የኢሕአዴግ የ1993 ተሃድሶ እና የ2008 የዳግም ተሃድሶ ንቅናቄዎች፣ መሰረታዊ ልዩነታቸው ምንድን ነው?

Wednesday, 24 August 2016 14:45

የኢህአዴግ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ከነሐሴ 10 እስከ ነሐሴ 15 ቀን 2008 .ም ድረስ ስብሳባ ማካሔዱን አስታውቋል። በዚህ ስብሳባው ያለፉትን አስራ አምስት ዓመታት የተጓዙበትን የፖለቲካ ኢኮኖሚ መንገዶችን መገምገሙን ይፋ አድርጓል። እንዲሁም ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴው በድርጅቱ የቀረበለትን የአስራ አምስት ዓመታት የፖለቲካ ኢኮኖሚ ሒደቶችን የሚመለከት የግምገማ ሃሳብ መነሻ በማድረግ በኢትዮጵያ ውስጥ የተመዘገቡ አዎንታዊ ለውጦች እና በተጨባጭ የሚታዩ ድክመቶችን በዝርዝር ተመልክቶ ገምግሟል።

የኢህአዴግ ሥራ አስፈፃሚ የአስራ አምስት ዓመታት የፖለቲካ ኢኮኖሚ ግምገማውን ሲያደርግ መነሻ ያደረገው የድርጅቱን አራተኛ ጉባኤ እንደሆነ ይታመናል። የተሃድሶ መስመር የማጥራት እርምጃ ድርጅቱ የወሰነው በ1993 ዓ.ም. ቢሆንም በጉባኤ አጻድቆ ወደ ተግባራዊ ሥራዎች የገቡት ከአራተኛው የድርጅቱ ጉባኤ በኋላ ነው።

በዚህ ጹሁፍ በ1993 ዓ.ም. የነበረው የተሃድሶ ንቅናቄ መነሻዎች ምን ነበሩ? በአራተኛው ጉባኤ የድርጅቱ ውሳኔዎች እና የመስመር መረጣው ምን ይመስል ነበር? የሚሉትን ሰነድ ይመለከታቸዋል። በመቀጠል የ2008 ዓ.ም በሥራ አስፈፃሚው ይፋ የሆነው የተሃድሶ መስመር ምን የተለየ ይዘት አለው? ድርጅቱ ያስመዘገባቸው የለውጥ ጉዞዎች በሥራ አስፈፃሚው የቀረቡትን እና ለሌሎች ተያያዥ ጉዳዮችን ለማንሳት ይሞክራል።

 

1993 የተሃድሶ መስመር

የ1993 የተሃድሶ መስመር አስፈላጊነት የተነሳው በመሰረታዊነት በኢትየ-ኤርትራ ጦርነት መነሻ ነው። በተለይ ኢሕአዴግ በኤርትራ ጉዳይ ከፍተኛ ዋጋ የከፈለ ድርጅት ከመሆኑ በላይ በኤርትራ ሕልውና ላይ ትክክለኛ መስመር መከተሉን የሚያምን ድርጅት ነው። ይህም በመሆኑ ሻዕቢያ ከጀርባው በጩቤ ሊወጋው ቀርቶ ከሻዕቢያ ጋር መሰረታዊ ተቃርኖ ውስጥ እንገባለን የሚል ትንታኔ እንዳልነበረው ሰነዶቹ ያሳያሉ። ሻዕቢያ ግን ከጀርባው ወጋው። ጦርነቱ ግን በኢትዮጵያ መንግስት አሸናፊት መቋጨቱ የሚታወስ ነው።

የ19993 ዓ.ም የተሃድሶ መስመር በኢሕአዴግ መሰረታዊ ችግሮች ተብለው የተለዩትን በሁለት መንገድ የሚቀመጡ ናቸው። አንደኛው (አንጃው እየተባለ የሚጠራው ቡድን) ያቀረባቸው መሰረታዊ ችግሮች፣ “የተወሰነው አመራራችን ተንበርካኪ መሆኑ ነው፣ ለሻዕቢያ እና ለኢምፔሪያሊዝም ያደረው። የላብአደር ፓርቲያችን የፈረሰው፣ ይኽው ተንበርካኪ ኃይል በኢምፔሪያሊዝም ስለተገዛ ነው።” የሚል ነበር።

