የሕዳሴው ግድብ፤ ብሔራዊ መለዮን ለመቀየር እየተንደረደረ ይገኛል

Wednesday, 05 April 2017 12:32

-    የፕሮጀክቱ 57 በመቶ ተከናውኗል

 

በዓለም አቀፉ ሕብረተሰብ ዘንድ ኢትዮጵያ በረሃብና በድርቅ ስሟ ሲነሳ የነበረበት ታሪክ ጨርሶ ጠፍቷል ባይባልም፤ ቢያንስ ሀገሪቷን ሙሉ ለሙሉ የሸፈነ ረሃብ ባለፉት አስራ አምስት ዓመታት አልተከሠተም። በድርቅ እና የሰው ሠራሽ ምክንያቶች የሚፈጠሩ ምጣኔ ሀብታዊና ማኅበራዊ ችግሮች ግን ሀገሪቷን ከመፈታተን እስከአሁን አልተገቱም።

 

 

ዓለም አቀፉ ሕብረተሰብ፣ በአንድ በኩል ኢትዮጵያ የሁለት አሃዝ እድገት ማስመዝገቧን እያመሰገነ፤ በሌላ በኩል፣ ድርቅ የሚያስከትላቸውን ችግሮች ለመቅረፍ እጁን እየዘረጋ በነበረበት ወቅት ነው፤ አዲስ የልማት አጀንዳን ያነገበና ፖለቲካዊ አንድምታው የገዘፈ ዜና በዐበይት የብዙኃን መገናኛዎች ያዳመጠው።

 

 

መጋቢት 24 ቀን 2004 ዓ.ም፣ የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ፣ ኢትዮጵያ፣ በናይል ወንዝ ላይ 6ሺ ሜጋ ዋት የሚያመነጭ “የሚሌኒየም ግድብ” ለመስራት የመሰረት ድንጋይ ማስቀመጣቸውን ለዓለም ዓቀፉ ሕብረተሰብ አበሰሩ። በሁለት አሃዝ እድገት እና በድርቅ መካከል ስሟ ሲነሳ የነበረችው ኢትዮጵያ፣ በአፍሪካ ትልቁን የኃይል ማመንጫ ግድብ ለመገንባት ማቀዷ፣ በዓለም አቀፉ ሕብረተሰብ የነበራትን የረሃብ ብሔራዊ መለዮ በአረንግዴ ልማታዊ አጀንዳ በመቀየር ተስፋ ያላት ሃገር የሚል አዲስ ብሔራዊ መለዮ (Nation branding) ለመያዝ በቅታለች።

 

 

አዲሱን የብሔራዊ መለዮ ስያሜ ከሚያጸኑት ዐበይት ክንዋኔዎች መካከል አንዱ፣ ይኽው የታላቁ ሕዳሴ የኃይል ማመንጫ ግድብ ግንባታ ነው፤ ግንባታው ከተጀመረ ስድስት ዓመታትን አስቆጥሯል። የመሰረት ድንጋዩ በተጣለበት ስድስተኛ ዓመት ክብረ በዓል ላይ ተገኝተን፣ ከግንባታው ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት ካላቸው አካላት ስለግንባታው ዋና ዋና ክፍሎች እና ወቅታዊ ሒደቱና ደረጃውን የሚያሳዩ መረጃዎችን እንደሚከተለው አቅርበናቸዋል። 

 

 

የግንባታው ዋና ዋና ክፍሎች

የዋናው ግድብ መጠኑ 10 ነጥብ 1 ሚሊዮን ኪዩቢክ ሜትር በRCC ኮንክሪት ሙሌት ቴክኖሎጂ የሚገነባ ሲሆን፤ ይህም በኢትዮጵያ ውስጥ ከጊቤ-III የኃይል ማመንጫ ቀጥሎ የሚገነባበት ዝቅተኛ ሲሚንቶ የሚጠቀምና ወጪ ቆጣቢ ቴክኖሎጂ ነው፤ ግድቡ ሲጠናቀቅ 145 ሜትር ከፍታና 1 ነጥብ 8 ኪ.ሜ. ርዝመት ይኖረዋል።

