ጅቡቲ፡ የኃያላን ሀገራት ወታደራዊ ፉክክር አዲሷ ሜዳ

Wednesday, 11 January 2017 14:45

-    በጅቡቲ እየበዛ የመጣው የውጭ ሀገራት የጦር ሰፈር ግንባታ

ለኢትዮጽያ መልካም አጋጣሚ ወይስ ሥጋት?

በአስማማው አያናው

መነሻ

በአለማችን ተነባቢ ከሆኑ መጽሄቶች አንዱ የሆነው ዘ ኢኮኖሚሰት (the Economist) በ ሚያዝያ 2016 እትሙ ስለ ጅቡቲ ይህን አለ “Everyone wants a piece of Djibouti. It is all about the base.'' በግርድፉ ሲተረጎም “ማንኛውም ሀገር ከጅቡቲ ትንሽ መሬት ይፈልጋል፤ ይህም ለጦር ሰፈር ግንባታ የሚውል ነው” እንደማለት ነው። የቅርብ አመታትን የጅቡቲን ስትራቴጅካዊ ተፈላጊነት ምን ያክል እያደገ እንደ መጣ ለታዘበ ሰው፣ ምን ያህል ይህ አገላለጥ ትክክለኛ እንደሆነ መረዳት ይችላል። አሁን ጅቡቲ ከልዕለ ሀያሏ አሜሪካ እና ሩቅ ምስራቅ እስያ ሀገራት ጀምሮ አፍንጫዋ ስር እሰከምትገኘዋ ሳዑዲ አረቢያ ድረስ በእጅጉ የምትፈለግ ሀገር ሆናለች። በአሁኑ ወቅት በተናጠልም ሆነ በጋራ ወታደራዊ ወይም የጦር ሰፈር (Millitary Base) በሀገሪቱ የገነቡ እና በመገንባት ላይ የሚገኙ ሀገራት ቁጥር ስምንት ደርሷል። ከቀድሞ ቅኝ ገዥዋ ፈረንሳይ እና አሜሪካ ውጭ ያሉት ሀገራት ባለፉት ስድስት እና ሰባት አመታት ውስጥ የመጡ መሆናቸውን ስንመለከት ደግሞ ጅቡቲ ለጦር እቅድ አመቺነት (Strategic) ጋር በተያያዘ ያላት ተፈላጊነት በምን ያክል ፍጥነት እያደገ እንደመጣ በግልጽ መረዳት እንችላለን።

በዚህ ጽሁፍ የሀገሪቱ ተፈላጊነትን ያናሩት ምክንያቶችን፣ የጦር ሰፈር ግንባታው በአለማችን ወታደራዊ ፉክክር የኃይል ሚዛን ላይ የሚኖረው አስተዋጽኦ፣ ከጅቡቲ በቅርብ እርቀት ለሚገኙ የቀጠናው ሀገራት ብሎም ከሁሉም ሀገራት በላይ ኢኮኖሚያዊ ትስስር ላላት ኢትዮጽያ ያለው መልካም አጋጣሚ እና ስጋት እንዲሁም መንግስት መውሰድ ያለበት የፖሊሲ አቅጣጫዎችን ለማመላከት እንሞክራለን።

የጅቡቲ ተፈላጊነት ለምን እየጨመረ መጣ?

ከአፍሪካ ቀንድ ሀገራት መካከል አንዷ የሆነችው ጅቡቲ ከመሬት አቀማመጧ ጋር በተያያዘ በርካታ ስትራቴጂካዊ ጥቅም ያላት ሀገር ናት። ሀገሪቱ በነዳጅ ሀብት የበለፀጉ የመካከለኛው ምስራቅ የአረብ ሀገራትን እና አፍሪካን የምታስተሳስር ናት (ከየመን በ20 ማይልስ ርቀት ላይ መገኘቷን ልብ ይሏል)። ይህም ቀይ ባህርን እና ህንድ ውቅያኖስን በማገናኘት በቀላሉ መርከቦች በሜድትራኒያን ባህር በኩል ወደ አውሮፓ እና አሜሪካ ለመላለስ እንዲችሉ አይነተኛ ሚና ካለው የባብል መንደብ ወሽመጥ (babel mendeb straight) በቅርብ ርቀት እንድትገኛ አስችሏታል። ይህ ማለት ደግሞ ከአለማችን በመርከብ ከሚመላለስ ሸቀጥ 20 በመቶ እና 10 በመቶ ለዓለም ገበያ የሚቀርብ ነዳጅ የሚያልፍበትን ይህን አካባቢን ለመቆጣጠር በሚፈልግ ማንኛውም ሀገር ተመራጭ ያደርጋታል። ምናልባት ይህን በማሟላት ረገድ ኤርትራም ጥሩ አካባቢያዊ ጠቀሜታ ቢኖራትም የኢሳያስ አፈወርቂ መንግስት አምባገነንነት እና ቀጠናውን የማተራመስ ስትራቴጂ በኃያላኑ በተለይም አሜሪካ፣ አውሮፓና እስያ ሀገራት ተመራጭነቷ ዝቅተኛ እንዲሆን አድርጓታል። እነዚህ አካባቢያዊ ጠቀሜታ እንዳሉ ሆነው በየመን እና በሶማሊያ ያለው አለመረጋጋትም ለተፈላጊነቷ ሌላ ምክንያቶች ተደርገውም ይጠቀሳሉ።

በአንጻሩ መቀመጫውን ለንደን በማድረግ በአለም አቀፍ ጸጥታ እና ደህንነት ዙሪያ ገለልተኛ የፖሊሲ ምክር ሀሳቦችን በማቅረብ የረጅም አመታት ልምድ ያለው የካተም ሀውስ (Cathem House) ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ እያደገ ለመጣው የጅቡቲ ኢኮኖሚያዊም ሆነ ስትራቴጂካዊ ተመራጭነት አራት ገፊ ምክንያቶችን (Drive Factors) ያስቀምጣል።

