“የቀድሞው የኢትዮጵያ ማዕድን ልማት አክስዮን ማኅበር የመንግስት ልማት ድርጅት የሥራ ኃላፊዎች በሕግ እንዲጠየቁልን”

Wednesday, 11 January 2017 14:41

“የቀድሞው የኢትዮጵያ ማዕድን ልማት አክስዮን ማኅበር

የመንግስት ልማት ድርጅት የሥራ ኃላፊዎች በሕግ እንዲጠየቁልን”

የታንታለም ዶሎማይት አምራች ሠራተኞች

“በቂ መረጃ ከቀረበልን በሕግ እንዲጠየቁ እናደርጋለን”

አቶ ሙሉጌታ ሰዒድ

የቀድሞው ዋናዳሬክተር ዶክተር ዘሪሁን ደስታ በጡረታ ተገለዋል

የፋይናንስ ዳሬክተሩ አቶ ፋሲል ሸዋረጋ ወደ አሜሪካ ኮብልለዋል

የተቋሙ ዳራ

“ተቋም” በ1982 ዓ.ም. የተቋቋመ ሲሆን በኢትዮጵያ የማዕድን ዘርፍ የማምረት አቅምን ለመጨመር የተቻለውን ከነውስንነቱ አበርክቷል።የተቋሙ ሌላ መገለጫ፣ በኢትዮጵያ ውስጥ ከፍተኛ የትውውቅ ትስስር ከጠለፋቸው መስሪያቤቶች በግንባር ቀደምትነት ከሚጠቀሱት መካከል አንዱ የቀድሞው የኢትዮጵያ ማዕድን አክሲዮን ማሕበር ነው።

 

የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ መለስ ዜናዊ የታንታለም ድንጋይ ዕሴት ሳይጨመርበት ወደ ውጪ ገበያ እንዳይቀርብ መመሪያ ማስተላለፋቸውን ተከትሎ፣ መንግስት ማዕድኖችን በጥሬው ለዓለም ገበያ ከማዋል ዕሴት ጨምሮ ለውጭ ገበያ እንዲቀርቡ ግልፅ ስትራቴጂ ነድፎ መንቀሳቀስ ከጀመረ ቆየት ብሏል።እንዲሁም ከኢኮኖሚና ከደህንነት አንፃር ስትራቴጂክ ማዕድኖች ተብለው ከሚቀመጡት መካከል አንዱ የታንታለም ማዕድንመሆኑ ተለይቶ ተቀምጧል።

 

ይህንን ማዕድን ዕሴት ጨምሮ ለውጪ ገበያ ለማቅረብ የሚያስችል ቴክኖሎጂን ወደ ሀገር ውስጥ ለማስገባት በመንግስት የልማት ድርጅቶች ተቆጣጣሪ ኤጀንሲ በኩል ከፍተኛ ጥረት መደረጉ አይዘነጋም። ተወዳዳሪ ኩባንያዎች ላለመቅረባቸው ኤጀንሲው ብዙ ምክንያቶች ሊያቀርብ ቢችልም ዋናው ምክንያቱ ግን፣ ከመንግስት ፍላጎት በላይ የአንዳንድ ግለሰቦች ፍላጎት ገዝፎ መውጣት መሆኑን ከዚህ በፊት ባሰፈርናቸው ጽሁፎች ማሳየት ችለናል።

 