 

 የግድቡ ግንባታ ሁለት ዋና የወንዙን አቅጣጫ ማስቀየር ኩነቶች እና ተጓዳኝ ግንባታ ሂደቶች አለው። ይኸውም፣ በግንቦት 20 ቀን 2005 ዓ.ም የተከናወነው የወንዙን አቅጣጫ በጊዜያዊነት በግድቡ ቀኝ በኩል የማስቀየር ሂደት ሲሆን፤ ሌላኛው ደግሞ በግድቡ ግራ በኩል በአራት የውሃ ማስኬጃ ትቦዎች አማካኝነት በታህሳስ 2008 ዓ.ም እንዲያልፍ ተደርጓል። በመሆኑም ቀድሞ ውሃው ይሄድበት በነበረበት (ኤፕን ቻናል) ግንባታው እየተከናወነ የሚገኝ ሲሆን፤ ከግድቡ በስተኋላ የተጠራቀመውን ወደ እያንዳንዱ የኃይል ማመንጫ ዩኒቶች ውሃ የሚያደርሱ 16 የብረት አሸንዳዎችና የታችኞችን ሀገራት የውሃ ፍላጎት ባገናዘበ መልኩ አገልግሎት የሚሰጡ ተጨማሪ ሁለት የቦተም አውትሌቶች ተገንብተው ወደ ሥራ ገብተዋል።

 

የኃይል ማመንጫ ቤቶች

ከዋናው ግድብ ግርጌ በቀኝና በግራ በኩል ሁለት የኃይል ማመንጫ ቤቶች የሚገነቡ ሲሆን፤ በስተቀኝ የሚገኘው የኃይል ማመንጫ ቤት 10 እንዲሁም በስተግራ በኩል በሚገኘው ደግሞ 6 የኃየል ማመንጫ ዩኒቶች ይኖሩታል። እያንዳንዱ ዩኒትም ከ375 ሜጋ ዋት በላይ የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጨት አቅም ያላቸው ጄኔሬተሮች ያሉት ሲሆን፤ ፕሮጀክቱ ሲጠናቀቅ ከጠቅላላው 16 ዩኒቶች የሚመነጨው የኤሌክትሪክ ኃይል ከ6,000 ሜጋ ዋት በላይ እንደሚሆን ይጠበቃል።

 

 እንዲሁም ቀደም ብለው ኃይል ማመንጨት ይጀምራሉ ተብለው የሚታሰቡት ዩኒት ሁለት ዩኒቶች (ዩኒት 9 እና 10) ሲጠናቀቁ በሚኖረው የውሃ መጠን በመጀመሪያ ወደ 216 ሜጋ ዋት የሚጠጋ ኃይል እንደሚያመነጩ የሚገመት ሲሆን፤ በሙሉ የውሃ የመያዝ ከፍታ ሲደርስ ደግሞ 750 ሜጋ ዋት የሚያመነጩ መሆናቸው ተገልጸል።

 

ውሃ ማስተንፈሻዎች (Spillways)

በፕሮጀክቱ የሚፈጠረው ሰው-ሰራሽ ሐይቅ (Reservoir) የማጠራቀም ከፍታ ከባህር ጠለል በላይ 640 ሜ (Full Supply Level) ነው። ይህንንም ተጨማሪ የውሃ መጠን ተቀብለው ከግድቡ በታች ለመልቀቅ የሚያስችሉ ከዋናው ግድብ ግራ በኩል መዝጊያ ያለው የውሃ ማስተንፈሻ (Gated Spillway)፤ በዋናው ግድብ መካከለኛ ክፍል (Low Block Emergency Spillway) እና በሳድል ግድብ በስተቀኝ በኩል የሚገኝ ውሃ ማስተንፈሻ (Emergency Spillway) እየተገነቡ ይገኛሉ።

