በድርቅ የተደቆሰው ግብርና እና የገበሬው ቀጣይ እጣ ፋንታ

Wednesday, 11 January 2017 14:51

በይርጋ አበበ

 

አቶ ደረሰ ሀብቴ በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን ምንጃር ሸንኮራ ወረዳ ውስጥ በሚገኝ ኮርማ ቀበሌ ነዋሪ ነው። ኑሮው የተመሰረተው በግብርና ላይ ሲሆን ባለትዳርና የልጆች አባት ነው። ወጣቱ አርሶ አደር ለእሱ እና ለቤተሰቡ የኑሮ መሰረት የሆነው ግብርና ላይ አንድ ሄክታር መሬት አለው። ይህ የእርሻ መሬት ግን በቂ ባለመሆኑ እና መሬቱ የሚገኝበት አካባቢ ከዝናብ እርሻ የዘለለ ውሃ የማይገባበት በመሆኑ ተጨማሪ መሬት ተከራይቶ ያርሳል። ይህ ወጣት አርሶ አደር ቀድሞውንም ከእጅ ወደ አፍ ያልዘለለ ገቢው ላይ ባለፈው ዓመት በተከሰተ የአየር ንብረት መዛባት ምክንያት ዓመቱን በችግር አሳልፏል። በዚህም እርፍ እና ጀራፍ የያዘበትን መዳፉን የዘይትና የዱቄት እርዳታ ለመቀበል ዘርግቶታል።

 ከላይ የተቀመጠው አርሶ አደር ታሪክ የአንድ ግለሰብ ተሞክሮ ይሁን እንጂ ከሰሜን ሸዋ ዞን ምንጃር ሸንኮራ ወረዳ እስከ ትግራይ ክልል ዛላንበሳ ከተማ ድረስ 19 የገጠር ቀበሌዎች ተዘዋውረን በተመለከትናቸው አካባቢዎች እና ካነጋገርናቸው አርሶ አደሮች መካከል የአብዛኞቹ ህይወት ከአቶ ደረሰ የተለየ አይደለም።

የመንግስት ኮምዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት ከእርሻ እና ተፈጥሮ ሀብር ሚኒስቴር ጋር በመተባበር የመኸር ሰብል ጉብኝት ለመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች አዘጋጀቶ ነበር። በዚህ የመስክ ጉብኝት በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ እና ሰሜን ወሎ ዞኖች እና በትግራይ ክልል ደቡባዊና ምስራቃዊ ዞኖች በ11 ወረዳዎች 19 ቀበሌዎችን የተመለከትን ሲሆን በጉብኝታችን ወቅትም በ2007 ዓ.ም በተከሰተው ድርቅ ምክንያት ጉዳት የደረሰባቸውን አካባቢዎች አይተናል። በጉዞአችን የተመለከትነውንና ከአርሶ አደሮቹ የተነሱ ጥያቄዎችን እንዲሁም የየአካባቢዎቹ የመንግስት ኃላፊዎች የሰጧቸውን ምላሾች ከዚህ በታች አቅርበነዋል።

 

 

የአርሶ አደሮቹ ችግርና የአስተዳደር አካላት መልስ

ቀደም ሲል በመግቢያችን እንደተጠቀሰው አርሶ አደር ደረሰ ሀብቴን ጨምሮ በ19ኙም ቀበሌዎች ያነጋገርናቸው አርሶ አደሮች የሚያነሷቸው ችግሮች ተመሳሳይ ናቸው። አርሶ አደሮቹ የሚያርሱት መሬት አነስተኛ መሆኑን ደጋግመው ገልጸዋል። በተለይ በትግራይ ክልል ምስራቃዊ ዞን ጎሎ መኸዳ፣ ጋንታ አፈሹም እና ሀወዜን ወረዳዎች የሚኖሩ አርሶ አደሮች በቤተሰብ ግማሽ ሄክታር ብቻ የእርሻ መሬት እንዳላቸው ገለጸዋል። ከመሬቱ መጠን አነስተኛነት በተጨማሪ ደግሞ የመሬቱ ምርታማነት አነስተኛ መሆን ሌላው የአርሶ አደሮቹ ፈተና ነው።

