በጋምቤላ ክልል ተቀራማች ቢሮክራቶች የዘረጉት ዓብይ ሙስና፤ በጥናት ይፋ መሆኑ አነጋጋሪነቱ እንደቀጠለ ነው

Wednesday, 28 December 2016 14:33

·         4 ነጥብ 96 ቢሊዮን ብር ብድር ተፈቅዶ 4 ነጥብ 27 ቢሊዮን ብር ባለሃብቶቹ ወስደዋል፤

·         ከ623 ባለሃብቶች መካከል 369 ባለሃብቶች ማልማት አልጀመሩም፤

·         የመሬት ካርታ የሚዘጋጀው በመኖሪያ ቤትና ጫት ቤት ነው፤

·         ለክልሉ ብሔረሰብ ባለሃብቶች በቂ ካፒታል አይቀርብም፤

·         ከተፈጠረው 4ሺ 776 ቋሚ የሥራ ቦታዎች ከነባሩ ብሔረሰቡ የተጠቀሙት 483 ያህሉ ብቻ ናቸው፡፡

 

በጋምቤላ ክልል በተለየ ትኩረት ጥናት ለምን አስፈለገ? በሌሎች ክልሎችስ ለምን በዚህ ደረጃ መጠናት አልተቻለም? የሚሉ ጥያቄዎች ተነስተዋል። ሰነዱ ያስቀመጠው ምላሽ፣  የግብርና ኢንቨስትመንት በክልሉ የመስፋፋቱ አስፈላጊ በመሆኑ፤ በክልሉ በግብርና ኢንቨስትመንት የሚታዩ ችግሮችን በመለየት የመፍትሄ አቅጣጫ ማስቀመጥ አስፈላጊ በመሆኑ፤ የክልሉን የሰላም፣ የልማትና መልካም አስተዳደር ተጠቃሚነት የማረጋገጥ አስፈላጊነት በመኖሩ መሆኑን አስቀምጧል።

በጋምቤላና /ጉሙዝ ክልሎች እየሰፉና እየተወሳሰቡ በመምጣታቸውጠቅላይ ሚኒስትሩ በተቀመጠው አቅጣጫ መሰረት በጋምቤላ ክልል ኢንቨስትመንት ሁኔታ ጥናት መካሄዱ ጨምሮ ገልጿል። ከየካቲት 14 እስከ ግንቦት 19 ቀን 2008 .ም ባለው ጊዜ ውስጥ ጥናቱ የተካሄደ ሲሆን  በጥናቱ በተለያዩ ማት የተወከሉ ከፍተኛ አመራሮችና ባለሙያዎች ተሳትፈዋል። የጥናት ቡድኑ ዝርዝር ሀሳቦችን እና የማጠቃለያ ምክረ ሀሳቦችን አያይዞ አቅርል።

የጥናቱ ዓላማ ተደርጎ የቀረበው፣ በጋምቤላ ክልል በግብርና ኢንቨስትመንት የተሰማሩ ባለሀብቶች ያሉበትን ሁኔታ የሚያሳይ መረጃ በመሰብሰብ፤ በመተንተን፤ ችግሮችን በመለየትና የመፍትሄ ሃሳቦችን ያካተተ ሪፖርት በማዘጋጀት ለጠቅላይ /ር /ቤት ማቅረብ ነው። 

በዚህ ጥናት እንደግብ የተያዙትና የተገኙት፣ በጋምቤላ ክልል በፌዴራል መንግስትና በክልሉ ያለውን የባለሃብት ምልመላ ሂደት፣ የአሰራር ስርዓትና ደንብን ተከትሎ መፈፀሙና አለመፈፀሙ ተለይቷል፤ በጋምቤላ ክልል በፌዴራልና በክልል ደረጃ ለግብርና ኢንቨስትመንት የሚውል መሬት የማጥናት የመለየትና ለባለሃብት በማስተላለፍ እንዲሁም ወደ ልማት የገቡና ያልገቡ ባለሃብቶች ዝርዝር መረጃ ተሰብስቦ ተደራጅቷል፤ በክልሉ ለሚካሄደው የእርሻ ኢንቨስትመንት አገልግሎት በብድር ሰጪ ተቋማት የተሰጠው ገንዘብ ለተፈቀደው ዓላማ መዋሉና አለመዋሉ በጥናት ተለይቷል፤ በጋምቤላ ክልል በግብርና ኢንቨስትመንት የተሰማሩ ባለሃብቶችን ለመደገፍና ለማበረታታት ከቀረጥና ታክስ ነጻ የሚያስገቸውን ተሽከርካሪ፣ የግንባታና የካፒታል እቃዎች ለታለመለት ዓላማ መዋሉ አለመዋሉ በጥናት ተለይቷል፤ በክልሉ የግብርና ኢንቨስትመንት የአካባቢው ማህበረሰብ ተሳታፊነት፣ ተጠቃሚነት እና ትስስር ምን እንደሚመስል ተለይቷል፤ በክልሉ በግብርና ኢንቨስትመንት ዙሪያ የሚታዩ የመልካም አስተዳደርና የኪራይ ሰብሳቢነት ችግሮች ተለይተው ከመፍትሄ ሃሳቦች ጋር ቀርበው ለተሳታፊ ለውይይት ክፍት ተደርገው ቅዳሜ ዕለት በጊዮን ሆቴል ውይይት ተደርጐባቸዋል። 

