“የአማራና የትግራይ ሕዝቦች፣ አብረው ታግለዋል፣ ሞተዋል፣ በአንድ ጉድጓድ ተቀብረዋል”

Wednesday, 10 August 2016 14:23

“የአማራና የትግራይ ሕዝቦች፣

አብረው ታግለዋል፣ ሞተዋል፣ በአንድ ጉድጓድ ተቀብረዋል”

አቶ ንጉሱ ጥላሁን

የአማራ ክልላዊ መንግስት የኮሚኒኬሽን ጽ/ቤት ኃላፊ

 

በአማራ ክልላዊ መንግስት ውስጥ በሚገኙ በጎንደር እና በባሕርዳር ከተሞች ሁለት ትልልቅ ሰላማዊ ሰልፎች ተካሂደዋል። በጎንደር የተደረገው ሰላማዊ ሰልፍ በሰላም ሲጠናቀቅ፣ በባሕርዳር የተደረገው ሰላማዊ ሰልፍ ግን ሰልፉ ሊጠናቀቅ በተቃረበበት ሰዓት በተነሳ ግጭት የዜጎች ሕይወት አልፏል። (በዚህ አጋጣሚ የሰንደቅ ዝግጅት ክፍል ለሟች ቤተሰቦች መፅናናትን ይመኛል)

ከሁለቱ ሰላማዊ ሰልፎች እና ከሌች ወቅታዊ ጉዳዮች ጋር በተያያዘ ከአማራ ክልላዊ መንግስት የኮሚኒኬሽን ጽ/ቤት ኃላፊ ከሆኑት ከአቶ ንጉሱ ጥላሁን ጋር ቃለምልልስ አድርገናል።

ለኮሚኒኬሽን ጽ/ቤት ኃላፊው ካነሳናቸው ጥያቄዎች መካከል፣ የወልቃይት ጥያቄ ከማንነት ወይንስ ከወሰን ጥያቄ ጋር የሚያያዝ ነው? እንዴት ይፈታል? የብአዴን የፖለቲካ አመራሮች በወልቃይት ጥያቄ ያላቸው አረዳድ እና አቋም ምን ይመስል? የተነሱት ጥያቄዎች ከመልካም አስተዳደር ጋር የሚያያዙ ናቸው ወይንስ የሥርዓት ለውጥ ጥያቄ ነው? የሚሉ ይገኙበታል። ለአንባቢዎቻችን በሚመች መልኩ ቃለምልልሱን እንደሚከተለው አቅርበነዋል።

 

 

ሰንደቅ፡- በጎንደር በባህር ዳር ከተማ በተደረጉ ሰልፎች መሰረታዊ መነሻው የመልካም አስተዳደር ችግሮች መሆናቸውን በብአዴን ከፍተኛ ባለስልጣናት ሲገለጽ ተደምጧል። ሆኖም በሰልፉ ላይ የተንፀባረቁ መፈክሮችም ሆኑ አንዳንድ ድርጊቶች  አጠቃላይ የስርዓት ለውጥ ፍለጋ የሚመስል ይዘት ያላቸው ናቸው። በዚህ ላይ የእርስዎ አስተያየት ምንድን ነው?

አቶ ንጉሱ፡-በመጀመሪያ ደረጃ መልካም አስተዳደር በሚለው ፍቺ ላይ መስማማት አለብን። መልካም አስተዳደር ማለት ሕብረተሰቡ ለሚያነሳቸው ማንኛውንም አይነት ጥያቄ ምላሽ መስጠት ነው። ይህም ሲባል ከህብረተሰቡ ለተነሳው ጥያቄ የሚሰጠው ምላሽ ጥያቄውን ላነሳው አካል የሚመችም የማይመችም ቢሆንም እንኳን አፋጣኝ ምላሽ ኃላፊነት በተሞላበት መልኩ መስጠት በመልካም አስተዳደር ማዕቀፍ ውስጥ የሚቀመጥ ነው። ስለዚህም ሕብረተሰቡ በተደጋጋሚ ጊዜ ላነሳቸው ጥያቄዎች እና ቅሬታዎች ፈጣን ምላሽ ባለመስጠታችን የመልካም አስተዳደር ጉድለት ፈጽመናል።

