተሰናባቹ ቦርድ የተቀጠረው ጠበቃ የሰራበት ገንዘብ ያልተከፈለው መሆኑን ገልፆ ክስ ከመሰረተ በኋላ በፍርድ ቤት አስወስኖ የአክስዮን ማህበሩ መረጃዎች ያለባቸውን ሶስት ኮምፒዩተሮችና ፎቶ ኮፒ ማሽንን የወሰደ መሆኑ ተመልክቷል። የድርጅቱን መረጃ የያዙትን ኮምፒዩተሮች ከሚወስድ ይልቅ ሌሎች ተሸከርካሪዎችን መውሰድ የሚችልበት እድል የነበረ ቢሆንም፤ ይህ ሳይሆን የቀረ መሆኑ በሪፖርቱ ላይ ተመልክቷል።

 

ጉባኤው በዕለቱ የተለያዩ ውሳኔዎችን ያሳለፈ ሲሆን ካሳለፋቸው ውሳኔዎች መካካለም ከዚህ ቀደም በአክስዮን ማህበሩ ላይ የንብረትም ሆነ የጥሬ ገንዘብ ጥፋት ያደረሱ ሰዎች በህግ የሚጠየቁበት ሂደት እንዲኖር ነው። ከዚሁ ጋር በተያያዘም በንግድ ሚኒስቴር በኩል የኦዲት ስራው ተከናውኖና የማጣራት ስራውም በሚገባ ተከናውኑ በሚገኘው ማስረጃ መሰረት ጥፋተኛው አካል ተለይቶ በህግ ተጠያቂ እንዲሆን ይደረጋል ተብሏል። አክስዮን ማህበሩ ከዚህ ቀደም የነበሩት የቦርድ አባላት ብዛት ሶስት የነበሩ ሲሆን በዚህ ጠቅላላ ጉባኤ ግን ወደ ሰባት ከፍ እንዲል ተደርጓል። የቦርዱ አባላት የተመረጡት በአክስዮን ማህበሩ ከፍተኛ የአክስዮን ድርሻ ያላቸው እንደዚሁም በሙያቸው አክስዮን ማህበሩን ሊያገለግሉ ይችላሉ የተባሉ ናቸው። የግብርና ሥራውን የሚያከናውንባቸው የተለያዩ የግብርና ቦታ ይዞታዎች ያሉት ሲሆን ከእነዚህም መካከል በምዕራብ ሸዋ  ባኮ ቲፔ ወረዳ 3 መቶ ሄክታር የእርሻ መሬት፣ አዋሽ ቢ ሾላ 15 ሄክታር መሬት ይገኙበታል። ከእነዚህም መሬቶች ላይ የግብርና ሥራው ተጠናክሮ እንዲቀጥል በጠቅላላ ጉበኤው ውሳኔ ተሰጥቶበታል። አክስዮን ማህበሩ ቀጣይ ሥራውን ለማከናወን የሚያስችለውን የፋይናስ አቅም  በማጠናከሩ ረገድ ከስራ እንደዚሁም ከባለአክስዮኑ የሚሰበሰቡ ገቢዎችን ለመጠቀም እቅድ ይዟል። ከባለአክስዮኖች ገንዘብን በመሰብሰቡ ረገድ ወደ 13 ሚሊዮን ብር አካባቢ እስከ ጥር 30 ድረስ ለመሰብሰብ ታስቧል።

ሱዳን ለአየር ንብረት ተጋላጭነት በከፍተኛ ደረጃ ከተመደቡት ሀገራት መካከል አንዷ ሆና መመደቧን የሲ ኤን ኤን ዘገባ አመልክቷል። ከተወሰኑ ዓመታት ወዲህ በሀገሪቱ በከፍተኛ ደረጃ እየጨመረ የመጣው የሙቀት መጠን የውሃ ትነቱን መጠን በፍጥነት እንዲጨምር እያደረገው መሆኑን ዘገባው ጨምሮ አመልክቷል። በሰሜን አፍሪካ ሀገራት እየተስፋፋ የሄደው በረሃማነት ሱዳንን ጭምር በማዳረስ ላይ መሆኑን የገለፀው ይሄው ዘገባ በተደረገውም ጥናት እ.ኤ.አ በ2060 አሁን በሱዳን ያለው አማካይ የሙቀት መጠን ከ1 ነጥብ 1 ዲግሪ ሴልሺየስና እስከ 3 ነጥብ 1 ዲግሪ ሴልሺየስ ከፍ ይላል። ይህንንም የሙቀት መጠን መጨመር ተከትሎም ከመደበኛ ዝናብ ይልቅ መደበኛ ያልሆነ ዝናብ በሀገሪቱ የሚታይ መሆኑ ተመልክቷል። ይህ ብቻ ሳይሆን ሀገሪቱም ለድርቅና ለውሃ እጥረት ተጋላጭነት እድሏም የሰፋ ነው ተብሏል።

