የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ ክለሳ የሚያሻው፤ የደቡብ ሱዳን እና የግብፅ ግንኙነት

Wednesday, 08 February 2017 14:23

በሳምሶን ደሳለኝ

 

ባለፉት አምስት አመታት በኢትዮጵያ እና በደቡብ ሱዳን መካከል የነበረው  ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነቶች እያዘቀዘቁ፣ በፍጥነት እየወረዱ ይገኛሉ። ደቡብ ሱዳን ነፃነቷን ካገኘች ማግስት ጀምሮ እስከ 2013 ድረስ ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር የነበራት ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት፣ መቶ በመቶ በመተማመን ላይ የቆመ እንደነበር የሚታወስ ነው። በተለይ ዓለም ዓቀፉ ማሕበረሰብም ለደቡብ ሱዳን ኢኮኖሚያዊ ዲፕሎማሲያዊ እና የጸጥታ ድጋፍ እንዲያደርግ የኢትዮጵያ መንግስት ሚና ከፍተኛ ነበር።

የቀድሞ የአሜሪካ ፕሬዝደንት ባራክ ኦባማ የፀጥታ አማካሪ የነበሩት ሱዛን ራይስ “ኢትዮጵያ የደቡብ ሱዳን አዋላጅ” ነበረች ሲሉ ምስክርነታቸውን መስጠታቸው በሁለቱ ሀገሮች መካከል የነበረውን የግንኙነት ደረጃ የሚያሳይ ነው። ሆኖም ግን በአሁን ሰዓት ከ“አዋላጅነት” ወደ አለመተማመን የወረደው የሁለቱ ሀገሮች ዲፕሎማሲ ግንኙነት ለሌሎች ሀገሮች መልካም ዕድል ይዞ መጥቷል። በተለይ በኢትዮጵያ ስትራቴጂክ ጥቅሞች ላይ በተቃርኖ ለቆሙት ለግብፅ እና ለኤርትራ አገዛዞች አጋጣሚው ሰርግና ምላሽ የሆነላቸው መስሏል። እንዲሁም ዑጋንዳ ኬኒያ የራሳቸውን ፍላጎቶች ለማስፈጸም ከፍተኛ ክፍተት አግኝተዋል።

በአንጻሩ ኢትዮጵያ በደቡብ ሱዳን ፖለቲካ ውስጥ የነበራት የገለልተኝነት ሚና እና አደራዳሪነት ጥያቄ ውስጥ ከመውደቁ በላይ፣ ፕሬዚደንት ሳል ቫኪር ማያርዲት ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር ዲፕሎማሲያዊ እሰጣ ገባ ውስጥ ገብተዋል። በተለይ በአዲሱ የናምቢያ ፕሬዚደንት በዓለ ሹመት ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃ/ማሪያም ደሳለኝ ለፕሬዝደንት ሳልቫኪር ማያርዲት እጃቸውን ሰንዝረው ሰላምታ ቢያቀርቡላቸውም፣ ፕሬዝደንት ሳልቫኪር ምላሽ ከመስጠት ተቆጥበው ቅሬታቸውን ለማሳየት ተጠቅመውበታል። በወቅቱም በሁለቱ ሀገሮች መካከል ያለው ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት እየሻከረ መምጣቱ ጥሩ ማሳያ ነበር።

ከዚህ በተጨማሪ፣ በጃንዋሪ 10 ቀን 2017 ፕሬዝደንት ሳልቫኪር ማያርዲት በግብፅ ያደረጉትን ይፋዊ የሥራ ጉብኝት ተከትሎ፣ ለፕሬዝደንቱ ቅርብ ናቸው የተባሉት አብርሃም ቾል ለNyamilepedia ዜና ማሰራጫ እንደተናገሩት “ደቡብ ሱዳን ብሔራዊ ጥቅሟን ለኢትዮጵያ መሥዋዕት አታቀርብም” ብለዋል። አያይዘውም፣ “ደቡብ ሱዳንን በማስቀደም ተስማምተናል። ለዚህም ነው፣ ከግብፆች ጋር የተወያየነው። እነሱ ከሌሎች ጎረቤት ሀገሮች በተሻለ አቅርቦት አድርገዋል።” ሲሉ አንፃራዊ አገላለጽ ተጠቅሟል።