የወሰን ጥያቄም ሆነ ከማንነት ጋር የተያያዙ በራስ ቋንቋ የመፃፍ የመደራጀት መብቶች ቢሆኑም ለእነዚህ ጥያቄዎች ምላሽ መስጠት ምላሾቹም ጠያቂው በሚፈልገው መልክ ይሁን አይሁን ምላሽ እስካልተሰጠ ድረስ ከመልካም አስተዳደር መርሆች መጓደል አንዱ ይሆናል። ስለዚህም ለእነዚህ ሲንከባለሉ ለነበሩ ጥያቄዎች ምላሽ አለመስጠት፣ ከሕብረተሰብ በኩል ሆኖ ሲታዩ ከመልካም አስተዳደር ጉድለት ጋር መታየታቸው ትክክል ነው። በእኛም በኩል ፈጣን ምላሽ መስጠት አልቻልንም ብለን ገምግመናል። ከዚህም መነሻ ነው፣ የሕብረተሰቡ ጥያቄዎች የመልካም አስተዳደር ጉድለት ጥያቄዎች ናቸው የምንለው እንጂ የሕብረተሰቡን ጥያቄዎች ለማሳነስ ፈልገን አይደለም። ከሕብረተሰቡ ጋር መወያየት መተማመን፣ ልዩነት ቢኖረን እንኳን በልዩነት ውስጥ መኖር እንደሚቻል ከሕብረተሰቡ ጋር ስምምነት ላይ መድረስ ተገቢ ነው ብለን ገምግመናል።

ሰንደቅ፡- ብአዴን የወልቃይት ጥያቄን የሚመለከተው ከወሰን ጋር በተያያዘ ነው ወይንስ የማንነት ጥያቄ አድርጎ ነው? የፓርቲው የፖለቲካ አመራሮች በወልቃይት ጥያቄ በደረሱበት ውሳኔ ላይ የተንፀባረቁ የልዩነት ሃሳቦች ካሉም ቢገልጹልን?

አቶ ንጉሱ፡- የማንነትም ይሁን የወሰን ጥያቄ የሚካተተው ከመልካም አስተዳደር ጋር ነው። ከወልቃይት አንፃር የተነሳውም ጥያቄ ምላሽ አለማግኘቱ ተገቢ ይሁን አይሁን ከመልካም አስተዳደር ጉድለት ጋር ተያይዞ የሚታይ ነው።

ቀደም ብለህ ከስርዓት ለውጥ ጋር የተያያዙ የሚመስሉ ድርጊቶች ነበሩ ላልከው፣ የወልቃይት ጥያቄን በምክንያትነት ተወስዶ ግጭቶች ቢከሰቱም ሕብረተሰቡ ከወልቃይት ጥያቄዎች በተጨማሪም ከዚህ በፊት የሚያነሳቸው ጥያቄዎችም፣ ቅሬታዎችም ነበሩ። ሕብረተሰቡ ቅሬታዎቹን እና ጥያቄዎቹ ፈጣን ምላሽ እንዲሰጣቸው ከመጠየቅ ውጪ የስርዓት ለውጥ ጥያቄ አላቀረበም፣ አላነሳም። ሰላማዊ ሰልፍ በተደረገባቸውም አካባቢዎች ሕብረተሰቡ ስርዓቱን እንደሚደግፍ ሲገልጽ ነበር። ምክንያቱም ሕብረተሰቡ ሰላም እንደሚፈልግ፣ ሌሎች ብሔር ብሔረሰቦች እንደሚያከብር መልክቶች ይዞ ሲያንጸባርቅ ነበር። በሕገ መንግስታዊ ስርዓት ውስጥ ሆኖ ጥያቄዎቹን ማቅረብ እንደሚችልም ይገልጽ ነበር።

