ለኢትዮጵያ እስከ 20 ሺህ ጦር ያሰለፉት ካስትሮ ሲታወሱ

Thursday, 01 December 2016 15:40

 

ባለንበት ዘመን በዓለማችን በስልጣን ላይ ቆይታ ረዥሙን ዕድሜ ካስቆጠሩት የሀገራት መሪዎች መካከል አንዱ የነበሩት ፊደል ካስትሮ አርፈዋል። ካስትሮ በ90 ዓመታቸው ህወታቸው ያለፈ ሲሆን ስልጣናቸውን ለወንድማቸው ራኦል ካስትሮ ያስረከቡት የጤንነታቸው ሁኔታ አስጊ ደረጃ ላይ መድረስ በጀመረበት በ2008 ዓ.ም ነበር። ካስትሮ ስድስት መቶ ጊዜ ያህል የግድያ ሙከራ የተደረገባቸው መሆኑን በተደጋጋሚ የሚገለፅ ጉዳይ ሲሆን ይህንን ሁሉ ፈተና አልፈው 90 ዓመት መድረሳቸው ለሁሉም ሰው ግርምትን የሚፈጥር ነው።

 

ካስትሮ ታሪካቸው ረዥም ቢሆንም ከኢትዮጵያ ጋር የሚያገናኛቸው ልዩ ታሪክ እንዳለ ግን መዘንጋት የለበትም። ካስትሮንና ኢትዮጵያን ያስተሳሰራቸው ታሪክ የጀመረው ሶማሊያ ኢትዮጵያን በወረረችበት ወቅት እስከ ሃያ ሺህ የሚደርስ ጦርን በማሰለፍ በወረራው ቅልበሳ ላይ የኩባዊያንን የደም አሻራን ማስቀመጣቸው ነው።  በእርግጥም ካስትሮ ከኢትዮጵያ ጋር የነበራቸው ትስስር የሚነሳበት ወቅት ቢኖር ይህ ወቅት ነው። አጠቃላይ ታሪካዊ ሂደቱም ከብዙ በጥቂቱ ይሄንን ይመስላል።

በጊዜው ስልጣን ላይ ለነበረው የደርግ መንግስት በርካታ ፈታኝ ሁኔታዎች ነበሩ። የኤርትራ ነፃነት ተዋጊ ኃይሎች ከተራ ሽምቅ ተዋጊነት ባለፈ ወደ ተደራጀ የውጊያ ስልት የተሸጋገሩበት ወቅት ነበር። በሰሜን ምዕራብ አቅጣጫ በሳዑዲ አረቢያና በሱዳን የሚታገዘው የኢዲዩ ጦር በሁመራ መተማ መስመር የጎንደር ከተማን ለመቆጣጠር ሰፊ የማጥቃት እንቅስቃሴንም በመጀመሩ ሌላው ፈተና ነበር።

 

ከሁሉም በላይ ደግሞ የኢህአፓ ኃይሎች የከፈቱት የከተማ ውስጥ የሽምቅ ውጊያ በስልጣን ላይ የነበረውን ምንግስት መያዣ መጨበጫ ያሳጣ ጥቃት ደግሞ መላ ሀገሪቱን የጦርነት አውድማ አድርጓታል። በጊዜው ኮሎኔል መንግስቱና ሌሎች የስልጣን ተቀናቃኞቻቸው የሚያደርጉት የውስጥ የስልጣን ሽኩቻ በራሱ ሌላኛው የሀገሪቱ ፈተና ሲሆን፤ ከእነዚህ የፖለቲካ ውጥንቅጦች መካከል አንዳቸውም መልክ ባልያዙበት ሁኔታ ከሁሉም የባሰው አስፈሪ ገፅታን ተላብሶ ብቅ ያለው የሶማሊያ ጦር የኢትዮጵያን አንድ አምስተኛ ግዛት ቆርሶ በኃይል ለመቀላቀል በሰፊ ወታደራዊ ዝግጅት ውስጥ መጠመዱ ነበር። “ታላቋ ሶማሊያ” በሚል የተስፋፊነት ህልም የሶማሌ ዘሮች ያሉበትን ግዛቶች በሙሉ በአንድ ግዛት ስር አጠቃሎ ሰፊ ግዛት ያላትን ሀገር የመፍጠር ድህረ ቅኝ ግዛት ህልምን የሰነቀው የዚያድ ባሬ መንግስት በኢትዮጵያ የኦጋዴንን ግዛት እንደዚሁም መላ ጂቡቲንና ሰሜን ኬኒያን በወታደራዊ ኃይል አንበርክኮ ወደ ሶማሊያ ለመቀላቀል ቀላል የማይባል ዝግጅትን ማድረግ ከጀመረ ረዘም ያሉ ዓመታትን አስቆጥሯል።

