“የሞባይል ኢንተርኔት የተቋረጠው ለዜጎች ጥቅም ሲባል ነው”

Wednesday, 07 December 2016 15:48

“የሞባይል ኢንተርኔት የተቋረጠው

ለዜጎች ጥቅም ሲባል ነው”

ዶክተር ነገሪ ሌንጮ

የመንግስት ኮምዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/በት ኃላፊ ሚኒስትር

በይርጋ አበበ

የኢትዮጵያ መንግስት ቃል አቀባይ (ኮምዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት ኃላፊ ሚኒስትር) ዶክተር ነገሪ ሌንጮ ባሳለፍነው ሳምንት በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ለብዙሃን መገናኛ ድርጅት ባለሙያዎች መግለጫ ሰጥተው ነበር። ሚኒስትሩ ከጋዜጠኞች የቀረቡላቸውን ጥያቄዎችና የመንግስታቸውን አቋም የሚመለከቱ መረጃዎችን ሰጥተዋል። በተለይ በአገራችን ሰሜኑ ክፍል (ሰሜን ጎንደር) ነፍጥ ካነገቡ ኃይሎች ጋር የመንግስት መከላከያ ሰራዊት አባሎች ጋር ግጭት ተይቷል ስለመባሉ፣ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ምክንያት የግል ጋዜጦች ተዘግተዋል ተብሎ ስለመነገሩ፣ ገዥው ፓርቲ በጥልቀት ታድሻለሁ ቢልም የካቢኔ ሹም ሹር እንጂ የህዝብን ጥያቄ እና ፍላጎት ያማከለ እርምጃ አልተወሰደም በሚባለው እና አገሪቱ ፍጹም ጸጥታ የራቃት ቀጠና ተብላ በውጩ ዓለም ተፈርጃለች ስለሚለው እንዲሁም የሞባይል ኢንተርኔት በተለይም የማህበራዊ ሚዲያውን መንግስት አቋርጧል በሚሉት ጉዳዮች ላይ የሰጧቸውን ማብራሪያዎች ከዚህ በታች አቅርበናቸዋል።

ጥያቄ፡- መንግስት ጥልቅ ተሃድሶ አድርጌያለሁ ባለ ማግስት የባለስልጣናትን ሹም ሽር አካሂዷል። ሆኖም መንግስት ከመልካም አስተዳደር ይልቅ ለፓርቲ አመራሮች እና አባላቱ ነው እንጂ ተጠያቂ የሆነ የለም። ይህ ደግሞ ቀደም ሲል በመንግስት በኩል ሲነገር ከነበረው ጋር የማይገናኝ ነውና በህብረተሰቡ ላይ የሚሰጠው አንድምታ ምንድን ነው?

መልስ፡- እንደሚታወቀው በቅርብ ጊዜ የተካሄደው የካቢኔ ለውጥ አንዳንድ ኃላፊዎች ከስልጣናቸው የተነሱበት ሁኔታ እንዳለ እናውቃለን። ሂደቱ እንደሚታወቀው አዲስ አይደለም፡፡ ከዚህ በፊትም ፓርቲው በየጊዜው ውሳጣዊ አሰራሩን እየፈተሸ እርምጃ ሲወስድ እንደቆዬ ሁላችንም የምናውቀው ጉዳይ ነው። አሁን ከቦታቸው የተነሱት ሌላ ቦታ ተሾሙ የሚባለው ምናልባት የሚመለከታቸውን ስራ መስራት ያለባቸው ሰዎች መስራት የሚችሉትን ስራ እንዲሰሩ የሚደረግበት ሁኔታ በየጊዜውም ደግሞ ተጠያቂ መሆን ያለባቸውም ካሉ በሂደት ታይቶ ያ ተጠያቂነት የሚቀጥልበት ሁኔታ ይኖራል ማለት ነው። ስለዚህ በደፈናው ቅድሚያ የሚሰጠው ለፓርቲው አመራር ነው የሚለው ትክክለኛ መረጃ አይመስለኝም።

