“የሃይማኖት ተቋማት በሠላም እና በልማት ስም ዴሞክራሲያዊ መብቶችን ማፈን አይችሉም”

Wednesday, 07 September 2016 14:08

“የሃይማኖት ተቋማት በሠላም እና በልማት ስም ዴሞክራሲያዊ መብቶችን ማፈን አይችሉም”

ዶክተር ፓስተር ዘካሪያስ ዓምደብርሀን

በይርጋ አበበ

ከዲፕሎማ ጀምሮ እስከ ሶስተኛ ዲግሪ (ፒኤ ች ዲ) ድረስ በተለያዩ ከስነ መለኮት ጋር የተያያዙ ትምህርቶች ተምረዋል። በአሁኑ ወቅት ደግሞ ዶክተር ኦፍ ሚኒስትሪያቸውን እየተማሩ በፕሮቴስታንት ኃይማኖት የእምነቱ ዶግማ መሰረት ፓስተር ሆነው ዓለም አቀፍ አገልግሎት እየሰጡ ይገኛሉ። ሙሉ ስማቸው ዶክተር ፓስተር ዘካሪያስ አምደ ብርሃን ይባላሉ። አገራዊ ጉዳዮችን በሃይማኖት መነጽር መዳሰስ እንደሚችሉ የሚገልጹትና ይህን ችሎታቸውንም በተለያዩ መጽሃፍት መልክ እያዘጋጁ ለንባብ የሚያበቁት ዶክተር ፓስተር ዘካሪያስ ዓምደ ብርሃን ከአንድ ዓመት በፊት ለንባብ ባበቁት “ምናብ እና ገሀድ” የሚለው መጽሀፋቸው የሃይማኖት ተቋማት በፖለቲካዊ ዘርፎች ሊጫወቱት ስለሚገባቸው ሚና በዝርዝር ጽፈዋል። የወቅቱ የአገራችንን ችግር በተመለከተም የሃይማኖት ተቋማት መሪዎች ተገቢውን ሚናቸውን እንዳልተጫወቱ ይገልጻሉ። በአጠቃላይ የወቅቱ የአገራችን ሁኔታ ዙሪያ ከሰንደቅ ጋዜጣ ጋር ሰፋ ያለ ቃለ ምልልስ አድርገዋል። የቃለ ምልልሱን ሙሉ ክፍል ለአንባቢያን በሚመች መልኩ አዘጋጅተን አቅርበነዋል።

ሰንደቅየወቅቱን የአገራችንን ፖለቲካዊ ሁኔታ እንዴት ያዩታል?

ዶክተር ዘካሪያስበጣም የሚያሳዝን ሆኖ ነው የሚታየኝ። በመጀመሪያ ደረጃ እየተሻሻለ መሄድ የሚገባው ነገር እየተበላሸ ሲሄድ ይታያል። ለምሳሌ አጼ ኃይለስላሴ የሰሯቸውን ስራዎች መጥፎውን አርሞ መልካሙን ከማስቀጠል ይልቅ ማቋረጥ ነው የተሰራው። አሁን በአገራችን ያለውን ወቅታዊ ሁኔታ የማየውም ያለፉት ስርዓቶች ላይ የማየውን ያለመረጋጋት ሽታ ነው የሚታየኝ። መሆን የሌለበት እና መከሰት ያልነበረበት ነገር ነው፣ የተከሰተውና እየሆነ ያለውም። ለዚህ ችግር ተጠያው ሁለት ወገን ይሆናል። መንግስትን ጨምሮ ራሱ ህዝቡም ተጠያቂ ናቸው።

ሰንደቅህዝብ ተቃውሞ ሰልፍ የወጣውና ተቃውሞውን እየገለጸ ያለው መብቴ ይከበር፣ ማንነቴ ይጠበቅልኝ፣ ሰብአዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶቼ ይረጋገጡልኝ እያለ ነው። በዚህ ሁኔታ አሁን አገሪቱ ውስጥ ለተፈጠረው ግጭት ህዝብ እንዴት ተጠያቂ ይሆናል?

