ሐረሪና የአናሳ መብቶች

Wednesday, 14 December 2016 14:15

የሐረር ሕዝብ በምስራቅ ኢትዮጵያ ከአዲስ አበባ 515 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ይገኛል። ክልሉን የኦሮሚያ ክልል ወረዳዎች ያዋስኑታል። በሰሜን ጃርሶ፣ በደቡብ ፈዲስ፣ በምዕራብ ሐረማያ፣ እንዲሁም በምስራቅ ጉርሱምና ባቢሌ ወረዳ ያዋስኑታል።

የሐረር ሕዝብ ክልል በውስጡ የተለያዩ የሃይማኖት እና ባሕል ያሏቸው ብሔረሰቦች በሰላም እና በመተሳሰብ የሚኖሩትበት ክልል ነው። የ1999 ዓ.ም የህዝብ እና ቤት ቆጠራ የክልሉ አጠቃላይ የሕዝብ ቁጥር 183ሺ 344 መሆኑን ያመለክታል። ከዚህ ውስጥ 8 ነጥብ 65 በመቶ የሐረር ብሔረሰብ ሲሆን፣ 56 ነጥብ 41 በመቶ የኦሮሞ፣ 22 ነጥብ 77 በመቶ አማራ፣ 4 ነጥብ 34 በመቶ ጉራጌ፣ 3 ነጥብ 87 ሱማሌ፣ 1 ነጥብ 53 በመቶ ትግሬ፣ እና 2 ነጥብ 4 የሌሎች ብሔረሰብ አባለት ናቸው።

የክልሉ ሕዝብ የሃይማኖት ስብጥር ሲታይ 68 ነጥብ 99 በመቶ እስልምና፣ 27 ነጥብ 1 በመቶ ኦርቶዶክስ፣ 3 ነጥብ 4 በመቶ ፕሮቴስታንት፣ 0 ነጥብ 3 በመቶ ካቶሊክ ሲሆኑ ቀሪ 0 ነጥብ 2 በመቶ ደግሞ የሌሎች እምነቶች ተከታዮች ናቸው። የክልሉ ካቢኔ በ2008 ዓ.ም ባጸደቀው መሰረት፣ በዘጠኝ ወረዳዎች እና በ36 ቀበሌች የተዋቀረ ነው።

ሐረሪዎች የሴም ቋንቋ ተናጋሪ ሲሆኑ ሙሉ ለሙሉ የእስልምና እምነት ሃይማኖት ይከተላሉ።

የሐረር ክልል ከሌሎች የኢትዮጵያ ክልሎች ጋር ሲነፃጸር በቆዳ ስፋትም ሆነ በሕዝብ ብዛት አነስተኛ ነው። ሆኖም እንደአንድ ክልል ተዋቅሯል። በሀረር በተደረገው የብሔረሰቦች ቀን በዓል የተሰራጩ ሰነዶች ሐረር እንደክልል የተዋቀረችበትን ምክንያቶች ጠቃቅሰዋል። በዋነኛነት ያስቀመጡት የብሔረሰቡን ታሪክ ነው።

ይኽውም፣ ሐረሪዎች ከጥንታዊው የሐርላ ማሕበረሰብ ጋር የሚተሳሰሩ፣ የሀረርን ከተማ የመሰረቱና ራሳቸው ለረጅም ዘመን ያስተዳደሩ መሆናቸው ይጠቅሳሉ። በተጨማሪ ከተማዋን የምስራቅ አፍሪካ የንግድ መናኸሪያ፣ የእስልምና ሃይማኖት ትምህርት ማስፋፊያና የስነ ጥበብ ማዕከል፣ በጁገል ግንብ የታጠረ የከተማ ማዕከል፣ በድንጋይ ግንብ የተሰሩ የራሳቸው ባሕል መልክ ያላቸው ቤቶች፣ ህንፃዎች እና መስጊዶች የሚገኙባት፣ ቅዱስ የእስልምና ማዕከል አድርገው ማቆየታቸው በመሰረታዊ ነጥቦች መቀመጣቸውን ተገልጻል።

