You are here:መነሻ ገፅ»ፖለቲካ

“ከህወሓት አንዳንድ አመራሮች በላይ

ለትግራይ ህዝብ ጠላት የለም”

አቶ ታደለ ደርሰህ የቪኢኮድ ዳይሬክተር

በይርጋ አበበ

አቶ ታደለ ደርሰህ የቪዥን ኢትዮጵያ ኮንግረስ ድርጅት (ቪኢኮድ) ዋና ዳይሬክተር ሲሆኑ በአገራዊ ጉዳዮች ላይ ሃሳባቸውን በግልጽ በመስጠት ይታወቃሉ። ለአገር እድገት ሶስት መሰረታዊ ነገሮች መሟላት አለባቸው የሚሉት አቶ ታደለ፤ የሶስቱን ተቋማት ማንነት ሲገልጹም ‹‹ነጻ ሚዲያ፣ የማህበራት ጠንካራነት እና ነጻ የፍትህ ስርዓት›› ናቸው ይላሉ። አቶ ታደለ በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ለሰንደቅ ጋዜጣ የሰጡትን አጠር ያለ ቃለ ምልልስ ከዚህ በታች አቅርበነዋል።

ሰንደቅ፡- ከ1990 ዓ.ም ወዲህ በኢትዮጵያ እና ኤርትራ መካከል ያለው ግንኙነት ፍጹም ሰላም የራቀውና የሻከረ ሆኖ ቆይቷል። በቅርቡ የተጀመረውን የመሪዎችን ግንኙነትና የአገራትን የግንኙነት እንቅስቃሴ እንዴት ያዩታል?

አቶ ታደለ፡- በመጀመሪያም አላስፈላጊና ምክንያት የሌለው ጦርነት ነበር የተካሄደው። የአንድ እናት ልጆች ሁለት ወንድማማችና እህትማማች ህዝቦች መካከል የተካሄደ የመጠፋፋት ጦርነት ነበር። በዚያ ‹‹ምክንያት አልባ ጦርነት›› የህይወት እና አካል መስዋዕት እንዲሁም አላስፈላጊ የንብረት ውድመት ያስከተለ ሲሆን ለዚያ ጦርነት መነሻ ምክንያት የነበሩ ሰዎች በታሪክም በህግም ተጠያቂ መሆናቸው አይቀርም። ከ70ሺህ በላይ ሰዎችን ያጠፋው ጦርነት ምንም እንኳን ለጊዜው የሁለቱን ህዝቦች ግንኙነት ቢያቋርጠውም ሁለቱ አገራትና ህዝቦቻቸው ግን ፈጽሞ የሚለያዩ አይደሉም።

ሁለቱ የማይነጣጠሉ ህዝቦች እንዲነጣጠሉ የተደረገው ከጦርነቱ በፊት ነው። ወደ ስልጣን እንደወጡ ለኤርትራዊያን ከኢትዮጵያ መገንጠል የቀረበላቸው የህዝበ ውሳኔ ምርጫ “ከነጻነትና ከባርነት” የሚል ነበር። በየትኛውም መመዘኛ ስናስበው አእምሮው የሚያገናዝብ ማንኛውም ሰው ከእነዚህ ጥያቄዎች “ባርነትን” ሊመርጥ አይችልም። ይህን ስንመለከት ከመጀመሪያውም ሁለቱ ህዝቦች እንዲለያዩ ሆን ተብሎ የታሰበ እና ኋላ ቀር ቃላትን ነበር የተጠቀሙት። ይህ የተደረገው ደግሞ ከጀርባው መሰሪ ተንኮሎች ስለነበሩ ያንን ለማስፈጸም የተደረገ ሴራ ነው።

ሰንደቅ፡- በሁለቱ አገራት መካከል የተካሄደውን ጦርነት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድን ጨምሮ በርካታ ሰዎች ያወግዙታል። ነገር ግን ከማውገዝ በዘለለ በህይወት ያሉትን ለጦርነቱ መነሻ ምክንያት የሆኑ ሰዎችን በህግ ተጠያቂ ለማድረግ አይቻልም? በህይወት የሌሉትስ በታሪክ ተጠያቂ ከመሆን አያመልጡም ሲሉ ምን ማለትዎ ነው?

አቶ ታደለ፡- አንደኛ ምንም ቢሆን ምንም ታሪክን ማዛባት አይቻልም። የሁለቱ አገራት ጦርነት ሲካሄድ በወቅቱ የሚጠቀሙ አካላት ነበሩ፤ እነዚህ አካላት ደግሞ የሚጠቀሙትን ያህል ተጠቅመዋል። በታሪክ ግን ምን ጊዜም ቢሆን ተወቃሾች ናቸው። በታሪክ ተወቃሽ የሚሆኑበት ምክንያት ደግሞ እነዛ ለአገራቸው ሲሉ ህይወታቸውን የከፈሉ የ70 ሺህ ኢትዮጵያዊያን አጽም ይፋረዳቸዋል። አላግባብ የወደመው ኢኮኖሚ ይፋረዳቸዋል፤ የኢትዮጵያ እና ኤርትራ ህዝብ አንድ መሆኑ ስለማይቀር የሁለቱ ህዝቦች በታሪክ ይፋረዷቸዋል። ይህ መሰሪ ተግባራቸው እስከመጨረሻው ድረስ የክፋት አሻራውን ይዞ ይቀጥላል።

ነገር ግን በህይወት ያሉት ለዛ ወንጀላቸው ማሰሪያ የሚሆናቸው ዘመኑ የይቅርታ እና የፍቅር ስለሆነ ማንም ሰው በታሪክ ይሳሳታል። እነዚህ ሰዎች የተሳሳቱት ስህተት፣ ከስህተት ሁሉ የገዘፈ ቢሆንም ለሰሩት ስራ ተጸጽተው የኢትዮጵያንና ኤርትራን ህዝብ በግልጽ ይቅርታ ከጠየቁ የሁለቱም አገራት ህዝቦች የይቅርታ ህዝብ ስለሆኑ ይቅር ይሏቸዋል። ነገር ግን እነዚህ ሰዎች ለመጸጸትና ይቅርታ ለመጠየቅ ወኔ ሊኖራቸው ይገባል። ምንም ሳይደረግና የተፈጸመ ነገር ሳይኖር መስቀል አደባባይ ላይ አስወጥተው በሀሰት ያስጨፈሩን ሰዎች ናቸው። እነዚህ የህወሓት መሪዎች በህግም በታሪክም ተጠያቂ መሆን ያለባቸው ለዚህ ሁሉ ጥፋታቸው ነው። እዚህ ላይ ግን በጥንቃቄ ሊታይ የሚገባው የትግራይን ህዝብ ከህወሓት መሪዎች ለይቶ ማየት እንደሚኖርብን ነው።

ሰንደቅ፡- ህወሓትን እና የትግራይን ህዝብ ለይተን ማየት አለብን ብለዋል። ቀደም ሲል ዶክተር አብይ አህመድም ይህንኑ ብለውታል። ህወሓቶች ደግሞ የትግራይ ህዝብ እና ህወሓት አይነጣጠሉም ሲሉ ተናግረዋል። እርስዎ ሁለቱ ይለያያሉ ያሉበትን ምክንያት ያብራሩልን?

አቶ ታደለ፡- የትግራይ ህዝብ ትልቁ ጠላት ማንም ሳይሆን ህወሓት ነው። ከህወሓት መሪዎች በላይ ለትግራይ ህዝብ ጠላት የለም። ለዚህ ነው የትግራይ ህዝብን እና ህወሓትን ለይተን ማየት አለብን የምለው። ምክንያም ጥቂት የህወሓት አፈጮሌዎች እና ካድሬዎች ወይም ደካሞች ሰሩት ብለን የትግራይን ህዝብ አንጠላም። እንደመር ስንል የትግራይን ህዝብ ጨምረን ነው፤ እንደመር ስንል ትናንት ህዝቡን ያናከሱት የህወሓት መሪዎች ተጸጽተው ህዝብን ይቅርታ መጠየቅ አለባቸው እያልን ነው። እነዚህ የህወሓት መሪዎች ለዚህ ጥፋታቸው በመጀመሪያ ደረጃ የትግራይን ህዝብ ይቅርታ መጠየቅ ይኖርባቸዋል።

ሰንደቅ፡- ኢትዮጵያ እና ኤርትራ ደም አፋሳሽ ጦርነት በኋላ አዲስ የግንኙነት ምዕራፍ ለመጀመር በመሪዎች ደረጃ ጥረት እየተካሄደ ነው። ዛሬም (ቃለ ምልልሱ በተካሄደበት እለት) ዶክተር አብይ ወደ አስመራ ተጉዘዋል። ነገር ግን ይህን የዶክተር አብይ እንቅስቃሴ የሚተቹ ፖለቲከኞች ‹‹ግንኙነቱ ትግራይን ያላካተተ ስለሆነ ትርጉም አልባ ነው›› ይሉታል። ትግራዮች ያልተሳተፉበት ግንኙነት ሲባል ምን ማለት ነው?

አቶ ታደለ፡- ቀደም ብዬ እንደነገርኩህ እኮ ነው። ‹‹ዛሬም ቢሆን ህወሓት የበላይ ነው። ስለዚህ የህወሓት መሰሪ ተግባር መቀጠል አለበት›› እያሉን ነው ያሉት። የኢትዮጵያ ህዝብ ደግሞ የህወሓት መሰሪ ተግባር ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ መቆም አለበት ነው እያለ ያለው። እነዚህ የህወሓት መሪዎች መሰሪነት የጀመረው እኮ አሁን አይደለም። በመጀመሪያ ደረጃ ገና በ1968 ዓ.ም ወደ ደደቢት በርሃ ሲወርዱ ባወጡት ማንፌስቶ ገጽ አራት ላይ ‹አማራ ጠላታችን ነው› ብለው አማራንና ትግራይን ያናከሱ ናቸው። ስለዚህ ያ መሰሪ ተግባራቸው ዛሬም እንዲቀጥል ነው የሚፈልጉት። ነገር ግን ያ መሰሪ ተግባራቸው የተቃጠለ ካርታ ነው፤ የትም ቦታ ሄዶ ሊሰራላቸው አይችልም። የትግራይ ህዝብ ዛሬ የሚፈልገው ከሌሎቹ የኢትዮጵያ ወንድምና እህቶቹ ጋር በጋራ ሆኖ በዚህች አገር ላይ ሁሉም እኩል ተጠቃሚ ሆኖ መኖርን እንጂ፤ በጥይት መደባደብን እና በሌላው ጉዳይ መወነጃጀልን እንዲሁም አድማ እና የህወሓትን መሰሪ ተግባር መፈጸም እና ሰለባ መሆንን አይደለም።

የትግራይ ህዝብ እንደሌላው የኢትዮጵያ ህዝብ መብቱን ያጣና በህወሓት መሰሪዎች ጭቆና የተረገጠ ህዝብ ነው። ንጹህ ውሃ ለማግኘት የተቸገረ እና የትምህርትም ሆነ የጤና አቅርቦት ያጣ ህዝብ ነው። እነዚህ የህወሓት መሰሪዎች ‹‹የትግራይን ህዝብ እንወክላለን›› የሚሉት ህዝቡን እንደዚህ እየበደሉ ነገር ግን የትግራይን ህዝብ ከሌሎቹ ወንድምና እህቶቹ ጋር እንዲለያይ እያደረጉት ነው። ስለዚህ የትግራይ ህዝብ እነዚህን ሰዎች በጽኑ ታግሎ ከትከሻው ላይ ሊያወርዳቸውና ላደረሱበት በደልም በህግ ሊፋረዳቸው ይገባል።

እነዚህ በትግራይ ህዝብ ትከሻ ላይ ተቀምጠው 27 ዓመት ሙሉ በደልና ግፍ ሲፈጽሙብን የከረሙት የህወሓት አንዳንድ መሪዎች ለፈጸሙት ግፍ ተጽጽተው ይቅርታ ሊጠይቁ ብቻ ሳይሆን እነሱ ለጨቆኑት ህዝብ ነጻ እንዲወጣ የተመረጠው ዶክተር አብይም በፈርኦን ቤት ያደገ ሙሴ መሆኑን ሊያውቁት ይገባል።

ሰንደቅ፡- ዶክተር አብይ አህመድ በፈርኦን ቤት ያደጉ ሙሴ ናቸው ለማለት ያስደፈረዎት ምንድን ነው?

አቶ ታደለ፡- ዶክተር አብይ ገና ከ15 ዓመታቸው ጀምረው ያደጉት በጨቋኝና መሰሪ ከሆኑት ከህወሓት መሪዎች ጋር ቢሆንም፤ እሳቸው ግን ለህዝባቸው ነጻነት፣ ፍቅርና ሰላም መስበክ የቻሉ ሰው ስለሆኑ ነው። ገና ከ15 ዓመታቸው ጀምረው እነዚህን ሰዎች በሚገባ አይተዋቸው መሰሪነታቸውንም ተረድተው እና ይህ አካሄዳቸውም ለኢትዮጵያ እንደማያዋጣ ተረድተው ጊዜውን ጠብቀው የተነሱ ሰው ናቸው። እሳቸውን ለዚህ ህዝብ የላካቸውም እግዚአብሔር ነው።

በነገራችን ላይ ዶክተር አብይ የሚያስፈልጉት ለኢትዮጵያ ብቻ አይደለም፤ ለምስራቅ አፍሪካ እና ለአፍሪካም የሚያስፈልጉ ሰው ናቸው። እኛም ብንሆን እኒህን ጠቅላይ ሚኒስትር በማንኛውም በምንችለው መንገድ ሁሉ ልናግዛቸውና ልንተባበራቸው ይገባል ብዬ አስባለሁ። እነዚህ ሰዎች ግን (የህወሓት መሪዎችን) ይህን እውነታ መቀበል ካልቻሉ ሰውነታቸውም ያጠራጥረኛል። ስለዚህ እነዚህ ሰዎች ይህን መሰሪነታቸውን ካላቆሙ እንኳን ለኢትዮጵያ እና ለትግራይ ህዝብ ቀርቶ ለራሱ ለህወሓት እና ለራሳቸውም አይበጁም። ጊዜው መሽቶባቸዋል።

ሰንደቅ፡- ዶክተር አብይ አህመድና አቶ ኢሳያስ አፈወርቂ የጀመሩት ግንኙነት ለቀጠናውና ለሁለቱ አገራት የሚኖረው ትርጉም ምንድን ነው?

አቶ ታደለ፡- በመጀመሪያ ደረጃ በዚህ ጉዳይ ይኖራል ብዬ የማስበው ጥቅም የሰው አእምሮ ሰላም ይሆናል። እናት ከልጇ፤ ባል ከሚስቱ፤ ወንድም ከወንድሙና እህት ከእህቷ ጋር ተለያይቶ ነው ላለፉት 27 ዓመታት የቆዩት። ስለዚህ እነዚህ መለያየት ያልነበረባቸው ህዝቦች አለመለያየታቸውን ያመጣል።

በሌላ ጎን ደግሞ ‹‹የውሃ እናት›› እየተባለች የምትጠራውን አገር (ኢትዮጵያን ለማለት ነው) ወደብ አልባ ማድረግ በታሪክ ማንም ይቅር ሊለው የማይችል ወንጀል ነው። ስለዚህ አሁን የሁለቱ መሪዎች ግንኙነት ይህንን ወንጀል እንዲቀር ያደርገዋል። አሰብ የእኛ ንብረት ሆኖ ሳለ በንብረታችን መጠቀም እየቻልን በሌላ ቦታ እንድንጠቀም የተደረገው በኢትዮጵያ ላይ ከፍተኛ የሆነ ኢኮኖሚ አሻጥር በመፈፀሙ ነው። ይህንንም ስለሚቃልል የመሪዎቹ መገናኘት ጠቀሜታ አለው።

ከዚህ በተጨማሪ ደግሞ ቦታው ስትራቴጂክ ነው። በዚህ ስትራቴጂክ ቦታ ላይየድርሻውን ለማግኘት የማይጠቀም አካል የለም። ብዙዎቹም አሰፍስፈው እየተጠባበቁ ነው። ስለዚህ ይህን የመሰለ ስትራቴጂክ ቦታ ሰላም እንዲሆን ማድረግ ለቀጠናው ሰላም ይሆናል። ምስራቅ አፍሪካ ሰላም ከሆነ ደግሞ መላ አህጉሩ ሰላም ይሆናል። ቀይ ባህር ሰላም ከሰፈነበት ዓለምም እንዲረጋጋ የራሱን ሚና ይጫወታል።

ከጦርነት ያተረፍነው ነገር ቢኖር ኪሳራችንን ማብዛት ብቻ ነው። እኛ ስንጣላ እነሱ (ምዕራባዊያንን) ለእኛ መሳሪያ ያቀብላሉ። እኛ በእነሱ ዘመን ያለፈበት መሳሪያ ስንተላለቅ ‹‹የሰላም ኮንፈረንስ›› ብለው ይጠሩንና በሌላ አቅጣጫ አዳዲስ የጦር መሳሪያዎችን እያመረቱ እንደገና እንድንጫረስ ያደርጉናል። ስለዚህ ይህ እኩይ ተግባር በምስራቅ አፍሪካ እንዲቆም የሚያደርግ የግንኙነት ጅማሮ ነው ብዬ አስባለሁ።

ሰንደቅ፡- የወደብ ጉዳይ ካነሱ አይቀር ኢትዮጵያ ወደብ እንዲኖራት ከኢህአዴግ ውጭ ያሉ ፖለቲከኞች ደጋግመው ይናገራሉ። በኢህአዴግ በኩል ግን ከአቶ መለስ ዜናዊ ጀምሮ የፓርቲው ከፍተኛ መሪዎች የወደብ ጥያቄን የሚያነሱትን ሰዎች ‹‹ጦርነት ናፋቂዎች›› ሲሉ ይወቅሷቸዋል። ቀደም ሲል የኢህአዴግ መሪዎች ወደብን ይገልጹበት ከነበረው እይታ ወጣ ባለ መልኩ ዶክተር አብይ የወደብን አስፈላጊነት ማቀንቀናቸው የኢህአዴግ እምነት ተቀይሯል ብለው ያስባሉ?

አቶ ታደለ፡- ይህ የኢህአዴግ እምነት ነው ብዬ አላስብም፤ አላንምም። የወደብ ጉዳይ የኢህአዴግ እምነት ቢሆንማ ኖሮ ታሪክ ወደፊት ዝርዝር ሁኔታውን ቢያወጣውም ሰኔ 16 ቀን 2010 ዓ.ም መስቀል አደባባይ ላይ በተጠራ ሰላማዊ ሰልፍ ላይ እንደዛ አይነት የህዝብን ስሜት የሚነካ ተግባር አይፈጸምም ነበር (ዶክተር አብይን ኢላማ ያደረገ የቦንብ ጥቃት መፈጸሙን)። የወደብ ጥያቄም የኢህአዴግ ፍላጎት አይደለም። የወደብ ጥያቄ ከኢህአዴግ ውጭ ያሉ ከመቶ ሚሊዮን በላይ ዜጎች የሚጠይቁት ጥያቄ ነው። ይህን የህዝብ ጥያቄ ደግሞ ኢህአዴግ መቀበል አለበት። ኢትዮጵያ ላይ ወደብ እንዳይኖራት የተፈረደባትም በኢህአዴግ በተለይም በህወሓት መሪዎች አማካኝነት ነው።

 

የኢትዮ-ኤርትራ ጦርነትን ተከትሎ ሁለት አስርት ዓመታት የፈጀው “ምንም ሰላም፤ ምንም ጦርነት የሌለበት” የመፋዘዝ ፖሊሲ በሰላም ለመቋጨት በሚያስችል ሁኔታ ውስጥ እንዳለ ፍንጭ የሚሰጥ ጉዳይ ባሳለፉነው ሳምንት ተስተውሏል።

በተለይ ጠቅላይ ሚኒስተር ዐብይ አሕመድ ሐምሌ 1 ቀን 2010 ዓ.ም. በአስመራ ያደረጉት ይፋዊ የሥራ ጉብኝት በሁለቱ ሕዝቦች መካከል የነበረውን የምንም ሰላም የምንም ጦርነት ፖሊሲን ወደ ዘላቂ ሰላም ሊቀይረው ይችላል ተብሎ ተስፋ ተደርጎበታል። ፕሬዚደንት ኢሳያስ አፈወርቂም በበኩላቸው የጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ የወሰዱት ተነሳሽነት ከግቡ እንዲደርስ አስፈላጊውን ሁሉ እናደርጋለን ማለታቸው፤ በቀጣይ በሁለቱ ሀገሮች የሰላም ስምምነት ላይ ይደርሳሉ የሚል ተስፋ በባለድርሻ አካላት አሳድሯል።

የኤርትራ ሕዝብ ለጠቅላይ ሚኒስተር ዐብይ አሕመድ ያሳየው አቀባበል በሁለት መልኩ የሚታይ ነበር። አንደኛው፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ ለሚከተሉት የ”ፍቅር ዲፕሎማሲ” እውቅና መስጠት ሲሆን፤ ሁለተኛው፣ የኤርትራ ሕዝብ በሁለቱ ሀገሮች መካከል በማንኛውም ዋጋ ሰላም እንዲሰፍን ያለውን ቁርጠኝነትና ፍላጎት ከፍ አድርገው ለማሳየት የተጠቀሙበት መድረክ ነው።

በፕሬዝደንት ኢሳያስ አፈወርቂ የሚመራው ገዢው ፓርቲ የጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይን ጉብኝት የተቀበለበት መንገድ አስገራሚ ነው። አንደኛው፣ ፕሬዝደንት ኢሳይያስ ለሃያ ዓመታት በይፋ ለኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት በብቸኝነት ሕወሓት ተጠያቂ ሲያደርጉ መሰንበታቸው ቢታወቅም፣ የሰላሙን ጥሪ ለመቀበል በምክንያትነት ያስቀመጡት የዶክተር ዐብይን የሰላም ዝግጁነትና ቀናነትን ነበር። ሁለተኛው፣ ፕሬዝደንት ኢሳያይስ በንግግራቸው ያራመዱት አቋም አሸናፊ መሆኑን ከመግለፃቸውም በላይ ንብረታችንም አላጣንም ብለዋል። የአስመራ ገዢውም ፓርቲና የኤርትራ ሕዝብ በትዕግስት የፈለጉትን ማግኘታቸውን አሳውቀዋል።

በኢትዮጵያ በኩል በገዢው ፓርቲ ውሳኔ መሰረት፣ ነፍጥ ላነሱ የፖለቲካ ኃይሎች እና ለሕግ ታራሚዎች ምህረት መስጠቱ የሚታወቅ ነው። በሁለተኛ ደረጃ ከኤርትራ መንግስት ጋር ስምምነት ለማውረድ፤ የአልጀርስ ስምምነትን ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ለመተግበር በወሰነው መሰረት ወደ ተግባር የተሸጋገረበት ክዋኔ ተደርጎ የሚወሰድ ነው። ይህም በመሆኑ ገዢው ፓርቲ በአስመራ ላይ በተከተለው ውሳኔ በአብዛኛው ሕዝብ ቅቡልነት አግኝቷል።

እንደመንግስት ስንመለከተው፣ የኢትዮጵያ እና የኤርትራ መንግስታት የተለያዩ የሰላምና የወዳጅነት ስምምነትን ተፈራርመዋል። በዚህ ስምምነት ቁልፍ ውሳኔ ተደርጎ የሚቀመጠው ሁለቱ ሀገሮች በይፋ የነበሩበት ጦርነት ማብቃቱን ማወጃቸው ነው።

የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ እና የኤርትራው ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ በሁለቱ ሃገራት መካከል የተደረሱ በርካታ የሰላምና ወዳጅነት ስምምነቶችን ፈርመዋል። እነሱም፤ በሁለቱ ሃገራት መካከል ያለውን ጦርነት በይፋ ማስቆምና ወደ አዲስ የግንኙነትና ወዳጅነት ምዕራፍ መሸጋገር፤ በፖለቲካ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊ፣ ባህላዊና የፀጥታና ደህንነት ጉዳዮች ላይ በትብብር መስራት፤ የአየርና የየብስ ትራንስፖርትን ማስጀመር፣ የተቋረጠውን የመደበኛ ስልክ አገልግሎት እንዲሁም የንግድ ግንኙነታቸውን ማስጀመርም ናቸው። በተጨማሪም፣ በሁለቱ ሃገራት መካከል ተቋርጦ የነበረውን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ለማስጀመር፣ የኢትዮጵያ ኤምባሲ በአስመራ የኤርትራ ኤምባሲ ደግሞ በአዲስ አበባ አበባ እንዲከፈት ተስማምተዋል።

የስምምነታቸው ማሰሪያ ነጥብ ተደርጎ የሚወሰደውን፣ በአልጀርሱ ስምምነት የገቧቸው የድንበር ስምምነቶች ገቢራዊ ለማድረግ እና ሁለቱ ሃገራት በቀጠናው ሰላም፣ ልማትና ትብብርን ለማምጣት በጋራ ለመስራት ከስምነት ላይ ደርሰዋል። በውጭ መገናኛ ሚዲያዎችና በማሕበራዊ ሚዲያ ውስጥ ተወሽቀው በሁለቱ ሀገሮች መካከል ሲካሄዱ የነበሩ የጥላቻን ፕሮፖጋንዳ በሮችን ለመዝጋት ተስማምተዋል።

የአፍሪካ ህብረት እና አውሮፓ ህብረት ኢትዮጵያ እና ኤርትራ የሰላምና የወዳጅነት ስምምነት መፈራረማቸውን አዎንታዊ እርምጃ ብለውታል። የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ሙሳ ፋቂ መሃመት ባወጡት መግለጫ፥ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ እና ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ የፈረሙትን የሰላምና የወዳጅነት ስምምነት አድንቀዋል፤ የሁለቱ ሀገራት የህዝባቸውን የጋራ ተጠቃሚነት በማስቀደም ግንኙነታቸን ለማሻሻል የወሰዱትን እርምጃ ተገቢ ነው ብለዋል።

አያይዘውም፣ ኢትዮጵያ እና ኤርትራ በአሁኑ ወቅት የጀመሩት የሰላም ሂደትም እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ2020 አፍሪካን ከጦር መሳሪያ ድምጽ ነፃ ለማድረግ ለተያዘው እቅድ መሰረት የሚጥል ነው ሲሉም አወድሰዋል። ኢትዮጵያ እና ኤርትራ በቀጣይም ግንኙነታቸውን ለማሻሻል ለሚያነናውኑት ተግባራት የአፍሪካ ህብረት አስፈላጊውን ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ መሆኑንም ሊቀመንበሩ ሙሳ ፋቂ መሃመት አስታውቀዋል።

በተመሳሳይ የአውሮፓ ህብረት ባወጣው መግለጫ፣ ኢትዮጵያ እና ኤርትራ የተፈራረሙት የሰላምና የወዳጅነት ስምምነት ታሪካዊ እና የሚደነቅ ነው ሲሉ ድጋፋቸውን አሳይተዋል። የአውሮፓ ህብረት ምክትል ፕሬዚዳንት ፌድሪካ ሞግሄሀርኒ ባወጡት መግለጫ፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ እና ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ የፈረሙት ስምምነት የሁለቱን ሀገራት ግንኙነት የሚያሻሽል ነው ብለዋል እንደሚያምኑ ገልጸዋል።

አክለውም ም/ፕሬዝደንት ፌድሪካ፣ ኢትዮጵያ እና ኤርትራ ላለፉት 20 ዓመታት በመካከላቸው የነበረውን ችግር በመፍታት ግንኙነታቸውን ለማሻሻል መስማማታቸው በአፍሪካ ቀንድ አካባቢ ቀጠናዊ ትብብር እንዲጠናከርና ሰላም እንዲሰፍን የሚያደርግ ነው ሲሉ ተስፋቸውን አስቀምጠዋል። እንዲሁም የአውሮፓ ህብረት በኢትዮጵያ እና በኤርትራ መካከል ያለው ግንኙነት አስተማማኝ ደረጃ ላይ እስከሚደርስ ድረስም አስፈላጊውን ሁሉ ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ መሆናቸውን ሕብረቱን ወክለው ገልፀዋል።

በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ የእጅ አዙር ጦርነት የምታካሂደው ግብፅ በበኩሏ፣ የኢትዮጵያ እና የኤርትራ መሪዎች አስመራ ላይ ተገናኝተው ታሪካዊውን የሰላም ስምምነት መፈራረማቸውን አደንቃለሁ ብላለች። የግብፅ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አያይዞም በመግለጫው እንደገለጸው፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ እና የኤርትራው ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ተገናኝተው መወያየታቸውም ለሀገራቱም ሆነ ለአካባቢው የሚኖረው አስተዋጽዎ ከፍተኛ ነው ብለዋል። በሁለቱ ሀገራት መካከል አዲስ ምዕራፍ ከመክፈት አልፎ በአፍሪካ ቀንድ ፀጥታ እና መረጋጋትን ከማስፈን አንጻር ያለ ጥርጥር ከፍተኛ አስተዋጽኦ ይኖረዋል ብሏል።

የሲዊዲን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማርጎት ዎሊስትሮም በበኩላቸው፣ ኢትዮጵያና ኤርትራ የፈረሙትን የሰላምና የወዳጅነት ስምምነትን እንደሚደግፉ ገልፀው፤ ሲዊዲን ለሁለቱ ሀገራት አስፈላጊውን ትብብር ለማድረግ ዝግጁ መሆኗን አስታውቀዋል።

የወቅቱ የአፍሪካ ህብረት ሊቀመንበር የሩዋንዳው ፕሬዚዳንት ፖል ካጋሜ እና የኬንያው ፕሬዚዳንት ኡሁሩ ኬንያታም ስምምነቱን ተከትሎ የእንኳን ደስ ያላችሁ መልዕክታቸውን ማስተላለፋቸው ይታወሳል። እንዲሁም፣ የተባበሩት አረብ ኤሚሬቶች የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሼክ አብዱላሂ ቢን ዛይድ አል ነኸያንም ስምምነቱን በማድነቅ፤ ሀገራቸው ሁለቱ ሀገራት በትብብር ሰላምና ብልፅግናን ለማምጣት የሚያደርጉትን ጥረት እንደምታግዝም አረጋግጠዋል።

