“ስማቸውን ባልጠቅስም በሌሎች አገሮች እንዳየኋቸው ሳይሆን የአገራችሁ ህዝብ ሰው አክባሪ እና ጨዋ ነው”

Wednesday, 15 February 2017 13:36

“ስማቸውን ባልጠቅስም በሌሎች አገሮች እንዳየኋቸው ሳይሆን

የአገራችሁ ህዝብ ሰው አክባሪ እና ጨዋ ነው”

                                 ሚስተር ሱሚት ዳሳናያኬ

በኢትዮጵያ የስሪላንካ አምባሳደር

በይርጋ አበበ

ስሪላንካ ወይም በቀድሞ ስያሜዋ “ሲሎን” በህንድ ውቅያኖስ አቅራቢያ ከሚገኙ የህንድ አጎራባች አገሮች መካከል አንዷ ስትሆን ለ450 ዓመታት የተለያዩ የአውሮፓ ቅኝ ገዥዎች በጉልበት ሲገዟት የነበረች አገር ነች፡፡ ከኔዘርላንድ እስከ እንግሊዝ የዘለቀው የአገሪቱ የቅኝ ተገዥነት ዘመን ፍጻሜ ያገኘው በ1948 እ.ኤ.አ. ቢሆንም አገሪቱ ግን ለ30 ዓመታት ገደማ በእርስ በእርስ ጦርነት ምክንያት እንደገና በሌላ የባሩድ ሽታ ስትታጠን ኖራለች። ከዓለም በህዝብ ብዛት ሁለተኛ ከሆነችው ህንድ 25 ኪሎ ሜትር በባህር የምትዋሰነው ትንሿ አገር ለ30 ዓመታት ገደማ የዘለቀው የእስር በእርስ ጦርነት ፍጻሜውን ያገኘው በ2009 እ.ኤ.አ. ሲሆን አገሪቱ በአሁኑ ወቅት በጥምረት መንግስት ትመራለች።

ስሪላንካ በቅርቡ በኢትዮጵያ ኤምባሲዋን በመክፈት ከኢትዮጵያ እና ከአፍሪካ ህብረት ጋር ሁሉን አቀፍ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ለመፍጠር እየሰራች መሆኗን የሚናገሩት አምባሳደሯ “በአጠቃላይ የአዲስ አበባውን ጨምሮ በአፍሪካ ስድስት ኤምባሲዎች ብቻ ናቸው ያሉን” ሲሉ ተናግረዋል።

በኢትዮጵያ የስሪላንካ አምባሳደር ሚስተር ሱሚት ዳሳናያኪ ከሰንደቅ ጋዜጣ ዝግጅት ክፍል ጋር ሰፋ ያለ ቃለ ምልልስ በጽ/ቤታቸው አድርገዋል። ዝግጅት ክፍላችን በተለያዩ ዓለም አቀፍ ጉዳዮች ዙሪያ ከአምባሳደሩ ጋር የተደረገውን ቃለ ምልልስ ለአንባቢያን በሚመች መልኩ ከዚህ በታች አቅርበነዋል።

ሰንደቅ፡- እ.ኤ.አ ከ1505 እስከ 1948 ከዘለቀው የቅኝ ግዛት ዘመን የተላቀቀችው ስሪላንካ ለ30 ዓመታት አካባቢም በእርስ በእርስ ጦርነት ስትታመስ ቆይታ ነበር። በአሁኑ ሰዓት ግን አገራችሁ የመካከለኛ ኢኮኖሚ ባለቤት ሆናለች። ከቅኝ ግዛት እና ከእርስ በእርስ ጦርነት ማግስት እንደዚህ አይነት ስኬት እንዴት ሊመዘገብ ቻለ?