ዶክተር ዘካሪያስመሰረታዊው ችግር የህዝብም የመንግስትም ችግር ነው ስልህ በህዝብ በኩል በዚህ መልኩ በተጠናከረ ሁኔታ ተቃውሞውን ለመግለጽ ይህን ያህል ጊዜ መቆየቱ እንደ ስህተት ይቆጠራል። አንዳንዶቹ የሚያነሷቸው ጥያቄዎች ከ14 ዓመት በፊት ጀምሮ የነበሩ ጥያቄዎች ናቸው። እነዚህን ጥያቄዎች እስካሁን ድረስ ሲንከባለሉ መቆየታቸው ተገቢ አልነበረም። መንግስት ደግሞ ጥያቄዎችን በትክክልና በአግባብ መመለስ አለበት። መመለስ ካቃተው ወይም ካልቻለ ደግሞ ህዝቡ በራሱ መንገድ ነው የሚመልሰው። እዚህ ላይ ሊነሳ የሚገባው ህዝቡ ሳይስማማው እንደተስማማው አድርጎ እየሄደ ነበር ማለት ነው። የተፈጠረው ችግር ድንገት የመጣ የመሰለው ለዚያ ነው። አንዳንዶቹ በእርግጥ ተደጋጋሚ ጥያቄ አቅርበናል የሚሉ አሉ።  መንግስትም ተጠያቂ እንዳይሆን ተዘናግቷል ወይም አውቆ አድፍጧል።

ሰንደቅበአንድ አገር ውስጥ እንደዚህ አይነት የፖለቲካ ቀውሶች በሚፈጠሩበትና አለመረጋጋት በሚያጋጥምበት ወቅት የሃይማኖት መሪዎች ሚና የጎላ ሊሆን ይገባል ይባላል። በተፈጠረው ችግር ጋር ተያይዞ የአገሪቱን የሃይማኖት ተቋማት መሪዎች ሚና እንዴት አዩት?

ዶክተር ዘካሪያስየኃይማኖት መሪዎች ከፖለቲካ ወይም ከአገር ሁኔታ ራቅ ብለው የኖሩ ይምሰላቸው እንጂ እየኖሩ አይደለም። የኃይማኖት መሪዎች ከፖለቲካ ቢርቁም የሚያገለግሉት ግን ህዝቡን ነው። ስለዚህ የሚያገለግሉት ህዝብ ታክስ ሲጫንበት መብቱ ሲረገጥና የተለያዩ ችግሮች ሲመጡበት ችግሩን የሚያንጸባርቀው ወደ ኃይማኖት መሪዎቹ ዘንድ ሂዶ ነው። ለምሳሌ በፕሮቴስታንት እምነት በሚደረግ የፖስተሮች አመራር ውስጥ ሰው ይዞ የሚመጣው አቤቱታ የኑሮ ውድነት የፖለቲካ ችግር ወዘተ የመሳሰሉትን ነው። ስለዚህ የኃይማኖት አባቶች ከፖለቲካው የራቁ ቢመስላቸውም አልራቁም። ራሳቸውን ገለልተኛ ማድረግ ያለባቸው እንደተቋምና ከፓርቲ አባልነት ርቀው ገለልተኛ የሆነ ስራ መስራት የሚያስፈልግ ማንነት ነው ለመያዝ የሚያስፈልጋቸው።

