በሰብዓዊ መብት የድርጊት መርሃ ግብር የተቀናቃኝ ፓርቲዎች ዕይታ

Wednesday, 14 December 2016 14:12

በይርጋ አበበ

ከ60 በላይ ህብረ ብሔራዊና ክልላዊ የፖለቲካ ፓርቲዎች ከ1983 ዓ.ም ጀምሮ አገሪቱን ከሚመራው የኢህአዴግ መንግስት ጋር ውይይት አካሂደው ነበር። የፓርቲዎቹ ውይይት ትኩረቱ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ባጸደቀውና በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ይጸድቃል ተብሎ በሚጠበቀው “ሁለተኛው የኢትዮጵያ ብሔራዊ የሰብአዊ መብት የድርጊት መርሐ- ግብር” አፈጻጸም ዙሪያ ነው።  

በመንግስት ግብዣ ከተደረገላቸው የአገሪቱ ተቃዋሚ ፓርቲዎች መካከል ሰማያዊ እና መኢአድ ስለ ውይይቱ አስተያየታቸውን ለሰንደቅ ጋዜጣ ሰጥተዋል። የሰማያዊ ፓርቲ የወጣቶች ጉዳይ ኃላፊ አቶ አንተነህ ተስፋዬ እና የመኢአድ ዋና ፀሀፊ አቶ አዳነ ጥላሁን ውይይቱን አስመልክቶ ለሰንደቅ ጋዜጣ የሰጧቸውን ማብራሪያዎች አቅርበነዋል።

 

 

ሰንደቅ:-በቅርቡ መንግስት ከተቃዋሚ ፓርቲዎቸ ጋር በሁለተኛው የብሔራዊ የሰብአዊ መብት የድርጊት መርሃ ግብር አፈጻጸም ዙሪያ ውይይት አድርጓል፡፡ ውይይቱን እንዴት አገኛችሁት የውይይቱን አስፈላጊነትስ እንዴት ገመገማችሁት?

አቶ አንተነህ:-እኛ (ሰማያዊ ፓርቲን ማለታቸው ነው) ውይይቱን ያየንበት መንገድ የሰብአዊ መብት መርሃ ግብሩ የአምስት ዓመት መርሃ ግብር ማለትም ከ2008 እስከ 2012 የሚተገበር ነው። አሁን ያለነው ደግሞ 2009 ዓ.ም ሶስተኛው ወር ተጠናቆ ወደ አራተኛው ወር እየገባን ባለንበት ሰዓት ነው ውይይቱ የተካሄደው። ይህ ማለት ደግሞ መርሃ ግብሩ መተግበር ከጀመረ ከአንድ ዓመት ከሩብ ሆኖታል ማለት ነው። ስለዚህ የእኛ ለውይይት መጋበዝ ለውጥ ያመጣል ወይም ግብአት ይሆናል ብለን አምነን አይደለም ወደ ውይይቱ የገባነው። ሆኖም እናንተ (ተቃዋሚ ፓርቲዎችን ለማለት ነው) ሁልጊዜ የውይይት እና የመፍትሔ አካል አትሆኑም፣ ሁልጊዜ መንቀፍ ብቻ ነው እየተባልን ከመንግስት የሚቀርብብን አስተያየት ስላለ ጥሪ ከቀረበልን በውይይቱ የምናነሳቸው አስተያየቶች ለውጥ አመጣም፣ አላመጣም የራሳችንን ሀሳብ መስጠት አለብን ብለን ነው ወደ ውይይት የገባነው። ነገር ግን የህዝብ ፓርቲ እስከሆንን ድረስ በቦታው ተገኝተን የህዝብን ስሜት ማንጸባረቅ አለብን ብለን ነው የሄድነው። ውይይቱ እንግዲህ ይጠቅማል፣ አይጠቅምም የሚለውን እነሱ ናቸው (መንግስትን) የሚወስኑት። ሰነዱን ያዘጋጀው የመንግስት አካል ስለሆነ የእኛን አስተያየት ወስደው እንደ ግብአት ተጠቅመው ለውጥ ሲያመጡ ነው ይጠቅማል፣ አይጠቅምም የሚለውን መረዳት የምንችለው።

ሰንደቅ:-ለውይይት ስትቀርቡ በመንግስት የተዘጋጀውን የመርሃ ግብር አፈጻጸም ሰነድ ገምግማችሁታል ብለን እናምናለን። በግምገማችሁ ሰነዱ ላይ ያገኛቸሁት ውጤት ምንድን ነው?