 

ያም ሆኖ በጂቡቲ የፈረንሳይን እንደዚሁም በኬኒያ የእንግሊዝ ቅኝ ገዢዎችን ማስጠንቀቂያ ማክበር ግድ የሆነበት ዚያድ ባሬ ሁለቱን ሀገራት በወታደራዊ ኃይል ከመተናኮስ በመቆጠብ ሙሉ ትኩረቱን ኢትዮጵያ ላይ አደረገ። የወረራ ሂሳቡን በመስራት ሙሉ ወታደራዊ አቅሙን ኢትዮጵያ ላይ እንዲያሳርፍ ካደረጉት ምክንያቶች መካከል ዋነኞቹ ሀገሪቱ በከፍተኛ የውስጥ የፖለቲካ ውጥረት ውስጥ መግባቷ፣ የፖለቲካ ስልጣኑን የያዘው መንግስት በህዝቡ ዘንድ ተቀባይነት የለውም ብሎ በማመኑና የሀገሪቱም ወታደራዊና ኢኮኖሚያዊ አቅም እጅግ የተዳከመ ነው ብሎ በማመኑ ነበር።

 

የሶማሊያ መንግስት ኢትዮጵያን ለመውረር ሲነሳ የሰራቸው ብዙዎቹ ሂሳቦች ከሞላ ጎደል ትክክል ነበሩ ማለት ይቻላል። ደርግ ከንጉሱ የተረከበው ጦር በቁጥርም ሆነ በወታደራዊ ሳይንስ ክህሎት በኩል ዘመኑ የሚጠይቀውን አቅም ገንብቶ ነበር ማለት አይቻልም።  ኢትዮጵያ ላይ ሁሉን አቀፍ ወረራን ለማካሄድ የ15 ዓመታት ዝግጅትን ያደረገው ጦር መመከት ይቅርና በሰሜን የኤርትራ ሽምቅ ተዋጊዎችን ሳይቀር በሚገባ መቋቋም የተሳነው የወቅቱ የሀገሪቱ መደበኛ ጦር፤ በስልጠና፣በትጥቅ አቅርቦትና በቁጥር ጭምር ብዙ መደራጀት የሚጠይቀው ነበር። ይህንን የተረዱት የወቅቱ የሀገሪቱ መሪ ኮሎኔል መንግስቱ ኃይለማርያም የሶማሊያን ጦር ወረራ ለመግታት የነበራቸው ብቸኛ አማራጭ በዲፕሎማሲው አቅጣጫ አጠንክሮ መግፋት ነበር።

 