እንዲሁም በዚሁ ጉብኝት የግብጹ ፕሬዚደንት አል-ሲሲ እና የደቡብ ሱዳን ፕሬዚደንት ሳል ቫኪር ማያርዲት የነጭ አባይ ውሃን መጠን በማበልጸግ ዙሪያ እና ከሕዳሴው የኃይል ማመንጫ ግድብ ግንባታ ጋር በተያያዘ ሥውር አፍራሽ ሥራዎችን ለመስራት ከስምምነት ላይ መድረሳቸው ዓብይ ሚዲያዎች ዘግበውታል። አንዳንዶቹ መገናኛ ብዙሃን ስምምነቱን መጥፎ ስምምነት (“dirty deal”) ሲሉ ጠርተውታል።

ከዚህ ስምምነት በኋላም ግብፅ ባሳለፍነው ሳምንት የደቡቡ ሱዳን መንግስት ተቃዋሚ ኃይሎች ይዞታን በጦር ጀቶች የደበደበች መሆኗን የደቡብ ሱዳን ታጣቂ ኃይሎች ከሰሞኑ ገልፀዋል። የሳልቫኪየር መንግስት በበኩሉ የግብፅ ተዋጊ አውሮፕላኖች በግዛቱ ገብተው ማንም ላይ ጥቃት አለመሰንዘራቸውን ገልጿል። በዚህ አጋጣሚም ግብፅ ለሳል ቫኪር ማርዲያት መንግስት ያላትን ታማኝነትና ድጋፍ ለማሳየት ተጠቅማበታለች። እንደሚታወሰውም፣ በፀጥታው ምክር ቤት በኩል በደቡብ ሱዳን መንግስት ላይ የጦር መሳሪያ ማእቀብ እንዲጣል በአሜሪካ በቀረበው ሞሽን ላይ፣ ግብፅ ድምፀ-ተአቅቦ በማድረግ ለደቡብ ሱዳን መንግስት አጋርነቷን ማሳየቷ የሚታወቅ ነው።

ግብፅ በደቡብ ሱዳን እና በኢትዮጵያ መካከል የነበረውን ጠንካራ የዲፕሎማሲ ግንኙነት ሰብራ በመግባት በኢትዮጵያ መንግስት ላይ የእጅ አዙር ተፅኖዎችን ለማሳረፍ ጠንክራ እየሰራች ነው። ከዚህም በፊት ኢትዮጵያ በአባይ ወንዝ ላይ ለምትሰራቸው የልማት ፕሮጀክቶች ዓለም አቀፉን ማኅበረሰብ በማስተባበር የብድር አቅርቦት እንዳይሰጥ ማድረግ ችላለች። እንዲሁም ዓለም አቀፉ ኩባንያዎች በሕዳሴው ኃይል ማመንጫ ግድብ ፕሮጀክት ግንባታዎች ላይ እንዳይሳተፉ ከፍተኛ ተፅዕኖ ለማሳደር የሞከረች ቢሆንም አልተሳካላትም። ከዓለም ዓቀፉ ማሕበረሰብ ኢትዮጵያን በዲፕሎማሲ እና በፖለቲካ ለመነጠል ጥረት ብታደርግም አልተሳካላትም። የማታንቀላፋዋ ግብፅ አሮጌውን የውጭ ግንኙነት ፖሊሲዋን በአዲስ መልክ በደቡብ ሱዳን ይዛ ብቅ ብላለች።

