ከሠም ስኳር ፋብሪካ የሂሳብ ቋት የለውም?

Wednesday, 15 February 2017 13:38

-    ኮርፖሬሽኑ ድጋፍ ሰጪ ሠራተኞችን ለምን ሥራ አስኪያጅ ያደርጋል?

-    ሠራተኞቹ ቅሬታ አላቸው

 

የኢትዮጵያ መንግስት በነደፈው የአንደኛው እና የሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ በኢንዱስትሪው ልማት ዘርፍ የተለየ ትኩረት ከተሰጣቸው ሜጋ ፕሮጀክቶች መካከል የስኳር ፋብሪካ ኢንዱስትሪ ግንባታዎች አንዱ ነው። በተለያዩ የሀገሪቷ ክፍሎች ከታቀዱት አስር የስኳር ፋብሪካ ግንባታዎች መካከል የከሠም ስኳር ልማት ፕሮጀክት አንዱ ነው።

የከሠም ስኳር ፋብሪካ አጀማመሩ በመተሐራ ስኳር ፋብሪካ ሥር እንደአንድ ቅርንጫፍ የስኳር ፋብሪካ አካል ተደርጎ ነበር። ስኳር ኮርፖሬሽን መቋቋሙን ተከትሎ መንግስት በሰጠው አቅጣጫ ከሠም ፋብሪካ ራሱን የቻለ አንድ ስኳር ፋብሪካ ሆኖ እንዲቀጥል ተደርጓል። በከሠም ፋብሪካ አደረጃጀት ላይ በተለይ በመሬት ዝግጅት እና በሰው ኃይል የመተሐራ ስኳር ፋብሪካ ድርሻ ከፍተኛ ነበር። ሁለቱ ፋብሪካዎች ሲለያዩም የንብረት ክፍፍሉ ረጅም ጊዜ የወሰደ ሲሆን ከኮርፖሬሽኑ የተገኘው መረጃ እንደሚያሳየው የንብረት ክፍፍሉ ሙሉ ለሙሉ መጠናቀቁን ነው።

      የከሠም ስኳር ፋብሪካ የከሠም ወንዝ መሰረት አድርጎ የተቋቋመ ሲሆን፣ በወንዙ ላይ የተገነባው የውሃ ግድብ ከ500 ሚሊዮን ሜትር ኪዩብ በላይ ውሃ የመያዝ አቅም እንዳለው ይነገራል። የተያዘውን ውሃ በመጠቀም 20ሺ ሄክታር የሸንኮራ አገዳ ለማልማት ታቅዷል።  በቀን 10ሺ ቶን የሸንኮራ አገዳ መፍጨት የሚችል ፋብሪካ ለመገንባት ከፍተኛ ርብርብ እየተደረገ መሆኑ የሚታወቅ ነው። ፋብሪካው በመጀመሪያው ምዕራፍ ግንባታ በቀን 6ሺ ቶን አገዳ የመፍጨት አቅም ይኖረዋል ተብሎ የሚጠበቅ ሲሆን፣ በዓመት 1ሺ 630 ቶን ስኳር እና 45ሺ ሜጋ ዋት የኤሌክትሪክ ኃይል ለማምረት የሚችል አቅም ይኖረዋል ተብሏል።

ፋብሪካው፣ በ2009 ዓ.ም  በጀት አመት 1.032 ሚሊዮን ቶን አገዳ በማቅረብ 1.039 በሚሊዮን ኩንታል ነጭ ስኳር፤ 1500 ሄክታር መሬት ላይ የሸንኮራ አገዳ ልማት ማስፋፋት እንዲሁም በተጓዳኝ 412,958 ኩንታል ሞላሰስ፣ 12,000 ኩንታል ፍራፍሬ ለማምረት አቅዷል። ሆኖም ግን፣ የከሠም ስር ፋብሪካ 2009  ዓ.ም. በጀት  የግማሽ  ዓመት  ሪፖርት የሚያሳየው እንዲሁም የከሠም ሠራተኞች ለሰንደቅ የጋዜጣ ዝግጅት ያቀረቧቸው ቅሬታዎች ሲደመሩ ፋብሪካው ያቀደውን ግቡን ለማሳካት ቅርብ ክትትል እና እርማት ከኮርፖሬሽኑ ኃላፊዎች እንደሚያስፈልግ አሻሚ አይደለም።