እንዲሁም በዙሪያቸው የሚገኙ ሕዝቦች የኩሽ ቋንቋ ተናጋሪዎች ሆነው ሳለ ሐረርዎች የራሳቸውን ቋንቋ ጠብቀው ያቆዩ፣ የራሳቸው የመገበያያ ገንዘብ የነበረው እና የተለያዩ የጨርቃ ጨርቅ እና ዕደጥበባት ውጤቶች አምራቾች የነበሩ፣ የውጪ ገቢ ንግድን ያከናወኑ የነበሩና በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ የራሳቸው ተፅዕኖ ያሳረፉ መሆናቸው ራሳቸውን ለማስተዳደር የሚያስችል ታሪካዊ መነሻ እንዳላቸው ማስረጃ ሆነው መቅረባቸውን የቀረቡ ማጣቀሻዎች ያሳያሉ።    

የሕዝብ ተወካዮች ጉባኤ ከጠቅላላው መቀመጫዎች ከጁገል የምርጫ ክልል በሚወከሉ አራት አባላት እና ከጁግል ውጭ ያሉ የከተማ ቀበሌዎችና የገጠር ገበሬ ማሕበራትን ከሚያጠቃልል የምርጫ ክልል የሚወከሉ 18 አባላት በአጠቃላይ 22 መቀመጫዎች ይኖሩታል። የሐረር ብሔራዊ ጉባኤ የሚኖሩት መቀመጫዎች 14 ሲሆኑ በክልሉ ውስጥና በሌሎች የኢትዮጵያ ከተሞችና ክልሎች በሚመረጡ ሐረርዎች ይወከላሉ።

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

  በዚሁ መሰረት የሐረር ሕዝብ ክልል ፕሬዝደንት የሚሾመው በሐረር ጉባኤ አቅራቢነት በምክር ቤቱ ሲጸድቅ ነው። ከዚህ በተጨማሪ የክልል ምክር ቤቱ አፈ ጉባኤና ምክትል አፈ ጉባኤ ሲኖሩት አፈ ጉባኤው በሕዝብ ተወካዮች ጉባኤ፣ ምክትሉ ደግሞ በሐረር ብሔራዊ ጉባኤ አቅራቢነት በምክር ቤቱ ሁለት ሶስተኛ ድምፅ የሚሾም ነው። ሁለቱ ጉባኤዎች የጋራና የተናጠል ስልጣን እና ተግባር ያላቸው ሲሆኑ በተለይ የሐረር ሕዝብን ቋንቋ፣ ታሪክ ቅረስ በሚመለከቱ ጉዳዮች ፓሊሲዎችን፣ ሕጎችንና መመሪያዎችን የማውጣት ተግባር የሐረር ብሔራዊ ጉባኤ ኃላፊነት ነው።

   

    የአናሳ መብት ፅንሰ ሃሳቦች ምንድን ናቸው?

የአናሳ ጽንሰ (Minority) ሃሳብን በተመለከተ በተለያዩ ባለሙያዎች የተለያዩ ፍቺዎች ቀርበዋል። ፈጽሞ የአናሳ መብቶችን ማክበር ከብሔራዊ አንድነት ግንባታ ጋር ተፃራሪ ወይም አስፈላጊነቱን የማይቀበሉም አሉ። በሌላ መልኩም የእያንዳንዱን ግለሰብ መብት በማክበር የአናሳ መብቶችን ማስከበር ይቻላል ብለውም የሚያምኑ አሉ። በአናሳ መብቶች ዙሪያ የተሻለ ትንታኔ ማቅረባቸው የሚነገርላቸው ሁለት ሊሂቃን አሉ። እነሱም፣ ፍራንሲስኮ ካፖቶርቲ እና ጁሌስ ዴስቼኒስ ናቸው።

