የምንም ጦርነት፣ የምንም ሠላም ሰለባ፤ ዛላአንበሳ

Wednesday, 07 September 2016 14:10

ባሳለፍነው ሳምንት በኢትዮጵያ እና በኤርትራ ድንበር መካከል በምትገኘው የድንበር ከተማ ዛላአንበሳ ውስጥ ተገኝተን ነበር። የኢትዮ-ኤርትራ ጦርነትን ተከትሎ ዛላአንበሳ ወደ ነበር የድንበር ከተማ መቀየሯ የሚታወስ ነው። በከተማው የሚታዩት አዛውንት እና ሕፃናት ናቸው። ከተማው እንደደም ረግቷል። የወደሙ ቤቶች ባንቀላፉበት ሁኔታ ነው የሚገኙት። በሻዕቢያ ቦምብ የፈረሰው ዱቄት ፋብሪካ ወደ ዱቄትነት ተቀይሮ ይታያል። ከከተማዎ ሁለት ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የሻዕቢያ ጦር ከምሽጋቸው ውስጥ ይገኛሉ።

የኢትዮጵያ መንግስት ከኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት በኋላ እየተከተለ ባለው ‘No War No Peace’ ፖሊሲ ኤርትራን በሚያዋስኑ የኢትዮጵያ ድንበር ከተሞች የሚገኙ ሕዝቦች የፖሊሲው ሰለባ ከሆኑ አስራ ስምንት አመታት አልፏቸዋል። ከዚህ ጋር በተያያዘ አሁን ስላለው ሁኔታ እና ስላለፈው ጊዜ መረጃ እንዲሰጡ አቶ ገ/ሥላሴ ገ/መድህን አነጋገርናቸው።

አቶ ገ/ሥላሴ ገ/መድህን ተወልደው ያደጉት በዛላአንበሳ ነው። በዛላአንበሳ ከልጅነት እስከ አዛውትነት እድሜያቸው፣ 70 ዓመታት ኖረዋል። “ኢትዮጵያ ሆቴል” የሚል ስያሜ ያለው አነስተኛ ሆቴል ባለቤት ናቸው። አቶ ገ/ሥላሴ ሰፋ ያለ መረጃ የሰጡን ቢሆንም ለአንባቢያን ይመች ዘንድ በዚህ መልክ አቅርበነዋል።

ሰንደቅ፡- በአሁን ሰዓት በኢትዮ-ኤርትራ ድንበር ላይ ያለው ሠላም እንዴት ነው?

አቶ ገ/ሥላሴ፡-እኛ ሠላም እንፈልጋለን። ሠላም ካገኘን በደንብ መራመድ እንችላለን። መንግስት የሚያወጣው ስትራቴጂ ጥሩ ነው። እኛ ኢትዮጵያን ሠላም ካገኘን በደንብ ማደግ እንችላለን። ልማታችን የሚያደናቅፉ አንዳንድ ኃይሎች አሉ እንጂ አሁን ያለው ወጣት ለልማት ያለው አመለካከት በጣም ጥሩ ነው።

ሕዝብ ለሕዝብ ጠብ የለንም። ጠቡ ያለው ከሻዕቢያ ሥርዓት ጋር ብቻ ነው። ለምሳሌ ከኤርትራ ድንበር አቋርጠው ወደ ኢትዮጵያ ድንበር ሲገቡ ሻይ አፍልተን ምግብ አቅርበን ነው የምንቀበላቸው። እንደቤተሰብ ነው የምናስተናግዳው። እኛ የጋብቻ ዝምድና አለን። ከኤርትራዊያን ጋር ያልተጋባ የለም። ሁላችንም ተጋብተናል። አብዛኛው ሰው የጋብቻው ዝምድናው ከኤርትራዊያን ጋር ነው። የኢሳያስ ስርዓት ነው እንጂ የሕዝብ ለሕዝብ ምንም ቁርሾ የለም።

ሰንደቅ፡- ገባ ወጣ የሚሉ በስለላ ላይ የተሰማሩ የሻዕቢያ ሰዎች አሉ ወይ?

አቶ ገ/ሥላሴ፡- ይህ ከባድ ነው። ምክንያቱም ከኤርትራ ወደ ኢትዮጵያ እንጂ ከኢትዮጵያ ወደ ኤርትራ ለሚሄዱ ሰዎች አይፈቀድም። ወደ ኢትዮጵያ ሲገቡ ግን ስደተኛ መስለው ለስለላ ሊሰማሩ ሊሆን ይችላል። ሆኖም ግን ተመልሰው ለመውጣት ሲሞክሩ ኬላ ላይ ይያዛሉ። ስለዚህም ብዙ እንደዚህ አይነት ተግባር የማድረግ እድል የላቸውም።

ሰንደቅ፡- ወደ ኋላ መለስ ብለው አንዳንድ ነገሮች ቢያነሱልን?