ጥያቄ፡- በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ምክንያት በዲፕሎማቶች ላይ በተጣለው እገዳ የተነሳ የቱሪዝም ገቢው ቀንሷል ይባላል። በዚህ ዙሪያ የሆቴል ባለቤቶችም መንግስት የተቀዛቀዘውን ገቢያቸውን የሚያስተካክሉበትን አሰራር እንዲዘረጋላቸው እንጠይቃለን ሲሉ ተናግረዋል። ይህን በተመለከተ የመንግስት አቋም ምንድን ነው?

መልስ፡- በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ማስፈጸሚያ ደንብ ላይ ዲፕሎማቶች ለደህንነታቸው ጥንቃቄ እንዲያደርጉ ባስተላለፉት መግለጫ ምክንያት በተወሰነ ደረጃ በቱሪዝም ቢዝነሱ ላይ ተጽእኖ ማሳደሩን አንዳንድ ሰዎች ሲገልጹ እንደነበረ እናውቃለን። ይሁን እንጂ ከእነ ጭራሹ ኢንቨስትመንት ላይ ወይም የቱሪዝም እንቅስቃሴ ላይ ከባድ ተጽእኖ አሳድሯል ብለን መደምደም አይቻልም። ስለዚህ መንግስት ምን እያደረገ ነው ለሚለው እንደሚታወቀው መንግስት የዲፕሎማቲክ ሚሽኖችን ጠርቶ በማናገር አሁን ያለው ሁኔታ ኢትዮጵያ ውስጥ ማንኛውም ሰው በሰላም ወጥቶ መግባት እንደሚችልና ቱሪስቶችም ደግሞ የሚፈልጉትን ቦታ በሰላም ሂደው ጎብኝተው መመለስ እንደሚችሉ መረጃዎች በጊዜው እየተሰጡ መሆናቸውንና ይህም ደግሞ ለውጭ ያየን እንደሆነ እንደ ጀርመን ዩናይትድ ኪንግደም እና ስፔን የጉዞ እቀባ ማንሳት የቻሉበት ሁኔታ አለ። ሌሎችም እንደዚህ አይነት ጥርጣሬ ያላቸው አገሮች ሙሉ በሙሉ እቀባቸውን የሚያነሱ እንደሚሆን ተስፋ እናደርጋለን።

ጥያቄ፡- በአገሪቱ አንዳንድ ቦታዎች በተለይም በሰሜን ጎንደር አካባቢ ትጥቅ ያነሱ ኃይሎች እና የመንግስት የመከላከያ ሰራዊት ተኩስ ከፍተዋል፣ ጦርነትም ተካሂዷል የሚል መረጃ አለ። በዚህ ላይ መንግስት የሚለው ምንድን ነው?

መልስ፡- ጸጥታን በተመለከተ እንደሚታወቀው ኢትዮጵያ ውስጥ ትልቅ የጸጥታ ችግር የለም፤ የሰሜን ጎንደርን ጨምሮ። አንዳንድ የፈጠራ ወሬ የሚያናፍሱ ትልቅ ውጊያ እየተካሄደ ነው ብለው ብዙ የሚሉት ነገር በኖርም ከእውነታው የራቀ መሆኑን መገንዘብ ያስፈልጋል። እንደሚታወቀው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን በስራ ላይ ለማዋል እንቅስቃሴ የሚደረግበት ሁኔታ አለ። በቁጥጥር ስር የሚውሉትን ሰዎችም በየጊዜው እየተከታተሉ እርማት ሰጥቶ የሚለቀቁበት ሁኔታ አለ። ከዚህ ውጭ ጦርነት ብሎ የሚነገር ነገር እንደሌለ እና በደቡብ ትግራይ (ወልቃይት ጠገዴ እና ቃፍታ ሁመራ ማለታቸው ነው) የኤርትራ መንግስት አሾልኮ ያስገባቸው የተወሰኑ የአሸባሪው ቡድን አባላት ነበሩ። ሆኖም ያንን ቡድን የትግራይ ሚሊሻዎች በቁጥጥር ስር እንዳዋሉትና ሰራዊቱም እነሱን እንደተቀበሉትና በቁጥጥር ስር እንዳሉ ይታወቃል። ከዚህ የበለጠ ኢትዮጵያ ውስጥ የጎላ የጸጥታ ችግር እንደሌለ መገንዘብ ያስፈልጋል።