አቶ አንተነህ:- ልክ ነህ ሰነዱን አይተነዋል። የድርጊት መርሃ ግብሩ ሰነድ በጣም ሰፊ ጉዳዮችን የዳሰሰ ነው። ነገር ግን እሱ ጥቅም ላይ ሊውል የሚችለው መጀመሪያ የሚደረገው ዳሰሳ ችግር ለመፍታት እስከሆነ ድረስ ችግሩን መረዳት አለበት። በሰነዱ ላይ ያየነው አንዱ ችግር ያደረጉት ዳሰሳ መሰረታዊ ነገሮች ላይ ማውጣት አልተፈለገም ወይም ደግሞ መረዳት አልቻሉም ማለት ነው። ምክንያቱም ሰነዱን አይተኸው ከሆነ የመጀመሪያውን መርሃ ግብር አፈጻጸምን ገምግመው (ኢቫሉዬት አድርገው) ያስቀመጡት ችግሩን አምኖ ለመቀበል ቁርጠኝነት የጎደላቸው መሆኑን ነው ያየነው።

ሰንደቅ:-ያልተዳሰሱት መሰረታዊ ችግሮች ተብለው በእናንተ በኩል የቀረቡት የትኞቹ ናቸው?

አቶ አንተነህ:-በመጀመሪያ ደረጃ ችግር እንዳለበት መንግስት የሚቀርቡበትን ችግሮች አምኖ መቀበል ይኖርበታል። እኛም ያቀረብነው ሃሳብ የተፈጠሩ ችግሮችን ለመፍታት መንግስት ችግሮቹን አምኖ መቀበልና ወደ መፍትሔ መሄድ አለበት ብለን ነው የገለጽነው። ለምሳሌ በህይወት የመኖር መብት የሚለው ላይ እንደ እኛ እይታ በቅርቡ በተፈጠሩ ችግሮች ላይ እንኳ የብዙ ዜጎች ህይወት ጠፍቷል። ህይወታቸው ከጠፉ ዜጎች መካከል በመንግስት የጸጥታ ሀይሎች የተገደሉት ቁጥራቸው ብዙ ነው። እንደ ሰብአዊ መብት የድርጊት መርሃ ግብር መንግስት ይዞ ሲነሳ ያንን ማጣራት ነበረበት። ያንን ያህል ሰው በመንግስት የጸጥታ ሀይል ሲገደል የሰዎችን በህይወት የመኖር መብት ነጥቋል ማለት ነው። ከዚህ በተጨማሪ በተለያዩ ጊዜዎችና አካባቢዎች በመንግስት ላይ በሚነሱ ታቃውሞዎች ምክንያት በሚፈጠር ግጭት የብዙ ሰዎች ህይወት አልፏል። ያንን አጣርቶ ተጠያቂ የሚሆኑ የመንግስት አካላትን ለፍርድ የሚቀርቡበትን ሁኔታ መካተት ነበረበት።

ከዚህ በተጨማሪ ደግሞ በብሔር ግጭት ምክንያት የሚሞቱ ሰዎችን በተመለከተ በሰላማዊ መንገድ እንዲፈቱ ባህላዊ የእርቅ ስርዓቶች እንዲጠናከሩ የሚል ድርጊት አስቀምጠዋል። ድርጊት ሲቀመጥ ደግሞ የውጤት አመላካች አብሮ ይቀመጣል። እሱ ላይ የተቀመጠው ውጤት አመላካች ላይ አጥፊዎች በህግ እንዲጠየቁ ይደረጋል ይላል። በሰላማዊ መንገድ በእርቅ እንዲፈቱ ከተባለ በህግ እንዲጠየቅ የሚል ነገር ማስቀመጥ አልነበረበትም።