የመጀመርያው ከ 1998-2000 (ሁሉም በፅሁፉ ላይ የሚጠቀሱ አመተ ምህረቶች እንደ አውሮፕያኑ አቆጣጠር ናቸው) የተካሄደው የኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት፣ ሁለተኛው የኢትዮጵያ ተከታታይ ኢኮኖሚያዊ እድገት፣ የ2001 አልቃይዳ ጥቃት ተከትሎ የተፈጠረው የአሜሪካ ወታደራዊ ስትራቴጅክ ለውጥ እና የመጨረሻው በኤደን ባህር ሰላጤ እና በሶማሊያ የባህር ጠረፍ  የባህረ ላይ ዘራፊዎች መበራከት ናቸው። እነዚህ ምክንያቶች በተለይም የመጨረሻዎቹ ሁለቱ እና የየመን እና ሶማሊያ አለመረጋጋት አንድ ላይ ተዳምረው የሚፈጥሩት ችግር አለማቀፋዊ ዳፋው ቀላል የሚባል አይደለም። ለዚህም ነው ሀገራት ኢኮኖሚያዊ ጥቅማቸውን ከማስከበር በዘለለ ወታደራዊ የጦር ሰፈር በመገንባት የጸጥታና ደህንነት ስጋታቸውንም ለመቀነስ ጅቡቲን ምርጫቸው ያደረጓት።

የመጀመሪያው እና ሁለተኛው ኢኮኖሚያዊ ምክንያቶች ከኢትዮጵያ ጋር የሚያያዙ ሲሆኑ ሌሎች ደግሞ በአሁኑ ወቅት በጅቡቲ የጦር ሰፈር በመገንባት በአካባቢው ያላቸውን ጥቅም ለማሰከበር እየሰሩ ያሉ አሜሪካን፣ ፈረንሳይ፣ የአውሮፓ ህብረት (ስፔን እና ጀርመን)፣ ጃፓን፣ ጣሊያን፣ ቻይና እና በቅርቡ ከጅቡቲ መንግስት ጋር የተስማማችው ሳዑዲ አረቢያን ይመለከታል።

የተሻለ ግንዛቤ ለመስጠት እነዚህ የጦር ሰፈር በሀገሪቱ የገነቡ ሀገራትን ከምክንያቶቹ ጋር በማስተሳሰር ለመመልከት እንሞክር።

አሜሪካ፡-  የአሜሪካን እና ጅቡቲን ስትራቴጂካዊ አጋርነት የፈጠረው የ 2001 የአልቃይዳ የሽብር ጥቃት ነው። ይህ ጥቃት አሜሪካን ፖለቲካዊም ሆነ የጸጥታ እና ደህንነት አስተሳሰብ በእጅጉ የቀየረ ነው። ለዓለምም ሆነ አሜሪካ የደህንነት ስጋት ከሀገራት አምባገነን መንግስታት በላይ በግለሰቦች የሚመሩ አሸባሪ ቡድኖች ናቸው ብሎ ያመነው የቡሽ አስተዳደር በሁሉም ጫፍ የሚገኙ የአልቃይዳ  ቡድኖችን ማጥፋትን ኢላማው ያደረገ ወታደራዊ ጥቃት ከፈተ። ከኢላማዎች ውስጥ ደግሞ አንዱ በየመን መቀመጫውን አድርጎ የነበረው አልቃይዳ በአረብ ፔንሲዮላ ወይም AQAP (Al-Qaeda in the Arabian Peninsula) በሚል ስያሜ የሚታወቀውየአልቃይዳ ክንፍ ነው። አሜሪካ ይህን የሽብር ቡድን ክንፍ ለማጥፋት ከየመን በቅርብ ርቀት የምትገኘውን ጅቡቲን መቀመጫ ለማድረግ በ2002 የጦር ሰፈሯን የገነባችው። በዚህ መልኩ አሜሪካ በአፍሪካ ብቸኛ የገነባችው የጦር ሰፈር ካምፕ ሊሞኒየር (Camp Lemmonier) ይባላል። በአሁኑ ወቅት 4,500 የሚደርሱ የባህር ሀይል ወታደሮች እና ሌሎች የደህንንነት ሰራተኞችን ይዟል። በአመትም 60 ሚለዮን ዶላር ለጅቡቲ መንግስት ይከፈልበታል። እስከ 2006 ድረስ ትኩረቱን በየመን አልቃይዳ ክንፍ ላይ አድርጎ የነበረው ይህ የአሜሪካ ጦር በኋላ ላይ የአልሻባብ የሽብር ቡድን በሶማሊያ መስፋፋቱን ተከትሎ ትኩረቱንም ወደዚህ አድረጓል። ከ2011 ጀምሮ ደግሞ በሰው አልባ  አውሮፕላን  በመታገዝ ጭምር የፀረ ሽብር ዘመቻው ላይ ከፍተኛ ሚና ተጫውቷል።

በአጠቃላይ አሜሪካ በጅቡቲ ያቋቋመችው ይህ የጦር ሰፈር በፀረ ሽብር ዘመቻ፣ የባህር ላይ ዘራፊዎችን በማጥፋት እና በቅርቡ ደግሞ የየመንን ብጥብጥ ተከትሎ ሁኔታውን በቅርበት እንድትከታተል እና ጥቅሟን እንድታስከበር ዋና ማዕከል ሆኖ እያገለገለ ነው።