ጥያቄ፡- በአገሪቱ አብዛኛው ክፍል የተነሱ ችግሮች ምክንያታቸው አንድም ሚዲያው በደንብ ባለመስራቱ ነው የሚል አስተያየት አለ። እርስዎ ወደዚህ ቦታ ከመምጣትዎ በፊትም በተደጋጋሚ በሚያቀርቧቸው ጥናታዊ ጽሁፎችዎ ላይ ሚዲያው ጠንካራ ስራ እየሰራ አይደለም ሲሉ ነበር። አሁን ይህን ቦታ ከያዙ በኋላ ሚዲያውን የሚያነቃቃ አሰራር ይዘረጋሉ ብለን ተስፋ እናድርግ?

መልስ፡- ሚዲያን በተመለከተ የምነነጋገረው ስለናንተ ነው (የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎችን) በአገራችን ዴሞክራሲ እንደሚታወቀው ምናልባት የሁለት አስርት ዓመታት (ኢህአዴግ ስልጣን ከያዘበት ጊዜ ጀምሮ ለማለት ነው) እድሜ ያለው ነው። ይህ የዴሞክራሲ ሂደትም ገና በግንባታ ላይ ያለ ነው ማለት እንችላለን። ከ240 ዓመታት በላይ እንዳስቆጠሩት እንደ አሜሪካ እና ህንድ ዴሞክራሲ እንዲሁም እንደሌሎችም አገራት መቁጠር እንደማንችል እናውቃለን። ነገር ግን ደግሞ በ21ኛው ክፍለ ዘመን ተቀምጠን ግዴታ ሌሎች ያስቆጠሩትን ዓመት ማሰቆጠር አለብን ማለት አይደለም። ስለዚህ የምንፈልገው ጠንካራ ዴሞክራሲ ህዝባችን በአጠቃላይ የሚረኩበት ዴሞክራሲ እንዲገነባ የሚዲያ ሚና ትልቅ እንደሆነ በህገ መንግስቱ ውስጥ በትክክል ተቀምጦ ይገኛል። እንዲሁም ደግሞ ሚዲያን በተመለከተ ደንቦች እና ህጎች እንደተደነገገ እናውቃለን። ይሁን እንጂ ተግባሩን በተመለከተ ብዙ ተግዳሮቶች እንዳሉት እናውቃለን፡፡ ነገር ግን በሚጠበቀው ደረጃ ሚዲያው ኃላፊነቱንም እንዲሁም ተጠያቂነቱንም አውቆ ትክክለኛ አጥጋቢ ስራ እየሰራ ነው ማለት እንደማይቻል ይታወቃል። ያው እንደጠቀስከው የጥናታችን ውጤት እንደሚያሳየው በጎ ጅምር እንዳለ እናውቃለን፡፡ ልማት እንዲበረታታ ወይም ደግሞ ሰዎች በልማቱ እንዲሳተፉ ሚዲያ የሚሰራበት ሁኔታ እንዳለ ሆኖ የዴሞክራሲ ግንባታ እና የመልካም አስተዳደር በተለይም ደግሞ የተጠያቂነት አሰራር እንዲኖር ማድረግ ላይ ክፍተቶች አሉ። ይህ እንግዲህ ከአሁን በኋላ በዚህ ሁኔታ መቀጠል አለበት ወይ ለሚለው መቀጠል እንደሌለበት ነው የምናየው። ይህንን ለማስተካከል ደግሞ አሰራር ወሳኝ ስለሆነ አሰራሩን በመፈተሽ እንዲስተካከሉ የምንሰራበት ሁኔታ ይኖራል። እንዲሁ የስጋት ድባብ እንዳለ በማየት ጋዜጠኞች ስራቸውን በአግባቡ እንዳይሰሩ የሚያደርጓቸውን በትክክል በመፈተሽ፣ እያንዳንዱ ዜጋ ዴሞክራሲ እንደሚፈልገው በእኩልነት እንዲንቀሳቀሱ ለማድረግ ጥረቶች ይደረጋሉ ማለት ነው። ስለዚህ በመንግስት በኩል የሚሰሩ ስራዎች እንደተጠበቁ ሆኖ በሚዲያ ተቋማት ውስጥ በተሳተፉት በተለይም ደግሞ በጋዜጠኞችና በኃላፊዎች የሚሰሩ ስራዎችም ይኖራሉ ማለት ነው።   