ከምስራቅ አፍሪካ ሀገሮች የሰላምና የደህንነት አንፃር በባለድርሻ አካላት ከፍተኛ ድጋፍ የተቸረው የሰላም እርምጃ ነው። የኬኒያው ፕሬዝደንት ዑሁሩ ኬኒያታ የሰላም ስምምነቱን አስመልክተው፣ “እንኳን ደስአላችሁ፤ ጎረቤታችሁ በመሆናችን እንኮራለን” ካሉ በኋላ ለሰላም ስምምነቱም መተግበር እገዛ እንደሚያደርጉ አሳውቀዋል። ኢጋድ በበኩሉ ኢትዮጵያ ለሰላም ስምምነቱ የወሰደችውን ተነሳሽነት አድንቋል። ኤርትራም ወደ ኢጋድ አባልነቷ እንድትመለስ ጥሪ አቅርቧል።

ኢትዮጵያ የመንግስታቱ ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት በኤርትራ ላይ የጣለውን ማዕቀብ እንዲያነሳ ይፋዊ ጥያቄ ማቅረቧ ታውቋል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ አዲስ አበባ ከተመለሱ በኋላ ከመንግስታቱ ድርጅት ዋና ፀሃፊ አንቶኒዮ ጉተሬዝ ጋር ከተወያዩ በኋላ ተመድ በኤርትራ የጣለውን ማዕቀብ እንዲያነሳ ለዋና ፀሃፊው ይፋዊ ጥያቄያቸውን አቅርበዋል። ጥያቄው የቀረበላቸው የመንግስታቱ ድርጅት ዋና ፀሃፊ አንቶኒዮ ጉተሬዝ በበኩላቸው፥ ኤርትራ ላይ የተጣለው ማዕቀብ ከዚህ በኋላ ብዙ ጊዜ ተግባር ላይ እንደማይቆይ ተናግረዋል።

ዋና ፀሃፊው ኢትዮጵያና ኤርትራ መደበኛ ግንኙነታቸውን ለመጀመር መስማታቸውን ተከትሎ፥ ምክር ቤቱ በኤርትራ ላይ የጣለው ማዕቀብ ከዚህ በኋላ ተግባር ላይ የሚቆይበት ምክንያት የለም ብለዋል። አያይዘውም ዋና ፀሐፊው፣ ሁለቱ ሃገራት ከድንበር ጋር በተያያዘ የደረሱት የድንበር ማካለል ጉዳይ እንዲሳካም ተመድ ሁኔታዎችን ለማመቻቸት ዝግጁ መሆኑንም ገልጸዋል።

የትግራይ ክልላዊ መንግስት እና የትግራይ ህዝብ የኢትዮ-ኤርትራ ሁኔታ በዘላቂነት ለመፍታት በሚደረገው ሁሉን አቀፍ ጥረት ከኤርትራ ህዝብ ጎን እንደሚቆሙ አረጋግጠዋል።

ምክር ቤቱ ባወጣው መግለጫ፣ በሁለቱ ሀገራት መካከል ለ20 ዓመታት የዘለቀው ሰላምም ጦርነትም የሌለበት ሁኔታን በዘላቂነት ለመፍታት በኢህአዴግ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ የቀረበውን ወሳኔ ተከትሎ ህወሓትና የትግራይ ክልል መንግስትም በተመሳሳይ አኳኋን የትግራይ እና የኤርትራ ህዝቦች ወንድማማችነት ወደነበረበት ሁኔታ ለመመለስ ጠንክረው እንደሚሰሩ መወሰናቸውንና ውሳኔያቸውም ለመላው የትግራይ ህዝብ፣ ለሁሉም የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች እንዲሁም ለኤርትራ ህዝብ ይፋ ማድረጋቸውን አስታውሷል።

መግለጫው የትግራይ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት የኢትዮጵያ እና የኤርትራ መንግስታት የሁለቱ ህዝቦች ሰላም በዘላቂነት ለመፍታት እያሳዩት ያለው ዝግጁነትና ተነሳሽነት የክልሉ መንግስት እንደሚያደንቅ አስታውቋል። በተለይ የኤርትራ ህዝብ ለ20 ዓመታት የዘለቀውን ሁኔታ በመፍታት የአትዮ-ኤርትራ ወንድማማችንትና ወዳጅነትን ለማጠናከር ያሳየው ፍላጎት፣ ጉጉትና ፍቅር እጅግ የሚያስደስትና ከፊት ለፊታችን ብሩህ ተስፋ እንዳለም የሚገለፅ ነው ብሏል። በመሆኑም የትግራይ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ለኤርትራ ህዝብ ያለው ወንድማዊ አድናቆት ከፍ ያለ መሆኑን መግለፅ ይፈልጋል ብለዋል። የሁለቱ ሀገራት ህዝቦች የተጀመረውን ሰላም የማረጋገጥ ስራ ይበልጥ ለማጠናከር በአጭር ጊዜ ውስጥ ቀጥተኛ የሆነ የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት በመጀመር ወንድማማችነታቸውንና ወዳጅነታቸውን እንዲያጠናክሩ ጥሪው አቅርቧል።

ኢትዮጵያ ቴሌኮሚኒኬሽን በበኩሉ ወደሥራ ገብቻለሁ ብሏል። አያይዞም፣ ወደ ኤርትራ ስልክ መደወል ለምትፈልጉ በሙሉ አጭር ማብራሪያ ይህንን ይመስላል፤ “በመደበኛ ስልክ ለመደወል ሲፈልጉ በመጀመሪያ +291ን መጻፍ ቀጥሎ 1ን በመጫን የደንበኛዉን ስልክ ቁጥር መጻፍ፤በሞባይል ለመደወል ደግሞ በመጀመሪያ +291ን መጻፍ ቀጥሎ 7ን በመጫን የደንበኛውን ቁጥር መጻፍ፤ ለሁለቱም /ለመደበኛና ለሞባይል/ስልኮች ታሪፍ ተመሳሳይ ሲሆን በደቂቃ 10 ብር ከ29 ሳንቲም ነው።”

 

ተቃውሞ

ላለፉት 26 ዓመታት ኤርትራን ያስተዳደሩት ፕሬዝደንት ኢሳይያስ ብቻ ናቸው። በኤርትራ ምድር ሕገ-መንግስት የለም። የሲቪል ሶሳይቲ የለም። በግል ይዞታ የሚተዳደር ሚዲያ የለም። ነፃ ፍርድ ቤት የለም። የሃይማት ነፃነት ለተወሰኑ እምነቶች ብቻ የተፈቀደ ነው። አስራ ስምንት ዓመት የሞላው ወጣት የብሔራዊ ውትድርና አገልግሎት እንዲሰጥ ይገደዳል። በሲቪል አገልግሎት የሚሰጡ ተቋማት በወታደራዊ ተሿሚዎች ይያዛል። በአስገዳጅ ሁኔታ ዜጎች በነፃ ጉልበታቸውን እንዲሰጡ ይገደዳሉ።

ከአጠቃላይ የኤርትራ ሕዝብ አስራ ሁለት በመቶ የሚሆነው ከሀገር ተሰደው ወጥተዋል። በተባበሩት መንግስታት ከፍተኛ የስደተኞች ኮሚሽን (United Nations High Commissioner for Refugees (UNHCR) report) ሪፖርት መሰረት በእ.አኤ. በ2016 ብቻ 52ሺ ኤርትራዊያኖች ከሀገራቸው ተሰደው ወጥተዋል። በ2012 የኤርትራ ፕሬዝደንት ኢሳያስን በመቃወምና ሂስ በማድረግ ከኤርትራ መንግስት ሸሽቶ የወጣ የአንድ ሚኒስትር ቤተሰቦች አሜሪካዊ ዜግነት ያላት የአስራ አምስት አመት ልጁን እና የሰማንያ ዓመት እድሜ ያላቸውን አያቱን እና የሰላሳ ስምንት ዓመት ወንድ ልጁን ወደ እስር ቤት መወርወራቸውን ሪፖርቱ ያሳያል። እስካሁንም ድረስ አለፍርድ እስር ቤት ውስጥ ናቸው ተብሏል። በሃይማኖት ረገድም ሱኒ ኢስላም፣ ኦርቶዶክስ፣ ካቶሊክ እና ሉተራን እምነቶች ብቻ ነው የሚፈቀደው።

ከላይ የሰፈሩትን ወቅታዊ የኤርትራ ፖለቲካ ኢኮኖሚ ማሳያዎችን እያነሱ በተለይ በስደት ሀገር የሚገኙ ኤርትራዊያን፣ “ለስደት ለውርደት ለእንግልት” ከዳረገን ፕሬዝደንትና ከሻዕቢያ ጋር፤ ጠቅላይ ሚኒስተር ዐብይ አሕመድ እንዴት ስምምነት ያደርጋሉ ሲሉ በዩቲዩብ እና በሌሎች ማሕበራዊ ሚዲያዎቸች ተቃውሞቸውን እያሰሙ ይገኛሉ።

በኤርትራ መንግስት ላይ ነፍጥ አንስተው እየታገሉ ያሉ ኃይሎች በበኩላቸው፣ የኢትዮጵያ መንግስት እኛን በተመለከተ ምንም ዓይነት ውይይት ሳያደርግ ወይም የእራሳችን አማራጭ እንድንወስድ ሳንማከር ከኤርትራ መንግስት ጋር የሰላምም ስምምነት ለማድረግ መወሰኑን ተከትሎ፣ ሕልውናችን አደጋ ውስጥ ወድቋል ሲሉ ስጋታቸውን አስቀምጠዋል።

ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ የኤርትራ መንግስት ተቃዋሚ ኃይሎች አመራር ለሰንደቅ እንደገለጽት፤ “የኢትዮጵያ መንግስት ነፍጥ ላነሱበት ኃይሎች ምህረት በማድረግ ወደ ሰላማዊ ትግል እንዲገቡ ሲፈቅድ፣ የኤርትራ ተቃዋሚ ኃይሎች እጣፈንታ ምን ሊሆን ይገባዋል ብሎ አልመከረም። በጋራ የኤርትራ መንግስትን የሽብር ፖለቲካ ኢኮኖሚን ስንመክት ከርመን፣ አሁን ላይ የኢትዮጵያ መንግስት በተናጠል የወሰደው የሰላምም ስምምነት፣ የኢትዮጵያ መንግስትን ለሰብዓዊ መብት፣ ለዴሞክራሲ እና ለነፃነት ያለውን ታማኝነት ጥያቄ ውስጥ የሚጥል ነው” ብለዋል።

አያይዘውም፤ “ከዚህ በፊት በጀበሃ አመራሮች ላይ በኢትዮጵያ ግዛት ውስጥ በመግባት የሻዕቢያ ቡድን የፈጸመው ግድያ፤ ነገ እኛ ላይ እንደማይደገም ዋስትናችን ምንድን ነው? ሲሉ ለኢትዮጵያ መንግስት ጥያቄያችን አድርሱልን” ብለዋል።

ሰኔ 24 ቀን 2010 ዓ.ም ባሕርዳር ከተማ የ“መደመር ቀን” በሚል መሪ ቃል በመቶ ሺዎች በሚቆጠሩ የከተማውና የአካባቢው ሕዝቦች በአንድ ላይ ተሰባስበው በተለያዩ ዝግጅቶች አክበርዋል። አምስት መቶ ሜትር ርዝመት በስድሰት ሜትር ስፋት አረንጓዴ ቢጫ ቀይ ባንድራ ይዘው በውጣት ዝግጅቱን አድመቀውታል።

የሰለፉ መሰረታዊ ዓላማ የጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አሕመድ የ“መደመር” ፖለቲካዊ መርህን ለመደገፍና፤ ለመደመር ያለመ መሆኑን ከአዘጋጆቹ ተደምጧል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ በአካል በስብሰባው ላይ ባይገኙም “ለባሕርዳር ከተማ እና አካባቢው ነዋሪዎች የከበረ ሰላምታ እና መልካም የለውጥ ምኞታቸውን” በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ለታዳሚው አስተላልፈዋል።

በባሕርዳር ስታዲየም ዝግጅት ላይ በርካታ ሰዎች ተጋብዘው ንግግር አድርገዋል። ንግግር ካደረጉት መካከከል አቶ ደመቀ መኮንን፣ አቶ ገዱ አዳርጋቸው፣ ብርጋዴን ጀነራል አሳምንው ፅጌ፣ ወ/ሮ እማዋይሽ አለሙ እና አቶ ሽባባው የእኔአባት ይገኙበታል። በቀረቡት ንግግሮች ላይ ተንተርሰን ፖለቲካዊ ትንታኔዎች ከማቅርብ፤ የመረጥነው እንዳለ ማቅርብ ነው። ምክንያቱም ንግግር ካቀረቡት ሰዎች አውድ ውጪ፣ ትንታኔ ከማቅረብ ለመቆጠብ ነው።

በድጋፍ ሰልፉ ላይ ለየት ያለና ወደፊት ብዙ ሊያነጋግር የሚችል ሃሳብ የተሰነዘረው ከወ/ሮ እማዋይሽ አለሙ ነው። ይኸውም፤ ወ/ሮ እማዋይሽ ለድጋፍ ሰልፈኛው ያቀረቡት ጥያቄ “የአብረን እንስራ ጥሪ ሲቀርብልን በተቀደደልን ቦይ ለመፍሰስ ነው ወይንስ የሽግግር መንግስት ለማቋቋም?” የሚል ነው። ይህ ሃሳብ ብዙ ጉዳዮች የታጨቁበት ብዙ ገጽ ወሬ መልዕክት ያለው መሆኑን ብንገነዘብም፤ እሳቸው ካሉት በላይ ብዙ ዕርቀት መሄድ አልፈለግንም።

ሆኖም ግን የድጋፍ ሰልፉ ገዢ ሃሳብ ይሆናሉ በማለት የብአዴን ሊቀመንበር የአቶ ደመቀ መኮንን እና የምክትል ሊቀመንበሩን የአቶ ገዱ አዳርጋቸውን ንግግሮች በተቻለ መጠን ሙሉውን አስፍረነዋል። በሊቀመናብርቱ ሊተላለፉ የተፈለጉትን መልዕክቶች፣ አንባቢዎቻችን በተረዳችሁበት አግባብ እንድትወስዱት ለእናንተው ተውነው። የአውዱን ፍቺ ነፃነት ለመጠበቅ በማሰብ ነው። መልካም ንባብ።

 

 

ም/ጠ/ሚ አቶ ደመቀ መኮንን

ባህርዳር ላይ ያስተላለፉት መልዕክት

 

በቅድሚያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድ . . . በአካል በዚህ ታሪካዊ ሰልፍ ላይ ባይታደሙም፤ በመንፈስ ግን አብረውን እንደሆኑ በመግለጽ ለባህርዳር ከተማ እና የአካባቢዋ ነዋሪዎች የከበረ ሰላምታ እና መልካም የለውጥ ምኞታቸውን በክብር አስተላልፈዋል።

እነሆ ዛሬ! እንደዚህ በደመቀ አብሮነት እና ባሸበረቀው ህዝባዊ ሰልፍ በመካከላችሁ ተገኝቼ ይሄን ንግግር ሳደርግ የተሰማኝ ልባዊ ደስታ እና የፈጠረብኝን ውስጣዊ ፍሰሃ ምንኛ ትልቅ እንደሆነ እኔ ብቻ ነኝ የማውቀው።

ይህ ታሪካዊ ቀን ቀጣዩን ጊዜ የተሻለ እና ክልላችንን እና ሀገራችንን ተመራጭና ተወዳጅ፣ የሰላምና የልማት ምድር ለማድረግ ብሩህ ዕለት የወገገበት ነው። ለዚህ ዕለት ዕውን መሆን በየፈርጁ የታገሉ፣ የደሙና የቆሰሉ፣ ከዚያም አልፎ ክቡር ሕይወታቸውን የሰው በዚህ አደባባይ ክብርና ሞገስ ለእነሱ ይሁን። እናመሰግናለን።

ባህርዳር የክልላችን መናገሻ ከተማ ብቻ ሳትሆን፤ በለሱ ቀንቷቸው ጎራ ያሉ የሃገራችን እና የሌሎች ዓለም ሰዎች በፍቅር የሚማረኩላት፤ ስለውበቷና ስለምቹነቷ ደጋግመው የሚመሰክሩላት፤ የሃገራችን ከተሞች ፈርጥ ነች።

ባህርዳር - ጣናን ተንተርሳ፣ ጊዮንን እንደመቀነቷ አገልድማ ታላላቅ ጥበቦችን በማህፀኗ ያቀፈች ድንቅ ሃብታችን ነች። አሁን. . .አሁን! በሃገር አቀፍ ደረጃ የዘመናዊነትና የብልፅግና ማሳያ ምልክት ከሆኑ ውብ ከተሞች መካከል አንዷ ባህርዳራችን ነች። እንኳን በዚች ውብ ከተማ በሚካሄደው ደማቅ ህዝባዊ ሰልፍ ላይ በጋራ ለመታደም አበቃችሁ፤ አበቃን።

ይህ ትዕይንት፣ የለውጥ ጥማት፣ የዴሞክራሲና የሠላም ፍላጐት ብቻ አይደለም። ኃይልም ነው። ጉልበትም ነው። ሁሉንም ዕውን የሚያደርግ አቅም ነው። ዛሬ እዚህ ፊት ለፊታችሁ ቆሜ በአይበገሬነትና በተስፋ የሚደልቀው ልባችን ዓለት ሲያንቀጠቅጥ፣ ድህነትን ሲንጥ ይሠማኛል። ለዓለም ሁሉም ይሰማል።

ይህ አስደማሚ የጥምረታችን ኃይል የትኛውንም መሰናክል ገርስሶ፣ እንቅፋቶችን ሁሉ አፍርሶ ድህነትና ኋላቀርነትን ታሪክ እንደሚያደርግ አልጠራጠርም። ይህ እንዳለላ ሙዳይ፣ እንደ ህብር ሙካሽ የተንቆጠቆጠ ውበታችን የኢትዮጵያዊነት ፈርጥ ሆንነ፤ ሕዝቦቿን በውበት ሠድረንና ደምረን ለሀገራችን ድምቀት እንደምንሆን ይሄው ያየን ሁሉ ይመሰክራል። አብረን ቆመን አንጀታችን እንደክራር፣ ልባችን እንደከበሮ ተዋህዶ እየፈጠረ ያለው ዜማ ልዩ ኀብረ ዝማሬ ነው። ለሁሉም የሚጥም፣ ሁሉም የሚሰማው፣ ሰሞቶ የሚያበቃው ብቻ ሳይሆን አብሮ የሚደመርበት የፍቅር ቅኝት ነው። ፍቅራችን ሁሉንም ያሸንፋል።

የዛሬው የምስጋናና የድጋፍ ትዕይንት እያደር በየፈርጁ የሚገለጥ የአደራ ጥራዝ የብርታት ስንቅ ነው። አደራው የሁሉም፤ አቅሙም የጋራ ነው። ይህን ለውጥ ከዳር ለማድረስ ስንበረታ እንደዛሬው ተመሰጋግነን፣ ስንሰንፍ ተወቃቅሰን፣ ተግሳፃችሁን ሰምተን ልንታረምና ልናገለግላችሁ ቃል የምንገባበት መድረክም ነው።

በዘመን ቅብብሎሽ አያቶቻችን እና አባቶቻችን . . . በአገር ፍቅር የነደደው ነፍስ፤ በነፃነት ጥማት የተሞላው መንፈስ፤ ለችግር የማይንበረከክ ነፃና ኩሩ ህዝብ፤ በፈተናዎች ፊት ፀንታ ሳትበገር የምትቆይ ሃገር አቆይተውናል።

ገና ከጥንቱ! አገርና ህዝብ ሲደፈር "ከራስ በላይ ንፋስ!" የሚል አስተሳሰብን አሽቀንጥረው "ከራስ በላይ ሃገር!" መኖሩን በታላቅ ጀግንነት ወድቀው፤ ተዋድቀው ክብሯን የጠበቀች እና ነፃነቷን ያስጠበቀች ሃገር በአደራ አውርሰውናል።

በቀደሙት የታፈረችውን ሃገር፤ በእኛ ደግሞ . . . የለውጥ ጉዟችን ፈተና ቢበዛውም ሃገራችን ከስኬት ማማ ላይ እንድትታይ በቁጭት እና በስስት ለውጥን በምኞት ሳይሆን በተግባር ለማምጣት የምንታትርበት ምዕራፍ ላይ እንገኛለን።

እነሆ ዛሬ! ያለማንም ቀስቃሽ እና ጎትጓች በገዛ ፍቃዳችን በዚህ ታላቅ ስቴዲየም የተገናኘነው በተጀመረው ሃገራዊ አዲስ የለውጥ ስሜት አጋርነታችንን ለመግለፅና ይኸው ለውጥ በክልላችን ግለቱን ጠብቆ እንዲቀጥል ባለቤትነታችንን ለማሳየት ነው።

ባለፉት ዓመታት በአገር ደረጃም ሆነ በክልላችን ለለውጥ መነሻ የሆኑ ስራዎች ተመዝግበዋል። ነገር ግን ከሚጠበቀው ለውጥ አኳያ የሰራነው ትንሽ፤ የወቃነው ደግሞ ዕፍኝ እንደማይሞላ እንገነዘባለን።

ዛሬ የሰጣችሁን ድጋፍ እና የለገሳችሁን ምስጋና የከረሙ ችግሮችን በሙሉ ጠራርገን ስላስወገድን እንዳልሆነ በሚገባ እንረዳለን። ዋናው ነገር ጅምር የለውጥ አያያዛችን "የሚያጠግብ እንጀራ ከምጣዱ ያስታውቃል!" የሚል መነሻ መሆኑን አንዘነጋም።

ለውጡን በሚጠበቀው ከፍታ ለማስቀጠል በየደረጃው ያለን መሪዎች ካለፈው ጉድለታችን ተምረን ቃላችንን ለማደስና ህዝባችንን ለመካስ ከፊታችሁ ቆመናል። ንቅናቄው ጥቂቶች የሚዘውሩት፤ ብዙዎች የሚታዘቡት ሳይሆን ሁሉም በባለቤትነት ሊተውንበት የሚገባ ነው።

በዚህ መስተጋብር መሪዎች ስናጠፋ እየተቆነጠጥን፤ በጎ ስንሰራ እየተበረታታን እንድንቀጥል ዛሬ ብቻ ሳይሆን ሁሌም ከጎናችን ታስፈልጉናላችሁ።

ህዝቡ ባልተሸበበ አዕምሮ በነፃነትና በሃላፊነት መንፈስ ድጋፍና ተቃውሞውን የመግለፅ ባህሉ መጠናከር አለበት።

ህዝቡ እንደ ንስር ዓይን ችግሮችን ነቅሶ የሚያወጣበት እና እንደ ዶ/ር አዲስ አለማየሁ የተባ ብዕሩ ስንዴውን ከእንክርዳዱ የሚለይበት አቅሙን ከመቼውም ጊዜ በላይ በእጅጉ እንሻለን።

በፓለቲካ አስተሳሰባችን እዚህ ወይንም እዚያ ልንቆም እንችላለን። የአንደኛው ወይም የሌላኛው አስተሳሰብ አራማጅ ልንሆን አንችላለን። የ”እኔ ሃሳብ የተሻለ ነው፣ የበለጠ ይጠቅማል“ ብለንም ልንፎካከርም እንችላለን። መሠረታዊው ጉዳይ ሁላችንም ለዚህች ሀገር ጥቅምና የተሻለ ነገር ፍለጋ የተሰማራን መሆናችን ነው፤ እርግጠኝነትና ልባዊነት የሚያስፈልገው እዚህ ላይ ነው።

ብዕራችሁ የተባ፣ አዕምሯችሁ የሰላ እንዲሁም ተሳትፏችሁ ደግሞ የነቃ መሆን ዘመኑ ራሱ ይጠይቃል። መንግስት ይሄን ድባብ እንዲፈጠር አቅሙ የፈቀደውን ጠጠር መወርወር እንጂ የዜጎች ባላጋራና የዲሞክራሲ ስርዓት ደግሞ ደንቀራ መሆን አይገባውም። ይሄ ያፈጀበት አካሄድ ነው።

በምንገነባው ስርዓት በዴሞክራሲ ግንባታ እና በሰብዓዊ መብት አያያዝ ያለፉትን ስርዓቶች መርገምና መውቀሳችን ሳያንስ በዚህ ዘመንም አሳፋሪና አሳዛኝ ድርጊቶች ተፈፅሟዋል። ብዙ ዋጋም አስከፍለውናል።

ከዚህ በኋላ ፀረ-ዴሞክራሲ በቃ ብለናል፤ እያንዳንዱን ድርጊታችንና ስራችንን በንቃት ተከታታሉ። አካሄዳችንና ሁኔታችን ከዴሞክራሲ ያፈነገጠና የዜጎችን መብት የሚጋፋ ሆኖ በተገኘበት ጊዜ ሁሉ ልትታገሉን እና አደብ ልታስገዙን ይገባል።

በዚህ አያያዝ ኢትዮጵያውያን በነፃ አገራቸው፣ በነፃነት የሚያስቡባት፣ በነፃነት የሚፅፉባት፣ ያለ ገደብ የሚመረጡባትና የሚመርጡባት፣ የዴሞክራሲና የፍትህ ስርዓትን የሚመሩና የሚያስተባብሩ የጋራ ተቋማት የተገነቡቧት፤ ዴሞክራሲያዊ አገር ባለቤት ይሆናሉ።

ይህ የህዝብ ጎርፍ፣ ሚሊዮኖች ያላንዳች ልዩነት በተባበረና ከፍ ባለ ድምፅ እየዘመሩለት ያለውን ኢትዮጵያን የዳበረና የተረጋጋ ዴሞክራሲ ባለቤት የሆነች አገር የማድረግ ጉዞ ነው።

ነገር ግን ዕዚህ ላይ ሊጤን የሚገባው አንድ ታላቅ ቁም ነገር አለ። ዲሞክራሲ እንደፈለግን እንድንሮጥ እንደሚያስችለን፤ ሁሉ ልጓምንም ያበጃል። ልጓሙ የየግል ሩጫችንን በህግ ጥበቃ የተበጀላቸው የሌሎች የዜጎችን መብቶች እንዳይጋፋ ሲባል የተበጀ ነው። እናም የዲሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ነፃነትንና ሃላፊነትን በሚዛኑ ያያዘ መሆን ይገባዋል።

ፍቅራችንና አብሮ የመኖር ዕሴታችን ዕንዲሁ በምስጋና ቀንና በሰላሙ ጊዜ ብቻ የምናሳያቸው ሳይሆኑ በችግርና በፈታኝ ወቅትም ቢሆን ፀንተው የሚቆዩ ሃብቶች ናቸው። በዚህ የአብሮነትና የአካታችነት ባህሪያችንን የሚሸረሸሩ አዝማሚያዎችን በጽናት ማውገዝ ይጠይቀናል።

የአማራ ክልል ህዝብ በአገራችን ቀደምት የገናናነት ታሪክ የበኩሉን ወሳኝ ሚና የተጫወተ ባለታሪክና ኩሩ ህዝብ ነው። አለመታደል ሆኖ ያ! የገናናነት አገራዊ ቁመና ተቀይሮ የከፋ ድህነትና ኋላቀርነት ቸነፈር ውስጥ ብዙ ዋጋ የከፈለ ነው። የአማራ ብሄር በታሪክ፣ በባህልና በቋንቋ እንዲሁም በሌሎች እሴቶች በአገር ግንባታ ሂደት ትልቅ ቦታ ያለው ነው።

ይህ በእንዲህ እንዳለ ባለፉት ስርዓቶች ጥቂቶች ከሌሎች አካላት ጋር በጥቅም ተሳስረው በፈፀሙት ስህተት፤ በአማራው ላይ በተካሄደ የተሳሳተ አስተምህሮ ሰፊው የአማራ ህዝብ በሌሎች ህዝቦች በዳይ፣ ዕዳ ከፋይና የተለየ ተጠቃሚ መስሎ እንዲታይ አድርጎታል። በዚህ ብዙ መፈናቀል፤ ተጠርጣሪ እና ለሌሎች ችግሮች እንዲጋለጥ ሆኗል።

ከዚህ አኳያ የነበሩ ስህተቶችን በማረም የብሄራችንን እና የሃገራችንን ክብር ተመልሶ ገናናነታችንን ለማረጋገጥ መረባረብ ይገባናል። "ትልቅ ነበርን፤ ትልቅም እንሆናለን!" ይለዋል እንዲህ ነው።

ይህን ታላቅ ክልላዊና አገራዊ ራዕይ እውን ለማድረግ መሪ ድርጅቱ ብአዴን/ኢህአዴግ ላስመዘገባቸው ጅምር ስራዎች እንደሚመሰገን ሁሉ ላጠፋውና ላጎደለው ሃላፊነቱን ይወስዳል።

አሁን የተጀመረው የለውጥ ማዕበል ካለፈው ጉድለት ተምሮ በፅናት መጓዝን ይጠይቃል። ይህን የለውጥ ማዕበል በሙሉ ልብ ተቀብሎ ድርሻን መወጣት የግድ ይላል። ከዚህ ውጭ በእኔ አውቅልሃለሁ ፈሊጥ መንታ መንገድ መወጠን አይቻልም። መፍትሄው የህዝብን የለውጥ ፍላጎት አድምጦ ከእሱ ጋር በመሰለፍ ለውጡን በትክክለኛ አቅጣጫ መምራት ብቻ ነው።