ገዳዩም ሟቹም አማኝ ናቸው ላልከኝ ነብሰ ገዳይ አማኝ ሊሆን አይችልም። ምክንያቱም አሁን ያለው ግጭት የፖለቲካ የበላይነት እንጂ ወረራ አይደለም። የፖለቲካ የበላይነትን ለማስጠበቅ በሃሳብ ማሳመን እንጂ በመሳሪያ ማሳመን መደፍጠጥ ነው።መደፍጠጥ ደግሞ መንፈሳዊነት አይደለም። ስለዚህ ገዳዩም ሟቹም አማኝ ናቸው ማለት ይከብደኛል። ነገር ግን አገር ለመጠበቅ የወጡ ሁሉ ሀይማኖት የላቸውም እያልኩህ አይደለም። በዚህ አይነቱ ግጭት የሃይማኖት መሪዎች ሚና የጎላ የሚያደርገውም ለዚያ ነው። የሃይማኖት መሪዎች በግጭት አፈታት ዙሪያ ሚናቸው ከፍተኛ ነው። ምክንያቱም በግጭት አፈታቱ ላይ የኃይማኖት መሪዎች የሚንቁትም የሚፈሩትም አካል ሊኖር አይገባም። የሚንቁትም ሆነ የሚፈሩት አካል በበዛ ቁጥር አድሏዊነት ይታይባቸዋል። በነገራችን ላይ የሃይማኖት ተቋማት ሲቋቋሙ አላማቸው ግጭትን ለመፍታት አይደለም። በአገር ውስጥ የሚፈጠሩ ግጭቶችን መፍታት የሚቻለው በህገ መንግስቱ ነው። ይህ ሲባል ግን ቤተ አምልኮዎች የመጀመሪያ ድርሻቸው ግጭት ማስታረቅ አይደለም ቢባልም በህገ መንግስት አተረጓጎም ወይም በግጭት አፈታትና አመላለስ መግባባት ካልተቻለ ሽምግልና ያስፈልጋል። ይህ ደግሞ የሃይማኖት ተቋማት ሚና ይሆናል።

ሰንደቅየወቅቱን የአገራችንን ሁኔታ አስመልክቶ መግለጫ ሰጥተዋል። አገሪቱ የበርካታ ሀይማኖት ተከታይ ህዝቦች ምድር እንደመሆኗ በፕሮቴስታንት ኃይማኖት ውስጥ የሃይማኖቱ መሪዎች ምን እያደረጋችሁ ነው?

ዶክተር ዘካሪያስልክ ነህ፤ የሁሉም ሃይማኖት መሪዎች መግለጫ ሊሰጡ ይገባቸዋል።መግለጫቸው ግን በቆፈን የተያዘ የካድሬ ሽታ ሊኖረው አይገባም። እውነትን እውነት ማለት አለበት። የፕሮቴስታንት ሃይማኖት መሪዎች ምን እያደረጋችሁ ነው ላልከኝ በፕሮቴስታንት እምነት መሪዎች በኩል ትንሽ ችግር አለ። ችግር አለ ስልህ የፕሮቴስታንት እምነት መሪዎች አገራዊ የሆነ አመለካከት ላይ የዳበረ ሰብዕና አልያዝንም። ዝምታ እና ለዘብተኝነት እናበዛለን። ነጥሮ የወጣ መልዕክትን ማስተላለፍ የሚችል መሪ ለማብቀል እያሰብን ቢሆንም እስካሁን አላበቀልንም። ስለዚህ በአገሪቱ ወቅታዊ ሁኔታ ላይ ከጸሎት ያለፈ ተሳትፎ ያደረግን አይመስለኝም።

ይህ የሆነው በሶስት ምክንያቶች ነው። የመጀመሪያው በማህበራዊ ሳይንስ ላይ ያለን እውቀት አናሳ መሆን ነው። ሁለተኛው የፍርሃት ቆፈን ነው። ይህ የፍርሃት ቆፈን ከዚህ በፊት በደረሰባቸው ወይም ገና ይደርስብናል ብለው በሚሰጉት ሊሆን ይችላል። ሶስተኛው ምክንያት አድርባይነት ነው። ይህ ደግሞ ትልቁ ችግር ተንበርካኪነትን ከማምጣት በተጨማሪ የገለልተኝነት ሚናን ያጠፋል። ስለዚህ የዳኝነት ሚናን መጫወትን ያስቆምና በጸሎት ስም፣ በፍቅር ስም እና በሰላም ስም ሂዶ መሸጎጥን እንደ አማራጭ መውሰድ ነው ችግሩ። ሌላው ደግሞ የሰማይ ዜግነትን አጥብቆ በመያዝ የምድር ነገሮች ላይ የዳበረ ነገር አለመያዝ። ለምሳሌ ሙሴ፣ ኤሊያስን፣ ኤልሳን ወይም ጳውሎስንም ብናይ እነዚህ ሁሉ የእግዚያብሔር ሰዎች በምድራዊ ጉዳዮች ላይ ቀጥተኛ ተሳትፎ ነበራቸው።

