“ከኩባ ወታደሮች ጋር በአንድ ጉድጓድ ተቀብረናል፤ ውለታቸውንም ትውልድ አይዘነጋውም”

Wednesday, 07 December 2016 15:39

“ከኩባ ወታደሮች ጋር በአንድ ጉድጓድ ተቀብረናል፤ ውለታቸውንም ትውልድ አይዘነጋውም”

ብርጋዴን ጀነራል ዋሲሁን ንጋቱ

 

የሆለታ ገነት ጦር ትምህርት ቤት የ21ኛ ኮርስ ምሩቅ ሲሆኑ፣ በሙያቸው ታንከኛ ናቸው። በአሜሪካ እና በታላቋ ሶቪየት ሕብረት የታንከኛ ትምህርታቸውን ተከታትለዋል። ለሰላሳ አመታት በኢትዮጵያ ጦር ሰራዊት ውስጥ አገልግለዋል። በአሁን ሰዓት ጡረታቸውን አስከብረው መጽሐፍ በመፃፍ ላይ አተኩረዋል።

በ1956 ዓ.ም. ወደ ሶማሊያ ግዛት ተመድበው ግዳጃቸውን የተወጡ ያገር ባለውለታ ናቸው። በወቅቱ ከሶማሌ መንግስት ጋር በተደረገው ጦርነት በፈጸሙት ወታደራዊ ጀብድ ከእነአብዲሳ አጋ፣ ከእነስዩም ጋር፣ ከጃንሆይ እጅ የጦር ሜዳ ጀግና ሜዳሊያ ከወሰዱት መካከል አንዱ ናቸው።

ጀነራሉ፣ በወቅቱ በነበረው ጦርነት የሶማሌን መንግስት ጦር አሸንፈው ሃምሳ ኪሎ ሜትር ድረስ ወደ ሶማሌ ግዛት ዘልቀው መግባታቸውን አስታውሰዋል። የሶማሌ መንግስት ከአስራ ሶስት ዓመታት በኋላ ተጠናክሮ ኢትዮጵያን መውረሩን ወደኋላ መለስ ብለው በቁጭት ያስታውሱታል። በወቅቱ አምስት ሚሊዮን የማይሞሉ የሶማሌ ሕዝቦች በ1969 እና 1970 ዓ.ም. ኢትዮጵያን ለመውረር መብቃታቸውን፣ ለጀነራል ዋሲሁን እስካሁን ድረስ እንደ እግር እሳት የሚለበልባቸው መሆኑን ይናገራሉ። ሕዳር 11 ቀን 1970 ዓ.ም. ከሶማሌ መንግስት ጋር በተካሄደው ጦርነት በጥይት ተመተው ቆስለዋል። በሀገር ውስጥ ሁለት ጊዜ ቀዶ ጥገና ካደረጉ በኋላ፣ ወደ ሃንጋሪ በመሄድ የፕላስቲክ ቀዶ ጥገና ተደርጎላቸዋል።

በጊዜው የነበረውን ነባራዊ ሁኔታ ጀነራሉ ሲያስታውሱ፣ በጊዜው በቂ ጦር መሳሪያ ሀገራችን አልነበራትም። ለጦር መሣሪያ ግዢ የተፈጸመ ክፍያ ቢኖርም፣ የወቅቱ የአሜሪካ ፕሬዝደንት የነበሩት ጂሚ ካርተር የጦር መሳሪያ አቅርቦት ለኢትዮጵያ እንዳይፈጸም ከልክለዋል። በወቅቱ ቀዳማዊ ኃ/ስላሴ እንዲሁም ደርግ በጦር መሣሪያ እና በወታደራዊ ኃይል የተጠናከሩ አልነበሩም። አብዮትም በሀገር ውስጥ ተቀጣጥሎ የመንግስት ለውጥም ተደርጎ ነበር። በዚህ ወሳኝ ምዕራፍ ላይ ነበር፣ የኩባ መንግስት እና ሕዝብ የደረሱልን። ጀነራሉ እርግጠኛ ሆኜ የምናገረው፣ “ከኩባ ወታደሮች ጋር በአንድ ጉድጓድ ተቀብረናል። ውለታቸውን ከሚሊዮን አመታት በኋላ የሚመጣው ትውልድም አይዘነጋውም።” ብለዋል። ሰሞኑን በ90 ዓመት ዕድሜያቸው ያረፉትን የኩባ የቀድሞ ፕሬዚደንት ፊደል ካስትሮ ከኢትዮጵያ ጋር የነበራቸውን ግንኙነት መነሻ በማድረግ ከጄኔራል ዋሲሁን ጋር ያደረግነውን ቃለ ምልልስ በዚህ መልክ አቅርበነዋል።

ሰንደቅ፡- ፊደል ካስትሮ እና የኩባ ሕዝብ ከሶማሌ መንግስት ጋር በተደረገው ጦርነት እንዴት ይታወሳሉ?