ሁለተኛው (አሸንፎ የወጣው የተሃድሶ መስመር ኃይል የሚባለው) ያቀረባቸው መሰረታዊ ችግሮች፣ “የጥገኝነት (የኪራይ ሰብሳቢ) ዝቅጠት በድርጅታችን ውስጥ ስር ሰዶ የድርጅቱን ዴሞክራሲያዊ ባሕሪ አሽመድምዶ፣ አብዮታዊ ልማታዊ ባህሪን ስላመነመነው ነው። ኢትዮጵያ ከምዕራቡም ዓለም ጋር በጋራ ጥቅም ላይ ግንኙነት መመስርቷ ትክክለኛና ወቅቱ የሚጠይቀው ጉዳይ ነው። ስለኢምፔሪያሊዝም ያረጀ ያፈጀ መፈክር ማንሳት ሽፋን ፍለጋ ነው” የሚል ነበር።

በእነዚህ ሁለት መሰረታዊ ልዩነቶች በሕወሓት በኩል ለአንድ ወር በተደረገው ውይይት በ15 ለ13 አንጃው መሸነፉን የድርጅቱ ሰነድ ያሳያል። አንጃው በኦህዴድና ደኢህዴን ላይ የተመሰረተ የስንጠቃ ሙከራውን እስከመጨረሻ ገፍቶ የነበረ ቢሆንም በተወሳሰበ ትግል መክሸፉንም በሰነዱ ሰፍሯል። ብአዴን ከሞላ ጎደል ሁሉንም አጀንዳዎች አንጃውን በሚቃወም አቅጣጫ በተባበረ ድምፅ የደመደሙበት ሁኔታ ፈጥሮ እንደነበር ተገልጿል።

በመጨረሻም በአቶ መለስ ዜናዊ የተመራው ንቅናቄ አዲስ ኃይል ሆነ በመውጣት ድርጅቱን ተቆጣጥሯል። በመቀጠልም የተሃድሶ መሰረታዊ ጉዳዮችን ላይ የተዘጋጁ ፅሁፎች በአራቱም ድርጅቶች በሰፊው ተበትነው ክርክር ውይይት እንዲካሄድባቸው ተደረገ። አራቱም ፓርቲዎች በተዘጋጀው የውይይት ሰነዶች ላይ ከተወያዩ በኋላ አራተኛው የድርጅቱ ጉባኤ ተካሔደ። ጉባኤውን በተመለከተ ከድርጅቱ ሰነድ ላይ የተወሰደው ቃል በቃል በዚህ መልክ ቀርቧል።

 

አራተኛው ጉባኤ በከፊል

“አራተኛው ጉባኤ የድርጅታችን ዋነኛ ችግር ምን እንደሆነ በትክክል ማስቀመጡ፣ በአገራችን ፈጣን ልማትና የዳበረ ዴሞክራሲ የሚረጋገጡበት ሳይንሳዊ መስመር የቀየሰ መሆኑ፣ ከዚህ በመነሳትም የቆዩትን የድርጅቱን አብዮታዊና ዴሞክራሲያዊ አቋሞችና ባህሪያት በአዲስ መስመር ላይ መልሶ በመገንባቱ ብቻ አልነበረም ልዩና ታሪካዊ ጉባኤ የሆነው። በንቅዘት ጎዳና ረጅም ርቀት ተጉዞ የቆየው ድርጅት በምን መልኩ ሊታደስና በሂደት ዴሞክራሲያዊና አብዮታዊ ባህሪው እየተጠናከረ ሊሄድ እንደሚችል በትክክል ለይቶ ተጨባጭ ተግባራዊ መፍትሔ ስላስቀመጠም ጭምር ነው። አራተኛ ጉባኤው የድርጅታችን ዝቅጠት መሰረታዊ የፖለቲካ ኢኮኖሚ ምንጮች እንዳሉት በትክክል ያስቀመጠ ጉባኤ ስለነበረ የዝቅጠቱ አደጋ በሞቅ ሞቅ ሊወገድ እንደማይችል በተራዘመ የትግል ሂደት ብቻ ደረጃ በደረጃ እየተወገደ እንደሚሄድ ግልጽ አድርጎ ነበር።

