ኢትዮጵያ አባይን የመጠቀም መብቷ የተከበረው ከምኒልክ ዘመን ጀምሮ ነው

Wednesday, 28 December 2016 14:29

በይርጋ አበበ

በርዝመቱ ከዓለም አንደኛ ደረጃ ላይ የተቀመጠው ታላቁ የአባይ ወንዝ በግዝፈቱ ከአፍሪካ ቀዳሚ የሆነ የኤሌክትሪክ ማመንጫ ግድብ ሊሰራበት መሆኑ ከተነገረ ዘንድሮ አምስተኛ ዓመቱ ላይ ይገኛል። በቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ አማካኝነት የግድቡ ግንባታ የመሰረት ድንጋይ በተቀመጠበት ወቅት ግንባታው በአምስት ዓመት (በ2008 መገባደጃ ቢበዛ በ2009 ዓ.ም) ሊጠናቀቅ እንደሚችል አቶ መለስ ተስፋቸውን ገልጸው ነበር። ግንባታውን ገንብቶ ለማጠናቀቅም እስከ 80 ቢሊዮን ብር አስፈላጊ መሆኑ ተገልጿል። የግንባታው ሙሉ ወጭ በአገሪቱ ህዝብ እና መንግስት ብቻ የሚሸፈን መሆኑም በወቅቱ ከተገለጹት የመንግስት መግለጫዎች ይገኝበታል።

በአባይ ወንዝ ላይ እንኳንስ እስከ 74 ቢሊዮን ኪዩቢክ ሊትር ውሃ ማጠራቀም የሚችል ግዙፍ ግድብ መገንባት ቀርቶ በተፈጥሯዊ የአየር ንብረት መለዋወጥ ምክንያት የዝናብ እጥረት በኢትዮጵያ ተከስቶ በአባይ ወንዝ የውሃ ፍሰት መጠን ላይ ተጽእኖ ቢያሳድር ህይወቱ በወንዙ ላይ የተመሰረተው የግብጽ መንግስት ጩኸት አያድርስ ነው። የኢትዮጵያ መንግስትም በዚህ ትልቅ ወንዝ ላይ ትልቅ ገንዘብ አፍስሶ ትልቅ ፕሮጄክት ሲጀምር ከግብጽ መንግስት ትልቅ ተቃውሞ እንደሚጠብቀው ሳይገነዘብ አይቀርም። የግብጽ መንግስት እና ህዝብ በአባይ ወንዝ ላይ የተመሰረተ ህልውና ያላቸው በመሆኑ የወንዙን የእለት ተዕለት ሁኔታ በንቃት መከታተል የጀመሩት ገና ከፍጥረተ ዓለም ጀምሮ ነው ማለት ይቻላል። አገሪቱ ገና በቅኝ ቅዛት ስር በነበረችበት ወቅትም እንኳ ግብጽ የአባይን ውሃ ለመጠቀም ከሱዳን ጋር ባደረገችው ልዩ ስምምነት (1929 እና 1959 እ.ኤ.አ) የውሃውን አብላጫ ክፍል መጠቀም የሚያስችላትን እድል አመቻችታ ወስዳለች። የወንዙን ውሃ ከ80 በመቶ በላይ የምታስተዋጻው ኢትዮጵያ ግን ውሃውን ለቅኔ መዝረፊያ የዘለለ እንዳይሆን ወስናባታለች።

በ2003 ዓ.ም የመሰረት ድንጋዩ የተጣለው እና በግንባታ ላይ ያለው “የህዳሴ” ግድብም በግብጽ እና በመጠኑም ቢሆን በሱዳን በኩል ከፍተኛ ተቃውሞ ገጥሞት ቆይቷል። የሶስቱ አገራት መንግስታትም ለበርካታ ጊዜያት በአዲስ አበባ በካርቱምና በካይሮ የሶስትዮሽ ውይይቶችን በውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮቻቸው፣ በውሃ ሃብት ሚኒስትሮቻቸውና በመሪዎቻቸው ሳይቀር ውይይት አካሂደዋል። የሶስቱ አገራት የውሃ ዘርፍ ምሁራንም ሰፊ ውይይት ያካሄዱ ሲሆን በመጋቢት ወር 2007 ዓ.ም ካርቱም ላይ መሪዎቹ የመርህ ስምምነት (Declaration of Principle) ተፈራርመዋል።