ግብፅ በደቡብ ሱዳን ፖለቲካ ውስጥ ሥውር እጇን ማስገባት የምትፈልገው ቢያንስ በሁለት መሰረታዊ ምክንያች ነው። አንደኛው፣ ከዚህ በፊት የግብፅ መንግስታት ይከተሉት የነበረውን ኢትዮጵያን የማተራመስ ፖሊሲ በአዲስ መልክ ለመተግበር ካላቸው ፍላጎት በመነጨ ደቡብ ሱዳንን በአማራጭነት መጠቀምን በመምረጣቸው ነው። ከዚህ በፊት በኤርትራ በኩል ኢትዮጵያን የማተራመስ ፖሊሲያቸውን ሲያስፈጽሙ መኖራቸው የሚታወስ ነው። አሁን ላይ ግን የአስመራ አገዛዝ በደረሰበት ወቅታዊ የፖለቲካ ቁመና የግብፅ አጀንዳ ማስፈጽም የሚችልበት አቅም የለውም። እንደ መንግስት የመቀጠሉ ጉዳዩም አስተማማኝ አይደለም። በተለይ የአስመራ ውስጣዊ ፖለቲካ ለብዙ ወጣት ኤርትራዊያን መሰደድ ምክንያት በመሆኑ ተግዳሮቶቹ ቀላል አይደሉም።

ሁለተኛው፣ ግብፅ ከሕዳሴው ኃይል ማመንጫ ግድብ ግንባታ ጋር የተያያዘ ሥውር አጀንዳ ለማስፈጸም ከመሻት የመጣ ነው። በርግጥ በቀጥታ በሕዳሴው ግድብ ላይ የምታመጣው አደጋ ይኖራል ተብሎ ቢያንስ አሁን ላይ አይገመትም። ሆኖም የኢትዮጵያ መንግስትና ሕዝብ አለመረጋጋት ውስጥ በመክተት፣ ከተዘረጋው የልማት እንቅስቃሴው በመግታት ትኩረቱን ወደ ጸጥታና የማረጋጋት ሥራዎች ላይ እንዲያደርግ አስገዳጅ ሁኔታዎችን መፍጠር ላይ እየሰራች ትገኛለች። በውጭ ግንኙነት ፖሊሲያቸው ኢትዮጵያን ታሪካዊ ጠላት አድርገው ማስቀመጣቸው፣ ከኢትዮጵያ በተሻለ ሁኔታ እንዳይዘናጉ ከመሆናቸውም በላይ ያገኙትን ቀዳዳ ለመጠቀም እንዳይዘናጉ ጉልበት ሆኗቸዋል።

እንዲሁም ግብፆች የደቡብ ሱዳን ውስጣዊ የፖለቲካ ቀውስን በመጠቀም የአልበሽር መንግስት ለመጣል  እየተጠቀሙበት ይገኛሉ። ፕሬዝደንት አልበሽርም ግብፅ የሱዳን መንግስት ተቃዋሚዎችን እየረዳች መሆኑን መነሻ በይፋ ክስ አቅርበዋል። የሱዳን መንግስት በሕዳሴው ኃይል ማመንጫ ግድብ ተጠቃሚ በመሆኑ ለግድቡ ግንባታ ድጋፉን በይፋ መስጠቱ፣ በግብፅ ፖለቲከኞች ጥርስ ውስጥ እንዲገባ አድርጎታል። እንዲሁም የፕሬዝደንት አልበሽር መንግስት ለኢትዮጵያ ሕዳሴ ኃይል ማመንጫ ግድብ ግንባታ ድጋፍ መስጠታቸው፣ በግብፅ በኩል ታሪካዊ ጠላት ተደርገው ተፈርጇል። በተጨማሪም ሱዳን በሕዳሴው ግድብ ግንባታ ተቃውሞዋን አለማሰማቷ፣ ግብፅ በዓለም ዓቀፉ ማኅበረሰብ ፊት በሕዳሴው ግድብ ግንባታ ዙሪያ ተፅዕኖ ለማሳደር የምታደርገው እንቅስቃሴ አርግቦባታል።