የዚህ ጥናት ውስንነትን አጥኝው በግልፅ አስቀምጧል። ይኽውም፣ በጋምቤላ ክልል ውስጥ በሚገኙ 3 ዞኖች (አኙዋሃ፤ ኑዌርና መጃንግ) እና በስራቸው በሚገኙ 7 ወረዳዎች እና በአንድ ልዩ ወረዳ ውስጥ ያሉ 623 በግብርና ኢንቨስትመንት የተሰማሩ ባለሃብቶች ላይ የተደረገ የዳሰሳ ጥናት መሆኑ ተገልጿል።

ጥናቱ የተካሄደበትን ስልቶችም ቀርበዋል። ሆኖም ግን ከተሳታፊ ባለሃብቶች የተሰማው፣ ‘ጥናቱ እኛን ያካተተ ባለመሆኑ አንቀበለውም’ የሚል ነበር። አጥኝው ቡድን ግን ጥናቱ እንዴት እንደተካሄደ በግልጽ አስፍሯል። የጥናት ቡድን በጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት የካቢኔ ጉዳዮች ኃላፊ ሚኒስትር የተመራ ሲሆን ከፍተኛ የመንግስት የሥራ ኃላፊዎችና ባለሙያዎች በጥናቱ ተሳትፈውበታል።

አጥኚው ቡድን መረጃ የመሰብሰብ ስልቱን በሁለት ደረጃ ከፍለው ሠርተዋል። አንደኛው፣ በፌዴራል፤ በክልልና በወረዳ ደረጃ 172 ባለሙያዎችና ኃላፊዎች፤ በክልልና በየወረዳው 260 ባለሃብቶች (24 የክልሉ የነባር ብሄረሰብ ተወላጆች) እና በየቀበሌዎቹ የተለያዩ የማህበረሰብ ክፍሎችን ያካተቱ 245 ተወካዮችን በ35 የቡድን ውይይት መድረኮች ተሳትፈዋል። እንዲሁም የ623 ባለሀብቶች መሬት ልኬታ መረጃ ተወስዶል።

በሁለተኛ የመረጃ አሰባሰብ የተጠቀሙት፣ በፌደራል፤ በክልሉና በወረዳ ተቋማት የሚገኙ የፖሊሲ ሰነዶች፤ አዋጆች፤ ደንቦችና የአሰራር መመሪያዎች፤ ሪፖርቶችንና ጠቃሚ የሆኑ ሰነዶች ተገናዝበዋል። እንዲሁም በጥናቱ ላይ ባለሃብቶች እንዲካተቱ ተደርጓል። ይኽውም፣ በክልሉ በሚገኙ 3 ዞኖች (አኙዋሃ፤ ኑዌርና መጃንግ) እና በስራቸው በሚገኙ 7  ወረዳዎች እና በአንድ ልዩ ወረዳ ውስጥ ያሉ 623 ባለሃብቶች ታይተዋል ብለዋል።

መረጃው የተተነተነበት ዘዴ ከተሳታፊ ባለሃብቶቹ ቅሬታ የቀረበበት ቢሆንም አጥኝው ቡድን የተጠቀመበትን አስቀምጧል። ይኽውም፣ የተጠቀሙት ቀላል የትንተና ዘዴዎች ናቸው። እነሱም፣ በመቶኛ፤ ፓይ ቻርት፤ ባር ግራፍ በተጨማሪም የቡድን ውይይት ቃለ-ጉባኤዎችና የእያንዳንዱን ባለሃብት ሁኔታ የሚሳዩ መረጃ በሰንጠረዥ ተዘጋጅተው ተተንትነዋል።

የጥናቱ ውስጣዊ ይዘትን ከዚህ እንደሚከተለው እንመልከታቸው።

 