ሌላው ሚዲያ የተሻለ ሆኖ በትክክል የሚፈለገውን የዴሞክራሲ ስርዓት እንዲገነባ የሚያደርገው የመረጃ ፍሰቱ እንደሚፈለገው ሲሆን በመሆኑ የዚህ ጽ/ቤት አንዱ ስራውም ደግሞ መረጃን በትክክል የሚገኝበት ሁኔታ ማመቻቸት ስለሆነ በዚህ ላይም የሚሰሩ ስራዎች ይኖራሉ። ያንን በሂደት የምናየው ይሆናል። ነገር ግን ሁላችንም መረዳት ያለብን አሁን በነበረበትና ባለንበት ወይም ደግሞ በምንሰራበት ሁኔታ በመቀጠል ዛሬ ላይ ዜጎቻችን የሚያነሱትን ጥያቄ መመለስ እንችላለን ብለን ማሰብ የለብንም። ኃላፊነቱ በሚዲያ ባለሙያዎችም በጋዜጠኞችም ላይ እንዳለ ጠንቅቀን በማወቅ ራሳችንን መጠየቅ አስፈላጊ ይሆናል ብዬ ነው የማምነው።

ጥያቄ፡- ከአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ጋር በተያያዘ በህትመት ላይ የሚሰሩ የግል መገናኛ ብዙሃን ተቋማት (ለምሳሌ አዲስ ስታንዳርድ) ለመዝጋት እንደተገደዱ ገልጸዋልና ይህስ መንግስትን ምን ያህል ያነቃዋል?

መልስ፡- በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ምክንያት ስራችንን ለማቆም ተገድደናል የሚሉ እኔ እዚህ እስከመጣሁ (የኮምዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት ኃላፊ ሚኒስትር ሆነው ከተመደቡ በኋላ) የቀረበልኝ ጥያቄ የለም። ወይም ደግሞ እንደዚህ አይነት ችግር ውስጥ ገብተናል የሚሉም የሉም። ምናልባት እንደዚህ አይነት ስጋት ውስጥ የገቡ የግል ሚዲያ ተቋማት ካሉ ምክንያቱን በትክክል ይዘው መቅረብ ይችላሉ። በመርህ ደረጃ እንደምናውቀው ግን ነጻ ሚዲያ ለዴሞክራሲ ግንባታ ወሳኝ ሚና ስለሚጫወቱ በግል የተያዙ ሚዲያዎችም ተጠያቂነታቸውን እና ኃላፊነታቸውን አውቀው የዜጎቻችንን ፍላጎት በትክክል እስካገለገሉ ድረስ እነሱን መደገፍ ነው እንጂ የሚዘጉበት ምክንያት እንደሌለ ነው የሚታየኝ።

ጥያቄ፡- በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ምክንያት በቁጥጥር ስር የዋሉ ሰዎች መረጃ ይሰጣል ቢባልም ከህብረተሰቡ የሚነሳው ቅሬታ ግን የተነገረው ቃል እየተተገበረ አይደለም፡፡ ቃል የተገባውና እየሆነ ያለው ፍጹም ተቃራኒ ነው ይባላል። በዚህ ጉዳይ ላይ የሚሰጡት ምላሽ ምንድን ነው?

