ኢንጂነር ይልቃል ጌትነት በፓርቲያቸውም በምርጫ ቦርድም እውቅና እንደሌላቸው መገለፁ እያነጋገረ ነው

Thursday, 01 December 2016 15:43

-    ፓርቲው ኢንጂነሩን በ154 ሺህ ብር ጉድለት እየፈለጋቸው ነው

 

ሰማያዊ ፓርቲ መሰከረም 28 ቀን 2009 ዓ.ም በመኢአድ ቅጥር ግቢ ውስጥ አስቸኳይ ድንገተኛ ጠቅላላ ጉባኤ አካሂዶ የስራ አስፈጻሚ ሹም ሽር አካሂዶ ነበር። ፓርቲው በእለቱ ካሳለፋቸው ውሳኔዎች መካከልም በስነ ምግባርና በገንዘብ ጉድለት ችግር አለባቸው ያላቸውን የቀድሞ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላት (ሊቀመንበሩንና ምክትል ሊቀመንበሩን ጨምሮ) ያሰናበተበት ውሳኔው አንዱ ነው። ሆኖም ፓርቲው በጠቅላላ ጉባኤ ያሰናበታቸው የቀድሞው ሊቀመንበር ኢንጅነር ይልቃል ጌትነት አሁንም ድረስ የፓርቲው ሊቀመንበር እሳቸው መሆናቸውን በአደባባይ እየገለጹ ይገኛሉ። አዲሱን የሰማያዊ ፓርቲ ሊቀመንበርም ሆነ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴውን እንደማያውቁት ኢንጅነሩ በአደባባይ እገልጹ ይገኛሉ።

ኢንጅነር ይልቃል ጌትነት በአደባባይ ስለሚናገሩት ጉዳይ የሰማያዊ ፓርቲ የኦዲት እና ኢንስፔክሽን ኮሚሽን ሰብሳቢ አቶ አበራ ገብሩ እና የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የጽ/ቤት ኃላፊ የሆኑትን አቶ ወንድሙ ጎላ አነጋግረናቸዋል። የሁለቱን ኃላፊዎች ማብራሪያ ለአንባቢያን በሚመች መልኩ ከዚህ በታቸ አቅርበነዋል።

 

 

ሰንደቅ፡- የቀድሞው ሊቀመንበር ኢንጅነር ይልቃል ጌትነት የሰማያዊ ፓርቲ  ሊቀመንበር እኔ ነኝ፤ የተመረጡትን የፓርቲውን ሊቀመንበርና ሥራ አስፈፃሚዎችን አላውቃቸውም እያሉ በአደባባይ እየተናገሩ ይገኛሉ። በዚህ ላይ ያላችሁ አስተያየት ምንድን ነው?

አቶ አበራ፡-ኢንጅነሩ የሚናገሩት ተቀባይነት የለውም። ከዚህ በፊትም የመጨረሻ ማስጠንቀቂያ የደረሳቸው መሆኑ ይታወቃል። መታወቅ ያለበት በሕጋዊ መንገድ በመተዳደሪያ ደንባችን ተከትለን ነው ጠቅላላ ጉባኤ ያደረግነው። በምርጫ ቦርድም የሚታወቅ ጠቅላላ ጉባኤ ነው ያከናወነው። ተገቢ የምርጫ ቦርድ መመዘኛዎችን አሟልተናል። ይህንን ሁሉ ሕጋዊ መስመር ተከትለን ባደረግነው ጠቅላላ ጉባኤ ኢንጅነር ይልቃል ጌትነት ከሥልጣናቸው ተነሱት።  የሕግ በላይነት ኢንጅነሩ የሚያውቁ ከሆነ በሕግ አግባብ ሥልጣናቸውን ካጡ በኋላ በአደባባይ እኔ ነኝ ሊቀመንበር ማለታቸው ያስገምታቸው ይሆን እንጂ የሚያተርፉት ትርፍ አይኖርም። ጉባኤው የተካሄደው የምርጫ ቦርድ ታዛቢ በተገኙበት በመሆኑም፣ የምርጫ ቦርድ ሕጋዊ ግንኙነት የሚያደርገው ከፓርቲው ጋር ብቻ ነው። አሁንም ግንኙነታችን እንደቀጠለ ነው። አሟሉ የሚሉንም መረጃዎች በቅደም ተከተላቸው እየተለዋወጥን ነው። ስለዚሀም ኢንጅነር ይልቃል ጌትነት በአደባባይ መናገራቸው ሕገመንግስታዊ መብታቸው ቢሆነም ከሕግ አግባብ ውጪ የሚናገሩት ግን በየትኛውም መመዘኛ ተቀባይነት የለውም።