 

የኮርቻ ቅርፅ ያለው ግድብ (Saddle Dam)

ይህ ግድብ 50 ሜትር ከፍታ እና 5 ነጥብ 2 ኪ. ሜትር ያህል ርዝመት ያለው ሲሆን፤ የግድቡ አካል ውሃ በማያሳልፍና በማያሰርግ መልኩ የሚገነባ ሆኖ የድንጋይ ሙሌቱም መጠን ወደ 15 ሚሊዮን ሜትር ኪዩብ የሆነ በግድቡ አቅራቢያ በሚገኝ የድንጋይ ግብዓት እየተገነባ ያለው ግድብ ነው።

 

የኃይል ማከፋፈያ ጣቢያ

ከዋናው ግድብ በ1 ነጥብ 4 ኪ.ሜ. ርቀት ላይ ባለ 500 ኪ.ቮ. ባለ ሁለት ባዝባር የኃይል ማከፋፈያ ጣቢያ ይገኛል። የኃይል ማከፋፈያ ጣቢያው  ወደ ትራንስፎርመሮች የሚገባውን የመነጨ ኃይልና ወደ ማስተላለፊያ መስመሮች የሚወጣውን ገቢና ወጪ ቤዮችን ያካትታል፤ ይህ ባለ 500 ኪ.ቮ. ማከፋፈያ ጣቢያ በኢትዮጵያ የቮልቴጅ መጠን ታሪክ አንጻር ከፍተኛው መሆኑ ከባለሙያዎች ማብራሪ መረዳት ችለናል። 

 

የኃይል ማስተላለፊያ መስመር

ከኃይል ማመንጫው የመነጨውን ኃይል ወደ ብሔራዊ የኃይል ትስስር ለማገናኘት የሚያስችል ከታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ፕሮጀክት በደዴሳ - ሆለታ - አዲስ አበባ የሚደርስ 725 ኪ.ሜ. ርዝመት ያለው ባለ 500 ኪ.ቮ. ባለ ሁለት ሰርኩዩት ከፍተኛ የኃይል ማስተላለፊያ መስመር ግንባታ ተጠናቋል።

 

ከዚህም በተጨማሪ 240 ኪ.ሜ. ርዝመት ያለው ባለ 400 ኪ.ቮ. ከፍተኛ የኃይል ማስተላለፊያ መስመር ከታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ፕሮጀክት እስከ በለስ ኃይል ማመንጫ ጣቢያ ድረስ ተገንብቶ አገለግሎት እየሰጠ ይገኛል። በአሁኑ ጊዜም ለፕሮጀክቱ ግንባታ የሚውል የኤሌክትሪክ ኃይል ከብሔራዊ የኃይል ስርጭት መረብ ማቅረብ ያስቻለ ሲሆን፤ ይኸው መስመር ፕሮጀክቱ ተጠናቆ ኃይል ማመንጨት ሲጀምርም ወደ ሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል የኃይል ማስተላለፊያ በመሆን ያገለግላል።

 

በአሁን ሰዓት በመከናወን ላይ ያሉ ሥራዎች ሲቪል ኢንጂነሪንግ ሥራዎች

የፕሮጀክቱ ሲቪል ኢንጂነሪንግ ሥራ የሚያካትታቸው ተግባራት የሚከተሉት ናቸው፤ የዋናው ግድብ ግንባታ፤ የኮረቻ ቅርፅ ያለው ግድብ ግንባታ፤ የኃይል ማመንጫ ቤቶች ግንባታ፤ የማስተንፈሰ በሮች ግንባታ የ500 ኪ.ቮ. ማከፋፈያ ጣቢያ ግንባታ፤ የውስጥ ለውስጥ መንገዶችና ከግድቡ በታች ድልድይ ግንባታ፤ የሰራተኞች መኖሪያ ካምፕ ግንባታ ናቸው።