የህዝቡን አብዮታዊ እንቅስቃሴ በልማትና በዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ዙርያ በማቀጣጠል፣ በአንድ በኩል የኪራይ ሰብሳቢነትን መሰረት መናድ በሌላ በኩል ደግሞ ድርጅቱ በአብዮታዊ ማዕበሉ ውስጥ ገብቶ እየጠራና በእንቅስቃሴው ግንባር ቀደም ሆነው የወጡትን ኃይሎች እያቀፈ መጠናከር እንዳለበት መሰረታዊና ዘላቂ መፍትሄው ይኸው እንደሆነ በትክክል አስቀምጧል። ይኸው በህዝብ እንቅስቃሴ ላይ የተመሰረተና አደጋውን የመቋቋም የተራዘመ ትግል እንደተጠበቀ ሆኖ ኢህአዴግ በጉባኤው ማግስት በነበረበትም ሁኔታ ቢሆን የህዝቡን እንቅስቃሴ ለማቀጣጠል የመጀመሪያውን ክብሪት ሊጭር የሚችልበት ደረጃ ላይ እንደደረሰ በተገቢው መንገድ አስቀምጧል።

ጉባኤው እንዲህ ወዳለ ድምዳሜ የደረሰበት ዋናው ምክንያት የተሃድሶ መስመሩ ይፋ የድርጅቱ መስመር የሆነበት ደረጃ ላይ በመድረሱ ነበር። ድርጅቱ ይህን አቋም እንደይፋ አቋም እስከያዘ ድረስ በቅድሚያና በዋናነት ይህንኑ ህዝባዊ መስመር ባለቤቱ ወደሆነው ሰፊው ህዝብ በማድረስ ህዝቡ በዚህ ዙሪያ ቀጣይ እንቅስቃሴ የሚያካሄድበትን ሁኔታ መፍጠር ይቻላል ተብሎ ስለመታመነ ነው።ህዝቡ ይህን ወደመሰለው እንቅስቃሴ ከገባ ድርጅቱም በእንቅስቃሴው ሂደት ይሻሻላል፣ ድርጅቱ ሲሻሻል የህዝቡ እንቅስቃሴ በይበልጥ ይግላል፣ የህዝቡ እንቅስቃሴ በይበልጥ ሲግል ድርጅቱ በይበልጥ ይጠራል። በዚሁ ተመጋጋቢ ሂደት የኪራይ ሰብሳቢነት ዝቅጠቱ አደጋ እየተወገደ ይሄዳል የሚል ሳይንሳዊ ድምዳሜ ስለተያዘ ነው።

ከጉባኤው ማግስት ድርጅቱ እንዲህ ዓይነቱን መስመር ከመጨበጡም ባሻገር በሂደት የፈፀማቸውን ስህተቶች በግምገማ፣ ሂስና ግለሂስ ኮርኩሞ ድርጅቱ ቢያንስ መስመሩን ለህዝቡ ለማድረስ የሚችልበት ደረጃ ላይ ደርሶ ስለነበር ነው። እናም ጉባኤው ቀጣዩ ዋና ተግባር የተሃድሶ መስመሩን በመያዝ ፈጥኖ ወደ ህዝቡ በመውረድ የህዝቡን የልማትና የዴሞክራሲ እንቅስቃሴ ማቀጣጠል ነው ብሎ ወሰነ። በዚሁ ሂደት ውስጣችንን በየጊዜው እየፈተሽን በአንድ በኩል ከህዝቡ አብዮታዊ ትግል የምናገኘውን ጉልበት በመጠቀም ድርጅታችንን በይበልጥ የምናጠራበት፣ በሌላ በኩል ደግሞ በዚሁ ሂደት ድርጅታችንን በይበልጥ አጠናከርን የህዝቡን አብዮታዊ እንቅስቀሴ በተሻለ አመራር በበለጠ ጥራትና ግለት እንዲቀጣጠል ማድረግ እንደምንችልና እንደሚገባን አስቀመጠ።