የቀድሞ የተቋሙ ኃላፊዎች ከፈጸሙት ስህተት ሳይጠቀስ የማይታለፈው፣ በኢትዮጵያ ማዕድን ልማት አክሲዮን ማሕበር በ15 ሚሊዮን ብር የተጠና የአዋጪነት ሰነድን፣ የእስራኤሉ ኤሌኒቶ ኩባንያ በራሱ ተቋም የተጠና አድርጎ ከመንግስት አካሎች ለድርድር የቀረበበት አስደጋጭ ክስተት ነው።ይህንን 15 ሚሊዮን ብር የሚገመት የመንግስትን የአዋጪነት ጥናት ሰነድ ለኤሌኒቶ አሳልፎ የሰጠ አካል እስካሁን በኃላፊነት የተጠየቀ የለም። በኢትዮጵያ ማዕድን ልማት አክሲዮን ማሕበር ዋና ሥራአስኪያጅ የነበሩት ዶክተር ዘሪሁን ደስታ፣ ለሰንደቅ ጋዜጣ በፃፉት ደብዳቤ “ከአክሲዮን ማሕበሩ ባልታወቀ መንገድ ካለፈቃድ ተወስዶ እንደራሱ አድርጎ አቅርቦ ነበር” ከማለታቸው ውጪ ተጠያቂ ያደረጉት አካል የለም።

 

ሌላው ተጠቃሽ ምንአልባትም በጣም አሳፋሪ የተቋሙ ታሪክ፣ በቀድሞ በማዕድን ሚኒስትሩበአቶ ቶሎሳ ሻጊ የሚመሩ የመንግስት የተለያዩ መስሪያቤቶች ተወካዮች እና ባለሙያዎች የተካተቱበት አጥኝ ቡድንከአንድ ከአውስትራሊያ ኩባንያ ጋር ለረጅም ጊዜ ውይይት አድርጎ ሰነዶችን ፈትሸው ኩባንያው፣ ከፋይናንስ፣ ከቴክኖሎጂ እና ከልምድ አንፃር በኢትዮጵያ ውስጥ ታንታለምን ማልማት የሚችል ሙሉ አቅም ያለው መሆኑን አረጋግጠው ለጠቅላይ ሚኒስትር ኃ/ማሪያም ደሳለኝ ሪፖርት አድርገው፤የቀድሞው የኢትዮጵያ ማዕድን ልማት አክሲዮን ማሕበር አዲስ በተዋቀረው በኢትዮጵያ ፌደራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ የመንግስት የልማት ድርጅቶች ሚኒስቴር ስር ሆነው ጥናቱን ወደተግባር እንዳይገባ የተቻለውን ሁሉ በማድረግ ተሳክቶላቸዋል።

 

በድጋሚ ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ኃ/ማሪያም ደሳለኝ ለቀድሞዋ ለመንግስት የልማት ድርጅቶች ሚኒስትር ለወ/ሮ ደሚቱ ሃምቢሳ ቦንሳ በሰጡት መመሪያ ከአውስትራሊያው ኩባንያ ጋር ታንታለምን ለማልማት መስሪያቤታቸው ድርድር እንዲያደርግ ማዘዛቸው የሚታወስ ነው። ሚኒስትሯም በቀጥታ ወደ ድርድርከመግባታቸው በፊት በአዲስ መልክ የአውስትራሊያውን ኩባንያ እንዲጠና መመሪያ ወደታች አውርደው ነበር።ሚኒስትሯም፣ ባዋቀሩት የጥናት ቡድንየአውስትራሊያው ኩባንያ ታንታለም ለማልማት የሚችል ዓለም ዓቀፍ ደረጃውን የጠበቀ መሆኑ አረጋግጠዋል።

 

