“ያለን አማራጭ፣ የኪራይ ሰብሳቢ ፖለቲካ ኢኮኖሚን ቆርጦ መጣል ወይም ሀገር እንዲበተን መፍቀድ ነው”

Wednesday, 17 August 2016 13:32

“ያለን አማራጭ፣ የኪራይ ሰብሳቢ ፖለቲካ ኢኮኖሚን ቆርጦ መጣል

ወይም ሀገር እንዲበተን መፍቀድ ነው”

አቶ ፍቃዱ ተሰማ

የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት የኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ኃላፊ

      በኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት አንዳንድ አካባቢዎች ለወራት ከዘለቀውና አሁንም እየታየ ካለው አለመረጋጋት ጋር በተያያዘ ከክልሉ የመንግሥት ኮምኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ኃላፊ አቶ ፍቃዱ ተሰማ ጋር ያደረግነው ቆይታ እንደሚከተለው ቀርቧል።

 

      (ሰንደቅ ጋዜጣ ሰሞኑን በተነሳው ተቃውሞ ህይወታቸውን ላጡ ዜጐቻችን የተሰማውን ጥልቅ ሐዘን እየገለፀ ለቤተሰቦቻቸውም መጽናናትን ይመኛል።)  

 

ሰንደቅ፡- በኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት ውስጥ የተነሳው ተቃውሞ በተለይ በአንዳንድ ቦታዎች እንደቀጠለ ነው። ሁኔታዎቹን መቆጣጠር ለምን አልተቻለም?

አቶ ፍቃዱ፡-በክልላችን ውስጥ የተፈጠረ ሁከት መኖሩ ተጨባጭ እውነታ ነው። በ2008 ዓ.ም ህዳር አካባቢ በምዕራብ ሸዋ በኩል በተወሰኑ ወረዳዎች እና ዞኖች የተቀሰቀሰ ብጥብጥ አለ። የብጥብጡ መነሻውን ከሕብረተሰቡ ጋር በጋራ ገምግመናል። እንደሚታወቀው ላለፉት አስር አመታት ከፍተኛ የኢኮኖሚ ለውጥ ያስመዘገብን በመሆናችን ከዚህ የዕድገት ለውጥ ጋር ተያይዞ የህብረተሰቡ የመጠቀም ተጨማሪ ለውጦች የመፈለግ ፍላጎቶች ጎልተው ወጥተዋል። ለምሳሌ መንገድ፣ የውሃ አቅርቦት የደረሳቸው የተሻለ ጥራት ያለው አቅርቦት ይጠይቃሉ። ከሁለት አንዱ የተሟላላቸው ሁለቱም እንዲሟላ ይጠይቃሉ። ጨርሶም ያልደረሳቸው ቅሬታ እና ተጠቃሚነት ይጠይቃሉ። ስለዚህም እድገቱ እየቀጠለ ሲመጣ ሕብረተሰቡ የተጠቃሚነት እና የተደራሽነት ጥያቄዎችን ያቀርባል። የሁሉንም ፍላጎት በአንድ ጊዜ ለማሟላት ከባድ ስለሚሆን ክፍተቶች በዚህ መካከል ይፈጠራሉ።

በዋናነት ጎልቶ የወጣው ግን የወጣቶች ሥራ አጥነት ነው። በክልላችን 8 ነጥብ 1 ሚሊዮን ወጣት ነው ያለው። ይህ ቁጥር ለሌሎች ሀገሮች አጠቃላይ የህዝብ ብዛታቸውን የሚገልጽ አሃዝ ነው። ከዚህ ያነሰ የህዝብ ቁጥር ያላቸውም ሀገሮች አሉ። በእነዚህ ሀገሮችም ሥራ አጥ ወጣቶች ይገኛሉ። በኦሮሚያ ክልል ውስጥም ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ወጣቶች ከዩኒቨርስቲ ተመርቀው ቢወጡም፣ ሁሉንም ማስተናገድ ወይም መሸከም የሚችል የኢኮኖሚ መሰረተ ልማት በተፈለገው ደረጃ ማድረስ ባለመቻሉ ወጣቶች ቅሬታ ያነሳሉ። ሥራ አጥነቱ በከተማም በገጠርም ውስጥ መኖሩ ግንዛቤ ተወስዷል። እነዚህና ሌሎች ችግሮች ተደማምረው የመልካም አስተዳደር ጉድለቶች አስከትለዋል። እነዚህ ክፍተቶች ላይ ነው የአመጽ ኃይሉ እየሰራ ያለው። በክልላችን ወጣ ገባ በሚሉ ብጥብጦች የሚስተዋሉትም በወጣቶቹ ላይ የአመጽ ኃይሉ እየሰራ ስለሚገኝ ነው። ካሳካነው የኢኮኖሚ እድገት የበለጠ ፈጣን እና አስተማማኝ ደረጃ ላይ ማድረስ ከቻልን ብጥብጡ የሚቀጥልበት እድል የለም።