ከዚህ በመነሳት ከጉባኤው ማግስት ጀምሮ በአንድ በኩል የተሃድሶውን መስመር መሰረት በማድረግ የመንግስት የልማትና የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች እንዲከለሱ እንዲስተካከሉና ለህዝቡና ለአስፈፃሚ አካላት በሰፊውና በተከታታይ እንዲቀርቡ ሲደረግ፣ በሌላ በኩል ከዚሁ ጎን ለጎን ደግሞ መስመሩን መሰረት ያደረጉ የልማት እንቅስቃሴዎች እንዲጀመሩ ተደረገ። እናም በዚህ መልኩ ብዙ ወራትን የጠየቀ ሰፊ የስልጠናና የውይይት ስራ በአባላት፣ በህዝቡና በስራ አስፈፃሚው አካባቢ ተካሄደ። ይልቁንም ከአራተኛው እስከ አምስተኛው ጉባኤ ድረስ የነበረው የሁለት ዓመት ጊዜ በአብዛኛው የውይይት ጊዜ ነበር ማለት ይቻላል። መስመሩን ለመተግበር ከፍተኛ ርብርብ ቢደረግም ከንቅዘት ወደ ጋለ የህዝብ እንቅስቃሴ መሸጋገር እንዲህ ቀላል ነገር ሆኖ አልተገኘም። ለበኋላ ትግሉ ጥሩ ልምድ ከማግኘት አልፎ በልማት መስኩ በነዚህ ሁለት ዓመታት የሚያስደስት ውጤት ሊገኝ አልቻለም። ይልቁንም 1994 እና 95 ተከታታይ ድርቅ የታየባቸው ዓመታት ስለነበሩ ኢኮኖሚያችን በእነዚህ ዓመታት ዜሮ ወይም ከዜሮ በታች የሆነ እድገት ያሳየባቸው ዓመታት ነበሩ። ሊነጋ ሲል ያለው ጨለማ የከፋው ጨለማ ነው እንዲሉ በተሃድሶው ማግስት እንኳን ፈጣን ልማት የወትሮውን ግራና ቀኝ የሚላጋ እድገትም ማስመዝገብ ሳይቻል ቀረ።

የኢህአዴግ አመራር የተሃድሶው መስመር ድርጅት አድን ብቻ ሳይሆን ህዝብና አገር አድን መስመር እንደሆነ በሚገባ ተገንዘቦ ነበር። ኢህአዴግ በጀመረው መንገድ ዘቅጦ ቢበታተን አገሪቱ የኪራይ ሰብሳቢ፣ የትምህክትና ጠባብነት ኃይሎች ሰለባ ሆኖ እንደምትበታተን ምንም ጥርጥር አልነበረውም። መበታተኑ የህዝብ ለህዝብ መናከስን አስከትሎ አገሪቱ ከሶማሊያ ወደ ከፋ እልቂት እንደምትገባም የሚያከራክር ጉዳይ አልነበረም። በዚህ ምክንያት ነው የተሃድሶው መስመር እውን መሆን በኃይማኖት መፃሕፍት አርማጌዶን ተብሎ የሚጠራው የአስከፊ እልቂትና ፍጅት ዘመንን የማስቀረትና ህልውናን የማረጋገጥ ጉዳይ ነው ብሎ ደምድሞ የነበረው።

እናም የተሃድሶ መስመሩ አሸናፊ ሆኖ ከወጣ በኋላም ፈጥኖ ወደ ተግባር ተገብቶ ፈጣን ልማት አለመረጋገጡ እጅግ በጣም አስጨንቆትና አሳስቦት ነበር። በዚህ ምክንያት በ1995 ላይ ባካሄደው ስብሰባው የጥፋት ናዳ በከፍተኛ ፍጥነት መራመድ ጀምሯል። ከናዳው በላቀ ፍጥነት መራመድ ካልቻልን፣ ከናዳው ባነሰ ፍጥነት እንኳን ብንራመድ በናዳው ከመዋጥ አንድንም፣ ስለሆነም እንደምን ተረባርበን ፈጣን ልማት ማረጋገጥ አለብን የሚል አቋም ወሰደ። ከናዳው በተሻለ ፍጥነት ለመራመድ ምን መደረግ እንዳለበት አስቀምጦ አምስተኛውን ድርጅታዊ ጉባኤ ለማካሄድ በቃ።