ልክ እንደ ትግራይ ክልል ሁሉ በአማራ ክልል ሰሜን ወሎ ዞን ሀብሩ እና ራያ ቆቦ ወረዳዎች የሚኖሩ አርሶ አደሮችም ከአንድ ሄክታር የዘለለ መሬት እንደሌላቸው ሲናገሩ በሰሜን ሸዋ ዞን በረኸት ወረዳ ደግሞ ችግሩ ከመሬት መጠን የዘለለ መሆኑን ይገልጻሉ። ከበረኸት ወረዳ አጠቃላይ የህዝብ ብዛት ውስጥ 90 ከመቶ የሚሆነው በግብርና እንደሚተዳደር የገለጹት የወረዳው የግብርና ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ወርቁ ደለለኝ የህዝቡ አጠቃላይ ብዛትም 42 ሺህ እንደሆነ ተናግረዋል። ይህን ያህል የህዝብ ቁጥር ያለው ወረዳ ባለፈው የድርቅ ወቅት ብቻ ከ37 ሺህ በላይ የሚሆነው ህዝብ እጁን ለምጽዋት እንዲዘረጋ መገደዱን ተናግረዋል። የድርቁ መጠን ቀነሰ በተባለበት በዚህ የመኸር ወቅት እንኳን ከ27 ሺህ በላይ ህዝብ የእለት ጉርሱን የሚሸፍነው ከምጽዋት መሆኑን ነው ከግብርና ኃላፊው የተገለጸው። 80 በመቶ የሚሆነው በቆላማ የአየር ንበረት የሚሸፍነው በረኸት ወረዳ ላለፉት አምስት እና ሶስት ተከታታይ ዓመታት በድርቅ የሚጠቁ ቀበሌዎችን የያዘ ነው። ይህ ሁሉ ችግር የተተበተበበት የወረዳው ህዝብ አሁንም ለተጨማሪ ድጋፍ እና ለሌላ የድርቅ ስጋት እንጋለጣለን የሚል ስጋት እንዳደረባቸው ነዋሪዎች ለጋዜጠኞች ተናግረዋል።

በዚሁ ክልል ሰሜን ወሎ ዞን ሀብሩ እና ራያ ቆቦ ወረዳዎች ደግሞ አርሶ አደሮቹ የመሬት ችግር እንዳለባቸወ የገለጹ ሲሆን በመስኖ የሚያመርቱትን ምርትም ገበያ አውጥቶ ለመሸጥ መቸገራቸውን ተናግረዋል። ባለፈው ዓመት በተከሰተው ድርቅ ምክንያት ለከፋ ቸግር ተዳርገው ማለፋቸውን ለመገናኛ ብዙሃን የገለጹት የራያ ቆቦ እና ሀብሩ ወረዳ አርሶ አደሮች ክፉውን ጊዜ ያሳለፉት በድጋፍና በድጎማ መሆኑን ገልጸዋል። በዚህ ዓመትም ቢሆን ተመሳሳይ ችግር ሊፈጠር እንደሚችል ስጋታቸውን ሲገልጹ ተሰምተዋል።

የሰሜን ሸዋ ዞን የግብርና መምሪያ ኃላፊ አቶ ደረጀ ማንደፍሮ በአጠቃላይ በዞኑ ከሚኖረው ከሁለት ነጥብ አንድ ሚሊዮን ህዝብ ውስጥ 106 ሺህ ያህሉ የእለት እርዳታ ፈላጊ መሆኑን ተናገረው ሆኖም ይህ የተረጂዎች ቁጥር ካለፈው ዓመት ጋር ሲነጻጸር ከግማሽ በላይ መቀነሱን ነው የገለጹት። ባለፈው ዓመት 380 ሺህ ህዝብ ለከፋ ችግር ተዳርጎ እንደነበረ የገለጹት አቶ ማንደፍሮ በዚህ ዓመት የተረጂዎች ቁጥር ሊቀንስ የቻለው በዞኑ መታረስ ከሚችለው ለም መሬት ላይ 502 ሺህ ሄክታሩ ታርሶ 16 ነጥብ ሶስት ሚሊዮን ኩንታል ምርት ሊገኝ እንደሚችል በመተንበዩ እንደሆነ ከገለጻቸው ለመረዳት ችለናል። ይህም ሆኖ ግን በዞኑ 88 የገጠር ቀበሌዎች ላይ ድርቁ መቀጠሉን በስፍራው ለተገኘው የጋዜጠኞች ቡድን አሰረደተዋል።

የሰሜን ወሎ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አበባው ሲሳይ ግን በዞኑ ተፈጥሮ የነበረውን ድርቅ መንግስት በቁጥጥሩ ስር ማዋሉን ተናግረው የከፋ ችግር አለመድረሱንም ገልጸዋል። አርሶ አደሮቹ የሚያነሱት ቅሬታም ቢሆን ትክክል አለመሆኑን ነው የተናገሩት።