ሰንደቅ፡- አሁን የሚያነሷቸውን ችግሮች የፖለቲካ አመራሩ በበቂ ዝግጅት እና አመራር ሰጪነት ለሕብረተሰቡ ለማሳወቅ የሄደበት እርቀት ምን ይመስላል?

አቶ ፍቃዱ፡-በነገራችን ላይ ከላይ የገለጽኩትን እና ለሌሎች ሁኔታዎችን ለሕብረተሰቡ በግል ተንትኖ አቋም እንዲይዝባቸው የሰራናቸው ሥራዎች ክፍተት ነበረባቸው።

ሰንደቅ፡- በምሳሌነት የሚጠቅሱት ይኖር ይሆን?

አቶ ፍቃዱ፡-አዎ። የአዲስ አበባ ማስተር ፕላን ለዚህ ጥሩ ማሳያ ነው። የዚህ ማስተር ፕላን እቅድ በሶስተኛ ወገኖች ተጠልፎ ለህብረተሰቡ በቀረበበት አግባብ ሳይሆን ከዘላቂ የከተሞች እድገት ጋር ተመጋጋቢ የሆነ የጋራ ልማት ተጠቃሚነትን በሚያንጸባርቅ መልኩ በአዎንታዊ ፍላጎት የተዘጋጀ ነው። ሕዝቡ ላይ የተረጨው የተሳሳተ መረጃ ሕብረተሰቡን ወደ ጥርጣሬ ውስጥ በመክተቱ ለብጥብጥ በር ከፍቷል። ሕዝቡም ጥርጣሬውን በማቅረቡ መንግስት የህዝቡን ድምፅ ሰምቷል።

ሌላው የኦሮሚያ ከተሞች አዋጅ ወጥቶ ነበር። አዋጁ ለኦሮሚያ ከተሞች እድገት አይነተኛ ጠቀሜታ አለው። ሆኖም ግን በዚህ አዋጅም ላይ ከሕብረተሰቡ ጋር የጋራ ግንዛቤ ባለመወሰዱ ጥርጣሬዎችን አስከትሏል። እዚህ ላይ ነው የአመጽ ኃይሎች የተጠቀሙበት። ለልማት የተቀረጸ አጀንዳን ለአፍራሽ ተልኳቸው ተጠቀሙበት። ሁከት ለመቀስቀስም አዋሉት። በመንግስት በኩል ምንም ያህል የልማት አጀንዳን የሚያሳካ እቅድ ቢሆንም ሕብረተሰቡ ካልተቀበለው ወደ ተግባር ውስጥ አያስገባውም። ለሕዝቡ ፍላጎት ቅድሚያ ይሰጣል።

ሰንደቅ፡- ከአዲስ አበባ ማስተር ፕላን ጋር በተያያዘ በስፋት ይነሳ የነበረው የገበሬዎች መፈናቀል ነበር። በዚህ ላይ ያልዎት አስተያየት ምንድን ነው?