 

ዋናው ግድብ በተመለከተ ያሉ ክንውኖች

በግድቡ ግንባታ ሂደት የቁፋሮ፤ የማጽዳት፣ የደንታል ኮንክሪት እንዲሁም የRCC (ሮለር ኮምፓክትድ ኮንክሪት) ሙሌት ሥራዎችን በቅደም ተከተል እየተከናወኑ ናቸው። እስካሁን ድረስ ከ7 ነጥብ 3 ሚሊዮን ያላነሰ የRCC አርማታ ሙሌት ሥራ ተከናውኗል። በአጠቃላይ በፕሮጀክቱ ውስጥም የቁፋሮ መጠን 21 ሚሊዮን ኪዩቢክ ሜትር ያህል እንደሚደርስ ተነግሯል።

 

ኃይል ማመንጫ ቤቶች ግንባታ

በግራና ቀኝ የኃይል ማመንጫ ቤቶች ማለትም (በሁሉም 16 ዩኒቶች) እንዲሁም በLow block እና Tailrace አካባቢ የቁፋሮ ሥራ ተጠናቆ የግንባታ ሥራው እየተካሄደ ይገኛል። እንዲሁም ቀደም ብለው ኃይል በሚያመነጩት ዩኒቶች፤ በኢፌክሽን ቤይ እንዲሁም በሌሎቹ በቀኝም በግራም ባሉ ዩኒቶች የኤሌክትሮ ሜካኒካል እና ኃይድሮ ሜካኒካል መሳሪያዎች ተቀባሪ አካላት ተከላና የአርማታ ሙሌት ሥራዎችም በቅንጅት እየተከናወኑ ይገኛሉ።

 

የወንዙን አቅጣጫ ለማስቀየር የሚከናወኑ ሥራዎች

የወንዙ አቅጣጫ ለሁለተኛ ጊዜ በሚቀየርበት በግድቡ ግራ በኩል አስፈላጊ ሥራዎች ተከናወኑው ወንዙ በታህሳስ 2008 ዓ.ም በዳይቨርሽን ቦክስ ከልቨርት በኩል እንዲያልፍ ተደርጓል። በመሆኑም ቀድሞ ውሃው ይሄድበት የነበረውን ቻናል ለRCC የማዘጋጀትና የመሙላት ሥራዎች በመከናወን ላይ ሲገኙ በአሁኑ ሰዓትም ከባሕር ጠለል በላይ እስከ 514 ሜትር ከፍታ ድረስ ተሞልቷል። እንዲሁም የዳይቨርሽን ከልቨርት የላይኛውና የታችኛው በሮች ምርት ተጠናቀው ወደ ሳይቱ በመድረሳቸው ከተከላው ጋር የተያያዙ ሥራዎች እየተከናወኑ ይገኛሉ።

 

የኮርቻ ቅርፅ ያለው ግድብ (Saddle Dam)

ይህ ግድብ 50 ሜትር ከፍታ እና 5 ነጥብ 2 ኪሎ ሜትር ያህል ርዝመት ሲኖረው የግድቡ አካል መጠን 15 ሚሊዮን ሜትር ኪዩብ ሙሌት ሲሆን ለዚሁም የሚያገለግል ግብዓት በግድቡ አቅራቢያ ካለ የድንጋይ ኳሪ የሚገኝ ነው።

 

የከርሰምድር ፍተሻ ሥራዎች ተጠናቀው የቁፋሮ ሥራውም አልቋል። የግድቡ አካል ግንባታ ሥራ (Embankment Construction) 9 ነጥብ 5 ሚሊዮን ኪዩቢክ ሜትር ያህል ደርሷል። ከዚሁ የግንባታ ሂደት ጎን ለጎን የግራውቲንግ፣ ፕላስቲክ ዳያፍራም ዎል ካስቲንግ ያሉ የውሃ ስርገትንና ማሳለፍን የሚከላከሉ ሥራዎች እንዲሁም የኢንስፔክሽን ጋለሪ ግንባታ ሥራዎች በመካሄድ ላይ ናቸው።