የከሠም ስር ፋብሪካ 2009 ዓ.ም. በጀት  የግማሽ  ዓመት ሪፖርት ይዘቱን እና የሠራተኞችን ቅሬታ ጋር እንዲያስታርቁልን ለከሠም ዋና ሥራአስኪያጁ አቶ ተገኑ ገናሞ ስልክ ደውለንን አነጋግረናቸው ነበር። ሥራአስኪያጁ ስብሰባ ላይ መሆናቸውን ገልጸውልን ከሰላሳ ደቂቃ በኋላ እንደምናገኛቸው ነግረውን ተለያየን። በመካከል የሥራ አስኪያጁ ፀሀፊ መሆኗን የገለጸችልን፣ ያቀረብነውን ጥያቄዎች በስልክ ተቀብላ ሥራ አስኪያጁ ምላሽ እንደሚሰጡን ገልፃልን ተለያየን። በመጨረሻም ሥራ አስኪያጁም ፀሐፊያቸውም የውሃ ሽታ ሆኑ። ዝግጅት ክፍላችን እንዲህ አቀረበው።

በከሠም የሒሳብ ቋት የለም?

የከሠም ስር ፋብሪካ 2009 ዓ.ም. በጀት  የግማሽ  ዓመት ሪፖርት ካጋጠሙን ችግሮች መካከል ብሎ ከዘረዘራቸው ውስጥ፤ የሒሳብ ቋት አለመኖር፤ የሽያጭ እና የግዢ ተፈፃሚ ሰነድ ከኮርፖሬሽኑ ሲላክ የተሟላ አለመሆን፤ የሠራተኞች የትርፍ ሰዓት ክፍያ እያደገ መምጣት ናቸው።

ከሠራተኞቹም ለዝግጅት ክፍላችን የቀረበው ቅሬታ ተመሳሳይ ነው። ይኸውም፣ “በከሠም ስኳር ፋብሪካ ያለው የፋይናንስ አሰራር ሳይንሳዊ አይደለም። ክፍያ ፈጽሙ ከተባለ አንስቶ መፈጸም ነው። ከመዋቅር ውጪ ክፍያዎች ይፈጸማሉ። ከአሚባራ እርሻ ልማት ጋር ያለው የክፍያ አፈጻጸም በውል አይታወቅም። ዓመታዊ የፋብሪካው ሒሳብ ሰነድ ተወራርዶ አይዘጋም። ይህም በመሆኑ ለተበላሸ አሰራር የተጋለጠ ነው” የሚሉ ናቸው።

አንድ ስኳር ፋብሪካ የሒሳብ ቋት (Chart of Account) ሳይኖረው ወጪ እና ገቢውን እንዴት ሊያውቅ ይችላል? የማምረቻ ወጪውን ሳያውቅ የአንድ ኪሎ ግራም ስኳር ዋጋን መተመን ይችላል? ዓመታዊ የኢዲት ሪፖርት ማውጣትስ እንዴት ይቻለዋል? ሌሎች ጥያቄዎችንም ማንሳት ይቻላል። እንደሚታወቀው የከሠም ስኳር ፋብሪካ የፕሮጀክት የሒሳብ ቋቱን ዘግቶ ወደ ማምረት ሙከራ ገብቷል። ይህ ማለት ከሠም ስኳር ፋብሪካ እንደድርጅት በራሱ የሒሳብ ቋት መጠቀም ጀምሯል ተብሎ የሚወሰድ ነው። በሪፖርቱም ላይ እንደመፍትሄ አቅጣጫ የተቀመጠው፣ በራስ አቅም የሒሳብ ቋት ማዘጋጀት ነው።