ይህ የግብፅ እምቅ ፍላጐቷን ይዛ በአዲስ መልኩ የቀንዱን ሀገሮች ለማተራመስ ደቡብ ሱዳንን የመጨወቻ ካርድ አድርጋ ብቅ ማለቷ፣ አዲስ የኃይል አሰላለፍ እንዳይፈጠር ተሰግቷል። በተለይ ኢትዮጵያ የደቡብ ሱዳን አዋላጅ ሀገር ተደርጋ እየተወሰደች፣ ግብፅ ከየት መጣች ሳትባል የደቡብ ሱዳንን መንግስት እምነት ማግኘቷ የኢትዮጵያን የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ ጥያቄ ውስጥ የሚጥል ብቻ ሳይሆን በግብፅ እና በኢትዮጵያ መካከል ከፍተኛ ግጭት እንዳይፈጠር ስጋታቸውን የሚያስቀምጡ ባለሙያዎች ተበራክተዋል። ምክንያቱም፣ ደቡብ ሱዳን የቀድውን የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ሕይወት ሕልፈት ተከትሎ ለሶስት ቀናት ብሔራዊ ባንዲራዋን ዝቅ አድርጋ ያውለበለበች ሀገር፣ ዛሬ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅም ላይ አደጋ ከሚጥሉ ሀገሮች ጎን መሰለፍን በምክንያትነት ያነሳሉ። የደቡብ ሱዳን መንግስት ቅሬታዎችንም ይጠቃቅሳሉ።

በሳልቫኪር የሚመራው የደቡብ ሱዳን መንግስት፣ ኢትዮጵያ ዶክተር ሪክ ማቻርን ትደግፋለች ሲል ይከሳል። እንዲሁም ኢትዮጵያ ከአሜሪካ መንግስት ጋር ያላትን ጥብቅ ግንኙነት በማንሳት የኢትዮጵያን እቅስቃሴ በጥርጣሬ እንደሚያዩት በተደጋጋሚ የደቡብ ሱዳን ባለስልጣኖች ሲናገሩ ይሰማል። በተለይ ከ2013 እስከ 2015 የተነሳው የእርስ በእርስ ጦርነት በሁለቱ ሀገሮች መካከል አለመተማመን ፈጥሯል። ይህም ሆኖ የእርስ በእርስ ጦርነቱን የሽግግር መንግስት በማቋቋም ለመፍታት ተችሎም ነበር። ሆኖም የሽግግር መንግስቱ ም/ፕሬዝደንት ዶክተር ሪክ ማቻር ከሽግግር መንግስቱ በመውጣት ወደ ጫቃ መግባታቸው የሚታወስ ነው።

ይህንን የዶክተር ሪክ ማቻር ከሽግግር መንግስቱ መውጣት ካስቆጣቸው ሀገሮች አንዷ ኢትዮጵያ ነበረች። በይፋም ዶክተር ሪክ ማቻር የተቃዋሚውን ጎራ መሪ መሆናቸውን ኢትዮጵያ እንደማትቀበል አሳውቃለች። ዶክተር ሪክ ማቻርንም ከግዛቷ አባራለች።  በምትካቸው የተተኩትን ጀነራል ታባን የተቃዋሚ ጎራ ወኪል መሆናቸውን እውቅና ሰጥታለች። ኢትዮጵያ ይህን ያህል ርቀት ሄዳ ለደቡብ ሱዳን መንግስት መሪዎች መተማመንን ብትፈጥርም፣ የፕሬዝደንት ሳል ቫኪር መንግስት ከግብፅ ጉያ ውስጥ ለመውጣት ግን ፈቃደኛ አይደሉም።

በብዙ ባለድርሻ አካላትም ግልፅ ምላሽ ያጣው ጉዳይ ቢኖር፣ የደቡብ ሱዳን እና የኢትዮጵያ መንግስት ዲፕሎማሲያዊ ሰጣ ገባ የተፈጠረው፣ ሁለቱ ሀገሮች በርግጥ እኩያ ሀገሮች ሆነው ነው? ወይንስ የኢትዮጵያ የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ መርሆች ከገቢራዊነት የራቁ በመሆናቸው ነው? የሚሉት ይገኙበታል።

የኢትዮጵያ መንግስት የአፍሪካን ቀንድ ከሕዳሴው ጉዞ አንፃር ገምግሞ ያስቀመጠው አቅጣጫ፣ ገቢራዊነቱ (Pragmatism) አጠያያቂ ይመስላል። ይኸውም፣ በአካባቢያችን (በቀንዱ) ሰላም እንዲሰፍን ማድረግ፤ ጠንካራ የኢኮኖሚ ትስስር ማድረግ፤ ኢጋድን ማጠናከር፤ የአባይ ወንዝ በሽታን መቋቋም መሆኑን በማያሻማ መልኩ ተቀምጧል። በርግጥ ከአካባቢው ጋር ጤነኛ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ መስተጋብር መፍጠር ለኢትዮጵያ እድገት ሁለንተናዊ ጠቀሜታው ምትክ አልባ ነው። ጥያቄው ግን፣ በኢትዮጵያ ፍላጎት ብቻ ከላይ የተቀመጡ አቅጣጫዎችን ተግባራዊ ማድረግ ይቻላል ወይ? የሚለው ነው። 