ዓለም የተፈናቃዮች ክትትል ማዕከል (International Displacement Monitoring Center) እንዳመለከተው ከሆነ በሱዳን ከፍተኛ የዝናብ መጠን ካስከተለው ጐርፍና ድርቅ ጋር በተያያዘ ሰዎች መፈናቀል የጀመሩት እ.ኤ.አ. ከ2013 ጀምሮ ነው። እስከዛሬም ድረስ እስከ 6 መቶ ሺህ የሚሆኑ ሱዳናውያን መኖሪያ ቀያቸውን ጥለው ለመሰደድ የተገደዱ መሆኑን ይሄው የሲ ኤን ኤን ዘገባ ጨምሮ ያመለክታል።

በሱዳን አነስተኛ የእርሻ መሬት ይዞታ በርካታ ገበሬዎችን ከያዙ ሀገራት መካከል አንዷ ስትሆን 70 በመቶ የሚሆነው የገጠር ነዋሪ ሱዳናዊ የዝናብ ጥገኛ አርሶ አደር ነው። ግሎባል ሀንገር ኢንዴከስ እንዳመለከተው ከሆነ የምግብ ዋስትና ፈተና ካለባቸው 113 ሀገራት መካከል ሱዳን የ8ኛ ደረጃን ይዛለች። ይህም ሀገሪቱን በዓለማችን የምግብ እህል ዋስትና ማረጋገጥ ከገቡ 15 ኋላቀር አገራት መካከል አንዷ አድርጓታል ተብሏል። ከተወሰኑ ዓመታት ወዲህ የሱዳን አርሶ አደሮች ምርትም በከፍተኛ ደረጃ እየወረደ መሆኑን ይሄው ዘገባ ያመለክታል።

ችግሩን ከመሰረቱ ለመቋቋም የሱዳን መንግስት የራሱን የአጭርና የረዥም ጊዜ እቅድን ነድፎ መንቀሳቀስ ይጠበቅበታል ተብሏል። ሱዳን ከአየር ለውጡ ጋር በተያያዘ ዜጐቿ የቢጫ ወባ፣ ወባና የኰሌራ ተጠቂ የመሆን እድላቸውም ሰፊ ነው ተብሏል።

ያደጉትና በኢንዱስትሪ የበለፀጉት ሀገራት ለአየር ንብረት ብክለት ምክንያት በመሆናቸው በለውጡ ተጠቂ ለሆኑ ታዳጊ ሀገራት የገንዘብ ድጋፍ እንዲያደርጉ ሰፊ ትግል ሲደረግ ቆይቷል። የዚህ የአየር ንብረት ለውጥ ድጋፍ ከሚያስፈልጋቸው ሀገራት መካከል ኢትዮጵያን ጨምሮ ሱዳንን የሚያካትት መሆኑን ዘገባው ጨምሮ ያመለክታል።

 

በሀገር ውስጥ በሥራ ላይ ያሉ የተንቀሳቃሽ ስልኮችን ለመቆጣጠር ላለፉት ዓመታት ስትሰራ የቆየችው ቻይና ከፈረንጆቹ አዲስ ዓመት 2017 ዕለት ጀምሮ ያልተመዘገቡ ቀፎዎች ከሥራ ውጪ ያደረገች መሆኗን ቻይና ደይሊ ከሰሞኑ ባሰራጨው ዘገባ አመልክቷል። እንደዘገባው ከሆነ መንግስት ይህንን እርምጃ ከመውሰዱ በፊት ማናቸውም በሀገሪቱ ያሉ ተንቀሳቃሽ ስልኰችን ባለቤቶች እንዲያስመዘግቡ ተደጋጋሚ ጥሪ ሲያቀርብ ቆይቷል። ጥሪው በኤሌክትሮኒክስ ሚዲያዎች በሕትመት ውጤቶችና በማኅበራዊ ሚዲያዎች ሳይቀር ሲሰራጭ የቆየ መሆኑ ታውቋል።