 

ጊዜያዊ የመዳረሻ እና የቋሚ መንገዶች ግንባታ

አዲሱን የአሶሳ - ጉባ መንገድ እንዲሁም ቋሚ መንገዶችና ጊዜያዊ መዳረሻ መንገዶችን ጨምሮ የ124 ነጥብ 8 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያለው መንገድ ግንባታ እየተከናወነ ይገኛል፤ አፈፃፀሙም 99 በመቶ ደርሷል ተብሏል።

 

ሞቢላይዜሽንና ሎጂስቲክ

የተቋራጩ ሠራተኞች የመኖሪያ ካምፕና የቢሮዎች ግንባታ

የተለያዩ 10,500 የሥራ ተቋራጩ ሠራተኞችን የማስተናገድ አቅም ያላቸው የመኖሪያ ካምፕ ቤቶች ግንባታ ተጠናቆ አገልግሎት እየሰጠ ይገኛል። በጊዜያዊና ቋሚ ካምፖች ውስጥ ለአማካሪ መሐንዲሱና ፕሮጀክት ቢሮው ሰራተኞች የሚያገለግል የመኖሪያ ካምፕ ተጠናቆ አገልግሎት እየሰጠ ይገኛል።

 

የተቋራጩ ሎጂስቲክ ኢንስታሌሽን ኮንስትራክሽን

ጊዜያዊና የተለያዩ የግንባታና ተከላ ሥራዎች በሳይቱ የተከናወነበት ነው፤ ከነዚህም መካከል ወርክሾፕ፣ ነዳጅ ማደያ፣ ላቦራቶሪ፣ ክሊኒክ፣ ቢሮዎች፣ የብረት ማከማቻ (Steel Yard)፣ የደማሚት ማከማቻ (Explosive Store) እና እንዲሁም ዋናው RCC ኮንክሪት ማምረቻ መሳሪያዎችና ተያያዥ ፕላንቶች ተከላ ያጠቃልላል። እነዚህም ሥራዎች ሙሉ ለሙሉ ተጠናቀው አገልግሎት በመስጠት ላይ ይገኛሉ።

 

የኮንክሪት ማምረቻ መሣሪያ የመገጣጠም ሥራ

በዋናው ግድብ ቀኝ እና ግራ በኩል የRCC ፕላንት ተከላው ተጠናቆ የRCC ምርት በማከናወን ላይ ይገኛል።

 

የኤሌክትሮ ሜካኒካልና የኃይድሮሊክ ስትራክቸር ሥራዎች

የፕሮጀክቱ የኃይል ማመንጫ፤ የ500 ኪሎ ቮልት ስዊችያርድ፣ የኤሌክትሮ ሜካኒካል እና የሃይድሮ ሜካኒካል ዲዛይን፤ ምርት፤ አቅርቦት ተከላና ፍተሻ ሥራዎች በብረታብረትና ኢንጅነሪንግ ኮርፖሬሽን (ብ.ኢ.ኮ) እየተከናወኑ ይገኛሉ፤ በዚህም በአሁኑ ሰዓት የተለያዩ የኤሌክትሮሜካኒካል እና የሃይድሮሜካኒካል ምርትና ተከላ እየተከናወኑ ይገኛል።

 