ፈረንሳይ፡- ፈረንሳይ የጅቡቲ ቅኝ ገዥ የነበረች ሀገር እንደመሆኗ በሀገሪቱ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ወታደራዊ ሁነቶች ላይ ያላት ተፅእኖ ቀላል ሚባል አይደለም። ጅቡቲ በ1977 ነፃነቷን ብትቀናጅም እንደ ሌሎች የአፍሪካ ሀገራት ሁሉ እንደውም በጣም ባስ ባለ መልኩ ከፈረንሳይ ጥገኝነት በተለይም በወታደራዊ መስክ በቀላሉ መላቀቅ ፈተና ሆኖባት ቆይቷል። በነጻነት ማግስት ሁለቱ ሀገራት የተፈራረሙት ወታደራዊ ስምምነት ማሳያ ነው፡ በ1977 የተፈረመው ይህ ስምምነት ፈረንሳይን ከማንም ውጫዊ ሀይል ጅቡቲን የመጠበቅ ሀላፊነትን ይሰጣል። በዚህም ምክንያት ፈረንሳይ ይህን ማድረግ የሚያስችላትን የጦር ካምፕ እንድተመስረት አስችሏታል። ከሶስት አስርት አመታት በላይ በአፍሪካ ትልቁን የፈረንሳይ ወታደሮች መኖርያ የነበረው ካምፕ ሞንክላር (camp monclar) ብቸኛ የጅቡቲን የአየር እና የባህር ድህንነትን ሲቆጣጠርም ቆይቷል።

ለጅቡቲ መከላከያ ሀይልም የገንዘብ እና ስልጠና ድጋፍ በመስጠትም ለማጠናከር ሲሰራ ቆይቷል። ይህም ፈረንሳይን በአካባቢው ያላትን ጥቅም ለማስከበር ከማስቻሉም በላይ በሀገሪቱ ጉዳይ ላይም ቀዳሚ እና ብቸኛ ወሳኝ አካል እንድትሆን እድል ፈጥሮላታል። ነገር ግን ከ2002 ጀምሮ አሜሪካ ወደ ስፍራው መምጣቷን ተከትሎ ፈረንሳይ በጅቡቲ የነበራት የበላይነት እየቀነሰ ሊመጣ ግድ ብሎታል። ይህም ሀገሪቱ በጅቡቲ የነበራትን ወታደሯች ቁጥር እንድትቀነሰ እስከማድረግ አድርሷታል። ይሁን እና በአካባቢው በተለይም በህንድ ውቅያኖስ  የባህር ላይ ዘራፊዎች መበራከት ተከትሎ መረከቦቿን ከዚህ አደጋ ለመጠበቅ የጦር ሰፈሯን በእጅጉ ተጠቅማበታለች። በተለይም ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ የጅቡቲ ጂኦ-ፖለቲካዊ ተፈላጊነት ማደግን የተመለከተችው ፈረንሳይ በ2011ም ከጅቡቲ ጋር አዲስ ስምም ነትን በማድረግ እና 30 ሚሊዮን ዩሮ  ለሀገሪቱ መከላከያ ሀይል በመስጠት በጅቡቲ የነበራትን የበላይነት ለመመለስ እየታተረች ይገኛል።

የአውሮፓ ሕብረት (ጀርመን፣ ስፔን)

ጀርመን እና ስፔን በአውሮፓ ህብረት ስም ወደ ጅቡቲ ወታደሮቻቸውን የላኩት የሶማሊያን መንግስት አልባ መሆንን እንደ ምቹ ሁኔታ በመውሰድ እንዲሁም በህንድ ውቅያኖስ አቅራቢያ የባህር ላይ ዘራፊዎች መበራከታቸውን ተከትሎ ነው። በዓለማችን የነዳጅ ምርትን እና ሌሎች ሸቀጦችን በማመላለስ ስራ ከሚበዛባቸው የባህር መስመሮች አንዱ የሆነው ይህ አካባቢ በአንድ ወቅት የባህር ላይ ዘራፊዎች መረከቦችን በማገት ገንዘብ መሰብሰቢያ አድረገውት ነበር። በተለይም ከ2008 ጀምሮ ይህ ወንጀል በእጅጉ በመስፋፋቱ ምክንያት የአውሮፓ ህብረት የአባሎቹን ሀገራት መረከቦችን ለመከላከል እንዲቻል ከሁለቱ ሀገራት የተውጣጡ ወታደሮችን በጅቡቲ ሊያሰፍር ችሏል። የህብረቱ ጦር እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ የፈረንሳይ ወታደራዊ የጦር ሰፈርን ይጠቀም ነበር። አሁን ላይ የራሱን ጦር ሰፈር ስለመገንባቱ የሚገልጥ ፅሁፍ ግን አስካሁን ማግኘት አልቻልኩም።

ጣሊያን እና ጃፓን

ሁለቱም ሀገራት ልክ እንደ አውሮፓ ህብረት የባህር ላይ ዘራፊዎችን ለመከላከል በሚል ከባህር ማዶ በጅቡቲ የጦር ካምፕ ለመገንባት ተገድደዋል። ጣሊያንም ከ300 በላይ ወታደራዊ ሐይል የሚይዝ የጦር ሰፈር አላት። ጃፓን በበኩሏ በዓመት 30 ሚሊየን ዶላር አመታዊ ክፍያ በያዘችው 12 ሄክታር የጦር ሰፈሯ ላይ 600 ወታደሮች አሏት። ይሁን እና ሮይተርስ ባለፈው ጥቅምት ወር ላይ የጃፓን ከፍተኛ የጦር አመራሮችን ዋቢ አድረጎ በሰራው ዘገባው የቅርቡ የቻይና መስፋፋት ስጋት ውስጥ የጣላት ጃፓን በጅቡቲ ያላትን ወታደሮች ቁጥርም ሆነ ይዞታዋን ለማስፋት አቅዳለች ብሏል።

ቻይና እና ሳዑዲ አረቢያ

የሁለቱ ሀገራት ወታደራዊ ሰፈር ግንባታ ብዙ መመሳሰሎች አሉት። አንዱ መመሳሰላቸው ከአለም አቀፍ መነጋገሪያነታቸው ይመነጫል። በጎረቤት ሀገር ጅቡቲ ከባህር ማዶ ወታደሮቻቸውን ካሰፈሩ ሀገራት ሁሉ እንደ ቻይና እና ሳዑዲ ዓረቢያ የዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙሀን ሆነ ፖለቲከኞች መነጋገሪያ የሆነ ሀገር የለም። ይህ ደግሞ ሁለቱም ሀገራት ጅቡቲን ሲመርጡ በዚህች ሀገር ቀድመው ወታደራዊ ሰፈር ካቋቋሙ አልያም በአካባቢው ከሚገኙ ሀገራት ጋር ካላቸው ወታደራዊ እሰጥ አገባ የተነሳ ነው ከሚል ድምዳሜ በመነጨ ነው መነጋገርያ መሆናቸው። ይህም ሌላው ምስላቸው ነው።