ጥሪውንም ተከትሎ በርካታ የሀገሪቱ ዜጐችና ነዋሪዎች ስልካቸውን ማስመዝገባቸው የታወቀ ሲሆን፤ ይሁንና ጥሪውን ችላ ብለው ያላስመዘገቡ ግለሰቦች ግን የፈረንጆቹ አዲስ ዓመት በጠባበት ዕለት በእጃቸው ያለው ተንቀሳቃሽ ስልክ ከጨዋታ ውጪ ሆኖ አግኝተውታል።

መንግስት ስልኰቹ ከማዕከል አገልግሎት እንዳይሰጡ ካደረገ በኋላ ግለሰቦቹ በጥቂት ቀናት ውስጥ ስልካቸውን በማስመዝገብ ወደ አገልግሎቱ የማይገቡ ከሆነ ቁጥሮቻቸውን ሳይቀር በመዝጋት ሙሉ በሙሉ አገልግሎቱን የሚያቋርጥ መሆኑን አስታውቋል። በቻይና ከአንድ ተንቀሳቃሽ መስመር በላይ መያዝ የተለመደ ሲሆን፤ በአሁኑ ሰዓት 1 ነጥብ 54 ቢሊዮን የተንቀሳቃሽ ስልክ መስመሮች በስራ ላይ መሆናቸውን የዤኑዋ ዘገባ ያመለክታል።

ዘገባው በቻይና በአሁኑ ሰዓት የኢንተርኔት ተጠቃሚዎች ቁጥር 686 ሚሊዮን መድረሱን ገልጿል። በሀገሪቱ እያደገ ከመጣው ከፍተኛ የኢኰኖሚ እድገት ጋር ተያይዞ የመረጃ ልውውጥ መጠንም በዚያው መጠን ማደጉ የቻይናን መንግስት የቁጥጥር ሥርዓት ክፉኛ ሲያሳስበው ቆይቷል። መንግስት የመረጃ ቁጥጥሩን ለማጠናከር የተንቀሳቃሽ ስልኰችን ለመመዝገብ እንቅስቃሴ የጀመረው እ.ኤ.አ. በ2013 ነበር፤ ሆኖም ከበርካታ ዓመታት ሂደት በኋላ ወደተግባር የተገባው በያዝነው የፈረንጆቹ 2017 አዲስ ዓመት ነው።

ከበርካታ ማስታወቂያና ማስጠንቀቂያ በኋላ ቀፎዎቻቸውን ያላስመዘገቡ ዜጐች በአዲሱ ዘመን መባቻ እኩለ ሌሊት ጀምሮ ቀፎዎቻቸው ጥሪን፣ መደወልንም ሆነ አጭር መልዕክትን ማስተናገድ ሳይችሉ ቀርተዋል። አሁንም ቢሆን በተሻለ የኢኰኖሚ እድገት ውስጥ የምትገኘው ቻይና ባለፉት 30 ዓመታት 7 መቶ ሚሊዮን የሚሆን ህዝቧን ከድህነት ማውጣቷን ዘገባዎች ያመለክታሉ። እንደ ሁዋይት ፔፐር መረጃ ከሆነ እ.ኤ.አ. በ1949 የአንድ ቻይናዊ አማካይ እድሜ 49 ዓመት የነበረ ሲሆን፤ ይህ የእድሜ ጣሪያ እ.ኤ.አ. በተወሰደው ወደ መረጃ 76 ዓመት ተመንድጓል። በ1949 ከ80 በመቶ በላይ ቻይናዊ ያልተማረና ለትምህርት ከደረሱት ልጆች መካከልም የትምህርት እድል ማግኘት የቻሉት 20 በመቶ ብቻ ነበሩ። እ.ኤ.አ. በ2015 ለአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት እድሜያቸው ከደረሱ ልጆች መካከል የትምህርት እድል ማግኘት የቻሉት ደግሞ 99 ነጥብ 88 በመቶ መሆናቸውን ቻይና ደይሊ ያመለክታል።