ነገር ግን ሰልፍ በተደረገባቸው አካባቢዎች ባሕርዳርን ጨምሮ የሰላማዊ ሰልፍ ዓላማ ያልሆኑ መልዕክቶች ተላልፈዋል፣ ድርጊቶችም ተፈጽመዋል። ብዙዎች የተሰውለትን በርካቶች አካላቸውን ያጡለትን ሕገመንግስታዊ ስርዓት የተገነባበትን እና የዚህ ምልክት የሆነውን ሰንደቅ ዓላማ ክብር የነፈገ፣ ዝቅ ያደረገ ከዚያም ባሻገር የአንድነታችን የህብረታችን የመቻቻላችንን ሁለተናዊ እሴት ሊያፋልስ የሚችል መልዕክት ከሰላማዊ ሰልፈኛ ሳይሆን በሰላማዊ ሰልፈኛ ውስጥ ሰርገው በመግባት፣ አሁን አሁን ደግሞ መልክተኞች ብቻ ሳይሆኑ ጦር ቦምብና ሽጉጥ በመያዝ ሰላማዊ ሰልፉን ወደ ብጥብጥ የመምራት ዝንባሌዎች እና ተጨባጭ ተግባሮች ሲፈፀሙ ታይተዋል።

ሕዝቡ ጦር ታጥቆ፣ ቦምብ ጨብጦ፣ ሽጉጥ ይዞ ወደ ሰልፉ አልገባም። ሕዝቡ ሰንደቅ ዓላማ አላወረደም። ሕዝቡ በሕገ መንግስቱ ያምናል። ሕዝቡ በሕገ መንግስታዊ ስርዓቱ ያምናል። ስለዚህም ሕዝቡ የስርዓት ለውጥ ጥያቄ አቅርቧል የተባለው “መሰረት” የለውም። የስርዓት ለውጥ ጥያቄዎች ለማቅረብ የሞከሩት ስርዓቱን በአመጽ በኃይል ለመናድ ተልዕኮ የተሰጣቸው ወገኖች ናቸው። ይህንን የተፈጠረውን አጋጣሚ በመጠቀም የሰላማዊ ሰልፈኛውን አጀንዳ ቀምተው እነሱ ወደሚፈልጉት የአጀንዳውን አቅጣጫ ቀይረው መልዕክት አስተላልፈዋል። ወደ ተግባራዊ እንቅስቃሴ ውስጥም ገብተዋል።

የክልሉ መንግስት የወልቃይት ጥያቄንም ሆነ ሌሎች ጥያቄዎች ሕገ መንግስቱን ተከትለው እስካቀረቡ ድረስ ተገቢነታቸውን ያምናል፣ ይቀበላል። ሆኖም ግን የወልቃይት ጥያቄን ሽፋን አድርገው ሕገወጥ እንቅስቃሴ ማድረግ አንደኛ፣ የተነሳው ጥያቄ በሕግ አግባብ እንዳይፈታ እንቅፋት ይሆናል። ሁለተኛ፣ የሕዝቡም ጥያቄ አይደለም። ይህም ሲባል ሕዝቡ ሥርዓት የመለወጥ እና ሕገመንግስታዊ ስርዓቱን በኃይል የመናድ ፍላጐት የለውም። በተለይ ደግሞ ከሰሜን ጎንደርና ከጎንደር አካባቢ ሕዝብ አኳያ ሲወሰድ ይህ ስርዓት እንዲመጣ ለበርካታ ዘመናት ታግሎ የታጋዩ ጋሻ ከለላ መከታ ሆኖ ያገለገለ ሕዝብ እና እራሱ ታግሎ የወለደው ስርዓት ስለሆነ ይህንን ስርዓት አያፈርስም። ስርዓቱም እንዴት እንደበቀለ ስለሚያውቅ ስርዓቱ እንዴት ማደግ እንዳለበትም የሚናገር ሕዝብ በመሆኑ በሰላማዊ መንገድ ሲንቀሳቀስ፣ የተለየ ተልዕኮ ያነገቡ ኃይሎች ግን ይህንን የሕዝቡን ሰላማዊ እንቅስቃሴ ወደሌላ ዓላማ ለመውሰድ እየጣሩ ይገኛሉ። ይህ ማለት ግን ሕዝቡ የስርዓት ለውጥ ጥያቄ አቅርቧል ማለት አይደለም።

ሰንደቅ፡- የወልቃይት ጉዳይ ጥያቄ በሕገ መንግስቱ አግባብ መቅረብ እንደሚችል ገልጸዋል። ሕገ መንግስቱ የኢትዮጵያ አውራ ሕግ ከሆነ ከሃያ ዓመታት በላይ ሆኖታል። ዛሬ ላይ የወልቃይት ጥያቄ አዲስ አጀንዳ ሆኖ እንዴት ሊቀርብ ቻለ? ጥያቄውን ያቀረቡ የሕብረተሰብ ክፍሎች መሰረታዊ ምክንያቶችስ ምንድን ናቸው?