በትግራይ ክልል ራያ አላማጣ ወረዳ “ላዕላይ ዳዩ” ቀበሌ ነዋሪ የሆኑት መላከጽዮን የማነ ንጉስ ደግሞ በግማሽ ሄክታር መሬታቸው በቆሎ እና ጤፍ ማምረት ቢችሉም የምርቱ መጠን እጅግ አነስተኛ በመሆኑ በዓመቱ አጋማሽ እጃቸውን ለእርዳታ እንደሚዘረጉ ገልጸዋል። ቀደም ብሎም ቢሆን የእርሻ መሬት እጥረትና የመሬቱ ምርታማነት ዝቅተኛ መሆኑን የገለጹት አርሶ አደሩ ድርቁ በመከሰቱ ደግሞ የችግራቸው መጠን በመባባሱ እስካሁን ድረሰ ኑሯቸውን በእርዳታ ለመግፋት መዳረጋቸውን ተናግረዋል። በዚሁ ክልል ምስራቃዊ ዞንም ተመሳሳይ ችግር መኖሩን አስተያየታቸውን ለጋዜጠኞች የሰጡ አርሶ አደሮች ተናግረዋል።

የትግራይ ክልል ምስራቃዊ ዞን ዋና አሰተዳዳሪ ወይዘሮ ዓለም ጸጋይ እና የደቡባዊ ዞን ግብርና መምሪያ ኃላፊ አቶ ገብረእግዚያብሔር አረጋዊ ከአርሶ አደሮቹ የተነሳው ችግር መኖሩን አምነው ሆኖም ለችግሮቹ መንግስት አፋጣኝ መልስ በመስጠት ለድርቅ የማይበገር ኢኮኖሚ መገንባቱን ተናግረዋል።

 

የችግሩ ጥልቀት እና በመንግስት የተወሰደ የመፍትሔ እርምጃ

ድርቅ ተፈጥሯዊ ክስተት ነው። ሆኖም ድርቁን ተከትሎ ርሃብ እንዳይፈጠርና የሰዎች እና የእንስሳት ሞትም ሆነ መፈናቀል እንዳይኖር በመንግስት በኩል ሊወሰዱ የሚገባቸው የጥንቃቄ እርምጃዎች ወሳኝነት አላቸው። ይህን በተመለከተ የኢትዮጵያ መንግስት በ2007/2008 ዓ.ም የተፈጠረው ድርቅ (ኤልኒኖ) በአገሪቱ ዜጎች ላይ የከፋ ችግር ሳያስከትል እንዲያልፍ ጠንካራ ስራ መስራቱን አሳውቋል። የብሔራዊ ፕላን ኮሚሸነሩ ዶክተር ይናገር ደሴ ሰሞኑን ከመንግስት መገናኛ ብዙሃን ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ መንግስት ድርቁን ያለ ውጭ ድጋፍ መቋቋም መቻሉን ተናገረዋል።

በሌላ በኩል ደግሞ የጋዜጠኞች ቡድን ተዘዋውሮ በተመለከታቸው አካባቢዎች የመንግስተ ኃላፊዎች አስተያየታቸውን ሲሰጡ መንግስት ድርቁን ያለ ማንም ድጋፍ መቆጣጠር እንደቻለ ነው የገለጹት። በትግራይ ክልል ደቡባዊ ዞን ለደረሰው ድርቅ የእንስሳት መኖ ችግር ለመቅረፍ 20 ሚሊዮን ብር የሚገመት መኖ ከራያ ቢራ ፋብሪካ መደጎሙን የራያ አላማጣ ግብርና ጽ/ቤት አስታውቋል። በዚሁ ክልል ምሥራቃዊ ዞን ለደረሰው ድርቅ ደግሞ ለእንስሳት መኖ ከምዕራብ ትግራይ ዞን መገኘቱን የዞኑ ኃላፊዎች ተናግረዋል።

ከላይ የተጠቀሰው እርምጃ መንግስት እና ህዝብ ችግሩን በጊዜያዊነት ለመቅረፍ የወሰዱት ሲሆን በዘላቂነት መፈታት ካልተቻለ ግን ተዘዋውረን በጎበኘናቸው አካባቢዎች አሁንም ስጋት መኖሩን ገልጸውልናል። ይህን መሰል ሰጋት ለመቀነስ ምን ተወስዷል? ብለን የጠየቀናቸው በአማራ ክልል የሰሜን ሸዋ፣ ሰሜን ወሎ፣ በትግራይ ክልል ደቡባዊ እና ምሥራቃዊ ዞኖች የመንግስት ኃላፊዎች “ለድርቅ የማይንበረከክ ኢኮኖሚ ለመገንባት መንግስትና ሀዝብ አብሮ እየሰራ ነው። ለአርሶ አደሮቹ የግብርና ግብአቶችን በስፋት ማቅረብ እና አርሶ አደሩም በቴክኖሎጂ የመጠቀም አቅሙን እንዲያሳድግ ሙያዊ ድጋፍ ማድረጋችንን አጠንክረን እንገፋበታለን” ሲሉ መልሰ ሰጥተዋል።