 

በኢትዮጵያ ከዋና ዋናዎቹ የኢኮኖሚ ዘርፎች መካከል አንደኛው የኮንስትራክሽኑ ኢንዱስትሪ ነው። እንደ ኮንስትራክሽን ሚኒስቴር መረጃ ከሆነ ዘርፉ ከአጠቃላይ የሀገር ውስጥ ዓመታዊ ምርት እድገት ውስጥ የ 8 ነጥብ 5 በመቶ ድርሻን ይዟል። በሰው ኃይል ደረጃም እስከ 1 ነጥብ 2 ሚሊዮን የሚሆን ሰውን ያቀፈ ሲሆን፤ እንደ መረጃው ከሆነ ከሀገሪቱ አጠቃላይ ሰራተኛ የሰው ኃይል ውስጥ 12 በመቶ የሚሆነውን ድርሻ አቅፏል።

 ኢንዱስትሪው በአምስት ዓመታት ጊዜ ውስጥ  በእጥፍ ያደገ መሆኑ ቢመለከትም ዘርፉ አሁንም ድረስ በበርካታ ዘርፈ ብዙ ችግሮች የተተበተበ መሆኑን ከሰሞኑ በአዲስ አበባ  የተባበሩት መንግስታት ኢኮኖሚክ ኮሚሽን የተካሄደው ሀገር አቀፍ የኮንስትራክሽን የንቅናቄ ኮንፍረንስ ያመለክታል። የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪው አሁን እያሳየ ካለው እድገት አኳያ በበርካታ ችግሮች የታጠረ መሆኑን በብዙ መልኩ ተመልክቷል። ከእነዚህ ችግሮች መካከልም በዋነኝነት የተጠቀሱትን  እንደሚከተለው ተመልክተናቸዋል።

ያለ አማካሪ ግንባታቸው የሚከናወን ህንፃዎች ጉዳይ

የሀገር ውስጡ የኮንስትራክሽን ዘርፍ ከሚታዩበት ችግሮች አንዱ ተደርጎ በተደጋጋሚ በዘርፉ ባሉ ባለሙያዎች የሚታየው የሥነ ምግባር ጉድለትና አቅማቸውን የማይገልፅ የብቃት ማረጋገጫ ጉዳይ ነው። እንደ ሚኒስቴር መስሪያቤቱ መረጃ ከሆነ አንዳንድ ባለሙያዎች የሚሰጣቸው የምስክር ወረቀት በብቃት ምዘና ላይ ያልተመሰረተ በመሆኑ የያዙትን ደረጃ የሚገልፅ አይደለም።

የሥራ ተቋራጮችን በተመለከተ አብዛሃኞቹ ከደረጃ 4 እስከ 10 ያሉት ዝቅተኛ ቴክኖሎጂዎችን የሚጠቀሙ፣ በዘመናዊ የአስተዳደርና ፋይናስ የማይመሩ፣ብዙም ልምድን ባላከበቱ ባለሙያዎች የሚመሩና የሚሰሩ መሆኑ ተመልክቷል።

ከዚህም በተጨማሪ በብዙ ሀገራት የሚሰራበት ልዩ የሥራ ተቋራጭ       (Special Contractors) አሰራር በሀገሪቱ እየዳበረ ካለመሄዱ ጋር በተያያዘ በአብዛኛው ሁሉንም ስራ ጠቅልሎ የሚሰራው አንድ ሥራ ተቋራጭ መሆኑ የተመለከተ ሲሆን፤ ይህም በአንድ መልኩ ግንባታውን በሚያከናውነው ሥራ ተቋራጭ ጫናን ከመፍጠር ባሻገር፤ “ልዩ የሥራ ተቋራጮች” በኢንዱስትሪው በብዛት እንዳይፈጠሩ እንቅፋት ሆኗል ተብሏል።

