መተባባር ብቸኛ አማራጭ መሆኑ ግንዛቤ የተወሰደበት መድረክ

Wednesday, 03 August 2016 14:42

 

 

በአዲስ አበባ በዋሽንግተን ሆቴል ከጁላይ 28 ቀን እስከ ኦገስት 1 ቀን 2016 ከተለያዩ የምስራቅ አፍሪካ ሀገሮች የተወጣጡ ጋዜጠኞች ከናይል ውሃ አጠቃቀም ጋር በተያያዘ ስለሚዘግቧቸው ዘገባዎች አጋዥ የሆነ የስልጠና መድረክ በሲውድን ዓለም ዓቀፍ የውሃ ኢንስቲትዩት እና በኢንትሮ ተዘጋጅቶ ነበር፡፡ 

በዚህ ስብሳባ ላይ ከግብፅ፣ ከሱዳን፣ ከደቡብ ሱዳን እና ከኢትዮጵያ የተጋበዙ ጋዜጠኞች ተሳታፊ ነበሩ፡፡ በስልጠናው በምስራቅ ናይል ተፋሰስ ሀገሮች ውስጥ ከናይል ውኃ አጠቃቀም ጋር በተያያዘ የሚሰራጩ ዘገባዎች አዎንታዊ ይዘት እንዲኖራቸው እና ሀገሮቹ ወደ ትብብር መድረክ እንደሚመጡ የሚያስችሉ የተለያዩ ግብዓቶች የቀረቡበት ነበር፡፡ በዚህ ስልጠና ላይ ከፍተኛ ባለሙያዎች የተለያዩ የጥናት ወረቀቶች አቅርበዋል፡፡

የጥናት ሰነዶቹ ከቀረቡ እና ጥልቅ ውይይት ከተደረገባቸው በኋላ ሁሉም ተጋባዥ ጋዜጠኞች እና በስልጠናው የተሳተፉ ባለሙያዎች በጋራ በመሆን የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ የኃይል ማመንጫ ግድብን ጎብኝተዋል፡፡ በዚህ ጉብኝታቸው ከዚህ በፊት በሕዳሴው ግድብ ዙሪያ የነበራቸውን ግንዛቤ እና ከጉብኝቱ በኋላ የተፈጠረባቸው ስሜት እንዲያካፍሉን የተወሰኑ ጋዜጠኞችን ጋብዘን አነጋግረናል፡፡ የስልጠና ሰነዶችን በተመለከተ በቀጣይ የምንዘግበው ይሆናል ፡፡ ለዛፌ ለአንባቢያን እንዲመች በዚህ መልኩ አቅርበናል፡፡

 

 

ጋዜጠኛ አያህ አማን

ከአል-ሾሩክ/አል-ሞኒተር (ግብፅ)

ሰንደቅ፡- በፊት የነበረሽ አረዳድ እና አሁን ከጉብኝቱ በኋላ ያገኘሽው መረዳት ምን ይመስላል?

አያህ አማን፡- ካለፉት አምስት አመታት እስካሁን ድረስ ስለኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ዘገባዎች ሳቀርብ ነበር። የኢትዮጵያ የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ፕሮጀክት ኤክስ የሚባል ግድብ በናይል ወንዝ ላይ እንደሚገነቡ ይፋዊ መግለጫ ሲሰጡ ለእኛ ግብፆች በጣም ትልቅ እና ጠቃሚ ዜና ነበር። በተለይ ለእኔ ከውኃ ጋር የተያያዙ ጉዳዮች በተለይ ድንበር ተሻጋሪ ወንዞች ላይ ካለፉት ስድስት አመታት እስካሁን ድረስ  ስከታተል ነበር። ከናይል ወንዝ ጋር የተያያዙ ጉዳዮችን እንዲሁም በናይል ወንዝ ዙሪያ በካይሮ በካርቱም ሲደረጉ የነበሩ ድርድሮችን ተከታትያለሁ። እነዚህ ድርድሮቹ አንዳንዴ ግጭት ሌላ ጊዜ ውጥረት እንዲሁም ለዘብ ያሉ ይሆናሉ። አሁን ግን በአካል ተገኝቼ ግድቡን መጎብኘት በመቻሌ በጣም ጠቃሚ የሆነው ልምድ ማግኘት ችያለሁ። እንደጋዜጠኛም ለሕዝብ ለማስተላልፋቸው ዘገባዎች የተሻለ ግብዓት አግኝቻለሁ። ላለፉት በርካታ አመታት ምን እየተሰራ እንደሆን ማየት ባልቻልንበት ሁኔታ ዘገባዎች ስናቀርብ የነበረ በመሆኑ ሥራችን አስቸጋሪ ነበር።