ከ2008 ጀምሮ በነበረው የፀረ-ባህር ላይ ዘራፊዎች እንቅስቃሴ ቻይና ከፈረንሳይና አሜሪካ ጋር በመሆን በአካባቢው ወታደራዊ እንቅስቃሴ ስታደርግ የቆየች ቢሆንም ቋሚ ወታደራዊ ሰፈር ለመገንባት ግን ፍላጎትን አላሰየችም ነበር። ይሁን እና በየመን የተከሰተውን የእርስ በእርስ ብጥብጥ ተከትሎ ከ100 በላይ ዜጎችን ከዚህች ሀገር ለማስወጣት በሚል በቀጠናው ስትንቀሳቀስ እና በደቡብ ሱዳን በተመሳሳይ ጊዜ በሀገሪቱ ያላትን ኢኮኖሚያዊ ጥቅም ለማስጠበቅ 700 የሚደርሱ ወታደሮችን ወደ  አዲሷ ሀገር ድንበር ሰታስገባ ብዙዎች ቻይና በቀጠናው ቋሚ ሀይል እንዲኖራት ትፈልጋለች ሲሉ መላምታቸውን እንዲሰጡ ተገድደው ነበር። እርግጥም ብዙም ሳይቆይ በየካቲት 2016 በሰሜናዊ ጅቡቲ ወታደራዊ ሰፈር ማቋቋሟን ቻይና ይፋ አድርጋለች። በቀጠናው በብጥብጥ ውስጥ ባሉ ሀገራት ያሏት ዜጎቿን ለማውጣት እና በአካባቢው ለምታካሂደው የሰላም ማስከበር እና ሰብአዊ አገልግሎት ስራ ሎጅስቲክስ አቅርቦት ማዕከል እንዲሆን ታስቦ የተገነባ ነው ስትልም አላማውን ገልጣለች።

ይህ ወታደራዊ ሰፈር ቻይና ከደቡብ ቻይና ባህር ውጭ ለመጀመርያ ጊዜ የገነባችው ነው። ለጅቡቲም 20 ሚሊዮን ዶላር በየዓመቱ ለመክፈልም ተስማምታለች። ታዲያ ቻይና ባልተለመደ መልኩ ለመጀመርያ ጊዜ ከባህር ማዶ የገነባችው ይህ የጦር ሰፈር ሀገሪቱ በኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ ረገድ በቀጠናው ያላትን የበላይነት የምታሰጠብቅበት ብቻ ሳይሆን በወታደራዊ መስኩም ከአሜሪካ ጋር የምትገዳደርበት ጭምር ነው፣ እየተባለለት ነው።

ሌላዋ ሀገር ሳዑዲ አረቢያ በበኩሏ በቅርቡ ነው በጅቡቲ ከባህር ማዶ ወታደራዊ ሰፈር ማቋቋም እንደምትፈልግ ያስታወቀችው። የውክልና ጦርነት (Proxy War) ሰለባ የሆነችውን የመንን ወደማያባራ የእርስ በእርስ ብጥብጥ መግባቷን ተከትሎ በአፍሪካ ቀንድ ፖለቲካ ላይ እጇን እያስረዘመች የመጣችው ሳዑዲ እና የዓረብ ሀገረ አጋሮቿ በኤርትራ አሰብ ወደብን በተራዘመ ጊዜ ኪራይ እንደተቆጣጠሩ ሁሉ በጅቡቲም ወታደራዊ እንቅስቃሴ እንዲኖራቸው ይፈልጋሉ። ይህ ደግሞ የምንጊዜም ባላንጣዋ የሆነችውን እና በየመን ጦርነት የሁቲ ተቃዋሚዎችን ትደግፋለች የምትባለው ኢራንን በአካባቢው ያላትን መስፋፋት ለመግታት የምትከተለው ፖሊሲ (contaiment policy) አካል ነው። ያም ሆነ ይህ ግን ጅቡቲ እና ሳዑዲ በወታደራዊ መስክም የቅርብ ጊዜ ሸሪኮች ሁነዋል።

በአጠቃላይ በአሁኑ ወቅት በጅቡቲ የጦር ካምፕ የገነቡ እና እየገነቡ ሰለመሆናቸው በግልጥ ከታወቁ ከላይ የተጠቀሱት ሀገራት በተጨማሪ ህንድ እና ሩስያም ፍላጎት እንዳላቸው በጭጭምታ ደረጃ እየተገለጠ ይገኛል።

የባህር ማዶ የጦር ሰፈር ግንባታ እና ወታደራዊ የሀይል ሚዛን

የወታደራዊ ሳይንስ ጠበብቶች አንድ ሀገር ከባህር ማዶ የምታካሂደው የጦር ሰፈር ግንባታን ለወታደራዊ የሀይል ትንበያ (Power Projection) እንደ አንድ መለኪያ ይጠቀሙበታል። ይህም ማለት ሀገራት በአጭር ጊዜ በቀጠናቸው አልያም በሌላ አካባቢ ለሚከሰት ግጭት ፈጣን ምላሽ የመስጠትና ወታደራዊ ስጋቶችን የመቋቋም (Detterence) አቅም የሚገመገምበት ሚዛን ነው። ስለዚህም ይህ መለኪያ በሀገራት መካከል ያለውን ወታደራዊ የሀይል ሚዛንን ለመገመት እና ቀጣዩን ለመተንበይም የራሱ የሆነ ድርሻ አለው ማለት ይቻላል። በዚህም ምክንያት በጅቡቲ ያለው የሀገራት እሽቅድድም አላማው ምንም ይሁን? ምንም በሀገራቱ መካከል ወታደራዊ አቅምን ለማሳየት እንደሚደረግ የሀይል ፉክክር ሊወሰድ የሚችል ነው። ለዚህም በአሜሪካ እና ቻይና፣ በሳዑዲ እና ኢራን እንዲሁም በቻይና እና ጃፓን መካከል ያለው ወታደራዊ ሽኩቻ ግልጥ ማሳያ ነው።