በዚህ ሰነድ የአባይ ወንዝ በሽታ መቋቋም በሚለው ክፍሉ፣ “የግብፅ ሕዝብ የገዥው መደብ ፕሮፖጋንዳ ሰለባ በመሆኑ እንጂ አቋማችን መብትና ጥቅሙን የማይነካ በመሆኑ፣ ፀረ ኢትዮጵያ አቋም የሚይዝበት ምንም ምክንያት የለም። በአባይ ወንዝ አጠቃቀም ጉዳይ ላይ ከምናደርጋቸው ትግሎች ውስጥ በጣም ውስብስብ የሚሆነውና በዚያም ልክ ከፍተኛ ግምት የሚሰጠው ጉዳይ የግብፅ ህዝብ የአቋማችንን ፍትሐዊነት እንዲገነዘብ የማድረግ ጉዳይ ነው። ይህ ስራ ከባድ ቢሆንም ያለመታከትና ተስፋ ባመቁረጥ ሁልጊዜም ሊፈፀም የሚገባው ነው። በማንኛውም ወቅት የኢትዮጵያ ህዝብና መንግስት የግብፅን ህዝብ የሚጎዳ ወይም የሚዘልፍ ነገር እንዳይነገርና እንዳይሰራ ማድረግ የመጀመሪያው ጉዳይ ይሆናል። ከዚህም ባሻገር የተለያዩ መድረኮችን በመጠቀም መልዕክታችንን ለግብፅ ህዝብ ለማድረስ ያለመታከት መስራት ይኖርብናል።

ከላይ የተጠቀሱት ስራዎች መሰራት ያለባቸው ቢሆኑም፤ በአጭርና በመካከለኛ ጊዜ የግብፅ መንግስትን አቋም ያስቀይራሉ ተብሎ አይገመትም። ስለሆነም የራሳችንን አቅም ቆጥበን በአባይ ወንዝ ላይ ለልማታችን አስፈላጊ የሆኑና ከፍትሃዊ አቋማችን የሚመነጩ ስራዎችን መስራት መቀጠልና ማጠናከር አለብን። በዚህ ረገድ የውጭ ብድርና እርዳታ የማግኘት ዕድላችን ውስን እንደሆነ በመገንዘብ በወሳኝ መልኩ በራሳችን ውሱን አቅም ላይ መመስረት ይኖርብናል። ግብጾች በእጅ አዙርና በቀጥታ ሰላማችንን ለማደፍረስ የሚያደርጉትን ጥረት በማጋለጥ፣ ከጎረቤቶቻችን ጋር ያለንን ግንኙነት ከላይ በተጠቀሰው አኳሃን በማሻሻልና ተጋላጭነታችንን በማስወገድ ራሳችንን መከላከል አለብን። ግብፅ ከዚህ አልፋ ቀጥተኛ ወረራ የመፈፀም ዕድሏ በጣም ትንሽ ቢሆንም፤ ራሳችንን የመከላከል አቅማችንን ከኢኮኖሚ እድገታችን ጎን ለጎን ማጎልበት አለብን።

እነዚህን ስራዎች በአግባቡ እስከሰራን ድረስ በአጭርና በመካከለኛ ጊዜም ባይሆን ውሎ አድሮ የግብፅ ገዥው መደብ የኛን ፍትሃዊ አማራጭ ከመቀበል የተሻለ መንገድ እንደሌለ መቀበሉ አይቀርም። ስለሆነም ከግብፅ ጋር ያለውም ችግር ቢሆን ከረጅም ጊዜ አኳያ በሰላማዊ መንገድ ሊፈታ የሚችል ነውና ከወዲሁ የሰላሙን መንገድ ጠበቅ አድርገን ይዘን መራመድና የግብፅን መንግስት ወደ ሰላም መንገድ ለመመለስ ያለመታከት መስራት ይኖርብናል። በእርግጥ ይህ ስራ በአጭር ጊዜ ውስጥ ተጨባጭ ውጤት የሚያስገኝ ስለሆነ ዋናው ትኩረታችን ከላይ የተዘረዘሩትን ሌሎች የመፍትሄ ሃሳቦች መተግበር ላይ መሆን ይኖርበታል።”