ሰንደቅይህ የሆነው የመንግስት እና የሃይማኖት መለያየት (ሴኪዩላሪዝም) ያመጣው ፈተና ነው? እርስዎ በትምህርት ጉዳይ የአሜሪካን እና የተለያዩ አገራት  ተሞክሮ ያውቁታል ብዬ አስባለሁና የእኛን አገር የሃይማኖት ተቋማት መሪዎች ተሳትፎ እንዴት ያዩታል?

ዶክተር ዘካሪያስየኢትዮጵያ ችግር እኮ መንግስት እና ሃይማኖት አንድ አይደለም የሚለው ሳይሆን መጋባታቸው ነው። እንዲያውም የጫጉላ ዘመናቸው አልቆ ፍጹም ጋብቻ ውስጥ የገቡ ነው የሚመስለው። መንግስት የተናገረውን የሚደግም የሃይማኖት ተቋም መሪ ከካድሬው በላይ ካድሬ ሲሆን መንግስት እና ሃይማኖት ተፋተዋል ማለት አይቻልም። በአሜሪካ ያለውን ስንመለከት ደግሞ ይፋቱ እንጂ የሃይማኖት ተቋማቱ መሪዎች በፖለቲካው ላይ ጫናቸውን ያሳድራሉ። በነገራችን ላይ ሴኪዩላሪዝም ማለት እኮ የመንግስት ባለስልጣናት በሃይማኖት ጉዳዮች ጣልቃ ገብተው አያማስሉም እንጂ ሃይማኖቶች በሚመቻቸው በኩል ተጽእኖ አያሳርፉም ማለት አይደለም። በአሜሪካ ኢቫንጄሊካን ሃይማኖት መሪዎች ምዕመናቸውን በማህበራዊ ጉዳዮች ላይ ተሳትፎ እንዲያደርጉ ይቀሰቅሳሉ። ለምሳሌ ውርጃን እና የተመሳሳይ ጾታ ጋብቻን ኢቫንጄሊካኖቹ ይቃወማሉ። ብዙ ጊዜ ተሰብስበውም የድጋፍ ፊርማ አሰባስበው ተቃውሟቸውን ያቀርባሉ። ይህን የሚያደርጉት እንደዚህ አይነት ነገሮችን (የተመሳሳይ ጾታ ጋብቻን እና ውርጃን) እንደማይቀበሉት በፓርቲው ላይ ተጽእኖ ለማሳረፍ ነው። የሃይማኖት ተቋማት መሪዎች በግላቸው ከሚያመጡት ተጽእኖ የተነሳ ምዕምኖቻቸውም ፖለቲካውን ይቀያይሩታል።

ሴኪዩላሪዝም ማለት የሃይማኖት ተቋማት በዝምታ እና በፍርሃት ቆፈን መያዝ ማለት አይደለም። በነገራችን ላይ የሃይማኖት ተቋማት የጀግኖች ማምከኛም አይደሉም፣ የዴሞክራሲ መብቶችን መጠየቂያ ማምከኛ መንገዶችም አይደሉም፣ የህዝብ ማፈኛ መሳሪያም አይደሉም። የሃይማኖት ተቋማት በሰላም እና በልማት ስም ዴሞክራሲያዊ መብቶችን ማፈን አይችሉም። ለማፈን መሞከር የሚሰራም አይደለም። ምክንያቱም ያለንበት ዘመናዊ የሚባል ዘመን ላይ ስለሆነ ህዝቡ ማንን እንደሚሰማ በሚገባ ያውቃል። ስለዚህ የሃይማኖት ተቋማት መሪዎች ትክክልኛ ሚናቸውን መያዝና መጫወት ይገባቸዋል።

ሰንደቅከአንድ ዓመት በፊት ለንባብ ባበቁት “ምናብ እና ገሃድ” መጽሃፍ ላይ የሃይማኖት መሪዎችን ቸልተኝነትና ተንበርካኪነት በዚህ ዘመንም ይታያል ብለዋል። በምን መልኩ ነው ተመሳሳይነታቸው?