ሌላው በእኛ በኩል የቀረበው ሀሳብ በብሔር ምክንያት ግጭቶች ተፈጥረዋል። በተፈጠረው ግጭት የተነሳም ህይወት ጠፍቷል። ያንን ችግር እንዲፈጠር ያደረገውን ምክንያት አጣርቶ የችግሩን ምንጭ ማወቅ ነበረበት። እንዲያውም ያለን የፌዴራል ስርዓት (ዘውጌ ፌዴራሊዝም) ለዚያ ግጭት ያበረከተውን አስተዋጽኦ ማጥናት ያስፈልጋል። በድርጊት መርሃ ግብሩ ላይ ይህ መካተት ነበረበት።

ሰንደቅ:-በሰነዱ መገቢያ ላይ ከ1983 ዓ.ም በኋላ በህዝብ ፈቃድ የተመሰረተው መንግስት የዜጎችን ሰብአዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች ለማረጋገጥ ዴሞከራሲን ማስፈን እና ልማትን ማረጋገጥ በኢትዮጵያ ነባራዊ ሁኔታ የሃገራዊ ህልውና ጉዳይ እንደሆነ በጽኑ በማመን ያልተቆጠበ ጥረት ሲያደርግ ቆይቷል ይላል። እናንተ ደግሞ የተነሱ ግጭቶችን አንስታችኋል። መንግስት እንደሚለው ያንን ያህል ጥረት ካደረገ መሬት ላይ የሚታየው ግጭት እንዴት ተፈጠረ ብላችሁ ጠይቃችኋል?

አቶ አንተነህ:- የድርጊት መርሃ ግብሩን ሰነድ ካየህ ችግሮቹ መኖሩን አለማመን ነው ያለው። እንዲያውም የመጀመሪያው የድርጊት መርሃ ግብር ሙሉ በሙሉ መሳካቱን ብቻ ነው የገለጸው። ስለዚህ የሚታየውም ችግሮቹን በመካድ የተሞላ ሰነድ ነው። ለምሳሌ የመምረጥና የመመረጥ መብትን ሲገልጽ ምርጫ ቦርድን ገለልተኛ እንደሆነ አድርጎ ነው የሚቆጥረው። ነገር ግን እንደሚታወቀው ምርጫ ቦርድ ገለልተኛ እና ነጻ አይደለም። በሁሉም ችግሮች ላይ የሚሰጠው ችግሩን ክዶ ስኬቱን ብቻ መግለጽ ነው። በነገራችን ላይ ይህ ሰነድ ከመጀመሪያውም አያስፈልግም። ምክንያቱም መግቢያው ላይ የተቀመጠው ማብራሪያ እውነት ቢሆን አስፈጻሚው አካል ስራውን በአግባቡ የሚሰራ ቢሆን የድርጊት መርሃ ግብር ለምን ያስፈልጋል። የልማት መብት የመምረጥና የመመረጥ መብት ሀሳብን በነጻ የመግለጽ መብት ቢከበር እኮ በሰነድ አዘጋጅቶ ማቅረብ አስፈላጊም አይሆንም። የህግ ችግሮች ቢኖሩም እንኳ የአፈጻጸም ችግር ባይኖርና አስፈጻሚዎችም በሙስና የተጨማለቁ ባይሆኑ ከመሪዎች ጀምሮ ቁርጠኝነቱ ቢኖራቸው ለውጥ ያመጣ ነበር

ሰንደቅ:-በመጀመሪያው የድርጊት መርሃ ግብር ድክመቶች ተብለው ከቀረቡት መካከል የሰነዱ እንግሊዝኛ ትርጉም ተጠናቆ ለህትመት አለመቅረብ እና የህዝብ ግንኙነት ስራው ዝቅተኛ መሆን የሚሉት ይገኙበታል። በሌላ በኩል ደግሞ እናንተ (ተቃዋሚ ፓርቲወች) ለውይይት የተጋበዛችሁት ለግብአት መሆኑ ተገልጿል። የመጀመሪያው ሰነድ ከትርጉምና ከህዝብ ግንኙነት ስራ ድክመት በዘለለ ሙሉ በሙሉ በስኬት ከተጠናቀቀ የእናንተ ግብአት ምናልባት ለትርጉም ስራ እና ለህዝብ ግንኙነት ተልዕኮ ነው ማለት ነው?