ከዚህም ጋር በተገናኘ ቀድመው ኃይል ማመንጨት ለሚጀምሩት ዩኒቶች (ዩኒት 9 እና ድኒት 10) የተርባይንና ጀነሬተር ምርት ተጠናቆ ወደ ሳይት ተጓጉዞ የተከላ ሥራው በመከናወን ላይ ነው። ቀድመው ኃይል ማመንጨት ከሚጀምሩት ዩኒቶች ውጭ ያሉት 14 ዩኒቶችና የተዛማጅ መሳሪያዎች ወይም ዕቃዎች የምርትና የተከላ ሂደትም እንደቀጠለ መሆኑ ተገልጸል።

 

ከዚህም በተጨማሪ ቀድመው ኃይል ማመንጨት ለሚጀምሩት ዩኒቶች ፓወር ትራንስፎርመሮችና ሻንት ሪአክተር ምርት ተጠናቆ ለተከላ ዝግጁ ሆኗል። ከኃይድሮሊክ ስቲል ስትራክቸር ሥራዎች ጋር በተገናኘ የቦተም አውትሌትና ቀደም ብለው ለሚገቡት ዩኒቶች የትራንዚሽንና እንዲሁመ የላይኛውና የታችኛው በሮች ምርትና በተጓዳኝም የተከላ ሥራዎች እየተከናወኑ ይገኛሉ።

 

500 ኪ.ቮ. የኤሌክትሪክ ኃይል ማስተላለፊያ መስመርና

የማከፋፈያ ጣቢያ ግንባታ

ከታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ፕሮጀክት ተነስቶ በቤንሻንጉል ጉሙዝ፣ በኦሮሚያ ምዕራብ ወለጋ አልፎ እስከ ሆለታ የሚደርሰውና 725 ኪሎ ሜትር ግንባታው ተጠናቆ የዋናውን ኃይል ማመንጨት በጉጉት እየተጠባበቀ የሚገኘው ከህዳሴ-ደዴሳ-ሆለታ የተዘረጋው ጥምር ባለ 500 ኪሎ ቮልት ከፍተኛ የኤሌክትሪክ የኃይል ማስተላለፊያ መስመር ግንባታው ለአገልግሎት ዝግጁ ሆኗል።  

 

ተጨማሪ መረጃ

የሚገኝበት ቦታ፡ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ከጉባ ከተማ 20 ኪ.ሜ. ርቀት አካባቢ ላይ ይገኛል።

ከአዲስ አበባ ወደ ፕሮጀክቱ የሚወስዱ አማራጭ መንገዶች

አማራጭ 1፡ ከአዲስ አበባ በስተሰሜን ምዕራብ ደብረ-ማርቆስ፣ እንጅባራ እና ቻግኒ ከተሞችን በማቋረጥ በ730 ኪ.ሜ. ርቀት ላይ ይገኛል።

አማራጭ 2፡ ከአዲስ አበባ በስተምዕራብ ነቀምትና አሶሳ ከተሞችን በማቋረጥ በ830 ኪ.ሜ. ርቀት ላይ ይገኛል።

የሚያመነጨው የኤሌክትሪክ ኃይል፡ ከ6,450 ሜጋ ዋት

አማካይ የውሃ ፍሰት መጠን፡ 1,547 ኪዩቢክ ሜትር በሰከንድ

የውሃው መጠን ከፍታ፡ ከባህር ጠለል በላይ 640 ሜ. ከፍተኛ እና ከባህር ጠለል በላይ 590 ሜ. ዝቅተኛ፤

የዋናው ግድብ ከፍታ እና ርዝመት፡ 145 ሜ. ከፍታ፣ 1 ነጥብ 8 ኪ.ሜ. ርዝመት

የኮርቻ ቅርፅ ግድብ (Saddle Dam) ከፈታ እና ርዝመት፣ 50 ሜ. ከፍታ፣ 5 ነጥብ 2 ሜ. ርዝመት

ግድቡ ሲጠናቀቅ የሚፈጠር ኃይል ስፋት፡ 1,874 ስኩየር ኪ.ሜ.¾

የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ 6ኛ ዓመት በዓል አከባበር ከፊል ገፅታዎች

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
540 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 877 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us