ሰንደቅ፡- በጉባኤያችው ላይ የገንዘብ ጉድለት እና የሰነድ ማጭበርበር ውንጀላዎች ቀርበው ነበር። እንዲሁም ሰነዶች ተቀምጠውባቸው የነበሩ ቢሮዎች ተሰብረው በፖሊስ እጅ መሆናቸውም ይታወቃል። ምክር ቤቱም የቀረበውን ሪፖርቱ አጽድቋል። በሪፖርቱ መሰረት ማጣራት እንዲደረግ መታዘዙም ይታወቃል። በዚህ ላይ እየሰራችሁት ያለው ነገር ምን ይመስላል?

አቶ አበራ፡- በገንዘብ ጉድለት የሚጠየቁትን ካጎደሉት የገንዘብ መጠን ጭምር ጽፈን በደብዳቤ አስታውቀናል። ተጠያቂ ለሆኑት ግለሰቦች በስማቸው በጽ/ቤታችን ላይ ለጥፈን እንዲያውቁት አድርገናል። የደብዳቤውን ሙሉ ይዘትም በድረ ገጻችን በኩል ለህዝብ ይፋ ሆኗል። ምርጫ ቦርድም በዚህ ጉዳይ ላይ ጥያቄ አቅርቦልን መልስ ሰጥተናል። የጠፋውን ገንዘብ መጠን በደብዳቤው ላይ ተገልጻል። በደብዳቤው በተገለፀው የገንዘብ ውድመት ላይ ኢንጂነር ይልቃል ጌትነት በ154 ሺህ ብር እና አቶ ስለሺ ደግሞ በ56 ሺህ ብር ተጠይቀዋል።

ሰንደቅ፡- ስለዚህ የቀድሞው ሊቀመንበር በምን ያህል ገንዘብ ምዝበራ ተጠያቂ እንደሆኑ ገልጻችሁ ማስታወቂያ አውጥታችኋል? ከሊቀመንበሩ ጋርስ አብረው ተጠያቂ የሚሆኑ ሰዎች እነማን ናቸው?

አቶ አበራ፡- ለኢንጅነር ይልቃል በግላቸው ነግረናቸዋል። ያጎደሉትን የገንዘብ መጠን ጠቅሰን በጽ/ቤታችን ማስታወቂያ መለጠፊያ ቦታ ለጥፈናል። ከቀድሞው ሊቀመንበር ጋር ተጠያቂ በመሆን አቶ ስለሺ አቶ ወሮታው ዋሴ ይገኙበታል። ከእነዚህ ሰዎች በተጨማሪም በተለያዩ ምክንያቶች ያልገለጽናቸውና ወደፊት ማንነታቸውን የምንገልጻቸው ተጠያቂ ሰዎች መኖራቸው መታወቅ አለበት።

ሰንደቅ፡- ኢንጅነር ይልቃል ሰማያዊ ፓርቲን ወክለው ከአሜሪካ ኤምባሲ፣ ከአውሮፓ ህብረት እና ከሌሎች የዲሎማቲክ ኮሚኒቲዎች ጋር እንዲሁም ከሌሎች ዓለም አቀፍ ተቋማት ጋር ፓርቲውን ውይይት አያደርጉም ማለት ነው?