በዚህ ነጥብ ላይ ያነጋገርናቸው የስኳር ኮርፖሬሽኑ የኮርፖሬት ፋይናንስ ማሻሻያ ዋና ሥራአስፈፃሚ አቶ መሳ ዘይኑ እንደገለፁልን፣ “የሒሳብ ቋት ሳይኖር ወጪህን መቆጣጠር አትችልም። የከሠም ስኳር ፋብሪካ በኮርፖሬሽኑ ኦዲት ተደርጎ በሰነድ አለ። ፋብሪካው በሙከራ ላይ ነው ያለው። “test commissioning` ላይ ነው ፋብሪካው የሚገኘው። ይህ ሲጠናቀቅ ነው፣ ፋብሪካው ከቻይኖቹ ወደ መንግስት የሚተላለፈው። ሁሉም ወጪ በራሱ የሒሳብ ቋት ውስጥ ነው የተቀመጠው። ለከሠም ፋብሪካ እንዲሁም ሌሎች ፋብሪካዎች አንድ ወጥ የፋይናንስ ሥርዓት እያዘጋጀን በመሆኑ ሲጠናቀቅ ምላሽ ያገኛል” ብለዋል።

 

ሸንኮራ አገዳ ልማት ማስፋፋት

በሪፖርት ሰነዱ ላይ የ6 ወሩ የስኳር፣ ሸንኮራ አገዳ ልማት ማስፋፋት፣የሞላሰስ እና የፍራፍሬ ምርት እቅድ አፈፃፀም በተመለከተ ከሠራተኞቹ የቀረበው ቅሬታ፣ “ስድስት ወር በዋናነት ለማከናወን ከታቀዱ ሥራዎች መካከል 1808.8 ሄ/ር የሸንኮራ አገዳ በመቁረጥ 2921266 ኩንታል ሸንኮራ አገዳ በመፍጨት እንዲሁም 294,850 ኩንታል  ስኳር ማምረት ነዉ። ሆኖም ግን 1448.86 ሄ/ር መሬት የሸንኮራ አገዳ በመቁረጥ 1,742,191 ኩ/ል የሸንኮራ አገዳ በመፍጨት 123,830 ኩ/ል ስኳር የተመረተ ሲሆን አፈፃፀሙም 42 በመቶ ነው።

እንዲሁም፣ የሸንኮራ አገዳ ልማት ማስፋፋትን በተመለከተ 619 ሄ/ር መሬት  በመትከል  በስድስት ወር ዉስጥ የተከናወነዉ 77.98 ሄክታር ሲሆን አፈፃፀሙ 13 በመቶ ነዉ። በዚህ ሥራ አፈፃጸም ተጠያቂው ማነው?” የሚል ጥያቄ ከሠራተኞቹ ቀርቧል።

ሠራተኞቹ ለሥራ አፈፃፀም መውረድ በዋና ምክንያትነት የሚያቀርቡት በዋና ሥራ አስኪያጅ የአመራር ብቃት ላይ ነው። ይኸውም፣ “ዋና ሥራአስኪያጁ የአቅርቦት ባለሙያ በመሆናቸው በፋብሪካው እና በእርሻው ላይ ስለሚካሄደው አሰራር የሚያውቁት ነገር የለም። ወይም በቂ እውቀት የላቸውም። ይህም በመሆኑ ከመሬት ዝግጅት እስከ ተከላ ድረስ ያለውን የአፈፃፀም ሁኔታ በቅጡ መተንተን፣ መከታተል ባለመቻላቸው የተከሰተ መሆኑን” ሠራተኞቹ ለሰንደቅ ገልጸዋል።