ኢትዮጵያ አንዳንዶቻችን የቅንጦት ህይወት የምንገፋባት እና እንዳሻችን የምንፈነጭባት፤ ሌሎቻችን ደግሞ ባይተዋር የምንሆንባት ሀገር መሆን የለባትም። እናም በእናት አገርና በጋራ ጎጇችን በእኩልንትና በፍቅር እንኖራለን።

አገራችን በተያያዘችው የለውጥ መንፈስ አስቀድመው ለተፈፀሙ እኩይ ታሪኮች ዳግም እንዳይፈፀሙ ትምህርት ወስደንባቸው፤ አዲስ ታሪክ ለመስራት ደግሞ የተለኮሰውን መነሳሳት ሂደቱን በአግባቡ ልንመራውና ልንገራው ይገባል።

በቅርቡ በመዲናችን አዲሳ አበባ በንፁሃን ዜጎቻችን ላይ የደረሰው ጉዳት በአገራችን የሚደረገው የዴሞክራሲ ስርዓት ምንም እንኳን በወሳኝነት በፍጥነት መጓዝ እንደሚቻል ከወዲሁ አፋችን ሞልተን ለመናገር ቢያስችለንም ሂደቱ የአልጋ ባልጋ ጉዞ እንደማይሆን ፍንትው አድርጎ የሚያሳይ ክስተት ነው።

በዚህ አጋጣሚ እኔና ባልደረቦቼ ክልላችንና ኢትዮጵያን የተረጋጋና የዳበረ ዴሞክራሲ ባለቤት የማድረግ የቤት ስራን ዳር ለማድረስ ከህዝባችን ጋር በመሆን በፅናት እንደምንዘልቅ ላረጋግጥላችሁ እወዳለሁ።

በታሪካችን አንዳችን በሌላችን ላይ ተነስተናል። ሲከፍም ቃታ ስበን አንዳችን የሌላችንን አካል አቁስለናል። አልያም አጉድለናል። ምንም እንኳ ትናንት የተከሰቱ መጥፎ ታሪኮችን መዘንጋት ሰዋዊው የማስታወስ ችሎታችን የማይፈቅድልን ቢሆንም ለወደፊት የጋራ ጥቅምና ጉዞ ሲባል ሆን ተብሎ እኩይ ትዝታዎችን መቀየር በእጅጉ ያስፈልጋል።

እናም እንደዚህ ዓይነቱን ቅስቀሳና ውትወታ የሚያስተላልፉት ሃይሎች ጆሮ ዳባ ልበስ ልንላቸው ይገባል። አማራ የሚታወቅበት መለያ ባህሪው አካታችነቱና አቃፊነቱ ነው። አማራ የሚታወቅበትን እሴቶችን ጠብቆ መቀጠል የሚገባው ሲሆን፤ ተናጥል ችግሮች እንኳ ቢያጋጥሙ ህዝብን እና ግለሰብን ለይቶ እንዲታረም እና እንዲስተካከል ማድረግ እንደሚገባ፤ ከዚህ ውጭ የጥላቻ፣ የዘረኝነት፣ የበቀል እና የጎጠኝነት አረሞችን በማስወገድ ብቻ ሳይሆን ይህው ለትውልድ እንዳይተላለፍ ተግተን መስራት ይኖርብናል።

እኛ ኢትዮጵያውያን ከይቅር ባይነት በላይ የምናከብረውና ዋጋ የምንሰጠው ነገር የለም። “ ይቅርታ” በልባችንም በመሐላችንም ትልቅ ቦታ አለው። ዛሬም ይህንን ቦታውን ልናሰፋ መሐላችንም ይቅርታ እርስት እንዲሆን እንውደድ። ይቅር አንባባል። ለየአካባቢው የሚታየውን ግጭትና መቃቃር ከመሠረቱ አክስመን በይቅርታችን እንደይመለስ አድርገን እንጠበው።

ኢትዮጵያውያን ነንና ይሄ አያቅተንም። በትንሹም ሆነ በትልቁ ሆድ መባባስ ቀርቶ አንዳችን ለሌሎችን የፍቅር ማዕድና አውድ እንሁን።

በሚሊዮኖች ተደግፎ የተቀጣጠለው ለውጥ ወደ ኋላ መመለስ ቀርቶ ማዝገምን አይታገስም። መፍትሄው በህዝብ ባለቤትነት እና በወጣቱ መሪነት በፍጥነት መጓዝ ነው። ካሁን በኋላ ሃገራችን ለሁሉም በእኩል የተመቸች፤ ዜጎቿ እኩል የሚደመጡባት፤ እኩል የሚሳተፉባት የጋራ ማዕዳችን ሆና ትቀጥላለች። ለዚህ እውን መሆን በፅናት መታገል ይኖርብናል።

ከዚህ አኳያ የስራ ባልደረቦቼ እና እኔ ቴዎድሮስና ገብርዬ ሆነን ተጋግዘን፤ አለቃ እና ምንዝር ሳንሆን፤ የአንድ አላማ ተሰላፊዎች በመሆን ህዝባችንን የሰላም፤ የዴሞክራሲ እና የልማት ፍላጎት ዳር እናደርሳለን።

በዚህ አጋጣሚ አበክሬ ላነሳ የሚገባ አንድ ቁም ነገር አለ። በኛ በአመራሮቹ በኩል፤ ህዝቡን በሚፈለገው ደረጃ ያለማዳመጥ፤ ያለማቀፍ፤ ያለማቅረብ፤ እና ለያይቶ ማየት ችግር አለ። እንዲሁም በምሁራኑ እና በወጣቱ እንዲሁም ባለሃብቱ የዳር ተመልካች የመሆን እና በራስ አገር ላይ ባይትርነቱ ተስተውሏል።

ክልላችንም ሆነ ሃገራችን ወደ ፊት ሊገሰግሱ የሚችሉት እና በለውጡ ዘልቀው ተጠቃሚነታቸውን የሚያረጋግጡት እኛ አመራሮቹ ችግራችንን ቀርፈን አቃፊና ደጋፊ ስንሆን ወጣቱ፤ ምሁሩ እና ባለሃብቱ ደግሞ ባይተዋርነቱን ትቶ የሃገሬ እና የክልሌ ጉዳይ ያገባኛል ደግሞም አመራሮቹ፤ የኔ ክፋይ ናቸው ብሎ አብሮ ሲሳተፍ እና ወደ ተግባራዊ እንቅስቃሴ ሲገባ ብቻ ነው።

እርግጠኛ ሆኜ የምነግራችሁ ከእንግዲህ እንደማንሳሳት ሳይሆን እንደምናደምጣችሁ፣ እንደከዚህ ቀደሙ ዘግይተን ሳይሆን ፈጥነን እንደምንመልስላችሁ እና በዚያው ፍጥነት እንደምንስተካከል ነው። ምስጋናችሁን ብቻ ሳይሆን ተግሳፃችሁን ከልብ ሰምተን ፈጥነን ለመታረም ዝግጁ መሆናችንን በልበ ሙሉነት አረጋግጥላችኋለሁ።

በተቻለን መጠን ባለን አቅም ሁሉ በህዝባዊነት እንደምናገለግላችሁ፣ ደከመን ሠለቸን ሳንል ሃላፊነታችንን ለመወጣት ጥረት እንደምናደርግ ላረጋግጥላችሁ እወዳለሁ።

"የተናገሩት ከሚጠፋ የወለዱት ይጥፋ!" በሚል ዕሴት ታንፆ ለቃሉና ለማዕተቡ ታማኝና ሟች ከሆነ የታላቁ ህዝባችን ክፋዮች ነንና ይህንን ቃል እንጠብቃለን።

በዚህ አጋጣሚ ብአዴን በአማራው ስም በውጭ አገር የተደራጁና ለሱ የሚታገሉ የፖለቲካ ድርጅች፣የተለያዩ ማህበራዊ የሚዲያ ተቋማት በሰላም ለመንቀሳቀስ እስከወሰኑ ድረስ ወደ ክልላችን መጥተው እንዲቀሳቀሱ ጥሪ እያስተላለፈ እኛም ከግማሽ መንገድ ድረስ ተጉዞ ለህዝባችን ጥቅም መከበር አብሮ ለመስራት ዝግጁ መሆናችንን አረጋግጣለሁ።¾

አቶ ገዱ አንዳርጋቸው

በባህር ዳር በተደረገው የድጋፍ ሰልፍ

 

ከሁሉ በማስቀደም በሚያለያዩንን ጉዳዮች ላይ ጊዜያችንን ማባከኑን ትተን አንድ በሚያደርጉን ጉዳዮች ለመተሳሰር በመፈለግ ቃል ወደምንገባበት የ“መደመር” ቀን ሁላችንም እንኳን አደረሰን!

ሃገራችን ከአመታት የሰላም እጦት በአጭር ጊዜ ውስጥ ወጥታ አንፃራዊ ሰላም የሰፈነባት ናህዝቦቿ አንድ መሆን የጀመሩበት ጊዜ ላይ እንገኛለን። የጥይትድምፅና ለቅሶ ያደነቁራቸው የነበሩ ከተሞቻችን ሰላምንና ፍቅርን ከፍ አድርገው መዘመር ጀምረዋል።

ልጀ እንደወጣ ይቀራል ብለው ሰቀቀን ውስጥ ወድቀው የነበሩ የእናት አንጀቶች በሰላም ማረፍ ጀምረዋል። ይህ ለኛ ለኢትዮጵያዊያን የትናንቱ ገናና ታሪካችንና የነገው ታላቅ ተስፋችን ማስተሳሰሪያና ማረጋገጫ ማህተምነው።

የአማራ ህዝብ ከሌሎች የኢትዮጵያ ህዝቦች ጋር አንድ በመሆን በሀገራችን ጠንካራ መንግስት እንዲመሰረት፣ ታሪክ እንዳይበላሽና ነፃነት እንዳይገፈፍ ጥንትም ጀምሮ የሰራና የታገለ ጀግና እና ባለ ታሪክ ህዝብነው። የእንግሊዝ ወራሪ ኃይልን ፊት ለፊት ከመጋፈጥ እስከ አድዋ ድል፣ ከኢትዩጵያ አንድነት ምስረታ እሰከ አፍሪካ ዉህደት ጥሪና ገቢር ድርስና ከዚህም በኋላ ሃገራዊና አህጉራዊም ገድል እየፈፀመ የመጣ ህዝብ ነው።

የኢትዮጵያ ታሪክና ትውፊት ከትውልድ ትውልድ ሳይዛባ እንዲተላለፍ ከመፃፍ ከትቶ እስከ ማስቀመጥ የዘለ ቀሃገራዊ ውለታ ያለው ህዝብ፣ ለተራበ ፈትፍቶ አጉራሽ፣ ለተጠማ ቀድቶ የማይበቃው፣ ለወደደው ማርና ለጠላውም ኮሶነው።

ዛሬ በሀገራችን እየታየ ያለው የለውጥ ተሰፋ ደርዝ ያለው እንዲሆን የአማራ ህዝብ ተደራጅቶም ሆነ በተናጠል የሰራው ታሪክ ዘመን የማይሽረው ነው ብለን ብንናገር መታበይ አይሆንም። ሁላችሁንም የዚህ አንጸባራቂ ታሪክ ባለቤቶች ናችሁና እንኳን ደስ አላችሁ እንኳን ደስ አለን ስላችሁ በኩራት ነው።

ሃገራችን ከወደቀችበት እንደገና መነሳት ጀመረች እንጅ ገና በቅጡ መራመድ አልተቻላትም። አሁን ያሳየነውን አንድነትና ፍቅር በማይናወጥ መሰረት ላይ አንፀንየኔን፣ የእናንተን፣ የልጆቻችንንና የልጅልጆቻችንን እድል ተሰፋ እንዲበቅልበት ማድረግ ካልቻልን በዚህ የታሪክ ምዕራፍ ውስጥ በአጋጣሚ መገኘታችን ትርጉም የለውም። በስራችን ውጤት ዛሬ እንዲህ አምሮብንና ተውበን ብንታይም ልንሻገራቸው የሚገባ በርካታ ወንዞችና ሰበርባራ መንገዶች ከፊት ለፊታችን ይጠብቁናል። እንደጀመርነው ሁሉንም እናልፋቸዋለን። ግን ስንቅያስፈልገናል። ስንቁም ፍቅር፣ አንድነትና ተሰፋ ነው። አንድስንሆን የማይደፈሩ መስለው ይታዩ የነበሩ ተራሮችን መናድ እንደምንችል ተምረናል። ስንደመር ብረትን ማቅለጥ እንደምንችል አይተናል። ስንፋቀር በሃገራችን የይቅርታና የምህረት ዝናብ እንደሚዘንብ ተገንዝበናል።

ዛሬ ሃገራችን ደስታና ፍቅር ብቻ የሚታይበት ሃገር አይደለችም። የኛ አንድ መሆን የእግር እሳት የሆነባቸው ያልታደሰውና የአሮጌው ዘመን ቁማርተኞች ከእግር እግራችን ስር እየተከተሉ መንገዳችንን በስጋት ድርሊ ያሰናክሉት ሲሞክሩ እየታዩ ነው። ሰላም የዋለው ሃገር ሰላም እንዳያድር፣ ለሰላም የተዘረጉ እጆች ሳይጨባበጡ እንዲቆረጡ ስራ ውለቴ ብለው የሚደክሙ ሽንፈትን ያልተቀበሉ ደካሞች ከዙሪያችን አልጠፋም። ድል መንሻው ዘዴ የታወቀና የተለየ ነው። አንድ መሆን፤ መደመር።ተለያይተን ሞክረነዋል አልተሳካልንም። ተነቃቅፈንና ተጠላልፈን አይተነዋል፤ የጅብ እራት ነው የሆን። እናም አንድነትን በጥብቅ እንሻለን። አንድነት የሚጀምረው ከቤት ነው። የአማራ ህዝብ ራሱ አንድ ሳይሆን ኢትዩጵያን ያህል ትልቅ ሃገር አንድ ለማድረግ አይቻለውም።

ከደጃችን ያለውን ቆሻሻ ሳናፀዳ ንፁህና የፀዳ ችሃገር መፍጠር ያዳግተናል። ረጅሙን የፍቅርና የአንድነት ጉዞ ከአጠገባችን ካሉ ቤተሰቦቻችን ጋር እጅ ለእጅ በመያያዝና በመተሳሰብ እንጀምረው።

ለክልላችን ወጣቶች

የክልላችን ህዝብ አፍላጉልበትን ከእውቀትና ከአስተዋይነት ጋር የተላበሰ ቆፍጣና ወጣት ይፈልጋል። እርምጃችሁ ሁሉ በማስተዋልና በጥበብ እንዲሆን፣ ሰሜትንትታችሁ ምክንያታዊነትን፣ ጥላቻን ትታችሁ ፍቅርን፣ መገፋፋትን ትታችሁ አንተ ትብስ አንተ ትብስ መባባልን ሂወታችሁ በማድረግ በክልላችሁ የተጀመረው አንድነትና ተሰፋ እንዳይጨናገፍ ትታደጉት ዘንድ ጥሪ አቀርብላችኋለሁ። አሁን አንገት የምንደፋበትና ሙሾ እምናዎርድበት ወቅት አይደለም። ያለፈውን ረስተን በአዲስ ተስፋና ጥንካሬ ወደፊት እንራመድ።

ለሀይማኖት አባቶች

በሀገራችን ወንድማማችነትና እህትማማችነት መሰረቱ ሰፍቶ ታላቅ ታናሹን በተለመደው ኢትዩጵያዊ ባህል እንዲያከብርና ሰላም በሀገራችን እንዲበዛ ተግታችሁ ታስተምሩን ዘንድ እንደልጅነቴ በክብር እጠይቃችኃለሁ።

ለጥበብ ሰዎች

ትናንት ለሰላምና ለሰው ልጅ ክብር ያልተመለሰው ብዕራችሁ ዛሬም በምድራችን ፍቅርና መተሳሰብ እንዲሰፍን፣ ዲሞክራሲ እንዲስፋፋ፣ የተተባተበው እንዲፍታታ፣ የደበዘዘው እንዲተባ፣ የአማራ ህዝብ ታሪክ እንዳይዛባና እንዳይጠፋ አቅማችሁና የሞያ ደረጃችሁ በሚፈቅደው መጠን ሁሉ ከጐናችን ቁማችሁ እንድንተጋገዝና እንድንደመር ጥሪ አቀርብላችኋለሁ።

ለተፎካካሪ ፖርቲዎች

በሀገር ውስጥም ሆነ ከሀገር ውጭ የአማራን ህዝብ በልማትና በዲሞክራሲ ተጠቃሚ እና ደርጋለን የሚል ሀሳብ ይዛችሁ የምትሰሩ ተፎካካሪ ፖርቲዎች እንዳላችሁ እናውቃለን።

አላማችሁና ፍላጐታችሁ የአማራን ህዝብ መጥቀም እስከሆነ ድረስ በፍቅር አይን እንመለከታችኃለን። ከፊታችን ያሉ ትልልቅ ችግሮችን ተራርቀን በመቆምልና ሽንፋቸው እንደማንችል ተገንዝባችሁ ከሀገርውጪ ያላችሁተመልሳችሁ፣ ኢትዩጵያ ውስጥ ያላችሁም ተቀራርበን አንድ በሚያደርጉን ነገሮች ላይ ተመስርተን አብረን እንስራ።

አንድ የሚያደርጉን ነገሮች ሁል ቆመሳፍርት የላቸውምና በሚያለያዩን ጥቃቅን ነገሮች ጊዜ ሳንጨርስ በጊዜ ወደቤታችን እንሰብስብ።

ለአጐራባች ክልል ህዝቦችና ድርጅቶች

ዘመኑ አለም አንድ እየሆነ ያለበት ነው። አንዳችን የጐደለንን ሌላችን ሞልተን፣ የአንዱ ቤት የሌላውም ጭምር ይሆን ዘንድ ማንነታችን ጠብቀንና አክብረን በመካከላችን በማይገባ ያጠርነውን አጥር በጊዜ አፍርሠን በጋራና በመተባበር በመስራት አንዲት ጠንካራ ኢትዩጵያን ለመገንባት እንረባረብ።

ለክልላችንና ለፌዴራል መንግስት የፀጥታ አባላት

ለክልላችንና ለመላ ኢትዩጵያ ሰላምና አንድነት እየከፈላችሁት ያላችሁትን ዋጋ አሳምሬ እገነዘባለሁ። ሀገራችን ሰላሟ የተጠበቀና እኩልነት የተረጋገጠባት ሆና እስክትዘልቅ ክንዳችሁ ሳይዝል፣ ነፃና ገለልተኛ ሆናችሁ የሰላም ምልክትነታችሁን መሰረት እንድታስይዙት አሳስባችኋለሁ። ኢትዩጵያ ንፁህ ደም ሳይሆን ፍቅር የሚፈስባት፣ በስጋት ሳይሆን በራስ መተማመን የተሞሉ ልጆች ያሏት ሃገር ትሆን ዘንድ የጀመራችሁትን ጀግንነት አበርትታችሁ እንድትቀጥሉ ጥሪ ቀርቦላችኋል።

ለሚዲያ ባለሞየወችና ጦማሪያን

በሃገራችን እየታየ ያለው ተስፋ ፍሬ ያፈራ ዘንድ እውነቱን ለህዝቡ አሳዉቁ። ከመላው ህዝባችን የምንደብቀው ጉዳይ የለንም። ስኬታችንም ሆነው ድቀታችን በልክ በልኩ እየተቆጠ ለህዝብ ጀሮ ይደርስ ዘንድ ሙያችሁ የሚጠይቀውን ዲስፕሊን ጠብቃችሁ ስሩ። ማዛባት ሁላችንንም ያጠፋናልና አሁን እንደጀመራችሁት ጣፋጭ ስኬትን ከመራራ እውነት ጋር አጣጥማችሁ ተራመዱ።

መጪው ጊዜ የአማራ ህዝብ የሚሰደድበት፣ የሚሸማቀቅበት፣ አንገት የሚደፋበት ሳይሆን በኩራት ቀና ብሎ የሚሄድበትና ከቁዘማ የሚላቀቅበት ነው። ከእንግዲህ ሆድ ሊብሰን አይገባም። ከእንግዲህ የትናነቱን እያነሳን መብሰልሰል ሳይሆን አንገታችንን ቀና አድረገን በተስፋ ወደፊት መራመድ ነው መለያችን። ሁላችንም ለዚህ እውን መሆን ተቀራርበንና ተደምረን እንስራ።¾

በይርጋ አበበ

የኢህአዴግ አስተዳደር በአገሪቱ ለተነሱ ግጭቶችና ብጥብጦች ራሱን ተጠያቂ ማድረጉን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ዶክተር አብይ አህመድ ተናግረዋል። ቀደም ባሉት ዓመታት አሸባሪ ተብለው በፓርላማ የተፈረጁ ድርጅቶችን በተመለከተም ዶክተር አብይ ሲናገሩ፤ ለስልጣን ማስጠበቂያ ወይም ስልጣን ለማግኘት ሲባል ሰውን መግደል፣ ማሰር እና ማሰቃየት የእኛ ተግባር ነው በማለት ነበር ኢህአዴግ እንጂ ሌላ አሸባሪ ድርጅት እንደሌለ የገለጹት። ይህን ተከትሎም በጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚመራው የሚኒስትሮች ምክር ቤት ባሳለፍነው ቅዳሜ ባደረገው መደበኛ ስብሰባ አርበኞች ግንቦት ሰባት፣ ኦነግ እና ኦብነግ የተባሉ ድርጅቶችን በሽብርተኝነት የሚያስፈርጃቸው አዋጅ እንዲነሳ ወስኖ ለፓርላማ አቅርቧል።

በሌላ በኩል ደግሞ የጸረ ሽብርተኝነት አዋጅን ጨምሮ በኢትዮጵያ የፖለቲካ ብዝሃነትን እና የዴሞክራሲ ምህዳሩን ያጠበቡ ናቸው የተባሉ የተወሰኑ የህግ ክፍሎችን ለማሻሻል በጠቅላይ አቃቤ ህግ አስተባባሪነት ኮሚቴ ተዋቅሯል። በሽብርተኝነት ስም በተፈረጁ ድርጅቶች አባልነትና ግንኙነት አላቸው ተብለው የታሰሩ ሰዎች እስካሁን ሲፈቱ ቢቆይም ገና ያልተፈቱ መኖራቸውን ተከትሎ አዋጁ ከተሻሻለ እና አሸባሪ ተብለው የተፈረጁ ድርጅቶችም ፍረጃው ከተነሳላቸው የታሰሩት የማይፈቱበት ምክንያት የለም ሲሉ ምሁራንና ፖለቲከኞች ይናገራሉ። በጸረ ሽብርተኝነት አዋጁ ዙሪያ ከምሁራን እና ፖለቲከኞች ጋር ያደረግነውን ቃለ ምልልስ ለአንባቢያን በሚመች መልኩ ከዚህ በታች አቅርበነዋል።

…….

 

የጸረ ሽብር አዋጁ እና የምሁራን እይታ

 

የህግ ባለሙያውና በሽብርተኝነት ወንጄል የተከሰሱ ፖለቲከኞችን ጉዳይ ጥብቅና በመቆም የሚታወቁት አቶ ተማም አባቡልጉ ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው የጸረ ሽብርተኝነት አዋጁ ሙሉ በሙሉ መወገድ አለበት ብለው ያምናሉ። የህግ ባለሙያው ሃሳባቸውን ሲያቀርቡም ‹‹በሁለት መንገድ አዋጁ መወገድ አለበት። የመጀመሪያው ነገር ኢትዮጵያ በሽብርተኝነት የተጋላጭነት ደረጃዋ ዝቅተኛ ቦታ ላይ የምትቀመጥና የሽብር ስጋት የማያሰጋት ሲሆን፤ በሌላ መልኩ ደግሞ አዋጁ ውስጥ ያሉ አብዛኞቹ ክፍሎች በወንጀለኛ መቅጫ ህጉ ላይም የተካተቱ ናቸው›› ብለዋል። የኢትዮጵያ መንግስት አዋጁን የስልጣን ማስጠበቂያው አድርጎታል ብለው የሚናገሩት አቶ ተማም ‹‹በጸረ ሽብር አዋጁ እኮ የማያስከስስ ነገር የለም። አሁን አንተ ጋዜጠኛ በመሆንህ ብቻ ልትከሰስና ልትታሰርም ትችላለህ። እስካሁን በዚህ አዋጅ የተቀጡትም ሆነ የተከሰሱት ሙሉ በሙሉ ኢትዮጵያዊያን ብቻ እንጂ አሸባሪ ሲቀጣ አላየንም። ይህ ደግሞ የሚያሳይህ በፖለቲካ ልዩነት የሚመጣበትን ሀይል አፍኖ ለመያዝ ገዥው ፓርቲ ያወጣው እንደሆነ ነው›› ብለዋል።

የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ጉባዔ (ኢሰመጉ) ስራ አስፈጻሚ አባል እና የህግ ባለሙያው አቶ አመሃ መኮንን በበኩላቸው ‹‹አዋጁ ሲወጣ አገራችን በተለይ በምስራቅ አፍሪካ ቀጠና የምትገኝ ከመሆኑ አንጻር ለሽብር የተጋለጠች ስለሆነች ህዝቧንና አገሪቱንም ከሽብር ለመጠበቅ በሚል ነው መግቢያው ላይ የተቀመጠው። ሆኖም በተግባር እንደምናየው ከአዋጁ አፈጻጸም ጋር በተያየዘ የተከሰሱ ሰዎችን ጥብቅና በመቆም እንዳየሁት ሙሉ በሙሉ ዓላማውን የሳተ እና አዋጁ በሚወጣበት ወቅት ተፎካካሪ ፓርቲ አባላት እንዲሁም ምሁራን አዋጁ አስፈላጊ አይደለም፣ በኢትዮጵያ ላይ ተጋርጦባታል የተባለውን የሽብር ስጋትም በነበረው መደበኛ ህግ ማስተካከል ይቻላል ብለው ይከራከሩ ነበር። አሁን ያየሁትም የምሁራኑና የፖለቲከኞቹ ስጋት ትክክል እንደነበረ ነው። በእኔ ግምት በአዋጁ ከተከሰሱት ውስጥ 95 በመቶ የሚሆኑት እውነትም ሁላችንም በምንስማማበት ሽብርተኛ ተብለው ሊቀጡና ሊወገዙ የሚገባቸው ሰዎች ሳይሆኑ ይልቁንም ለህዝብ መብት የሚታገሉ፣ የመንግስት አስተዳደር ይስተካከል እና የተለየ የፖለቲካ አስተዳደር ያስፈልጋል ብለው የታገሉ ፖለቲከኞች፣ ጋዜጠኞች እና ጦማሪያን ናቸው። መከሰሳቸውም ብቻ ሳይሆን በማረሚያ ቤት እጅግ አሰቃቂ አያያዝ ይፈጸምባቸው ነበር። አዋጁ ባለፉት ዓመታት መንግስት የተለየ አመለካከት ያላቸውን ዜጎች ለመጨፍለቅ፣ ለማሳደድ፣ ለማፈን እና ለማሸማቀቅ ጥቅም ላይ ካዋላቸው ህጎች አንደኛውና በጣም አደገኛው ነው ብዬ ነው የማየው›› ሲሉ አዋጁ ለምን ዓላማ እንደዋለ ተናግረዋል።

አቶ አመሃ አክለውም ‹‹አዋጁ ሲወጣ አንዳንዶቻችን በቅንነት አይተነው ነበር። አገራችንን ከሽብርተኝነት ለመጠበቅና ለመከላከል ያስፈልጋል ብለን ነበር።›› ሲሉ በወቅቱ የነበራቸውን ስሜት ገልጸዋል። ከዚሁ ጋር አያይዘውም አዋጁ ለዜጎች አፋኝና አሸማቃቂ በመሆኑ ቅድሚያ ተሰጥቶ ሊስተካከል ይገባል የሚል እምነት እንዳላቸው ገልጸው፤ ሊሻሻል ዝግጅት መኖሩንም አድንቀዋል።

‹‹የጸረ ሽብር አዋጁ የፍርሃት ፕሮጄክት ነው›› የሚሉት የቀድሞው የአንድነት ለፍትህና ለዴሞክራሲ ፓርቲ ስራ አስፈጻሚ አባል የነበሩት ፖለቲከኛው ዶክተር ንጋት አስፋው፤ ከአቶ ተማም አባቡልጉ አስተያየት ጋር ይስማማሉ። ዶክተር ንጋት ሃሳባቸውን ሲስብራሩም ‹‹አዋጁ ህዝብን አፍኖ ለመግዛት የታለመ ፕሮጄክት ነው። በአንድ አገር ምንም አይነት የዴሞክራሲዊ መብቶች በሌሉበት ውስጥ አፋኝ አዋጆች ይወጣሉ ከአፋኝ አዋጆች አንዱ ደግሞ ይህ የጸረ ሽብር አዋጅ ነው›› ብለዋል። ምሁሩ አያይዘውም አዋጁን ከመመልከታችን በፊት አዋጁን ያጸደቀውን አካል መመልከት ይበጃል ይላሉ። ‹‹የአገራችንን አጠቃላይ የፖለቲካ ሂደቱን እንመልከት። በእኔ እምነት የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ውስጥ የኢትዮጵያ ህዝብ አልተወከለም ብዬ ነው የማምነው። ምክር ቤቱ የኢህአዴግ ተወካዮች ምክር ቤት እንጂ የኢትዮጵያ ህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መባል የለበትም። አስፈጻሚዎቹም ሆኑ ህግ ተርጓሚው በሙሉ በኢህአዴግ ሰዎች ተይዞና የኢትዮጵያ ህዝብ ከፖለቲካ ውክልና ተገልሎ የሚወሰን ውሳኔ የህዝብን ጥቅም ያስከብራል ብሎ ማሰብ አይቻልም። ስለዚህ ይህ አዋጅም ይህን ህዝብ ረግጦ ለመግዛትና እንደፈለጉት ለማገላበጥ እንዲመቻቸው ካወጧቸው አፋኝ አዋጆች አንዱ ነው›› በማለት አዋጁ አስፈላጊ አይደለም ሲሉ ሃሳባቸውን ሰጥተዋል።