አቶ አበራ፡- አዲስ አበባ ለሚገኙ ኤምባሲዎች እና ለዓለም ዓቀፍ ተቋማት በሙሉ አሳውቀናል። ይህ ማለት ዓለም ዓቀፉ ተቋማት ሰማያዊ ፓርቲ አዲስ ሊቀመንበር መምረጡን ያውቃሉ። በሀገር ውስጥም ጥሩ ማሳያ የሚሆነው በሸራተን አዲስ ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን ባዘጋጀው የውይይት መድረክ ላይ ኢንጅነር ይልቃል የተገኙት በግላቸው መሆኑን ከመድረኩ አቶ ብሩክ መግለፃቸው የሚታወስ ነው። ከዚህ መረዳት የሚቻለው አንድ ሊቀመንበር በሕግ የተቋቋሙ ተቋማት ሳያውቁት በአደባባይ ሊቀመንበር ነኝ ማለቱ የሰውዬውን ብስለት ያሳይ ይሆናል እንጂ የሚፈይድለት አንዳች ነገር የለም።

ሰንደቅ፡- አዲሱን ሊቀመንበራችሁን በምርጫ ቦርድ በኩል ለማስጸደቅ የሄዳችሁበት ሒደት ምን ይመስላል?

አቶ አበራ፡- እንደሚታወቀው የጠቅላላ ጉባኤ ውሳኔዎችን ምርጫ ቦርድ በአንድ ጊዜ አይቀበልም። በጉባኤው የተወሰኑ ውሳኔዎችን እና አጠቃላይ የጉባኤውን ዝርዝር ለቦርዱ ልከናል። የተላከውን ሰነድ ቦርዱ ከተመለከተ በኋላ መስተካከል ያለበት ካለም እንዲስተካከል ይገልጽልናል። ስለዚሀም በምርጫ ቦርድ የሕግ አግባብ የአዲሱን ሊቀመንበራችን ጉዳይ በተመለከተም በቅርቡ እንጨርሳለን። ምርጫ ቦርድም በዚህ ጉዳይ ከእኛ ጋር ያለው ግንኙነት በመልካምነት እየሄደ ይገኛል። በአሁን ሰዓት የፓርቲያችን ሊቀመንበር አቶ የሸዋስ ናቸው።¾

***          ***          ***

 

“የሰማያዊ ፓርቲ እስካሁን

ከመተዳደሪያው ደንብ ውጪ አይደለም”

አቶ ወንድሙ ጎላ

የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ጽ/ቤት ኃላፊ

ሰንደቅ፡- ሰማያዊ ፓርቲ በጠቅላላ ጉባኤውን ካካሄደ በኋላ አቶ የሸዋስን ሊቀመንበር አድርጎ መምረጡ ይታወቃል። ሆኖም የቀድሞው ሊቀመንበር አቶ ይልቃል ጌትነት የፓርቲው ሊቀመንበር እኔ ነኝ እያሉ ይገኛሉ። የፓርቲውን ጠቅላላ ጉባኤ በተመለከተ ጽ/ቤታችሁ ያለው መረጃ ምንድን ነው?

አቶ ወንድሙ፡- ፓርቲው ቀደም ብሎ የጠራውን ጉባኤ ኢንጅነር ይልቃል “ውጭ ስለነበርኩ ይራዘምልን” ብለው ጠይቀውናል። እኛም እንደዚህ አይነት ጥያቄዎች እንዳይነሱ ጉባኤያቸውን እንዲያራዝሙ ጠይቀናቸው ነበር። በኋላ የሰማነው ነገር የፓርቲያቸው የቁጥጥር ኮሚሽን ስራ አስፈጻሚውን በትኖታል የሚል ነው። ሰራ አስፈጻሚ ኮሚቴው ከተበተነ ደግሞ የግድ ጠቅላላ ጉባኤ ተጠርቶ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ መቋቋም ነበረበት። በዚህ መሰረትም ተወካይ እንድንልክላቸው ለጽ/ቤታችን በጠየቁት መሰረት ጉባኤውን የሚታዘብ ተወካይ ልከንላቸው ጉባኤያቸውን አካሄዱ። ጉባኤው ከተጠናቀቀ በኋላ ኢንጅነር ይልቃል መጥተው በጉባኤው አልተገኘሁም አሉን። እንደቅሬታ ተቀብለን ይዘነዋል። ሆኖም የሰማያዊ ፓርቲው የጉባኤውን ሙሉ ሪፖርት ልኮልናል፣ እኛም እየመረመርነው እንገኛለን። ማሟላት ያለባቸውን አንዳንድ ጥያቄዎችን ጠይቀናቸዋል። ያንን ካሟሉና ለቦርድ ቀርቦ ውሳኔ ከተሰጠ ኢንጅነር ይልቃል ፕሬዝዳንት ነኝ የሚሉት ጉዳይ የሚያበቃ ነው የሚሆነው።