ጥናቱን መነሻ በማድረግ የመንግስት የልማት ድርጅቶች ሚኒስቴር ዴኤታ የነበሩት አቶ ቶሎሳ፣ የአውስትራሊያው ኩባንያ ዕሴት ለመጨመር ያለውን ዕቅድ እና አምርቶም ወደ ውጭ ገበያ ለመላክ ያለውን ቁርጠኝነት እንደሚያደንቁ ጠቅሰው ይፋዊ የሆነ ድርድር ከኩባንያው ጋር መንግስት ማድረግ እንደሚፈልግ በደብዳቤ ጽፈው ለኩባንያዊ አሳውቀዋል።እንዲሁም ለኢትዮጵያ ማዕድን ፔትሮሊየም እና ባዮ ፊውል ኮርፖሬሽን መስሪያቤት የመደራደሪያ ነጥቦችን በፍጥነት እንዲያዘጋጅ በግልባጭ አስታውቀዋል።ኩባንያው በበኩሉ ለይፋዊ ድርድር መጠራቱ እንዳስደሰተው ገልፆ አዲስ አበባ በመገኘት ለድርድር ዝግጁ መሆኑን አስታውቋል።ሆኖም አሁን ከኃላፊነት ላይ የተገለሉት የሥራ ኃላፊዎች የሚኒስትሯን የጥናት ሰነድ ወደ ተግባር እንዳይለወጥ አድርገው መሥሪያቤቱን ለቀዋል።ከመንግስት ፍላጎት በላይ የአንዳንድ ግለሰቦች ፍላጎት ገዝፎ መውጣት የለውጥ ሒደቱን ቆልፎ ይዞታል።ጠቅላይ ሚኒስትር ኃ/ማርያም ደሳለኝ የሰጡትስ የአቅጣጫ መመሪያም ውኃ በልቶት እንዲቀር የተቻላቸውን አድርገው ተቋሙን ለቀዋል፡፡

 

እነዚህ የልማት ማነቆዎች ባሉበት ሁኔታ የታንታለም ዶሎማይት ፊልድስፓርና ኳርትዝ አምራቾች የመንግስት ያለህ? ሲሉ ቅሬታቸውን ለአደባባይ ያበቁት። የሠራተኞቹ ደብዳቤ እንደሚከተለው ነው።

 

አንድ የመንግስት ልማት ድርጅት ወይም መስሪያ ቤት የሀገሪቱን ሕግና ደንብ ብሎም የሃገሪቱን ሕገ-መንግስታዊ ስርዓት ማክበር መተግበር እና የዜጎችን ሰብአዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶችን ማክበር ግዴታ እንዳለበት ሕገመንግስቱ ይደነግጋል። ይህ ማለት የሃገሪቱን መተዳደሪያ የሆነው ብሔር ብሔረሰቦች ህዝቦች ወደውና ፈቅደው ያፀደቁትን ሕገመንግስት ማክበር ብሎም ለሃገሪቱ ሕግና ስርዓት ተገዢ መሆን እንዳለበት በግልጽ ይገልፃል። አለበለዚያ ይህ ድርጅት ወይም መስሪያ ቤት የመንግስት የልማት ድርጅት ወይም ተቋም ሳይሆን ተቋሙ የፖለቲካ ፓርቲ ድርጅት ነው ማለት ነው።

 

መንግስት ላቀዳቸው ልማት የሠላም፣ የዴሞክራሲና የመልካም አስተዳደር ስራዎች ለህዝቡ ለማጎናፀፍ በየደረጃ ተጠቃሚ ለማድረግ ሀገራችን ከበለፀጉት ሀገሮች ተርታ ለማሰለፍ ሌት ተቀን ደፋ ቀና እያለች ባለችበት በአሁኑ ሰዓት፣ ዜጎችን ለእንግልት ለከፍተኛ ወጪና በመንግስት ላይ አመኔታ እንዲያጡ ኑሮአቸውንም በትክክል እንዳይመሩ፣ ቤተሰባቸውን በአግባቡ እንዳያስተዳድሩ ሳይፈልጉ ተገደው ወደ ክስ እንዲገቡ፣ በየመንገዱ በየፍርድ ቤቱ በማመላለስ ለከፍተኛ ወጪ እንዲዳረጉ ሆነዋል።

 