ከዚህ ውጪ የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪው ሌላኛው ፈተና ተደርጎ የተጠቀሰው የአማካሪ ድርጅቶችና ባለሙያዎች እጥረት ጉዳይ ነው። የዚህን ዘርፍ የባለሙያዎች እጥረትና ችግሩን በተመለከተ የሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የአቅም ግንባታ ፕሮግራም ማዕቀፍ በሚከተለው መልኩ አስቀምጦታል። “በአማካሪ ድርጅቶች የተሰማሩባቸው የሥራ ዘርፎች በርካታ ቢሆኑም በአካባቢ ስብጥርና ከፍተኛ ልምድን በሚጠይቁት ሥራዎች ዙሪያ እጥረት ይታያል። በቤቶች ልማት ፕሮግራም ላይ ለአብነት በሁሉም ክልል በአርክቴክቸራል፣ በስትራክቸራል፣ በኤሌክትሪካል እና በሳኒተሪ ዲዛይን እንደዚሁም በአፈር ምርመራና በግንባታ ሥራ ቁጥጥር ለማሳተፍ የአማካሪዎች እጥረት ተከስቷል።

 ይህም በበኩሉ የሥራ መጓተትን እና ሥራዎችም በሚፈለገው ጥራትና ወጪ መሰራታቸውን በየደረጃው ለማረጋገጥ እንቅፋት ሆኖ ይታያል። የምክር አገልግሎት ሽፋንን ስንመለከት ከመንግስት ግንባታ ውጪ ያሉ ግንባታዎችን የሚከታተል ምንም የቁጥጥር ስርዓት ባለመኖሩ የህንፃ ግንባታዎች ደረጃዎችን በማይመጥኑ ባለሙያዎች ወይም አማካሪዎች ወይም ያለ አማካሪ እንዲከናወኑ መደረጉ የተለመደ ክስተት ሆኗል።”

ወደ መሬት መውረድ ያልቻለው የህንፃ አዋጅ

በኢትዮጵያ የህንፃ ኢንዱስትሪውን የሚመራ አንድ የህግ ማዕቀፍ ያልነበረ ሲሆን ይህንን ህግ እውን በማድረግ የግንባታውን ሂደት ለመከታተልና ለመቆጣጠር ጥረት ሲደረግ ቆይቷል። ከዚሁ ጋር በተያያዘም የኢትዮጵያ ህንፃ አዋጅ በ2001 እንዲወጣ ተደርጓል። አዋጁ የሰራተኛ ደህንነትን፣ ከግንባታ ጋር በተያያዘ መኖር ስለሚገባው የአካባቢ ደህንነትና ጥበቃ፣ እንደዚሁም ከዲዛይን አውጪ ጀምሮ ግንባታን እስከሚያከናውነው አካላት ድረስ ተጠያቂነትን የሚያሰፍን የህግ ማዕቀፍ ነው። ህጉ ከዚህም በተጨማሪ  ግንባታን በተመለከተ መረጃ ማጣራትን፣ የዲዛይን ምርመራና የግንባታ ፈቃድ አሰጣጥን እንደዚሁም የክትትል ቁጥጥርን ብሎም ህንፃው ተገንብቶ ከተጠናቀቀ በኋላ ደግሞ የመጠቀሚያ ፈቃድን መስጠትን ጭምር አካቶ የያዘ ነው።

  ሆኖም አዋጁ ከወጣ ስምንት ዓመታት የተቆጠሩ ቢሆንም  ህጉን ወደ መሬት እንዲወርድ በማድረጉ ረገድ ግን እስከዛሬም ድረስ በርካታ ችግሮች ይታያሉ። በኮንስትራክሽን ሚኒስቴር የሬጉላቶሪ ዘርፍ አማካሪ የሆኑት አቶ ሰይፉ ገብረ ሚካኤል አዋጁን ወደ መሬት ወርዶ እንዳይተገበር ያደረጉት በርካታ ምክንያቶች መኖራቸውን ይገልፃሉ። ለአዋጁ መሬት አለመውረድ ምክንያት ተደርገው ከተጠቀሱት መካከል አንደኛው ህጉን  ወደ ትግብራ ከመግባቱ በፊት አዋጁን ለማስፈፀም የሚያስችሉ ደንብና መመሪያዎች የማዘጋጀቱ ጉዳይ ጊዜ በመውሰዱ ነው።