አቶ አንተነህ:- አንተ ያነሳኸው የሰነዱ እንግሊዝኛ ትርጉም ተጠናቆ አለመቅረብ የሚለው ነገር እንደ ድክመት መቅረቡ በአንድ በኩል አስቂኝም ነው፤ በሌላ በኩል ደግሞ አሳዛኝ ነው። ዝም ብሎ ድክመት መግለጽ ስላለበት ብቻ የተጻፈ ነው። በመጀመሪያ ደረጃ የእኛ የስራ ቋንቋ እንግሊዝኛ ሳይሆን አማርኛ ነው። እንደነገርኩህ እኛ የተጠራነው እንደተለመደው “ተቃዋሚዎችን አወያይቻለሁ” ለማለት ይመስለኛል። እኛ ግን ቅድም እንደነገርኩህ የመፍትሔ እና የውይይት አካል አትሆኑም የሚለውን ለማስቀረት ነው ገብተን ሀሳባችንን ያንጸባረቅነው። ለምሳሌ አመለካከትን እና ሃሳብን የመግለጽ መብትን በተመለከተ ነጻ ሚዲያን የማስፋፋት የሚል አንድም ቦታ አልተገለጸም። እንደ አገር ስናየው አንዱ ትልቁ ችግራችን ዜጎች ሃሳባቸውን በነጻ የሚገልጹበትና የመንግስትን ድክመቶች የሚያሳውቅ ሚዲያ አለመኖር ነው። መንግስት ከልቡ መሻሻል ከፈለገ የነጻውን ሚዲያ ማስፋፋት ይኖርታል። የግሉ ፕሬስ ከገበያ የወጡበት ምክንያት ምንድን ነው የሚለውን ማጣራት አንዱ የዴሞክራሲ መገለጫ ነው፡፡ ይህንን ግን ለማድረግ መንግስት ድፍረቱ ያለውም አይመስልም።

ሰንደቅ:-እናንተ ያቀረባችኋቸውን ሃሳቦች ሰምተው የመንግስት ተወካዮች የሰጧችሁ ምላሽ ምንድን ነው?

አቶ አንተነህ:- እንደነገርኩህ ብዙ አስተያየት ነው ያቀረበነው። ለምሳሌ በመጨረሻው የሰነዱ ክፍል ለመብት ጥሰት ተጋላጭ የሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎች መብቶች በሚለው ላይ አገራችን ውስጥ ምን ያህል ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች እና የነጻው ሚዲያ ሰዎች እንደሚታሰሩ እናውቃለን። እነዚህ አካላትም በጸጥታ ሀይሎች እና አስፈጻሚ አካላት ትልቅ የመብት ጥሰት የሚካሄድባቸው ሰለሆኑ “ለመብት ጥሰት ተጋላጭ የሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎች” ከሚለው እንዲመደቡ ሃሳብ አንስተን ነበር። ለሁሉም ጥያቄዎች መልስ ባይሰጠንም ለዚህች ጥያቄ በፓርላማ የመንግስት ተጠሪ ሚኒስትር የሆኑት አቶ አስመላሽ ወልደስላሴ “የፖለቲካ ፓርቲዎች እነዚህ አካላት (የፖለቲካ ፓርቲዎችና የነጻው ሚዲያ ጋዜጠኞች ለመብት ጥሰት ተጋላጭ የሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎች ከሚለው ምድብ) ይጨመሩ ብለዋል፡፡ እኛ ግን እንደ ፖለቲካ ፓርቲ እንጂ በሌላ መልኩ አናየውም” ብለው የመለሱልን ብቸኛ መልስ ነው። ከዚህ ውጭ ለየትኛውም ጥያቄዎቻቸንና ሀሳቦቻቸን የተሰጠ መልስ የለም።

ሰንደቅ:-ቀደም ሲል ምርጫ ቦርድ ነጻና ገለልተኛ አይደለም ሲሉ ገልጸውልኛል። በዚህ የፓርላማ ዘመንም ከገዥው ፓርቲ አባላት ውጭ በፓርላማው አልተገኘም። አሁን ደግሞ በተለያዩ ጉዳዮች ዙሪያ እናንተን በፓርላማ እየጠራ የሚያደርገውን ውይይት መንግስትና ምርጫ ቦርድ የቤት ስራቸውን በአግባቡ መስራት ባለመቻላቸው ችግር ሲፈጠር የተወሰደ እሳት የማጥፋት ስራ ነው ሲሉ ይገልጹታል። እርስዎ በዚህ ሀሳብ ላይ ያልዎ ምላሽ ምንድን ነው?