 

 

ጸረ ሽብር አዋጁ ማዕከል ያደረገው ክፍል

የህግ ባለሙያዎቹ አቶ ተማም አባቡልጉም እና አቶ አመሃ መኮንንም ሆኑ ፖለቲከኛው ዶክተር ንጋት አስፋው በጋራ የሚስማሙበት ነጥብ ‹‹ጸረ ሽብር ህጉ የተወሰነ የህዝብ ክፍልን ማዕከል አድርጎ ለማጥቃት ተግባር ላይ ውሏል›› ይላሉ። ከአረና ሊቀመንበሩ አቶ አብርሃ ደስታ እስከ ሙስሊም መፍትሔ አፈላላጊ ኮሚቴዎች ድረስ በሽብርተኝነት የተከሰሱ ሰዎችን ጥብቅና የቆሙት አቶ ተማም አባቡልጉ ሲናገሩ በዚህ አዋጅ ዋጋ የከፈለችው ኢትዮጵያ ናት። በርካታ የፖለቲካ ተሳትፎ ያላቸው ንቁ ምሁራንን፣ ጋዜጠኞችን እና ጦማሪያንን ለማሰር የወጣ አዋጅ በመሆኑ በእነዚህ ዜጎች መታሰር ደግሞ አንደኛ የቤተሰብ አስተዳዳሪዎች በመታሰራቸው ቤተሰብ ዋጋ ከፍሏል፤ አገር እንደ አገር መብቱን ተግባራዊ ለማድረግ የሚፈልግ ምሁርና ንቁ ተሳታፊው ክፍል ሲሸማቀቅ ዋጋ ከፍላለች›› ሲሉ በፀረ ሽብርተኝነት አዋጁ ትኩረት የተደረገባቸውን አካላትና አገር የከፈለችውን ዋጋ ጭምር ገልጸዋል።

ፖለቲከኛው ዶክተር ንጋት በጸረ ሽብር አዋጁ ምክንያት ‹‹ኢትዮጵያ በተለይም የአዲስ አስተሳሰብ ፈላጊው ትውልድ ዋጋ ከፍሏል‹‹ ይላሉ። ‹‹ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ ለምን የታሰረ ይመስልሃል? አንዷለም አራጌስ ለምን ታሰረ? እነዚህንና መሰል የዚህ ዘመን ለውጥ አራማጅ ወጣቶች ለእስር የተዳረጉት በኢህአዴግ የተቀነባበረ የስልጣን ማስጠበቂያ አፋኝ አዋጅ የተነሳ ነው›› ይላሉ። ለዚህ ደግሞ ይላሉ ፖለቲከኛው ዶክተር ንጋት፤ ‹‹ለዚህ ደግሞ ኢህአዴግ አፋኝ፣ ገራፊና አሳሪ ሆኖ ህዝቡንና ንቁ ተሳትፎ የሚያደርጉ ፖለቲከኞችን ባሸበረበት ተግባሩ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ በይፋ ይቅርታ ጠይቀዋል እኮ። ይህ ሁሉ የሆነው ለስልጣን ሲባል የታሰበ እና ዓላማ አድርጎ ሊያጠቃ የተነሳውም ለስርዓቱ አስተዳደር የማይመቹ ሰዎችን ለማጥፋ ነው›› ሲሉ ሃሳባቸውን አቅርበዋል።

 

 

ቀጣይ ጉዞ

በዶክተር ብርሃኑ ነጋ የሚመራው አርበኞች ግንቦት ሰባትም ሆነ ኦነግና ኦብነግ ከሽብርተኝነት መዝገብ እንዲሰረዙ የሚኒስትሮች ምክር ቤት መወሰኑን ተከትሎ በህግ ስርዓቱ መሰረት ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀርቦ ውሳኔ ይሰጥበታል ተብሎ ይጠበቃል። ሆኖም በእነዚህ ድርጅቶች ስም የታሰሩ ፖለቲከኞችና የአገሪቱ ዜጎች አሁንም እስር ቤት መኖራቸው ይነገራል። ጸረ ሽብር አዋጁ ከመነሳቱም ሆነ ከመሻሻሉ በፊት በሽብርተኝነት የታሰሩ ሰዎች ከእስር የተፈቱም ነበሩ። እንደ አቶ አንዳርጋቸው ፅጌ ያሉ የአርበኞች ግንቦት ሰባት አመራር በዶክተር አብይ አህመድ ግብዣ ቤተመንግስት ገብተው የተነጋገሩ ሲሆን ከእስር ለመፈታታቸውም ዶክተር አብይ ስልጣናቸውን ለድርድር አቅርበው እንዳስፈቷቸው ራሳቸው አቶ አንዳርጋቸው ተናግረዋል። ሆኖም አሁንም ድረስ እስር ቤት ውስጥ ያሉ በሽብርተኝነት የተከሰሱ ሰዎች እጣ ፈንታ ምን ሊሆን ይችላል? ስንል ሶስቱንም ምሁራን ጠይቀናቸው ነበር። የታሰሩት በሙሉ መፈታት እንዳለባቸው ተናግረው በዚህ ህግ ምክንያት ዋጋ ለከፈሉ ዜጎች መንግስት የህሊና እና የሞራል ካሳ እንዲከፍል ጠይቀዋል። በስራ ላይ የነበሩ ደግሞ ወደ ስራቸው እንዲመለሱ በተጨማሪም ህጉ ለዜጎች ጥቅም እንጂ ለስልጣን መጠበቂያ እንዳይሆን ተማጽነዋል።

 

 

በምሁራኑ የተነቀፉ የአዋጁ ክፍሎች

ዶክተር ንጋት አስፋው እና አቶ ተማም አባቡልጉ አዋጁ ሙሉ በሙሉ አያስፈልግም ሲሉ አቶ አመሃ መኮንን ግን የአዋጁን መሻሻል የሚደግፉ ምሁር ናቸው፡ ሶስቱም ምሁራን ታዲያ ከአዋጁ ክፍል ውስጥ በተለየ መልኩ ለዜጎች ተስማሚ አለመሆናቸውን የሚናገሩባቸው ክፍሎች በርከት ያሉ ናቸው። በሽብርተኝነት ስለመሰየም እና ሽብርተኛ ተብሎ በተጠረጠረ ሰው ላይ ስለሚወሰድ ናሙና፣ ለፖሊስ መረጃ የመስጠት ግዴታና ፖሊስ ከተጠርጣሪው መረጃ ለመውሰድ የሚጠቀመው ሀይል፣ የምርመራ ጊዜ እና በሽብር ተግባር ስለመሳተፍ የሚሉ አንቀጾች ይገኙበታል።

በምሁራኑ ከተጠቀሱት የአዋጁ ክፍሎች መካከል በተለይ ‹‹መረጃ የመስጠት ግዴታ እና ናሙናዎችን የመስጠት ግዴታ›› የሚሉትን ክፍሎች በትኩረት ተናግረውባቸዋል። አንቀጽ 21 እና 22 ሲሆኑ ከአዋጁ የተጠቀሱትን ቃል በቃል አስፍረናቸዋል።

 

 

ናሙናዎችን የመስጠት ግዴታ (አንቀጽ 21)

ፖሊስ በሽብርተኝነት ወንጀል ጉዳይ የተጠረጠረ ሰው የእጅ ጽሑፉን፣ የጣት አሻራውን ፣ ፎቶግራፉን፣ የፀጉሩን፣ የድምፁን፣ የደሙን፣ የምራቁንና ሌሎች በሰውነቱ የሚገኙ ፈሳሽ ነገሮችን ናሙናዎች ለምርመራ እንዲሰጥ ሊያዝ ይችላል። በተጨማሪም የህክምና ምርመራ እንዲያደርግ ሊያዝ ይችላል። ተጠርጣሪው ለምርመራው ፈቃደኛ ካልሆነ ፖሊስ አስፈላጊ የሆነ ተመጣጣኝ ሀይል ተጠቅሞ ከተጠርጣሪው ናሙና ሊወስድ ይችላል።

 

መረጃ የመስጠት ግዴታ (አንቀጽ 22)

የሽብርተኝነት ወንጀል ለመከላከል ወይም ምርመራ ለማከናወን ፖሊስ ለምርመራው የሚረዳው መሆኑን በሚገባ የሚያምንበትን መረጃ ወይም ማስረጃ ከማናቸውም የመንግሥት መሥሪያ ቤት፣ ባለሥልጣን፣ ባንክ፣ የግል ድርጅት ወይም ግለሰብ እንዲሰጠው ሊጠይቅ ይችላል። መረጃ ወይም ማስረጃ የተጠየቀው ወገን መረጃውን ወይም ማስረጃውን የመስጠት ግዴታ አለበት።

“የሰላም ድርድሩ በኢትዮጵያ የፖለቲካ ሽግግር ላይ

አሉታዊ ሚና እንዳይኖረው ጥንቃቄ ያስፈልጋል”

ፕሮፌሰር መድሃኔ ታደሰ

 

የኢትዮጵያ መንግስት በኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት መነሻ የተላለፈውን የአልጀርስ ስምምነት አለምንም ቅድመ ሁኔታ ለመተግበር መወሰኑን ይፋ አድርጓል። የኤርትራ መንግስት በበኩሉ በኢትዮጵያ መንግስት የቀረበለትን የሰላም ጥሪ መቀበሉን አስተውቋል።

ማክሰኞ ከቀኑ አራት ሰዓት የኤርትራ መንግስት የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የሚመራ ልዑክ አዲስ አበባ ገብቷል። ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድም ለልዑካን ቡድኑ አቀባበል አድርገውለታል።

በዚህ አምድ በሁለቱ ሀገሮች መካከል የሚተገበረው የአልጀርስ ስምምነት በምን ደረጃ የሚገለጽ ነው? የኤርትራ መንግስት ለሰላም ድርድሩ የሰጠው ምላሽ አንደምታዎች ምን ይመስላሉ? ፕሬዝደንት ኢሳያስ አፈወርቂ ስምምነቱን ከመቀበላቸው ጋር አያይዝው ሕወሓትን ለመጎንተል ለምን አስፈለጋቸው? በድርድሩ የሁለቱ ሕዝቦች ተሳትፎ እንዴት ይታያል? እና የመደመር ፖለቲካን በተመለከተ ከፕሮፌሰር መድሃኔ ታደሰ ጋር፤ ፋኑኤል ክንፉ ቆይታ አድርጓል።

ፕሮፌሰር መድሃኔ ታደሰ በአሁን ሰዓት በለንደን ኪንግስ ኮሌጅ የዓለም አቀፍ የፀጥታና ደህንነት ፕሮፌሰርና መምህር ናቸው። በአፍሪካ ቀንድ የደህንነትና የፀጥታ ተመራማሪ በመሆን ላለፉት ሃያ አመታት ሰርተዋል። በአፍሪካ ሕብረት የደህንነትና ፀጥታ አማካሪና ተመራማሪ በመሆን አገልግለዋል።

 

ሰንደቅ:- የኢትዮጵያና ኤርትራ የአልጀርሱ ስምምነት ለመተግበር ፈቃደኛ መሆናቸውን እየገለጽ ነው። ወደተግባር ይለወጣል የተባለውን ስምምነት እንዴት ያዩታል?

ፕሮፌሰር መድሃኔ፡-በመጀመሪያ ሁለት ነገሮች በግልጽ መቀመጥ አለባቸው። ይህም ሲባል፣ ኢሕአዴግ እየተዘጋጀ ያለው ለሁሉም አቀፍ የሰላም ስምምነት ነው? የተቀበለው የአልጀርሱን ሙሉ ስምምነት ነው? ወይንስ የድንበር ኮሚሽኑን ውሳኔ ነው? የአልጀርሱ ስምምነት ከሆነ ሁሉን አቀፍ የሰላም ስምምነት ነው። ለሰላም ቅድሚያ መሟላት ያለባቸውን ቅድመ ሁኔታዎች ያስቀደመ የስምምነት ማዕቀፍ ነው። ይህንን ስምምነት ሙሉ ለሙሉ አለምንም ቅድመ ሁኔታ ለመተግበር ከሆነ ያስኬዳል።

የድበር ኮሚሽኑ ውሳኔን ብቻ ከሆነ የስምምነቱ አንዱን አካል ወስዶ መተግበር ነው የሚሆነው። ይሄ ድንበርን ብቻ ስለሚጐላ ብዥታ ይፍጥራል። አነስ የሚል ስምምነት ነው የሚሆነው። ስለዚህም በግልጽ ማስቀመጡ ተገቢነቱ ከፍ ያለ ነው የሚሆነው።

ሰንደቅ:- አሁን ካለው ተጨባጭ ሁኔታ የተሻለ ተደርጎ የሚወሰደው የትኛው ነው?

ፕሮፌሰር መድሃኔ፡- የአልጀርሱን ስምምነት ሙሉ ለሙሉ መተግበር የተሻለ ውጤት ያመጣል። ምክንያቱም በዚህ ሙሉ የስምምነት ሰነድ ውስጥ የሰፈሩትን ነጥቦች መመልከቱ ጠቃሚ ነው። ይኸውም፣ የጦርነቱን መንስኤዎችን ማየት፤ ድንበር ማካለል፤ የካሳና ቅሬታ ጉዳዮችን ዕልባት መስጠት፤ እነዚህ ሁኔታዎች ወደተግባር ገብተው እስከሚጠናቀቁ ድረስ በሁለቱ ሀገሮች መካከል የሰላም አስከባሪና የፀጥታ ቀጠና መመስረት፤ ሁለቱን ሀገሮች እያነጋገሩ ስምምነቶችን መጨረስ ያጠቃልላል።

ስለዚህ የሚደረገው የሰላም ስምምነት ድርድር ነው። ይህም በመሆኑ፣ ከኤርትራ ጋር የሚደረገው ማንኛውም ዓይነት ድርድር ማዕከሉ ሰላም መሆን አለበት፤ ይገባልም። ሰላም ሲባል በድንበሩ ጉዳይ፤ በሕዝቡ እንቅስቃሴ፤ የንግድ እንቅስቃሴ፤ የፀጥታ ጉዳይ፤ በሁለቱም የፀጥታ ሓይሎች የሚደረግ ትብብር፤ ይህንን ሁሉ ነው የሚያጠቃልለው። ለሰላም ዝግጁነት ከሌለ የአልጀርስን ስምምነት መፈጸም አይቻልም።

አንዷን የአልጀርስ ስምምነት ውሳኔ ብቻ ነጥሎ ወደ ስምምነት ውስጥ ለመግባት መሞከር ውጤት አያመጣም። ምክንያቱም የኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት መነሻው ድንበር አልነበረም። የግጭቱ መንስኤ የፖለቲካ ኢኮኖሚ ጉዳይ ነው፤ የፀጥታ ጉዳይ ነው፤ በአካባቢው ባለው የኃይል አሰላለፍ ጉዳይ ነው፤ ስለዚህም የግጭቱ መሰረት ሰፊ ነበር። ይህንን በሚፈታ መልኩ ነው የሰላም ስምምነቱ መቃኘት ያለበት። የውይይቱ መድረክ በዚህ መልክ ከሆነ፣ ረጀም ርቀት መጓዝ ያስችላል።

ሰንደቅ:- የኤርትራ መንግስት ለቀረበለት የሰላም ድርድር የሰጠውን ምላሽ እንዴት ይመለከቱታል?

ፕሮፌሰር መድሃኔ፡- የኢትዮጵያ መንግስት የአልጀርስ ስምምነትን አለቅድመ ሁኔታ ለመተግበር ያቀረበውን የሰላም ድርድር፣ የኤርትራ መንግስት የተቀበለበትን ሁኔታ አፅንዖት ሰጥቶ መመልከቱ ጥሩ የሚሆን ይመስለኛል። ይህም ሲባል፣ ከኤርትራ መንግስት ይጠበቅ የነበረው ምላሽ እናንተ (የኢትዮጵያ መንግስት) ከተቀበላችሁት ጥሩ፤ በተመረጠ ቦታ፣ ሸምጋዮች በተገኙበት፣ ቅድመ ሁኔታዎች ተነስተው፣ ለመወያየት ዝግጅት እናደርጋለን የሚል ነበር። ይህ ማለት የመቀበል የመጀመሪያው ምላሽ ነበር የሚጠበቅበት። የኤርትራ መንግስት ያደረገው ዘሎ ወደ አዲስ አበባ ልዑክ እንልካለን ነው ያለው።

እዚህ ላይ መታየት ያለበት፣ በየትኛው ማዕቀፍ ውስጥ ሆኖ ነው ወደ አዲስ አበባ ልዑክ እልካለሁ የሚል ምላሽ ያቀረበው። ወደ አዲስ አበባ የሚመጣው የኤርትራ ልዑክ፣ በኢትዮጵያ ወቅታዊ ፖለቲካ ለውይይት ነው? ወይንስ ለድንበር ኮሚሽኑ ውሳኔ ነው? ወይንስ ለአልጀርሱ ሙሉ ስምምነት ነው? ለዚህም ነው ምላሹ ጥያቄ የሚያጭረው።

ለምን ቢባል፣ የኤርትራ መንግስት በድንበር ግጭቱም ሆነ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ በአካባቢው ፀጥታ ጉዳይ የነበረው አቋም ይታወቃል። ከነበረው አቋም አንፃር የኤርትራ ልዑክ ወደ አዲስ አበባ ሲመጣ ሁለቱም ሀገሮች እንደሁለት ሉዑላዊ ስልጣን እንዳላቸው አካሎች ቆጥረው በኢትዮጵያ በኤርትራ ጉዳይ ሰላም ሊያመጣ የሚችል የአልጀርስ ስምምነት መፈተሽና መነጋገር ላይ ነው ማተኮር ያለባቸው። ይህ ጉዳይ በግልፅ መቀመጥ አለበት። ለነገሩ አሁን የመፈታተሽና የመጠናናት ጊዜ ብቻ ነው። በኢትዮጵያ በኩል ጊዜ ወስዶ ሃሳቦችን ቀምሮ ለመደራደር ትንሽ እርጋታ ያስፈልጋል። አሁን አስፈላጊ የመፈተሻ ጥያቄዎች ከተጠየቁም በቂ ናቸው።

ኢትዮጵያ ውስጥ የመጣው ለውጥ ኢሕአዴግ ውስጥ ባሉ እና ከኢሕአዴግ ውጪም ባሉ ኢትዮጵያዊ ኃይሎች ብቻ የመጣ ለውጥ ተደርጎ መሰመር አለበት። ኢትዮጵያ ውስጥ የሚመጣን በጐ ለውጥ የኢትዮጵያውያን ባለቤትነት ብቻ የተረጋገጠበት ሆኖ መውጣት አለበት። ሌሎች የለውጥ አካል ነን ብለው ተደርበው ባይገቡ፣ ይመረጣል። አይጠቅምም። ሌሎች ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው ለውጥ ይመለከተናል ብለው ለመደራደር ለመነጋገር እንመጣለን ሲሉ፣ የኢትዮጵያ መንግስትና ሕዝብ የእራሱን አቋም በግልጽ መያዝና ማስቀመጥ አለበት። ምክንያቱም የትኛውም ድርድር በኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅምና ደህንነት ላይ የተንጠለጠለ መሆኑን መገንዘብ ተገቢ ነው። በነፃነት የሚካሄድ ድርድር መሆን አለበት። የቅርብ ጊዜ የመጐዳት ታሪካችንም የሚያስተምረው ይሄን ነው።

ሰንደቅ:- ፕሬዝደንት ኢሳያስ አፈወርቂ የሰላም ድርድሩን መቀበላቸው ባሳወቁበት ንግግራቸው፣ የሕወሓት ጉዳይ ያበቃለት ጨዋታ ነው ሲሉ የሰላም ጥሪውን ለመቀበል እንደአንድ ምክንያት አስቀምጠዋል። ይህ በኢትዮጵያ የውስጥ ፖለቲካ ጣልቃ መግባት ተደርጎ ሊወሰድ ይችል ይሆን?

ፕሮፌሰር መድሃኔ፡- የኢትዮጵያ የውስጥ ፖለቲካ ባለቤቱ ኢትዮጵያዊያን ናቸው። ኢትዮጵያዊያን የጣልቃ ገብ ፖለቲካ ፈጽሞ መፍቀድ የለባቸውም። የኢትዮጵያ መንግስት ያቀረበው ጥሪ የአልጀርስ ስምምነቱን ዓለምን ቅድመ ሁኔታ ለመተግበር ዝግጁ መሆኑን ብቻ ነው። ከዚህ ውጪ በሀገር ውስጥ ፖለቲካ የኤርትራ መንግስት መፈትፈት የሚጠበቅበት አይመስለኝም። በኢትዮጵያም በኩል እንዲሁ። በተመሳሳይ ሁኔታም፣ በኤርትራ የውስጥ ፖለቲካም ማን ስልጣን ያዘ፣ ማን ወረደ፣ ቀጣይ የኤርትራ ፖለቲካ ዕጣ ፈንታ ምን ይሆናል የሚሉት ጉዳዮች ለኤርትራውያን መተው ብቻ ነው። በኤርትራ ጉዳይ ሶስተኛ ወገን ገብቶ ቢፈትፈት ተገቢ አይደለም።

ፕሬዝደንት ኢሳያስ የፖለቲካ ጨዋታው አልቋል ማለታቸው ቢያንስ በኢትዮጵያ ውስጥ የፖለቲካ ጨዋታ መኖሩን አምነዋል። በአስመራ ውስጥ የፖለቲካ ጨዋታ ፈጽሞ የሚታስብ አይደለም። ስለዚህ በአሉታዊ መልኩ የፖለቲካ ጨዋታ የሚለውን አስቀመጡት እንጂ ፕሬዝደንት ኢሳያስ፣ ለፖለቲካ የሚሆን ከባቢያዊ ሁኔታዎች በኢትዮጵያ ውስጥ መኖሩን ማመናቸውን መውሰዱ ጠቃሚ ነው። በኤርትራ ውስጥ፣ የምጣኔ ሃብት ደረጃውም የዜጎችም ነፃነት መፈናፈኛ በሌለበት የመጨረሻው ደረጃ ይዘው ነው የሚገኙት። የዜጎች መፍለስ እንደሕዝብ ኤርትራን ሊያጠፋት ከጫፍ ደርሷል። ሕገመንግስት የሌለበት ሀገር ነው። በአንፃራዊነት ከወሰድነው በኢትዮጵያ ያለው የፖለቲካ ሽግግር ቢያንስ እንደ ሂደት የተሻለ ነው።

ስለዚህም ኢትዮጵያ ውስጥ ባለው ፖለቲካ ላይ ተንተርሶ ከኢትዮጵያ ጋር እንነጋገራለን፤ እንዲሁም ኢትዮጵያ ወደ አዝቅት እንዳትገባ የድርሻችን እንወጣለን ተብሎ በአንድ ሉዐላዊ ሀገር የውስጥ ጉዳይ ለመግባት መሞከር፤ የኢትዮጵያን የፖለቲካ ሽግግርን ያበላሸዋል። ዴሞክራሲውን ያበላሸዋል። ከኤርትራ ጋር የሚደረገውን ድርድር ሙሉ ለመሉ ያበላሸዋል። ከመጀመሪያው ነገሮቹን ለያይቶ ማየት የግድ ነው።

ሰንደቅ:- ፕሬዝደንት ኢሳያስ የሕወሓት የፖለቲካ ጨዋታ አብቅቷል የሚለው አገላለፃቸው፤ ከኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት መጀመር ምክንያቶች ጋር እንዴት ነው የሚታየው? ወይም ዝምድናው ምን ይመስላል?

ፕሮፌሰር መድሃኔ፡- ጦርነቱ በኤርትራ በኩል እንደተጀመረ የካሳ ኮሚሽኑም አረጋግጧል። ከታሪክም ከፖለቲካም አንፃር ውሃ የሚቋጥር መከራከሪያ አይደለም። እንዳውም በኤርትራ ጉዳይ ሕወሓት የተወቀሰው፣ ሕዝባዊ ግንባር ሐርነት ኤርትራ ኢትዮጵያ ውስጥ እንደፈለገ እንዲፈነጭ አድርጓል በሚል ክስ ነው። ይኸውም፣ ለኤርትራ ነፃነት ድጋፍ ሰጥቷል፤ ተሽቀዳድሞ ዕውቅን ሰጥቷል፤ ከስሜት አንፃር ለኤርትራ ያዘነብላል የሚሉ ክሶች ናቸው ሲቀርቡበት የነበረው። ከዚህ ጋር በተያያዘም በተለይ በኢትዮጵያ ተቃዋሚ ኃይሎች ከፍተኛ ክሶች ይቀርቡበት ነበር።

አሁን ይህንን ገልብጠው፤ የኤርትራ መንግስት ሕወሓት በሌለበት ነው ብሔራዊ ጥቅማችን የምናስከብረው ማለታቸው አስገራሚ ነው። በኢትዮጵያ ሁኔታ እንደፈለግን መንቀሳቀስ የምንችለው ‘የሕወሓት ተፅዕኖ በቀነሰበት ወቅት’ ነው ማለታቸው፣ ለኢትዮጵያ ሕዝብ ምን ዓይነት መልዕክት እንደሚሰጥ ግልፅ ነው። የኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት መነሻም ምን እንደነበረ በግልጽ ያሳያል። የጦርነቱ መነሻ፣ አለከልካይ በኢትዮጵያ የፖለቲካ ኢኮኖሚ ውስጥ የመሳተፍ ስትራቴጂ ነበር። ኢትዮጵያ ውስጥ አንጋሽና አውራጅ መሆን። ይሄ ምኞት ተቀይሯል አሁን? መረጋገጥ አለበት። የኤርትራ ፖለቲካ ኢኮኖሚ የተመሰረተው፣ በቀንዱ ሀገሮች ባሉ ኃያላን ሀገሮች የውስጥ ጉዳይ ገብቶ የኤርትራን ብሔራዊ ጥቅም በሚያስጠብቅ መልኩ ተንቀሳቅሶ የሀገራቱን ዝምድና መቀየር ነው። ይህ በሱዳን፣ በደቡብ ሱዳን፣ በየመን፣ በኢትዮጵያም ተሰርቶበታል። ለቀጠናው መረበሽ ከፍተኛ አስተዋጽዖ የነበረውም፤ ይኸው የኤርትራ ብሔራዊ ጥቅም ለማስከበር የነደፉት ፖሊሲያቸው ነው።

በዚህ ፖሊሲያው መነሻ ኢትዮጵያና ኤርትራ ወደ ጦርነት ውስጥ ገብተዋል። ምንም ሰላም ምንም ጦርነት የሌለበት ቀጠና ፈጥረው ተቀምጠዋል። ለሁለቱም ሕዝቦች የማይበጅ ሁኔታዎች ተከስተዋል። ይህንን ወደሰላም እናምጣው ስንል፣ የጦርነቱ ምንጭ ምን ነበር? የመሬት ጉዳይ ጦርነቱ እንዲነሳ በትክክል አስተዋፅዖ ነበረው ወይ? የጦርነቱን መነሻ ረስተን ችግሩን ሳንፈታ ኢትዮጵያና ኤርትራ ዘላቂ ሰላም ማስጠበቅ እንችላለን ወይ? ብለን ወደኋላ መመለስና ማየት አለብን። ይህንን የምናደርገው፣ ለመካሰስና አንዱ አጥፊ ሌላው ተበዳይ የሚል ዳኝነት ለመስጠት አይደለም፤ ወይም ቂም ቁርሾ ለመተው አይደለም። የፈለግነውን ሰላምም ለማበላሸት አይደለም። በትክክል ችግራችን ምንድን ነው ብለን ለመወያየት ከስሩ ለመፍታት እንዲያግዘን ነው።

የጦርነቱ መነሻ ለጊዜው የሰላም መዝሙር ሲባል ገሸሽ ማድረጉ ጠቃሚ ቢሆንም፣ እውነተኛ የሰላም ድርድር ውስጥ ሲገባ እነዚያ የጦርነት መነሻው የነበሩ ምክንያቶች ናቸው የኢትዮጵያና የኤርትራ መፃዒ እድሎችን አቅጣጫ የሚወስኑት። ጥያቄዎችን ከጦርነት ይልቅ በሰላም እንዴት እንፍታቸው ነው? ተሳስተን በጦርነት የፈታናቸው ለጦርነቱ መነሻ የነበሩ የፖለቲካ ኢኮኖሚ የአካባቢው ፀጥታ እና የኃይል አሰላለፍ የበላይነት ጉዳዮችን በሰላም በንግግር እንዴት እንፍታቸው ነው? ይህም ሲባል እንደ ሁለት ልዑላዊ ሀገሮች ማለት ነው። ወደዚህ ነው መምጣት ያለብን።

አሁን በኤርትራ በኩል ያለው ዕሳቤ በሰላሙ ላይ ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር እደራደራለሁ ግን የተወሰነ ተፅዕኖ የሚፈጥሩ ኃይሎች ስለተዳከሙ ይህንን እድል ልጠቀምበት እችላለሁ፣ ይህንን አጋጣሚ መጠቀም አለብኝ፣ ከሚል መነሻ ከሆነ በግልፅ ጉዳዩን አውጥቶ እንደማይሰራ፣ ሁለቱን ሕዝቦችንም እንደማይጠቅም ማስመር ያስፈልጋል። ምክንያቱም ሰላምም አያመጣም፤ በኢትዮጵያ የፖለቲካ ሽግግር ላይም አሉታዊ ተፅዕኖ ያስከትላል።

ሰንደቅ:- በሁለቱ አገራት ድንበር አካባቢ ያሉትን ሕዝቦች ማሳተፉስ እንዴት ነው ታሳቢ የሚደረገው?