ዶክተር ዘካሪያስፍቅር እስከ መቃብር መጽሃፍ ላይ የሃይማኖት መሪዎች ከእነ ፊታውራሪ መሸሻ ጋር የጠበቀ ግንኙነት ስለነበራቸው፣ ተንበርካኪ ተንሸራታች እና ለዘብተኛ ነበሩ። በጽድቁ ጉዳይ ላይም ተንበርካኪነታቸው ይታይ ነበር። እንደ ጉዱ ካሳ አይነት ገጸ ባህሪ ደግሞ ሃይማኖተኛ ነው፡፡ ነገር ግን ፊታውራሪ መሸሻን ሲሞግታቸው ታያለህ። ጉዱ ካሳን ወደዚህ ዘመን ስናመጣው እንደ ነጻ ፕሬስ አድርገህ ልትወስደው ትችላለህ። ፊታውራሪ መሸሻ ጉዱ ካሳን ስላልሰሙ ከገበሬዎች ጋር ያመጸው አበጀ በለው አሰራቸው። አበጀ በለው ሁልጊዜ የሚመጣው ጉዱ ካሳ ሲታሰር ነው።

በዚህ ዘመንም የህሊና ልዕልና ያላቸውን የነጻውን ፕሬስ ስታፍን እና ስታስር አመጽ ይመጣል። መጽሃፍ ቅዱስ ራሱ “አሮጌ አቁማዳ ላይ አዲስ ወይን ጠጅ አይቀመጥም” ይላል። በማህበራዊ ሚዲያ አዲሱ አስተሳሰብ በገባበት ማህበረሰብ ዘንድ ሚዲያን አፍነህ የተሳሳተ መረጃ እየሰጠህ ህዝቡን ልታስተዳድረው አትችልም። ምክንያቱ ዘመኑ የስልጣኔ በመሆኑ የመረጃ አማራጮች የበዙበት ዘመን ነው። ስለዚህ የመረጃ ምንጩ በበዛ ቁጥር ሃቀኝነት ግልጸኝነት እና መልካም አስተዳደር አስፈላጊ ናቸው። አለበለዚያ ጉዱ ካሳን (ነጻ ሚዲያን) ስታፍነው ገበሬው ይሸፍታል። መጽሀፌ ላይ ያልኩት ይህን ነው።

ሰንደቅመገናኛ ብዙሃን እና የሃይማኖት ተቋማት የገዥው ፓርቲ የድጋፍ መሳሪያዎች ናቸው እየተባሉ ይታማሉ። ይህን በተመለከተ የእርስዎ ምልከታ ምንድን ነው? በኢህአዴግ የ15 ዓመታት የተሃድሶ ግምገማንስ እንዴት አዩት?

ዶክተር ዘካሪያስሚዲያው ቀጥተኛ ደጋፊ ነው። የሃይማት ተቋማቱ ደግሞ እሱ (መንግስት) የሚሰጠውን መግለጫ መልሰው የሚገልጹ ሆነዋል። ይህ መታረም አለበት። ስለዚህ የሃይማኖት ተቋማት ነጻነትን በተሃድሶ ውስጥ ማስገባት አለባቸው። ህዝቡ የሃይማኖት ተቋማት ነጻ አይመስሉንም ካለ ተቋማቱ ነጻነታቸውን ማስጠበቅ አለባቸው። ለምሳሌ መንግስት “ሁከት ነው” ሲል የሃይማኖት ተቋማት ተቀብለው “ሁከት ነው” ይላሉ። ለምንድን ነው ሁከት ነው የሚሉት? አጥንተዋል ወይ? ካጠኑስ ስራቸው (የህዝቡ እንቅስቅሴ) ሁከት ይሁን፣ አይሁን ምንድነው መነሻቸው? እነዚህ ጥያቄዎች ሳይመለሱ መንግስት ሁከት ነው ስላለ ሁከት ነው ካሉ የሽምግልና ሚናቸውን፣ ኃላፊነታቸውንም፣ ነገ ከነገ ወዲያ የሚመጣውን ችግር በሽምግልና ለመፍታት የሚያስችሉትን መንገዶች ሁሉ ቆረጡ ማለት ነው።