ቢቢሲ በድህረ ገጹ ቀደም ባሉት ጊዜያት የጅቡቲን ሁኔታ በተመለከተ ባሰፈረው ዘገባው ላይ በወቅቱ ገና ሳይረጋገጥ ይነገር የነበረው የቻይና በጀቡቲ  ያላት ወታደራዊ እንቅስቃሴ ነገር ለአሜሪካ ትልቅ የራስ ምታት ሁኗል ብሎ ነበር። ይህንንም በአንድ ወቅት የአሜሪካ ም/ቤት አባል ለውጭ ጉዳይ ሚኒስተሩ ጆን ኬሪ ያቀረቡትን ሀሳብ መነሻ በማድረግ የበለጠ ያጠናክረዋል። ቻይና በቀጠናው እያሳየችው ያለው ፍላጎት አሜሪካ በወታደራዊ መስክ በአፍሪካ ቀንድ እና በአካባቢው የዓረብ ሀገራት ላይ የነበራትን የበላይነት አደጋ ውስጥ የሚጥል ነው ሲሉ ነበር ሴናተሩ ለጆን ኬሪ ስጋታቸውን ያስቀመጡት። ይህ የሴናተሩ ሀሳብ የወታደራዊ ሰፈር ግንባታ ሩጫው በቀጠናው የነበረውን የውጭ ሀገራት ወታደራዊ የሀይል አሰላለፍ ሊያናጋ እንደሚችል የሚያሳይ ነው።

በሌላ በኩል ከቀዝቃዛው ጦርነት ጀምሮ ከአሜሪካ ጋር ግልጽ ወታደራዊ ፉከክር ውስጥ የገባችው ሩስያ በጀቡቲ ወታደሮቿን የማስፈር ፍላጎት አላት የሚለው ወሬ እንደ ቻይና ቆይቶ ወደ እውነታ ከተቀየረ የአፍሪካ ቀንድ እንደ ምስራቅ አውሮፓ እና መካከለኛዎ ምስራቅ ሁሉ ሌላ ወታደራዊ እሰጥ አገባ ማስተናገዱ አይቀርም። በጃፓን እና ቻይና መካከል ያለው ሁኔታም ተመሳሳይነው።

ታዲያ ይህ ከፍተኛ ወታደራዊ ፉክክር ውስጥ ያሉ ሀያላን ሀገራት ጦር በአንድ አካባቢ መሰባሰብ የሀይል ሚዛንን በማዛባት ቀጠናውን ብሎም አህጉሩን ወደማያቋርጥ ብጥብጥ ሊመራ ይችላል ሲሉ የፖለቲካ ተንታኞች ስጋታቸውን ይገልጣሉ።

የጅቡቲ ባህር ማዶ ጦር ሰፈር ግንባታው ለኢትዮጽያ መልካም አጋጣሚ ወይስ ስጋት?

በጅቡቲ እያደገ የመጣውን ሀገራት ከባህር ማዶ የሚገነቡት ወታደራዊ ሰፈር ለኢትዮጵያ ብሎም ለቀጠናው ሀገራት የሚኖረውን ጥቅም እና ጉዳት ከማየታችን በፊት ቅደሚያ ኢትዮጵያና ጅቡቲ ያላቸውን ኢኮኖሚያዊ፣ፖለቲካዊ ና የህዝብ ለህዝብ ትስስሩ እስከምን ድረስ ነው የሚለውን ማየት የበለጠ ነገሩን ግልጥ ለማድረግ ያስችለናል።

ኢትዮጵያና ጅቡቲ

በጽሁፉ መግቢያ ላይ የጅቡቲ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ኢኮኖሚያዊ እና ስትራቴጂካዊ ተፈላጊነት ማደግ በምክንያትነት የካተም ሀውስ ካስቀመጣቸው አራት ነጥቦች መካከል ሁለቱ ኢትዮጵያን ይመለከታሉ። ምክንያቶቹ ደግሞ በዋናነት ከኢኮኖሚዊ ሁኔታዎች ጋር የተሳሰሩ ናቸው።  የመጀመሪያው ምክንያት እ.ኤ.አ ከ1998-2000 ድረስ የዘለቀው የኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት ነው። ይህ በእርግጥም ኢትዮጵያ በወቅቱ ለወጪ እና ገቢ ምርቷ ትጠቀምበት ነበረውን የአሰብ ወደብ ሙሉ በሙሉ ያሳጣት አጋጣሚ ነው። ታዲያ ይህን ተከትሎ ነበር የጅቡቲ ወደብ የኢትዮጵያ ብቸኛ አማራጭ መሆን የቻለው። ሌላ አማራጭ መሆን የሚችለው የበርበራ ወደብ ቢሆንም በሶማሊያ መንግስት አልባነት ምክንያት የተፈጠረው ወስጣዊ ብጥብጥ ሁኔታውን እንዳይታሰብ አድርጎታል። በእንደዚህ ሁኔታ ኢኮኖሚያዊ ትስስራቸው ያደገው ሁለቱ ሀገራት ባለፉት አስርት አመታት ኢትዮጵያ ያስመዘገበችውን ፈጣን እድገት ተከትሎ ትስስሩ የበለጠ እየጠነከረ መጥቷል፣ ይህ በሁለተኛ ምክንያትነት የተቀመጠ ነው።