ሚስተር ሱሚት፡- አገራችን ከቅኝ ግዛት በ1948 ነጻነቷን ያገኘች ትንሽ አገር ስትሆን (የአገሪቱ የቆዳ ስፋት 65,610kmብቻ ነው) ሁለት ዋና ዋና ፓርቲዎች ያሏት የመድብለ ፓርቲ ስርዓት የምትከተል አገር ነች። እንደሚታወቀው መድብለ ፓርቲ ቢኖርም ስልጣን የሚይዘው አንደኛው ብቻ በመሆኑ አገራችን ወደ ጦርነት ልትገባ ችላለች። ይህ ጦርነት አገራችንን በማንኛውም መልኩ እየጎዳት በመሆኑ ወደ ድርድር በማቅናት የእርስ በእርስ ጦርነቱ እ.ኤ.አ በ2009 ፍጻሜ አገኘ። በአገራችን ታሪክም ለመጀመሪያ ጊዜ ሁለቱ ዋና ዋና ፓርቲዎች (ለ50 ዓመታት በላይ ከስልጣን ተገልሎ የቆየው እና ስልጣኑን በብቸኝነት ለ50 ዓመታት የተቆናጠጠው መንግስት) ሌሎች ትንንሽ ፓርቲዎችን ባሳተፈ መልኩ በተካሄደ ውይይት በደረሱበት ስምምነት ዴሞክራሲያዊ የአንድነት መንግስት መሰረቱ።

የፖለቲካ ኢኮኖሚ ተልዕኮዎችን በኃላፊነት የሚወስደው መንግስት መሆኑ ይታወቃል። ሁለቱ ዋና ዋና ፓርቲዎች ያለ ማንም ጣልቃ ገብነት ወደ መንግስት ስልጣን ከመጡ ደግሞ አገራችን ባለማቋረጥ እድገት ውስጥ ማለፍ ቻለች። ለዚህ ደግሞ ምክንያቱ መንግስቱ በህዝብ እምነት እንዲጣልበት ያደረገ ሲሆን ቀጥተኛ የውጭ ኢንቨስትመንት ስሪላንካን ተመራጭ በማድረጋቸው ደግሞ ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ በስሪላንካ ላይ እምነት ማሳደር ቻለ። የአገራችን ኢኮኖሚ እድገት ሊመጣ የቻለው በዚህ መልኩ በተደረገ ስራ ነው።

ከዚህ በተጨማሪም እ.ኤ.አ እስከ 1978 ድረስ በኮማንድ ኢኮኖሚ ስር የነበረው የአገራችን የኢኮኖሚ ፖሊሲ ሊበራላይዝ መደረጉን ተከትሎ ለወጣቶች ሰፊ የስራ እድል የሚሰጡ የኢንዱስትሪ ፓርኮችን በስፋት መገንባት ጀመርን። ኤክስፖርትን ማዕከል ያደረገ የማኑፋክቸሪንግ አምራች ፋብሪካዎችን በስፋት ገነባን። የውጭ ኢንቨስትመንት ፖሊሲን በመቅረጽ ኢንቨስተሮችን መሳብ ቻልን። ያ ውሳኔ ትክክለኛ የፖለቲካ ውሳኔ ነበር። ምክንያቱም ያ ውሳኔ ለበርካታ ወጣቶች የስራ እድል ከመፍጠሩም በላይ የሳይንስና ቴክኖሎጂ የእውቀት ሽግግርን መተግበር እንድንችል አድርጎናል።

ሰንደቅ፡- የጣምራ መንግስት እስከመመስረት የደረሰ ብሔራዊ እርቅ እና መግባባት የተፈጠረው የፖለቲካ ስልጣንን በጋራ ለመጠቀም ብቻ ነው ወይስ ከዚያ የዘለለ አገራዊ አጀንዳዎችን ማከናወን ችላችኋል?