የሶማሊያው መሪ ዚያድ ባሬ ኢትዮጵያን ለመውረር ሲያደርጉት በነበረው ዝግጅት የተወሰነ ጦር መሳሪያ ከአሜሪካ፤ እንደዚሁም በኮሚኒስትነታቸው ደግሞ  ከቀድሞዋ ሶቬየት ህብረትና መሰል  መንግስታት በገፍ ያገኙ ሲሆን ግብፅና ሳዑዲ አረቢያን ከመሰሉ መንግስታት ደግሞ ሰፊ ፋይናንስ ማሰባሰብ ችለዋል። በአፍሪካ የመጀመሪያው ሳይንሳዊ ማርክሲስት ሌኒንስት ርዕዮተ ዓለም ተከታይ መሆናቸው ከቅኝ ግዛት ነፃነት ማግስት ብዙም ሳይቆዩ ያወጁት ዚያድ ባሬ የሶቪየቶችን ቀልብ በመግዛታቸው የሁለቱ ሀገራት ግንኙነት በእጅጉ እየተጠናከረ ሄዷል። አሜሪካ ከንጉሱ ዘመን ጀምሮ በአስመራ ቃኘው ጦርና በቀይ ባሕር አካባቢ የአሜሪካ መንግስት ወታደራዊ ይዞታውን እንዲተክል በመፍቀዷ ሶቪየቶች በአካባቢው ያለውን ወታደራዊ ሚዛን ለማስጠበቅ ከሰሜን የመን ባሻገር የህንድ ውቅያኖሷን ሶማሊያን በርዮተ ዓለማዊ አጋርነት መያዝ ነበረባቸው።

 

ደርግ ስልጣን ሲይዝ ከበርካታ የሀገር ውስጥ ግራ ዘመም ኮሚኒስታዊ ኃይሎች ጋር መፋለሙና የንጉሱን ዘመን የአሜሪካን የቃኘው ጦርንም ቢሆን ባለበት እንዲቀጥል ማድረጉ ለምስራቁ ዓለም ፍረጃ ተጋላጭ እንዲሆን አድርጎታል። ይህም በመሆኑ ሶቪየቶች የሶማሊያን ወራሪ ኃይል በዘመናዊ መልክ ሲያደራጁና ሲያዋቅሩ ጦሩ በጊዜው አሉ የተባሉትን ሶቪየት ሰራሽ ሚግ 23 የጦር አውሮፕላኖች ሳይቀር እንዲታጠቅ ተደርጓል። ይህ ብቻ ሳይሆን ጊዜ ወስዶም በቂ ስልጠና እና አየር ሀይሉን ከምድር ጦሩ ጋር የማዋሀድ ስራው የተሰራ ሲሆን ወረራውንም ለመጀመር በድንበር አካባቢ አንዳንድ አቅምን የመፈተሽና የትንኮሳ ስራም ይሰራ ነበር።

 

የሶማሊያ መንግስት በሶሻሊስት ርዕዮተ ዓለም ተከታይነቱ በበቂ ሁኔታ ራሱን ሲያስታጥቅ ኢትዮጵያ በአንፃሩ በንጉሱ ዘመን ከቀጠለው የቆየ አሜሪካ ሰራሽ መሣሪያ ውጪ ምንም አይነት የተደራጀ የጦር መሳሪያ ትጥቅ አልነበራትም። አሜሪካንን ከማግባባት ተጨማሪ የጦር መሳሪያን ለማስገባት የተደረገው ሙከራ ውጤት አለማምጣቱ ተረጋገጠ። አሜሪካ የወቅቱን መንግስት በሰብአዊ መብት ጥሰት አጥብቃ በመኮነኗ የኢትዮ አሜሪካ ግንኙነቱ የበለጠ እየሻከረ ሄዶ ወደ ቃላት ጦርነት አመራ።

 

የአሜሪካ የቆየ ወታደራዊ ወዳጅነት ብዙም እንደማያስኬድ በሚገባ የተረዱት የደርግ ባለስልጣናት ሀገሪቱ የተደቀነባትን ወረራ ለመቀልበስ የነበራቸው ብቸኛ አማራጭ ሙሉ በሙሉ ጠቅልለው የምስራቁን የኮሚኒስት ጎራ መቀላቀል ነበር። ኢትዮጵያ በአንድ መልኩ ቁርጠኛ የኮሚኒስቱ ጎራ አጋር መሆኗን ለማሳየት፤ በሌላ አቅጣጫ ደግሞ የሶማሊያን የወረራ እቅድም በዲፕሎማሲ ለማጋለጥ ሲባል ሰፊ የሆነ ዓለም አቀፍ የዲፕሎማሲ ሥራ መሰራት ነበረባት።

 