አቶ አንተነህ:- የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ዓላማው የተለያዩ የህዝብን አስተያየት የሚያንጸባርቁ ሃሳቦች ይንሸራሸሩበረታል የሚል ነው። ያ ከሆነ ደግሞ እንደ መርህ ካየኸው የፓርላማ አባል ያልሆኑ የተቃዋሚ ፓርቲዎችን እየጠራ ማወያየት አግባብ አይደለም። ምክንያቱም ህዝብን የሚወክሉ ተመራጮች አሉኝ የሚል ቢሆን ኖሮ እኛን በህዝብ አልተወከላችሁም የሚለንን ጠርቶ ማወያየት ባላስፈለገው ነበር። ነገር ግን እራሳቸውም የሚያውቁት እውነታ አለ “ፓርላማው ህዝብን የሚወክል አይደለም”። ምክንያቱም ነጻና ፍትሃዊ ምርጫ ተደርጎ ህዝቡ ይወክሉኛል የሚላቸውን አካላት የመረጣቸው አይደለም፡፡ ፓርላማ ውስጥ የተገኙት። ስለዚህ መንግስት የህዝቡን ፍላጎት የሚወክሉ አባላትን አያገኝም እንደገና ለሚያወጣቸው ህጎችን የህዝቡን ስሜት የጠበቀ ሳይሆን በህዝቡ ላይ የሚጫን እንደሆነ መንግስት አምኖ የተቀበለበት ውሳኔ ነው (ተቃዋሚዎችን በፓርላማ ጠርቶ ማነጋገሩን) ብለን የተቀበልነው። ይህን አምኖ መቀበሉ ጥሩ ነው።

     

***          ***          ***

አቶ አዳነ ጥላሁን

የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት (መኢአድ) ዋና ፀሀፊ

ሰንደቅ:-በቅርቡ መንግስት ከተቃዋሚ ፓርቲዎቸ ጋር በሁለተኛወ የብሔራዊ የሰብአዊ መብት የድርጊት መርሃ ግብር አፈጻጸም ዙሪያ ውይይት አድርጓል ውይይቱን እንዴት አገኛችሁት የውይይቱን አስፈላጊነትስ እንዴት ገመገማችሁት?

አቶ አዳነ:- ወይይቱ እነሱ እንዳሉት 62 ፓርቲዎች የተሳተፉበት በመሆኑ እንደ ውይይት ጥሩ ነው ማለት ይቻላል። ከዚያ ውጭ ግን በወይይቱ የተነገሩና ኢህአዴግ ሊያንጸባርቃቸው የፈለጉ ጉዳዮች ላይ ያራሳችን ጥርጣሬዎች አሉ። ቢሆንም ኢህአዴግ መፍትሔ ወስዶ ከተቃዋሚዎች ጋር መወያየቱ እንደ ትልቅ ነገር ሊታየለት ይችላል።

ሰንደቅ:- ኢህአዴግ ሊያንጸባርቃቸው የፈለጉ ጉዳዮች ላይ የራሳችን ጥርጣሬ አለን ሲሉ በየትኞቹ ነጥቦች ላይ የተጠራጠራችሁት?