ሰንደቅ፡- ላለፉት ስድስት አመታት የህዳሴ ግድብ የግንባታ ሁኔታዎችን መመልከት ሳትችይ ዘገባዎች አቅርበሻል። አሁን የግድቡን የግንባታ ሁኔታዎች ተመልክተሻል። ያየሽው ነገር አዘጋገብሽን ይቀይረው ይሆን?”

አያህ አማን፡- በርግጠኝነት። ቢያንስ አሁን መሬት ያለውን ያየሁትን እጽፋለሁ። በግብፅ ውስጥ ጋዜጠኞቹም ሆኑ ሕዝቡ በተጨባጭ ምን እየተደረገ እንደሆነ አያውቁም። እንደውም አንዳንዴ የውኃ ፍሰቱ ተቋርጦ ግድቡ ውኃ እየተሞላ ነው ይባላል። በሌላ ጊዜ ውኃ መሙላት አልተጀመረም ይባላል። አሁን መሬት ያለውን መመልከቴ ለሕዝብ፣ ለመንግስት ከፍተኛ ኃላፊዎች እንዲሁም ለባለሙያዎች በማቀርበው ዘገባ ላይ መተማመን የበለጠ ይጨምርልኛል። በርካታ ባለሙያዎች ለጋዜጠኞች እንዲሁም በቴሌቪዥን ለሕዝባችን የህዳሴ ግድቡን በተመለከተ እና ከግድቡ ጋር የተያያዙ ትንታኔዎች ያቀርባሉ። ከድርድሮች በስተጀርባ ያሉ አስተሳሰቦችን ይተነትናሉ። ይህን የሚያደርጉት ግን በሕዳሴው ግድብ ግንባታ ዙሪያ ምን እየተከናወነ እንደሆነ ሳይመለከቱ ነው።

ሰንደቅ፡- የምታቀርቢው ዘገባ የሕዝቡን በሕዳሴ ግድብ ላይ ያለውን አረዳድ የሚቀይረው ይመስልሻል?”

አያህ አማን፡-በትላንትናው ዕለት በግል የፌስ ቡክ ገፄ ላይ ያየሁትን መረጃ ለቅቄ ነበር። ከውሃ ጋር በተገናኘ ዘገባዎችን ማንበብ ፍላጎት ያላቸው በርካታ ተከታዬች አሉኝ። እንዲሁም ከፍተኛ ኃላፊዎች፣ በውጭ ጉዳይ ሚኒስትር፣ በውሃ ሚኒስትር ውስጥ እና በካይሮ ዩኒቨርስቲ ተመራማሪ የሆኑ ጓደኞችም አሉኝ። ሁሉም የሚጠይቁኝ “በእውነት ምን እየተሰራ እንሆነ ተመልክተሻል? በኢትዮጵያኖቹ በኩል ሙሉ ግልጽነት ነበር?” የሚሉ ናቸው። የሰጠሁት ምላሽም፣ ማንም ይህን አድርጉ ያን አታድርጉ ያለን የከለከለን የለም፤ በሙሉ ነፃነት ነው የጎበኘነው፤ የምንፈልገውን ሁሉ በፎቶ ካሜራችን አንስተናል። አየህ፣ የጋዜጠኝነት ስራ አስቸጋሪ ከሚያደርጉት አንዱ ከዋናው ምንጭ መረጃን አለማግኘት መሆኑን መረዳት ትችላለህ።

ሰንደቅ፡- ለመጀመሪያ ጊዜ ይህ የግብፅ የጋዜጠኞች ቡድን ነው የህዳሴ ግድብ የጎበኘው። ሌሎች የግብፅ ጋዜጠኞች በተመሳሳይ መልኩ የህዳሴ ግድቡን እንዲጎበኙ ታበረታቻለሽ? እንዲሁም ሕዝቡ እንዲጎበኘው?