ከሁሉ በላይ ሰራተኛው በመንግስት ላይ አመኔታ እንዲያጣ፣ የልማት የሰላም እና የዴሞክራሲ ትሩፋቶችን እንዳያገኝ እንዲጎሳቆል አድርገዋል። ድብቅ የፖለቲካ አጀንዳቸውን በመፈፀም መንግስትና ህዝብ የሰጣቸው ኃለፊነት ወደ ጎን በመተው የግል ጥቅማቸውንና ክብራቸውን በማሳደድ ለሕገ-ወጥ ዓላማ በማዋል፣ መስሪያቤቱን ለሕገወጥ አሰራር እንዲጋለጥ፣ በተለያየ መንገድ የመንግስትና የህዝብ ሃብት ገንዘብ ለራሳቸው ሀብት ማከማቻ እያደረጉ የሰራተኛውን መብትና ጥቅም በሕገወጥ መንገድ በማፈን ስርዓት አልበኝነት እንዲስፋፋ፣ የኢንዱስትሪ ሰላም እንዲያጣ፣ ሕግና ሥርዓት እንዲጣስ በማድረግ ግንባር ቀደም በሚና ነበራቸው።

 

ሰራተኛው መብቱን እንዳይጠይቅ ሲያሻቸው በመቅጣት፣ በማባረር፣ ደረጃውን በመቀነስ፣ ካሻቸውም በዝውውር በማንገላታት በማዋከብ ስራውን ኑሮውን በትክክል እንዳይኖር፣ እንዳይሰራ አድርገዋል። መብቱን ጠይቆ ምላሽ ሲያጣ ፍትህ ፍለጋ በመመላለስ ያለ የሌለ አቅሙን ለትራንስፖርት፣ ለጠበቃ ወጪ፣ ለፎቶ ኮፒ እናም ለትርጉም እንዲያወጣ አድርገውታል። ጉዳዩ ተገቢ ሆኖ ሳለ ፍትሐዊ ጥያቄ መሆኑን እያወቁ፣ ይግባኝ በመጠየቅ የሰራተኛውን ኑሮ ከማጎሳቆልም ባሻገር የመንግስትና የሕዝብ ሐብት ገንዘብ ያለአግባብ ፍርድ ቤት ጉዳይ ማስፈፀሚያ በማድረግ፣ ዳኞችን በተለያየ ጥቅማ ጥቅም በመደለል በማታለል ሰራተኛው እንዲጎሳቆል በማድረግ፣ የህዝብና የመንግስት ሀብት አላስፈላጊ በሆነ መልኩ እንዲባክን አድርገዋል። አምራች ኃይል ሰራተኛው ከማምረት ይልቅ ፍርድ ቤት በመመላለስ የሥራ ጊዜውን ፍትሕ ፍለጋ እንዲመላለስ አድርገውታል።

 

ከዚህም ባሻገር የሥራ ኃላፊዎቹ ዓላማና ግብ ድብቅ የፖለቲካ ዓላማ በመሆኑ ሕግን በማጣቀስ ሕጋዊ በመምሰል አላማቸውን ውጥናቸውን የሕግ ሽፋን በመጠቀም ዘረፋና ብልሹ አሰራርን ምርጫቸው አድርገው ከታች እስከ ላይ ሰንሰለት በማበጀት የመንግስት ልማት ድርጅት ታርጋ በመለጠፍ የዓላማቸው ማሳኪያ ቁልፍ መሳሪያ አድርገው ወንጀል በመስራት ሰራተኛውን ለእንግልት ለድህነት በመዳረግ ሰራተኛው ለፍቶ ያገኘውን ሀብቱን ለፍርድ ቤት ለጠበቃ ውክልና ለትራንስፖርት ወጪ ተዳርጓል።

 