ካፓቶርቲ ስለአነሳ መብቶች ሲገልጽ፣ “ከሀገሪቱ ሌሎች ሕዝቦች አንፃር በቁጥር በጣም ዝቅተኛ፣ ተፅዕኖ የማሳረፍ አግባብነት የሌለው፣ አባላቱም የሀገሪቷ ዜጎችን የሚወክል ከሌሎች የሀገሪቱ ህዝቦች ልዩ የሆነ የብሔር፣ የሐይማኖት ወይም የቋንቋ መገለጫዎች ባለቤት የሆነ አንድ ቡድን የሚመለከት ሲሆን የዚሁ ቡድን አባላትም ባሕላቸውን፣ ወጋቸውን፣ ሃይማኖታቸውን ወይም ቋንቋቸውን ለመጠበቅ ያላቸው ፍላጎት በግልጽ ያረጋገጡ እንደሆኑ ብቻ ነው” ብሏል። (Francesco Capotorti;study on the right of person belonging to ethinc religious and linguistic minorities UN documents/E/CN.4/Sub/2/384/Add.1-7 (1977))

ዴስቼኒስ በበኩሉ፣ “የሀገሪቱ ዜጎች የሆኑ አባላት ያቀፈ በቁጥርም አናሳ የሆነ እና በዚያው ሀገርም ተፅዕኖ ለማሳረፍ አግባብነት የሌላቸው ከብዙሃኑ ህብረተሰብ ልዩ የሆ የብሔር፣ የሃይማኖት ወይም የቋንቋ መገለጫዎች ባለቤት የሆነ አንድ ቡድን የሚመለከት ሲሆን ይኽውም ቡድን በሕግና ሆነ በተጨባጭ ከብዙሃን ጋር እኩልነት በመቀዳጀት ዓላማ ራሳቸውን ለመታደግ የጋራ ፍቃድና ፍላጎት የአንድንነት መንፈስ በመካከላቸው በግልጽ የሚታይ እንደሆነ ብቻ ነው” ብሏል። Jules Desechenes, proposal concerning a definition of the term `Minority` minorities UN documents/E/CN.4/Sub/2/384/Add.1-7 (1985))ነጥብ

ከላይ ከሰፈሩት ጽንሰ ሃሳቦች የጋራ መገለጫ ተደርገው የሚወሰዱት፣ የቁጥር መስፈርት፣ ተፅዕኖ ያለማሳረፍ አግባብነት፣ ልዩ የሆነ የማንነት መገለጫ ባለቤትነት፣ የሀገሪቷ ዜጋ መሆን እና የቡድን አንድነት ህብረት ዋና ዋና የአናሳነት መስፈርቶች ተደርገው መወሰዳቸውን ነው። ከአናሳዎች መገለጫ አይነቶች የሚጠቀሱት፣ የብሄር አናሳዎች (Ethinic Minority)፣ የሃይማኖት አናሳዎች (Religious Minority) የቋንቋ አናሳዎች (Linguistic Minority) የብሔራዊ አናሳዎች (National Minority) የነባር ሕዝቦች (Indigenous Peoples) ናቸው።

 

ከዓለም ዓቀፍ የአናሳ መብቶች ተሞክሮ የሚጠቀሱ

ዩናይትድ ኪንግደም

ዩናይትድ ኪንግደም /United Kingdom/ constitutional monarchy ስርዓትን የምትከተል ዲሞክራሲያዊ እንዲሁም የተለያዩ ብሔሮች የሚኖሩባትና ብዝሃነት /Ethnic diversity/ የምታስተናግድ አገር ነች። ከ60-70 ሚሊዮን ህዝብ የሚኖርባት ዩናይትድ ኪንግደም 84 ነጥብ 3% ህዝብ ነጭ ብሪታኒያዎች ሲሆኑ የተቀሩት ደግሞ በተለያዩ ጂኦግራፊያዊ ክልል የሚኖሩ ስኮትላንዶች /Scotland 7 ነጥብ 6% አካባቢ፣ ዊልስ /Wales 3 ነጥብ 4% አካባቢ እና ሰሜን አየርላንዶች Northern Ireland 2 ነጥብ 7% አካባቢ ይሆናሉ። በአገሪቱ አራት እራሳቸውን የቻሉ ግዛቶች ያሉ ሲሆን እነርሱም ኢንግሊዝ፣ ስኮትላንድ፣ ዌልስ እና ሰሜን አየርላንዶች ናቸው። አራቱም የራሳቸው መንግስታዊ አወቃቀርና የራሳቸው ጉባኤ ወይም ፓርላማ በየአካባቢያቸው ሲኖራቸው በአገር አቀፍ ደረጃ በሚገኘው ፓርላማም ተመጣጣኝ ውክልና አላቸው።