1.  የባለሀብት ምልመላና የፍቃድ አሰጣጥ ስርዓት

ጥናቱ የባለሀብት ምልመላና የፍቃድ አሰጣጥ ስርዓትን በክልል ደረጃ በተመለከተ ያገኛቸው  መሰረታዊ ግድፈቶች፣ በክልሉ የግብርና ኢንቨስትመንት አዋጅ ያለ ቢሆንም ደንብና የማስፈጸሚያ መመሪያ አልተዘጋጀለትም፤ በባለሙያ ሳይጣሩና ሳያሟሉ ባለሃብቶችን የሚመለመሉበትና ፈቃድ የሚሰጥ አሰራር ተከትለዋል፤ ባለሀብቱ የሌላውን ባለሀብት ፕሮፖዛል ኮፒ ያቀርባል፤ ከበላይ አመራሩ በሚሰጥ የቃልም ሆነ የጽሁፍ ትእዛዝ የኢንቨስትመንት ፈቃድ ይሰጣል።

በፌደራል ደረጃ የተስተዋሉ ችግሮች ቢኖሩም የተሻሉ ናቸው ተብለዋል። ይኽውም፣ የምልመላ ችግር አለ ተብሎ ባይወሰድም በተግባር ግን ውጤታማ ሆነው አልተገኙም፤ የፍቃድ እድሳትና ስረዛ የሚከናወነው የባለሀብቱ የልማት ውጤት ያለበት ደረጃ በመስክ ጥናት ተረጋግጦ ሳይሆን ከክልሎች በሚላከው የባለሀብቱ አፈጻጸም ሪፖርት ላይ ተመስርቶ መሆኑን ክፍተት እንዳለው ተመላክቷል።

ተያያዥ ችግሮች ተደርገው የተነሱት፤ የምልመላና የፈቃድ አሰጣጥ ስርዓቱ ወጥነት አለመኖር፤ ብልሹ አሰራር መኖር፤ ከፈቃድ አሰጣጥ ተያይዞ ሰፊ ኪራይ ሰብሳቢነትና ህገ ወጥነት መኖር፤ የባንክ ብድር ለማግኘት  ሲባል ፈቃድ መስጠት፤ የድጋፍና ክትትል ስርዓት ያልተዘረጋለትና በተለይም በክልል ደረጃ የግልጽነትና ተጠያቂነት አለመኖር ተጠቃሽ ናቸው።

የባለሀብት ምልመላና የፍቃድ አሰጣጥ ስርዓትን በተመለከተ አጠቃላይ ምልከታውን ጥናቱ ሲያስቀምጥ፣ ከባለሃብት ምልመላ አኳያ በክልሉ ለግብርና ኢንቨስትመንት ያለውን አመችነትና የመንግስትን ድጋፍ በመጠቀም ተጨባጭ ልማት ለማምጣት የተሰማሩ ባለሃብቶች ቢኖሩም በአቋራጭ ለመበልጸግ የሚሰማሩም እንዳሉ ግንዛቤ ተወስዷል። እንዲሁም ባለሃብቶችን በተቀመጠው የምልመላ መመዘኛ መሰረት የሚመለመሉ እንዳሉ ሁሉ በተገቢ መንገድ ሳይመለመሉ የሚገቡ ባለሀብች መኖራቸውንና አሰራሩም ለኪራይ ሰብሰቢነት የተጋለጠ መሆኑ ተረጋግጧል።

እንዲሁም መረጃ ልውውጥና አያያዝ ስርዓት የሌለው፤ የቅንጅት ጉድለት ያለበት፤ የድጋፍና ክትትል ስርዓት ያልተዘረጋለትና በተለይም በክልል ደረጃ ደንብና መመሪያ ያልተዘጋጀና በግለሰቦች ፍላጎት ላይ ተመስርቶ የኢንቨስትመንት ፈቃድ የሚሰጥ በመሆኑ የግልጽነትና ተጠያቂነት ክፍተቶች ያሉበት መሆኑን ጥናቱ ያመለክታል።

 

2.  መሬት ማዘጋጀትና ማስተላለፍ

የመሬት ማዘጋጀት እና ማስተላለፍ ሥራዎች መሰረታዊ የሕግ ማዕቀፍ እንደሌላቸው ጥናቱ ያመለክታል። ይህም ሲባል፣ የመሬት ዝግጅት ስርዓት፣ የመሬት ጥናት ከተስማሚነትና ከአካባቢ ጥበቃ አንጻር አስቀድሞ የማስታቀረቅ ስራዎች አይሰሩም፤ ከረቂቅ ያለፈ የመሬት ጥናትና የህግ ማዕቀፍ የለም፤ የአቅም ውስንነት ይታያል፤ መሬት ማስተላለፍን በተመለከተ የመሬት ማስተላለፍ የህግ ማዕቀፍ የለም። በፌደራል ኮኦርድኔት ተሰጥቶት ባለሃብቱ ሲስማማ ይተላለፋል። በክልል መሬት በባለሃብቱ በግል በማፈላለግ ወይም በደላላ ጥቆማ ይተላለፋል። የመሬት ኪራይ ውል፤ መሬት ሳይዘጋጅ ውል ይፈረማል፤ በደላላ፣ በአመራርና ባለሙያ ጥቆማ መሬት ይፈለጋል፣ በአንድ ውል 2 እና 3 ቦታ ይሰጣል።