አቶ ንጉሱ፡- የወልቃይት ጥያቄ ሆነ ለሌሎች የማንነት ጥያቄዎች የሚነሱበት መሰረታዊ ምክንያት እኛ በወቅቱ አግባብ ባለው ሁኔታ ምላሽ ባለመስጠታችን የመጣ ነው። ከሕብረተሰቡ ጋር ተወያይተን ምላሽ እንዲያገኝ ባለማድረጋችን ነው ቅሬታ ሊያድር የቻለው። አሁንም ምላሽ ማግኘት ካለበት በሕገ መንግስቱ ብቻ ነው።

ሰንደቅ፡- ወልቃይትን በተመለከተ በብአዴን ሥራ አስፈፃሚ እንዲሁም በፓርቲው ከፍተኛ ካድሬዎች ያለው አረዳድ እና የውሳኔ አሰጣጥ ላይ ያላቸው የጋራ መግባባት ምን ይመስላል?

አቶ ንጉሱ፡- አንድ ነው። ብአዴን አንድ አቋም ነው ያለው።   

ሰንደቅ፡- ምን አይነት አቋም?

አቶ ንጉሱ፡- ቀደም ብዬ በገለጽኩት አግባብ።

ሰንደቅ፡- በሕገ መንግስቱ ማለትዎት ነው?

አቶ ንጉሱ፡- በጦርነት አያምንም።

ሰንደቅ፡- በተደጋጋሚ ለዚህ ብጥብጥ የሶስተኛ ወገኖች አጀንዳዎችን ተጠያቂ አድርጋችኋል። በወሰዳችሁት ግምገማ የሶስተኛ ወገኖች አጀንዳዎች እና በሶስተኛ ወገንተኝነት የሚፈረጁ ኃይሎች የትኞቹ ናቸው?

አቶ ንጉሱ፡- በሕገ መንግስቱ እውቅና ያለውን የብሔር ብሔረሰቦችን እኩልነት የሚያንጸባርቅን ሰንደቅ ዓላማ ማውረድ የአማራ ሕዝቦች ፍላጎትም አቋምም አይደለም። ይህ ተግባር ለክልሉ ባዕድ ነው። በሌሎች ኢትዮጵያውያን ወገኖች ላይ የጥላቻ ቅስቀሳ ማድረግ የአማራ ሕዝብ ዕሴቶች አይደሉም። የሌሎች ናቸው። እነዚህን ተግባሮች እና አመለካከቶች በመያዝ የኢትዮጵያ ሕዝቦችን እድገትና ልማት ለማጨናገፍ ሌትተቀን የሚሰራው የሻዕቢያ አገዛዝ መሆኑ ሁሉም ኢትዮጵያዊ የሚያውቀው ጥሬ ሃቅ ነው። ሻዕቢያ በቀጥታ በኢትዮጵያ ላይ አደጋ መፈጸም እንደማይችል በተደጋጋሚ በተሰጠው ምላሽ ስላረጋገጠ፣ በእጅ አዙር ኢትዮጵያን ለማተራመስ እየሰራ መሆኑ የሚታወቅ ነው። ሁሉም የሚያውቀው ጉዳይ ነው።

የሻዕቢያን አመለካከት የሚከተሉ ሻዕቢያን የሚመግቡ ግንቦት ሰባት እና የመሳሰሉት የጥፋት ኃይሎች ሕብረተሰቡ በክልላችን ውስጥ የተፈጠረውን የመልካም አስተዳደር ጉድለት ለመጠየቅ በወጣው ሰላማዊ ሰልፍ ውስጥ ሰርገው በመግባት ከሕብረተሰቡ ፍላጎት ውጪ መልዕክቶችን ለማስተላለፍ ሞክረዋል። የሕዝቡን አጀንዳዎች ለመቀማት ጥረት አድርገዋል። የክልላችን ሕዝብ ሰላም እና የልማት ሥራዎችን እያሳየው ያለውን ስርዓት ዋጋ ከፍለው ነው ያገኙት። ስለዚህም ለአፍራሽ ኃይሎች ፍላጎት ዋጋ ከፍለው ሥርዓታቸውን አያፈርሱም።

ሰንደቅ፡- በአማራ እና በትግራይ ሕዝቦች መካከል ታሪካዊ ፋይዳቸው ከፍ ያለ ማሕበራዊ መስተጋብሮች መኖራቸውን ከግምት ስናስገባ የወልቃይት ጥያቄ እና ሰልፎቹን ተከትሎ አንዳንድ የተፈጸሙ ድርጊቶች ተገማች አልነበሩም። በዚህ ላይ የእርስዎ አስተያየት ምንድን ነው?   