ሚስተር ሱሚት፡- ለብሔራዊ እርቅ መንገዱን የጠረገው ሁሉንም ወገን አሳታፊ የሆነ ውይይትና ድርድር ተካሂዶ ገለልተኛ ምሁራንና የህዝብ ወኪሎች በተገኙበት ብሔራዊ አንድነትን እና ኢኮኖሚያዊ እድገትን ማሳደግ በሚቻልበት መልኩ የህገ መንግስት ቀረጻ ሂደት ተካሂዷል። አገራችን ከቅኝ ግዛት ነጻ ስትወጣ የነበራትን ህገ መንግስት እ.ኤ.አ በ1972 ማሻሻል ብትችልም በ1978 እንደገና ለመቀየር ተገድዳለች። በአሁኑ ወቅት ደግሞ አዲስ የተዋቀረው የዴሞከራሲያዊ አንድነት መንግስት በመርህ ደረጃ ሁሉም ፓርቲዎች አዲስ ህገ መንግስት መውጣት አስፈላጊ መሆኑን በተስማሙበት መሰረት ሁሉንም ወገን የሚያሳትፍ አዲስ ህገ መንግስት ለማውጣት ምሁራንና የህዝብ ወኪሎች ከፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች ጋር ከወራት ፊት ጀምሮ ውይይት እያካሄዱ ነው። የህገ መንግስት አርቃቂ ኮሚቴዎቹ ሁሉንም የአገሪቱ ክፍል ተዘዋውረው ከህዝብ ወኪሎች ጋር ከተወያዩ በኋላ የሚያዘጋጁት ረቂቅ ይቀርብና በመንግስት ደረጃ ውይይት ይደረግበታል።

ረቂቁ በዚህ መልኩ ከተዘጋጀ በኋላ እንደገና ወደ ህዝብ ቀርቦ ህዝብ ሲቀበለው ህገ መንግስት ሆኖ ይወጣል ማለት ነው። አገራችን በምታወጣው አዲሱ ህገ መንግስት የእምነትና የአመለካከት ነጻነት ሰብአዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች ይበልጥ የሚከበሩበት ይሆናል ብዬ አስባለሁ። ምክንያቱም በቀድሞው ህገ መንግስት በስፋት ያልነበሩትን ችግሮች የኢኮኖሚ እድገት እና ብሔራዊ ጉዳዮችን የመሳሰሉ ወሳኝ ነጥቦች አዲሱ ህገ መንግስት በስፋት የሚዳስስ በመሆኑ ነው። ከዚህ በተጨማሪም ሁሉም የፖለቲካ እና ብዙሃኑ የህዝብ ክፍል የሚሳተፍበት ህገ መንግስት መሆኑም ዴሞክራሲን በተሻለ መንገድ ማጎልበት ይችላል። 

ሰንደቅ፡- ስሪላንካ ወደ 21 ሚሊዮን የሚጠጋ ህዝብ አላት። ከዚህ ህዝቧ መካከል የኃይማኖትና የጎሳ ብዝሃነት ያላት አገር ብትሆንም የምትከተለው የመንግስት ስርዓት ግን አሃዳዊ ነው። ከዚህ የመንግስት ስርዓት ይልቅ ፌዴራላዊ ስርዓት የሀይማኖትና የጎሳ ብዝሃነት መብትን ለማስከበር የተሻለ እንደሆነ ይነገራል። የኃይማኖትና የብሄር  የብዝሃነት በአሃዳዊ ስርዓት እንዴት ይታያል?

ሚስተር ሱሚት፡- በህገ መንግስቱ በግልጽ የመንግስቱ ስርዓት አኃዳዊ እንደሆነ ተገልጿል። በግልጽ መሬት ላይ የሚያሳየውም አገራችን የጎሳ እና የኃይማኖት ብቻ ሳይሆን የፖለቲካ ብዝሃነት (መድብለ ፓርቲ ሲስተም) ያለባት መሆኑን ነው። በአኃዳዊ የመንግስት ስርዓት ውስጥ ሆነን የሀይማኖት፣ የባህል፣ የጎሳ እና የፖለቲካ ብዝሃነት በአገራችን ይተገበራል። የመንግስቱ ስርዓት (አኃዳዊ መንግስት) እነዚህን ብዝሃነቶች አቻችሎ ለመኖር ችግር አልሆነብንም። ነገር ግን ስልጣንን ከአንድ ማዕከል አውጥቶ ወደ ክልሎች ማውረድ ስለሚቻልበት መንገድ ውይይት በማድረግ በአዲሱ ህገ መንግስት ችግሩ እንዲቀረፍ ይደረጋል ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ።