በዚህም ምክንያት ኑሮን በትክክል እንዳይመራ አድርገውት ችግር ውስጥ ይገኛል። ለዚህም በቂ ማስረጃ እራሱ ሰራተኛ ቢሆንም የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት የምስራቅ ሸዋ አሰሪና ሰራተኛ ወሳኝ እውነታ ቦርድ፣ የጉጂ ዞን ቦረና ፍርድ ቤት የሰባ በሶሩ ወረዳ ፍርድ ቤት እና ሂርባ ሙዳ ወረዳ ፍርድ ቤት አብይ ምስክሮች ናቸው። ያለማጋነንም ዓመቱን ሙሉ ፍርድቤቶቹን ሌላውን ማኅበረሰብ ማገልገል ትተው የኢትዮጵያ ማዕድን ልማት አክሲዮን ማኅበር ሰራተኞችን አቤቱታ ከማዳመጥ ውጪ ለሌላ ማኅበረሰብ የፍትሕ አገልግሎት ለመስጠት ጊዜ የላቸውም። ምክንያቱም ቁጥሩ እጅግ በጣም ብዙ ሰራተኛ በእነዚህ ፍርድ ቤቶች በየቀኑ በየሳምንቱ በቀጠሮ ስለሚመላለስ ለፍርድ ቤቶቹ ከፍተኛ ጫና ፈጥሮባቸዋል።

 

ስለዚህ የሚመለከተው የመንግስት አካል ችግሩ ሥር የሰደደና ረጅም ጊዜ የቆየ በመሆኑ ተገቢው ክትትል ተደርጎ አፋጣኝ ምላሽ መሰጠት ይገባዋል። የመስሪያ ቤቱ አሰራር በብልሹ አሰራር ለሕገ-ወጥነት የተጋለጠና ግልፀኝነት፣ ፍትሐዊነት፣ ተጠያቂነት የጎደለው ከመሆኑ በላይ አንባገነንነት የተሞላበት አመራሩ ከላይ እስከታች በየደረጃው የአሰራር አደረጃጀት ችግር ያለበት ሲሆን፤ ከዛም ባሻገር የህዝብና የመንግስት ሃብት ንብረት ያለአግባብ በመጠቀም የግል ጥቅማቸውን በማሳደድ ሙሉ ጊዜያቸውን አሳልፈዋል። እያሳለፉም ይገኛሉ። የኢትዮጵያ ማዕድን ልማት አክሲዮን ማኅበር የመንግስት ልማት ድርጅት ለሃገር ለህዝብ እንዲጠቅም ካስፈለገ በግልፀኝነት ሁሉንም ያማከለ የአሰራር የአደረጃጀት እና ተጠያቂነት ያለው ሊሆን ይገባል። አሁን በዚህ መስሪያ ቤት ያለው ሃቅ ግን ከዚህ በተቃራኒ ነው።

 

በአጠቃላይ መስሪያ ቤቱ በብልሹ አሰራር የተተበተበ የተዘፈቀ መልካም አስተዳደር ፈጽሞ የጎደለበት ዝርክርክነትና ሕገወጥነት የሞላበት በአድሎአዊ አሰራር የተተበተበ፣ በመንግስት ልማት ድርጅት ስም ሕገወጥ ተግባር የሚፈፀምበት፣ የብዙሃኑ መብት የተረገጠበት፣ የታፈነበት የዜጎች ሰብአዊና ዴሞክራሲያዊ መብት የሚጣስበት፣ የእኩልነት የፍትሕ ጉድለት የሚታይበት የሚፈፀምበት፣ ለግል ጥቅም ብቻ ቅድሚያ የሚሰጥበት፣ የሃይማኖት የብሔር እኩልነት የሚጣስበት፣ ሙስና እንደ ሕጋዊ አሰራር የሚሰራበት የሚፈፀምበት የሚታይበት፣ ከሁሉም በላይ ለሃገሪቱ ሕግና ሥርዓት ብሎም ለሕገመንግስታዊ ስርዓት የማይገዛ ስልጣንን ያለአግባብ በመጠቀም የዜጎችን ሰብአዊና ዴሞክራሲያዊ መብት የሚጣስበት የሚጨፈለቅበት የሕዝብና የመንግስት ሃብት ያለአግባብ የግለሰቦች መጠቀሚያ ማበልፀጊያ የሆነበት ሲሆን፤ ዜጎች ያለአግባብ ከስራቸው የሚባረሩበት የሚፈናቀሉበት ሕገወጥ መስሪያቤት ነው።