የሦስቱን አናሳዎች የስኮትላንድ፣ የዌልስ እና የሰሜን አየርላንድ ጉዳይን ከተመለከትነው፣ ሶስቱም የራሳቸው ግዛትና አስተዳደር አላቸው፤ የራሳቸው ጉባኤ እንዲሁም በሃውስ ኦፍ ኮመን /House of Commons/ እንደቅደም ተከተላቸው 59፣ 40 እና 13 ውክልና አላቸው።

 

በኖርዌይ (Norway) የሳሚዎች ጉባኤ

ኖርዌይ በዲሞክራሲ ካደጉት አገር የምትመደብ ስትሆን፣ በዚች ሀገር የሚገኙ በአውሮፓ ነባር ህዝብ መካከል የሚመደቡ በቁጥራቸው እጅግ አናሳ የሆኑ ከጠቅላላ ሕዝቡ 14 ነጥብ 6 % ሳሚዎች ናቸው። በአሁኑ ጊዜ ሳሚዎች በኖርዌይ ስዊድን፣ ፊንላንድ እና ራሺያ ውስጥ ይኖራሉ።

በኖርዌይ ውስጥ ሚኖሩ የሳሚ ብሔር አባላት ቁጥር ብዛት በውል ባይታወቅም በ2005 በተካሄደው ከ18 ዓመት በላይ የሆኑትና ምርጫ የተመዘገቡ 11ሺ ነበሩ። በሀገሪቱ ሁለት ፓርላማ ያለ ሲሆን አንደኛው የሳሚ ጉባኤ (Sumedigii) ሲሆን ሌላኛው የኖርዌይ ፓርላማ ይባላል። የሳሚ ጉባኤ 39 አባላት አሉት። በ1984 በኖርዌይ ፓርላማ አጽዳቂነት የተቋቋመ ሳሚዎች ፖለቲካ፣ ባህላቸው፣ ቋንቋቸውን የሚያስፋፉበት እና ራሳቸውን የሚያስተዳድሩበት ጉባኤ ነው።

ይህ ጉባኤ ከፖለቲካው ኃላፊነት በተጨማሪ ባህል፣ ቋንቋና ትምህርትን ለማስፋፋት አራት ካውንስሎች ማለትም የሳሚ ቅርስ ካውንስል፣ የቋንቋ ካውንስል፣ የባህልና የሳሚ ልማት ፈንድ አሉት። በአሁኑ ጊዜ የሳሚ ቋንቋ ከኖርዌይ ቋንቋ ጋር እኩል እውቅና ተሰጥቶታል። አገሪቱ በ1987 በወጣው አዋጅ መሠረትም ሳሚዎች በቋንቋቸው ትምህርት የህዝብ አገልግሎት እና የመዳኘት ተግባራቸው ይከናወናሉ። ይህ ጉባኤ አናሳ ሳሚዎች ብቻ የሚወዳደሩበት እና የሚመረጡበት የሳሚ ም/ቤት ነው። ሳሚዎች በምርጫው ጊዜ ለሳሚ ም/ቤት ምርጫ ክልል ወይም ለጠቅላላው ምርጫ ክልል ለመምረጥ በመመዝገብ በዚያው አግባብም ድምጻቸውን ይሰጣሉ።

 

ፊንላንድ

ፊንላንድ የአናሳ መብት በማክበር ረገድ ጥሩ ስም ያላት ሀገር ነች። በዚሁ ዙሪያም ህግ በማውጣት በነዋሪዎችዋ መካከል መከባበርና መቻቻልን ለማስፈን ችላለች።