ከዚሁ ጋር በተያያዘም በአንዳንድ የኮሚኒስት ሀገራት ኮሎኔል መንግስቱን ያካተተ ልዑካን ቡድን እንደዚሁም በሌሎቹ ደግሞ የወቅቱን ከፍተኛ የፖለቲካ አመራሮች ባከተተ መልኩ በርካታ የስራ ጉብኝቶች ተደርገዋል። በእነዚህ ተከታታይ ጉብኝቶች ከተካተቱት ሀገራት መካከል ነበር፤ የቀድሞዋ ሶቪየት ህብረት፣ ቻይና፣ ሰሜን ኮሪያ፣ ምስራቅ፣ የቀድሞዋ ቼኮዝሎቫኪያ፣ ቡልጋሪያ፣ ሩማንያ፣ የቀድሞዋ ጎዝላቪያ፣ኩባና ደቡብ የመን ይገኙበት ነበር። በጊዜው የኢትዮጵያ የፖለቲካ አመራሮች ቁርጠኛ ኮሚኒስት መሆናቸው አስረግጠው ማስረዳታቸውና ይህንንም በተግባር ለማሳየት የቻሉትን ያህል ጥረት ማድረጋቸው ሶቪየቶችም ሆኑ ሌሎች ኮሚኒስት ሀገራት ከሶማሊያ ጎን ተሰልፎ ኢትዮጵያን ከጀርባ ከመውጋት ይልቅ ሁለቱ ሀገራት ወደ ድርድር እንዲገቡ የራሳቸውን ፖለቲካዊ ተፅዕኖ ማድረግ  ጀመሩ። ይህ አይነቱ አካሄድ ለኢትዮጵያ ታላቅ ዲፕሎማሲያዊ ድል ሲሆን ለዚያድ ባሬና ለሶማሊያ በአንፃሩ ታላቅ ሽንፈት ነበር።

 

በዚህም ዙሪያ የነበረውን የሰላም ድርድር ባለመቀበል የታላቋን ሶማሊያ ህልም እውን ለማድረግ ቁርጠኛ የነበረው የዚያድ ባሬ መንግስት በእንቢታው በመቀጠሉ ተፅዕኖው በከፍተኛ ደረጃ እያየለ ሄደ። በዚህ ወቅት ነበር ፊደል ካስትሮ ቁርጠኛ አቋም በመያዝ የሰይ ድባሬን መንግስት በጥብቅ መሞገት የጀመሩት። ፕሬዝዳንቱ ሶማሊያ ከሌሎች ኮሚኒስት ሀገራት አመራሮች ጋር በመሆን የሶማሊያ አመራሮች ከኢትዮጵያ መንግስት አመራሮች ጋር ለድርድር እንዲቀመጡ ከፍተኛ የተሰሚነት ተፅዕኗቸውን ማሳረፍ ጀመሩ።

 

በዚህም በሞስኮ አንድ ስብሰባ በከባድ የድርድር ተፅዕኖ ስር የወደቁት የሶማሊያ አመራሮች ሳይወዱ በግዳቸው የፊት ለፊት ድርድር ለማካሄድ ውሳኔ ላይ ደረሱ። ሁለቱን ሀገራት በማደራደር የጦርነቱን ደመና በሰላማዊ መንገድ ለመቋጨት ቁርጠኛ የነበሩት ፊደል ካስትሮ በተገባው ቃል መሰረት የሶማሊያ ባለስልጣናት በቃላቸው እንዲፀኑ በተደጋጋሚ መወትወታቸውን ተያያዙት። ወደ ሶማሊያም በማምራት በቀድሞዋ ኮሚኒስት ሀገር ደቡብ የመን ዋና ከተማ ኤደን በሚደረገው ድርድር ላይ ባለስልጣናቱ እንዲገኙ ተጨማሪ ውትወታቸውን በማካሄድ በቀጥታ ወደ አዲስ አበባ አመሩ። ካስትሮ በመቋዲሾ በነበራቸው ቆይታ ድርድሩ ቀድሞውኑ የከሸፈ መሆኑን አስቀድመው የተረዱ ቢሆንም፤ ቢያንስ ግን የፊት ለፊት ድርድሩ በሶማሊያ እምቢተኝነት መክሸፉ ኢትዮጵያን ለተጨማሪ የዲፕሎማሲ ድል የሚያበቃ መሆኑን ግን ያወቁ ነበር።