ጥናቱ የመሬት ኪራይ/ሊዝ ተመንና ዋጋ በተመለከተ አስገራሚ አሃዞችን አስቀምጧል። ይኽውም፣ ከ716 ባለሀብቶች ውስጥ 449 በሙሉ፣ 48 በተቆራረጠ ሁኔታ የከፈሉ እና 119 ምንም የኪራይ/የሊዝ ዋጋ ያልከፈሉ መሆናቸውን በጥናት ተረጋግጧል።

መሬት ማዘጋጀትና ማስተላለፍ ጋር በተያያዘ የተነሱ ተያያዥ ችግሮች አሉ። እነሱም፣ በከፍተኛ የይዞታ መደራረብ በሶስት መቶ ሰማንያ አንድ ሰነዶች ላይ ችግር አስከትሏል። አሰራሩ ለኪራይ ሰብሳቢነትና ለደላላ ትስስር የተጋለጠ በመሆኑ ለብልሹ አሰራር መፈጠር ከፍተኛ አስተዋፅዖ አበርክቷል። የአቅም ውስንነት እና የደንና ጥብቅ ቦታዎች ጉዳት አድርሷል። የሚሰጠው ውል መብትና ግዴት ያልጣለ መሆኑ በችግርነት ተነስቷል። 

በዚህ ዘርፍ በጣም አስገራሚው የይዞታ ካርታ አሰጣጥ ስርዓትን በተመለከተ የቀረበው የጥናት ውጤት ነው። ይኽውም የካርታ አሰጣጥ ስርዓት የለም። ይህም በመሆኑ ከ623 ባለሃብቶች ውስጥ 508 ባለሃብቶች የይዞታ ካርታ ያላቸው፤ 104 ባለሃብቶች የመሬት ይዞታ ካርታ የሌላቸውና 11 ምንም የሌላቸው ናቸው። ይህም ሆኖ፣ ካርታው የሚሰራው በቢሮ ሳይሆን በመኖሪያ ቤትና ጫት ቤት ውስጥ መሆኑ ይፋ ተደርጓል።

በመኖሪያ ቤትና በጫት ቤት የሚፈበረኩት ካርታዎች መዘዛቸው ቀላል አልነበረም። ይህም ሲባል፣ የ381 ባለሃብቶች 45,531.11 ሄ/ር መሬት ተደራርቦ ተገኝቷል። ከባለሃብቶች መሬት ከወረዳ ወረዳ መደራረብ ተከስቷል። በአንፃሩ ሲታይ፣ የአካባቢ ተወላጅ ባለሀብት ወደ ልማት ማስገባት የክልሉን ባከሃብቶች ለማበረታታት የሚያስችል የህግ ማእቀፍ የተሰራ የለም። ለክልሉ ባለሃብቶች በቂ የካፒታል ችግር አይቀርብላቸውም። የባንክ ብድር አይመቻችላቸውም። አመራሩ ለክልሉ ባለሃብቶች የሚሰጠው ድጋፍ አናሳ ነው ወይም የለም። ከሌላ ክልል የመጡ ግን በጣም ተጠቃሚዎች ናቸው።

 

3.  መሬቱን ወደ ልማት ማስገባት

በጋምቤላ ክልል ጥናቱ ካረጋገጠው እና የብዙዎቹን ትኩረት የወሰደው የተወሰደው መሬት ወደ ልማት አለምግባቱ ነው። ለዚህ ነጥብ በቂ ማሳያ የሚሆነው፣ 623 ባለሃብቶች 630,518 ሄ/ር መሬት ተረክበው ከወሰዱት መሬት ይለማል ተብሎ የተጠበቀው 405,572.84 ሄ/ር ቢሆንም የለማው መሬት መጠን 64,010.62 ሄ/ር ወይም 15.78 በመቶ ብቻ  መሆኑ፣ የመሬት ወረራ ከሚባለው አተረጓጓም ውጪ ለትርጉም አዳጋች የሆነ አሰራር ተደርጎ ቀርቧል።  የሚገርመው 369 ባለሃብቶች ማልማት ያልጀመሩ ሲሆኑ ከነዚህ ውስጥ 140 ምንጣሮ የጀመሩ መሆናቸው ነው።