አምስተኛው ጉባኤ ከናዳው በተሻለ ፍጥነት እንራመዳለን በሚል ተስፋና ይህንን ለማድረግ በሚያስችሉ እቅዶች ዙሪያ የተካሄደ ጉባኤ ስለነበረ የእመርታ ጉባኤ ተብሎ ተሰየመ። የጉባኤው አሰያየም ከምንም ነገር በላይ ከናዳው የማምለጥ ተስፋንና ቁርጠኝነትን ያንፀባረቀ፣ በልማቱና በዴሞክራሲ ስርዓት ዙሪያ እመርታዊ እድገት ለማስመዝገብ ያስችላሉ ተብለው የተገመቱ እቅዶችን የያዘ ስለነበር ነው።

እንደአጋጣሚ ሆኖ የ95-96 ክረምት ጥሩ ዝናብ የታየበት ስለነበረና ከተሃድሶው ወዲህ የተጀማመሩ ስራዎች እየተጠረቃቀሙ መጥተው ለውጥ ማምጣት የጀመሩበት ደረጃ ላይ ደርሰው ስለነበረ ኢኮኖሚው በ1996 ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ ከ13% በላይ በሆነ እድገት ተወነጨፈ። እውነትም የእመርታ ጉባኤ። 97ም ተመሳሳይ እድገት የሚመዘገብበት ሁኔታ ስለተፈጠረ በተሃድሶው ማግስት የታዩት ሁለት የጨለማ ዓመታት በሁለት ተከታታይ የብርሃን ዓመታት መተካታቸው ተበሰረ። ምድረ ኢህአዴግ ከናዳው እያመለጥን ነው፣ በእርግጥም እመርታዊ እድገት እየስመዘገብን ነው ብሎ ተስፋው ለመለመ። በእንደዚህ ዓይነት የለመለመ መንፈስና የአሸናፊነት ወኔ ላይ ሆኖ ነበር ኢህአዴግ በ1997 የሚካሄደውን ሶስተኛውን አገር አቀፍ ምርጫ እንከን የለሽ ምርጫ ሆኖ እንዲከናወን ወስኖ ለምርጫው ስኬት የተረባረበው።

ተቃዋሚዎች ከመቼውም ጊዜ በላይ ተደራጅተውና ተባብረው የህዝቡን ቅሬታዎችና ኃላቀርነቶች በትክክል አንብበው የራሳቸውንና አጋሮቻቸውን ኃይል አስተባብረው በዘመቱበት የ97ቱ ምርጫ ላይ ኢህአዴግ በተሃድሶው መስመር አሸናፊነትና ተከትሎም ምርጫው የሚካሄድበት ዓመትን ጨምሮ በተገኘው የልማት ድል በመተማመን ህዝባችን የድል መንገድ መያዛችንን አይቶ ያለአንዳች ጥርጥር በከፍተኛ ድምጽ ይመርጠናል በሚል ምኞት አይሉት ግምገማ ላይ ተመስርቶ ነበር ወደ ምርጫ 97 ዘመቻ የገባው።” ይላል ሰነዱ።

 

የሥራ አስፈፃሚው የ15 አመታት

ግምገማ ምን ይመስላል?