 

ፕሬዝዳንቱ እጅግ አስቸጋሪ የነበረውን የሶማሊያ ጉብኝት እንዳጠናቀቁ አዲስ አበባ ገብተው የሰላም ድርድሩን ሂደት ለኮሎኔል መንግስቱ ማስረዳት ነበረባቸው።    ካስትሮ መጋቢት 14 ቀን 1968 ዓ.ም ምሽት ላይ አዲስ አበባ በገቡበት ወቅት ከተማዋ ከኢህአፓ ሽምቅ ተዋጊዎች ጋር ተያይዞ ከፍተኛ ውጥረት ውስጥ ስለነበረች እዚህም እዚያም የተኩስ ድምፅ ይሰማ ነበር። በወቅቱ የተኩሱን ድምፅ ሰምተው ለኮሎኔል መንግስቱ ጥያቄ ካቀረቡ በኋላ በተሰጣቸው ምላሽ “ኢትዮጵያ በትክክለኛ አብዮት ውስጥ የምትገኝ ሀገር መሆኗን ተረድቻለሁ” የሚል ምላሽ መስጠታቸው ይነገራል።

 

ኢትዮጵያም ሆነች ሶማሊያ የሶሻሊስት ርዕዮተ ዓለም ተከታይ ሀገራት በመሆናቸው “አብዮቱ አብዮቱን መውጋት የለበትም” የሚል አቋም ላይ የደረሱት ፊደል ካስትሮና አጋሮቻቸው፤ ዚያድ ባሬ በእንቢተኝነታቸው ከቀጠሉ ግን ከሁለት ሀገራት መካከል አንዱን መርጦ ለመደገፍ ቁርጠኛ ነበሩ። በጊዜው የዲፕሎማሲ ስሌት መሰረት የቀደመው የሶማሊያ ድጋፍ ወደ ኢትዮጵያ እንደሚዞር ጥርጥር አልነበረውም።

 

የተቆረጠው ቀን ደርሶ ከቀይ ባህር ማዶ ባለችው ኤደን ከተማ ወሳኙ ድርድር ተጀመረ። በዚህ ድርድር ፊደል ካስትሮ፣ የወቅቱ የደቡብ የመንን ፕሬዝዳንት፣ኮሎኔል መንግስቱ እና ዚያድ ባሬ ተገኙ። ድርድሩን ወደፊት ለመግፋት የተደረገው ጥረት በዚያድ ባሬ ፍላጎት ማጣት ሳይሳካ ቀረ። ሁኔታውን ከመጀመሪያው እስከመጨረሻው የተረዱት ፊደል ካስትሮ በድርድሩ መክሸፍ ጦርነቱ አይቀሬ መሆኑን በመመልከት የኢትዮጵያ ባለስልጣናትን አፅናንተው ወደ ሀገራቸው አመሩ።

 

ካስትሮ ከዚያን ወቅት ጀምሮ የኢትዮጵያን ሉአላዊነት ለማስጠበቅ በሚደረገው ራስን የመከላከል ሂደት ውስጥ ያልተቆጠበ ድጋፋቸውን ለመስጠት ቃል ገቡ። የመጀመሪያ ስራቸውንም የጀመሩት ሂደቱን በቅርብ ሲከታተሉ ለነበሩት የኮሚኒስት ሀገራት፤ የሶማሊያን እምቢተኝነትና የኢትዮጵያን የሰላም ፍላጎት ማስረዳት ነበር። ካስትሮ  በነበራቸው መልካም ስምና ዝና ከፍተኛ ተፅዕኖ ፈጣሪ መሪ ስለነበሩ አጠቃላይ ሂደቱን በተመለከተ ለሶቬቱ መሪ ብሬዥኔቭ እንደዚሁም ለምስራቅ ጀርመኑ መሪ ኤሪክ ሆኔከርና ለሌሎች የምስራቁ ዓለም ሀገራት በሚገባ በማስረዳት ኢትዮጵያ ድጋፍን እንድታገኝ ማድረግ ችለዋል።