በርግጥም ባልተለመደ መልኩ ኮርፖሬሽኑ የፋብሪካ ድጋፍ ሰጪ ሠራተኞችን በሥራ አስኪያጅነት ሲሾም ይታያል። ለምሳሌ በመተሐራ በወንጂ ስኳር ፋብሪካ የሰው ኃይል ክፍል (Human resources) ኃላፊ የነበሩትን በዋና ሥራአስኪያጅነት ሾሞ ነበር።  በወንጂ ስኳር ፋብሪካ በሥራ አስኪያጅነት የተቀመጡትም የሒሳብ ባለሙያ (accounting) ናቸው። በከሠም ደግሞ የአቅርቦት ባለሙያ (purchasing and supply management) ሥራ አስኪያጅ መሆናቸው ሠራተኞች በቅሬታ አቅርበዋል።

ከዚህ በፊት በነበረው የስኳር ፋብሪካ ሥራ አስኪያጅ ሹመት ከምርት ሒደት ጋር ቀጥተኛ ግኝኙነት ያላቸው ባለሙያዎች ነበር የሚሾሙት። ይህም ሲባል፣ በእርሻ ሙያ ወይም በፋብሪካ በተለይ ኢንጅነሮች ወይም ፕሮዳክሽን ክፍል የሚሰሩ ኬሚካል መሃዲሶች ወይም ኬሚስቶች ነበሩ ሲሾሙ የነበሩት። ይህ የአሰራር ልምድ ሳይሆን፣ ከማምረት ጋር ቀጥተኛ ተሳትፎ ስላላቸው። ይህንን ውጤታማ አሰራር የለወጠው ኮርፖሬሽኑ በፖለቲካ አመራሮች እጅ መውደቁ እና በጥገኝነት ላይ ተቸንክሮ ባለሙያዎችን ገፍቶ ረጅም ርቀት በመጓዙ የመጣ ነው። አሁንም በባለሙያዎች እጅ ሙሉ ለሙሉ የኮርፖሬሽኑ አስተዳደር የተያዘ ባለመሆኑ ችግሩ እንደሚቀጥል ይጠበቃል።

 

 

የሰው ኃይል ፍልሰት

ሪፖርቱ እንደሚያሳየው በከሠም ስኳር ፋብሪካ ከ1ሺ 697 በላይ ቀሚ ሠራተኞች መኖራቸውን ነው። ከዚህም ዉስጥ በስድት ወሩ አፈፃፀም ከ126 በላይ መካከለኛ አመራር እና ሠራተኞች ከሥራ ለቀዋል። ለእነዚህ ሠራተኞች ፋብሪካው ለስልጠና ከፍተኛ ወጪ አውጥቷል።

ሠራተኞቹ ለመልቀቃቸው ዋናው ምክንያት “የመልካም አስተዳደር ችግር” መሆኑ ለዝግጅት ክፍላችን ተገልጿል። ከሚያነሷቸው ችግሮች መካከል፣ በደረጃ እድገት፣ በዝውውር፣ በድጋፍ እና ክትትል ላይ እኩል ያለ ማየት፤ የመኖርያ ቤት ችግር፣ በአንድ መኖሪያ ቤት ውስጥ ለአራት እና ለአምስት ተሰብስበው ሠራተኞች እንዲያድሩ መደረጉ፤ አምባገነናዊ አስተዳደር በመኖሩ ሠራተኞች መብታቸዉን ሲጠይቁ ተገቢዉ ምላሽ ከመስጠት፣ ሥራ መልቀቅ ትችላላችሁ እየተባሉ ማሸማቀቅ፤ የሥራ ኃላፊዎች የስነምግባር ችግርንም ጠቅሰዋል።