 

በአጠቃላይ ይህ ሕገወጥ አሰራር ሃገርን ሕዝብን መንግስትን የሚጎዳ ከመሆኑም ባሻገር ልማትን የሚያደናቅፍ ዓላማ ስለሆነ የሚመለከተው የመንግስት አካል ጉዳዩን በሚገባ አጣርቶ በነዚህ ሥራ ኃላፊዎች ላይ ተገቢውን እርምጃ መውሰድ አለበት እንላለን። (ከሰላምታ ጋር)

 

ከሠራተኞቹ ቅሬታ ጋር በተያያዘ ያነጋገርናቸው የኢትዮጵያ ማዕድን ፔትሮሊየም እና ባዮ ፊውል ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ ሙሉጌታ ሰዒድ ከሰራተኞቹ የተነሱትን ቅሬታዎች እንደሚያውቁት በመግለጽ ለሰንደቅ በሰጡት ማብራሪያ፣ “ሠራተኛ ማሕበር አልነበራቸውም፤ እንዲደራጁ ማሕበር እንዲመሰርቱ አድርገናል። ቅሬታ ካቀረቡት መካከል በድርድር የፈታነው አለ። ሌሎች ቅሬታዎችን መብታቸው በመሆኑ በፍርድ ቤት እየታየላቸው ይገኛል። በመሰረታዊነት ግን ቅሬታቸው የነበረው የደሞዝ ማስተካከያ ጥያቄ ነው። በእኛ በኩል ባደረግነው ጥናት ደሞዛቸው በጣም ዝቅተኛ መሆኑን ተረድተናል። በጥናቱ መሰረት ማሻሻያ አድርገን ለማስተካከል እየጠበቅን ነው። ከሠራተኛው በኩል ያለው ቅሬታ ዘገየ የሚል ነው” ብለዋል።

 

“ሠራተኞቹ የፋይናንስ ኃላፊው መጥፋት ከእኛ እንቅስቃሴ ጋር የተገናኘነው ይላሉ፣ መጋዘን ተሰብሮም የተዘረፈ የታንታለም ምርት አለ፡፡ በፀረ-ሙስና ኮሚሽን ጉዳዩ እየተመረመረ ይገኛል ብለዋል፡፡ መኪናዎች ሳያራጁ በጨረታ እንዲሸጡ ተደርገዋል፡፡” በዚህ ላይ ምን ምላሽ አልዎት? ተብለው ተጠይቀው በሰጡት ምላሽ፣ “አቶ ፋሲል ሸዋረጋ ፈቃድ ጠይቆ ነው የሄደው። ከፀረ ሙስና ጋር ተያይዞ የተነሳው ከዛሬ ስምንት ዓመት በፊት መጋዘን ተሰብሮ ተሰረቀ ተብሎ ማጣራት ሲደረግበት ነበር። በፌደራልና በኦሮሚያ ፀረ ሙስና ተቋማት እንዲሁም በኦሮሚያ ፍትህ ቢሮ በኩል ሲታይ የነበረ ቢሆንም በመረጃው ውስብስብነት በወቅቱ በነበረው ችግር ውጤታማ መሆን አልቻለም። በእኛ በኩል እያደረግነው ያለነውም ከምን ደረሰ እያልን እየጠየቅ ነው። ሠራተኛው ስላነሳው ሳይሆን ለምን ውጤቱ አልተገለጸም የሚለውን እየሄድንበት ነው ያለው። ውጤቱ መታወቅ አለበት። ተጠያቂ ሰው ካለም መጠየቅ አለበት። ይህንን እየገፋነው ነው ያለው።”

 