ሚዲያ ነጻነቱን ካልጠበክለት ህዝቡ ሚዲያውን ማመን ያቅተውና ሌሎች አማራጭ ሚዲያዎችን ማለትም መንግስት የከለከላቸውንም ሆነ ያልከለከላቸውን ማየት ይጀምራል። ለምሳሌ ማህበራዊ ሚዲያን እንደዋና የመረጃ ምንጭ አድርጎ ይወስደዋል። ይህ የመጣው ከሚዲያው አለመታመን ነው። ሰው በተፈጥሮው አማራጭ መንገዶችን መጠቀም ይፈልጋል። ጫማ ሲገዛ እንኳን አንደኛው ሱቅ ጥሩ ጫማ መሆኑን ቢነግርህ ሌላኛው ሱቅ ዘንድ ሂደህ ታረጋግጣለህ። ስለዚህ የኢትዮጵያ ሚዲያ የሚነግረውንም ትክክለኛ መሆኑን እና አለመሆኑን ወደ ማህበራዊ ሚዲያ ይሄዳል። ወደ ሌሎች ሚዲያዎችም ይሄዳል።

ሰንደቅየኢትዮጵያ ሚዲያ ሲሉ በመንግስት በጀት እና ቁጥጥር ስር ያሉትን ነው ወይስ የግል ሚዲያውንም ያጠቃልላል?

ዶክተር ዘካሪያስበመንግስት ቁጥጥር ስር ያልሆኑትም ቢሆኑ ዛቻ እና ፍራቻ አለብን ብለው ስለሚያስቡ በራሳቸው ላይ ቅድመ ምርመራ ያደርጋሉ። የመንግስት ሚዲያዎች ደግሞ መንግስት እንዲባልለት ከሚፈልገው በላይ በመደባበቅ አለቆቻቸውን ማደሰት ይፈልጋሉ። በዚህ ድርጊታቸውም ህዝቡ መንግስትን እንዳያምን እነሱንም እንዲጠላ ያደርጉታል። ለምሳሌ በቅርቡ በተካሄደው የሪዮ ኦሊምፒክ አትሌት ፈይሳ ሌሊሳ የተቃውሞ ምልክት ሲያሳይ ሩጫውን የምመለከትበት የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን አቋረጠው። በዓለም መገናኛ ብዙሃን የታየን ዘገባ የእኛው ሲያቋርጠው እኔም ሆንኩ ሌላው ህዝብ “ይህን ሚዲያ አላምነውም” የሚል አቋም ነው የምንወስደው። ስለ ጎረቤት አገር አፋኝነት ዘግበው እዚህ ያለውን ሲያልፉት ህዝቡ ምን ይላል? እነዚህ እስካልታረሙ ድረስ ተሃድሶ አለ ብዬ አላስብም።

ስለተሃድሶው ወዳነሳኸው ስመጣልህ ተሃድሶ ማለት እውነትን ለመነጋገር ወይም ያለፈውን ጥፋት አርሞ ለመመለስ የሚደረግ ውይይት ነው። ተሃድሶን በሁለት መንገድ ማየት አለብን፡፡ ይህም ማለት በቲዮሪም ሆነ በተግባር መፈተሽ አለበት። ተሃድሶ መካሄድ ያለበት ህዝቡን እንዴት ለተጨማሪ ዓመታት መግዛት አለብን ከሚል መንፈስ ተነስቶ ሳይሆን ህዝቡን እንዴት እንጠቅማለን? ከሚለው ጥያቄ መነሳት አለበት። በስልጣን ማማ ላይ ለመረጋጋት ከሆነ ግን ተሃድሶ ሊባል አይችልም።

ሰንደቅየአገር ሽማግሌዎች በዚህ ሚናቸውን እየተወጡ አይደለም ወይም ደግሞ ለዚህ አይነት ከባድ አገራዊ ኃላፊነት ራሳቸውን ያዘጋጁ የአገር ሽማግሌዎች የሉም ይባላል። በዚህ ላይ የእርስዎ እይታ ምንድን ነው?