ኢኮኖሚያዊ እድገቱን ተከትሎ በወደብ ኪራይ እና ተጠቃሚነት ብቻ ታጥሮ የነበረው የሁለቱ ሀገራት ኢኮኖሚያዊ ግንኙነት በታላለቅ የጋራ የመሰረተ ልማት ግንባታ የሚታጀብበትንም እድል መፍጠር ችሏል። ይህም ከኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት እሰከ ባቡር እና ወደብ ግንባታ የዘለቀ ነው። ዘኢኮኖሚሰት ላይ እንደሰፈረው በአሁኑ ወቅት ሁለቱ ሀገራት በጋራ የገነቧቸው እና እየገነቧቸው የሚገኙ ፕሮጀከቶች የገንዘብ መጠን አስር ቢሊየን ዶላር ደርሷል። የኢትዮጵያን 90 በመቶ ወጭ እና ገቢ ምርት ከሚያስተናግደው የጅቡቲ ወደብ የተሻለ ቅርበት የሚኖረው የሶስቱ ሀገራት(ጀቡቲ፣ ኢትዮጵያ እና ደቡብ ሱዳን) ፕሮጀክት የሆነው ታጁራ ወደብን ጨምሮ ከ9 ቢሊየን ዶላር በላይ የተበጀተላቸው ሌሎች ፕሮጀክቶችንም ለመስራት ሁለቱ ሀገራት ውጥን ይዘዋል። እነዚህ አሀዞች የሀገራቱን ኢኮኖሚያዊ ትስስር (Economical Interdependence) ምን ያክል እየተጠናከረ ስለመምጣቱ የሚያሳዩ ናቸው። አሀዞቹ ይህም ብቻ አይደለም ሌላም ነገር ይነግሩናል፡ ጅቡቲ ለኢትዮጵያ ምን ያክል የምታስፈልግ ሀገር ስለመሆኗ።

ሁለቱ ሀገራት ያላቸው ግንኙነት ኢኮኖሚያዊ ብቻ የታጠረ አይደለም፤ ይልቁንስ ፖለቲካዊ እና ወታደራዊ ጭምር እንጅ። የቀጠናው ህብረት በሆነው ኢጋድ (IGAD) መቀመጫ የሆነችው ጅቡቲ ኢትዮጵያ ይህን ተቋም በመምራት በአፍሪካ ቀንድ ያለውን አለመረጋጋት በዘላቂነት በመፍታት ከግጭት ይልቅ የልማት ኮሪደር እንዲሆን ለማስቻል በምታደርገው ጥረት ውስጥ ሁሌም ከጎን የምትገኝ ሀገር ናት። በወታደራዊ መስክም ቢሆን ሁለቱ ሀገራት ሶማሊያ ውስጥ አልሻባብን ለማጥፋት በተሰማራው የአፍሪካ ህብርት ሰላም አስከባሪ ሀይል (AMISOM) ውስጥ በኪስማዮ በአንድ የጦር ግንባር  ተሰልፈዋል። ኢትዮጵያና ጀቡቲ የአፋር እና ኢሳ ሶማሌ ጎሳዎችን የሚጋሩ እና የረጅም አመታት የህዝብ ለህዝብ ግኑኝነት ያላቸውም ሀገራት ናቸው።

መልካም አጋጣሚ እና ስጋቶች

ኢትዮጵያ ከጅቡቲ ጋር ጠንካራ ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊ እና የህዝብ ለህዝብ ትስስር እንዲሁም የጋራ ተጠቃሚነት ያዳበረች ሀገር ናት። ይህም በመሆኑ የውጭ ሀገራት በጅቡቲ ወታደራዊ ጦር ሰፈር ግንባታ የራሱ የሆነ መልካም አጋጣሚ እና ስጋትን ለኢትዮጵያ ይዞ መምጣቱ አይቀሬ ነው።

ለኢትዮጵያ ብሎም ለቀጠናው እነዚህ ሀገራት በሚገነቧቸው የጦር ሰፈሮች የሚያሰማሯቸው ወታደሮች እንቅስቃሴዎች ኢትዮጵያ እና ለቀጠናው ሀገራት ጭምር ስጋት የሆነን ጉዳይ ነው። እነዚህን ሀገራት ጅቡቲ እንዲከትሙ ያደረጋቸው ግልጥ ምክንያቶች (ሚስጥራዊ አጀንዳዎች እንዳሉ ሁነው ማለትነው) ሽብርተኝነት፣ የባህር ላይ ዘራፊዎች እና አዳዲስ የሚፈጠሩ የቀጠናው ሀገራት ውስጣዊ ግጭቶች ናቸው። እነዚህ ምክንያቶች ደግም በውጭ ግንኙነት ፖሊሲዋ ቀጣይነት ያለው ኢኮኖሚያዊ ልማት የሚረጋገጠው ውስጣዊ ሰላምን ብቻ ሳይሆን አካባቢዊ መረጋጋት ሲመጣ ብቻ ነው በሚል በግልፅ ላስቀመጠችው ኢትዮጵያ ትልቅ የራስ ምታት ናቸው። የሶማሊያ አለመረጋጋት የወለዳቸው የባህረ ላይ ዘራፊዎች በአንድ ወቅት ከምንም በላይ ቀጠናዊ ስጋት ነበሩ። መርከቦችን በማገት በድርድር የሚያገኙት ጠቀም ያለ ገንዘብ በዚሁ ቢቀጥል ለሽብር ቡድኖች የማይውልበት ምንም ምክንያት አልነበረም። ታዲያ የእነዚህ ሀገራት መምጣት ዘራፊዎቹ አሁን ለደረሱበት የመክሰም ደረጃ ትልቅ አሰተዋፅኦ አበርክቷል።