ሰንደቅ፡- አሁን ባለው ተጨባጭ ሁኔታ ከፓርቲው ጋር የምታደርጉት ግንኙነት ከኢንጅነር ይልቃል ጋር ነው ወይስ አዲስ ከተመረጠው ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ጋር ነው?

አቶ ወንድሙ፡- በፓርቲያቸው መተዳደሪያ መሰረት ትልቁ የስልጣን አካል ጉባኤው ነው። ስለዚህም ግንኙነታችን በጉባኤው ከተመረጠው ሊቀመንበር እና ሥራ አስፈፃሚዎች ጋር ነው። የጉባኤ ሪፖርት የተቀበልነውም ከአዲሶቹ አመራሮች ነው።  በምርመራ ጊዜ የተለየ ነገር ካላጋጠመን በስተቀር ወይም የጉባኤው ሪፖርት መሰረታዊ ጉድለት ከሌለበት ግንኙነታችን ከአዲሶቹ ተመራጮች ጋር ነው።

ሰንደቅ፡- በምክር ቤታቸው ያስተላለፉትን ውሳኔ እና እናንተ የምትመረምሩትን ሪፖርት በምን ያህል ጊዜ ነው ይፋ የምታደርጉት?

አቶ ወንድሙ፡- በቀረበልን ሪፖርት ላይ አንድ ሁለት ጊዜ ጠርተን እንዲያብራሩልን ጠይቀናቸዋል። መሟላት ያለባቸውንም እንዲያሟሉ ነግረናቸዋል። እነዚህን ጥያቄዎች አሟልተው ሲያቀርቡልን ለቦርዱ እናቀርባለን። ስለዚህ ተሟልተው ከቀረቡልን በቀጣዮቹ ሁለት ሳምንታት ውስጥ ይጠናቀቃል ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ። እስከዚያው ድረስ ግን አዲሱን የሰማያዊ ፓርቲ ሊቀመንበር እንደ ፓርቲው ሊቀመንበር በመቀበል አብረን እየሰራን ነው።

ሰንደቅ፡- የኢንጅነር ይልቃል ቅሬታ መልስ እስከሚያገኝ ድረስ የፓርቲው አዲሱ ካቢኔ አካሄድ ትክክል ነው ማለት ይቻላል?

አቶ ወንድሙ፡- ፓርቲው መተዳደሪያ ደንቡን መሰረት አድርጎ ነው ሪፖርቱን የላከው። እስካሁን የተከተሉት አካሄድ ትክክል ነው። በሌላ መልኩ ኢንጅነር ይልቃልም ቅሬታ አቅርበዋል። ስለዚህም የአዲሱን ስራ አስፈጻሚ ሪፖርት እና የኢንጅነር ይልቃልን ቅሬታ ጎን ለጎን ነው ጽ/ቤቱ እያየው ያለው። የመጨረሻው ውሳኔ የቦርዱ ነው የሚሆነው።

የአዘጋጁ ማስታወሻ

በዚህ ጉዳይ ላይ ተጨማሪ ማብራሪያ እንዲሰጡን ኢንጅነር ይልቃል ጌትነትን በተንቀሳቃሽ ስልካቸው ደውለን ብንጠይቃቸውም ምላሽ ሊሰጡን ፈቃደኛ አልሆኑም።¾

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
554 ጊዜ ተነበዋል

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us