አቶ ፍቃዱ፡-በርግጥ እንዳልከው ከአርሶ አደሮች መፈናቀል ጋር በተያያዘ ብዙ ሲነገር ነበር። መታወቅ ያለበት ግን ኢንቨስትመንት የሀገር እድገት ጉዳይ ነው። የሥራ ዕድል የመፍጠር ጉዳይ ነው። የውጭ ምንዛሪ የማግኘት ጉዳይ ነው። የቴክኖሎጂ ሽግግር ጉዳይ ነው። ከገጠር ወደ ከተማ የሚደረግ እድገት ነው። ከግብርና ወደ ኢንዱስትሪ የሚደረግ ሽግግር ነው። በአጠቃላይ ኢንቨስትመን በአንድ ሀገር ውስጥ ሁለንተናዊ ተፅዕኖ የሚያሳርፍ ዘርፍ ነው። የዓለም የእድገት ሽግግር ያለፈበት ሒደት ነው። በኢትዮጵያ ውስጥ የሚደረገውም ከዚህ የተለየ አይደለም።

ሰንደቅ፡- ለአርሶ አደሩ የሚሰጠው የተነሺነት ካሳ ጥያቄ ከሚቀርብባቸው አንዱ ነው። በሚሰጠው ካሳ ላይ ያደረጋችሁት ግምገማስ ይኖር ይሆን?

አቶ ፍቃዱ፡- የካሳው የክፍያ መጠን ብቻ ሳይሆን፣ ካሳ የተቀበለ አርሶ አደር በቀጣይ የወሰደውን የካሳ ገንዘብ ምን ላይ እንደሚያውለው አመላካች የሆነ የህግ ማዕቀፍም አልነበረም። ከዚህ በመነሳት ሶስት መሰረታዊ ችግሮቹን መፍቻ አስቀምጠናል።

ይሔውም፣ አንደኛ የሚሰጠው የመሬት ካሳው ገበያን ያማከለ እና የገንዘብ የመግዛት አቅምን ያገናዘበ እንዲሆን። ሁለተኛ፣ ካሳውን አርሶ አደሩ ከተቀበለ በኋላ ምን ላይ እንደሚያውለው? እንዴት ዘላቂነት ወዳለው ሕይወት ካሳውን መለወጥ እንደሚችል የሚያግዝ ኤጀንሲ ተቋቁሟል። ሶስተኛው በለቀቀው መሬት ላይ በሚገነቡ የኢንቨስትመንት እድሎች አርሶ አደሩ ቀጥተኛ ተጠቃሚ የሚሆንበትን አሰራር ተዘርግቷል። አርሶ አደሩ እና ልጆቹ ሥራ ዕድሎች የሚያገኙበትን ሁኔታዎች የሚያመቻች አሰራር ተዘርግቷል።

ከዚህ በተያያዘ የሚነሳው የወረዳ እና የዞን ጥያቄዎች ናቸው። ሰፋፊ ወረዳዎች በመኖራቸው ለአሰራር ቅልጥፍና አመቺ አለመሆናቸው ተነስቶ ነበር። በተለይ በ22 ወረዳዎች አገልግሎት ለማግኘት ሕብረተሰቡ ከፍተኛ ርቀት የሚጓዝ በመሆኑ ለአሰራር አመቺ በሆነ መልኩ ወረዳዎች ተፈቅደው ችግሩ ተቀርፏል። የዞን ጥያቄዎችም በኢሊባቡር ለረጅም ጊዜ ሲጠይቅ ነበር። በደሌ ላይ ዞን እንዲቋቋም ከሕብረተሰቡ ጋር ተማክረን ፈተነዋል። እንዲሁም ምዕራብ ጉጂ በተመሳሳይ ሁኔታ ቡሌ ቦራ ላይ የተፈቀደበት ሁኔታ አለ። 

የተነሱ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ደረጃ በደረጃ ከክልላችን ሕብረተሰብ ጋር በመነጋገር እየፈታን ነው ያለነው። አሁንም ብዙ ርቀት መጓዝ ይጠብቀናል።

ሰንደቅ፡- ችግሩ የመልካም አስተዳደር መጓደል መሆኑ ግንዛቤ ተወስዶ ምላሽ እየሰጣችሁ መሆኑን አስቀምጠዋል። ሆኖም በኦሮሚያ የተቀሰቀሰው ተቃውሞ እንደቀጠለ ነው። እነዚህን ሁኔታዎች እንዴት ያስታርቋቸዋል? ተቃውሞውስ በመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች ዙሪያ ብቻ የታጠረ ነው ብሎ መውሰድ ይቻላል?