ጀነራል ዋሲሁን፡-የሶማሌ መንግስት በ1969 ዓ.ም. ሰባት መቶ ኪሎ ሜትር የኢትዮጵያን ግዛት ዘልቆ ወረራ በፈጸመበት ጊዜ ነበር፣ ኮሎኔል መንግስቱ ለፊደል ካስትሮ ባቀረቡት ጥሪ መሰረት የኩባ ወታደሮች የደረሱልን። በከፍተኛ የቁስ እና የሰብዓዊ ሕይወት በመክፈል ከኢትዮጵያ ጦር ሰራዊት ጋር በጋራ በመሆን በ1970 ዓ.ም. የሶማሌን መንግስት ጦር አሸንፈን ከሀገራችን እንድናስወጣ ያበረከቱልንን ዋጋ ሁሌም ስናስታውሰው እንኖራለን። ፊደል ካስትሮ እና የኩባ ሕዝብ የሚታወሱት፣ ሉዐላዊ ግዛታችን እንድናስጠብቅ በሰጡት ወታደራዊ አመራር እና በከፈሉልን የሕይወት መሰዋዕትነት ነው። ግንኙነታችን ዘላለማዊ የሚያደርገው፣ በደም የተሳሰረ በመሆኑ ነው።

ሰንደቅ፡- ኩባዊያን በጦርነት ውስጥ የነበራቸው ሚና ምንድን ነበር?

ጀነራል ዋሲሁን፡-እንደሚታወቀው በኒካራጓዋ፣ በሞዛምቢክ፣ በአንጎላ በመጨረሻ ደግሞ በኢትዮጵያ የኩባን ጦር ሰራዊት በመምራት ይዘው የመጡት በወታደራዊ አመራራቸው ከፍተኛ እውቅና የነበራቸው ጀነራል ኦቸዋ ናቸው። ከኢትዮጵያ መከላከያ ሚኒስቴር የኩባን ጦር ሰራዊት ለመቀበል በመከላከያ ሚኒስትሩ ጀነራል ኃ/ጊዮርጊስ ሃ/ማሪያም ከተመራው ልዑክ ውስጥ አንዱ ነበርኩ።

የኩባ ጦር ሰራዊት ይዟቸው የመጣው ታንኮች አሰብ ወደብ ደርሰዋል። ከአሰብ እስከ ዑጋዴን ድረስ ታንክ እየነዱ መሄድ የማይታሰብ ነው። ታንኮቹን በሎቤድ ጭነን እስከ አዋሽ አርባ ድረስ አመጣናቸው። ከአዋሽ አርባ እስከ ድሬደዋ ድረስ የኩባ ታንከኞች ናቸው ታንኮቹን እየነዱ ያደረሷቸው። ወደ መቶ የሚጠጉ ታንኮች ናቸው። የሶማሌ መንግስት በአየር ማረፊያ በሰሜን በኩል ድሬደዋን ለመያዝ አስራ አምስት ኪሎ ሜትር ርቀት ብቻ ነበር የቀረው። ሃያ፣ ሃያ ታንኮች በተለያዩ ቦታዎች በማሰማራት በሶማሌ ጦር ላይ በከፈትነው ማጥቃት ድሬዳዋ በጠላት እጅ እንዳትወድቅ አድርገናል። በዚህ ጦርነት የኩባ ታንከኞች አስተዋጽዖ ከፍተኛ ነበር።

ሰንደቅ፡- ምን ያህል የኩባ ወታደሮች በጦር ግንባር ተሰውተዋል?

ጀነራል ዋሲሁን፡- የኩባ ጦር ሰራዊትን በአብዛኛው የተጠቀምንባቸው በወታደራዊ አመራር አሰጣጥ እና ቴክኒካል በሆኑ ጉዳዮች ላይ ነበር። ይህም ሆኖ በካራማራ እና በጭናግሰን በተደረገው የመልሶ ማጥቃት ውጊያ ላይ ከመቶ አርባ በላይ የኩባ ወታደሮች ሕይወታቸውን መስዋዕት አድርገው ለእኛ ሉዐላዊነት መከበር ተሰውተዋል። ከባቢሌ ሃያ አምስት ኪሎ ሜትር ላይ እኔም ቆስዬ ነበር።

ሰንደቅ፡- ከወታደራዊ ዲሲፕሊን አንፃር የኩባ ወታደሮች እንዴት ይገለፃሉ?

ጀነራል ዋሲሁን፡- በወታደራዊ ሥርዓት እና በወታደራዊ ዲሲፕሊን እጅግ የተካኑ ናቸው። ነባሮች ናቸው፤ ልምድ ነበራቸው። ኮሎኔሉ ለጀነራሉ ያለው አክብሮት። ሻለቃው ለኮሌኔል ያለው አክብሮት። ለኮሎኔሉ ሻይ የሚቀዳው ሻለቃው ነው። ለሥራ የተፈጠሩ ናቸው። እንዲሁም ሁለገብ ሠራተኞች ናቸው። የመኪና ሾፌር፣ የታንክ መካኒክም ናቸው። አንዱ ወታደር ከአንድ ሙያ በላይ የሚያውቅ ነው። ከባሕሪ አንፃር በቀላሉ ከሰው ይግባባሉ። በጣም ግልጽ ሰዎች ናቸው።

ሰንደቅ፡- ከኩባ ሕዝብ ጋር ያለን ግንኙነት ከተከፈለው መስዋዕትነት አንፃር ጎልቶ የወጣ አይደለም። ፊደል ካስትሮም በአዲስ ትውልድ ብዙ የታወሱ አይመስልም። ይህ የሆነበት ሁኔታ ምን ይመስልዎታል?