የህዳሴ ግድብ ህዝባዊ ማስተባበሪያ ጽ/ቤት ሰሞኑን በሚዲያ አጠቃቀም ዙሪያ ከመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች ጋር ውይይት አካሂዶ ነበር። ለመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎቹ ጥናታዊ ጽሁፎችንም ምሁራን (ኢንጅነር ጌዲዮን አስፋው፣ አቶ አቤል አዳሙ እና ዶክተር ያዕቆብ አርሳኖ) ያቀረቡ ሲሆን የመገናኛ ብዙሃንም በጽሁፎቹ ላይ ውይይት አካሂደዋል። በቅርቡ በአቶ ኃይለማሪያም ከተሾሙት የፌዴራል መንግስቱ ካቢኔዎች መካከል አንዱ የሆኑት ዶክተር ኢንጅነር ስለሽ በቀለም የውይይት መድረኩን በንግግር ከፍተውታል። የውይይቱን ጭብጥም ጠቅለል ባለመልኩ ከዚህ በታች አቅርበነዋል።

 

 

“በግንባታ ላይ የሚገኝ ግድብ”

የሶስቱ አገራት ውይይት ጭብጥ

የኢትዮጵያ የግብጽ እና የሱዳን መንግስታት ለአራት ዓመታት ተኩል እና ከዚያ በላይ በአባይ ወንዝ እና በህዳሴው ግድብ ዙሪያ ሰፋ ያለ ውይይት አካሂደዋል። የሶስቱን አገራት ውይይት በተመለከተ ገለጻ ያቀረቡት ኢንጅነር ጌታሁን አስፋው በ2013 የግድቡን ጥናት የሚያጠናው ቡድን የጥናት ሪፖርቱን በ2005 ዓ.ም ማቅረቡን ገልጸው ሆኖም በወቅቱ ኢትዮጵያ የጥናቱን ሪፖርት አለመቀበሏን ተናግረዋል። ኢንጅነር ጌዲዮን የድርድሩን ዋና ዋና ሂደቶች ሲገልጹም “የዓለም አቀፍ ኤክስፐርቶች ፓናል መቋቋምና አንድ ዓመት የፈጀውን ጥናት ለሶስቱ አገራት ማቅረብ፣ የፓናሉን ምክረ ሃሳቦች ተግባራዊ የሚያደርጉ ከሶስቱ አገራት የተውጣጡ 12 አባላት ያሉት የሶስትዮሽ ኮሚቴ መቋቋም እና ሁለቱን ጥናቶች ለማከናወን ከፈረንሳይ አማካሪዎች ጋር ኮንትራት መፈራረም” የሚሉት እንደሆኑ ተናግረዋል። ሁለቱ ጥናቶች ያሏቸውን ሲያቀርቡም “የውሃ ፍሰቱን በተመለከተ እና የውሃ ፍሰቱ በታችኞቹ የተፋሰሱ አገራት ላይ የሚያስከትለውን ተጽእኖ የሚሉት ናቸው” ብለዋል።

የሶስቱ አገራት ድርድር ትልቅ ትኩረት የሚሻ ጉዳይ ሲሆን በተያያዘ እና በተለይም የሱዳን እና የግብጽ መንግስታት የሚሰጡት ትኩረት ከፍተኛ መሆኑ ይታወቃል። ይህን በተመለከተም በኢትዮጵያ በኩል በውይይቱ የሚሳተፉ አካላትን ኃላፊነት ምን መሆን እንዳለበት ኢንጅነር ጌዲዮን ሲገልጹ “በሶስቱ አገራት መካከል የሚካሄደው ውይይት የኢትዮጵያ ህዝብ የጋራ ንብረት በሆነው ውሃ ላይ መሆኑን ሁልጊዜና በማንኛውም ወቅት መገንዘብና ድርድሮች በጥንቃቄ መካሄድ አለባቸው” በማለት አሳስበዋል። ጥንቃቄ የተሞላበት ድርድር የሚለውን ሀረግ ሲያብራሩም “የተደራዳሪዎቸ አቅም (በእውቀት እና በችለሎታ) ማደግ አለበት” ብለዋል። 