አቶ ፍቃዱ፡-በእኛ በኩል በተወሰደው የመልካም አስተዳደር ችግሮች ዙሪያ ምላሽ እየሰጠን ሕብረተሰቡም አንፃራዊ እርካታ እያገኘ ተያይዘን እየሰራን ነው። ሆኖም በክልሉ ውስጥ የተጀመረው ብጥብጥ ወጣ ገባ እያለ እንደቀጠለ ነው የሚታየው ለሚለው ምላሽ ለመስጠት የጥፋት ኃይሎቹ የብጥብጥ ማስነሻ ምክንያቶችን መመልከት ተገቢ ነው የሚሆነው።

ይኽውም፣ መንግስት ባልሰራቸው የመልካም አስተዳር ጉድለቶች መነሻ ሕብረተሰቡን ወደ ሚፈልጉት አጀንዳ ለማነሳሳት ከፍተኛ ሥራዎች ሲሰሩ ነበር። ወደ ሚፈልጉት አጀንዳዎች የተንቀሳቀሰ የህብረተሰብ ክፍል አለ ብለው አምነዋል። ስለዚህም በመልካም አስተዳር ጉድለት ሽፋን ሕብረተሰቡን ማንቀሳቀስ ከቻልን ለምን ወደ ስርዓት ለውጥ ብጥብጡን አናደርሰውም ብለው እየሰሩ ነው የሚገኙት። ሕገ መንግስታዊ ስርዓቱን በኃይል ለመገርስ ወጣቱ ላይ እየሰሩ ነው። ስለዚህም በክልላችን ውስጥ የተፈጠረው የመልካም አስተዳደር ጥያቀዎችን ይዘታቸውን በመቀየር ወደ ስርዓት ለውጥ እየተንቀሳቀሱ መሆናቸውን አሁን አመራሩ ግንዛቤ ወስዷል።

ለዚህ ድምዳሜ በቂ ማሳያ የሚሆነው ይህ የጥፋት ኃይል በሕብረተሰቡ ውስጥ ሰርጎ በመግባት በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በአሸባሪነት የተፈረጀውን የኦነግ ባንዲራዎች ሲያውለበልብ ተመልክተናል። ሆኖም ግን በክልላችን ከሚገኙት 8 ነጥብ 1 ሚሊዮን ወጣቶች መካከል በዚህ ተግባር ውስጥ የተሰለፉት በጣም ጥቂቶች ናቸው። አጠቃላይ እንቅስቃሴው ግን ከመልካም አስተዳደር ጉድለት ጋር ከነበረው በጣም የራቀ የስርዓት ለውጥ ናፋቂዎች አጀንዳ መሆኑ ግንዛቤ መውሰዱ ጥሩ ነው።

ሰንደቅ፡- በአሁኑ ወቅትም በኦሮሚያ ክልል ውስጥ ግን ተደጋጋሚ ሰልፎች ይደረጋሉ። በዚህ ላይ ያልዎት አስተያየት ምንድን ነው?

አቶ ፍቃዱ፡-ሰልፍ መደረጉ መብት ነው። ጥያቄው ሰልፉን የጠራው አካል ማን ነው? ሰልፉ ለምን ዓላማ ነው የተጠራው? ሰልፉ የት እና መቼ ነው የሚከናወነው? እነዚህን መመለስ የሚችል ሰልፍ ተደርጎ ከሆነ ምላሽ መስጠት ይቻላል። እንደማንኛውም ግለሰብ በማሕበራዊ ድረ ገፆች የተጠራ ሰልፍ ነው የሚል መላመት ተይዞ የሚሰጥ ምላሽ የለም። ለሰልፉ ትርጓሜም መስጠት አይቻልም። መንግስት ለባለቤት አልባ ሰልፎች ከዚህ በፊት ምላሽ የሰጠው ሕብረተሰቡን ከተሳሳተ መረጃ መጠበቅ ካለበት ኃላፊነት መነሻ እንጂ ለሰልፎቹ እውቅና በመስጠት አለመሆኑ መታወቅ አለበት። ሰልፉም የዋለው ለሁከት እና ለብጥብጥ ነው። የዜጎችም ህይወት ጠፍቷል። መሆን ያልነበረባቸው በርካታ ኃላፊነት የጎደላቸው ተግባሮች ተፈጽመዋል።

ሰንደቅ፡- የተወሰደው እርምጃ ተመጣጣኝ አለመሆኑን ዓለም ዓቀፍ ተቋማት እና ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች እንዲሁም አንዳንድ ዜጎችም ሲናገሩ ይደመጣል። በተወሰደው እርምጃው ላይ ያላችሁ አረዳድ ምን ይመስላል?