     የኢህአዴግ የሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ከነሐሴ 10 እስከ 15 ቀን 2008 ዓ.ም ባካሄደው መደበኛ ስብሰባ ጠንከር ያሉ ውሣኔዎችን አሳልፏል። መግለጫው በአወንታዊነት ከጠቀሳቸው መካከል፤ ህገ መንግስታዊ ዴሞክራሲያዊ የፖለቲካ ስርዓት ግንባታ በመካሄድ ላይ ነው፣ የዴሞክራሲያዊ ፖለቲካዊ ስርዓት ግንባታ ሂደት የዜጎችና የልዩ ልዩ ማህበረሰቦች የፖለቲካ መብቶች ህጋዊ እውቅናና ዋስትና አግኝተው ተከብረዋል፣ የብሄር ብሄረሰቦችን ማንነት ያስከበረ አዲስ ዓይነት ፌደራላዊ የእኩልነት ስርዓት ተገንብቷል፣ የሃይማኖት እኩልነት ተከብሮ መንግስትና ሃይማኖት ተነጣጥለዋል፣ የዜጎችና የመላ ህዝባችን ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች እንዲከበሩ ቅድሚያ ሰጥቶ የተጀመረው የዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ ህዝብ የሚጠቀምበት ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ስርዓት በመገንባት ረገድ ረጅም ርቀት ተጉዟል።
     የነደፍነውን ግብርና መር የኢኮኖሚ ልማት አቅጣጫ ተከትለን በመጓዝ ኢኮኖሚያችን ላለፉት አስራ ሶስት ዓመታት ባለ ሁለት አሃዝ ተከታታይ ዕድገት እንዲያስመዘግብ ለማድረግ ችለናል። ባሳለፍነው ዓመት ያጋጠመንና በታሪካችን ታይቶ የማይታወቀውን የድርቅ አደጋ ትርጉም ያለው የውጭ እርዳታ ሳናገኝ በራሳችን አቅም ልንቋቋም መቻላችን በአገራችን ምን ያህል የተጠናከረ የኢኮኖሚ ግንባታ ሲካሄድ እንደቆየ የሚያመላክት ነው። በከተሞች የኢንዱስትሪ ልማት በመስፋፋት ላይ ሲሆን፣ የአገልግሎት ዘርፉም እጅግ ፈጣን ዕድገት አሳይቷል። ትምህርትን በማስፋፋት ረገድ አገራችን የተጓዘችበት ሂደትና ርቀትም እጅግ የሚያስመካ ነው። ዛሬ ከአገራችን ህዝብ 30 በመቶ ያህሉ በትምህርት ገበታ ላይ ይገኛል። መከላከልን መሰረት ያደረገ የጤና ፖሊሲ በአገራችን ከፍተኛ ለውጥ ተመዝግቧል። በዚህ የተነሳ በ1983 ዓ.ም. አርባ አምስት ዓመት ብቻ የነበረው የዜጎች አማካይ ዕድሜ በአሁኑ ጊዜ ወደ 64 ከፍ ብሏል።

 