በፊንላድ የስዊድን ቋንቋ ተናጋሪዎች ከአናሳዎች መካከል በጣም ዝቅተኛ የማህበረሰብ አባላት ካላቸው አናሳዎች ቀዳሚ ሲሆኑ ከጠቅላላው ህዝብ ብዛት 5 ነጥብ 7 በመቶ ድርሻን ይይዛሉ። እነዚህ አናሳዎች በቋንቋቸው እንዲጠቀሙ ከመደረጉም በላይ ይኸው የአናሳዎች ቋንቋ ከፊንላንድ ቋንቋ ጎን ለጎን የአገሪቱ የስራ ቋንቋ ሆኖ እንዲያገለግል ተደርጓል።

በአገሪቱ የሚገኙትን አናሳና ነባር የሆኑ ሳሚዎች በተመሳሳይ መልኩ በቋንቋቸው እንዲጠቀሙ፣ ትምህርት እንዲማሩ፣ በፍርድ ቤት እንዲዳኙ ተደርጓል። በተጨማሪም ሳሚዎች የራሳቸው ምክር ቤት /Sami parliaments/ እንዲኖራቸው የፊንላንደ ፓርላማ እ.ኤ.አ በ1973 “የሳሚ አናሳዎች” የሚል ሕግ አጽድቆ ተግባራዊ አድርጓል። በዚህም መሠረት ሳሚዎች የራሳቸውን ዕድል በራሳቸው የሚወስኑበት ደረጃ ላይ ደርሰዋል። በየጊዜው በሚደረገውም ምርጫ በመሳተፍ ለሳሚ ጉባኤ አባላት ድምጽ ይሰጣሉ። ከኖርዌይ ከሚገኙ ሳሚዎች አንጻር ሲታይ በፊንላንድና በስዊድን የሚገኙ ሳሚዎች ብዛት እጅግ ያነሰ ነው።

ምንም እንኳን ዘግይቶ ቢፀድቅም በስዊድንም የሚገኙ ሳሚዎች ተመሳሳይ የፖለቲካ ተሳትፎ እንዲጎናፀፉ ተደርጓል። እ.ኤ.አ በ1992 የስዊድን ፓርላማ ህግ በማውጣት የስዊድን ሳሚ ጉባኤ /Swedish Sami Parliament/ እንዲቋቋም በመደረጉ በ1993 ለመጀመሪያ ጊዜ በተመሳሳይ የጉባኤዎቹ ተግባራት በሦስቱም አገራት በአብዛኛው ተመሳሳይ ነው።

 

ኒውዚላንድ- ማኡሪ አናሳዎች

ኒውዚላንድ የአናሳ መብት አክባሪ አገር ነች። ኒውዚላንድ ውስጥ ማኡሪ (The Maori people) የሚባል አናሳ ብሔር የሚገኝ ሲሆን ከኒውዚላንድ ከ1ሺ 300 ዓመታት በፊት ይኖር እንደነበር የሚታወቅ ብሔር ነው። ማኡሪዎች ከ1840 በኋላ የራሳቸውን መሬት በመነጠቃቸውና በሌሎች ምክንያቶች ይደርስባቸው በነበረው ጭቆና ቁጥራቸው አናሳ ለመሆን ባህላቸውም ሊጠፋ ደርሶ ነበር። በአሁኑ ጊዜ ማኡሪዎች ከኒውዚላንድ ጠቅላላ ሕዝብ ብዛት 14-15 በመቶ ናቸው።