አቶ አዳነ:-የሚገርመው ነገር ኢህአዴግ ብዙ ነጥቦችን ያነሳል። ለምሳሌ የመጀመሪያውን የሰብአዊ መብት ድርጊት አፈጻጸም ላይ በድክመት ያስቀመጡት ሰነዱን በእንግሊዝኛ ተተርጉሞ አለመቅረቡ ነው ይላሉ። ይህ በእውነት ህዝብንና አገርን መናቅ ነው በጣም የሚያሳዝን ነው። ምክንያቱም በዚህች አገር ቤቶች ፈርሰዋል፣ ዜጎች ሞተዋል፣ ተፈናቅለዋል፣ ያላግባብ ታስረዋል። ከዚህ የዘለለ በደልም ተከናውኗል። ኢህአዴግ ግን መንግስት ቢሆንም ሌሎቹን ችግሮችና በደሎች ሁሉ ትቶ ይህችን በእንግሊዝኛ ተተርጉሞ አለመቅረብን እንደችግር ነቅሶ ማውጣቱ በጣም የሚያሳዝን ሆኖ ነው ያገኘሁት።

ሰንደቅ:- መኢአድ በውይይት ላይ እንደ ፓርቲ በየትኞቹ ጉዳዮች ላይ ጥያቄ አቀረበ?

አቶ አዳነ:- በብዙ ጉዳዮች ላይ ነው ጥያቄ ያቀረብነው። ለምሳሌ በትምህርት ጉዳይ፣ የመኖሪያ ቤት የማግኘት መብት፣ በትምህርት ጥራት ዙሪያ ጥያቄዎችን አንስተናል። ነገር ግን ሁሉንም ኢህአዴግ በሚፈልጋቸው መስመር እና እሱ ባሰባቸው መንገዶች ዙሪያ እንጂ ከሌሎች አካላት የሚነሱ ሀሳቦችን የሚዳስስ አልሆነም። በአጠቃላይ ስመለከተው ግን ውይይቱ ከልብ የታመነበት አይደለም።

ሰንደቅ:- ቀደም ሲል ውይይቱ ጥሩ ነበር ብለውኝ ነበር እኮ…….

አቶ አዳነ:- ልክ ነህ፤ እኔ ጥሩ ነበር ያልኩህ በመርህ ደረጃ ያለውን ነው። ምክንያቱም ተቃዋሚ ማለት ለኢህአዴግ እንደ ጠላት ነው የሚታየው ተቃዋሚ ማለት ሁልጊዜ ጸረ ሰላም ጸረ ልማት ነው። ነገር ግን ነብስ ገዝተው በውይይት ደረጃ ለመወያየት መፈለጋቸውን ስመለከት ከእነሱ ተፈጥሯዊ ባህሪ አኳያ አንድ ትልቅ ለውጥ ነው ለማለት ነው። ከዚያ ውጭ ግን ያቀረቡትን ስታየው እነሱ የሚፈልጉትን ብቻ እንድንሰማ እንጂ ተጨባጭ የሆነውን ሁኔታ ያገናዘበ አይደለም ነው ያልኩት።

ሰንደቅ:- በተለያዩ ጉዳዮች ዙሪያ እናንተን በፓርላማ ቀርባችሁ እንድታደረጉ መጋበዙ መንግስትና ምርጫ ቦርድ የቤት ስራቸውን በአግባቡ መስራት ባለመቻላቸው ችግር ሲፈጠር የተወሰደ እሳት የማጥፋት ስራ ነው ሲሉ ይገልጹታል። ምክንያቱም የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ተወያይተው ውሳኔ ማሳለፍ ሲገባቸው እናንተ ፓርላማ ያልገባችሁ ፓርቲዎች መጋበዝ አልነበረባቸሁም ይባላል። እርስዎ በዚህ ሀሳብ ላይ ያለዎት ምላሽ ምንድን ነው?

አቶ አዳነ:- እኔም የምመለከተው በዚህ መልኩ ነው። ይገርምሃል ውይይቱም ሆነ የጋራ ምክር ቤት የሚባለው ነገር ኢህአዴግ በፈለገው ሰዓት ከኪሱ እየዘገነ ዴሞክራሲን የሚያድለው ለማድረግ ከመፈለጉ ውጭ እነሱም እኛም በፖሊሲ ደረጃ ያለንን ልዩነት ወደ ማጥበብና ወደ መፍትሔ ባልመጣንበት ሁኔታ፤ ከዚያም አልፎ ተርፎ ሊያስማሙ በሚችሉባቸው ነጥቦች ባልተስማማንበት ደረጃ እነሱ ባረቀቁትና ባጸደቁት ሰነድ ብቻ በየሶስት ወሩ ስንጠራችሁ ትመጣላችሁ የሚል ነገር ነው የሰጡን። ኢህአዴግ ያለበትን ከፍተኛ የሆነ የህዝብ ጥላቻ በእኛ መሰላል ለመወጣጫ ተጠቅሞ ስልጣኑን ለማስጠበቅ የተጠቀመበት ስራ ነው። እነሱ እየፈለጉ ያሉት እነሱ ቆጥረው በሰጡን መድረክ እየገባን አጨብጫቢ ሆነን እንድንለይ የመፈለግ ባህሪ ሆኖ ነው ያየሁት። ይህንንም አቶ አማኑኤል አብርሃ የተባሉ የመንግስት ተወካይ በውይይቱ ላይ ገልጸውልናል።