ሥራ አስፈፃሚው የነቀሳቸው ተግዳሮቶች

    የመንግስት ስልጣን የህዝብን ኑሮ ለማሻሻልና አገራዊ ለውጡን ለማስቀጠል እንዲሆን ከማድረግ ይልቅ የግል ኑሮ መሰረት አድርጎ የመመልከትና በአንዳንዶችም ዘንድ የግል ጥቅም ከማስቀደም ጋር የተያያዘ እንደሆነ አረጋግጧል።
     በአሁኑ ጊዜ ህዝብን በማስመረር ላይ ያለው ችግር ዋነኛ መንስዔ ይህ ነው። ከዚህ በመነሳት ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴው ደረጃውና መጠኑ ምንም ይሁን ምን የመንግስት ስልጣንን ካለ ያለአግባብ ለግል ኑሮ መሰረት ለማድረግ የሚታየው ዝንባሌና ስህተት መታረምና መገታት እንዳለበት፣ ይህን ለማድረግ የሚያስችል ተጨማሪ እርምጃም መውሰድ እንዳለበት ወስኗል።
    ዝንባሌው በሚታይባቸው ቦታዎች ሁሉ በአግባቡ እየተፈተሸ እንዲስተካከልና የድርጅታችን ጥራትና ጥንካሬ ተጠብቆ እንዲቀጥል አስፈላጊ የሆነው ርምጃ ሁሉ እንዲወሰድ ወስኗል። ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴው በዚህ ረገድ ከራሱ ጀምሮ የሚታዩ የጥገኝነት አስተሳሰቦችና መገለጫ የሆኑትን ጠባብነትና ትምክህተኝነትን እንዲሁም የጥገኝነት ተግባራትን በጥብቅ በመታገል ይህ አዝማሚያ እንዲገታ ለማድረግ የሚያስችሉ ዝርዝር ዕቅዶችንም አዘጋጅቷል።
    መንግስት ከህዝብ ጋር በከፈታቸው መድረኮች ሁሉ ህዝቡ ተስፋውን የማያለመልሙ ድክመቶች እንዲታረሙ ሲታገል እንደቆየም ይገነዘባል።
ድርጅታችን ኢህአዴግ ገና ከጥዋቱ ልማታዊና ዴሞክራሲያዊ መንግስት ለመገንባት ሲነሳ በአንድ በኩል መንግስታዊ ስልጣንን የህዝብና የአገር መገልገያና ጥቅም ማስከበሪያ መሳሪያ ለማድረግ በማሰብ ቢሆንም ባለንበት የዕድገት ደረጃ ጠንካራና ጤናማ መንግስት የመገንባት ጉዳይ ከፈተናዎች ውጭ ይሆናል ብሎ አያምንም። ይልቁንም እንደእኛ ባሉ የሽግግር ኢኮኖሚ ውስጥ ባሉ አገሮች ሁሉ በአንዳንዶች ዘንድ መንግስትን ከህዝብ አገልጋይነት መስመር እያስወጡ የግል መጠቀሚያ ለማድረግ የሚደረግ ጥረት የማያቋርጥ ፈተና እንደሚሆን ያምናል።
    ባለፉት ዓመታት በአገራችን የህዝብ መብትና ጥቅም ቅድሚያ አግኝቶ የተከበረበት ስርዓት ለመገንባት ባካሄድነው ትግል ካላግባብ የመጠቀም ዝንባሌ ወይም ኪራይ ሰብሳቢነት ትልቁ ፈተናችን እንደሆነ ለአፍታም ቢሆን ሳይነሳ የቀረበት ጊዜ የለም። መላው የአገራችን ህዝቦችም ቢሆኑ ካላአግባብ መጠቀም የሚሹ ሰዎች የመንግስት ስልጣንን የግል ብልፅግና ማረጋገጫ ለማድረግ በመሻት በሚፈጥሩት እንቅፋት የለመለመ ተስፋቸው ለአደጋ ሊጋለጥ እንደሚችል ያላነሱበት ጊዜ የለም።
    እነሆ ዛሬ ድርጅታችን በዚህ ችግር ምክንያት የተፈጠረውን አደጋ መሰረታዊ መንስዔዎች በሌላ በማንም ሳያሳብብ በመንግስትና በድርጅት ማዕቀፍ እንደሚታይ ቀዳሚ ችግር እንደሆነ ተገንዝቦ ይህንኑ ለማስተካከል የሚያስችል እንቅስቃሴ ጀምሯል። እንቅስቃሴው በአዲሱ በጀት ዓመት መጀመሪያ ላይ በሚጠበቁ የለውጥ ፕሮግራሞች ተጠናክሮ ተግባራዊ መደረግ ይጀምራል።
     በመሆኑም የተጀመረው አገራዊ የለውጥ እንቅስቃሴና እንደገና የመታደስ ጥረት ለላቀ ፍሬ እንዲበቃ መላ የአገራችን ህዝቦች ሰላማዊና ህጋዊ ትግላቸውን አጠናክረው እንዲቀጥሉ ጥሪያችንን እናቀርባለን። በዚህ አጋጣሚ የውጭም ሆነ የውስጥ ፅንፈኛ ፀረ ሰላምና ፀረ ልማት ኃይሎች ህዝቡ በሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ ትግሉ የገነባውን ስርዓት በቀጣይነት ለማሻሻል የሚያደርገውን እንቅስቃሴ መጠጊያ አድርገው ሁከትና ትርምስን ለማስፋፋት የሚያደርጉትን ጥረት በፅናት እንዲመክትና በሀገራችን ህዝቦች ብሔሮችና ብሔረሰቦች መካከል ያለውን መልካም ግንኙነትና አብሮነት በአስነዋሪ የዘረኝነት ፕሮፓጋንዳቸው ለማላላት የሚያደርጉትን አፍራሽ እንቅስቃሴ እንዲያመክነው ጥሪያችንን እናቀርባለን።

 