ከዚህ በተረፈ ግን ስለ ሀይማኖት ነጻነትና የብሔር (የጎሳ) እኩልነት አሁን በምንጠቀምበት ህገ መንግስትም ዋስትና ያገኘ በመሆኑ አገራችን በጎሳ እና በኃይማኖት ብዝሃነት ላይ ችግር ገጥሟት አያውቅም። ማንኛውም ሰው የፈለገውን እምነት መቀበልን ጨምሮ የሃይማኖት ተቋማትን (መስጊዶችን፣ ቤተ ክርስቲያኖችን፣ የቡድሃና የሂንዱይዝም ቤተ አምልኮዎችን) በመረጡት ቦታ የመገንባት መብት አላቸው። ስለዚህ የፖለቲካና የሃይማኖት እንዲሁም የጎሳ ብዝሃነትን ለማክበር የግድ ፌዴራሊዝም ስርዓትን መከተል አስፈላጊ ነው ብዬ አላምንም።

ሰንደቅ፡- አገራችሁ በኢትዮጵያ ኤምባሲዋን ለመክፈት የወሰነችው ለምንድን ነው?

ሚስተር ሱሚት፡- የሁለቱ አገራት ግንኙነት የተጀመረበትን ለማወቅ ታሪክ ስንመረምር ወደ እ.ኤ.አ 1972 ይወስደናል። ከዚያ ጊዜ ጀምሮ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነታችን ሳይቋረጥ ቢቆይም ኤምባሲ ሳይኖረን ቆይቷል። እ.ኤ.አ በ2015 ስልጣን የያዘው አዲሱ መንግስት ስልጣን በያዘ ማግስት በስሪላንካ እና በኢትዮጵያ መካከል ያለው የሁለትዮሽ የዲፕሎማሲ ግንኙነት ወደ ላቀ ደረጃ እንዲሸጋገርና ከአፍሪካ ጋር ለምናደርገው ግንኙነት በአዲስ አበባ ኤምባሲ መክፈት እንደሚኖርብን አመነ። ምክንያቱም አንተም እንደምታውቀው ኢዲስ አበባ የአፍሪካ ህብረት የዲፕሎማቲክና የፖለቲካ መቀመጫ ናት። የአፍሪካ ኢኮኖሚ ኮሚሽን (ኢሲኤ) መቀመጫም አዲስ አበባ ነው። ከዚህም የተነሳ የአገራችን ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር (ማንጋላ ሳማራዊራ) የሚመሩት ቡድን በጉዳዩ ላይ ሰፊ ውይይት ካካሄደ በኋላ በአዲስ አበባ ኤምባሲ ስለሚከፈትበት ጉዳይ የአገራችንን ውሳኔ ለኢትዮጵያ መንግስት ስንገልጽለት ጥያቄያችንን ወዲያውኑ ተቀብሎ ኤምባሲያችንን እንድንከፍት ተደረገ። እኔም የመጀመሪያው አምባሳደር ሆኜ መንግስት ስለመደበኝ የመንግስትን ጥሪ ተቀብዬ ወደ አዲስ አበባ መጣሁ።

ሰንደቅ፡- በኢትዮጵያ የመጀመሪያው የስሪላንካ አምባሳደር ሆነው በአገርዎ መንግስት ተሹመዋል። በዚህ የተነሳም የአገርዎ የአፍሪካ ህብረት ተወካይ ሆነዋል። ስለ አፍሪካ በተለይም ስለ ምስራቅ አፍሪካ ፖለቲካ ያለዎት ግንዛቤ ምን ያህል ነው?