እነዚህ አዋጁን ሊያስፈፅሙ የሚያስችሉ ደንቦችና መመሪያዎች እስከ 2003 ዓ.ም ድረስ ሲዘጋጁ  የቆዩ መሆኑን አቶ ሰይፉ ይገልፃሉ። ከዚህም በተጨማሪ  ከፌደራል እስከ ክልል ድረስ ህጉን በማስፈፀሙ በኩል ሰፊ ኃላፊነትን የሰጠው ለህንፃ ሹም ፅህፈት ቤት ነው። እንደ አቶ ሰይፉ ገለፃ የዚህን ፅህፈት ቤት አደረጃጀት የመፍጠሩ ሂደትም ረዥም ጊዜ መውሰዱ አንዱ ለአዋጁ መተግበር መጓተት ምክንያት ነው። ሌላኛው አዋጁ ተፈፃሚ የሚሆንባቸውን ከተሞች የመለየቱ ስራም ሌላው ጊዜ የወሰደ ምክንያት ተደርጎ ተጠቅሷል።

ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ከኢትዮጵያ ስታስቲክስ ኤጀንሲ ጋር በመተባበር  ህጉ ሊተገበርባቸው የሚችሉ 248 ከተሞች ሲለዩ የቆዩ መሆኑ ታውቋል እነዚህም ከተሞች አሰር ሺህ እና  ከዚያ በላይ ነዋሪዎችን የያዙ ናቸው ተብሏል። በዚህም መሰረት መመሪያዎችና ደንቦች በየክልሉና ከተሞች እንዲሰራጩ በማድረግ ከተከናወነ በኋላ  እነዚህ ሁሉ ቅድመ ስራዎች ተሰርተው በ2004 መጨረሻ አካባቢ በ248 ከተሞች መሬት ወርዶ እንዲተገበር  ለማድረግ ጥረት የተደረገ መሆኑን አቶ ሰይፉ ይገልፃሉ።

 በዚህም ሂደት እስከ መጀመሪያው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን መጨረሻ ድረስ ህጉን በ177 ከተሞች እንዲተገበር እንቅስቃሴ መደረጉ ተመልክቷል። ሆኖም  አዋጁ ላይ የተቀመጡት ድንጋጌዎች በሙሉ በሙሉ ለመተግበር ያልተቻለ መሆኑን አቶ ሰይፉ ጨምረው ይገልፃሉ። በዚህ ዙሪያ ሰፊ ክፍተት መኖሩን ያመለከቱት ባለሙያው፤ ለዚህ ሰፊ ክፍተት መፈጠር ምክንያት የሆኑ በርካታ ማነቆዎች መኖራቸውን በመግለፅ። ቀደም ሲል ከተጠቀሱት ችግሮች በተጨማሪ ሌሎች ችግሮችም ታክለው ህጉ እንዳይተገበር እንቅፋት እንደሆኑ ገልፀዋል።

በዚህ በኩል ህጉ በቅድሚያ መንግስት በሚገነባቸው ህንፃዎች ላይ  ተፈፃሚ እንደሆነ ጥረት ሲደረግ የቆየ ቢሆንም ጥረቱ ሳይሳካ የቀረ መሆኑን ኃላፊው ጨምረው አመልክተዋል። የህንፃ ሕጉን በመተግበሩ ረገድ ወጥነት የሌለ መሆኑን ያመለከቱት ባለሙያው ግለሰብ ገንቢዎች በህጉ መሰረት ፈቃድ እያገኙ ግንባታቸውን እንዲያከናውኑ የሚደረገብት አሰራር የተጀመረ ቢሆንም የመንግስት ህንፃዎች ግን የግንባታ ፈቃድ ሳያገኙ የሚገነቡበት ሁኔታ መኖሩን አመልክተዋል።

የዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነት ጉዳይ

በዚህ ኮንፍረንስ ከተነሱት ወሳኝ ሌሎች ጉዳዮች መካከል አንደኛው የሀገሪቱ ተቋራጭ ኩባንያዎች አለም አቀፍ ተወዳዳሪነት ጉዳይ ነው። የየኩባንያዎቹ ኃላፊዎችና ባለሙያዎች ካነሷቸው ጥያቄዎች አንዱ የሀገሪቱ ሥራ ተቋራጮች በምን መልኩ ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪ መሆን ይችላሉ? የሚለው ጉዳይ ነው። የሁለት ቀኑ ውይይትና ጥያቄዎች ተጨምቀው ከተላኩላቸው በኋላ በመጨረሻ በኮንፍረንሱ ላይ በመገኘት ማጠቃለያ ሀሳብ የሰጡት ጠቅላይ ሚኒስትር ሀይለማርያም ደሳለኝ፤ የሀገር ውስጥ ስራ ተቋራጮች አለም አቀፍ ተወዳዳሪ ለመሆን በመጀመሪያ በሀገር ውስጥ ብቁ ተወዳዳሪ መሆን ያለባቸው መሆኑን አመልክተዋል። ኢትዮጵያ ውስጥ በርካታ የውጭ ኩባንያዎች በግንባታው ዘርፍ ተሰማርተው እየሰሩ መሆኑን የገለፁት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ በእነዚህ ሰፊ አቅምን በሚጠይቁ የሀገር ውስጥ ግንባታዎች የአገር በቀል ተቋራጭ ኩባንያዎች ተሳትፎ አነስተኛ መሆኑን አመልክተዋል።

ችግሩን ፈቶ የሀገር ውስጥ ተቋራጮችን አቅም ወደ አለም አቀፍ ደረጃ ከፍ ለማድረግ በመሰረታዊነት ሁለት ስራዎች በራሳቸው በተቋራጮቹ መሰራት የሚገባቸው መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትሩ አመልክተዋል። እነዚህም በአንድ መልኩ በሀገር ውስጥ ግንባታን ከሚያከናውኑ የውጭ ተቋራጮች ጋር በንዑስ ተቋራጭነት በመስራት አለም አቀፍ ልምድንና አሰራርን መቅሰም ሲሆን ሁለተኛው በጠቅላይ ሚኒስትሩ የቀረበው የመፍትሄ ሀሳብ ከውጪ ተቋራጭ ኩባንያዎች ጋር በሽርክና (Joint Venture) መስራት ነው።

 የሀገር ውስጥ ተቋራጮችን ከውጭ ሀገር ተቋራጭ ጋር በሽርክና እንዲሰሩ በማድረጉ ረገድ ግን የኢትዮጵያ ሥራ ተቋራጮች ማኔጅመንት ዘመናዊነት ብዙ ሊፈተሽ የሚገባ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትሩ አመልክተዋል። የኢትዮጵያ ሥራ ተቋራጭ ኩባንያዎች ከባለሙያዎች ውጪ በቤተሰብ ስብስብ የሚመሩበትን አሰራር ማስወገድ ካልቻሉ በስተቀር ከውጭ ኩባንያዎች ጋር በሽርክና ለመስራት የማይችሉ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትሩ አመልክተዋል።

በኢትዮጵያ ከአነስተኛ ፎቆች ባለፈ ሰማይ ጠቀስ ፎቆች መገንባት የተጀመረ መሆኑን ያመለከቱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ እነዚህን ሰማይ ጠቀስ ፎቆች በመገንባቱ ረገድ የሀገሪቱ የሥራ ተቋራጮች አቅም ያላደገ በመሆኑ ሙሉ በሙሉ በውጭ ኩባንያዎች የተያዙ መሆናቸውን በመግለፅ፤ ኩባንያዎቹ በሀገር ውስጥ ያለውን ውድድር በብቃት የሚያሸንፉበትን አቅም እየፈጠሩ መሄድ ከቻሉ ወደ አለም አቀፍ ተወዳዳሪነት የሚሸጋገሩበት እድል ያለ መሆኑንም አመልክተዋል። ሆኖም የሀገር ውስጡ ግንባታ በውጪ ኩባንያዎች እየተወረረ ባለበት ሂደት ግን ስለ አለም አቀፍ ተወዳዳሪነት ማሰብ የማይቻል መሆኑ ጨምረው ገልፀዋል።


Warning: Illegal string offset 'active' in /home/sendekne/public_html/templates/leo_news/html/pagination.php on line 94

Warning: Illegal string offset 'active' in /home/sendekne/public_html/templates/leo_news/html/pagination.php on line 100

Warning: Illegal string offset 'active' in /home/sendekne/public_html/templates/leo_news/html/pagination.php on line 94

Warning: Illegal string offset 'active' in /home/sendekne/public_html/templates/leo_news/html/pagination.php on line 100

Warning: Illegal string offset 'active' in /home/sendekne/public_html/templates/leo_news/html/pagination.php on line 94