እንዲሁም በመተዳደርያ ደንቡ መሰረት አንድ ሥራ መሪ ጥብቅነት ወይም ዉክልና የሚሰጠዉ ስራ መደቡ ክፍት ሲሆን በአፈፃፀም ከፍተኛ ዉጤት ያለዉ አመራር ወይም ሠራተኛ በቅርብ ተጠሪዉ ይመደባል ይላል። ይሁን እንጂ በጥብቅነት ወይም በዉክልና የተመደበዉ አመራር ለሦስት ወር ይመደባል። አስገዳጅ ሁኔታ ካለ ለተጨማሪ ሦስት ወር ይሠራል። ከስድስት ወር መብለጥ የለበትም ተብሎ ተደንግጓል።

እየተፈጸመ ያለው የተለየ ነው ሲሉ ሠራተኞቹ ቅሬታቸውን አቅርበዋል። ሥራ አስኪያጁ ከወደደህ በሶስት ወር በፊትም ይጸድቃል። ጎምበስ ቀና የማትል ከሆነ አንድ ዓመት በላይ በጥብቅነት ያስቀምጥሃል። ረጅም ጊዜ በጥብቅነት ሠርተህ ከቦታው ሲያነሱም ለሞራል እንኳን ሠራተኛው የተነሳበት ምክንያት አይነገረውም። ከዚህ ቀን ጀምሮ የተነሱ መሆንዎትን አሳውቃለሁ ተብሎ ይፃፋል፤ አበቃ። የትም መጠየቅ አንችልም፤ ከሠም እንደዚህ ነው ብለዋል። ማስረጃ ለሚፈልግ የመንግስት አካል ቀርቦ የሚያነጋግረን ከሆነ እናቀርባለን ሲሉ አክለዋል።

የአሚባራ እርሻ ልማት በተመለከተ

በስድስት ወሩ ሪፖርት ላይ እንደቀረበው፣ ከአሚበራ አገዳ በማመላለስ  ፋብሪካውን  ለመመገብ  ከፍተኛ ጥረት እየተደረገ  ቢሆንም  የመንገዱ  ርቀቱ  በጣም  አስቸጋሪ  እና ፈተኝ  መሆኑ  ለከፍተኛ ወጪ ፋብሪካውን ዳርጓታል።

በተጨማሪ ችግርነት የቀረቡትኮርፖሬሽኑ /ከሠም ስኳር ፋብሪካ/ እና አሚባራ እርሻ ልማት ምርታማነታቸውን ለማሳደግ እና ትርፋማ ሆነው እንዲቀጥሉ ለማድረግ የተናጠልና የጋራ ስራዎች አለመለየታቸው በምክንያትነት ተቀምጧል። ሐምሌ 2003 ዓ.ም በጸደቀው የፋይናንስ መመርያ ገጽ 13/31 አንቀጽ 2.2 ንዑስ አንቀጽ 2.2.4 መሰረት ተሰብሳቢ ሂሳቦችን ቢያንስ በየ ስድስት ወሩ አንድ ጊዜ ከደንበኞች ሂሳብ ጋር የማስታረቅ ስራ መሰራት ሲገባው ከአሚባራ ጋር የማስታረቅ ስራ አልተሰራም።

በአሚባራ እርሻ ልማት ስም በዱቤ ከኮርፖሬሽኑ ለወጡ ወጪዎች ሒሳቡ ተሰርቶ ሲላክለት ከራሱ መረጃ ጋር አመሳክሮ ልዩነት ካለ በ7 /ሰባት/ ቀናት ውስጥ ለኮርፖሬሽኑ የማሳወቅና ማስተካከያ የማሰራት ኃላፊነት ያለበት መሆኑ የሚታወቅ ቢሆንም፣ ድርጅቱ በተጠቀሰው የ7 ቀናት ጊዜ ውስጥ ልዩነቱን ያለማሳወቁና ማስተካከያ ለማሰራት ጥያቄ ያለማቅረቡ የተላከለትን ሒሳብ እንደተቀበለው መቆጠሩን የሚያሳይ ሰነድ ያለመኖሩ፤