መልስ፡- ከአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ጋር በተያያዘ በቁጥጥር ስር የዋሉ ሰዎች በተመለከተ መረጃ በትክክል አይገለጽም የሚል ጥያቄ እንዳለ ነው የተነሳው። ይህንን በተመለከተ ኮማንድ ፖስቱ በየጊዜው ማብራሪያ ይሰጣል። በሌላ በኩል ደግሞ ፓርላማው መርማሪ ቦርድ ወክሏል፡፡ ሌሎች ሲቪክ ማህበራትና የህግ አካላትም ተሳታፊ ሆነው ባላቸው የመረጃ መረብ ተጠቅመው የህግ የበላይነት በትክክል ስራ ላይ እንዲውል ይደረጋል ማለት ነው። በተመሳሳይ ሁኔታ ከኮማንድ ፖስቱ የሚወጡ መረጃዎች እንዳሉ ሆኖ ከሌላ የመረጃ ምንጭም በየጊዜው መረጃ የሚገኝበት ሁኔታ እንዲመቻች በእኛ በኩል (ኮምዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት) የምንችለውን ሁሉ እናደርጋለን ማለት ነው። ስለዚህ የሚወሰዱ እርምጃዎች በትክክል ለህዝብ መገለጽ ግዴታ እንደሆነ አስቀምጧል። በዚያ መሰረት የሚሰራበት ሁኔታ እንዳለ ነው የምገልጸው።

ጥያቄ፡- የሞባይል ኢንተርኔት በአንዳንድ የአገራችን ክፍሎች መጠቀም የሚያስችል ሲሆን በሌሎቹ ደግሞ ተገድቧል። ቅድም እርስዎ እንደገለጹትም ሆነ በዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብት ኮሚሽን እንደተረጋገጠው ዜጎች መረጃ የማግኘት መብት አላቸው። ዜጎች ከማህበራዊ ሚዲያ መረጃ እንደሚያገኙ ይታወቃልና በአገራችን እገዳ የተጣለበት የሞባይል ኢንተርኔት አገልግሎት እስከመቼ ይቆያል?

መልስ፡- የሞባይል ኢንተርኔትን በተመለከተ እንደሚታወቀው ኢንተርኔት አልተዘጋም። መረጃ ነጻነት ላይ ገደብ ተጥሏል ተብሎ በተለያዩ ዓለም አቀፍ ተቋማት የሚናፈሱ አሉባልታዎች አሉ። እንደሚታወቀው ከማህበራዊ ሚዲያ ጋር በተያየዘ የሞባይል ኢንተርኔት ቴክኒካሊም ይሁን ከእሱ ጋር የተያያዘ የተደረገው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ አካል እንደሆነ መገንዘብ ያስፈልጋል። የትኛውም ሚዲያ ለዜጎች የሚጠቅም መሆን አለበት። መንግስት ለዜጎች ጥቅም ለአገሪቷ ዕድገት ብሎ ነው ያመጣው። ነገር ግን የዜጎች ጥቅም በሚጎዳበት ጊዜ ደግሞ በየጊዜው የሚወሰዱ እርምጃዎች ይኖራሉ፡፡ ለዚህም ነው የማህበራዊ ሚዲያ የተቋረጠው። ይህም በሂደት ታይቶ የሞባይል ዳታ ላይም አስፈላጊው እርምጃ ይወሰዳል ማለት ነው።