 

 

የአምራቾቹ ችግር

በአንድ በኩል በዝናብ እጥረት የተነሳ የእለት ጉርስ ያጡ ዜጎች እጃቸውን ለምጽዋት ሲዘረጉ በሌላ በኩል ደግሞ ተፈጥሮ ባደላቸው ወሃ ተጠቅመው ገበያ መር ምርቶችን (እንደ ቀይ ሽንኩርት፣ ጎመንና ካሮት) ያመረቱ ዜጎች ምርታቸው ሲባክንና ዋጋ ሲያጣ ይታያል። ቀደም ሲል በተጠቀሱት የአማራ እና ትግራይ ክልሎች ቁጥራቸው አይብዛ እንጂ አርሶ አደሮች በመሰኖ ማምረት ቢጀምሩም በገበያ እጥረት እና በተሻሻለ የመስኖ ቴክኖሎጂ እጦት መቸገራቸውን ተናግረዋል።

አርሶ አደሮቹ እንደ ቀይ ሽንኩርትና ጎመን የመሳሰሉ የጓሮ አትክልቶችን በመስኖ ማምረት ቢጀምሩም ምርቶቻቸውን የሚሸጡት ከዋጋ በታች መሆኑን በምሬት ይገለጻሉ። ለዚህ ደግሞ ምክንያቱ አንድም የመስኖው ቦታ ከከተማ በመራቁና መንገዶቹም ለትራንስፖርት ምቹ ባለመሆናቸው ሲሆን በሌላ በኩል ደግሞ በነጋዴውና በአምራቾቹ መካከል የሚገባው የደላላ መረብ እንደሆነ ነው የገለጹልን። ምርቶቻቸውን ማሳቸው ድረስ ሂዶ የሚገዛቸው ባያገኙም አርሶ አደሮቹ በራሳቸው ወጪ ወደ ገበያ ለማቅረብ የሚያደርጉት ጥረትም የሚጠበቀውን ያህል እንዳልሆነላቸው ተናግረዋል። ከዚህ በዘለለ ደግሞ ለረጅም ዓመታት ጥገና ባልተደረገላቸው የመስኖ መስመሮች ምክንያት ወሃ እየባከነባቸው በመሆኑ የሚፈልጉትን ያህል ማምረት አለመቻላቸውንም ተናግረዋል።

የአርሶ አደሮቹን ጥያቄዎች በተመለከተ መንግስት ምን እያከናወነ እንደሆነ የጠየቅናቸው የየዞኖቹ አመራሮች የሰጡን ምላሽ “የገበያ ችግር መኖሩን በግምገማችን አረጋግጠናል። በዚህም በቀጣይ መወሰድ ያለባቸውን እርምጃዎች በተመለከተ የደረስንበት ድምዳሜ የገበሬዎች ህብረት ስራ ዩኒየኖችን በማጠናከር ገበሬው ምርቱን በቀጥታ ለዩኒየኖቹ የሚያቀርብበትን መንገድ ማጠናከር እንዳለብን ነው። ከዚህ በተረፈ ደግሞ የተሻሻሉ የቴክኖሎጂ ግብአቶችን (እንደ ጄኔሬተር እና የውሃ መሳቢያ ፓምፕ የመሳሰሉትን) ገበሬዎቹን በማደራጀት እናቀርባለን” የሚል ነው።

የድርቁ በትር የበረታባቸው

በ1990 ዓ.ም የኤርትራው መንግስት ሻዕቢያ በከፈተው ወረራ ከፍተኛ ጉዳት ከደረሰባቸው የትግራይ ክልል ከተሞች መካከል እንደ ዛላንበሳ የተጎዳ የለም ማለት ይቻላል። ከተማዋ ሙሉ በሙሉ በጦርነቱ የፈረሰች ሲሆን ነዋሪዎቿም የቋጠሩት ጥሪት አንድም ሳይቀር ጠፍቶባቸዋል።