ኮርፖሬሽኑ ከድርጅቱ የቀረበውን የሸንኮራ አገዳ መዝኖ የአንድ ማሳ ምርት እንደተረከበ ህጋዊ ደረሰኝ ለአሚባራ እርሻ ልማት ያለመስጠቱ፤ የኮርፖሬሽኑና የአሚባራ እርሻ ልማት የታተሙና ተከታታይ ቁጥር ያላቸው ቋሚ ሰነዶችና እንደ የሥራ ፀባዩ በኮርፖሬሽኑና በድርጅቱ ስምምነት ህጋዊ ሰነዶች ያለመዘጋጀታቸው፤ የአሚባራ እርሻ ልማት ከኮርፖሬሽኑ በዓይነትና በጥሬ ገንዘብ ክፍያ ለሚጠይቃቸውም ሆነ ለሚረከባቸው ንብረቶች ከአሚባራ እርሻ ልማት የተሟላ ህጋዊ ሰነድ ያለማግኘቱ፤

ለአሚባራ እርሻ ልማት በዱቤ ለቀረቡ ንብረቶችና አገልግሎቶች ኮርፖሬሽኑ ህጋዊ ሰነድ አዘጋጅቶ ያለመስጠቱ፤ የአሚባራ እርሻ ልማት የሸንኮራ አገዳ ተክሎና የመስኖ መሰረተ ልማት የመድን ሽፋን እንዲገባለት አድርጎ ወጪውን መሸፈኑን እንዲሁም የገባውን የመድን ሽፋን ፖሊሲ ኮርፖሬሽኑ እንዲደርሰው የማይደረግ መሆኑ፤ የአሚባራ እርሻ ልማት አስፈላጊውን የሰብል እንክብካቤ ስራዎች ባለማድረጉ ለሚደርሰው የምርት ብክነት ተጠያቂ የሚሆንበት የአሰራር ስርዓት አለመኖሩ፤

በአሚባራ እርሻ ልማት የሸንኮራ አገዳ መሰብሰብ /ለቀማ/ ስራውን ያለማቋረጥ /24 ሰዓት/ ማከናወኑን ሸንኮራ አገዳ ተቆርጦ በድርጅቱ ጉድለት በወቅቱ መነሳት ወይንም መሰብሰብ የሚገባው አገዳ ሳይሰበሰብ ቢቀር በዚህ ሳቢያ አገዳውን ወደ ጋሪ ለመጫን የሚያስከትለውን ተጨማሪ የማሽነሪ ወጪ የአሚባራ እርሻ ልማት እንዲሸፍን ያለመደረጉ፤ በማሽነሪ ከማሳ አገዳ ማውጣት በማይቻልበት ወቅት የአሚባራ እርሻ ልማት በሰራተኞቹ እንዲወጣ ያለማድረጉና ይህንን በማያደርግበት ወቅት ኃላፊነቱን እራሱ እንዲወስድ ያለመደረጉ በተፈጠረ የአሰራር ክፍተት ፋብሪካውን በአንድም በሌላ መንገድ ችግር ውስጥ ጥለውታል።

ምርታማነት ማነስ (Low Productivity)

በስድስት ወር ሪፖርቱ በቀረበው የምርታማነት ማነስ ምክንያቶች መካከል፣ የመሬት ምርታነት ማነስ፤ የሚቆረጠው አገዳ ከሚፈለገው በላይ ውሃ ማጠጣት፤ ባልታወቀ የፋብሪካው ምክንያት የሚሉ ተዘርዝረዋል።

የከሠም ስኳር ፋብሪካ ዋና ሥራአስኪያጅ ከላይ ለሰፈሩት የምርታማነት ማነስ ምክንያቶች ምላሽ ቢሰጡን ከቀረበባቸው የድጋፍ ሰጪ የሥራ ክፍል ቅሬታ ጋር ለማስታረቅ በጣም የቀለለ ነበር።¾

ይምረጡ
(6 ሰዎች መርጠዋል)
843 ጊዜ ተነበዋል

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us