ፕሮፌሰር መድሃኔ፡- የአልጀርሱ የሰላም ስምምነት ሙሉ ለሙሉ በሁለቱ ሀገሮች መተግበር ከተቻለ ምላሽ አለው። በነገራችን ላይ ከአስመራ ወደ አዲስ አበባ የሚያመጣ መንገድ የሚያልፈው በጎንደርና በትግራይ ነው። የሰላሙም መስመር የሚያንጸባርቀው ይሄንኑ ነው። እንደው ዘለህ በአውሮፕላን ከሚኒልክ ቤተመንግስት ጋር በተሳሰሩ ጉዳዮች ላይ ብቻ ተመስርተህ ሰላሙን አመጣዋለሁ ማለት ሰላሙን ከማበላሸቱ ውጪ የሚፈይደው ነገር አይኖርም።

ሰንደቅ:- ያለፈው አልፏል፤ ኢትዮጵያና ኤርትራ አዲስ ምዕራፍ መጀመር አለባቸው የሚሉ ወገኖች አሉ። በዚህ ላይ ምን አስተያየት አልዎት?

ፕሮፌሰር መድሃኔ፡- ያለፈው አልፏል ማለት እኔ እስከሚገባኝ፣ በጦርነትና በግጭት አንቀጥልም እንጂ ምንም ስላለፈው ነገር አይነሳ ማለት አይመስለኝም። ያለፈውን ሳናነሳ እንዴት መደራደር እንችላለን? አዲሱ ምዕራፍ የሚሆነው፣ የሁለቱ ሀገሮች ግንኙነቶች ምን መምስል አለባቸው? በድንበር ዙሪያ ያሉ ሕዝቦች እንዴት ይንቀሳቀሱ? ነፃ እንቅስቃሴ እንዴት ይሁን? የኢኮኖሚ ግንኙነቶች እንዴት ይሁኑ? የስልጣኔና የባህል ሽርክናችን እንዴት ነው የምናበለፅገው? መዳበር ያለበት በአካባቢው ፀጥታ ላይ በትብብር እንዴት ነው የምንሰራው? እነዚህን የመሳሳሉ ጥያቄዎችን አሁን ካለው ተጨባጭ ሁኔታዎች ጋር በመነሳት ምላሽ መስጠት ነው።

ሰንደቅ:- የመደመር ፖለቲካ መርህን እንዴት አገኙት?

ፕሮፌሰር መድሃኔ፡- መደመር የሚባለው አስተሳሰብ እኔ የሚገባኝ፤ ሰፋ ያለ ሀገራዊ መግባባት ቅርጽ አድርጌ ነው የምወስደው። ይህ ማለት፣ በወሳኝ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ ኢትዮጵያዊያን ተመሳይይ አቋም እንድንይዝ እንዲኖረን ማድረግ ነው። የክፍፍል፣ የጥላቻ፣ የቂም፣ የመጠላለፍ፣ የመጠላላት በተለይ በዘር በሃይማኖት በፖለቲካ አቋም ሊሆን ይችላል፤ ይህንን አስወግደን እንደአንድ ሀገር ማሰብ አለብን ነው።

ከዚህ በፊትም በተደጋጋሚ ሳነሳው የነበረው፣ ከብሔር ይልቅ ወደ ዜግነት ማድላት አለብን። ምክንያቱም ሁሉም ዜጋ ሲሆን፤ ይደመራል። የዜግነት መብትና ግዴታችን ሁላችንም ላይ በአንድ ዓይነት መፈጸም አለበት። ይህንን አስተሳሰብ ማስረጽ ይገባል። አንድ ሀገር ነው ያለን፤ ስለዚህም ከልዩነታችን ይልቅ አንድነታችን ማተኮር አለብን። መደመር ማለት በዚህ መልኩ ነው የሚገባኝ።

ከዚህ ውጪ ግን በምንወስዳቸው ርዕዮተዓለምና የፖለቲካ አቋሞች ላይ፤ ሁሉም የፖለቲካ ኃይሎች መደመር አለባቸው ማለት አይደለም። ምክንያቱም የፖለቲካ ብዝሃነት ይቀንሳል። ዴሞክራሲያዊ ሂደቶችንም ይደፈጥጣል። ከገዢው ፓርቲ በተቃራኒ የፖለቲካ አስተሳሰብ ላይ ያሉ የፖለቲካ ኃይሎችን የመቀነስ፣ የማግለል ሁኔታዎች እንዳይፈጠር በጥንቃቄ መያዙ ጠቃሚ ነው። መደመሩ ሌሎችን እንዳይቀንስ ማስተዋል ይጠይቃል። በመደመር ፖለቲካ፤ ሁሉም ኢትዮጵያዊያን በዜግነታቸው የሚመስላቸውን የፖለቲካ አቋም አደረጃጀት ይዘው፣ የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅምና ልዑላዊነትን በሚያስከብር መልኩ በሕገመንግስታዊ ሥርዓት በሕግ የበላይነት ላይ አንድ ዓይነት ጥላ ሥር ይሰባሰባሉ ነው። ሁሉም በሕግ ፊት እኩል ኢትዮጵያዊ ነው፤ እንደማለት ነው።

ዋናው መደመር ማለት የተለያየ አቋምና ዳራ ያለው የአንድ አገር ዜጋ በአንድ የረዥም ጊዜ የብሔራዊ ደህንነት ስትራቴጂ ጥላ ስር ሲቀመጥ ነው።

ሰንደቅ:- የጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ የለውጥ እርምጃ ፍጥነት የተፎካካሪ ፓርቲዎችን አጀንዳ ጨርሶ ወስዶታል፤ በገዢው ፓርቲ ውስጥም መንገራገጭ ፈጥሯል የሚሉ ወገኖች አሉ። በዚህ ነጥብ ላይ ምን አስተያየት አልዎት?

ፕሮፌሰር መድሃኔ፡- ከዚህ በፊት የተቃዋሚ ጎራውን የፖለቲካ ካርድና አጀንዳ ጠቅልሎ የመወስድ እድላቸው ሰፊ መሆኑን አንስቼዋለሁ። የጠቅላይ ሚኒስትሩ ፍጥነት ተቃዋሚ ጎራውን ብቻ ሳይሆን፣ ኢሕአዴግ ውስጥ ይኸው ፍጥነት የፓርቲውን ባሕሪ በሚቀይር መልኩ እየተጓዘ ይመስለኛል። በኢሕአዴግ ውስጥም፣ በተቃዋሚው ጎራም መደናበር መፈጠሩ አይቀርም።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ አሁን በያዙት ፍጥነት ሲታይ፣ በአንድም በሌላ መልኩ ተቃዋሚ ኃይሎች አብረዋቸው እንዲሰሩ እድል የሚፈጠር ነው። ይህ ማለት አጀንዳው እየተወሰደ በሄደ ቁጥር የተወሰነው ወደ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ክልል ውስጥ መግባት ሀገራዊ ፓርቲ ክልል ውስጥም መግባት የምናይበት ሁኔታ ሊፈጠር ይችላል። አዲስ የፖለቲካ ኃይል አሰላለፍ የሚፈጥር ሁኔታ በኢትዮጵያ ውስጥ ተፈጥሯል። አዲስ የፖለቲካ ካርታም (political trajectory) ተፈጥሯል። የኃይል አሰላለፉ ጠርቶ መልክ እስኪይዝ ድረስ፣ እንዲሁም የመደመር ፖለቲካ ተጨምሮበት ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ የፖለቲካ ኃይሎች እነማን ናቸው? እራሳቸውን ችለው የቆሙ ጠንካራ፣ ደካማ የምትላቸው መልኩ መለየት በሚያስቸግር መልኩ ለተወሰነ ጊዜ ሊቀጥል ይችላል። አጠቃላይ በሀገር ደረጃ ግን የኃይል አሰላለፉን እየቀረው ነው።

ሌላው የጠቅላይ ሚኒስትሩ የለውጥ ፍጥነት የፖለቲካ መነቃቃቱን እንዲጨምር አድርጓል። በኢትዮጵያ ፖለቲካ ያገባናል የሚሉ ዜጎች ኃይሎች በተለያየ መልኩ እንዲንቀሳቀሱ እድል ፈጥሯል። በአንድ መልኩ ለዴሞክራሲው ማበብ ጠቃሚ ነው። ሁሉም ዜጋ ፖለቲካ ያገባኛል የፖለቲካ መድረኩን ተጠቅሜ ድምፅን ማሰማት እችላለሁ የሚል እምነት እንዲይዙ አስችሏል። በሰላማዊ መንገድ ስልጣን ለመያዝ እድሉ አለ የሚል ተስፋም እንዲያጭር አድርጓል። ይሄ በጣም በጐ ነገር ነው።

ከኢህአዴግ አንፃር ከወሰድነው፣ ከደረስንበት የማንነት ቀውስ ጋር በተያያዘ መልኩ አዲስ የኃይል አሰላለፍ የመፈጠር እድሉ እየጨመረ ነው። አንዱ ትልቁ ለውጥ በገዢው ፓርቲ ውስጥ የዴሞክራሲያዊ ማዕከላዊነት ሙሉ ለሙሉ መዳከም ነው ያመጣው። ቀደም ባሉት ጊዜ በአንድ ጉዳይ ላይ አራቱም ፓርቲዎች ተወያይተው አንድ አቋም ይዘው በተባበረ ድምጽ ይሰሩ ነበር። አሁን ግን በአንድ ውሳኔ ባገኘ ጉዳይ ላይ ተቃውሟቸውን ማሰማት መጀመራውን ነው። ቅሬታው የሚገለጸው በውስጣዊ የድርጅቱ መስመር ቢሆን አንድ ነገር ነው። ቅሬታዎቹ እየቀረቡ ያሉት በመገናኛ ብዙሃን አማካኝነት ነው። ሙሉ ለሙሉ ዴሞክራሲያዊ ማዕከላዊነት በሌለበት መልኩ ተደርጎ የሚወሰድ ነው።

ይህ ማለት ዴምክራሲያዊ ማዕከላዊነት ሲዳከም ለአዲስ ግልጽ የወጡ የፖለቲካ ሹኩቻዎች በር ይከፍታል። በአራቱ ድርጅቶች ጭምር። የፖለቲካ ልጓም የሚይዘው ነገር የለም። ከዚህ አንፃር የጠቅላይ ሚኒስትሩ ፍጥነት ከሌሎች አጋር ፓርቲዎች ፍጥነት እኩል አይሆንም። ፍጥነቱ በጨመረ ቁጥር ልዩነቶቹ እየሰፋ ነው የሚሄዱት። ኢሕአዴግ ከማንነት ቀወስ ወደ መሰንጠቅ መሸጋገሩ አይቀርም። ከዛ ወደ አዳዲስ ስብስቦች ሊሸጋገር ይችላል። ለምሳሌ የተወሰኑት የኢህአዴግ አባል ድርጅቶች ከሌሎች የብሔር ድርጅቶች ጋር መቀናጀትና መተባበር በሚያስችል መልኩ አዳዲስ ጥምረቶች እየተሰሩ የሚፈርሱበት ሂደት ሊፈጠር ይችላል። ዶ/ር አብይና ዋነኛው የኢህአዴግ ክፋይም ተቃዋሚዎችን በተወሰነ ደረጃ ባካተተ መልኩ አንድ ጣምራ አገራዊ የፖለቲካ ፓርቲ ለመፍጠር ሊገደድ ይችል ይሆናል። የገዢ ፓርቲና የተቃውሞው ጐራ መደባለቅና ፍጥነቱን ስትረዳ አዳዲስ የልሂቅ ድርድሮችና ውሎች (Elite Bargain & Elite Pact) የሚመጣበት እድልም ሰፊ ነው። ለዚህ ሁሉ ዋናው ተቋማዊ የሆነና አሳታፊ በሚባል መልኩ ሂደቱን ማስኬድ ነው።¾

 

በይርጋ አበበ

ዘርፈ ብዙ ችግርና ሰቆቃ በዜጎቹ ላይ የሚጭነው የምስራቅ አፍሪካ ፖለቲካ በተለይም የኤርትራና ኢትዮጵያ ገዥዎች ግጭት አካባቢውን የሰላም አየር እንዳያገኝ አድርጎታል። በዚህ ክፍለ አህጉር ከሚገኙት አገራት ኬንያ ብቻ የተሻለ ሰላምና መረጋጋት ሲኖራት ቀሪዎቹ ስደት፣ ረሃብ፣ የዜጎች ስቃይ፣ የገዥዎች ፈላጭ ቆራጭነትና የእርስበርስ ጦርነት ሰለባዎች ናቸው።

ከሚያዝያ 29 ቀን 1990 ዓ.ም ጀምሮ በጦርነትና በመደባበር ውስጥ የቆዩት ኢትዮጵያ እና ኤርትራ ከዶ/ር አብይ ወደ ሥልጣን መምጣት በኋላ ግንኙነታቸው እየተቀየረ ይመስላል። በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ሳይቀር “የምድራችን አሰቃቂ ጦርነት እና በርካታ የህዝብ እልቂት የታየበት” የሚል ስያሜ የተሰጠው የኢትዮጵያና ኤርትራ መንግሥታት ጦርነት ከተጠናቀቀ 16 ዓመት ቢያልፈውም አካባቢው ሰላም ርቆት ቆይቷል። በአልጀሪያው ፕሬዝዳንት አብዱላዚዝ ቦቶፍሊካ አደራዳሪነት የተኩስ አቁም ስምነት ላይ የደረሱት የሁለቱ አገራት መንግሥታት በድንበር አከላለል ጉዳይም ተስማምተው በኢትዮጵያ በኩል አቶ መለስ ዜናዊ በኤርትራ በኩል ደግሞ አቶ ኢሳያስ አፈወርቂ ተፈራርመዋል። ሆላንድ ዘሔግ ላይ በተደረሰው የፍርድ ውሳኔ መሠረት አልጀርስ ላይ የስምምነት ፊርማ የተፈራረሙት ሁለቱ መሪዎች በስምምነታቸው መሠረት አካባቢውን ከጦርነት ቀጠና አላቀው ሰላም ወደ ነበረበት ሁኔታ መመለስ አልቻሉም።

ኤርትራ “የድንበር ኮሚሽኑ ውሣኔ ተግባራዊ ይሁንልኝ፣ የተፈረዱልኝ መሬቶች ይሰጠኝ” ስትል፤ በኢትዮጵያ በኩል ደግሞ ኢህአዴግ መራሽ መንግሥት ስምምነቱን ባይክድም ነገር ግን ከስምምነቱ ውጭ የሆነ ሌላ “ሰጥቶ መቀበል” የሚባል ባለ አምስት ነጥብ መስፈርት አስቀመጠ።

ሁለቱም መሪዎች የኮምዩኒዝም አስተሳሰብ ቅኝት መሆናቸውን ተከትሎ ተቀራርቦ ከመስማማት ይልቅ በሁለቱም ጽንፍ ነገሩ እየከረረ ሄዶ በመጨረሻም ያለ ስምምነት 16 ዓመት ቆዩ። በእነዚህ 16 ዓመታት ውስጥ ደግሞ ኤርትራ ላይ የኢኮኖሚ ማዕቀብ የተጣለ ሲሆን በዚህ ማዕቀብ መጣል ደግሞ “የኢትዮጵያ ሴራ አለበት” ሲሉ ኤርትራዊያን ገዥዎች ይናገራሉ።

ከአቶ መለስ ዜናዊ ህልፈት በኋላ የሁለቱ አገራት ግንኙነት የተሻለ መልክ ሊባባስ እንደሚችል ተስፋ ተጥሎ የነበረ ቢሆንም የኤርትራ መንግሥት ከአቶ ኃይለማርያም የቀረበለትን ጥያቄ ውድቅ አድርጎት ቆይቷል። አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ በአንድ ወቅት ኢትዮጵያ ቴሌቭዥን ሲናገሩ “ተደጋጋሚ ጥያቄ አቅርበነል። ከ50 ጊዜ በላይም ጥያቄ ብናቀርብም ፈቃደኛ አይደሉም” ሲሉ ተናግረው ነበር። አቶ መለስም ቢሆኑ የሁለቱ አገራት ግንኙነት ወደነበረበት የሰላም እና የፍቅር መስመር ሊመለስ የሚችለው አስመራ ያለው መንግስት ከስልጣን ሲወገድ ብቻ ነው ሲሉ ተናግረው ነበር።

ዶ/ር አብይ አህመድ መጋቢት 24 ቀን 2010 ዓ.ም በህዝብ ተወካዮች ም/ቤት ባደረጉት ንግግር ከኤርትራ መንግሥት ጋር በልዩ ሁኔታ ግንኙነታችንን እናጠናክራለን ብለው ሲናገሩ ብዙዎች አምነው መቀበል ተቸግረው ነበር። ሆኖም ሰኔ 12 ቀን 2010 ዓ.ም የኤርትራው ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈሰወርቂ የዶ/ር አብይን ጥሪ ተቀብለው አገራቸው ለድርድር ፈቃደኛ መሆኗን ገለፁ። በቅርቡም አንድ የልዑካን ቡድን ወደ አዲስ አበባ እልካለሁ ሲሉ ተናገሩ። ይህን መግለጫቸውን ተከትሎ ዶ/ር አብይ አህመድ በአፀፋው “አመሰግናለሁ” ሲሉ ወልቂጤ ላይ ተቀምጠው መግለጫ አስተላለፉ። ትናንት ሰኔ 19 ቀን 2010 ዓ.ም ደግሞ በሶስት ከፍተኛ ባለስልጣናት (አቶ የማነ ገብረ-አብ፣ አቶ ኡስማን ሳልህ እና አምባሳደር አርአያ ደስታ) የተመራ የልዑካን ቡድን አዲስ አበባ ገባ። ቦሌ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ ሲደርስም ዶ/ር አብይ አህመድና ሌሎች ከፍተኛ ባለሥልጣናት (ዶ/ር ወርቅነህ ገበየሁና የጦር ኃይሎች ም/ል ኢታማዦር ሹም ጀኔራል ብርሃኑ ጁላ) አቀባበል አደረጉላቸው።

ይህን ተከትሎም የሁለቱ አገራት ግንኙነት ወደየት ሊሄድ ይችላል? የሚሉ ጥያቄዎች አብረው ሊነሱ ይችላሉ። ኢትዮጵያዊያን ፖለቲከኞችና አብዛኛው ህዝብ “የአሰብ ወደብ ይገባናል” የሚል ጥያቄ የሚያነሳ ሲሆን የኢህአዴግ ባለሥልጣናት ግን በዚህ ጉዳይ ከማንም ጋር ለመነጋገር ፈቃደኛ አይደሉም። በተለይ አቶ መለስ ዜናዊ የወደብን ጉዳይ በተመለከተ በፓርላማቸው ሲናገሩ “ወደብ እንደማንኛውም ሸቀጥ ስለሆነ ከሚስማማን አገር ገዝተን ልንጠቀም እንችላለን። የሻዕቢያ መንግስት ግን አሰብን ሊጠቀምበት የሚችለው ለግመል ማጠጫ ነው” ሲሉ ተናግረው ነበር። አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝም ይህንኑ አመለካከት ይጋራሉ። ገና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር በነበሩበት ወቅት ለአንድ የአገር ውስጥ ጋዜጣ በሰጡት ቃለ ምልልስ “ተቃዋሚዎች የአሰብን ወደብ የኢትዮጵያ ናት ብለው የሚናገሩት የህዝብ ድጋፍ ለማግኘት እንጂ ወደቡ እንደሚገባን ስለሚያውቁ አይደለም” ብለው ነበር። አቶ በረከት ስምኦንም “የወደብ ጥያቄ የሚያነሱት ጦርነት ናፋቂዎች ናቸው” ሲሉ መናገራቸው ይታወሳል።

አሁን ሁለቱ አገራት ግንኙነት መልኩን ቀይሮ ሰላማዊ ጉርብትና የሚታይበት ከሆነ ኢትዮጵያ ምን ትጠቀማለች? ኤርትራስ የምታገኘው ምንድን ነው? የሚለው ጥያቄ መነሳቱ አይቀርም። ኤርትራዊያን ለ16 ዓመታት በፅኑ ሲያነሱት የቆየው የድንበር ኮሚሽኑ ውሳኔ ተግባራዊ እንዲሆን ነበር። ይህን ጥያቄያቸውን ደግሞ የኢህአዴግ ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ በማያዳግም መልኩ እንደሚመለስላቸው አሳውቋል። የኢትዮጵያ መንግሥት እዚህ ውሳኔ ላይ የደረሰበትን ምክንያት ሲገልፅም “ለሰላም ሲባል” እንዲሆን አስታውቋል።

በዚህ ጉዳይ ላይ ለሰንደቅ ጋዜጣ አስተያየታቸውን የሰጡት የኦሮሞ ፌዴራሊስት ኮንግረስ (ኦፌኮ) ሊቀመንበር ዶ/ር መረራ ጉዲና “የሁለቱ መንግሥታት ውይይት እስካሁን ምን መልክ እንዳለው ባላውቅም በግሌ ግን ኢትዮጵያ ልትጠቀም በምትችልባቸው ነጥቦች ላይ ውይይት ይደረጋል ብዬ አስባለሁ” ብለዋል።

ዶ/ር መረራ ኢትዮጵያ መጠቀም አለባት የሚለውን አመለካከታቸውን ሲያብራሩም “ወደብ ፍለጋ የምትዞረው ኢትዮጵያ የአሰብን ወደብ እንድትጠቀም የሚያስችል ስምምነት ሊደረስ ይችላል። ይህ ከሆነ ደግሞ ኢትዮጵያ ለወደብ ኪራይ የምትከፍለውን መጠን ሰፊ ገንዘብ ይቀንስላታል። ከዚህ በተጨማሪም በሁለቱ አገራት ድንበር ላይ ላሰፈረችው ከፍተኛ ቁጥር ያለው የጦር ሰራዊት የምታወጣውን ወጭ ስለሚቀንስላት የሁለቱ አገራት ስምምነት ለሁለቱም ጠቀሜታ አለው” ብለዋል።

አቶ ኢሳያስ የዶ/ር አብይ አህመድን የሰላም ጥሪ መቀበላቸውን ባሳወቁበት ወቅት በሰጡት መግለጫ ኢትዮጵያ ውስጥ አዲስ የፖለቲካ ለውጥ አለ። ቀደም ሲል ህወሓትና የእሱን አመለካከት የሚያራምዱ አጋሮቹ ለለውጥ ዝግጁ አልነበሩም” ሲሉ መግለፃቸውን በርካታ የኤርትራ መንግሥት ጋዜጦችና ቢቢሲ አማርኛው ክፍል ለንባብ አብቅተዋል። ይህን ንግግራቸውን በተመለከተ አስተያየት የሚሰጡ ምሁራን የህውሓት መራሹ ኢህአዴግ አስተዳደር እየተዳከመ መምጣቱን ተከትሎ የኢሳያስ የሰላም ፍላጎት ማደጉን ይናገራሉ።

ባሳለፍነው ቅዳሜ ረፋዱ ላይ በመስቀል አደባባይ በተከናወነው የድጋፍ ሰልፍ ላይ በዶ/ር አብይ አህመድ ላይ ያነጣጠረ የግድያ ሙከራ ማድረጉን አቶ ኢሳያስ አፈወርቂ እና መንግሥታቸው “በፅኑ” እንደሚያወግዙት ተናግረዋል። ቀደም ባሉት ዘመናት ኢትዮጵያ ውስጥ የሚፈጠሩ ግጭቶች፣ ፍንዳታዎችና የሽብር ድርጊቶች በሙሉ “የኤርትራ መንግስት ተላላኪዎች ተግባር” እየተባለ ሲነገር እንደመቆየቱ፤ ሰሞኑን በዶ/ር አብይ ላይ የተደረገውን የግድያ ሙከራ የኤርትራ ባለሥልጣናት ማውገዛቸው የሁለቱን አገራት ግንኙነት እውነትም ወደ ሰላማዊ መንገድ እየተሸጋገረ ነው እንዲባል ተስፋ ሰጭ መሆኑን ፖለቲከኞች ይናገራሉ።

“ከኤርትራ ጋር በሰላምና በፍቅር ተሳስቦና ተረዳድቶ መኖሩ ተገቢ ነው” ሲል የገለፀው ሰማያዊ ፓርቲ በበኩሉ፤ “ኢህአዴግ የሚመራው መንግስት ተረጋግቶ እንዲያስብና ኢትዮጵያ ከኤርትራ ጋር በሚያዋስኑን ድንበር ጉዳይ በዓለም አቀፍ ፍርድ ቤት በወቅቱ በነበሩ መሪዎች የተፈጠረውን ክፍተት መድፈን የሚያስችል የህግ አግባብ ካለ ከምሁራን ጋር በአግባቡ መወያየት እና በመምከር ሌሎች መፍትሄዎችን መፈለግ እንዳለበት ማሳሰብ እንሻለን። የስምምነቱ አፈፃፀምም ቢሆን ለህዝብ በዝርዝር ያልተቀመጠ እና የአሰብን ጉዳይ ማካተት አለማካተቱ ያልተጠቆመ በመሆኑ ይህን ለህዝብ መግለፅ ተገቢ ነው እንላለን” ሲል የሁለቱ መንግስታት ግንኙነት በጥንቃቄ መታየት እንዳለበት አስታውቋል።

ከ1998 ዓ.ም ጀምሮ ከምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግሥታት ድርጅት (ኢጋድ) የተገለለችው የኢሳያስ አፈወርቂ አገርስ ወደ ማህበሩ ተመልሳ ለቀጠናው ሁለንተናዊ ለውጥ የበኩሏን ትወጣለች ወይስ በአቋሟ ፀንታ ትቆያለች? የሚለውም የሚታውቀው ወደፊት በሚኖረው የውይይት ውጤት ይሆናል። በአጠቃላይ ግን የሁለቱ መንግስታት መስማማት የሁለቱንም አገራት ዜጎችና የቀጠናውን ፖለቲካል ኢኮኖሚ ተጠቃሚ እንደሚያደርገው አያጠያይቅም። በዚህ መካከል ግን የኢትዮጵያ መንግስት በኤርትራ ላይ እየቀረፅኩ ነው ሲለው የነበረው የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ሳይዘነጋ ማለት ነው።

  

~ በዘር ተጨፋጭፈን ብንባላ ለልጅ ልጅ የምናተርፈው ከባድ ውርደትና ክህደት ነው!