አቶ ፍቃዱ፡-መንግስት በጠፋው የዜጎች ህይወት የተሰማውን ሐዘን ገልጿል። ከፍተኛ የሀገር ሀብትም ወድሟል። በዚህ ሁኔታው ውስጥ የተወሰደው እርምጃ ተመጣጣኝ ነው፣ አይደለም የሚለውን በገለልተኛ ወገን የሚጣራ እንጂ መንግስት ምን ሊል ይችላል። ይህንን ለማጣራት የተቋቋመ ተቋም ሥራ ነው የሚሆነው። የነበረው ሁኔታ ግን እጅግ አደገኛ መሆኑ የሚካድ አይደለም።

ይኽውም፣ በሕግ ቁጥጥር ስር የዋሉ እስረኞችን ለማስፈታት መሞከር፣ የፀጥታ ኃይሎችን መሣሪያ በኃይል የመቀማት፣ የፀጥታ ኃይሎችን በጦር መሳሪያ መግደል፣ እነዚህ ተግባሮች በምንም መመዘኛ የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች የወለዳቸው ናቸው ተብሎ የሚወሰዱ አይደሉም። በመልካም አስተዳደር ሽፋን በሌሎች ሀገሮች እንደሚደረገው ግልፅ የሆነ የቀለም አብዮት ነው የጥፋት ኃይሉ ለመፈጸም የሞከረው። በክልላችን ውስጥ ይህን የቀለም አብዮት ለመተግበር የተንቀሳቀሰው ኃይል የኦነግ ባንድራ እና የሚታወቁ መፈክሮችን እያሰሙ ነበር። በሌሎች ክልሎችም የተደረጉት እንቅስቃሴዎች የተበታተኑ ሳይሆን ግንባር የፈጥረው የፈጸሙት ስለመሆኑ ብዙ ማሳያዎች ማቅረብ ይቻላል።

ሰንደቅ፡- በአንዳንድ ተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲዎች እና በማሕበራዊ ሚዲያ ንቁ የፖለቲካ ተሳትፎ ያላቸው ሰዎች ኦሕዴድ የኦሮሞን ሕዝብ አይወክልም የሚሉ ክሶች ሲሰነዝሩ ይሰማል። በዚህ ላይ ያልዎት አስተያየት ምንድን ነው?

አቶ ፍቃዱ፡-እነዚህ ኃይሎች ኦሕዴድ የኦሮሞ ሕዝብ ውክልና የለውም ብለው የሚከሱት ኦሕዴድ በኦሮሞ ሕዝብ ውስጥ ማሕበራዊ መሰረት የለውም ከሚል መነሻ አይደለም። የክሳቸው መሰረታዊ መነሻ በአመለካከት ስለምንለያይ ነው። አንደኛው የትምክህት አመለካከት ነው። ይህ አመለካከት በመዋቅር ደረጃ የፈረሰ ቢሆንም የሞተ ግን አይደለም። ከፍተኛ ትግል ይፈልጋል። የኢኮኖሚ መሰረታችን እየሰፋ ሲሄድ ሊሞት የሚችል አመለካከት ነው። ሁለተኛው፣ ከጥበት አመለካከት ጋር የሚያያዝ ነው። እንደሕዝብ የኦሮሞ ሕዝብ የጥበት አመለካካት የለውም። መሰረታቸውን በኦሮሞ ሕዝብ ላይ ያደረጉ ሆኖም የጥበት አመለካከትን በማራመድ ፖለቲካዊ ግባቸውን የሚያሳኩ የሚመስላቸው ኃይሎች አሉ። ለዚህ ጥሩ ምሳሌ የሚሆነው ኦነግ ነው።