Warning: Illegal string offset 'active' in /home/sendekne/public_html/templates/leo_news/html/pagination.php on line 100

Warning: Illegal string offset 'active' in /home/sendekne/public_html/templates/leo_news/html/pagination.php on line 94

Warning: Illegal string offset 'active' in /home/sendekne/public_html/templates/leo_news/html/pagination.php on line 100

Warning: Illegal string offset 'active' in /home/sendekne/public_html/templates/leo_news/html/pagination.php on line 94

Warning: Illegal string offset 'active' in /home/sendekne/public_html/templates/leo_news/html/pagination.php on line 100

Warning: Illegal string offset 'active' in /home/sendekne/public_html/templates/leo_news/html/pagination.php on line 94

Warning: Illegal string offset 'active' in /home/sendekne/public_html/templates/leo_news/html/pagination.php on line 100

Warning: Illegal string offset 'active' in /home/sendekne/public_html/templates/leo_news/html/pagination.php on line 94

Warning: Illegal string offset 'active' in /home/sendekne/public_html/templates/leo_news/html/pagination.php on line 100

Warning: Illegal string offset 'active' in /home/sendekne/public_html/templates/leo_news/html/pagination.php on line 94

Warning: Illegal string offset 'active' in /home/sendekne/public_html/templates/leo_news/html/pagination.php on line 100

Warning: Illegal string offset 'active' in /home/sendekne/public_html/templates/leo_news/html/pagination.php on line 94

Warning: Illegal string offset 'active' in /home/sendekne/public_html/templates/leo_news/html/pagination.php on line 100

Warning: Illegal string offset 'active' in /home/sendekne/public_html/templates/leo_news/html/pagination.php on line 94

Warning: Illegal string offset 'active' in /home/sendekne/public_html/templates/leo_news/html/pagination.php on line 100

Warning: Illegal string offset 'active' in /home/sendekne/public_html/templates/leo_news/html/pagination.php on line 94

Warning: Illegal string offset 'active' in /home/sendekne/public_html/templates/leo_news/html/pagination.php on line 100

Warning: Illegal string offset 'active' in /home/sendekne/public_html/templates/leo_news/html/pagination.php on line 94

Warning: Illegal string offset 'active' in /home/sendekne/public_html/templates/leo_news/html/pagination.php on line 100

Warning: Illegal string offset 'active' in /home/sendekne/public_html/templates/leo_news/html/pagination.php on line 94

Warning: Illegal string offset 'active' in /home/sendekne/public_html/templates/leo_news/html/pagination.php on line 100

Warning: Illegal string offset 'active' in /home/sendekne/public_html/templates/leo_news/html/pagination.php on line 94

Warning: Illegal string offset 'active' in /home/sendekne/public_html/templates/leo_news/html/pagination.php on line 100

Warning: Illegal string offset 'active' in /home/sendekne/public_html/templates/leo_news/html/pagination.php on line 94

Warning: Illegal string offset 'active' in /home/sendekne/public_html/templates/leo_news/html/pagination.php on line 100

Warning: Illegal string offset 'active' in /home/sendekne/public_html/templates/leo_news/html/pagination.php on line 94

Warning: Illegal string offset 'active' in /home/sendekne/public_html/templates/leo_news/html/pagination.php on line 100

Warning: Illegal string offset 'active' in /home/sendekne/public_html/templates/leo_news/html/pagination.php on line 94

Warning: Illegal string offset 'active' in /home/sendekne/public_html/templates/leo_news/html/pagination.php on line 100

Warning: Illegal string offset 'active' in /home/sendekne/public_html/templates/leo_news/html/pagination.php on line 94

Warning: Illegal string offset 'active' in /home/sendekne/public_html/templates/leo_news/html/pagination.php on line 100

Warning: Illegal string offset 'active' in /home/sendekne/public_html/templates/leo_news/html/pagination.php on line 94

Warning: Illegal string offset 'active' in /home/sendekne/public_html/templates/leo_news/html/pagination.php on line 100

Warning: Illegal string offset 'active' in /home/sendekne/public_html/templates/leo_news/html/pagination.php on line 94

Warning: Illegal string offset 'active' in /home/sendekne/public_html/templates/leo_news/html/pagination.php on line 100
Page 1 of 46

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us