አያህ አማን፡- የመጀመሪያ ነገር ምን እየተሰራ እንደሆነ ተመልክቻለሁ። ትንሽ ግድብ አይደለም። እየተገነባ ያለም አይደለም፣ ተገንብቶ እውን ሆኗል። የግንባታውም ሒደት ከፍተኛ ነው። ሀገሬም አንባቢዎቼም ተከታዮቼም ግድቡ መሬት ላይ አለ። ግድቡ በድርድር ላይ አይደለም። ይህ በጣም ጠቃሚ ጉዳይ ነው። እስካሁን ድረስ የህዳሴ ግድብ የሚባል የለም የሚሉ አሉ። እስካሁንም ድርድር እያልን ጊዜ እያጠፋን ነው። የእኔም ሆነ የጓደኞቼ ዘገባ የሚሆነው ተደራዳሪ ወገኖቻችን ላይ ከፍተኛ ግፊት ማሳደር ነው። አንድ ነገር ማድረግ አለባቸው። ድርድሩን ማፋጠን አለባቸው።

አንድ የምጨምረው ነገር ቢኖር ለፕሮጀክቱ ማኔጀር ኢንጅነር ስመኘው ያለኝ አድናቆት ከፍተኛ ነው። ምክንያቱም በስራ ምክንያት ብዙ የውኃ ኢንጅነሮችን ከዚህ በፊት አነጋግሬ አውቃለሁ። ይህ ሰው ግን ኢንጅነር ብቻ አይደለም፣ ዲፕሎማት እና ሥነምግባሩ ከፍተኛ ደረጃ ላይ የደረሰ ሰው ነው። በቀጣይ በማቀርበው ዘገባ ከፍተኛ ሽፋን ከምሰጣቸው ጉዳዮች አንዱ ስለዚህ ኢንጅነር ነው። 

 

 

 

ጋዜጠኛ ባሴም አቦ

አልሃራም ኦንላይን (ግብፅ)

ሰንደቅ፡- ከጉብኝቱ በፊት የነበረህ መረዳት ምን ይመስላል?

ባሴም አቦ፡- ከመምጣቴ በፊት አሉታዊ የሆነ መረዳት ነበረኝ ለማለት አልችልም። ሆኖም ወደጎን የማላደርገው ጉዳይ ይዤ ነበር የመጣሁት። ይኽውም፣ ግድቡ ግብፅ በናይል ወንዝ ላይ ያላትን የውኃ ድርሻ መጠን ይቀንሰው ይሆን የሚል ጥያቄ ነበረኝ። ሆኖም የህዳሴውን ግድብን በአካል ተገኝተን መጎብኘታችን እንዲሁም የግድቡን የተለያዩ ክፍሎች በምንጎበኝበት ወቅት ከፕሮጀከት ማናጀሩ ከኢንጅነር ስመኘው ያገኘናቸው ቴክኒካል ትንታኔዎችን መሰረት አድርገን ግድቡ ግብፅን እንደማይጎዳት አረጋግጠናል። አሁን እንኳን የግድቡ ግንባታ እየተከናወነ ወደታችኞቹ ሀገራት የናይል ውኃ ፍስት አልተቋረጠም። ይህንን በአይናችን አይተናል።

ሰንደቅ፡-በአልሃራም ኦንላይን የሕዳሴ ግድብን የተመለከቱ በርካታ ጽሁፎች ይስተናገዳሉ። ከዚህ በፊት የተፃፉት ጽሁፎች እንደተጠበቁ ሆነው፣ በዚህ ጉብኝት ውስጥ ያገኽው አዲስ ግብዓት አለ? ለአንባቢዎቻችሁ ለሕዝባችሁ በጉብኝታችሁ ወቅት የተመለከታችሁትን ሁሉንም ነገር ታቀርባላችሁ?