አቶ ንጉሱ፡- የትግራይ ክልል ሕዝብ እና የአማራ ክልል ሕዝብ የግንኙነት ገመድ የላላ ሳይሆን እጅግ ጥብቅ ነው። የቅርብ ጊዜ ሳይሆን ረጅም ታሪክ ያለው ነው። ሕዝቦቹ ወንድማማች ናቸው። አብረው ታግለዋል፣ ሞተዋል፣ በአንድ ጉድጓድ ተቀብረዋል። ይህንን ሁለቱም ሕዝቦች ያውቃሉ።

የሁለቱ ሕዝቦች ግንኙነት የማይመቻቸው ግን ሁለቱ ሕዝቦች ሲጋጩ ሁለቱ ወገኖች ሲባሉ ትርፍ የሚያተርፉ በመሐሉ ሲጨመቅ ጠብ ይልልናል ብለው የሚያስቡ ሃይሎች ሁለቱን ሕዝቦች ለማጫራስ የተለያዩ ሙከራዎች ያደርጋሉ። የተለያዩ ቅስቀሳዎች ያደርጋሉ። እነዚህን የጥፋት ኃይሎች ለመታገል ሁለቱም ሕዝቦች እጅ ለእጅ ተያይዘው ይሰራሉ። አሁንም ቢሆን በሁለቱ ክልሎች መካከል በሁለቱ ሕዝቦች መካከል ቅንጣት ታክል የአቋም መዋዠቅ፣ መጠራጠር እና ጠብ የለም። ሊኖርም አይችልም። ምክንያቱም ሁሉም አካባቢውን ያለማል ያሳድጋል እንጂ አንዱ በሌላ መልክ ሌላውን ሕዝብ እያየ የሚቀጥልበት ሁኔታ እንደሌለ በበቂ ሁኔታ የአማራ ሕዝብ ይረዳል። በዚህ መልክ ነው መታሰብ ያለበት።

ሰንደቅ፡- እውነቱ ይህ ከሆነ፣ ተገማች ያልሆኑ ተግባሮች አደባባይ እስከሚወጡ ድረስ ምን እየሰራችሁ ነበር? ከፖለቲካ አመራሩ፣ ከደህንነት መዋቅሩ እና ከተለያዩ ሕዝባዊ አደረጃጀቶች ይህንን መሰል ተገማች ያልሆነ ተግባር አምልጦ እንዴት ሊፈጸም ቻለ?

አቶ ንጉሱ፡- ይህ የሆነው ሲንከባለሉ የነበሩ ጥያቄዎች፣ አሁን እኛ የምንፈጥራቸው የመልካም አስተዳደር ችግሮችን መፍታት ባለመቻላችን ነው። ሕብረተሰቡ እነዚህን ችግሮች ለመፍታት እየተንቀሳቀሰ ነው ብለን ችግሮቹን ለመፍታት ከዛሬ ዓመት ነሐሴ ጀምሮ ድርጅትም መንግስትም ቃል ገብተው ርብርብ እየተደረገ ነው። ከፍተኛ ርብርብም እየተደረገም በሚፈለገው መጠን ችግሮቹን ለመቅረፍ ብዙ ሥራዎች ይቀራሉ። ቅሬታዎቹን ቀደም ብለን እናውቃቸዋለን። እነዚህን ቅሬታዎች በበቂ መልክ ካልፈታን ሀገር እንደሚበተንም እናውቃለን። ስለዚህም ሀገር ለማዳን እየሰራን ነው።