ከአስከፊው ጦርነት በኋላም ዛላንበሳ (ወረዳው ጉሎ መኸዳ ይባላል) በድርቅ ችግር ውስጥ ወድቋል፡፡ ከተማዋ ከአስር ሺህ የሚልቁ ዜጎች ሲኖሯት ሁሉም ዜጎቿ ነገን ለመኖር ዛሬን በእርዳታ ማለፍ ግድ ይላቸዋል። ይህን መረጃ የሰጡን የወረዳው ግብርና ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ካሳ ሀጎስ ናቸው። በወረዳው 331 ሺህ 131 ኩንታል ምርት ለማምረት ቢታሰብም የተገኘው ምርት ግን ከ275 ሺህ ብዙም ፈቅ አላለም። ለዚህም በወረዳው የሚታረሰው ለም መሬት ዝቅተኛ መሆን (11 ሺህ 204 ሄክታር) ሲሆን ሌላው የችግሩ ምክንያት ደግሞ አካባቢውን ድርቅ ደጋግሞ የሚጎበኘው መሆኑ ነው።

እንደ ወረዳው የግብርና ጽ/ቤት ኃላፊ ባለፈው ዓመት ከ102 ሺህ የጉሎ መኸዳ ወረዳ ህዝብ ውስጥ 63 ሺህ 132 ያህሉ ዛሬን የተመለከቱት ከመንግስት በሚደረግላቸው እርዳታ ነበር። በዚህ ዓመት የተረጂዎቹ ቁጥር ቢቀንስም 10ሺህ 250 የዛላንበሳ ነዋሪዎች ግን ከእነ ችግራቸው ዘልቀዋል።

በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን በረኸት ወረዳ (በቀድሞ ስያሜዋ ቡልጋ) ተፈጥሮ ፊቷን ያዞረችባትና ችግርም ቤቱን የሰራባት ወረዳ ነች። ከ42 ሺህ ህዝቧ መካከል ከ37 ሺህ የሚልቀው በመንግስት ድጋፍ ቀናትን ማለፍ ቢችልም ዘንደሮም 27 ሺህ 819 ያህሉ ከእነ ችግሩ የሚገኝ ህዝብ ነው። ቆላማ የአየር ንብረት ያለው የበረኸት ወረዳ 18 በመቶው ህዝቡ የአርጎባ ብሄረሰብ ሲሆን ቀሪው አማራ ነው። በአካባቢው እንደ ከሰም አይነት ግዙፍ የስኳር ፋብሪካ ፕሮጀክት ቢኖርም አሁንም ድረስ አካባቢው በድርቅ እየተሰቃየ መሆኑን ከወረዳው ግብርና ጽ/ቤት ያገኘነው መረጃ አመልክቷል። በተለይ በከሰም ፕሮጀክት አካባቢ የሚገኙ አምስት ቀበሌዎች ከዝናብ ጋር ከተያዩ ዓመታት መቆጠራቸውን የጽ/ቤቱ መረጃ ይገልጻል። በእነዚያ ቀበሌዎች እንስሳትም ሆነ ሰዎች ለጉሮራቸው የሚሆን ጠብታ ውሃ አለመኖሩን የገለጹልን የወረዳው ግብርና ጽ/ቤት ኃላፊ ጉዳዩን ለበላይ አካላት (ለዞን አመራሮች) ቢያመለክቱም መልስ እንዳልተሰጣቸው ገልጸውልናል።

እንደማሳረጊያ

ከስምንት የመገናኛ ብዙሃን ተቋማት የተወጣጣ የጋዜጠኞች ቡድን ተዘዋውሮ በተመለከታቸው አካባቢዎች የአገሪቱ ዋና የኢኮኖሚ ምንጭ ግብርና በድርቅ ምክንያት ጉዳት ሲደርስበት መቋቋም የሚችል አርሶ አደር አለመፈጠሩን ነው። በተደጋጋሚ ሞዴል አርሶ አደር እየተባሉ የሚሸለሙ አርሶ አደሮች ሳይቀሩ በአንድ የመኸር ወቅት በተፈጠረ የዝናብ እጥረት እጅ ሲያጥራቸው ታይተዋል። ይህንም ሳይደብቁ ነግረውናል። በድርቅ የተደቆሰው የአገሪቱ ግብርና እና የግብርናው መሪ ተዋናይ (አርሶ አደሩ እና አርብቶ አደሩ) ከተመሳሳይ አዙሪት የድርቅ ችግር የሚላቀቅበትን መንገድ መፈለግ የነገ ሳይሆን የዛሬ ስራችን ነው። 

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
560 ጊዜ ተነበዋል

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us