በእነዚህ ሁለት አደገኛ አመለካከቶች የታጠሩ የፖለቲካ ኃይሎች፣ ዴሞክራሲያዊ ብሔርተኝነትን መሰረት ያደረገውን የኦሮሞ ሕዝቦች ዴሞክራሲያዊ ድርጅት - ኦሕዴድን ሲከሱ ይደመጣሉ። ወደፊትም ይከሳሉ። አሁንም የሚከሱት ክስ ተመሳሳይ ነው። የኦሮሞን ሕዝብ ከሌሎች ብሔር ብሔረሰቦች ነጥሎ አዲስ የኦሮሞ ገዢ መደብ መፍጠር ነው ዓላማቸው። ይህንን አይነት ተመሳሳይ ታሪኮች ያለፍናቸው የማያዋጡ የጣልናቸው ናቸው። ከሌሎች ብሔር ብሔረሰቦች ጋር በእኩልነት ለመኖር እንጂ የገዢ መደብ ለመመስረት ኦሕዴድ መቼም ቢሆን ትግል ውስጥ አይገባም።

ሰንደቅ፡- ሰሞኑን የቀድሞ የመከላከያ ሚኒስቴር ኤታማዦር ሹም የነበሩት ጀነራል ፃድቃን በለቀቁት ጽሁፋቸው ላይ፣ የኢሕአዴግ ፀረ-ዴሞክራሲያዊነትነት ያጎላነው ብለው ከጠቀሱት ውስጥ ከኦነግ ጋር የነበረውን ቅራኔ አፈታት ነው ብለዋል። በዚህ በጀነራሉ ሃሳብ ኦሕዴድ ምን ይላል?

አቶ ፍቃዱ፡-ድርጅቱ የግለሰቦችን የመፃፍ መብት ያከብራል። በግለሰቦች ጽሁፍ ላይም ድርጅቱ የሚለው ነገር የለም። ሆኖም ኦነግ በራሱ ጊዜ የሽግግር መንግስቱን ቻርተር ረግጦ እንደወጣ ግን ድርጅቱ ያውቃል።

ሰንደቅ፡- ጠቅላይ ሚኒስትር ኃ/ማሪያም ደሳለኝ ከኦሮሞ ሕዝብ አባ ገዳዎች ጋር ከተወያዩ በኋላ በብጥብጡ በደረሰው አደጋ ለተጎዱ ወገኖች ካሳ እንደሚሰጥ መናገራቸው ይታወሳል። የካሳ ሒደቱ ምን ደረጃ ላይ ይገኛል?

አቶ ፍቃዱ፡- እኔ እንዳለኝ መረጃ አባ ገዳዎቹ የጠየቁት የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎችን ነው። በቦረና በኩል የዩኒቨርስቲ ጥያቄ ነበራቸው። የመንገድ እና የዘገዩ ፕሮጀክቶች ጥያቄዎችም ነበሩ። እነዚህ ጥያቄዎች ከክልል ርዕሰ መስተዳድር ጋር መክረውበታል። ጥያቄዎቹ የፌደራል መንግስት የሚመልሳቸው በመሆኑ ከጠቅላይ ሚኒስትር ኃ/ማሪያም ደሳለኝ ጋር ተገናኝተው ተወያይተዋል። በብጥብጡ ለጠፋው ንብረትም ሆነ ሕይውት በኦሮሞ ባሕል እና እሴቶች መሰረት ድጋፍ ይደረጋል። የግጭት አፈታቱም በባሕላችን የሚፈጸም ነው የሚሆነው።

ሰንደቅ፡- በተነሳው ተቃውሞ የተያዙ በርካታ ዜጎች አሉ። የእነዚህ ዜጎች በማረሚያ ቤቶች ውስጥ ያለው አያያዝ ምን ይመስላል?