ሰንደቅ፡- የመጨረሻዎቹን የኢሕአዴግ የባሕርዳር እና የመቀሌ ጉባኤዎች ዋነኛ አጀንዳዎች የነበሩት መልካም አስተዳደር እና የኪራይ ሰብሳቢ ፖለቲካ ኢኮኖሚ የበላይነት መያዙን የሚያትቱ ነበሩ። በሁለቱም ጉባኤዎች የተላለፈው ውሳኔ ሁለቱንም ችግሮች ለመድፈቅ ነበር። ዛሬም እርስዎም በተመሳሳይ ሁኔታ ቃል እየገቡ ነው። አብዛኛው ሕብረተሰብ የሚለው፣ ኢሕአዴግ ሌላው ቢቀር እራሱ ፓርቲው ያመነውን፣ በሰነድ ያሰፈረውን ችግሮቹን እንኳን ለመፍታት ፖለቲካዊ ቁርጠኝነት እርቆታል። የመሐላ መንግስት ሆኗል ነው። በዚህ ላይ የእርስዎ ምላሽ ምንድን ነው?

አቶ ንጉሱ፡- ይህንን ግምገማ ኢሕአዴግ ሆነ ብአዴን ሲያስቀምጥ ለይስሙላ አይደለም። ከልባችን ነው። ሀገር እና ሕዝብ ለመምራት ለመቀየር ኃላፊነት የተሸከመ ድርጅት ነው። በተጨባጭ ደግሞ በአይን የሚታይ የሚዳሰስ ለውጥ ያመጣ ድርጅት ነው፣ መንግስት ነው። ዓለም የመሰከረለት ለውጥ ሲመጣ ግን እጥረቶችም ነበሩ። አሁንም እነዚህን እጥረቶች ለመፈታት አቅም አለኝ ብሎ ነው፣ ኢሕአዴግም ብአዴንም ለሕዝቡ ቃል የገቡት።

በብአዴን በኩል እነዚህን ችግሮች ንቅስ አድርጎ አውጥቶ ደረጃ በደረጃ ባለፉት ወራት ከሕዝቡ ጋር ውይይት አድርጎ ሕዝቡ ያነሳው ጥያቄዎች የትኞቹ ተፈቱ፣ ያልተፈቱት የትኞቹ ናቸው እያለ እየገመገመ ለሕዝብ ማቅረብ ጀምሯል። አመራሩ በየጊዜው ከሕዝቡ ቅሬታዎች እየተቀበለ እየተነተነ ችግሮቹን እየፈታ ነው ያለው። የአማራ መገናኛ ብዙሃን በግልጽ የህዝቡን ችግሮች እንዲያስተናግዱ አቅጣጫ አስቀምጠን እየሰራን ነው። ሕዝቡ የሚያቀርባቸው የመልካም አስተዳደር ችግሮች በመገናኛ ብዙሃን በቀጥታ ለሕዝቡ እንዲቀርቡ እየተደረገ ነው። የክልሉ ርዕሰ መስተዳደር ጨምሮ በመገናኛ ብዙሃን ከሕብረተሰቡ ጥያቄዎች በቀጥታ እንዲቀርቡ እየተደረገ ምላሽ እንዲሰጡባቸውም እየተደረገ ነው። ምላሽ ለሚያስፈልጋቸውም ጥያቄዎች ቃል እንዲገቡ ይደረጋል። ይህንን ሥራችንን ሕዝባችንም ያረጋግጣል። የተሰራው ሥራ ግን አሁንም በቂ አይደለም። በመሰረታዊነት የሕዝቡን ችግር የፈታም አይደለም። ሆኖም ግን እንደምንፈታው ሕዝቡም ያውቃል።

ስለዚህም ከጉባኤ መልስ ችግሮች አልተፈቱም ሳይሆን በመፍታት ሒደት ላይ ነው ያለነው። አሁንም በዚህ በጀት ዓመት ያሉንን ችግሮች ገምግመን ለይተን በቀጣይ በ2009 ዓ.ም ሙሉ ለሙሉ ለመፍታት ተዘጋጅተናል። ገና ጀማሪና እና በመገንባት ላይ ያለ ሀገር በመሆኑ ጥያቄዎቹ በርካታ እንደሚሆኑ የሚጠበቅም ነው። 

ይምረጡ
(6 ሰዎች መርጠዋል)
1317 ጊዜ ተነበዋል

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us