ግድቡ መገንባት ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ እስካሁን ድረስ በርካታ የሶስትዮሽ ድርድር መካሄዳቸውን ያስታወሱት ኢንጅነር ጌዲዮን ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ በተለይ የግብጽ ተወካዮች የመለሳለስ ስሜት እያሳዩ መሆናቸውን ገልጸዋል። ሆኖም ግን ግብጽ በኢትዮጵያ ላይ “በተለያዩ አቅጣጫዎች ተጽእኖ በማድረግ ላይ እንደሆነች ግልጽ ነው። ይህንን ለመቋቋም ግን የተቀናጀ ዝግጅት ማድረግ ያስፈልጋል” ሲሉ የገለጹ ሲሆን የግብጽን የተለያየ አቅጣጫ ተጽእኖ እና በኢትዮጵያ በኩል መደረግ አለበት ያሉትን ዝግጅት ሲገልጹም ግብጾች በዲፕሎማሲ በኩል ለመደራደር እንደሚፈልጉ ይህ አልሆን ሲላቸው ደግሞ የታችኞቹን ተፋሰስ አገራት ለመደለል እንደሚሞክሩ፣ ከዚህ ባለፈም ደግሞ ጉዳዩን ለዓለም አቀፉ ፍርድ ቤት እንደሚያቀርቡት ጭምር የሚዝቱ መሆናቸውን ገልጸዋል። ገፋ ሲልም ነፍጥ ለማንሳትና ቃታ ለመሳብም እንደማይመለሱ የገለጹት ኢንጅነር ጌታሁን የኢትዮጵያ መንግስትም እነዚህን የተለያዩ ጫናዎች መመከት የሚያስችለውን ዝግጅት ማድረግ እንደሚኖርበት ነው የተናገሩት። ሶስቱ አገራት ድርድር የሚያካሂዱት “በግንባታ ላይ ያለ ግድብ (The Dam under Construction) በሚል መነሻ ነጥብ መሆኑን ከጋዜጠኞች ለቀረበላቸው ጥያቄ ኢንጅነር ጌዲዮን አስፋው የሰጡት ምላሽ ነው።

መገናኛ ብዙሃን እንዴት ይዘግቡ?

በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የጋዜጠኝነትና ኮምዩኒኬሽን ትምህርት ቤት አስተማ የሆኑት አቶ አቤል አዳሙ የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎችና ተቋማት የህዳሴውን ግድብ በተመለከተ እንዴት መዘገብ እንዳለባቸው የሚያሳስብ ጽሁፍ አቅርበው ነበር። ምሁሩ በጥናታዊ ጽሁፋቸው የግብጽ መገናኛ ብዙሃን በአባይ ዙሪያ የሚዘግቡት እና የእኛ አገር መገናኛ ብዙሃን በተመሳሳይ ጉዳይ የሚሰጡት ሽፋን እንደማይመጣጠን ገልጸዋል። በተለይ አንዳንድ የአገራችን ሚዲያዎች እንደዚህ አይነት ትልቅ አገራዊ ጉዳዮችን ትተው የአውሮፓ ተጫዋቾችን የጫማ ቁጥርና የሚስቶቻቸውን አልባሳት ምርጫ ሳይቀር ሲያወሩ መዋላቸው፤ የአንድን ሬዲዮ ጣቢያ ባለቤት ልጅ የሰርግ ፕሮግራም ሲያስተላለፉ በመዋል እንደሚጠመዱ ነው የገለጹት። “ሚዲያ ትልቅ አቅም አለው፣ በአሁኑ ሰዓት ዓለም ምን እየሆነ እንደሆነ የምናውቀው በሚዲያ ነው። ያለ ሚዲያ መኖር አይቻልም። ለህዝብ የሚጠቅም ነገር በመስራት አገራዊ ሚናውን መጫወት አለበት” ብለዋል።