ጀነራል ዋሲሁን፡-እንደሚታወቀው የመንግስት ለውጥ ሲኖር የአይዲዮሎጂ ለውጥ የሚጠበቅ ነው። ከ1983 ዓ.ም. በኋላ በኢትዮጵያ አዲስ መንግስት በመሆኑ የአይዲዎሎጂ ለውጥ ተደርጓል። ኮሎኔል መንግስቱ ኃ/ማሪያም እስከነበሩበት ጊዜ ፊደል ካስትሮ ባበረከቱት አስተዋፅዖ መጠን ይታወሱ ነበር።

አሁንም ቢሆን ከኩባ መንግስት እና ሕዝብ ጋር መልካም የሆነ ወዳጅነት ነው ያለን። የኢትዮጵያ መንግስት ፕሬዝደንት ዶክተር ሙላቱ ተሾመ ለፊደል ካስትሮ ቀብር ወደ ሃቫና መሄዳቸው ተገቢና አሁንም የሁለቱ መንግስታት ግንኙነት በጥሩ ሁኔታ ላይ መሆኑ ማሳያ ነው። ወደፊትም የሚመጣ መንግስት እንዲሁም ሕዝቡ ማወቅ ያለበት እውነታ፣ ከኩባ ወታደሮች ጋር በአንድ ጉድጓድ ተቀብረናል። ከሌሎች ሀገሮች በተለየ በኢንቨስትመንት ወይም በሌላ መልኩ የሚገልጽ ግንኙነት ብቻ አይደለም ያለን። በኢትዮጵያ ሕዝብ እና በኩባ ሕዝብ መካከል ያለው ግንኙነት፣ በደም የተሳሰረ ግንኙነት ነው። ይህንን ውለታቸውን፣ ከሚሊዮን አመታት በኋላ የሚመጣው ትውልድም አይዘነጋውም። ደም፣ ከውኃ ይወፍራል። መንግስት ቢቀያየርም በሁለቱ ሀገሮች ያለው ግንኙነት መቼም አይቀየርም።

ሰንደቅ፡- የኩባ ጦር ሰራዊት ከኢትዮጵያ ሲወጣ የነበረው ሽኝት ምን ይመስል ነበር?

ጀነራል ዋሲሁን፡-በጊዜው የተባበሩት መንግስታት የኩባ ጦር ሰራዊት ከአፍሪካ ለቆ እንዲወጣ ትዕዛዝ ማስተላለፉ የሚታወስ ነው። ከኢትዮጵያ እንዲወጡ የተደረገው ግን ቀነ ገደብ አስቀምጠው ነበር። የኩባ ጦር ሰራዊት ዘጠነኛ ብርጌድ ወይም ኖቫ ብርጌድ ተብሎ ነበር የሚጠራው። የመጨረሻው የሽኝት ቀን በታጠቅ ማሰልጠኛ የተቀበልኳቸው እኔ ነበርኩ። የኩባ ጦር ሰራዊት መሪዉ ጀነራል ኦቼ ነበር።

በዚህ የሽኝት ሥርዓት ላይ ጀነረል ኦቼ ያቀረበው ጥያቄ የሚደንቅ ነበር። ጀነራል ኦቼ “እኛ ለኢትዮጵያ መንግስት እና ሕዝብ ተዋግተናል፣ ሞተናል። ከእናንተ የምንፈልገው ነገር የለም። ግን ኩባን ኢምፔሪያሊዝም (አሜሪካ በወቅቱ በኩባዎች ዘንድ ኢምፔሪያሊዝም እያሉ ነው የሚጠሯት) ቢወራት፣ አንተ ኩባ መጥተህ አብረኽን ትዋጋለህ? ትሞታለህ?” ብሎ ነበር የጠየቀኝ።

የሰጠሁት ምላሽ፣ ኢምፔሪያሊዝም ኩባን ቢወር፣ ሃቫና በመምጣት ከኩባ ጦር ሰራዊት ጋር በጋራ በመሆን ስድስተኛውን ብርጌድ ይዤ በመምጣት እዋጋለሁ! እሞታለሁ! በማለት ቃሌን ሰጥቼ ተንበርክኬ ነበር፣ የኩባ ባንዲራ  የተቀበልኳቸው። አሁንም ድረስ የተቀበልኩት የኩባ ባንዲራ በመኖሪያ ቤት ይገኛል። አንድ ቀን ለሙዚየም አስረክበዋለሁ።¾

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
464 ጊዜ ተነበዋል

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us