ሰንደቅ:- በየሶስት ወሩ ስንጠራችሁ እየመጣችሁ እንወያያለን ተብለናል ሲሉ ገልጸውልኛል። ይህ አባባል በፓርቲያችሁ ላየ የሚያሳድረው አንደምታ ምንድነው?

አቶ አዳነ:- ይህ አባባል በመጀመሪያ ደረጃ ንቀት ነው። በሌላ በኩል ደግሞ ለዚህች አገር እኔ ብቻ ነው የማወቀው ማለት ነው። ከዚህ በተረፈ ደገሞ ኢህአዴግ በአማራ፣ በኦሮሚያ እና በሌሎች የአገሪቱ ክፍሎች የተነሱበትን ህዝባዊ ቁጣዎች ለማስተንፈስ እና ራሱን ስልጣን ላይ ለመቆየት ከማደረግ ውጭ ለህዝብ አስቦ እስካሁን ያሉበትን ችግሮች ፈትሾ የመቻቻል ፖለቲካም ሆነ ልብ ገዝቶ የህዝብን ጥያቄ እና የህዝብን መብት ለማክበር ያደረገው እንዳልሆነ ነው የማወቀው።

ሰንደቅ:- ለውይይት ስትቀርቡ በመንግስት የተዘጋጀውን የመርሃ ግብር አፈጻጸም ሰነድ ገምግማችሁታል ብለን እናምናለን። በግምገማችሁ ሰነዱ ላይ ያገኛቸሁት ችግር ምንድን ነው?

አቶ አዳነ:- በመጀመሪያ ደረጃኢህአዴግ ሁሉም ጥሩ ሆኖ እንደተሰራ ብቻ ነው የገለጸው። ሌላውን ትተን በሰብአዊ መብት ደረጃ የመኖሪያ ቤት የማግኘት መብት ቢልም በነሃሴ ወር ነው የዜጎችን ቤት ያፈረሰው። በዚያ የክረምት ወቅት ዝናብ በሚዘንብበት ጊዜ ነው የዜጎችን ቤት አፍርሶ ህጻናትን የያዙ እናቶች እና አዛውንቶች ጎዳና ላይ የወደቁት። ያንን እንኳ ሰነዱ ላይ አላስቀመጡም። በፍትህ አካባቢ ላይ ችግር አለ፣ ሀሳብን እና አመለካከትን በመግለጽ ዙሪያ ክፍተት አለ፣ ፓርቲዎቸ በሚያደርጉት መደራጀት ከፍተኛ ችግር አለ፣ ሌላው ቀርቶ ፍርድ ቤት በነጻ ያሰናበተውን ፖሊስ በጉልበቱ እያሰረ ነው ያለው። ሰነዱ እነዚህን ችግሮች ሳያካትት “የእንግሊዝኛ ትርጉም ተጠናቆ አለመቅረብ” ብሎ ነው የቀረበው። ይህ ሁሉ ባለበት ሁኔታ ሰነዱ የሚገልጸው የመልካም አስተዳደር ችግር መኖሩን ነው። በአጠቃላይ ኢህአዴግ ሊሰማው የሚፈልገው ራሱ ያሰበውን ለጆሮው የሚጥመውን እንጂ መሬት ላይ ያለውን ተጨባጭ እውነታ እንዳልሆነ ነው የተረዳሁት። 

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
431 ጊዜ ተነበዋል

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us