የኢትዮጵያ መሪዎች ቀጣይ ለሰሩት የመሣሪያና የዲፕሎማሲ ድጋፍ ሰፊውን የመደላድል ስራ የሰሩት ራሳቸው ካስትሮ ነበሩ። ኢትዮጵያ የዚህ ወረራ ተጠቂ መሆኗን የተረዱት በርካታ የምስራቅ አውሮፓ ሀገራት ከፍተኛ የሆነ የጦር መሳሪያ ድጋፍ ለማድረግ ቃል ገቡ። ይህ መልካም ቢሆንም ለኢትዮጵያ ግን ሌሎች ፈተናዎችም ነበር። አንደኛው አሜሪካ ሰራሽ መሳሪያ የለመደውን የኢትዮጵያ ጦር በአፋጣኝ ከሶቪየትና ከምስራቅ አውሮፓ መሳሪያዎች ጋር ራሱን አለማምዶ ወረራውን እንዲመክት ማድረግ ነው። ይህ ብቻ ሳይሆን ከገበሬው ተመልምሎ የአጭር ጊዜ ወታደራዊ ስልጠና ያገኘውን ህዝባዊ ሰራዊት ጦር ከመደበኛው ጦር ጋር አዋህዶ ለ15 ዓመታት የተዘጋጀውን የሶማሊያ ጦር እንዲቀለብስ ማድረጉም ሌላው ፈተና ነበር።

 

ሀገራት ቃል የገቧቸውን ጦር መሳሪያዎች በተሟላ ሁኔታ እያቀረቡ ባልነበረበት ሁኔታ  ካስትሮ ሶቪየት ሰራሽ ባለ አገልግል የነፍስ ወከፍ መሳሪያዎችን በመላክ የግንባር ቀደምነቱን ስፍራ ያዙ። ወረራውን ለመከላከል በሚደረገው ትንቅንቅ የኢትዮጵያ ጦር ክፍተትንም በመረዳት ቀዳዳውን ሊሸፍን የሚችል 20 ሺ የኩባ ጦርም ወደ ኢትዮጵያ እንዲላክ አደረጉ። ኩባዊያን የኢትዮጵያን ለኡላዊነት ለማስከበር ከኢትዮጵያዊያን ጎን ሆነው ተዋደቁ። ከአካል ጉድለት እስከ ህይወት የሚደርስ መስዋዕትነትንም ከፈሉ። ጦርነቱ በኢትዮጵያ አሸናፊነት በድል ከተጠናቀቀ በኋላም ቢሆን ኩባ ለኢትዮጵያ ሰፊ የኢኮኖሚ እገዛ በማድረግና ለበርካታ ተማሪዎችም በኩባ ነፃ የትምህርት እድል እንዲያገኙ በማድረግ ሰፊ ስራን ሰርታለች።

 

ካስትሮ ከኮሎኔል መንግስቱ ጋር ጥብቅ ወዳጃዊ ግንኙነትም ነበራቸው። ኮሎኔል መንግስቱ በተደጋጋሚ የተቃጣበቸው የግድያ ሙከራና ፊደል ካስትሮም በተደጋጋሚ የአሜሪካ የግድያ ሴራ ማምለጣቸው አንደኛው የግል ትስስራቸው መገለጫ ነበር። ሁለቱም መሪዎች እጅግ የፀና ፀረ አሜሪካ አቋም ነበራቸው።አብዮታዊው መሪ ፊደል ካስትሮ ከኮሎኔል መንግስቱ የውስጥ የፖለቲካ ትግል ደምሳሽነት ጋር ተመሳሳይ ባህሪ የነበራቸው ናቸው።

   

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
474 ጊዜ ተነበዋል

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us