በኢትዮጵያ ላይ ጅሀድ አውጆ የነበረው የሶማሌ የእስላማዊ ፍርድቤቶች ህብረት መፈራረስን ተከትሎ የተፈጠረው የአልሻባብ የሽብር ቡድን ደርሶበት ከነበረው ሶማሊያን የመምራት እና ቀጠናውን የማተራመስ ከፍተኛ አቅም ወረዶ አሁን ላይ ለደረሰበት መዳከም በኢትዮጵያ መሪነት የቀጠናው ሀገራት ከወሰዱት ወታደራዊ ርምጃ ባለፈ የእነዚህ ሀገራት ድጋፍም ትልቅ ሚና ነበረው። አሜሪካ ከ2011 ጀምሮ በቀጠናው ያሰማራችው ሰው አልባ አውሮፕላን (Drone) ከ ጅቡቲ ካምፕ ሊሞኒየር እየተነሳ ባለፈው ሚያዝያ ወር የተገደለው ሀሰን አሊ ዶሪን ጨምሮ በረካታ የአልሻባብ መሪዎችን ገድሏል። ይህ አሜሪካ በጅቡቲ ወታደራዊ ሰፈሯ የአፍሪካ ቀንድ የጋራ ወታደራዊ ሀይል (CJTF-HOA) አማካኝነት ከምትሰጠው ወታደራዊ ስልጠና እና የደህንንት የመረጃ ልውውጦች ድጋፍ በተጨማሪ ማለት ነው። በሶማሊያ ለሚገኘው የሰላም አስከባሪ ሀይል በጅቡቲ ያሉ አብዛኞቹ ሀገራት የገንዘብ እና ሌሎች ወታደራዊ ድጋፍም ይሰጣሉ። ይህም ሌላው ጥቅም ነው። እነዚህ ሀገራት የቀጠናው ሀገራት ጋር ካላቸው የጥቅም ትስስር በመነጨም ወታደራዊ ሀይላቸውን ለማዘመን የሚያስችል የገንዘብ ድጋፍ በግል ለሀገራት የሚሰጡትም እንደተጠበቀ ሆኖ ማለት ነው።

ሀገራቱ እነዚህ መልካም አጋጣሚዎች በጅቡቲ በገነቡት ወታደራዊ ሰፈር አማካኝነት ለኢትዮጵያ የፈጠሩ ቢሆንም ከዚህ ያልተናነሱ ገፋ ሲልም ከዚህ የባሱ ስጋቶችን ይዘው መጥተዋል።

ስጋት

በመጀመሪያ ደረጃ የጎረቤት ሀገር ጂቡቲ የውጭ ሀገራት የወታደር ጦር ሰፈር መበራከት ለኢትዮጲያ የሚኖረው ሥጋት፣ የጅቡቲን በራስ የመወሰን አቅምን ሊያሳጣ ይችላል የሚል ነው። ኢትዮጲያ በጂቡቲ ካላት ከፍተኛ ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ ጥቅም አንጻር ሲገመገም ለኢትዮጲያ ጂቡቲ ከምንም በላይ አስፈላጊ እንደሆነች መደምደም ይቻላል።ታዲያ አሁን በሀገሪቱ ያሉት ልዕለ ሀያሏን አሜሪካ ጨምሮ በኢኮኖሚ እና በዓለም ፖለቲካ ላይ አቅምን የገነቡ ሀገራት ይችን ሀገር አንድም በፖለቲካ አልያም በገንዘብ ማሽከርከር ከቻሉ የኢትዮጲያን በጥቅሞቿ ላይ የመደራደር ሀሳብ አንድ ደረጃ ወደ ላይ ከፍ አደረገው ማለት ነው። ይህም ማለት ጂቡቲ ስለ ውስጣዊ ሁኔታዋ አሜሪካ ወይም ቻይና የምትወስንላት ከሆነ ኢትዮጵያ በቀላሉ ጥቅሞቿን ለማስከበር ከጂቡቲ ጋር ሳይሆን የምትደራደረው፣ ከነዚህ ጡንቻቸው ከዳበረ ሀገራት ጋር ይሆናል ማለት ነው። ይህ ደግሞ ለኢትዮጵያ ነገሩን በጣም ከባድ ያደርግባታል። ይህ አንዱ ስጋት ነው።

ሌላው ስጋት ደግሞ ኢትዮጲያ ብሎም የቀጠናው ሀገራት ከማንም ያልወገነ ግንኙነት ከሀያላኑ ሀገራት ጋር በመመስረት ከድህነት ለመውጣት የሚያደርጉትን ጥረት “ከእኔ” ወይም “ከነሱ” በሚል የቡድን ስሜትን መሰረት ባደረገ የሀገራቱ ፉክክር ምክንያት ይህን ጥቅም ሊያጡ  ይችላሉ። ለዚህ ደግሞ ለአለማችን ቁርሾ የሚበረክትበትን የደቡብ ቻይና ባህር አካባቢ ያሉ ሀገራትን ሁኔታ ብቻ መመልከት በቂ ነው። በዚህ ቀጠና ያሉ እንደ ፍሊፒንስ፣ ቬትናም፣ ማሌዥያ እና የመሳሰሉት ሀገራት በዋናነት  በአሜሪካ እና በቻይና በሚደረገው ቁርሾ ከአንዳችን ጋር ተሰለፉ በሚል ወዲያና ወዲህ ሲመቱ አይተናል። አሜሪካን TPPA (Trans Pacfic Partinership Agreement) በሚል ከቀረጥ ነጻ ምርት ወደ ሀገሬ ታስገባላችው ስትል በኢኮኖሚያዊ ጥቅም ስትሰበስብ፣ ቻይና ደግሞ በሌላ ጥቅም መልሳ ስትወስዳቸው መታዘብ ችለናል። ስለዚህ ይህ ቀጠናም የዚህ ጎራ አሰላለፍ ሰለባ መሆኑ አይቀርም። ይህ ደግሞ እንደገለጽኩት ከድህነት ጋር ትግል ላይ ላሉ  ኢትዮጵያ እና መሰል ሀገራት አንድ አማራጭን ብቻ የሚሰጥ በመሆኑ ለጉዳት የሚዳርግ እንጂ ለጥቅም የማይሆን ነው።