እንዲሁም ልማት ከገቡት 254 ውስጥ 216 በውላቸው መሰረትና 38 ከውል ውጭ ያለሙ ናቸው፤ 152 ባለሃብቶች 3969.796 ሄ/ር መሬት ከይዞታቸው ውጭ አልምተዋል፤ በ2007 እና 2008 ዓ/ም 172 ባለሃብቶች መሬት የተረከቡ ሲሆኑ 31 በምንጣሮ ደረጃና 16 ልማት የጀመሩ ሲሆን ቀሪ 125 እንቅስቃሴ የላቸውም።

በእርሻ ቦታዎች የሚገነቡት ካምፖች አደረጃጀት ራሱን የቻለ አንድ የችግሩ ማሳያ ሆኖ ቀርቧል። ይህም ሲባል፣ ከ623 ባለሀብቶች 179 የተሟላ ካምፕ አላቸው፤ 95 ባለሀብቶች ዝቅተኛ የካምፕ አደረጃጀት ያላቸው ሲሆን 349  ባለሃብቶችምንም ካምፕ የላቸውም። እንዲሁም የካምፕ አደረጃጀታቸው በቆርቆሮና በሳር ጭምር የተሰሩ በመኖራቸው ጥራት የላቸውም ተብሏል።

ሌላው ለልማት ተብለው የእርሻ መሳሪያዎችን እንዲገዙ መንግስት ከፍተኛ እገዛ እንደሚያደርግላቸው የሚታወቅ ቢሆንም የጥናቱ ውጤት ግን አሳዛኝ ነው። ይኽውም፣ 226 ባለሀብቶች የእርሻ መሳሪያ ያላቸው ሲሆን 397 ባለሀብቶች (11 በቡና ልማትና 1 በንብ ማነብ የተሰማሩ ባለሃብቶችን ጨምሮ) የእርሻ መሳሪያ የሌላቸው ናቸው።

የስራ እድል ፈጠራ በተመለከተ የክልሉ ሕዝብ ተጠቃሚ አይደለም ማለት ይቻላል። ምክንያቱም ለ4776 ቋሚ ሠራተኞች የሥራ ዕድል የተፈጠረ ቢሆንም ከነባሩ ብሔረሰብ  483 (10.11 በመቶ) ብቻ ተጠቃሚ የሆኑት። ከሌላ ብሔር የመጡት 4293 ተጠቃሚ መሆን ችለዋል። ለዚህ መፋለስ በምክንያትነት የቀረበው የነባር ብሄረሰብ ተወላጆች በውስን ስራ ላይ የሚቀጠሩ መሆናቸውን ብቻ ነው።  

ባለሃብቱን ወደ ልማት እንዲገባ የሚደረገው ክትትል አነስተኛ መሆኑም ተጠቅሷል። ይሄውም፣ ለባለሃብቱ የሚደረግ ድጋፍና የክትትል አናሳ መሆን፤የባለድርሻ አካላት የቅንጅት ጉድለት ልማታዊ የሆኑትንና ያልሆኑትን ባለሃብቶች እየለዩ የማስተካከያ ርምጃ አለመውሰድ፤ በባለሃብቱ የሚታዩ ክፍተቶችን ለይቶ አለመፍታት ተጠቅሰዋል።

መሬቱን ወደ ልማት ለማስገባት የተለያዩ ችግሮች መኖራቸውም ተንስቷል። እነሱም፤ ከመሬት ይዞታቸው ጋር ተመጣጣኝ የሆነ የእርሻ መሳሪያዎች ዝግጅት አይታይባቸውም። የአካባቢው ብሄረሰብ ተወላጅ ሰራተኞች ቁጥር እጅግ በጣም ዝቅተኛ ነው። ከ623 ባለሃብቶች ውስጥ 369 ባለሃብቶች ወደ ተጨባጭ ልማት አለመግባታቸውና የማስተካከያ እርምጃ አለመወሰዱ፤ ወደ ልማት የገቡትም አፈጻጸማቸው 15 በመቶ ብቻ መሆኑ ተጠቅሷል።

መሬቱን ወደ ልማት ማስገባት አለመቻል ያስከተለውን ችግር በማጠቃላያ ሃሳብ ተካቶ ቀርቧል። ይኽውም፣ በሀገር ደረጃ የሚጠበቀው የግብርና ምርት በመጠንና በጥራት ካለመመረቱ ባሻገር ከኢንቨስትመንቱ በክልል ደረጃ የሚጠበቁ የስራ ዕድል ፈጠራ፣ የአካባቢ ገቢ ማዳበር የቴክኖሎጂ ሽግግር ማረጋገጥ አንጻር ኢንቨስትመንቱ ውጤታማ አለመሆኑን  ታውቋል።

 እንዲሁም በፌዴራልና በክልል እስከ ወረዳ የሚገኘው ሰፋፊ ግብርና ኢንቨስትመንትን የሚከታተልና የሚደግፍ መንግስታዊ መዋቅር የማስፈጸምና የመፈጸም አቅም ደካማ እንደሆነ በጥናቱ ተመላክቷል።