አቶ ፍቃዱ፡-በነገራችን ላይ እንደዚህ አይነት ብጥብጥ በሚፈጠርበት ወቅት  በአብዛኛው የሚያዘው ሳያውቅ የተቀላቀለው እና በማረጋጋት ላይ የሚገኙ ዜጎች ናቸው። ነውጡን የሚመሩት ከጀርባ የሚደበቁ በመሆናቸው የሚያመልጡበት እድል ሰፊ ነው። ግጭትም ስለሚፈጠር በቦታው ላይ የመለየት ስራዎች መስራት ከባድ ነው። ሆኖም ከጉዳዩ ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት የሌላቸው በአንድም በሌላ መልኩ በግጭቱ ወቅት የተያዙ ወዲያው ነው የሚለቀቁት። የተለቀቁም አሉ። በሁለተኛ ደረጃ በብጥብጡ ቀጥተኛ ተሳታፊ የሆኑ ሆኖም በንብረት እና በሰው ሕይወት ላይ ጉዳት ሲያደርሱ እጅ ከፍንጅ ያልተያዙ ዜጎች፣ በቀጥታ ወደ ተሃድሶ ነው የሚገቡት። ስለሕግ የበላይነት በቂ ግንዛቤ እንዲወስዱ ይደረጋል። በሶስተኛ ደረጃ ያሉት፣ በብጥብጡ ላይ ቀጥተኛ ተሳታፊ በመሆን የሕይወት የቀጠፉ ንብረት ያወደሙ ዜጎች በሀገሪቱ ሕግ በመደበኛ ፍርድ ቤት የሚዳኙ ነው የሚሆነው።

ሰንደቅ፡- በግልፅ የሚባለውን ለማስቀመጥ፣ ኦሕዴድ “በሕወሓት ከፍተኛ ባለስልጣኖች የሚዘወር ፓርቲ ነው” የሚል ክሶች በተደጋጋሚ ይሰማሉ። ድርጅታችሁ በዚህ መሰል ክሶች ላይ ምን ይላል?

አቶ ፍቃዱ፡- አንተ በክስ መልክ አቀረብከው እንጂ ከሃያ ዓመታት በላይ በተቃዋሚ ጎራ የተሰለፉ ኃይሎች የዘወትር መዝሙር ነው። ያረጀ፣ የከሸፈ የፖለቲካ ስልት ነው። በሌሎች ድርጅቶችም ላይ ተመሳሳይ መዝሙር ነው የሚዘምሩት። ኦሕዴድ ከማንም ስር አይደለም። ከማንም የበላይ አይደለም። ሕወሓት ከማንም ስር አይደለም። ከማንም የበላይ አይደለም። ግንባር መስርተን በእኩያነት ነው የምንሰራው። የምንከተለው መስመር አብዮታዊ ዴሞክራሲ ነው። በፕሮግራም እና በዓላማ ነው የተገናኘነው።

ኦሮሚያን የሚያስተዳድረው ኦሕዴድ ነው። የኢሕአዴግ ዓላማ እና ፕሮግራም አራቱም ፓርቲዎች በክልሎቻቸው ውስጥ ነው የሚተገብሩት። የክልሎቹ አስፈፃሚ፣ ሕግ አውጪ እና ሕግ ተርጎሚ አካሎች ናቸው የእለት ተዕለት ስራዎችን የሚፈጽሙት። የአዛዥና የታዛዥ ግንኙነት የለም። ድምጽ በድምጽ የመሻር መብት ያለው አንድም አካል የለም።

የዘማሪዎቹ እምቅ ፍላጎት ግን የአንድ ብሔረሰብ የበላይነት አለ የሚል የተሳሳተ መረጃ በማስፋፋት የዴሞክራሲ ብሔርተኞችን እንቅስቃሴ በመቀልበስ፣ የትምክህትና የጥበት አስተሳሰባቸውን በሕዝብ ላይ ለመጫን ነው።

ሰንደቅ፡- አሁን ከተፈጠሩት ችግሮች እንዴት መውጣት ይቻላል?

አቶ ፍቃዱ፡-የጥፋት ኃይሎቹ ሕዝባዊ መሰረት ይዘው አይደለም እየሰሩ ያሉት። እነዚህ ኃይሎች መሰረታቸውን ያደረጉት ባልተሰሩ የመልካም አስተዳደር ጉድለቶች እና በኪራይ ሰብሳቢው ላይ ነው። ስለዚህም ያለው አማራጭ፣ እነዚህ የጥፋት ኃይሎች ሀገር እንዲበትኑ መፍቀድ ወይም የመልካም አስተዳደር ችግሮች መፍታት እና የኪራይ ሰብሳቢ ፖለቲካ ኢኮኖሚን ነቅሎ መጣል ብቻ ነው። ድርጅታችን ችግሩን በዚህ አቅጣጫ ለመፍታት ነው ያስቀመጠው። 

ይምረጡ
(3 ሰዎች መርጠዋል)
1134 ጊዜ ተነበዋል

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us