አያይዘውም፣ ተቋሙን የፀረ ሙስና ተቋም እንዲመረምርልን አድርገን የሰጡት ውጤት አለን። እንደሚባለው ሳይሆን የንብረት አያያዝ መስተካከል እንዳለበት አስታውቀውናል። የተለያዩም መርሃ ግብር ተቀርፆም እየተሰራ ነው ያለው። መኪናዎች ሳይበላሹ ለጨረታ ቀርበው ይሸጣሉ የተባለው ንብረት የሚወገደው በመንግስት ንብረት ግዢና አስተዳደር በኩል በተቀመጠ መመሪያ ነው። ከዚህ መመሪያ ውጪ ሊፈጸም አይችልም። ከሠራተኞቹ የቀረበው የመኪና ሽያጭ መረጃ ለእኔ የደረሰኝ ነገር የለም” ብለዋል።

 

“የፋይናንስ ዳሬክተሩ ተገቢውን የሒሳብ ሰነዶች አስረክቦ ነው የሄደው?” ተብለው ሲጠየቁ የሰጡት ምላሽ፣ “ፈቃድ ወስዶ ወክሎ ነው የሄደው። ይህም በመሆኑ ኮሚቴ ተሰይሞ ሰነዶችን እየተረከበ ነው የሚገኘው። የሒሳብ ፋይሎች፣ በእሱ ስር ሲከናወኑ የነበሩ የሥራ ፋይሎች ኮሚቴ ታዛቢ ባለበት እየተሰበሰቡ ናቸው። የሚተካውም ሰው ተሳታፊ ተደርጓል። በሙስና የተጠረጠረ ሰው ከሆነ ከሀገር እንዳይወጣ መንግስት ማድረግ ይችል ነበር። ምክንያቱም በሙስና የሚጠረጠር ሰው ከሀገር እንዳይወጣ ለኤርፖርት  የፀጥታ ክፍል ስሙ ይተላለፋል። በፌደራል እና በኦሮሚያ ፖሊስ በኩል በቀረበው ፋይል ላይ ቃሉን እንዲሰጥ ተደርጓል።” ሲሉ አቶ ሙሉጌታ ገልጸዋል፡፡

 

“የተቋሙ ዋና ዳሬክተር በእጃቸው የሚገኘውን ሰነድና ቁስ አስረክበዋል። በእሳቸው ቦታ የተተካ ሰው የለም። አስተዳዳሪ በአሁን ሰዓት የለንም እያሉ ነው? በዚህ ላይ ምን ይላሉ” አቶ ሙሉጌታ “ከተጠናው መዋቅር ጋር ተያይዞ ምላሽ የሚሰጠው ነው። በመዋቅሩ መሰረት ሰው እየተፈለገ ነው፣ በቅርቡ ይመደባል። ዶክተር ዘሪሁን በተቋሙ የሉም። በዚህ አጋጣሚ ግን ሠራተኛው መብቱን ለማስከበር የተበላሸ አሰራሮችን ለመታገል የሚያደርገውን እንቅስቃሴ ሳይሸማቀቅ አጠናክሮ መቀጠል አለበት። ማኔጅመንቱም ከሠራተኛው የለውጥ እንቅስቃሴ ጎን መሆኑ ማረጋገጥ እወዳለሁ ብለዋል።” በማለት የሠራተኞቹ ትግል ፍታህዊ መሆኑን አመላክተዋል

 

እንደሰንደቅ ምንጮች አዲሱ ሚኒስትር እንደተቋም የኢትዮጵያ ማዕድን ፔትሮሊየም እና ባዮ ፊውል ኮርፖሬሽን እየመረመሩት ይገኛሉ፡፡ ሆኖም ከአውስትራሊያ ኤምባሲ ጋር የተሻረኩ፣ የቀድሞ ኃላፊዎች በኤምባሲው ሠራተኞች በመጠቀም ከኤርትራ መንግስት ጋር በሽርክና ሲሰራ ለነበረው ላይንታውን ኩባንያ የድለላ ሥራዎች እየሰሩ መሆኑ ታውቋል፡፡  

ይምረጡ
(1 ሰው መርጠዋል)
413 ጊዜ ተነበዋል

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us