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አሕመድ ከትላንት በስቲያ ሰኞ ሰኔ 11 ቀን 2010 ዓ.ም ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሰጡት ማብራሪያ የኢሕአዴግን ፖለቲካዊ ዳራ ግልጽነትና ድፍረት በተሞላበት አቀራረብ የተሳሳተ መሆኑን አስመርው አስቀምጠዋል፡፡ በተለይ መንግስታቸው አሸባሪ መሆኑን አምነው፣ በሕዝቡ ምህረት በሥልጣን ላይ መቀጠሉን ይፋ አድርገዋል፡፡ አያይዘውም፣ ሕዝቡ “ለእኛ” ከሰጠውን ምህረት፣ ተፎካካሪ የፖለቲካ ኃይሎችም ሊደርሳቸው ይገባል በማለት፤ ፓርላማውን ሞግተዋል፡፡ አዲስ የፖለቲካ ኢኮኖሚ አቀራረብ ከድርጅታቸውም እንደሚጠበቅ አጽንዖት ሰጥተው አሳስበዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ካቀረቡት ሪፖርትና ከፓርላማ ተወካዮች ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች ከሰጡት ምላሽ ገዢ ሃሳቦች ናቸው ያልናቸውን እንደሚከተለው አስተናግደነዋል፡፡

 

ሽብርን በተመለከተ

~በሽብር ወንጀል ጭምር ተከሰው ከማረሚያ ቤት የተፈቱ ሰዎች ኢህአዴግ ባስቀመጠው አቅጣጫ የተፈፀመ እንጂ ህግ መጣስ አይደለም፡፡

~መንግስት አሰቃቂ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ጭምር በመፈፀም ራሱም የሽብርተኝነት ተግባር ሲፈፅም ቆይቷል፡፡

~ሽብር ስልጣን ላይ ለመቆየት ኢ-ህገ መንግስታዊ ድርጊት ላይ መሳተፍና ስልጣን ለመያዝ ኢ-ህገ መንግስታዊ ድርጊት ማድረግን ያካትታል፡፡

~ ሰውን ጨለማ ቤት ማስቀመጥ፣ አካልን ማጉደል የእኛ የመንግስት የአሸባሪነት ድርጊት ነው።

~ ሕገመንግሥቱ ጨለማ ቤት አስቀምጣችሁ ግረፉ፤ አሰቃዩ አይልም። አሸባሪ እኛ ነን። ኢህአዴግ ይቅርታ ጠይቋል፤ ህዝቡም ይቅር ብሎናል፤ ህዝቡ እኛን ማሰር ነበረበት፤ በይቅርታ አልፎናል።

~ሰብአዊ መብት ጥሰቶች ከወረዳ እስከ ፌደራል ድረስ በነበሩ እስር ቤቶች ነበር። መንግስት በዚህ ስራ አሸባሪ ነበር። ያለአግባብ ታስረው የነበሩ የይቅርታ አሰጣጦች በህግ የተሰሩ ናቸው። ማንም በህግ ይቅርታ ያገኘ ሰው ታራሚ እንጂ አሸባሪ አይደለም። ይህ ምክር ቤት አሸባሪ ድርጅት እንጂ ግለሰብን ብሎ አያውቅም። ጥላቻ ላይ ተመሰረተ የፖለቲካ አካሂድ ኪሳራ ነው። ዜጎችንም አላስፈላጊ ግጭት ውስጥ እያስገባ ነው።

~ ይህ ምክር ቤት አሸባሪ ድርጅት እንጂ ግለሰብን ብሎ አያውቅም። ጥላቻ ላይ ተመሰረተ የፖለቲካ አካሄድ ኪሳራ ነው። ዜጎችንም አላስፈላጊ ግጭት ውስጥ እያስገባ ነው ።

~ ግንቦት 7 ኦነግ፣ ኦብነግ ውጊያ ፋሽን ያለፈበት ጉዳይ ነው አቁማችሁ ኑ በሀሳብ ብልጫ ውሰዱ።

~ዶክተር ብርሃኑ ነጋ እኔን ገድለው ወይም አስገድለው ስልጣን መያዝ?.. እኔ እሳቸውን ገድዬ ስልጣን ላይ መቆየት?..ሁለቱም ጊዜ ያለፈባቸው ፋሽን ናቸው፤ አይጠቅሙም፡፡

~ ጃንሆይን አፍኖ መግደል መልካም እንዳልሆነ ከመንግስቱ መማር አለብን። ቤተመንግስት የኮሎኔል መንግስቱ መግረፊያ አለ። ይህ የጥላቻ ታሪክ ያብቃ።

~ በግፍ የታሰሩት እየተለቀቁ ነው። የቀረ ካለ እንፈታለን። እስረኛ ባንድ ጀምበር አይለቀቅም። ህግ እና ስርዓት አለው። በዚህ መሰረት ይከወናል።

~ ገለልተኛ የፍትህ ተቋም እንገነባለን። የተሟላ ዲሞክራሲ የለም። የተከማቸ ችግር ስላለ ቀስ እያልን እንፈታለን።

 

ዘረኝነት

~የአፍሪካ መሪዎች ያለቪዛ አፍሪካውያን በነጻ እንዲንቀሳቀሱ ሊያደርጉ ነው፡፡ አማራ በኦሮም፤ ትግራይ በአማራ ክልል በነጻ መንቀሳቀስ ካልቻለ ስለ አፍሪካ አንድነት ለማውራት አንችልም፡፡ አንድነትን እንሰበክ፡፡

~ ድንበር እና ወሰን ማምታታት አለ። አማራ እና ኦሮም፤ አማራ እና ትግራይ ድንበር የላቸውም። ወሰን ነው። ድንበራችን ከኬኒያ ጋር ነው። አንድ አማራ ነቀምት፤ አንድ ኦሮሞ ጅግጅጋ ላይ መኖር ካልቻለ ከባድ ነው። የትም ቦታ የመኖር መብት አለን። የፊዴራሊዝም ስርዓቱ ትላልቅ ችግርን እንጂ ትንንሽ ችግሮችን ማቆም አይችልም፣

~ የእርስ በርስ ጥቃት ዘር ወደመተላለቅ የሚመራ አጉል የፖለቲካ አካሂድ እና የጥቂቶች አላማ ነው። ይሄ እንዳሆን ግን ህዝባችን ልበ ሰፊ ነው

~ እኛ ተቸግረን ለልጆቻችን ችግር፣ ጥላቻ፣ ጸብና ግጭት ማውረስ የለብንም፤ እርቅና ሰላም ነው የሚያስፈልገን፣ ኢትዮጵያውያን ለሰላም የሚከፈል ማንኛውንም ዋጋ ለመክፈል ዝግጁ መሆን አለባቸው

~ሰው ሲፈታ አይናችን የሚቀላ በቀለኞች አንሁን።

~ አማራ በኦሮሞ፤ ትግራይ በአማራ ክልል በነጻ መንቀሳቀስ ካልቻለ ስለ አፍሪካ አንድነት ለማውራት አንችልም፣

~ ድንበር እና ወሰን ማምታታት አለ። አማራ እና ኦሮም፤ አማራ እና ትግራይ ድንበር የላቸውም። ወሰን ነው። ድንበራችን ከኬኒያ ጋር ነው፣

~ አንድ አማራ ነቀምት፤ አንድ ኦሮሞ ጅግጅጋ ላይ መኖር ካልቻለ ከባድ ነው። የትም ቦታ የመኖር መብት አለን፣

~በመግደልና በመገዳደል እኖራለሁ የሚል ሰው የተሸነፈ ሰው ነው።

      ~በዘር ተጨፋጨፍን ብንባላ ለልጅ ልጅ የምናተርፈው ከባድ ውርደትና ክህደት ነው!

~አንዱ ብሔር ሌላውን ብሄር ከክልሌ ውጣልኝ ማለት ኋላቀር አስተሳሰብ ብቻ ሳይሆን ህጋዊም አይደለም! መሬት የመንግሥት እና የህዝብ ሆኖ እያለ ማንም ከመሬት ውጣልኝ ማለት አይችልም።

~ይህ የዘረኝነት እና የጥላቻ አስተሳሰባችን ሊገረዝ ይገባል፡፡

~ ጥቂቶች በስሙ ነግደው ይሆናል እንጂ የትግራይ ህዝብ የተለየ ያገኘው ነገር የለም። ሚስተር ኤክስ አጠፋ ብለን የማያውቁ ሰዎችን ጭምር በዚያ ወንጀል ስም በጥላቻና በቂም ማየት ለኢትዮጵያ አይበጅም። መለየት ያስፈልጋል። መፈረጅና ማጥቃት ተገቢ አይደለም። የትግራይ ህዝብ መታገዝ መደገፍ የሚገባው ህዝብ እንጂ ተደምሮ የሚፈረጅ አይደለም። ደሃ ነው፤ ...ምንም የለውም። ጥፋት እንኳን ቢኖር ይቅርታ ያስፈልጋል፡፡

~ የፊዴራሊዝም ስርዓቱ ትላልቅ ችግርን እንጂ ትንንሽ ችግሮችን ማቆም አይችልም፡፡

~ በምስራቅ አፍሪካ ያለው ድንበር በቅኝ ገዥዎች የተሰራ በመሆኑ "አርቲፊሻል" ነው። በቅኝ ገዥዎች ፍላጎት የተሰራ ነው። የኬኒያ፣ ኦሮሞ እና የቦረና ኦሮሞ በሁለት ሀገር ይኖራሉ። በትግራይም ተመሳሳይ ነው። ተመሳሳይ ባህል ያላቸው ሀገራት ሁለት ሀገር ሆነዋል።

~በአብሮነታችን ለቀጣዩ ትውልድ ፍቅርን እናወርሳለን፡፡ ሰው ሲፈታ አይናችን የሚቀላ በቀለኞች አንሁን፡፡ ኢትዮጵያ በቂ ሀገር ናት፡፡ ጠንካራ ተቋም እናቋቁማለን፡፡

~የአማራ እና የትግራይን፤ የኦሮሞ እና የደቡብ ወሰን ጉዳዮችን በዘላቂነት እንመልሳለን፡፡

 

 

ኢኮኖሚ

~ርዕዮተዓለም ልማታዊ መንግስታት ወደ ካፒታሊስት ስርዓት የሚያደርስ መንገዶች እንጂ ልማታዊ መንግስት በራሱ ውጤት አይደለም፡፡ ፍላጎታችን ገበያ መር ካፒታሊስት ስርዓት መገንባት ነው፡፡ የመንግስት ፍትሃዊ ጣልቃገብነት ባማከለ መንገድ የግል ባለሃብቱን እያሳተፍን እንቀጥላለን፡፡

~የግል አዋጭነት ስላለው የግል ባለሃብቱን እናጠናክራለን፡፡ በመንግስት የተያዙ ሃብቶች ለግሉ እየተሰጡ ይሄዳሉ፡፡ ከ 25 ዓመት በፊት ቡና በመንግስት ብቻ ነበር፡፡ አሁን በግል ሆኗል፡፡ ይቀጥላል፡፡ የመንግስት ሞኖፖሊ ሊቀር ይገባል ሲሉ ከህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ኢኮኖሚው ጋር ተያይዞ ለቀረበላቸው ጥያቄ መልሰዋል፡፡

~ከመንግስት ወደ ግል ዝውውር ሲሰራ በጥናት ላይ ተመስርቶ ነው፡፡ የተሸጡ የመንግስት ሃብቶች ከዚህ ቀደም ያለውድድር የነበሩ ስለሆነ አላደጉም፡፡ አሁን ሁሉም ሃብቶች በውድድር ይሆናሉ፡፡ የቴሌኮም ገቢ ከውጭ ገቢ አላደገም፡፡ የሃብት ብክነትም አለ፡፡ ኔትውርክም ጥራት የለውም፡፡ 12 ሚሊየን ህዝብ ያላት ሶማሊያ እንኳን ትበልጠናለች፡፡ ስለዚህ በውድድር ለግሉ ዘርፍ እንሰጣለን፡፡ በአንዴ ሳይሆን በጥናት ተመስርተን የቴሌኮሚኒኬሽን ጉዳይ እልባት እንሰጣለን፡፡

~ከኃይል አቅርቦት አንጻር ህዘቡ መብራት እያገኘ አይደለም፡፡ መንግስት ብቻውን አይሰራውም፡፡ የግል ባለሃብቱ ሊሳተፍበት ይገባል፡፡ 35 ከመቶ ኃይል በትራንስፖርት ይባክናል፡፡ ስለዚህ ኃይል በአካባቢ እንዲሰራጭ ይደረጋል፡፡ ኃይል በአካባቢ ከሆነ ስርጭቱም ፍትሃዊ ይሆናል፡፡

~የአፍሪካ መሪዎች ኢትዮጵያን ጨምሮ የአፍሪካ አየር መንገድ አንድ እንዲሆን ተፈርሟል፡፡ የኢትዮጵያ አየር መንገድ በአፍሪካ የብዙ ሀገራትን ገዝቷል፡፡ ስለዚህ መንግስት ብቻውን መያዝ የለበትም፡፡ የግል ባለሃብቱም መጠቀም አለበት፡፡ ይህ ለተጨማሪ ትርፍ ይጠቅመናል፡፡ ስራችንንም ያቀላጥፍልናል፡፡

~መርከቦቻችን ቁመው ነው የሚውሉት፡፡ ጎረቤት ሀገራት ይበልጡናል፡፡ ወደ ኋላ መቅረት የለበትም፡፡ የሎጂክስትስ ስራችን ኋላቀር ነው፡፡ ከዓለም 160ኛ ነን፡፡ መርከቦቻችን ቁመው ነው የሚውሉት፡፡ ጎረቤት ሀገራት ይበልጡናል፡፡ ወደ ኋላ መቅረት የለበትም፡፡ የሎጀስቲክስ ዘርፉ ካልተስተካከለ ፈጣን ኢኮኖሚን መሸከም አንችልም፡፡ የውጭ ምንዛሬን ለማስተካከልም የሎጂስቲክስ ዘርፉ ለግል ባለሃብቱ ይሠጣል፡፡

~ የኢኮኖሚ ማሻሻያው ያስፈለገው የውጭ ብድር ለመክፈል፤ የሚዘገዩ ፕሮጀክቶችን ቶሎ ለመጨረስ፤ የስራ እድል ለመፍጠር። የገቢ ስራዓትን ለማዘመን አስፈላጊ በመሆኑ ነው።

~ በትንሽ ብር የጀመርነው ፕሮጀክት ከእጥፍ በላይ እየሆነ ነው። ለዚህም ነው የግሉን ዘርፍ ማሳተፍ የተፈለገው። የመንግስት ሞኖፖሊ ሊቀር ይገባል። ኔትወርክም ጥራት የለውም።

~ 12 ሚሊየን ህዝብ ያላት ሶማሊያ አራት የቴሌኮም ኩባንያ ሲኖራት እኛ ግን 100 ሚሊየን ህዝብ ይዘን ያለን ኩባንያ አንድ ብቻ ነው።

~የትምህርት ፍኖተ ካርታ ተዘጋጅቷል፡፡ በጥናት እየተሰራ ነው፡፡

~የኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶች ገቢ በ7 ነጥብ 7 ቢሊየን ወርዷል፡፡ የውጭ ምንዛሬውም ቀንሷል፡፡ በመሆኑም ጥቁር (የጓዳ) ገበያውን እንቆጣጠራለን፡፡

~የሚላኩ ምርቶች እንጨምራለን፡፡ የሀገሪቱ የውጭ እዳ ከ 24 ቢሊየን ዶላር በላይ ደርሷል፡፡ በቀጣይነት የማሻሻያ ስራዎች ይሰራሉ፡፡ ፕራይቬታይዤሽን አንዱ መንገድ ነው፡፡

 

የኢትዮ-ኤርትራ ጉዳይ፣

~ የአልጀርስ ስምምነት በፓርላማው ቀድሞ የጸደቀ ነው። ለአፍሪካ መሪዎችም ደርሷል። ዓለምም ያውቀዋል። መሆን የማይገባው ጦርነት አድርገናል። አስከፊ ጦርነት ነው። ጦርነት እያስታመምን አንኖርም።

~ ጦርነት አቁሙ ሲባል እያለቀሱ ከተመለሱት አንዱ እኔ ነኝ... ስሜቱን አውቀዋለሁ። እናቴ ያሳደገችው የወንድሜን ልጅ ባድሜ ላይ ነው ያጣሁት.... ወንድሜን ገብሬበታለሁ። ብዙ ጓደኞቼን ቀብሬ አልፌያለሁ። ስሜቱን አውቀዋለሁ፤ ነገር ግን የአልጀርሱን ስምምነት ያጸደቃችሁት እናንተ [የህዝብ ተወካዮች ምከር ቤት አባላት] ናችሁ። ቃለጉባኤውን ማየት ይቻላል። እኛ አዲስ ነገር አላመጣንም።

~የባድመ ጉዳይ አዲስ አይደለም። አስፈጽሙ ያላችሁንን ነው እያስፈጸምን ያለነው...

~ የድብቅ ፖለቲካ ካሁን በኋላ በቃ። የሥራ አስፈጻሚው ውሳኔ ለህዝባችን ቶሎ መስማት አለበት። ከህዝባችን የሚደበቅ ነገር የለም።

~ ደቡብ እና ሰሜን ኮርያ አንድ እየሆኑ ነው። ኤርትራ እና ኢትዮጵያም መቀራረብ አለባቸው። ለብሄራዊ ጥቅም እንተጋለን። የኤርትራ ህዝብ ወንድማችን ነው። ህዝብ ጠይቋል። ስለዚህ የተመለሰው የህዝብ ጥያቄ ነው።

 

ሚዲያ

~ ተዘግተው የነበሩ ድረ-ገጾች ተከፍተዋል። እንዳይጽፉ ተከልክለው የነበሩ አምደኞች በነጻነት እንዲጽፉ ለማድረግ ስራ ተሰርቷል።

ሚዲያዎች የህዝብ ድምጽ እንዲሆኑ የተጀመረው ስራ ተጠናክሮ ይቀጥላል። በቀጣይ የህዝብ ድምጽ እንዲሆኑም እንሰራለን።

 

ሙስና

~ መጠኑ ይስፋም ይነስ እንጂ ሌብነት ከጫፍ እስከ ጫፍ አለ። በሃይማኖት ተቋማት፣ በትምህርት ተቋማት፣ በመንግስት ተቋማት አለ። ማሰር የማይችል መንግስት አድርጎ የሚያስበን ሰው አለ፤ ግን ማሰር ከአባቶቻችን ጀምሮ ነበር፤ አዲስ ነገር አይደለም፤ እጃቸውን መሰብሰብ ያለባቸው ግን አሉ።

~ ሃብት የዘረፉ ሰዎች ኢትዮጵያ ውስጥ አሉ። ሌቦች አሉ። ሌቦች እንዳልታወቀባቸው ነገር እየሸረቡ ነው። እርምጃ እንወስዳለን። ስርዓቱ እኩል አይን የለውም። አጣርተን እናስራለን እንጂ አስረን አናጣራም።

~ ሙስና አምስተኛው መንግስት ነው የሚባለው የተደራጀ መዋቅራዊ ቡድን በመሆኑ ነው። መዋቅራዊ በመሆኑ በመገናኛ ብዙኃን ጭምር በመታገዝ ልንታገለው ይገባል።

~ የመንግስት ባለስልጣን በስራ ላይ እያለ ነጋዴ፣ ሀብታም መሆን አይችልም፤ ነጋዴ፣ ሀብታም መሆን ካማረው ቢሮውን ለቆ መሄድ አለበት።

 

ፖለቲካና ሌሎች

~የፖለቲካ ምህዳሩን ለማስፋት አስረኞች ተለቀዋል፡፡ ከውጭ ያሉትም ገብተዋል፤ እየገቡም ነው፡፡ የሚዲያ ነጻነት እንዲረጋገጥ የኢንትርኔት ጸኃፊዎች ነጻነት እየተረጋገጠ ነው፡፡ በቀጣይም ጠንክረን እንሰራለን፡፡ ነጻ ሚዲያ እንፈጥራለን፡፡ የፍትህ ህግ ማሻሻያ አዲስ ማዕቀፍ መርሃግብር ተዘጋጅቷል፡፡ የፍትህ ስራዓቱ ላይ ፍተሸ ይደረጋል፡፡ የኢኮኖሚ አሻጥርን ለማስቀረት ኢኮኖሚው ላይ ይሰራል፡:

~ የዲሞክራሲ ምንጩ ህዝብ ነው፣ ጸረ ዴሞክራሲ ከሆነ ግን መንግስት ህግን ማስከበር ግድ ይላል። ህግ አስከባሪዎችን ጠላት አድርጎ ማሰብ ተገቢ አይደለም።

~ መከላከያንም ማንም ዜጋ አይቶ መገምገም አለበት፤ መከላከያ በትንሽ ገንዘብ ህይወታቸውን የሚሰጡበት ቦታ እንጂ የሚፈራ አጥር አይደለም።

~ በውስጥ ያለ ፍቅር ለአገር ብቻ ሳይሆን በዓለም እንደመጣለን። ወደ ደቡብ ዛሬ ሂደን ነገ እናወያያለን። ኦሮሞ ከሶማሊያ፣ አማራ ከትግራይ ጋርም አለመግባባት አለ። እንፈታለን። እንደመር። እንወያያለን።

~ለብሄራዊ ጥቅም እንተጋለን፡፡ የኤርትራ ህዝብ ወንድማችን ነው፡፡ ህዝብ ጠይቋል፡፡ ስለዚህ የተመለሰው የህዝብ ጥያቄ ነው፡፡ የድበቃ ፖለቲካ ካሁን በኋላ በቃ፡፡ የሥራ አስፈጻሚው ውሳኔ ለህዝባችን ቶሎ መስማት አለበት፡፡

~ለኢትዮጵያ እኛ ብቻ አይደለንም የምንቆረቆር፤ ሁሉም ይቆረቆራል፡፡

~ኤርትራ ያላችሁ ሁሉ ወደ ሀገራችሁ ግቡ፤ እንደራደራለን፡፡

~የግንቦት ሰባት፤ የኦነግ፣ የኦብነግ ሰዎች በይቅርታ እንገናኝ፤ የትጥቅ ትግል አሮጌ ፋሽን ነው፡፡

~የቂም በቀል ፖለቲካ ይቁም፡፡ ኢህአዴግ ይቅርታ ጠይቋል፤ ህዝቡም ይቅር ብሎናል፤ ህዝቡ እኛን ማሰር ነበረት፡፡ በይቅርታ አልፎናል፡፡ ስለዚህ ይቅርታ ነው፡፡ እኛም ይቅር ብለናል፡፡

~ሶማሊያ እና ኢትዮጵያ ወደ አንድ ሀገርነት ልንመጣ ነው፡፡ ትልቅ ሀገር ለመሆን በጋራ እንደመራለን፡፡ ትንንሽ ደሃ ሀገር መሆን የለበትም፡፡¾

የብሄራዊ የፕላን ኮሚሽን ኮሚሽነር ዶክተር ይናገር ደሴ እንደሚሉት፣ ባለፉት ጥቂት አመታት ወደ ውጭ ከተላኩ ምርቶች የሚገኘው ገቢ በአማካይ 3 ቢሊየን የአሜሪካ ዶላር ላይ ሲቆም፣ ከውጭ ምርቶችን ለማስገባት የሚወጣው የውጭ ምንዛሪ ደግሞ ከ16 እስከ 17 ቢሊየን ዶላር ደርሷል። ስለዚህም፣ የሃገሪቱ ኢኮኖሚ በውጭ ንግድ መዳከም እና በውጭ ምንዛሪ እጥረት ሳቢያ አደጋ ውስጥ መግባቱ ተከትሎ የኢሕአዴግ ሥራአስፈፃሚ የፕራይቬታይዜሽን ውሳኔ ላይ ደርሷል።

ዶክተር ይናገር ደሴ “በተለይ” አሉ፣ “እንደ ስኳር ላሉ ፕሮጀክቶች የተወሰደው ብድር ደግሞ ወደ ምርት ሳይገባ እዳ መክፈያው ጊዜ ደርሷል” ብለዋል። ማን እዚህ ደረጃ ላይ እንዳደረሰው የሰጡት ዝርዝር መግለጫ የለም።

የኢትዮጵያ ስኳር ኮርፖሬሽን የሥራ ኃላፊዎች ግንቦት 1 ቀን 2008 ዓ.ም በ2008 የበጀት ዓመት የዘጠኝ ወራት የሥራ አፈጻጸም ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ለመንግሥት ልማት ድርጅቶች ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ባቀረቡት ሪፖርት፣ ተስፋ ቆርጠናል፤ ሕመም እየተሰማን ነው፤ ማለታቸው የሚታወስ ነው።

የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ኃ/ማሪያም ደሳለኝ በበኩላቸው፤ “ኢትዮጵያ በዘረጋችው መጠነ ሰፊ የስኳር ልማት መንግስት ትምህርት አግኝቶበታል” ከማለታቸው ውጪ ተጠያቂ ያደረጉት፤ የፓርቲም የመንግስትም ኃላፊ የለም። ቀጫጭን ኃላፊዎችን ለመጠየቅ የተደረገው ሙከራ እንደተጠበቀ መሆኑን፤ ልብ ይሏል።

በጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አሕመድ የሚመራው የኢትዮጵያ መንግስትና ገዢው ፓርቲ የስኳር ልማት ፕሮጀክቶችን ሙሉ ለሙሉ ወደ ግሉ ባለሃብት ልናሸጋግረው ነው፤ የሚል መግለጫ ባሳለፍነው ሳምንት ከማውጣታቸው ውጪ፣ ለስኳር ልማቱ ክሽፈት ተጠያቂ ስለሚሆኑ የመንግስትና የፓርቲ ኃላፊዎች ያሉት እንዳች ነገር የለም።

ሰነዳቸው እንደሚለው፣ በልማታዊ መንግስት ፖለቲካ ኢኮኖሚ፣ የግል ባለሃብቱ ሊሰማራባቸው በማይችሉ የልማት ፕሮጀክቶች ላይ መንግስት ጣልቃ እየገባ እንደሚያለማቸው በስፋት ሲናገሩ፤ አዳምጠናል። እንዲሁም መንግስት ከልማቱ ከሚያገኘው ትርፍ ጤነኛ ኪራይ በማደል ባለሃብቱና ዜጎችን የማብቃት ሥራዎች እንደሚሰራም፤ የገዢዎቹ ሰነድ ያሳያል።

መሬት ላይ ያለው እውነት እንደሚያሳየው፤ ገዢው ፓርቲና መንግስት በስኳር ልማቱ ከሽፈው፤ የግሉን ባለሃብት ሳያበቁ፤ ለልማቱ የተመደበውን የህዝብ ገንዘብ ለተመደበለት ዓላማ መዋል አለማዋሉን በሕግ የበላይነት ሳይዳኙ፤ የህዝብ ሃብት ወደ ግል ለማዞር ከውሳኔ ላይ ደርሰዋል። ምን ያህል ይሳካላቸዋል ወደፊት የምናየው ነው።

እኛ ጥያቄ ግን አለን? ይኸውም፣ ኮርፖሬሽኑ ኃላፊዎች በሪፖርታቸው እንዳስገነዘቡት፣ ኮርፖሬሽኑ ፋብሪካዎቹን ገንብቶና ምርት ኤክስፖርት በማድረግ ዕዳውን የመክፈል ኃላፊነቱን አልተወጣም። የአገሪቱን የስኳር ፍላጎት ማሟላት አልቻለም፤ ግንባታዎቹን ለማከናወን 77 ቢሊዮን ብር የውጭና የአገር ውስጥ ብድር ተብድሯል፤ አንድም ፋብሪካ ወደ ምርት ማስገባት አልቻለም፤ በየአመቱ 13 ቢሊዮን ብር ዕዳ ለመክፈል ተዘጋጅቷል። በዚህ የክሽፈት ሒደት ውስጥ ኃላፊነት መውሰድ ያለባቸውን አካሎች በሕግ የበላይነት መጠየቅ ያልቻለ ገዢ ፓርቲ፤ እንዴት የህዝብ ሃብቶችን በአክሲዮን ድርሻ በማዘዋወር ልማት ሊያረጋግጥ ይችላል? እምነት እንዴት ይጣልበታል? ለሚሉት ከመንግስት ምላሽ የሚሹ ናቸው።

ለመንግስት ምላሽ እንዲሰጥባቸው የስኳር ልማቱን ተጠያቂነት መልክ ባለው ሁኔታ ማስቀመጡ ተገቢ ነው። ይኸውም፣ የመጀመሪያው ውድቀትና ተጠያቂነት የሚጀምረው፣ የተንዳሆ ስኳር ፋብሪካ ተከላ ግንባታዎች፣ የእርሻና የመስኖ ልማቶችን የተመለከተ ነው። ሁለተኛው፣ አስሩ አዳዲስ የስኳር ፋብሪካዎች ግንባታ በተመለከተ ሲሆን፤ ሶስተኛው ከስኳር ልማት ፈንድ ጋር በተያያዘ መተሐራ ስኳር ፋብሪካ፣ ወንጂ ስኳር ፋብሪካና በፊንጫ ስኳር ፋብሪካዎችን ላይ ያስከተለው አሉታዊ ጫናዎችን የሚመለከት ነው።

 

 

በ“ልማታዊ መንግስት” አስተሳሰብ፣

የተንዳሆ ስኳር ፋብሪካ ታሳቢዎች

 

የተንዳሆ ስኳር ፋብሪካው በ “ልማታዊ መንግስታችን” ተጠናቆ ወደ ሥራ ገብቶ ቢሆን ኖሮ፣ በቀን 26ሺ ቶን አገዳ የመፍጨት እና በአመት ከ600ሺ ቶን ስኳር የማምረት አቅም ይኖረው፤ ነበር። ከስኳር ምርት በተጨማሪ፣ በአመት 55 ነጥብ 4 ሚሊዮን ሊትር ኢታኖል የማምረት አቅም ይኖረው፤ ነበር። በተጓዳኝም የተሰራው ግድብ ለመስኖ ስራዎች ልማት፣ ለእንስሳ፣ ለዓሣ እርባታ እና ከብቶች ለማድለብ አገልግሎት ላይ ይውል፤ ነበር። ከኃይል አቅርቦት አንፃር 120 ሜጋ ዋት የኤሌክትሪክ ኃይል የማመንጨት አቅም ይኖረው፤ ነበር።

ከሰው ኃይል አንፃር በመጀመሪያው የፋብሪካ ግንባታ 35ሺ ሠራተኞች፤ በሁለተኛው የፋብሪካ ግንባታ ሲጠናቀቅ ተጨማሪ 35ሺ ሠራተኞች በአጠቃላይ በስኳር ልማቱ ዘርፍ 70ሺ ሠራተኞች እንደሚኖሩት ይጠበቅ፤ ነበር። የተንዳሆ ስኳር ልማትን በበላይነት ይመሩ የነበሩት፤ የንግድ እና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር የቀድሞ ሚኒስትር አቶ ግርማ ብሩ እና ፕሮጀክቱን በማስፈጸም የቀድሞ የስኳር ድጋፍ ሰጪ ኤጀንሲ ዋና ዳሬክተር የነበሩት፣ አቶ በላይ ደቻሳ ናቸው። የመስኖና ውኃ ሥራዎቹን በበላይነት ይመሩ የነበሩት፣ አቶ አስፋው ዲንጋሞ በኋላ ደግሞ አቶ አለማየሁ ተገኑ ነበሩ።

የተንዳሆ ስኳር ፋብሪካ የውድቀት ሂደቶች በተመለከተ በሰንደቅ ጋዜጣ ቁጥር 558 በስፋት ያቀረብነው ቢሆንም፣ የተጨመቀው ዝርዝር ይህንን ይመስላል። የኢትዮጵያ መንግስት እ.ኤ.አ በኦክቶበር 2006 በቀድሞው የስኳር ድጋፍ ሰጪ ኤጀንሲ በኩል በአፋር ክልል ውስጥ አዲስ የስኳር ፋብሪካ ለመገንባት እንዲሁም በነባሮቹ ወንጂ እና ፊንጫ ስኳር ፋብሪካዎች የማስፋፊያ ስራዎች ለመገንባት ዓለም ዓቀፍ ጨረታ ማውጣቱ የሚታወቅ ነው።  

የሕንድ መንግስት ለተንዳሆ አዲስ ስኳር ፋብሪካ ግንባታ እና ለወንጂ እና ለፊንጫ ስኳር ፋብሪካዎች ማስፈፊያ 640 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር ብድር ፈቅዷል። ከተፈቀደው ብድር ጋር በተያያዘ ከአጠቃላይ የፋብሪካው ግንባታ እና ከፋብሪካዎቹ ማስፋፊያ ሥራዎች ውስጥ 85 በመቶ የሚሆነውን በሕንድ ኩባንያዎች እንደሚገነቡ በብድር ውሉ አስፍሮ ነው፣ ያበደረው። በጨረታውም፣ ከሃያ የሚበልጡ የህንድ ኩባንያዎች ተሳታፊ ነበሩ።

እ.ኤ.አ. በ2008 በይፋ የተንዳሆ ፋብሪካ ተከላ ለአሸናፊው ኦቨርሲስ ኢንፍራስትራክቸር አሊያንስ ኃላፊነቱ የተወሰነ ኩባንያ የተሰጠ ቢሆንም፣ በ2010 “ልማታዊ መንግስታችን” ለመረከብ ተዘጋጅቶ የነበረ ቢሆንም፤ ወፍ የለም።