ባሴም አቦ፡- የተመለከትኩትን ሁሉ አካፍላለሁ። አብዛኛው ግብፃዊያን የህዳሴ ግድቡ ጋር ምን እየተሰራ እንደሆነ አያውቁም። እኔ እዚህ የተገኘሁበት አላማም፣ ግብፅ በናይል ውኃ ላይ ያላት ድርሻ እንደማይነካ እውነተኛ እና ትክክለኛ መረጃ ለማቅረብ እና ለማረጋገጥ ነው። እንደኢንጅነር ስመኘው ገለፃ “እኛ ኢትዮጵያዊያን የናይል ውኃን የማስቀረትም የመያዝም ፍላጎት የለንም” ብለዋል። ከዚህ በፊት በአልሃራም ኦንላይን ላይ የሚጻፉ አርቲክሎች የውኃ ባለሙያዎችን ትንታኔዎች መሰረት ያደረጉ ናቸው። ስህተቶች ተፈጥረው ይሆናል። ምክንያቱ ደግሞ እነዚህ ባለሙያዎች የሕዳሴው ግድብን በአካል የጎበኙ አይደሉም። እንዲሁም መሬት ላይ እየተሰራ ስላለው ነገር አያውቁም። ስለዚህም የእኔ ስራ የሚሆነው፣ የተሳሳቱ መረጃዎች ካሉ ማስተካከል ነው።

ጉብኝታችን በጣም በግልፅነት የተከናወነ ነበር። ሁሉንም የግድቡን የግንባታ አካሎች ጎብኝተናል። በየምንፈልገውን መረጃዎች በቪዲዮ በፎቶ ካሜራዎች ቀርጸን መውሰድ ችለናል። በስራ ላይ ያሉ ሰራተኞችን አነጋግረናል። ከኢትዮጵያ ወንሞቻችን ጋር በጋራ በልተናል፤ ተኝተናል። የተደረገልን አቀባበል እና መስተንግዶ በጣም አስደሳች ነበር።

 

 

ጋዜጠኛ ፊሊፕ ማክ

የአይ ሬዲዮ ኤዲተር (ደቡብ ሱዳን)

ሰንደቅ፡- ስለሕዳሴው ግድብ ግንባታ የነበረህ መረጃ ምን ይመስላል?

ፊሊፕ ማክ፡- ወደ አዲስ አበባ ስመጣ የነበረኝ መረጃ ግብፅ በሕዳሴው ግድብ ግንባታ ላይ ፈቃደኛ አለመሆኗ ነው። በመገናኛ ብዙሃናቸውም የሰማሁትም ያነበብኩትም የህዳሴው ግድብ ወደግብፅ ወደሱዳን የሚፈሰውን የውሃ መጠን እንደሚቀንስ ነው። ይህም በመሆኑ ሱዳን የግብፅን አቋም ትደግፋለች። ግብፅ እና ሱዳን ከኢትዮጵያ ጋር ለመተባበር ፈቃደኛ አለመሆናቸውን ነበር።

የተዘጋጀልንን ስልጠናዎች ከተሳተፍኩ በኋላ ያገኘሁት መረጃ ግን የተለየ ነው። ይኽውም፣ ሱዳን የሕዳሴ ግድብ ግንባታውን አትቃወምም። ከዚህም በላይ ለግድቡ ግንባታ ድጋፍ ታደርጋለች። አስፈላጊ ቴክኒካል መረጃዎችም በመስጠት ትተባበራለች። በአንፃሩ ደግሞ ግብፅ ከፍተኛ ፍራቻ አላት። ምክንያታቸው ደግሞ የውሃ መጠን ድርሻቸው እንደሚቀንስ ነው የሚያምኑት። ሆኖም ከተሰጠን ስልጠና እና በጉብኝት ካገኘሁት መረጃ አንፃር የግብፅ ፍርሃት መሰረት የለውም። ግድቡ የኤሌክትሪክ ኃይል ካመነጨ በኋላ ውሃ ወደ ታችኞቹ ሀገሮች እንደሚፈስ ተረድተናል። አሁንም እየፈሰሰ ነው። ከፍተኛ ባለሙያዎቹ ያቀረቡልን ወረቀቶችም የሚያሳዩት ይህንኑ ነው። ስለዚህም ሁሉም ወገኖች ተባብረው የተፈጠሩትን ልዩነቶች መፍታት ይጠበቅባቸዋል። ሌላም ምርጫ የላቸውም።

 

 

ጋዜጠኛ መሐመድ አሚድ

ከሳፋራ ጋዜጣ (ሱዳን)

ሰንደቅ፡- የሕዳሴ ግድብ ግንባታን እንዴት አገኘ?