ሚስተር ሱሚት፡ ላለፉት 19 ዓመታት በተለያዩ ደረጃዎች የመንግስት ኃላፊነቶችን ተቀብዬ ስሰራ ቆይቻለሁ። በህንድ በኖርዌይ እና በካናዳ የስሪላንካ ኤምባሲዎች በተለያዩ ኃላፊነቶች አገልግያለሁ። በውጭ ጉዳይ ሚኒስትር የአፍሪካ እና የመካከለኛው ምስራቅ ጉዳዮች ዳይሬክተር ሆኜ ለሁለት ዓመታት ሰርቻለሁ። በዚህ የስራ መደብ ላይ በነበርኩበት ጊዜ ስለ አፍሪካ ለማወቅ ባደረኩት ጥረት መጠነኛ እውቀት ማግኘት ችያለሁ። ከዚህ በተረፈ ግን ብዙ ለማወቅ በተለይም ስለ ምስራቅ አፍሪካ ጥሩ እውቀት እንዲኖረኝ ጥረት በማድረግ ላይ ነኝ። ላለፉት 100 ቀናት ሙሉ ጊዜዬን ኤምባሲውን ለመክፈት ስለምንችልባቸው መንገዶች የሚያተኩሩ ስራዎችን በመስራት ተጠምጄ ነው የቆየሁት።

ሰንደቅ፡- የአፍሪካ ህብረት ተወካይ እና በኢትዮጵያ የስሪላንካ አምባሳደር ሆነው ስለመጡባት ኢትዮጵያስ ምን ያህል ያውቃሉ?

ሚስተር ሱሚት፡- በአገሪቱ የፖለቲካ መረጋጋት እንዳለ አውቃለሁ። አሁን ያለው መንግስትም አገሪቱን ለማሳደግና ልማትን ለማስፋፋት ብዙ እየሰራ እንደሆነ ይሰማኛል። ላለፉት 15 ዓመታትም ቀጣይነት ባለው መልኩ እድገት ያስመዘገበች አገርም ነች። ለኢኮኖሚ እድገት እጅግ በጣም አስፈላጊ የሆኑትን እንደ መንገድ እና ከዋና ከተማችሁ እስከ ጅቡቲ ወደብ የሚደርስ የባቡር ሃዲድ መሰረተ ልማቶችን መንግስታችሁ ገንብቷል። በተለይ ከአዲስ አበባ ጅቡቲ የተዘረጋው የባቡር ሃዲድ የንግድ እንቅስቃሴ ከማፋጠኑም በላይ ሀይል (Energy) ትቆጥባለላችሁ ጊዜያችሁም ይቆጠባል። ይህ ደግሞ አሁን እየገነባችሁ ላለው የኢንዱስትሪ ፓርኮች ምርቶችን ወደ ውጭ ገበያ ለማቅረብ አመቺ ይሆንላቸዋል።

ሰንደቅ፡- የስሪላንካ ኢኮኖሚ በዋናነት በቱሪዝምና በኢንቨስትመንት ላይ የተመሰረተ ሲሆን ግብርናም የማይናቅ ሚና የሚጫወት መሆኑን መንግስታችሁ ለዓለም ህዝብ የለቀቀው መረጃ ይገልጻል። ሰፊ ለም መሬት እና ምቹ የአየር ንብረት ከአምራች ወጣት ሀይል እና ከድንቅ የተፈጥሮ ሀብት ጋር አጣምራ የያዘችው ኢትዮጵያ ኢኮኖሚዋ እንዲያድግ ምን ማድረግ አለባት ይላሉ?

ሚስተር ሱሚት፡- ዲፕሎማት እንጂ ኢኮኖሚስት ባልሆንም እንደማየው አገራችሁ ወደ ተሻለ የኢኮኖሚ የእድገት ምዕራፍ እየሄደች ነው። በመሰረተ ልማት ግንባታ እንደ መንገድ ግንባታ እና የኃይል ማመንጫ ግንባታ በተለይም 6000 ሜጋ ዋት ማመንጨት የሚችለውና በአባይ ወንዝ ላይ እየተገነባ ያለው የኃይል ማመንጫ ግድብ የአገራችሁን ኢኮኖሚ በፍጥነት እንዲያድግ የሚያስችል አቅም ይኖረዋል ብዬ አምናለሁ። ምንም እንኳ በአሁኑ ወቅት ተደጋጋሚ የኃይል መቆራረጥ እንዳለ ብመለከትም እንደ ኅዳሴው ግድብ ያሉ የኃይል ማመንጫ ግድቦች ግን ለወቅቱ የኃይል እጥረት መፍትሔ ከመሆናቸውም በላይ ኃይል (power) ኤክስፖርት በማድረግ የውጭ ምንዛሬ ማግኘት የሚያስችል አቅም አላቸው። እንደገለጽከው አገራችሁ ጥሩ የአየር ንብረት አላት። የመሬት አቀማመጡም ቢሆን ማራኪ ነው። ስማቸውን ባልጠቅስም በሌሎች አገሮች እንዳየኋቸው ሳይሆን የአገራችሁ ህዝብ ሰው አክባሪ እና ጨዋ ነው። እንደነዚህ አይነት ሀብቶች ለኢኮኖሚ እድገት ወሳኝነት አላቸው።