በአሁኑ ጊዜ የማኡሪዎች አኗኗር ወደ ከተሜነት ተቀይሮ አብዛኛው ማኡሪዎች በከተማ አካባቢ ይኖራሉ። በሀገሪቱ በአጠቃላይ የማኡሪ እና የአጠቃላይ ምርጫ ክልል በሚካሄድ ምርጫ በሁለት በሚከፈል የሚፈፀም ነው። የማኡሪ የምርጫ ክልል ልዩ የምርጫ ክልል ሲሆን የሚመርጡትም የሚመረጡትም ማኡሪዎች ብቻ ናቸው። በተመሳሳይ የአገር አቀፍ ደረጃም እንዲሁ በአጠቃላይ 10 በመቶ ወንበር በፓርላማ ደረጃ ለማኡሪዎች የተያዘ ተቀማጭ (Reserve) ወንበር መሆኑ አገሪቷ ለአናሳ መብት የሰጠችውን ከፍተኛ ዋጋ ማሳያ ነው።

ማኡሪዎች ለተወካዮች ም/ቤት እና ለማኡሪ ጉባኤ በመሳተፍ የተጎናጸፉት ዕድል ራሳቸውን በራሳቸው እንዲያስተዳድሩ ቋንቋቸውንና ባህላቸውን እንዲጠቀሙና እንዲያዳብሩ ረድቷቸዋል። ማኡሪዎችን የሚመለከት አዋጆችና መመሪያዎችን በተለያዩ ጊዜያት ከማውጣታቸውም ባሻገር የማኡሪ ልማት ሚኒስቴር በሚኒስቴር ደረጃ ተቋቁሞ ለህዝቡ ማንሰራራትና ማደግ እንዲሁም የፖለቲካ ተሳትፎአቸው እንዲያድግ አስተዋፅኦ በማድረግ ላይ ይገኛል።

 

 

ፊጂ (Fiji)

ፊጂ እ.ኤ.አ በ1970 በዩናይትድ ኪንግደም ነፃ የወጣች አገር ስትሆን፣ በ1997 ባረቀቀችው ህገ መንግስት የዓለም አቀፍ ህጎችን በመከተል የአናሳዎች ድንጋጌዎችን፣ ልዩ ድጋፍ /affirmative action/ በማስፈር እንዲሁም ፖሊሲዎችና ፕሮግራሞችን ለመቅረጽ ችላለች።

በፊጂ ሁለት ም/ቤት ያለ ሲሆን እነዚህም የተወካዮች ም/ቤት /House of Representatives እና ሴኔት በመባል ይታወቃሉ።

በተጨማሪም በአገሪቱ ሁለት የምርጫ አይነቶች ማለትም አጠቃላይ ምርጫ /General electorate እና አናሳ ህዝቦች የሚሳተፉበት Communal ምርጫ ዓይነቶች አሉ። ፊጂ ብሔር /Fiji ethnic groups/ በአገሪቱ ነባር ብሔር ሲሆን ከጠቅላላው ህዝብ ብዛት 36 በመቶ በመሆን አናሳ ሊሆን ችሏል።

ባጠቃላይ ካሉት 71 ወንበሮች 46ቱ (64%) ክልል እና 25ቱ ደግሞ ለጠቅላ ምርጫ ክልል Open Constituency በሚደረጉ የምርጫ ውድድሮች የሚያዙ ወንበሮች ናቸው፤ ከ46ቱ የCommunal ወንበሮች መካከል፤ 23ቱ ለነባር ፊጂዎች indigenous Fijians፣ 19ኙ ለህንድ ፊጂዎች indian Fijis፣ 1 ለRotumans፣ 3ቱ ለቻይናዎችና ለሌሎች አናሳዎች ናቸው።

ከ71 ቀሪው 25 ወንበር ሁሉም መራጮች ፊጂዎችን ጨምሮ ድምጽ የሚሰጡበት አጠቃላይ የምርጫ ክልል ይሆናል። ፊጂዎች ሁለት ድምጽ የሚሰጡ ሲሆን አንዱ ለcommunal እና ሌላኛው ለአጠቃላይ ምርጫ ክልል የሚሰጡት ነው። (ኪትሴ፤ 98 ኢንሳይክሎፕዲያ በመሀመድ አህመድ የተጠቀሰ)

 

ሃንጋሪ (Hungary)