መሐመድ አሚን፡- በጣም ትልቅ ሥራ ነው የተመለከትኩት። ለኢትዮጵያን ወድሞቼ እንኳን ደስአላችሁ ማለት እፈልጋለሁ። ለእኛ አፍሪካውያንም ኩራት የሆነ ግድብ ነው። ከጉርብትና ከፍ ባለ ደረጃ ወንድማማች ለሆነው ለኢትዮጵያ እና ለሱዳን ሕዝቦች የተለየ ስሜት ይፈጥራል። ከዚህ በፊት የተለያዩ ባለሙያዎች ስለግድቡ ግንባታ ጥቅል እና ጥልቀት ያላቸው መረጃዎች አካፍለውን ያውቃሉ። ሆኖም ግን በአካል ተግኝቼ የግድቡን ሥራዎች ስመለከት ማመን የማልችለው ስሜት ነው የፈጠረብኝ። የትኛውም ባለሙያ የፈለገውን ያህል ቢያስረዳኝ በአካል ተገኝቼ ያየሁት ያህል ሊያስረዳኝ አይችልም። ከዚህ ጉብኝት አንድ ትልቅ ነገር የተረዳሁት ቢኖር ኢትዮጵያ ወደ እድገት ጎዳና ለመግባት እያኮበኮበች መሆኗን ነው። ከዚህ በፊት ከሁላችንም ጥቅም አንፃር በግድብ ግንባታ ላይ አዎንታዊ አመለካከት የነበረኝ ቢሆንም የግድቡ ግንባታ ሙሉ ስራዎችን ስመለከት የነበረኝን አመለካከት የበለጠ አጠናክሮልናል።

በአንዳንድ ቦታዎች ስንሰማው ሲነገር የነበረው ኢትዮጵያ በናይል ወንዝ ላይ ምንም ግድብ እየሰራች አለመሆኗን እንዲሁም የመስራት አቅምም እንደሌላቸው ነበር። ሆኖም መሬት ላይ የተመለከትነው በመገባደድ ላይ ያለ ግድብ ነው። ስለዚህም ሁሉም ወገን እውነቱን ተቀብሎ፣ ሁላችንም ተጠቃሚ የምንሆንበትን የትብብር መንገድ መፈለግ ተገቢ ነው። በርግጥ የሱዳን መንግስት እና ሕዝብ ለሕዳሴው ግድብ ሙሉ ድጋፍ ያለን እንደሆነ የሚታወቅ ቢሆንም ነገሮች በትብብር እንዲያልቁ ሥራዎች ተጠናክረው መሰራት አለባቸው።

 

 

 

ጋዜጠኛ ማናላ አግራም

ከሬዲዮ እና ቴሌቪዥን መጽሔት (ግብፅ)

ሰንደቅ፡- ከሕዳሴው ግድብ ጉብኝበት በፊት የነበረሽ ግንዛቤ ምን ነበር? ከጉብኝቱ በኋላስ ምን የተለየ ነገር አገኘሽ?

ማናላ አግራም፡- ህዳሴው ግድብ ከመምጣቴ በፊት የነበረኝ መቅረፅ በጣም አስፈሪ ነው። እንዲሁም አጠቃላይ የህዝቡም ግንዛቤ ከፍርሃት ጋር የተያያዘ ነው። የሕዳሴው ግድብ ወደ ግብፅ የሚፈሰውን የናይል ውኃ እንደሚያስቀረው በሕዝቡ የተያዘ ግንዛቤ ነው። እኔ እንደጋዜጠኛ የተለያዩ ባለሙያዎችን አነጋግሪያለሁ። ገሚሶቹ የህዳሴው ግድብ በግብፅ ላይ ጉዳት አያደርስም ይላሉ። ገሚሶቹ ደግሞ ግድቡ ጉዳት ያስከትላል ይላሉ። አሁን እዚህ የሕዳሴው ግድብ ጋር ሆኜ፣ የተሻለ ጥሩ ነገር ይሰማኛል። አሁን አንድ ነገር አውቄያለሁ፤ የሕዳሴው ግድብ ግብፅ አይጎዳም።