በዚህ ሰነድ የሰፈረው ፍሬ ነገር በየትኛውም መመዘኛ ጤናማ ግንኙነት ከሚፈልግ ሀገር የሚመነጭ ነው። ሆኖም ግን የቀንዱን ሀገሮች የፖለቲካ አሰላለፍ የተገነዘበ መሬት የሚይዝ አድርጎ መቀበል ግን ከባድ ነው። ለዚህ በቂ ማሳያ የሚሆነው፣ ግብፅ ከደቡብ ሱዳን ጋር የፈጠረችው ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ከሁለትዮች የልማት ግንኙነት ባሻገር፣ የኢትዮጵያ የልማት አውታሮችን ለማውደም ያለመ ሥውር አጀንዳ ያዘለ መሆኑ ነው። ይህ ማለት ግብፆች ኢትዮጵያን በውጭ ግንኙነት ፖሊሲያቸው በታሪካዊ ጠላትነት አስቀምጠው የሚሰሩ ሲሆን፤ በአንፃሩ ኢትዮጵያ በተራዘመ ትግል የግብፅ ገዢ መደቦች ሆኑ ሕዝቦችን ልብ የማሸነፉ የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ ቀርፃ እየሰራች ነው። የፖሊሲው ውጤቱ ግን ኢትዮጵያን በማተራመስ ቀጥሏል።

ይህንን የግብፅ የማተራመስ ፖሊሲን መከላከል የሚቻለው፣ የኢትዮጵያ መንግስት የግብፅ ገዢ መደቦች እና የህዝቡን በናይል ውኃ አጠቃም ላይ ያላቸውን የተዛባ አቋም በታሪካዊ ጠላትነት በሚፈረጅ የፖሊሲ አቅጣጫ መቀየስ ሲቻል ብቻ ነው። በዚህ መልኩ የውጭ ግንኙነት ፖሊሲው ማስቀመጥ ከተቻለ፣ በቀንዱ ሀገሮች መካከል በግብፅ መነሻ ለሚከሰቱ ማናቸውም አይነት እንቅስቃሴ ከተቀመጠው ፖሊሲ መነሻ ምላሽ መስጠት ያስችላል።

ለምሳሌ ግብፅ ከደቡብ ሱዳን ጋር በፈጠረችው ግንኙነት ኢትዮጵያን ለማተራመስ በጋራ እየሰሩ መሆናቸው የሚታወቅ ነው። በዚህ ውስጥ የግብፅ እንቅስቃሴን በታሪካዊ ጠላትነት የሚመለከት የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ የምናራምድ ከሆነ ገቢራዊ እርምጃ ለመውሰድ ቀላል ነው። ይኸውም፣ ኢትዮጵያ በአብዬ ግዛት ያሰፈረችውን የሰላም አስከባሪ ጦር ሰራዊት ማውጣት ይጠበቅባታል። ይህን በማድረግ ለደቡብ ሱዳን መንግስት ግልጽ ምላሽ መስጠት ይቻላል። ይህንን በማድረግ የግብፅን የማተራመስ ፖሊሲ ለመተግበር በማያስችላት ከባቢያዊ ሁኔታዎች ውስጥ ማስቀመጥ ይቻላል።

እንዲሁም የኢትዮጵያ ጦር አብዬ ግዛት ለቆ ሲወጣ፣ የደቡብ ሱዳን መንግስት በጃንጃዊት አረብ ሚኒሻዎች እና በዲንካ ጎሳዎች በሚነሳው ጦርነት ተወጥሮ የመፍረስ አደጋዎች ተደቅነውበት ከዚህ የአፍራሽ ሚናው እንዲቆጠብ ይገደዳል።¾     

ይምረጡ
(2 ሰዎች መርጠዋል)
619 ጊዜ ተነበዋል

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us