ሶስተኛው ስጋት ከሳዑዲ ጋር ይያያዛል። ይህች ሀገር የየመንን ግጭት ተከትሎ ከኤርትራ መንግስት ጋር የፈጠረችው የአንድ ወቅት ሽርክና የኤርትራን ጂኦ ፖለቲካዊ ጠቃሚነት በማሳደግ የሻቢያን አምባገነን መንግስት እንደገና እንዲያንሰራራ ያደርጋል በሚል ባንድ ወቅት መነጋገሪያ እንደነበር የሚታወስ ነው። ከዚህ አንፃር በተለይ በጂቡቲ የምትገነባው ወታደራዊ ሰፈር ያን ያህል ትልቅ ስጋት ለኢትዮጵያ ላይኖረው ይችላል። ከዚህ ይልቅ እንዲያውም የግብፅን በአካባቢው መስፋፋትና የተዳከመች ኢትዮጵያን የመፍጠር ውስጣዊ አጀንዳ ማስፈጸምን ለመግታት ሊረዳ ይችላል። ነገር ግን ይህንን የሳዑዲን መስፋፋት ተከትሎ ግብፅን መሰረት ያደረገ በኢትዮጵያን ላይ ስጋት መፍጠሩ አይቀሬ ነው።

ግብጽ እና ሳዑዲ በሶሪያ ጉዳይ ባላቸው አቋም ምክንያት ከሰሞኑ አለመግባባታቸው አይሏል። በተለይ ሳዑዲ በጂቡቲ የጦር ካምፕ እገነባለው ማለቷ ግብፅን ስጋት ላይ እንደ ጣላት ዘኒው አረብ (The New Arab) የተባለ ድረ ገጽ በስፋት አስነብባል። ይህን ስጋት ተከትሎ ምን አልባትም ግብፅ ወደቀጠናው እጇን በረጅሙ እንድታስገባ ምክንያት ሊሆን ይችላል። ይህ ደግሞ ለኢትዮጲያ ትልቅ አደጋ መሆኑ አይቀርም።

በአጠቃላይ በጂቡቲ ያለው ሁኔታ ከሁሉም ሀገራት በላይ በዚች ሀገር ኢኮኖሚያው ጥቅም ያላት ኢትዮጵያን በገንዘብ እና በፖለቲካዊ ተፅዕኖ እኩል መደራደር ከማትችላቸው ሀገራት ጋር ፊት ለፊት ሊያላትማት የሚችል ሥጋት ይዞ ብቅ ማለቱን ተገንዝቦ ፍተሻ ማድረጉ ይመከራል።

በመንግስት ሊወሰዱ የሚገቡ የፖሊሲ አቅጣጫዎች

ሀገር ውስጥ በሚታተም አንድ የግል ጋዜጣ ላይ በዲሴምበር 31 በወጣው ጽሁፍ ይህን በጅቡቲ ያለውን የሀያላን ሀገራት ወታደራው እንቅስቃሴ መበራከት ለመቋቋም ኢትዮጲያ ጥቅሞቿን ለማስከበር የባሀር ሀይል ወይም ወታደራዊ ሰፈር በጂቡቲ ልትገነባ ይገባል የሚል ምክረ ሀሳብ ቀርቦ ተመልክተናል። ይህ አንድ አራጭ መሆን ቢችልም ግን ኢትዮጵያ ይህን ማድረግ የሚያስችላት ወይም ከፍተኛ ወጭ መቋቋም የምትችልበት ኢኮኖሚያዊ አቅም አላት ወይ? የሚለው አጠያያቂ ነው።

ስለዚህ ሀሳቡ መልካም ቢሆንም ከሚያስፈልገው የገንዘብ አቅም እና የዘርፉን የሰው ኃይል እንደ አዲስ ለማቋቋም ከሚወስደው ጊዜ አንጻር ይህ ብዙም የሚያስኬድ መፍትሄ አይመስለኝም። ከዚህ ይልቅ መንግስት ተለዋዋጩን የአፍሪካ ቀንድ ፖለቲካ በየጊዜው በመተንተን የሚያጋጥሙትን እና ሊያጋጥሙ የሚችሉ ስጋቶችን ቀድሞ ለይቶ በየወቅቱ የሀገሪቱን ተጋላጭነት ሊቀንሱ የሚችሉ ጊዜያዊ እና ዘላቂ እርምጃዎችን መውሰዱ የተሻለ ይሆናል። ለምሳሌ የጅቡቲ ወደብን መጠቀም እድልን የሚያሳጣ ተግዳሮት ሊፈጠር ከቻለ ሌሎች የወደብ አማራጮችን ማየት የጉዳት መጠኑን ለመቀነስ ያስችላል። ከዚህ ጋር በተያያዘ ጅቡቲ ደቡብ ሱዳን እና ኢትዮጵያ ሊገነቡት ያሰቡት የታጁራ ወደብ ግንባታን ማፋጠን ለኢትዮጲያ ያለው ተቃሚነት ትልቅ ሊሆን ይችላል። ምክንያቱም በዚህ የታጁራ ወደብ ከቻይና ጦር ውጭ ብዙም ወታደራው እንቅስቃሴ አይስተዋልም። ይህ ደግሞ በተሻለ ሰላማዊ ሁኔታ ወደቡን ለመጠቀም ለኢትዮጵያ ጥሩ እድል ይፈጥርላታል።

በአጠቃላይ በዋናነት ድህነትን ማጥፋት ማዕከል ያደረገው የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ እስካሁን ባለው ነባራዊ እና አካባቢያዊ ሁኔታ ብዙ ርቀት ያስኬደ ቢሆንም አሁን የተፈጠሩት እና እየተፈጠሩ ያሉ ሥጋቶችን ለመመለስ የሚያስችል እና የሀገሪቱን ተጋላጭነት መቀነስ የሚያስችል አማራጮችን መመልከት ጊዜው መሆኑን ጠቋሚ ነው።¾       

ይምረጡ
(3 ሰዎች መርጠዋል)
728 ጊዜ ተነበዋል

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us