የሁለቱ የተሃድሶ ንቅናቄዎች መሰረታዊ ልዩነቶች

የ1993 ዓ.ም. የተሃድሶ ንቅናቄ መነሻዎች ውስጣዊ እና ውጫዊ ተደርገው የሚቀመጡ ናቸው። ውስጣዊ፣ ፖለቲካዊ ንቅዘት፣ ትምክት እና ጠባብነት ናቸው። ሁለተኛው፣  ከቀዝቃዛው ጦርነት ማክተም ጋር ተያይዞ የዓለም ከባቢያዊ ሁኔታም አሜሪካ መራሹ የዓለም ዓቀፉ ኢምፔሪያሊዝም ብቸኛ የዓለማችን ኃይል ሆኖ የወጣበት በመሆኑ ድርጅቱ አዲስ መስመር ለመከተል መወሰኑ ቢያንስ ምርጫ አልባ አማራጭ ተደርጎ የሚወሰድነው። እነዚህ የውስጥ እና የውጭ ከባቢያዊ የፖለቲካ ሁኔታዎች ኢሕአዴግ ወደ ተሃድሶ መስመር እንዲገባ እንዳስገደዱት መገመት ይቻላል።

የ2008 ዓ.ም. የተሃድሶ ንቅናቄ (“ዳግም የመታደስ”) እንደበፊቱ ውጫዊ እና ውስጣዊ መነሻዎች አሉት። ውስጣዊ መነሻው ሥርዓቱ መሰረታዊ የኢኮኖሚ እድገቶች እያስመዘገበ ያለበት ወቅት በመሆኑ የፓርቲው እና የመንግስት አንዳንድ ተሿሚዎች በተቀናጀ መልኩ የኪራይ ሰብሳቢ ፖለቲካ ኢኮኖሚ በሥርዓቱ ውስጥ በመዘርጋት ሀገሪቷ የምታፈራውን ሀብት ለመቀራመት ከፍተኛ እንቅስቃሴ ውስጥ በመግባታቸው የመጣ ነው። እንዲሁም በፓርቲ ውስጥ ጠባብነት፣ ትምክህት እና ጥገኝነት በከፍተኛ ደረጃ በመግነናቸው ነው። ከሕገመንግስቱ በተቃርኖ አንዳንድ የድርጅቱ የፖለቲካ አመራሮች መንቀሳቀስም በመጀመራቸው ጭምር ነው።

ውጫዊው ኃይል እንደበፊቱ ኢምፔሪያሊዝም ሳይሆን ሰፊው ሕዝብ ነው። ይህም ሲባል፣ ሥርዓቱ በኪራይ ሰብሳቢ የፖለቲካ ኢኮኖሚ ጫና ውስጥ መውደቁን ተከትሎ የመልካም አስተዳደር፣ የሕግ የበላይነት፣ የዴሞክራሲያዊ መብቶች ጥበቃ፣ የፖለቲካ መብቶች ጥበቃ፣ የሚዲያ ነፃነት፣ የሃብት ክፍፍል እና የሰብዓዊ መብቶች አያያዝ መጓደል በመፈጠሩ ሰፊው ሕዝብ ድርጅቱ ላይ ግፊት እያደረገ በመገኘቱ ነው። ሌላው ውጫዊ ኃይል፣ ድርጅቱን ሰርጎ የገባው በማንኛውም ዋጋ የሥርዓት ለውጥ ማምጣት የሚፈልገው ነው።

ስለዚህም በ2008 ዓ.ም ማገባደጃ የሚጀመረው የዳግም ተሃድሶ ንቅናቄ መሰረታዊ ለውጦች ማምጣት ካልቻለ አደጋው የከፋ ነው የሚሆነው። ምክንያቱም የሚጠበቁት ለውጦች በፓርቲው ጫማ ልክ ሳይሆን ከሰፊው ሕዝብ ፍላጎት አንፃር በመሆኑ ከፍተኛ የፖለቲካ ቁርጠኝነት የሚፈልጉ ውሳኔዎች ማሳለፍን ይጠይቃሉና። 

ይምረጡ
(3 ሰዎች መርጠዋል)
974 ጊዜ ተነበዋል

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us