ሰንደቅ፡ ከአዲስ አበባ ውጭ የጎበኙት የኢትዮጵያ ክፍል አለ?

ሚስተር ሱሚት፡ እስካሁን የነበረኝ ጊዜ እንደነገርኩህ ኤምባሲውን ለመክፈት ስለምንችልበት ጉዳይ ሙሉ ትኩረቴን ሰጥቼ ስንቀሳቀስ ነበር የቆየሁት። የመጎብኘት ፍላጎት አለኝ። አንተም ከጠቆምከኝ ሂጄ እጎበኛለሁ (ሳቅ)።

ሰንደቅ፡- አገራችሁ በአፍሪካ ምን ያህል ኤምባሲዎችን ከፍታለች?

­ሚስተር ሱሚት፡ በነገራችን ላይ ኤምባሲ መክፈት ወጭው ከባድ ነው። በአፍሪካ 55 አገሮች ቢኖሩም ኤምባሲ የከፈትንባቸው አገሮች ግን አዲስ አበባን ጨምሮ ስድስት (በግብጽ ካይሮ፣ በደቡብ አፍሪካ ፕሪቶሪያ፣ በኬኒያ ናይሮቢ፣ በናይጄሪያ አቡጃ እና በሲሸልስ) ብቻ ናቸው። እኔ ወደ አዲስ አበባ ስመጣ እነዚህን ኤምባሲዎች ጨምሮ በአፍሪካ ህብረት የአገሬ ተወካይ ሆኜ ነው የመጣሁት።  

ጥቂት ነጥቦች ስለ ዴሞክራሲያዊ ሶሻሊስት ሪፐብሊክ ስሪላንካ

$1-    ለ450 ዓመታት በቅኝ ግዛት ስር የቆየች አገር ስትሆን አጠቃላይ የህዝብ ብዛቷ ወደ 21 ሚሊዮን ይገመታል። የአገሪቷ ዋና ከተማ ኮሎምቦ ትባላለች።

$1-    የአገሪቱ ኦፊሻል ቋንቋዎች ሲንሃሊስ እና ታሚል ሲሆኑ እንግሊዝኛ እውቅና የተሰጠው ሌላው ቋንቋ ነው።

$1-    ከአገሪቱ ህዝብ 70 ነጥብ 2 በመቶ የሚሆነው የቡዲሂዝም ሀይማኖትን ሲከተል፣ 12 ነጥብ 6 በመሆው ሂንዱይዝምን ይከተላል። እስልምና እና ክርስትና ደግሞ እያንዳንዳቸው በቅደም ተከተል 9 ነጥብ 7 እና 7 ነጥብ 4 በመቶ የሚሆነው ህዝብ እምነቶችን ይከተላል።

$1-    የስሪላንካ የቆዳ ስፋት 65 ሺህ 610 ስኩየር ኪሎሜትር ሲሆን ከዚህ ውስጥ አራት ነጥብ አራት በመቶ የውሃ መጠን አለው።

$1-    በአገሪቱ 51 የህትመት መገናኛ ብዙሃን ሲኖሩ፣ 34 ቴሌቪዥንና 52 የሬዲዮ ጣቢያዎች ይገኛሉ።

(ምንጭ የ2012 ቆጠራን ዋቢ አድርጎ ዊኪ ፔዳ ያወጣው ሪፖርት)

                            

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
552 ጊዜ ተነበዋል

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us