ይህ እንዲሆን ግን ቅድመ ሁኔታዎች መሟላት አለባቸው። ይኽውም፣ የሁለቱም ሀገሮች ባለስልጣናት ቁጭ ብለው በትብብር መንፈስ መወያየትና መደራደር አለባቸው። በተለይ ኦፐሬሽኑን በተመለከተ። ግድቡ ውኃ የሚሞላበትን ጊዜ በድርድር መስማማት አለባቸው። በረጅም ጊዜ ግድቡ ውኃ የሚሞላ ከሆነ በግብፅ ላይ የሚያስከትለው ጉዳት የለም። ሆኖም ኢትዮጵያ በሁለት፣ በሶስት ወይም አራት ዓመታት ጊዜ ውስጥ ግድቡን በውኃ ለመሙላት ከወሰነች በግብፅ ላይ ጉዳት ያመጣል። ስለዚህም መተባበር አለብን። ሁላችንም አሸናፊ የሚያደርግ የትብብር መንገድ መፍጠር አለብን። ማናችንንም የሚጎዳ ተግባር መፈጸም የለብንም።

አንዳችን ሌላኛውን የሚጎዳ ሥራ እንሰራለን የሚል እምነት የለኝም። ግብፅና ኢትዮጵያ ከጥንት ጀምሮ ግንኙነት ያላቸው ሀገሮች ናቸው። በመካከላችን ውኃ ብቻ አይደለም የሚያገናኘን። ሀገሬ ግብፅ ኢትዮጵያን ለመጉዳት አትፈልግም። ልማት ማከናወን መብታችሁ ነው። የሕዳሴው ግድብን ለኃይል ማመንጫ መጠቀም መብታችሁ ነው። እኛም የናይልን ውኃን ለግብርና መጠቀማችን መብታችን ነው። ስለዚህም ሁሉም ነገር በትብብር መፍታት እንችላለን።

ሰንደቅ፡- በግብፅ መገናኛ ብዙሃን ስለህዳሴው ግድብ የሚዘገቡ ዘገባዎች አሉታዊ ጎናቸው ያመዝናል። በተጨባጭ በሕዳሴው ግድብ ምን እየተሰራ መሆኑን ተመልክታችኋል። ከዚህ አንፃር በቀጣይ ከግብፅ የሚወጡ መረጃዎች ድምጸታቸው ሚዛናዊ ይሆናል የሚል እምነት አለሽ?”

ማናላ አግራም፡- በርግጠኝነት። ዘጠኝ የምንሆን ከተለያዩ የመገናኛ ብዙሃን የተወጣጣን ጋዜጠኞች ነን ወደ ሕዳሴው ግድብ ለጉብኝት የመጣነው። ሕዝቡ የህዳሴው ግድብ እንደማይጎዳው በመረጃዎቹ ያምናል። ይህ በቅድመ ሁኔታዎች የሚቀመጥ ነው። ሁለቱ ሀገሮች ከተባበሩ ብቻ የሚፈጸም ነው። ይኽውም፣ ውኃ የሚሞላበትን ጊዜ በመተባበር መስማማት አለባቸው።

እኔ በግሌ ከናይል ውሃ አጠቃቀም ጋር በተያያዘ ከ2005 ጀምሮ ተሳታፊ ነርኩ። አዲስ አበባ ብዙ ጊዜ መጥቻለሁ። በየመንገድ በርካታ ኢትዮጵያን አነጋግሪያለሁ። አንዳቸውም ግብፅ እንድትጎዳ አይፈልጉም። የሚገርመው ኢትዮጵያኖቹ ግብፅ ሁሉንም ውኃ ለመውሰድ ትፈልጋለች ሲሉ የግብፅ አብዛኛው ሕዝብ ደግሞ ኢትዮጵያ የናይልን ውኃ ሙሉ ለሙሉ ልታስቀርብን ነው የሚል ፍራቻ አላቸው። ከዚህ የምንረዳው የተሳሳተ ግንዛቤ በሁለቱም ሕዝቦች መካከል መኖሩን ነው። ስለዚህም ሁላችንም ቁጭ ብለን በመተባበር መንፈስ ከተወያየን ከተደራደርን ሁላችንም ተጠቃሚዎች እንሆናለን። እዚህ የመጣነው ጋዜጠኞችም ለሕዝቡ መሬት ላይ ያየነውን መረጃ በትክክል ለመዘገብ እና በሚደራደሩ ኃላፊዎች ላይ ግፊት ለማድረግ ነው።¾

ይምረጡ
(3 ሰዎች መርጠዋል)
1121 ጊዜ ተነበዋል

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us