የአገር ውስጥ መገናኛ ብዙሃን በህዳሴው ግድብ ላይ ሊጫወቱት የሚገባቸው ሚና ከፍተኛ እንደሆነ አሳስበዋል። ነገር ግን ጋዜጠኞች ይህን ጉዳይ ሽፋን ሲሰጡት ለህዝብ አዝናኝና ማራኪ በሆነ መልኩ፣ ሰፊ ጥናትና ጥረት አካሂደው፣ እንዲሁም ወጥነት ባለው መልኩ መሆን እንዳለባቸውም አስገንዝበዋል። የግድቡ ወቅታዊ የግንባታ ደረጃ ምን ላይ እንዳለ ተከታትለው መዘገብም አስፈላጊ መሆኑን ያሳሰቡት መምህሩ፤ ጋዜጠኞች ዘገባዎችን በእውቀት ታጅበው ማቅረብ እንዳለባቸውም ተናግረዋል።

በአባይ ወንዝ ላይ የመጠቀም መብታችን

የሰሜን ምስራቅ አፍሪካ ፖለቲካ

በዚህ ጽሁፍ መግቢያ ላይ እንደተገለጸው የአባይ ወንዝ በርዝመቱ የዓለም ቀዳሚ ነው። ይህ ማለት ወንዙ በርካታ አገራትን እየረጋገጠ የሚሄድ ሲሆን ወንዙም ዓለም አቀፍ ነው ማለት ነው። በዓለም አቀፍ ወንዞች የውሃ አጠቃቀምን በተመለከተ ሁሉም የተፋሰሱ አገራት ሳይጎዱ ወይም አንደኛው ብቻ ብቸኛ ተጠቃሚ እንዳይሆን የሚገድቡ ዓለም አቀፍ ህጎች አሉ። ግብጽ እና ሱዳን ግን በቅኝ ግዛት ዘመን የተዋዋሏቸው (የተማማሏቸው) ሰነዶች በማንሳት የውሃው ብቸኛ ባለመብት እነሱ ብቻ እንደሆኑ አድርገው ይጮኻሉ። ለመሆኑ ኢትዮጵያ ለአባይ ወንዝ ከ80 በመቶ በላይ ውሃ እያዋጣች በወንዙ የመጠቀም መብቷ ምን ያህል ነው ለሚለው ጥያቄ በአባይ ወንዝ ላይ ሰፊ ጥናት ያጠኑት ዶክተር ያዕቆብ አርሳኖ መልስ አላቸው።

ዶከተር ያዕቆብ “በአባይ ወንዝ የመጠቀም መብቷ ያለቀለት ነገር ነው። ከዛሬ 115 ወይም ከዚያ በፊት የኢትዮጵያ የውሃ መብት በአጼ ምኒልክና በእንግሊዞች መካከል በተደረገው ስምምነት ውሰጥ የተወሰነ መብት እንዳለን ተረጋግጧል” ሲሉ ተናግረዋል። ይህንን ጉዳይ ብዙ ምሁራን ለመተርጎም ቢሞክሩም ዋናው ጉዳይ “ኢትዮጵያ ጎረቤቶቿ ውሃውን እንዳይጠቀሙ አትከለክልም እንጂ የመጠቀም መብቷ የተጠበቀ መሆኑ ያኔ በደንብ የተጠቀሰ ነው” የሚሉት ዶክተር ያዕቆብ አያይዘውም “በ1940ዎቹ ውስጥ በተደረጉት የዲፕሎማሲ ልውውጦች የኢትዮጵያ ጎረቤቶቿ የሚኖራቸው የውሃ አጠቃቀም የኢትዮጵያን መብት የሚነካ ስለሆነ በመካከላችን የሚኖረው ስምምነት የእኛን መብት ዛሬም ሆነ ነገ ሊነካ አይችልም የሚል ጠንከር ያለ አገላለጽ ተናግራለች። ከዚያ በኋላም በ1970ዎቹ መጀመሪያ ላይ የኢትዮጵያ መንግስት በተባበሩት መንግስታት ስብሰባ ላይ ማናቸውንም አይነት የውሃ ጉዳይን የሚመለከት ህብረት ዪየሚኖረን መብታችንን የሚያከብር ስምምነት ሲኖር ነው የሚል ጠንካራ ምላሽ ሰጥተዋል” በማለት ኢትዮጵያ በአባይ ወንዝ የመጠቀም መብቷን ታሪካዊ ዳራ ዶክተር ያዕቆብ ገልጸዋል።