አቶ ገ/ሥላሴ፡- ከዚህ በፊት ጓደኞች ነበሩን። እናበድራቸዋለን፣ እንበደራቸው ነበር። ችግሩ ሲፈጠር ግን አበዳሪ እና ተበዳሪ በዛው ነበር ገንዘቡን ይዞ የቀረው። ለምሳሌ የእኔ ታላቅ እህቴ ኮኮባት በሚባል ሥፍራ ከዚህ በጣም በቅርብ እርቀት ባለ የኤርትራ ግዛት ትኖራለች። በሁለት ኪሎ ሜትር ርቀት ታላቅ እህቴ አለች። አስራ ስምንት አመታት በሙሉ የእናት የአባቴ ልጅ ጋር አልተገናኘንም። ከሌሎች የአጎቴም ልጆች ጋር ጦርነቱ ከተካሄደ በኋላ ተገናኝተን አናውቅም። ትልቅ እንቅፋት የሆነን የኤርትራ ስርዓት ነው። ለመተሳሰብ ለመረዳዳት የሚሆን ስርዓት አይደለም። ይህ ነው የኢሳያስ ችግር። ይህንን ችግር ለመፍታት እያሰቡ ያሉት የኢትዮጵያ እና የኤርትራ ሕዝቦች ናቸው።

ይህን ሁሉ በደል ደርሶብን ሕዝቡ ወደ ኢትዮጵያ ድንበር ሲገቡ በአግባቡ ነው የምናስተናግዳቸው። ምክንያቱም ችግሩ ያለው ከሻዕቢያ ስርዓት እንጂ ከኤርትራ ሕዝብ ጋር እንዳልሆነ እዚህ ያለው ሕዝብ ጠንቅቆ ያውቃል። እኛ ዘንድ በክብር ይመጣሉ ስደተኞች ካምፕ እስኪደርሱ ድረስ አስፈላጊውን እገዛ እናደርግላቸዋለን። ስንቅ አዘጋጅተን፣ አብልተን፣ አጠጥተን ስደተኛ ካምፕ እናደርሳቸዋል።

ሰንደቅ፡- በቀን ምን ያህል ሰው ይመጣል?

አቶ ገ/ሥላሴ፡- በቀን አምስት ወይም ስድስት ሰዎች ይመጣሉ። አንዳንዴ ደግሞ በቀን አስር ሰዎች ድረስ ይገባሉ። ተደብቀው በሌሊት ነው የሚመጡት። በቀን ከተንቀሳቀሱ ከኤርትራ ድንበር ጠባቂዎች ይተኮስባቸዋል። በሌሊት ሲገቡ ግን የእኛ መከላከያ ሠራዊት ኬላ ከፍቶ ይቀበላቸዋል።

ሰንደቅ፡- በአካባቢው የሚታዩት አዛውንቶች እና ሕፃናት ናቸው። ወጣቶች የሉም። ምንድን ነው የዚህ ምክንያቱ?

አቶ ገ/ሥላሴ፡- በዚህ አካባቢ መዋዕለ-ንዋያቸውን የሚያፈሱ ኢንቨስተሮች አይመጡም። አድርገውት ቢሆን ለወጣቶች የስራ እድል ይፈጥሩ ነበር። በርግጥ መንግስት ተደራጁ እና ብድር አመቻቻለሁ ይላል። ሥራ ፍጠሩም ይላል።

ሰንደቅ፡- በዚህ መልክ እንዴት ትቀጥላላችሁ። መንግስት ወደ ጦርነት ውስጥ አልገባም ይላል። በሌላ በኩል ያሉ ወገኖች የመንግስት አቋም በድንበር አካባቢ ያሉ ሰዎችን ይጎዳል ይላሉ። ለምሳሌ ምንም ጦርነት፣ ምንም ሠላም ባለመኖሩ ዛላአንበሳ ተጠቂ ሆናለች። ለአስራ ስምንት አመታትም በዚህ መልኩ ሕይወታችሁ ቀጥሏል። ይህ የመንግስት ፖሊሲ መቀጠሉ በቀጣይ ምን ችግር ያመጣል?