የጨረታው አሸናፊ ከታወቀ በኋላ፣ በተደረገው ስምምነት የተፈቀደው ብድር ከተለቀቀበት ቀን አንስቶ በቀጣይ 30 ቀናቶች ውስጥ የተንዳሆ ስኳር ፋብሪካ ግንባታ እንደሚጀመር ተገልጿል። የፋብሪካው ግንባታ በሁለት ዙር ተከፍሎ እንደሚከናወንም መገለፁ የሚታወስ ነው። የመጀመሪያው የፋብሪካው ምዕራፍ ግንባታ በ2 ዓመት ውስጥ ይጠናቀቃል፤ የሁለተኛው የፋብሪካው ምዕራፍ ግንባታ ደግሞ የመጀመሪያው የፋብሪካው ግንባታ በተጠናቀቀ በቀጣዩ አንድ ዓመት ውስጥ ሙሉ ለሙሉ ተጠናቆ ወደ ስራ እንደሚገባ ተገለፆም ነበር፤ ነበር ሆኖ ቀረ እንጂ።

በተደጋጋሚ የሚመለከታቸውን መንግሥታዊ ተቋማት ስለ ተንዳሆ ስኳር ፋብሪካ የመጀመሪያው የጨረታ አሸናፊው ውጤት ለምን እንደተሰረዘ ጠይቀን እስካሁን ምላሽ፤ የሰጠን የለም። ለስኳር ፋብሪካ ተከላ የሚሆኑ ማሽነሪዎችን የሚያመርቱ ኩባንያዎች እያሉ፤ በምን አግባብ “trading house” ለሆነ ኩባንያ ጨረታው እንደተሰጠ እስካሁን ምላሽ፤ የለም። በጨረታው የተሳተፉት የህንድ ኩባያዎች በሀገራቸው ፍርድ ቤት ተካሰዋል። በሕንድ ፍርድ ቤት የተደረገው የክርክር መዝገብ ብዙ አመላካች ነገሮች ቢኖሩትም የተመለከተው የለም። ለጨረታ አሰጣጡ በተፈጠረ የፍርድ ቤት ክርክር የኢትዮጵያን መንግስት ከፍተኛ ዋጋ አስከፍሏል። ይህም ሲባል፣ እ.ኤ.አ. ከ2008 እስከ 2010 በተከራካሪ ወገኖች በሕንድ ፍርድ ቤት በተደረገው ክርክር በተንዳሆ ስኳር ፋብሪካ ተከላ ዋጋ ላይ ከፍተኛ ለውጥ አስከትሏል።

ይኸውም፣ እ.ኤ.አ. በ2008 በሕንድ እና በኢትዮጵያ መንግስት የተንዳሆ ፋብሪካ ተከላ በተመለከተ የብድር ስምምነት ሲያደርጉ፣ የአንድ አሜሪካ ዶላር በኢትዮጵያ ብር የሚመነዘረው 9 ብር ከ50 ሣንቲም የነበረ ሲሆን፤ በሕንድ ፍርድ ቤት የነበረው ክርከር ሲጠናቀቅ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ በሴፕቴምበር 1 ቀን በ2010 በሰጠው አዲስ የገንዘብ ምንዛሪ ተመን ለውጥ፤ የአንድ አሜሪካ ዶላር በኢትዮጵያ በ13 ብር ከ75 ሣንቲም ብር እንደሚመነዘር አስታውቋል። ከዚህ የገንዘብ ምንዛሬ ለውጥ ጋር በተያያዘ የተንዳሆ ፋብሪካ ተከላ ዋጋም በከፍተኛ ዋጋ እንዲንር ምክንያት ሆኗል።

ሌላው የምናቀርበው ጥያቄ፣ የመጀመሪያው ምዕራፍ የተንዳሆ ስኳር ፋብሪካ ተከላ ውጤታማ ሳይሆን ለሁለተኛው ምዕራፍ ተከላ ክፍያ የፈቀደው አካል ማነው? የስኳር ኮርፖሬሽኑ የስራ ኃላፊዎች ጥቅምት 19/03/07 ለኢንዱስትሪ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ባቀረቡት፣ የ2007 ዓ.ም. የነባር ፕሮጀክቶች ፊሲካል እቅዶች አንዱ ተንዳሆ ስኳር ፋብሪካ ፕሮጀክትን የተመለከተ ነበር። ባቀረቡት በሰነዱ ላይ እንደሰፈረው፣ የተንዳሆ ስኳር ፋብሪካ የመጀመሪያ ምዕራፍ ግንባታ (13,000 ቶን በቀን) በነሐሴ ወር 2007 ዓ.ም ጀምሮ ማምረት እንደሚጀምር፤ ይተርካል።

ሪፖርቱ አያይዞም፣ የተንዳሆ ስኳር ፋብሪካው ሁለተኛ ምዕራፍ ግንባታ ማናቸውም አስፈላጊ ቅደመ ክፍያዎች ለዋናው ኮንትራክተሩ መከፈላቸውን፤አስቀምጧል። በመጀመሪያው ምዕራፍ ወቅት ለቀጣዩ ምዕራፍ ግንባታ አስፈላጊው ዝግጅት በመደረጉ ይላል ሪፖርቱ፤ ሥራው በ2007 ዓ.ም የካቲት ወር ተጠናቆ መጋቢት 2007 ዓ.ም. ምርት እንዲጀምር፤ ያትታል።

እንዲሁም ሪፖርቱ፣ የመስኖ ግንባታና አገዳ ተከላ በተመለከተየተንዳሆ ስኳር ፋብሪካ የመጀመሪያ ምዕራፍ 13,000 ቶን በቀን የመፍጨት አቅም ስላለው ይህን የሚመጥን 25,000 ሔክታር ላይ በመስኖ የሚለማ አገዳ ተክል ሽፋን ስለሚጠይቅ፣ ኮንትራክተሩ የውሃ ሥራዎች ኮንስትራክሽን ድርጅት በ2007 ዓ.ም. የልማት ዘመን የመጀመሪያውን ምዕራፍ 25,000 ሔክታር ያላለቁ የመስኖ መሰረተ ልማት አጠናቆ ያቀርባል። በተጨማሪም የ18,000 ሔክታር የጥናትና ዲዛይን ስራ ይሰራል፤ ይላል። በተያያዘም አገዳ ተከላ በተመለከተ የ2006 ተከላ እስከ ሰኔ ወር መጨረሻ ሽፋኑ 18ሺ479 ሔክታር ደርሷል ይላል። እንዲሁም የአገዳ ተከላ በበጀት ዓመቱ (በ2007 ዓም.) 10ሺ 521 ሔክታር አገዳ ይተከላል ሲል ሰነዱ ያትታል። በተግባር የቀረበ የምርት ውጤት ግን የለም።

ጥያቄያችን፤ ለገዢው ፓርቲና ለኢትዮጵያ መንግስት፤ ኦቨርሲስ ኢንፍራስትራክቸር አሊያንስ ኩባንያ የተንዳሆ ስኳር ፋብሪካ የመጀመሪያ ምዕራፍ የፋብሪካ ተከላ ሥራውን እጅግ በወረደ አፈፃጸም ማከናወኑ እየታወቀ፣ ሁለተኛውን የተንዳሆ ፋብሪካ ተከላ ምዕራፍ ግንባታ እንዲያከናውን እንዴት ተፈቀደለት? ክፍያውስ እንዴት ተፈጸመ? በወቅቱ የነበረው 18ሺ 479 ሔክታር አገዳ የት አደረሳችሁት? ተጨማሪ ተተክሎ የነበረው 10ሺ 521 ሔክታር አገዳውስ ምን በላው?

ሌላው፤ በልማታዊ መንግስት ፖለቲካ ኢኮኖሚ መስመር ውስጥ ለማሳካት ያቀዳችሁት 600ሺ ቶን ስኳር፣ 55 ነጥብ 4 ሚሊዮን ሊትር ኢታኖል፣ 120 ሜጋ ዋት ኤሌክትሪክ፣ 70ሺ የሥራ እድል ፈጠራ እንደነበር ይታወቃል። የተፈለገው ውጤትም አልተላከም። ከዚህ አንፃር ገዢው ፓርቲ የልማታዊ መንግስት ተልዕኮን በመጨረስ ወደ ካፒታሊዝም እየተሸጋገረ ነው ተብሎ መውሰድ ይቻል ይሆን? ከአፈፃፀሙ አንፃር የሕዝብ ሃብቶችን ወደ ግል ይዞታ በማዘዋወር ይገኛል የሚባለው ውጤት እንዴት ይታያል?

የሕንድ ፓርላማ ልዑካን በተንዳሆ ስኳር ፋብሪካ አፈፃጸም ያሉትን መመልከቱ ጥሩ ነው። የፓርላማው አባላት ባቀረቡት ሪፖርት፣ የተንዳሆ ስኳር ፋብሪካ ተከላ የስራ አፈፃፀም ከሚጠበቀው በታች የወረደ በመሆኑ እሬታቸውን አቅርበዋል። አያይዘውም፣ ሕንድ በአፍሪካ ውስጥ ከቻይና ጋር ለምታደርገው የኢኮኖሚ ፉክክር በተንዳሆ ስኳር ፋብሪካ ግንባታ ላይ የታየው የአፈፃፀም ደካማነት የራሱ የሆነ አሉታዊ ተፅዕኖ ሊያሳድር እንደሚችል ያላቸውን ከፍተኛ ስጋት፤ ለመንግስታቸው አስታውቀዋል።

አስሩ ስኳር ፋብሪካዎችን በተመለከተ

የኢትዮጵያ ስኳር ኮርፖሬሽን የሚያስተዳድራቸው የስኳር ልማት ፕሮጀክቶች፤በደቡብ ኦሞ ዞን ኩራዝ አንድ፣ ኩራዝ ሁለት፣ ኩራዝ ሦስት፤ በአማራ ክልል በለስ አንድ፣ በለስ ሁለት፤ በአፋር ክልል ተንዳሆ አንድና ሁለት፤ በትግራይ ክልል ወልቃይት፤ በኦሮሚያ ክልል በአርጆ ደዴሳ የስኳር እና ከሰም ፕሮጀክቶች ናቸው። ይህንን የስኳር ልማት ተልዕኮ ለማስፈፀም በኃላፊነት ተቀምጠው የነበሩት አቶ አባይ ፀሐዬ፣ አቶ ሽፈራው ጃርሶ እና አቶ ወንድአወቅ አብቴ ናቸው።

በጥቅምት 19/02/07 የስኳር ኮርፖሬሽን ኃላፊዎች ለኢንዱስትሪ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ባቀረበው ሪፖርት ላይ ስለ ፋብሪካዎቹ ግንባታዎች ዝርዝር መረጃዎች ማስፈራቸው የሚታወስ ነው።

ያቀረቡት ሰነድ እንደሚያሳየው፣ የፋብሪካ ግንባታ የ2007 በጀት ዓመት ከስኳር ልማት ፈንድ እና ከአገር ውስጥ ብድር የተያዘ በጀትን በሚመለከት በሜቴክ እየተሰሩ ላሉት የበለስ አንድ እና ሁለት ብር 4 ነጥብ 26 ቢሊዮን፣ ለኩራዝ አንድ ብር 2 ነጥብ 30 ቢሊዮን በድምሩ ብር 6 ነጥብ 56 ቢሊዮን እንዲሁም ለተንዳሆ ምዕራፍ ሁለት ስኳር ፋብሪካ ግንባታ ብር 290 ነጥብ 76 ሚሊዮን፣ ለከሰም ብር 562 ነጥብ 5 ሚሊዮን፣ ለወንጂ ማስፋፊያ ፕሮጀክት ቀሪ ክፍያ ብር 608 ነጥብ 33 ሚሊዮን እና በውለታ መሰረት የሚከፈል ለመለዋወጫ የሚከፈል ብር 1756 (15 ነጥብ 6 USD) ሚሊዮን ብር፤ 7 ነጥብ 2 ቢሊዮን የተጠየቀ ሲሆን፤ ብር 1 ነጥብ 94 ቢሊዮን በበጀት ዓመቱ መያዙን ገልጿል።

ኮርፖሬሽኑ በዚሁ መሰረት ይላል፣ ለበለስ አንድ እና ሁለት ብር 792 ሚሊዮን፣ ለኩራዝ አንድ 300 ሚሊዮን፣ ለተንዳሆ ብር 290 ነጥብ 76 ሚሊዮን እንዲሁም ለከሰም ብር 562 ሚሊዮን ብር እንዲያዝ ተደርጓል። እንዲሁም በውጭ ብድር ለሚገነቡት ለወልቃይት ብር 4 ነጥብ 4 ቢሊዮን፣ ለኩራዝ 2 እና 3 ብር 4 ነጥብ 3 ቢሊዮን እና ለተንዳሆ ምዕራፍ ሁለት ፋብሪካ ግንባታ ብር 2.2 ቢሊዮን ጨምሮ በድምሩ ብር 12.9 ቢሊዮን ለፋብሪካ ግንባታ ተይዟል።

የነባር ፋብሪካዎች እና አዳዲስ ለሚገነቡ ፋብሪካዎች ለአማካሪ የሚከፈል ክፍያን በተመለከተ ለነባር ፋብሪካዎች የውጭ አማካሪዎች ብር 97 ነጥብ 7 (4 ነጥብ 89 USD) ሚሊዮን፣ አዳዲስ ለሚገነቡ ፋብሪካዎች ብር 120.98 (6 ነጥብ 04 USD) ሚሊዮን እንዲሁም ለአገር ውስጥ አማካሪዎች ብር 6 ነጥብ 11 ሚሊዮን በድምሩ ብር 208.12 ሚሊዮን ብር ለውጭ እና ለአገር ውስጥ አማካሪዎች የተፈቀደ ሲሆን፤ ይህም ከስኳር ልማት ፈንድ ከሚገኝ ገቢ እንደሚሸፈን ታሳቢ ተደርጎ የተያዘ መሆኑን ጠቁሞ፤ በጀቱ በዋና መ/ቤት በኩል እንዲያዝ ተደርጓል ይላል።

እንዲሁም በብረታ ብረት ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን አማካኝነት የሚገነባው የኦሞ-ኩራዝ ቁጥር 1 ስኳር ፋብሪካ መስከረም ላይ ተጠናቆ ህዳር 2007 ምርት ማምረት ይጀምራል ይላል። የኦሞ ኩራዝ 2 ፋብሪካ የፕሮጀክት ማስፈፀሚያ ፋይናንስ ከቻይና ልማት ባንክ በብድር effective ሆኖ የመጀመሪያው ቅድመ ክፍያ በ2006 በጀት ዓመት መጨረሻ ላይ የተፈፀመ ስለሆነ በዚህ አግባብ ሁለቱም ፋብሪካዎች በ24 ወራት እንዲጠናቀቁ የታቀደ ስለሆነ፤ በበጀት ዓመቱ 49 በመቶ ሥራ ይከናወናል ብሎ ኮርፖሬሽኑ እንደሚጠብቅ በሰነዱ ላይ አስፍሯል።

አያይዞም በብረታ ብረት ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን አማካኝነት የሚገነቡት ሁለት 12,000 ቶን በቀን የመፍጨት አቅም ያላቸው ፋብሪካዎች ጣና በለስ ቁጥር 1 እና ቁጥር 2 ታህሳስ ወር 2007 መጨረሻ እና በመጋቢት 2007 መጨረሻ እንደ ቅደም ተከተላቸው ተጠናቅቀው አገዳ ለመፍጨት ይዘጋጃሉ፤ ይላል። በብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን በመገንባት ላይ ላለው ስኳር ፋብሪካ የውሃ አቅርቦት እየተሰሩ ካሉት ካናሎች በመስመር ተገንጥሎ፤ ይገነባል ይላል።

ልብ ያለው ልብ ይበል፤ ከላይ የሰፈረው ሪፖርት በ2007 ዓ.ም. ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የኢንዱስትሪ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የቀረበ ሪፖርት ነው። ለማነፃፀር እንዲመች፣ የስኳር ኮርፖሬሽን የሥራ ኃላፊዎች ግንቦት 1 ቀን 2008 ዓ.ም. የ2008 የበጀት ዓመት የዘጠኝ ወራት የሥራ አፈጻጸም ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግሥት ልማት ድርጅቶች ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሪፖርት ባቀረቡ ወቅት፣ ተስፋ መቁረጥና ሕመም እየተሰማን ነው፣ ነበር ያሉት። ከዚህ መረዳት የሚቻለው ነጭ ውሸት የበዛበት ሪፖርት፤ ከኮርፖሬሽኑ ለሕዝብ ተወካዮች ም/ቤት እንደሚቀርብ ነው።

በተለይ መጠየቅ ያለበት እና የሚቆጨው ጉዳይ፣ የተንዳሆ ስኳር ፋብሪካን ምዕራፍ አንድን ማስረከብ ላቀተው ለኦቨርሲስ ኢንፍራስትራክቸር አሊያንስ ኩባንያ፤የምዕራፍ ሁለትን የፋብሪካ ተከላ መፍቀድና ክፍያ መፈፀሙ ነው። በአጠቃላይ በስኳር ልማቱ ክሽፈት ተጠያቂ አካሎች አለመኖራቸው ነው። በዚህ ሁኔታ የህዝብ ሃበት የሆኑትን በሽርክና እንዲያዞርና ልማት እንዲያረጋግጥ እምነት እንዴት እንሰጠዋለን?

 

 

የስኳር የልማት ፈንድ

የስኳር የልማት ፈንድ ተብሎ ስያሜ የተሰጠው የሂሳብ ቋት፣ ከመተሐራ ስኳር ፋብሪካ፣ ከወንጂ ስኳር ፋብሪካ እና ከፊንጫ ስኳር ፋብሪካ በሚገኝ ገንዘብ የሚንቀሳቀስ ነው። ስኳር ፋብሪካዎቹ ከሚያገኙት ገቢ የተወሰነ ይተውላቸውና፤ ቀሪው ትርፋቸው በስኳር ልማት ፈንድ ስም ለተቀሩት ስኳር ፋብሪካዎች ልማት እንዲውል የታቀደ ነበር። ውጤቱን ስንመለከተው፣ አንድ ውጤታማ ፋብሪካ ሳይኖረን ነባር ፋብሪካዎች በውጭ ምንዛሪ እጥረት ከመለዋወጫ ውጪ እንዲሆኑ አድርጓቸዋል። እንደበፊት አሰራር ቢሆን ኖሮ፣ ነባር ፋብሪካዎቹ የመጠባበቂ የራሳቸው ገንዘብ ያስቀምጡ ነበር። ችግር ሲገጥማቸው ከመጠባበቂያ ቋት በማውጣት ይጠቀሙ ነበር። ዛሬ ላይ ብድር ወስዶ የማያውቅ መተሐራ ስኳር ፋብሪካ፣ ብድር ውስጥ ተዘፍቆ መስማት፣ ለምናውቀው ሕመሙ በጣም የከፋ ነው። ከላካይ በሌላቸው ከፍተኛ የመንግስት ኃላፊዎች ውሳኔ መፈጠሩን ስለምናውቅ፣ ሕመሙ ድርብ ነው። የመጠየቅ አቅምም የለንም።   

እንደመውጫ ግን ገዢው ፓርቲ የሕዝብ ሐብቶችን ወደ ግል ይዞታዎች ከማስተላለፍ በፊት፣ በተጠያቂ አካሎች ላይ የሕግ የበላይነት መኖሩን ማሳየት ይጠበቅበታል። ይህን ማድረግ ካልቻሉ፤ ሙስና ውስጥ ለመዘፈቅ የቆረጡና ወደፊት ምህረትን በሚጠብቁ አዲስ የፖለቲካና የመንግሥት ሹመኞች ቢሮክራሲው መወረሩ የማይቀር የቅርብ እውነታ ነው።

ጊዜው የእርቅና የምህረት ነው ከተባለ፤ ቢያንስ `public inquiry` (ለሕዝባዊ ጥያቄ መልስ መስጫ መድረክ) በማድረግ ከነበረው ስህተት ትምህርት በመውሰድ ቀጣይ ሃብት ማዳን ይቻላል፡፡ እንግሊዝ የኢራቅን ወረራ በተመለከተ ለቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትሯ ቶኒ ብሌየር ባመቻቸችው የ`public inquiry` ሁሉንም ነገር አውቃ፤ ወረራው ከተባበሩት መንግስታት መርህ ውጪ መሆኑን አረጋግጣለች፤ ተምራበታለችም፡፡ ቶኒ ብሌየርንም ከተጠያቂነት ነፃ አድርጋለች፡፡ እኛም ሀገር መካሰሱ ካልተፈለገ፤ ቢያንስ ይህንን ማድረግ ጠቃሚ ነው።¾

በይርጋ አበበ

በኢትዮጵያ የትምህርት ጥራት መጓደል መኖሩን በርካታ የዘርፉ ምሁራን ይናገራሉ። ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይም በበዓለ ሲመታቸው እለት ከሰጧቸው ሰፊ ንግግሮች መካከል አንዱ የትምህርት ጥራቱን ማስተካከል እነደሆነ ተናግረዋል። ይህ የዶክተር አብይ አዲስ ካቢኔ ለውጥ ካደረገባቸው ዘርፎች መካከል አንዱ “በከፍተኛ ትምህርት አግባብነትና ጥራት ኤጄንሲ” ላይ የኃላፊዎችን ሹመት መስጠትና መንሳት ነበር።

ቀደም ሲል ኤጄንሲውን ሲመሩ የነበሩት ዶክተር ተስፋዬ…. ተነስተው በምትካቸው አቶ ቢኒያም ተወልደ በቦታው ተተክተዋል። አዲሱ የኤጄንሲው ዳይሬክተር በቅርቡ ከግል የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ባለንብረቶች ጋር ውይይት አካሂደው ነበር። ውይይቱንና እንዲመጣ ስለተፈለገው ለውጥ ከ ቢ.ኤስ.ቲ (BST) ባለቤትና ፕሬዝዳንት ዶክተር ተፈሪ ብዙአየሁ ጋር አጠር ያለ ቃለ ምልልስ አድርገናል። የቃለ ምልልሱን ሙሉ ክፍልም ከዚህ በታች አቅርበነዋል።

ሰንደቅ፡- አሁን ያለውን የአገሪቱን ሁኔታ እና የእናንተን ዘርፍ (የትምህርቱን ዘርፍ) ቀጣይ ጉዞ እንዴት ያዩታል?

ዶክተር ተፈሪ፡- ለውጥ ከራስ ይጀምራል። ለራሱ ያልተለወጠ ሌላውን ለመለወጥ እንዴት ይሞክራል? በምን ብቃት እና ሞራል ከማን ጋር ሆኖ ለውጥን ያስባል? የዚህ ጽሁፍ መነሻ የሆነኝ ሰኔ 1/2010 ዓም በትምህርት ሚኒስቴር አዳራሽ ውስጥ የከፍተኛ ትምህርት አግባበብነት እና ጥራት ኤጄንሲ ከግል የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት አመራሮች ጋር ያደረገውን ስብሰባ ላይ በመገኘት መታዛቤን ተንተርሶ ነው።

አዲሱ አመራር ብቅ ካለበት ጊዜ ወዲህ በተለይም ከሁለት ወር ወዲህ አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር ከተሾሙ ጀምሮ በሀገራችን የለውጥ ሽታዎችን ከማሽተት አልፈን ከአንዳንዶች ለውጦችም በተግባር ተጠቃሚዎች መሆናችን የማይካድ ነው። በገዛ ሀገራችን ያጣነውን ነጻነት እና በስጋት የመኖራችን ጉዳይ ዋስትና እያገኘ ከመጣ ሰነባብቷል። ያሰጉናል የምንላቸው አካላት ከመስመር ላይ ዞር ማለታቸውም ሌላው ለውጥ ነው። ለዘመናት ያጣናቸውን ወገኖቻችንን ከእስር ተለቀው ተቀላቅለውናል። በቤታችን ሆነን የምንፈልገውን የማየት የማዳመጥ መብቶቻችን ‹በሽብርተኝነት የተፈረጁት ሚዲያዎችን የተከታተለ…› የሚለውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን በማሰቀረት፤ እነዚያ የተፈረጁትን ተቋማትን እና ግለሰቦችን እገዳ በማንሳት የነፃነት አየር እንድነተነፍስ ሆነናል። እንግዲህ እነዚህን ለውጦች ማጣጣም በጀመርንበት ማግስት ነው ለዘመናት ለግልም ሆነ ለመንግስት ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የጥራት መቀጨጭ ምክንያት የሆነው የከፍተኛ ትምህርት አግባብነት እና ጥራት ኤጄንሲ አሰራር ብልሹነትን ለማስተካከል ሲባል አዲሱ ዋና ዳይሬክተር በቀጥታ በጠቅላይ ሚኒስትሩ ፊርማ የተሾሙት።

ይህንን ሹመታቸውን ተከትሎ ከከፊሉ የግል ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ባለድርሻ አካላት ጋር ለመተዋወቅ እና በችግሮቹ ዙሪያ ለመወያየት ታስቦ የምክክር ስብሰባ ተጠርቶ ነበር። በዕለቱ ከስበሰባው ጅማሬ አንስቶ ያልተለመዱ ጉዳዮችን ማስተዋል ጀመርን።ጥቂቶች ቀድመን እዚያ ስንደርስ አዲሱ ዋና ዳይሬክተር ብቻቸውን በረንዳው ላይ ቆመው በብስጭት መንፈስ ስልክ ያወራሉ። እኛ ቦቦታው ደርስን ከቆምን ቢያንስ ከ30 ደቂቃ በኋላ የኤጄንሲው ሰራተኞች በኤጄንሲው መኪና ለስብሰባው የሚሆን ቁሳቁሶችን ይዘው ስብሰባው ይጀመራል ከተባለበት ጊዜ በጣም አርፍዶ ተጀመረ።

ለውጥ የሚመስል ነገር የታዘብኩት ከመደበኛው አሰራር ወጣ ያለ ጉዳይ አንዱ አዲሱ ዋና ዳይሬክተር ማንም የመድረክ ስራውን ሳያቀናጅላቸው ላፕቶፓቸውን ሰካክተው እንደምን አደራችሁ ብለው በጊዜ ባለመጀመራቸው ይቅርታ በመጠየቅ ጀመሩ። የእርሳቸው ንግግርም ሆነ አቀራረባቸው በአጠቃላይ የስብሰባው አካሄድ ኢ-መደበኛ እና ከተለመደው ወጣ ያለ ነበር። ክብደትም ያጣ የሚመስል ይታየኝ ነበር። ምናልባትም ከለመድነው ነገር ወጣ ያለ ስለአጋጠመን ሊሆን ይችላል ብዬ አሰብኩኝ። ቢሆንም ቀጥዬ የማነሳውን ክፍተት የሚያሟላ መኖር ነበረበት እላለሁ። በየትኛውም ማህበረሰብ ውስጥ እና የስራ አካሄድ ውስጥ እንግዳ ሁኔታ ሲካሄድ ነባሩ አሰራር ለምን እንደተቀየረ የሚያወሳ ከአዲሱ ጉዳይ ጋርም የሚያስተዋውቅ መኖሩ የግድ ነው። አለበለዚያ ተሳታፊዎችን ያላከበረ የሚያስመስል ነገር ይሆናል።

ሰንደቅ፡- እርስዎ ስለ ለውጥ ሲናገሩ የለውጡን ሂደትና አካሄድ በተመለከተ ምን ይላሉ?

ዶክተር ተፈሪ፡- ለውጥ ፈላጊው አካል አብዮተኛ እና ጀብደኛ ሆኖ ራሱን ካቀረበ ለዓላማው ለውጥ ተባባሪና አብሮ የሚፈስ አጋር ያጣል። ነባሩ አካል ሙሉ በሙሉ እስካልተቀየረ ድረስ ቢያንስ አዲሱን ሰው የማስተዋወቅ ስራ ከነባሩ ይጠበቅ ነበር። በአዲሱ ኃላፊ መሾም ነባሮቹ ሙሉ በሙሉ አኩራፊዎች ከሆኑ ወይንም ብቃት የላቸውም ተብለው ወደጎን ቢተው እንኳ ባለቤት ነኝ ባይ የት/ሚ/ር ይህን ድርሻ መውሰድ ነበረበት። ለእኔ የትምህርት ጉዳይ የሀገሬ ጉዳይ በመሆኑ ያገባኛል። 27 ዓመታት በሙሉ እንጠቃለን በማለት እውነትን ፊት-ለፊት ካለመነጋገር በብዙ ዋጋ ከፍለንበታል። ምናልባትም ይህንን ጽሁፍ በማዘጋጀቴ ምክንያት ዘራፍ የሚል አካል ካለም ግድየለም የ27 ዓመታቱ ይበቃናል፤ አሁን ግን አይሞከርም እላለሁኝ። ቢሞከርም ስለ እውነት በማስመሰል አላጎበድድም።

ሰንደቅ፡- በዕለቱ የነበረው ውይይትና የውይይቱ ግብ ምንድን ነው? ከውጤታማነቱ አኳያስ እንዴት ይመለከቱታል?