ዶክተር ዘካሪያስእዚህ አገር ትልቁ ችግር የሆነው እኮ ተቋማት ወይ ጠፍተዋል ወይም ደግሞ አድርባይ ሆነዋል። ህዝቡ የሚያምናቸው ተቋማት ያሉ መሆናቸው ላይ ጥያቄ አለ። መንግስት ይህን ነገር አልፈለገምና ቆዩ እኛ እንጠይቅላችሁ የሚል የሽምግልና ውክልና የለም። ኢትዮጵያ ውስጥ አዲስ የሽማግሌዎች መማክርት ያስፈልጋል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ራሳቸው ያስፈልጋቸዋል።

ሰንደቅአሁን ኢትዮጵያ ያለችበት ሁኔታ አገሪቱንና ህዝቧን ወዴት የሚወስዳት ይመስልዎታል?  

ዶክተር ዘካሪያስይህን የማየው በሶስት መንገድ ነው። እንደ ሃይማኖተኛነቴ ሳየው ከእምነት አንጻር እግዚያብሔር ሠላም አውርዶ ችግሮች ተፈተው በሠላም የምንኖር ይመስለኛል። ይህ ተስፋዬ የመጣው ከመንፈሳዊ ሞራል የመጣ ተስፈኝነቴ ነው። ከስሜት አንጻር ካየሁት ደግሞ ድብልቅልቆሽ ነው። ሞት እያለ፣ ጦርነት ታውጆ፣ ሰዎች ደግሞ ሞትን አንፈራም እያሉ፣ ሌሎችም እንገድላለን እያሉ በሚሉበት ሁኔታ ሳየው ነው ድብልቅልቆሽ ስሜት ነው ያልኩት። ከእውቀት አንጻር ስቃኘው ደግሞ መፍትሔ መጥቶ ወደ ከፍታ እንወጣለን ወይም ወደ ቁልቁለቱ እንሄዳለን።

ሰንደቅወደ ከፍታ እንወጣለን ወይም ወደ ቁልቁለት እንወርዳለን የሚለውን ሃሳብዎን ያብራሩልን?

ዶክተር ዘካሪያስኢህአዴግም ታድሷል፤ የህዝቡንም ጥያቄ እመልሳለሁ ብሏል የሚለውን ተስፋ አድርገን ስንሄድ መፍትሔ እየመጣ ነው። በነገራችን ላይ የመጀመሪያው መፍትሔ ያለው በመንግስት እጅ ነው። ቀጥሎ ህዝቡ ላይ ነው። መንግስት መፍትሔ ለመስጠት ፈቃደኛ ሲሆን፣ የህዝቡን ጥያቄ የጥቂቶች ነው ማለቱን ሲያቆም መፍትሔ ይመጣል። ለምሳሌ የጎንደሩን ጥያቄ “የጥቂቶች ነው” ማለት ምን ማለት ነው?

ህዝቡ የጠየቀውን ጥያቄ መንግስት ለመስማትና መፍትሔ ለመስጠት ፈቃደኛ ከሆነ መፍትሔ አገኘን፣ ወደ ከፍታው ወጣን ማለት ነው። ይህ ካልሆነ ግን የህዝብ ጥያቄ ይቀጥላል፣ መንግስት ጥያቄውን ያስተባብላል፣ ይህ ሁኔታ ሂዶ መጨረሻ ላይ ህዝብ ያሸንፋል። በህገ መንግሰቱ ላይም ህዝብ የበላይ ነው ብለውናል።   

ይምረጡ
(6 ሰዎች መርጠዋል)
1332 ጊዜ ተነበዋል

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us