ዶክተር ያዕቆብ በጥናታዊ ጽሁፋቸው በተለየ መልኩ ትኩረት ያደረጉት ኢትዮጵያ የምትገኝበትን ጅኦ ፖለቲካ ሁኔታ የዳሰሱበት ነጥብ ነው። እንደ ዶክተር ያዕቆብ ገለጻ ኢትዮጵያ በሰሜን ምስራቅ አፍሪካ እምብርት (Epicenter) ነች። ይህ ቀጠና ደግሞ ባለው ተፈጥሯዊ አቀማመጥ የተነሳ ጅኦ ፖለቲካው የታመሰ ቀጠና ነው። በዚህ ቀጠና የምትገኘዋ አገራችን ልታደርገው የሚገባትን የቤት ስራ ሲገልጹም “የህዳሴው ግድብም ሆነ ሌሎች ግድቦችን ስንገነባ በጅኦ ፖለቲካው ትርምስ ውሰጥ የምንሰራው በመሆኑ ለዚህ የሚያስፈልገን ወሃ አለን የለንም ሳይሆን ውሃውን በምን ችሎታ፣ በምን ዝግጅት እና በምን ድርጅት ወይም ትብብር እንጠቀመዋለን? ቴክኒኩ ስራውን ይሰራል ፖለቲካው እና አመራሩ ግን ይህን የተገነዘበ መሆን አለበት። እውቀት፣ ችሎታ እና ቴክኒኩ ያስፈልገናል” ሲሉ ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ የሰሜን ምስራቅ እምብርት ላይ ያለች አገር በመሆኗ በውሃ አጠቃቀማችን ዙሪያ በተመለከተ በተለይም በአባይ ወንዝ ላይ “ማነው መሪ ተዋናዩ? የሚለውን መለየት አለብን። ሱዳን፣ ኬኒ፣ ያ ግብጽ ወይስ ሳዑዲ አረቢያ ናት ወይስ የእነሱ ወዳጆች ናቸው የሚሉትን ማወቅ እጅግ አስፈላጊ ነው” ሲሉ በጉዳዩ ላይ ትኩረት የሰጡት ዶክተር ያዕቆብ፤ “ኢትዮጵያ የቀጠናው የውሃ ማማ ናት ነገር ግን ይህን ውሃ ለመጠቀም እውቀቱ ብልሃቱ እና ጥንካሬው ያስፈልገናል። ጥንካሬውን ለማምጣት ደግሞ ፖለቲካል ኢኮኖሚ የእውቀት ግንባታ ያስፈልጋል” ሲሉ ሃሳባቸውን አክለው ተናግረዋል። በፖለቲካው ኢኮኖሚ እውቀት ግንባታ ዙሪያ በተጠያቂነና በኃላፊነት መሰራት ወሳኝነት አለው።

የመገናኛ ብዙሃን በህዳሴው ግድብ ግንባታ ዙሪያ በሚሰሯቸው ዘገባዎች ቋሚ እና ወቅቱን ጠብቆ የሚካሄድ የምሁራን ቃለ ምልልስ መካሄድ እንዳለበት የገለጹት ዶክተር ያዕቆብ አርሳኖ ነገር ግን ቃለ ምልልሱ መካሄድ ያለበት የተለያየ አመለካከት ካላቸው አካላት ማለትም የተቃዋሚ ፓርቲ አመራሮችንም ያካተተ መሆን እንደሚገባው ተናግረዋል።

የህዳሴው ግድብ እውነታዎች

ü  800 ኪሎ ሜትር ከአዲስ አበባ ያለው ርቀት

ü  155 ሜትር ከፍታ

ü  1840 ካሬ ሜትር ስፋት

ü  246 ኪሎ ሜትር ከግድቡ ኋላ ውሃው የሚሸፍነው ስፋት

ü  10 ወረዳዎች ከግድቡ ጋር የሚዋሰኑ

ü  74 ቢሊዮን ኪዩቢክ ሊትር ግድቡ የሚይዘው የውሃ መጠን

ምንጭ:- የህዳሴው ግድብ ህዝባዊ ማስተባበሪያ ጽ/ቤት¾

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
552 ጊዜ ተነበዋል

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us