ዶክተር ተፈሪ፡- የእለቱ ድርጊት የሚያወሳው ወይ ጉባኤው ተንቆአል አልያም ለውጡን ለብቻ ለማምጣት እየተሮጠ ያለ ይመስለኛል። ከነባሩ አካል ለሽግግሩ እንኳ የታጨ አለመኖሩን የታዘብኩት በስፍራው የተገኙት የኤጄንሲው ጥቂት ሰራተኞች በእለቱ ከመኪና ላይ እቃ ከማውረድ እና የሻይ መስተንግዶ ከማቅረብ ያለፈ የሰሩትን አላስተዋልኩኝም። ይህ ሁለት ነገር ያመላክታል፡- አንደኛው ግምት ነባሩ አካል አዲሱን ዋና ዳይሬክተር አልተቀበለውም ወይንም ገና የዳር ተመልካች ሆኖ መደበኛ ስራውን እየሰራ ነገሮች እስኪጠሩለት ድረስ የሚሆነውን በርቀት በመከታተል ላይ ያለ ያስመስላል።

ሁለተኛው ምክንያት ነባሩን ያለማሳተፍ ጉዳይ ነው። ነባሩ በብልሹ አሰራሩ ውስጥ ቀጥተኛ ተዋናይ በመሆኑ ለለውጥ የሚነሳሳ ሞራል ላይኖረው ይችላል ተብሎ ሊገመት ይችል ይሆናል። መቼም ከነባሩ መካከል ለተሳትፎ ቢጠየቅ ለሁለት ምክንያቶች ፈቃደኝነት የሚያሳይ የሚታጣ አይመስለኝም። አንደኛው ምክንያት ለስራ ኃላፊ የመታዘዝ ግዴታ፤ ሁለተኛው ምክንያት ከአዲሱ አመራር ጋር ለለውጥ መስራት የሚፈልግ አይጠፋም ባይ ነኝ። እንግዲህ ነባሩ ለተሳትፎ ተጠይቆ እምቢ ማለቱን ስላልተነገረን ለውጥ ፋላጊው አዲሱ አመራር የቀድሞዎቹን ላለማሳተፍ ፈልጓል ማለት ይቻላል። የተፈለገበት ምክንያትም እንደተነገረን የስብሰባው አካሄድ ከተለመደው አሰራር ወጣ እንዲል ያለ አስተዋዋቂ፤ ያለመድረክ መሪ፤ ያለሪፖርታዥ ተወያይተናል። የተለመደው አሰራር ምናልባት አሰልቺ፤ ፍሬያማ አይደልም ተብሎ ቢታሰብ እንኳን በዚህ ስብሰባ ነባሩ ካልተሳተፈ ለውጡን ከእነማን ጋር ለማምጣት ተፈልጎ ነው? የሚል ጥያቄ እንደዜጋ ማንሳት ግድ ነው። ስበሰባው ለሚዲያ ግብዓት ብቻ እንዲሆን ተፈልጎ ከሆነ ደግሞ ተሰብሳቢው ቢያንስ እንደዜጋ መከበር ነበረበት ባይ ነኝ። አዲሱ አመራር ከሚያመጣቸው ለውጦች አንዱ ቢሆንልን ይህንን ረዥም እጅ እንዲቆርጠው ነው።

ሰንደቅ፡- በትምህርቱ ዘርፍ እጃቸው ረጃጅም አካላት አሉ ብለዋል። እነዚህ ባለረጅም እጅ አካላት እነማን ናቸው? የኤጄንሲው ድርሻስ ምንድን ነው?

ዶክተር ተፈሪ፡- በኢትዮጵያ የከፍተኛ ትምህርት ጥራት ላይ ረዥም እጅ ያላቸው ብዙ ቢሆኑም ሁለት ዋና ዋና አካላት ግን ሁለቱንም ክፍል ማለትም የግሉንም ሆነ የመንግስት ተቋማትን ጎድተዋል። እነርሱም በመመሪያ እና በአሰራር ጠርንፈው የሀገሪቷን እድገት የጠላለፉ አካላት እና የመጫወቻው ሜዳው ሰፊ ሆኖ እያለ የሌላውን መብቃት እና ማደግ የማይፈልግ የአትድረሱብኝ በሽታ ያለባቸው ስግብግብ የሙያው ባለቤት ያልሆኑ የትምህርት ነጋዴዎች ሊሆኑ ይችላሉ።

እነዚህን አካላት ለመከላከል በሚያስችል ቁመና ላይ የሌለው የከፍተኛ ትምህርት አግባብነት እና ጥራት ኤጄንሲ (Higher education Relevance and Quality Agency-HERQA) የሀገሪቷን የከፍተኛ ትምህርት ጥራትን ማስጠበቅ ይቅርና ራሱን ማዳን አቅቶት ወይ ለውጥ አልያም መፍረስ አለብህ የሚባልበት ደረጃ ደርሷል። ምክንያቱም እነዚህ አካላት ይህን ተቋም ማለትም ኤጄንሲው በሁለት እግሩ እንዳይቆም፤ የተሻለ ነገር ለሀገሪቷ የትምህርት እድገት እንዳያበረክት አድርገውታል።

ገና ከምስረታው ጀምሮ እስከዛሬ መፍትሔ ያልተገኘለት ጉዳይ ኤጄንሲው የተመሰረተበት ዓላማ ለሁሉም አካላት ግልጽ ያለመሆን ወዲያ ወዲህ እንዲንገዋለል እንጂ የጠራ ቁመና ይዞ እንዳይቀጥል ዳርጎታል። ኤጄንሲው ለምንድነው የተመሰረተው? እየሰራ ያለውስ ከተመሠረተበት አላማ እንጻር ነው? ለዚህስ መመስረት ነበረበት ወይ? ተጠሪነቱስ ለማን መሆን አለበት? የሚሉት መልስ እስካላገኙ ድረስ የአዲሱ ዋና ዳይሬክትር ሹመት እና ብቻቸውን መንደፋደፍ የትም ላያደርሰን ይችላል ብዬ አስተያየት መስጠት እፈልጋለሁ። በርግጥ በዕለቱ ይህን ሃሳቤን ቁንጽል በሆነ መልኩ ለመግለጽ ሞክሬአለሁኝ-ሰሚ ካገኘ።

ሰንደቅ፡- ኤጄንሲውን በዚህ መልኩ ከገለጹት ለመሆኑ የተጣለበትን አደራና ተልዕኮ ለመሸከም የሚያስችል ቁመና የተላበሰ ነው?

ዶክተር ተፈሪ፡- እንደሚታወቀው ኤጄንሲው በሁለት ዳይሬክተሮች ማለትም የእውቅና አሰጣጥ ዳይሬክቶሬት እና የጥራት ኦዲት ዳይሬክቶሬት ተከፍሎ በዋና ዳይሬክተር እና ም/ዋና ዳይሬክተር ይመራል። የሁለቱ ክፍሎች ስራ ተደጋጋፊ ቢሆንም የየራሳቸው ድርሻ አላቸው። ኤጄንሲው እውቅና ሰጭ እና ጥራት አስጠባቂ ነው። የተለመደውም እየሰራ ያለውም ይህንኑ ነው። ራሱ እውቅና ሰጭ ሆኖ ተቋማት እርሱ ባወጣው መስፈርት መሰረት ጥራትን ስለመጠበቃቸው ይቆጣጠራል ማለት ነው። ሶስት ነገር ተደባላልቋል።

መስፈርት ያወጣል፤ በመስፈርቱ መሰረት እውቅናን ይሰጣል፤ በመስፈርቱ መሰረት ጥራትን ለማረጋገጥ ይቆጣጠራል። ይህ አካሄድ ኤጄንሲውን እንደማያዛልቀው ብቻ ሳይሆን እንደማይመጥነውም ጭምር በብዙ መልኩ ተብሏል።

የብዙዎች ሃገራት ተሞክሮዎችን ነባሩ የኤጄንሲው ቲም በደንብ ያውቃል። ብዙ የሀገር ሃብት ወጥቶበት ብዙዎቹ የኤጄንሲው ነባር ባለሙያዎች ልምዶችን ከሀገር ውጭ ተልከው ወስደዋል። ወደ ሀገር ውስጥም በመጋበዝ የልምድ ልውውጦች እና ስልጠናዎች ተደርገዋል። በዚህ ዙሪያ በሀገር ውስጥ ባለሙያዎች ጥናቶችም ተደርገዋል። የውጭ ሀገር ባለሙያዎችም የተሳተፉበት ጥናቶች እኔ እስከማውቀው ድረስ ነበሩ። ታዲያ ችግሩ ምንድነው? መፍትሔውስ? የሚሉትን ማየት ይኖርብናል።

ከሁሉ በላይ ይህንን ተቋም በኃላፊነትም ሆነ በተለያዩ እርከኖች የሚመሩት አካል ‹ከተወሰኑት በስተቀር› ባለሙያ ያለመሆን ብቻ ሳይሆን የሀገሪቷ የትምህርት ጥራት መጓደል አሳሳቢ ደረጃ ላይ መድረሱን እያወቁ ኃላፊነት ወስደው ለማስተካከል ዋጋ ያለመክፈል ችግር ነበረ። ሁለተኛው ይህ ተቋም እንዲቋቋምለት የፈለገው የሀገር አደራ ያለበት አካል ኤጄንሲው የማይመጥነውን ዓላማ ይዞ እንዲቀጥል በማድረግ ተቋሙን ባለቤት አልባ ከማድረግ አልፎ ለሀገሪቷ የከፍተኛ ትምህርት ጥራት መጓደል ምክንያት ሆኗል።

በዚህ ዙሪያ ትምህርት ሚኒስቴር በአንድ በኩል ሲፈልግ እንደማይመለከተው ዓይነት ጣቱን ወደ ኤጄንሲው እየጠቆመ በሌላ በኩል በግለሰብ አመራር ደረጃም ቢሆን እንደተቋም ሲፈልግ ብቻ ጣልቃ እየገባ በሌላ ጎኑ ደግሞ የኤጄንሲውን ተጠሪነት ከእጁ እንዳይወጣ እስከ ሰኔ አንድ ስብሰባው ድረስ እንኳን ሲሟገት ይታያል።

በመሆኑም ለለውጥ ቁርጠኝነት ከተፈለገ ኤጄንሲው የተቋቋመበትን ዓላማ በመፈተሽ ከዓላማው አንጻር ኤጄንሲውን እንደገና ማዋቀር፤ ከዚህ ዓላማ አንጻር የኤጀንሲውን አጋዥ ኃይል በህግ ማዕቀፍ ማስተሳሰር፤ ኤጄንሲውን ወደተፈለገበት ግብ ያመጡታል በሚባሉ ተገቢ የትምህርት ዝግጅት፤ ልምድ እና ክህሎት ባላቸው ባለሙያዎች ከላይ እስከታች ማደራጀት፤ የኤጄንሲውን ተጠሪነት እንደገና ማጤን፤ አዲሱ አመራር ሰላማዊ ሽግግሩ ላይ ቢያተኩር፤ በማለት ሙያዊ ምክሬን እለግሳለሁኝ።

 

“የፌዴራል የፀረ ሙስናና ስነምግባር ኮሚሽንን ያየ ከአስፈፃሚው ጋር አይጫወትም”

በሳምሶን ደሳለኝ

የምህረት አሰጣጥና አፈፃፀም አዋጅ ረቂቅ ግንቦት 28 ቀን 2010 ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀርቧል። የረቂቅ አዋጁ አስፈላጊነትን በተመለከተ የተለያዩ ሀገሮች ተሞክሮ በወፍ በረር ትንታኔ ተያይዞ ቀርቧል። ወደኋላ መለስ በማለትም የግሪክ፣ የአሜሪካ እና የደቡብ አፍሪካ የወንጀል ድርጊቶች ምህረት ልምዶችን ለማሳየት ተሞክሯል።

ምህረት ማድረግ ያተርፍ ይሆናል እንጂ፣ የሚያሳጣው ነገር አይኖርም ብሎ ማስቀመጥ ከባድ አይደለም። የምህረት፣ አሰጣጥና አፈፃጸም እንደየ ሀገሩ አውድ እንደሚለያይ ግን ግንዛቤ መውሰዱ ተገቢ ነው። ምህረት፣ የተወሰኑ ሀገሮች ልምድን በመውሰድ ብቻ የሚከናውን ሳይሆን የሀገሮቹን ተጨባጭ ሁኔታዎች ከግምት መውሰዱ ይመከራል። ቅዱስ ቃሉም እንደሚለው፣ የበደላችሁን ይቅር በሉ ነው። ስለዚህም ምህረት በማድረጉ ላይ ልዩነት አይኖርም።

ወደሀገራችን ተጨባጭ ሁኔታ ስንመጣ ዋናው ነጥብ ከምህረት አዋጅ በፊት የህግ የበላይነት ማክበርና ማስከበር የሚችል መንግስታዊ ቁመና ያስፈልገናል። የሕግ የበላይነት በዋናነት የሚያስፈልገን ገዢው ፓርቲን ከፖለቲካ ሙስና የጸዳ ለማድረግ ነው። ይህም ሲባል፣ የፖለቲካ ሙስና በሰነድ የሚወራረድ የተለመደ ሙስና ሳይሆን፣ በሕግ ሽፋን አስፈፃሚ አካል የሚፈጽመው ረቂቅ መንግስታዊ ሙስና ነው። በግለሰቦች ደረጃም ስንመለከተው፣ አንዳንዶቹ ምንጩ ያልታወቀ የፖለቲካ ስልጣን አላቸው፤ የፈለጉትን ቢሮክራሲ የማዘዝ፣ የመበርበር፣ የማስወሰን አቅም አላቸው። ለዚህም ነው፤ የህግ የበላይነት ማረጋገጥ ያልቻለ መንግስት፣ የምህረት አሰጣጡና አፈፃጸሙ ከፖለቲካ ሙስና እንዴት ሊነጠል እንደሚችል መገመት ከባድ የሚሆነው።

ወደ ዋናው ነጥብ ከመግባታችን በፊት የፌዴራል የፀረ-ሙስናና ሥነምግባር ኮሚሽን በገዢው ፓርቲ ባለሟሎች እንዴት እንደፈረሰ ማየቱ ተገቢ ነው። የጸረ-ሙስናና ሥነምግባር ኮሚሽን መጀመሪያ ተጠሪነቱ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ነበር። ይህም ማለት፣ ከአስፈፃሚ አካል ነፃ የሆነ መስሪያቤት ነበር። በወቅቱ ኮሚሽነር የነበሩት ወ/ሮ እንወይ ገ/መድኅን ራሳቸውን ነፃና ገለልተኛ አድርገው ሥራ መስራት ጀምረውም ከፓርቲ ስብሰባዎችም ለበርካታ ጊዚያት ርቀው ተቀምጠው ነበር። የወ/ሮዋ ሁኔታ ያልጣማቸው የአስፈፃሚ አካላት ኮምሽኑን በተመለከተ አንድ ነገር ማድረግ እንዳለባቸው ከውሳኔ ላይ ይደርሳሉ። ወ/ሮ እንወይም የብአዴን ማዕከላዊ ኮሚቴ ስብሰባ ጥሪ ሲደርሳቸው፤ ገለልተኛ ተቋም እንደሚመሩ አሳውቀው ጥያቄውን ውድቅ ያደርጋሉ። ይህም አካሄዳቸው ከኮምሽኑ እንዲሰናበቱ አብቅቷቸዋል።

በወቅቱ በወ/ሮ እንወይ እንቅስቃሴ ግራ የተጋባው የአስፈፃሚ አካል የኮምሽኑን ተጠሪነት ከፓርላማው ላይ ነጥቆ፣ ወደ አስፈፃሚው መዳፍ ውስጥ ከተተው። አስፈፃሚውም ኮሚሽኑን ከተግባሩ አላቆ የፖለቲካ ሙስና መስሪያቤት አደረገው። ኮሚሽኑ ወፎችን እንጂ ጭልፊቶችን ማደን የማይችል ተቋም አድርጎ ቀረጸው። አስፈላጊ ሲሆን ከፖለቲካው መስመር ያፈነገጡ ሰዎችን መልቀሚያ አደረገው። በሕግ የበላይነት ሳይሆን በገዢው ፓርቲ ኃላፊዎች የሚወሰኑ ውሳኔዎች አስፈፃሚ ሆነ። ኮሚሽኑም አስፈፃሚውን ቀና ብሎ ማየት የማይችል ተራ ታዛዥ ተቋም ሆኖ፣ በመጨረሻም በሕዝብ ተቀባይነት እንዳያገኝ አድርገው አፈራረሱት። ኮሚሽኑ ከፊል ዲፓርትመንቱ ወደጠቅላይ አቃቤ ሕግ ሲጠቃለልም በአስፈፃሚው ትዕዛዝ በርካታ ሰነዶች እንዲሰወሩ መደረጉን የውስጥ አዋቂ ምንጮች በወቅቱ በተለያየ ቦታ ሹክ ብለው ነበር ሰሚ ግን ሳያገኙ ቀርተዋል።

በተመሳሳይ ሁኔታ የኢትዮጵያ ፌደራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ምህረት አሰጣጥ እና አፈፃጸም ሥነ-ሥርዓት ረቂቅ አዋጅ፤ (4.1) የምህረት ቦርዱ ተጠሪነቱ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ይሆናል፣ ይላል። ወረድ ብሎም፣ የምህረት አሰጣጥ አፈፃጸም (11.2) ጠቅላይ ሚኒስትሩ የቦርዱን የምህረት የውሳኔ ሐሳብ ከተቀበለ በጉዳዩ ላይ ረቂቅ የምህረት አዋጅ በፌደራል ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ በኩል እንዲዘጋጅ ያደርጋል። (11.3) በዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ (2) መሰረት የተዘጋጀው ረቂቅ የምህረት አዋጅ የሚኒስትሮች ምክር ቤት መክሮበት ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ይቀርባል፤ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ከጸደቀ የፌደራል ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመሆን ያስፈጽማል፤ ይላል።    

እዚህ ላይ መታወቅ ያለበት ነጥቦች በኢትዮጵያ ተጨባጭ ሁኔታ የሀገሪቷን ሥርዓተ-መንግስት የሚመራው ጠቅላይ ሚኒስትር በሕዝብ ተወካዮች ምክርቤት አብላጫ ድምጽ ማግኘት ከቻለ የፖለቲካ ፓርቲ የሚሰየም እንጂ፤ በሕዝብ በቀጥታ ምርጫ የሚመረጥ አይደለም። የአዋጁም ረቂቅ ለሀገርና ለሕዝብ ጥቅምን መውጣቱን ስለሚጠቁም፣ ለሕዝብ ውክልና ያለው አካል ማነው የሚለውን ጥያቄ መመለስ ተገቢ ነው፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ናቸው? ወይንስ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት? ወይንስ የፕሬዝዳንቱ ነው? ምላሽ ለመስጠት ዛሬ መቶ በመቶ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በኢሕአዴግ እና አጋሮቹ መያዙን መመልከት የለብንም። ነገ ምን ሊፈጠር እንደሚችል ዛሬ ላይ ሆኖ መገመት አይቻልም።

ከዚህ ጋር በተያያዘ የአዋጁ መነሻ ጭብጡ በረቂቅ ሰነዱ እንዲህ ይላል፤ “በኢትዮጵያ ውስጥ ሰላምና መረጋጋትን የሚያደፈርሱ ሁኔታዎች በሚፈጠሩበት ወቅት የማሕበረሰቡን ሰላም እና ደህንነት ለማረጋገጥ እንዲሁም ፖለቲካዊ፣ ማሕበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ጥቅም በተሻለ መልኩ ለመጠበቅ ምህረት መስጠት የሚያስችል ሁኔታ መፍጠር አስፈላጊ በመሆኑ ምህረት የሚሰጥ ሥነ-ሥርዓት በሕግ መደንገግ ስለሚያስፈለግ የምህረት አሰጣጥና አፈፃጸም ሥነ-ሥርዓት አዋጅ ማውጣት አስፈላጊ ሆኗል፤” ይላል። ይህ የመነሻ ሃሳብ ለትርጉም የተጋለጠ አጠቃላይ ትንታኔ በመሆኑ፤ ከፓርቲ መሪዎች ይልቅ የህዝብ ውክልና መሰረቱ ሰፋ ለሚለው ምክርቤት መስጠቱ ተገቢነቱ ከፍ፤ ይላል።  

ነገሩን ትንሽ ዘርዘር ለማድረግ፣ “ጠቅላይ ሚኒስትሩ የቦርዱን የምህረት የውሳኔ ሐሳብ ከተቀበለ በጉዳዩ ላይ ረቂቅ የምህረት አዋጅ በፌደራል ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ በኩል እንዲዘጋጅ ያደርጋል።” የሚለው አንቀጽ አደገኛ ነው። ጠቅላይ ሚኒስትሩ የቦርዱን ውሳኔ ከምን አንፃር ነው “የሚቀበሉት” “የማይቀበሉት”፤ ከፓርቲያቸው ጥቅም? ከአስፈፃሚው ጥቅም? ከሕዝብ ጥቅም? ከእራሳቸው ጥቅም? ወይንስ ከአዋጁ አንፃር?፤ ምርጫው የጠቅላይ ሚኒስትሩ ነው የሚሆነው። ስለዚህም ወደፊት በተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲዎች የሚወከል የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንደሚኖር ታሳቢ አድርገን ስልጣኑን ሙሉ ለሙሉ ለምክር ቤቱ መስጠት አዋጪ ነው።

ሌላው የረቂቅ አዋጁ የተፈፃሚነት ወሰን (3.1) ይህ አዋጅ በማንኛውም የወንጀል ዓይነቶች ተጠርጣሪዎች፣ ተከሳሾች ወይም ፍርደኞች ላይ ተፈፃሚ ይሆናል፤ (3.2) በዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ (1) የተደነገገው የሰው ዘር በማጥፋት፣ ያለፍርድ የሞት ቅጣት እርምጃ መውሰድ፣ በአስገዳጅ ሰውን መሰወር እና ኢ-ሰብዓዊ የድብደባ ወንጀሎች ላይ ተፈፃሚ አይሆንም፤ ይላል። አዋጁ ተፈፃሚ የማይሆንባቸውን ወሰኖች ብሎ ያስቀመጣቸው፣ በአለም አቀፍ ሕግም ላይ የተቀመጡ አብይ ወንጀሎች ናቸው። ሆኖም፤ ከላይ ለማስቀመጥ እንደተሞከረው የምህረት አዋጁ የሀገሪቷን ተጨባጭ ሁኔታዎችን ከግምት ውስጥ ማስገባት አለበት የሚል መከራከሪያ ማስቀመጡ ጥሩ ነው።

ይህም ሲባል፣ በሀገራችን ውስጥ አንዱ እና ምንአልባትም ዋነኛው የአለመረጋጋት ምንጭ ፍትሃዊ የሃብት ክፍፍል አለመኖሩ ነው። ከገዢው ፓርቲ ፖለቲካ ኢኮኖሚ ጋር የተጠጋ፣ ከስራ እድል እስከ ዘረፋ የሚመቻችበት ሀገር ውስጥ ነው፤ ያለነው። በኪራይ ሰብሳቢ ፖለቲካ ኢኮኖሚ የበላይነት የተዘፈቀች ሀገር ውስጥ ነው፤ ያለነው። ምንም ዕሴት የማይፈጥሩ፣ የማይጨምሩ ኃይሎች የተቆጣጠሩት የንግድ ሥርዓት ያለባት ሀገር ውስጥ ነው፤ ያለነው። የሃብታቸው ምንጭ በማይታወቁ ሰዎች የተገነቡ ሕንፃና ሆቴሎች ያላት ሀገር ውስጥ ነው፤ ያለነው። የመንግስት ፕሮጀክቶች ደረጃውን ባልጠበቀ ግንባታ እየተገነቡ ዘረፋ በሚፈጸምባት ሀገር ውስጥ ነው፤ ያለነው። በአጠቃላይ ከዚህ ደሃ ሕዝብ አጥንት ላይ ስጋ የሚገነጥሉ፤ አብይ ሙሰኞች ያሉባት ሀገር ውስጥ ነው፤ የምንገኘው። ስለዚህም በሙስና የተጠረጠሩ ሰዎችን በግልፅ አዋጁ ምህረት እንደማይሰጥ ተፅፎ መቀመጥ አለበት።

ለዚህ ጥሩ ማሳያ የሚሆነው፣ ባለፉት ሁለት ወራት በኪራይ ሰብሳቢ ፖለቲካ ኢኮኖሚ ውስጥ ለተዘፈቁ ኃይሎች በይቅርታ ሽፋን በፖለቲካ ሙስና ክሳቸው እንዲቋረጥ መደረጉ ነው። ይህንን ያደረገው አካል ሕገመንግስታዊም ሆነ ከአዋጅ የሚመነጭ ስልጣን እንደሌለው ይታወቃል። በተለይ የተፈቱበት አግባብ በጥሬ ትርጉሙ ሲቀመጥ፣ “እነእንትና ሳይታሰሩ፤ እነእገሌ እንዴት ይታሰራሉ?” በሚል ተልካሻ ምክንያት ወገንተኝነት የተላበሰ ውኃ የማያነሳ መሆኑ ነው። ስልጡን አመራር ማግኘት ብንችል ኖሮ፣ ከዚህ በፊት ዘርፈዋል የሚሏቸውን ሰዎች ወደሕግ አቅርቦ ሥርዓት ማስያዝ እንጂ፤ የቀድሞዎቹ ሌቦች ማን ጠየቃቸውና “የእኛ ወገኖች” ይጠየቃሉ በሚል ምክንያት ለኪራይ ሰብሳቢዎች ወገንተኛ ሆኖ መገኘት የጊዜ ጉዳይ እንጂ፤ ከተጠያቂነት የማምለጥ ተደርጎ መውሰድ የፈቺውና የተፈቺውን መርህ አልባ ግንኙነት ከማሳየት የተለየ ትርጉም የለውም።

ስለዚህም “ይህ አዋጅ በማንኛውም የወንጀል ዓይነቶች ተጠርጣሪዎች፣ ተከሳሾች ወይም ፍርደኞች ላይ ተፈፃሚ ይሆናል፤” የሚለው አቀራረቡ ውሻ በቀደደው ጅብ ይገባል እንዲሉ፤ የህዝብ ሃብት ያዘረፉ፤ የዘረፉ፤ በገንዘብ አጠባ የተሰማሩ፤ ምንጩ ያልታወቀ ሃብት ባለቤት ለሆኑ ድርጅቶችም ግለሰቦችም፤ በምህረት አዋጁ ተፈፃሚ ማዕቀፍ ውስጥ እንደማይካተቱ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ጉዳዩ ለዝርዝር ምርመራ የተመለከተ ቋሚ ኮሚቴ በግልፅ ጽፎ በአዋጁ ማስፈር ይጠበቅበታል።

የአዋጁ ሌላው ግራ አጋቢ ይዘቱ ይህንን ይመስላል፤ በማጠቃለያው ማብራሪያ ላይ እንደሰፈረው፣ “የአዋጁ ምሕረት ሕገመንግስታዊ ይዘት ያለው በአብዛኛው ጥፋቶች፣ ሀገር መክዳት፣ የአመፅ ወንጀሎች እና በሀገርና በመንግስት ላይ አመፅ ማነሳሳት ወንጀል ለፈጸሙና በሕግ በተሰጠው የጊዜ ገደብ ውስጥ ወደ ሰለማዊ ኑሯቸው ተመልሰው የመንግስት ሕግ እና ሥርዓት ለማክበር ግዴታ ለሚገቡ ጥቂት ወይም መላው ወንጀለኞች መንግስት ያለፈውን ጥፋታቸውን ሙሉ ለሙሉ ስሪየት የሚያደርግበት ሥርዓት ነው። ምህረት መብት ሳይሆን የሀገር ሰላምና ደህነት ለማረጋገጥ በተወሰኑ የወንጀል ዓይነቶች በአንድ ደረጃ ለሚገኙ ተጠርጣሪዎች ወይም ወንጀለኞች ላይ ምርመራ ወይም የክስ ሒደት ከማስቀጠል ወይም ቅጣትን ከማስፈጸም ይልቅ ምህረት የተሻለ ውጤት ያመጣል ተብሎ ሲታሰብ የሚሰጥ ነው፤” ይላል።

ማጠቃለያው ላይ የሰፈረው የምህረት ይዘት፣ የጌታችን እየሱስ ክርስቶስ ምህረት እንጂ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሚሰጡት ምህረት አይደለም። ረቂቁ፣ የህግ የበላይነትን በአዋጅ የሚሽር የተንቦረቀቀ ልጓም የሌለው የምህረት ሰነድ፤ ነው። ለተወሰኑ ኃይሎች ቀዳዳ ለመክፈት ሆን ተብሎ በልካቸው የተሰፋ የምህረት ረቂቅ አዋጅ፤ ነው። በተለይ፤ በ“ሀገር በመክዳት” የተወነጀሉ ኃይሎች ግለሰቦችን ምህረት አደርጋለሁ የሚል መንግስት፣ በአለም የመጀመሪያው የኢትዮጵያ መንግስት ሳይሆን አይቀርም። ባሳለፍነው ሁለት ወራት በእንግሊዝ እና በሩሲያ መካከል ለተፈጠረው የዲፕሎማሲ ውጥረት እና ግጭት ምክንያቱ፤ ሩሲያዊ ሆኖ ለእንግሊዝ መንግስት ተቀጥሮ የገዛ ሀገሩን ሩሲያን ሲሰልል በነበረ፤ ግለሰብ መነሻ ነው። ስለዚህም “በሀገር ክህደት የተወነጀሉ ኃይሎችን ግለሰቦችን ለጊዜው ለመጥቀም ተብሎ የምህረት አዋጅ ማዘጋጀት፣ ከሀገር ከሃዲዎቹ የማይተናነስ ወንጀል ተደርጎ የሚወሰድ መሆኑ አሻሚ አይደለም።

እንደመውጫ ግን፣ የህግ የበላይነት ማረጋገጥ ቁርጠኛ የሆነ መንግስት፤ ቀጫጭን የፍትህ ማስፈጸሚያ መንጠላጠያ ሕጎች አያስፈልጉትም። የህግ በላይነትን ማረጋገጥ፤ ማስከበር፤ ብቻውን ለሁሉም ምላሽ ይሰጣል። ገዢው ፓርቲ ለሕግ የበላይነት እራሱን ካስገዛ፤ በዚህ ሀገር ውስጥ የሚወድቅ ቁስም ሰውም አይኖርም፤ ያለውም ምርጫ ይሄው ነው።

Page 1 of 27

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us