 

4.  ባለሃብቱ የቀረጥ ነፃና ታክስ ተጠቃሚነት

የባለሀብቱ የቀረጥ ነፃና ታክስ ተጠቃሚነትን በተመለከተ ከእውቀት ማነስ ይሁን ሆን ተብሎ ለኪራይ ሰብሳቢነት በር ለመክፈት ግልፅ ነገር የለም። ምክንያቱም፣ የወጣውን ደንብ ለማስፈጸም ከተሽከርካሪ በስተቀር ለሌሎች እቃዎች የአፈጻጸም መመሪያ አለመዘጋጀቱን ጥናቱ ይፋ በማድረጉ ነው።

ሌላው ከቀረጥ ነፃ ያስገቡ ባላሀብቶች ብዛት 242 ቢሆኑም በመስክ የተገኙ የቀረጥ ነፃ ተጠቃሚ የባለሀብቶች ብዛት 225 መሆናቸው አነጋጋሪ ነጥብ ነው። እንዲሁም የቀረጥ ነጻ የገቡ መሳሪያዎችና ተሽከርካሪዎች ውስጥ በመስክ ያልተገኙ አሉ፤ ከያዙት መሬት መጠን በላይ ትራክተር ያስገቡ አሉ። በፌደራል ኢንቨስትመንት ኮሚሽን፣ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለስልጣንና በክልል ኢንቨስትመንት ኤጀንሲ የቀረጥ ነፃ አሰራር፤ የክትትል፣ የቁጥጥር እና የመረጃ አያያዝ ችግሮች ታይተዋል። የቀረጥ ነጻ ድጋፍ ደብዳቤ ወጥነት የሌላቸው መሆኑ የአሠራር ክፍተት ፈጥሯል።

የቀረጥ ነፃና ታክስ ጋር በተያያዘ የተለያዩ ችግሮች መኖራቸው በጥናቱ ቀርቧል። እነሱም፣ አሰራሩ ለኪራይ ሰብሳቢነት የተመቻቸ እንዲሆን ዳርጎታል። በቀረጥ ነፃ ፈቃድ የገቡ የካፒታል እቃዎች ከታለመለት ዓላማ ውጭ መዋላቸው ተረጋግጧል።

የባለሀብቱን የቀረጥ ነፃና ታክስ ተጠቃሚነትን በተመለከተ በጥናቱ ላይ የቀረበው የማጠቃላያ ሃሳብ እንደሚያሳየው፣ የታክስና ቀረጥ ማበረታቻ ደንብ ከተሽከርካሪ በስተቀር ግልፅ የሆነ የአፈጻጸም መመሪያ የተዘጋጀለት ባለመሆኑ ለኪራይ ሰብሳቢነት የተመቻቸ እንዲሆን አድርጎታል። ከቀረጥ ነፃ የገቡ እቃዎች ከኤጀንሲው ከተወሰደና በመስክ ከተገኘ ቁጥር ልዩነት ያለው ሲሆን ይህም የቀረጥ-ነፃ ተጠቃሚዎች መረጃ አያያዝ ስርዓት ክፍተት እንዳለበት አሳይቷል። ከቀረጥ ነፃ የገቡ የተወሰኑ እቃዎች በክትትል ማነስ ምክንያት በእርሻው ውስጥ ያልተገኙና ለታለመለት ዓላማ እየዋሉ አለመሆናቸው ተረጋግጧል።

 

 

5.  የባንክ ብድር አሰጣጥ

በጋምቤላ ክልል የባንክ ብድር አሰጣጥ ስርዓት የተቀራማች ቢሮክራሲ (patronage bureaucracy) ነጸብራቅ ዋነኛ ማሳያ መሆኑን ጥናቱ በግልፅ አመላክቷል። ይህም ሲባል፣ የብድር አሠጣጡ ስርዓት የተዘረጋለት ቢሆንም መንግስት ተገቢውን ውጤት ማግኘት አለመቻሉ በማሳያነት ቀርቧል። ለምሳሌ ጥናቱ እንደሚያሳየው፣ ለ200 ባለሃብቶች (12 በንግድ ባንክና 188 በልማት ባንክ) ብድር ተሰጥቷል። በአሃዝ ሲቀመጥም 4.96 ቢሊዮን ብር ተፈቅዶ 4.27 ቢሊዮን ብር ለባለሃብቶች ተለቋል።  