ሃንጋሪ ህብረ ብሔራዊ አገር ስትሆን አናሳዎችን መብት በማክበር ቀደምት አገር ናት። አገሪቱ ባወጣቻቸው ህጎች በተለይ በ1993 የወጣው የአናሳዎች መብት (The Rights of National and Ethnic Minorities Act) ለአናሳዎች ህጋዊ ድጋፍና ማስተማመኛ በመስጠት አናሳዎች በፖለቲካው ተሳትፎ የማድረግ መብት፣ የራስ መስተዳድር የማቋቋም መብት ለመጎናፀፍ ችላለች። በዚህ ሕግ ለ13 አናሳዎች ዕውቅና በመስጠት የራሳቸውን አካባቢያዊና ብሔራዊ መንግስት መቋቋም መብትን እንዳላቸው በግልፅ አስፍራለች። ስለሆነም ለ13ቱም አናሳዎች ሀገር አቀፍ ፓርላማ አንድ አንድ ተወካይ እንዲኖቸው የተቀማጭ ወንበር ተይዟል።

በአገሪቱ ከ13 በላይ አናሳዎች የሚገኙ ሲሆን ከእነዚህም መካከል የሮማ ብሔሮች Roma/Gypsi ትልቁን ድርሻ በመያዝ በአገሪቱ አጠቃላይ አስር ሚሊዮን ሕዝብ ውስጥ 560,000.00 (5%) አካባቢ ይሆናሉ። እነዚህ አናሳ ሮማዎች የራሳቸውን የአናሳዎች መንግስት እንዲመሰርቱ ተደርጓል።

ሌሎችም እንዲሁ በተለያዩ ጊዜያት የራሳቸውን ራስ-ገዝ ለማቋቋም በቅተዋል። በሃንጋሪ አንዲት ፐርክ ተብላ በምትጠራ ክልል ዘጠኝ አናሳ ብሔሮችን በማሰባሰብ የተዋቀረች የዘጠኝ አናሳዎች ራስ አገዛዝ ተጠቃሽ ነች።    

  እንደመውጫ፣ የአናሳዎችን መብት ማክበር መዘመን እንጂ ሌላ ፍቺ ሊሰጠው አይችልም። በሐረር ክልል ውስጥም የአናሳዎች መብት በሕገ-መንግስቱ የተረጋገጠ መብት ሆኖ ቀጥሏል። እስካሁንም በመከባበር እና በመቻቻል በክልሉ ውስጥ ያሉ ብሔረሰቦች እየኖሩ ይገኛሉ።

ሆኖም ተዘዋውረን ያነጋገርናቸው ነዎሪዎች የተለያዩ ቅሬታዎች አሰምተውናል። እንደውም አንዳንዶቹ አሁን በክልሉ ውስጥ የሚታዩ የመልካም አስተዳደር ግድፈቶች “ከመከባበር እና ከመቻቻል” ወደ “መከባበር እና መቻል” እየተቀየሩ ነው ብለዋል። የተወሰነው የሕብረተሰብ ክፍል ሌሎቹን በመቻል እየኖርን ነው ሲሉ ተደምጠዋል። ቅሬታዎቹን ለማስፈር የሌሎች ወገኖችን ድምጽ ለመሰብሰብ ጊዜ ማግኘት ባለመቻላችን የአንድ ወገን ከማስተናገድ ተቆጥበናል። ችግሮቹን ለመፍታት ግን በሰለጠነ ሁኔታ ውይይቶች በስፋት በሐረር ክልል ውስጥ እንዲደረጉ መጠቆም ተገቢ ይሆናል። ችግሮችን ቁጭ ብሎ ተወያይቶ በመፍታት ሐረርን የሁሉም ብሔር ብሔረሰብ በእኩልነት የሚታይባት፣ ሠላምና ዴሞክራሲ የነገሰባት እንደስሟ የፍቅር ተምሳሌት ማድረግ ይቻላል።

(ከቀረቡት ሰነዶች የተወሰዱ ናቸው)

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
673 ጊዜ ተነበዋል

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us