አቶ ገ/ሥላሴ፡- በእኛ በኩል ኢሳያስን ማስወገድ የባሰ ችግር ያስከትላል። ምክንያቱም በእኛ ብቻ ተነሳሽነት እናስወግደው ካልን ቢወገድም አርፎ አይቀመጥም። ሁሌም ሲረብሽ ነው የሚኖረው። ኤርትራዊያን ካስወገዱት ግን እኛ ደርግን ታግለን እንደጣልነው ሁሉ፣ ዴሞክራሲ እንዲመጣ፣ ሠላም እንዲመጣ፣ ሁሉም የመሰለውን እንዲናገር፣ ሰው እንዲከበር ኤርትራዊያን ናቸው ኢሳያስን ታግለው መጣል ያለባቸው።  አንድ ጊዜ ሉዐላዊ ሀገር ናችሁ ብለን ካሳወቅናቸው በኋላ ሀገራቸው ገብተን ጦርነት ማንሳት ችግር ያመጣል።

ሰንደቅ፡- የቀረበው ጥያቄ፣ ከተማውን እያየነው ነው። ወጣቶች የሉም። ከተማው ፈራርሷል። በዚህ መልኩ መቀጠላችሁ ጉዳት የለውም ወይ?

አቶ ገ/ሥላሴ፡-ከተማውም፣ ሰዎቹም ይጎዳሉ። ሆኖም ግን አብዛኛው ኢትዮጵያዊ ግን ተጠቃሚ ነው። ጦርነት ውስጥ ብንገባ ሁሉም ኢትዮጵያዊ እና የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ነው የሚጎዳው። አሁን ላይ እየተጎዳን ያለነው ዛላአንበሳ እና ሁለት የድንበር ከተሞች ናቸው። ስለዚህም በድንበር የምንገኘው ሶስት ከተሞች ተጎድተን ሌላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ተጠቃሚ እንዲሆን የተደረገ ነው። ይህ የሆነው ግን ምርጫ በመጥፋቱ ነው። ይህ በመሆኑም ብዙ ቅሬታ የለንም።

ሻዕቢያ የሚፈልገው ይህ የምታዩትን አካባቢ በዶዘር አርሶ እኛን ማባረር ነው። ማንም ሰው በዚህ አካባቢ እንዲኖር አይፈልጉም። በጦርነት ጊዜ ይህንን ቦታ ተቆጣጥረው የነበረውን ሁሉ አውድመዋል። ያልወሰዱት አንዳች ነገር የለም። ምክንያታቸው ደግሞ ሙሉ ለሙሉ አርሰው የእርሻ ቦታ ማድረግ ነው።

ሰንደቅ፡- የሻዕቢያ ወታደሮች ከዛላአንበሳ በምን ያህል ርቀት ነው የሚገኙት?

አቶ ገ/ሥላሴ፡- ከፊት ለፊታችን በሁለት ኪሎ ሜትር ርቀት ነው የሚገኙት። ከጀርባችን ደግሞ አይን ለአይን ነው የምንተያየው። አንዳንዴ ለመተንኮስ ይተኩሳሉ። ኤርትራዊያን ድንበር አቋርጠው ወደ ኢትዮጵያ ሲገቡ ይተኩሳሉ። በድጋሚ ተቋቅመን እንጂ ዱቄት ፋብሪካ አውድመዋል። የመኖሪያ ቤቶች ቆርቆሮዎችን ወንፊት አድርገዋል። ቤቶች አፈራርሰዋል።

ሰንደቅ፡- አሁን የኢትዮጵያ መንግስት ምን እንዲያደርግላችሁ ነው የምትፈልጉት?

አቶ ገ/ሥላሴ፡- በእኛ እምነት መንግስት ችግራችን ያውቃል፤ እያየን ነው ብለን የምናምነው። ችግራችን ከመንግስት የተሰወረ ነው ብለን አናምንም። መንግስት ረዘም ያለ ብድር ቢያመቻችልን ወደተለያዩ ቦታዎች በመንቀሳቀስ መነገድ እንችላለን። ሰርተን ራሳችን መደጎም እንችላለን። ተንቀሳቅሰን ትርፍ ማግኘት እንችላለን። ምን አልባት ይህንን ፍላጎታችን መንግስት እያሰበበት ይሆናል። መቼም በሀገራችን በርካታ ቦታዎች እንደኛ የተቸገሩ ሰዎች በመኖራቸው ቅድሚያ የሚሰጡትን እየሰጡም ሊሆንም ይችላል።

ለምሳሌ እዚህ የንግድ ባንክ አንድ ቅርንጫፍ ነው ያለው። ምክንያቱም ኢንቨስተሮች እዚህ አይመጡም። የግል ባንኮች የሉም። መንግስት ነው የተወሰነ እየደገፈን ያለው። 

ይምረጡ
(3 ሰዎች መርጠዋል)
1045 ጊዜ ተነበዋል

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us