መንግስት ባለሃብቶችን ለማገዝ ይህንን ያህል እርቀት ቢሄድም ውጤቱ ዝቅተኛ ነው። ወይም ከሚጠበቀው በታች ነው። ለዚህ ውጤት መውደቅ የሚሰጡ ምክንያቶች፣ የፖሊሲ መቀያየርና የደንበኞች መጉላላት፤ አቀባባይ ደላሎች መበራከት፤ የባለሙያዎች የስነ-ምግባር ብልሹነት፤ ለብድር የተሰጠው ገንዘብ ስራ ላይ መዋሉን አለመዋሉን አለመከታተል፤ የግምት ሥራዎች በተለይም “Land Development Cost Estimation” እጅግ የተጋነነ መሆን ከቀረቡት ምክንያቶች ተጠቅሽ ናቸው።

እዚህ ላይ መታየት ያለበት ቁልፉ ነጥብ የባንክ ብድር እና የመሬት ልማት እንዴት ይገለፃሉ የሚለው ነው። ወይም የተለቀቀው ብድር እና የለማው መሬት በተነፃፃሪነት እንዴት ይቀመጣሉ? ጥናቱ እንደሚያሳየው፤ የባንክ ተበዳሪ ለሆኑት 194 ባለሃብቶች 1 ቢሊየን 994 ሚሊየን 408 ሺህ 174 ብር ተለቆላቸው 314,645 ሄ/ር መሬት እንዲለማ ሲጠበቅ የለማ መሬት 55,129 ሄ/ር (18 በመቶ) ብቻ መሆኑን ነው። እንዲሁም 47,139 ሄ/ር መሬት በምንጣሮ ደረጃ ላይ ይገኛል። ምንጣሮን ጨምሮ 33 በመቶ ይሆናል። የባንክ ተበዳሪ ከሆኑት ውስጥ 30 ባለሃብት በጣም ደካማ ናቸው። እንዲሁም የ104 ተበዳሪዎች 27,155.89 ሄ/ር መሬት የካርታ መደራረብ ታይቶባቸዋል። በየትኞቹ ካርታዎች ብድሩ ከባንክ እንደወጣ የጥናት ሰነድ አይገልፅም።    

ከዚህም በተጨማሪ የባንክ ብድርና ካምፕ አደረጃጀት በተመለከተ አሳዛኝ መረጃ ነው የቀረበው። ይኽውም፤ ለ175 ባለሃብቶች የተለቀቀው የገንዘብ መጠን ብር 326 ማሊየን 876 ሺህ 702 ሲሆን ከእነዚህ 200 ተበዳሪ ባለሃብቶች መካከል 180 ቋሚ፤ 19 ጊዜያዊ ካምፕና አንድ ምንም ካምፕ የሌለው ተገኝተዋል። ሆኖም ዝቅተኛ ካምፕ ያላቸው በእንጨትና ቆርቆሮ፣ በእንጨትና በሳር የተገነቡ ሲሆን በቂ አገልግሎት የማይሰጡ ናቸው።

በተመሳሳይ ሁኔታም የባንክ ብድርና የእርሻ መሳሪያዎችን የተመለከተው ጥናት አስገራሚ ነው። ይህም ሲባል፤ 112 ከልማት ባንክና 11 ባለሃብቶች ከንግድ ባንክ ለትራክተር/ማሽነሪ መግዥያ ብር 592 ሚሊየን 474 ሺህ 521 ተለቆላቸዋል፤ 251 ትራክተሮች የተገዙ ሲሆን በመስክ ምልከታ 244 ትራክተሮች ተገኝተዋል። 6 ከልማት ባንክና 1 ከንግድ ባንክ በድምሩ 7 ትራክተሮች በመስክ እይታ ያልተገኙ ናቸው።

 የባንክ ብድርና ተሽከርካሪ በተመለከተም ተመሳሳይ ሲሆን፤ ለ110 ባለሃብቶች ለተሸከርካሪዎች ብር 191 ሚሊየን 673 ሺህ 038 በባንኮች ብድር  ተለቆላቸዋል። 184 ተሸከርካሪዎች ተገዝተው 159 በመስክ የተገኙ ሲሆን 25 በመስክ ያልተገኙ ናቸው። በተያያዘም የተለያዩ ችግሮች መኖራቸው ተጠቅሷል። እነሱም፤ ኪራይ ሰብሳቢነት መኖር፤ብድሩ በሚፈለገው ደረጃ ለታለመለት ዓላማ አለመዋሉ፤ በባለሃብቶች ለልማት ሳይሆን የባንክ ብድር ለማገኘት ወደ ዘርፉ የመግባት አመለካከት መያዝ፤ የመሬት ይዞታ ካርታ መደራረብ፤ አድሎአዊነት (የክልል ተወላጆችን ተጠቃሚ አለመሆን) ከሚጠቀሱት መካከል ናቸው።