ጥያቄ፡- ባለፈው ዓመት ብቻ 90 ሺህ የሚሆኑ ኢትዮጵያዊያን ባልተመቻቸ ሁኔታ ራሳቸውን ለአደጋ አጋልጠው ለስደት ተዳርገዋል የሚል መረጃ ወጥቷል። ይህ ደግሞ የአገሪቱ ዜጎች ያሉበትን ደረጃ ያሳያል፡፡ ይባላል ምክንያቱም ዘጎቻችን እየተሰደዱ ያሉት እንደ የመን እና ሊቢያ ያሉ ጦርነት ባለባቸው ቀጠናዎች ነውና። በሌላ በኩል ደግሞ አስቸኳይ ጊዜ አዋጁ መታወጁንና የተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች መታሰራቸውን ተከትሎ አገሪቱ ፍጹም ነጻነት የሌላት አገር ናት የሚሉ መረጃዎችም ወጥተዋል። ይህን በተመለከተ መንግስት የሚሰጠው ምላሽ ምንድን ነው?

መልስ፡- ዛሬ ላይ ያሉት የመረጃ ምንጮች እንደምናውቀው አንዳንዶቹ እንደክረምት ውሀ የደፈረሱ መሆናቸውን መረዳት ያስፈልገናል። ስለዚህ የምንሰማቸውን መረጃዎች በሙሉ መሰረተ አላቸው ብለን መውሰድ የለብንም፤ ማጣራትና መምረጥ ይኖርብናል። ኢትዮጵያ ፍጹም ነጻነት የሌለባት አገር ናት ብለው የሚያናፍሱ የአገር ውስጥም ይሁኑ የተለያዩ ተቋማት በመጀመሪያ ደረጃ መረጃውን የሚያገኙት እንዴት ነው ብሎ ማጣራት ያስፈልጋል። ወይ የራሳቸው አጀንዳ ይዘው አገራችን ከዚህ በፊት የነበራትን ገጽታ ይዛ እንዳትቀጥል የፈለጉ ይመስላል። ነገር ግን ምንም ችግር የለም ብለንም መደምደም የለብንም። ምክንያቱም በዴሞክራሲ ባደጉት አገራትም ችግሮች በየጊዜው እንደሚፈጠሩ እናውቃለን። ስለዚህ የሚፈጠረውን ችግር የምንይዝበት እና የምናስተካክልበት ሁኔታ ነው መታየት ያለበት። አገሪቱ ፍጹም ነጻነት የሌለባት አገር ናት የሚለው ግን ፍጹም ውሸት መሆኑን መታወቅ ይገባል።

ከስደት ጋር የተነሳው በተለያዩ ጊዜያት ስደት በአፍሪካ እንዲሁም በሌሎችም አገራት ወደ አውሮፓ እና ሌሎች አገራት እንደ አሜሪካ ባሉ ሀገራት ለመሸጋገር ብዙ ጥረት ያደርጋሉ። በዚህ መካከልም ብዙ ጉዳት እንደሚደርስባቸው እናውቃለን። ነገር ግን ይህንን ችግር ካለው አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ጋር በማያያዝ ነጻነት የለም፣ ለዚህ ነው የሚሰደዱት የሚሉ ካሉ ይህ ስህተት እንደሆነ መግለጽ እፈልጋለሁ። እንደሚታወቀው የተሻለ ህይወት ፍለጋ በሰላምም ሆነ በሚያገኙት መንገድ የሚሄዱበት ሁኔታ አለ፤ ከየትኛውም የአፍሪካ አገራት። ኢትዮጵያ በስደት ዙሪያ የምታደርገው እያንዳንዱ ዜጋ በአገሩ ዜጋ ሰርቶ ማደግ እንደሚችልና የተሻለ ህይወት መኖር እንደሚችል የግንዛቤ ስራ መስራት ነው።¾

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
454 ጊዜ ተነበዋል

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us