በባንክ ብድር አሰጣጥ ላይ የጥናት ሰነዱ ያስቀመጠው ማጠቃለያ የልማት ባንኩ የሥራ ኃላፊዎች ከተጠያቂነት እንደማያመልጡ አመላካች ነው። ይኽውም፣ በክትትልና ድጋፍ ጉድለት በአንዳንድ ባለሀብቶች ለመሬት ልማት፣ ለህንፃ ግንባታ፣ ለማሽነሪ፣ ለተሽከርካሪና ለስራ ማስኬጃ የወሰዱት ብድር ለታለመለት ዓላማ እንዳልዋለ ተረጋግጧል፤ የኢትዮጵያ ልማት ባንክ የብድር አሰጣጥ ለኪራይ ስብሳቢዎች እና ለደላሎች የተጋለጠ በመሆኑ የብድር አሰጣጡ ፍትሀዊ አለመሆኑ ተረጋግጧል። እንዲሁም በመሬት የይዞታ ካርታ መደራረብ ችግር ምክንያት ባንኮች የተፈቀደውን ብድር በወቅቱ ለባለሀብቱ እንደማይለቀቅለት ጥናቱ ያሳያል።

እንደመውጫ በጠቅላይ ሚኒስትሩ ተነሳሽነት የተደረገው ጥናት በየትኛውም መመዘኛ ተቀባይነቱ ከፍ ያለ ነው። በተለይ በዚህ ጥናት የልማት ባንኩ የሥራ ኃላፊዎች፣ የጋምቤላ ክልል የፖለቲካ አመራሮች እና ባለሃብቶች በዘረጉት የቢሮክራሲ ሰንሰለት የሃገር ሃብትን እንዴት ሲቀራመቱት እንደነበር ቁልጭ አድርጐ የሚያሳይ ነው።

በተዘረጋው ተቀራማች የቢሮክራሲ ሰንሰለት ውስጥ ተሳታፊ የሆኑ ኃይሎችን ለሕግ ማቅረብ እና የሕዝብና የመንግስትን ሀብት ማስመለስ ቀጣይ ሥራ መሆን አለበት።

ከጋምቤላ የኢንቨስተሮች ማኅበር አመራር አባል የሆኑት አቶ የማነ አሰፋ የቀረበው የጥናት ሰነድ ባለሃብቶችን ያላካተተ በመሆኑ እንደማይቀበሉት አስታውቀዋል። ወደ ጋምቤላ የተጓዘው ባለሃብት የመንግስት ፖሊሲና ስትራቴጂን ተቀብሎ እንጂ ለመሬት ወረራ አለመሆኑ ሊታወቅ ይገባል ብለዋል።

አያይዘውም፣ “ከ2001 እስከ 2005 ድረስ የባንክ ብድር አልነበረም። ችግሮች እየተወሳሰቡ የመጡት ከ2005 በኋላ የባንክ ብድር ሲጀመር መሆኑ መታወቅ አለበት። ባለሃብቱ ከመንግስት ድጋፍ ውጪ ያለማው መሬት ዛሬ የመሬት ወረራ መባሉ ተቀባይነት የለውም። የሚወሰደውም ብድር በሔክታር 40 በ60 ነው። ሲጀመር በሔክታር 8ሺ ብር ሲሆን በሂደት በተደረገው ጥናት ከ43 እስከ 45ሺ ብር ደርሷል። ከሚወሰደው ብድር 80 በመቶ የሚሆነው ለቋሚ ንብረት ግዢ ነው የሚውለው። ትራክተር መግዣ፣ ለመሬት ልማት መኪና መግዣ፣ ካምፕ ግንባታዎች ላይ ነው የሚውለው። ቀሪው 20 በመቶ የሚሆነውም ብድር ስድስት ጊዜ ተከፋፍሎ ነው የሚሰጠው። ከ20 በመቶ ውስጥ ምን ያህሉ ገንዘብ ተርፎ ነው በአዲስ አበባ እና በመቀሌ ፎቅ ቤቶች የሚሰሩት ሲሉ” አቶ የማነ ጥያቄ አዘል አስተያየታቸውን ሰንዝረዋል።

አያይዘውም፤ ሕግ ባለበት ሀገር፣ ሥርዓት ባለበት ሀገር ውስጥ ያጠፋው ለይቶ መቅጣት እየተቻለ የአንድ ክልል ስም ለማጥፋት መሞከር ተቀባይነት የሌለው ተግባር መሆኑን ተናግረዋል።

ሌሎች ተሳታፊ ባለሃብቶችም ተመሳሳይ ቅሬታ በመድረኩ ላይ አቅርበዋል። መጀመሪያ የመንግስት ድጋፍ ይቅደም ሲሉም ጠይቀዋል። ¾

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
677 ጊዜ ተነበዋል

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us