ሃያ ሁለቱ ፓርቲዎች ለመደራደር ስምምነት ላይ ደረሱ

Wednesday, 12 April 2017 12:17

 

በሃያ ሁለት የፖለቲካ ፓርቲዎች እየተካሄደ የነበረው የቅድመ ድርድር ስምንተኛው ዙር ውይይት ሚያዝያ 2 ቀን 2009 ዓ.ም በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተካሂዷል።

ከስድስተኛውና ከሰባተኛው ዙር ውይይቶች ሲንከባለል የመጣው አከራካሪ ነጥብ ብዙ አወያይቷል። ይኸውም ፖለቲካ ፓርቲዎች በሚያደርጉት ድርድር ላይ አደራዳሪው ማን ይሁን የሚል የውይይት ሃሳብ ቀርቦ የነበረ መሆኑ ይታወቃል። ገዥው ፓርቲ እና የተወሰኑ የፖለቲካ ፓርቲዎች ነፃና ገለልተኛ አደራዳሪ በሚለው አማራጭ ሃሳብ ፈንታ፤ ድርድሩ በዙር በተሳታፊ የፖለቲካ ፓርቲዎች መመራት አለበት የሚል አቋም ማራመዳቸው የሚታወስ ሲሆን፤ ስድስቱ እየተባሉ የሚጠሩት (ሰማያዊ፣ መኢአድ፣ ኢዴፓ፣ መኢዴፓ፣ ኢራፓ እና አብአፓ) ነፃና ገለልተኛ አደራዳሪዎች መኖር አለባቸው የሚል አቋም አራምደዋል።

ሚያዝያ 2 ቀን 2009 ዓ.ም በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የተሰበሰቡት የፖለቲካ ፓርቲዎች ልዩነታቸውን ለማጥበብ በቅተዋል። በድርድሩም ለመቀጠል ተስማምተዋል። በውይይቱ ላይ በገዢ ፍሬ ነገርነት ከተነሱት መካከል ጥቂቱን በዚህ መልኩ አቅርበነዋል። 

 

 

በውይይቱ ላይ ቀዳሚ አቋማቸውን ያቀረቡት የስድስቱ ፓርቲዎች ተወካይ አቶ አስፋው ሀብተወልድ እንዳሉት፤ “ለገዳይ ስንዘፍን፤ ሠራተኛ እና ሥራ ፈጣሪን እናናንቃለን። …እኔ ያልኩት ካልሆነ ሞቼ እገኛለሁ እንላለን። ይህንን ሲወርድ ሲወራረድ የመጣው የሃገራችን ታሪክ የጦርነት ታሪክ አድርጎታል። በከፊልም ወርሰናል። እኔ ያልኩት ካልሆነ የሚባለው አስተሳሰብ በእውቀት መለወጥ ይገባዋል። ስድስቱ ፓርቲዎች በዚህ አስተሳሰብ ለውጥ ያምናሉ። በዚህ በሃያ አንደኛ ክፍለ ዘመን ላይ ሆነን የቆየው የባሕላችን ውጤት ጎድቶናል። …የሰጥቶ መቀበልን መርህ መቀበል የግድ ነው። ከስሜት ነፃ ሆነን ለሀገር እና ለወገን አስበን ታሪክ በበጎ ጎን ሊያስታውሰን ትውልድ ሊያመሰግነን በሚያስችል ደረጃ ድርድሩን እንድናካሂድና መልካም ደረጃ እንድንደርስ መኢአድ ከተባባሪዎቹ በአክብሮት ይጠይቃል። …ሕዝብ ለውጥ ይፈልጋል፤ በሳይንስም ለውጥ ብቻ ነው ዘላለማዊ። …በስነምግባር ደንብ መግባባት ያቃተን፤ ወደ ዋናው ድርድር አጀንዳ ብንገባ ምን ያህል መራመድ እንችላለን?… ከመቶ ሚሊዮን ሕዝብ በላይ ይመለከተናል። ከውጭ የተወሰኑ ይመለከቱናል። ድርድሩ ከፍፃሜ ካደረስን ያመሰግኑናል። ካላደረስነው ምን እንደሚፈጠር መገመት ያስቸግራል… የቻይናዊያን አባባል ከችግሩ ሳይሆን ከመፍትሄው ሁን ይላል። …ኢሕዴአግ በተለይ እንደቱርኩ የቀድሞ መሪ ከማል አታቱርክ በሀገራችን የመድብለ ፓርቲ ጀግና መሆን በእጁ ነው። …ዛሬም የገዢው ፓርቲ ኢሕአዴግ አቋም ካልተሻሻለ መኢአድ ከተባባሪዎቹ ጋር ሆኖ ያለአደራዳሪ አጀንዳ አቅርቦ የሁለትዮሽ ድርድር ለማድረግ ለሰላም ሲባል አቋማችንን አሻሽለን ቀርበናል። …ኢሕአዴግ መንገዱን እንዳይዘጋው አደራ እንላለን። …በእኛ ድርጅት በኩል እንኳን ብዙ አባላት ታስረውብናል። ትንሿ የእንቅስቃሴ ምህዳር በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ተገድባ አንዳች የፖለቲካ ሥራ ማከናወን አልቻልንም። በዚህ እና በሌሎች ምክንያቶች ድርድሩ ያለአንዳች ቅድመ ሁኔታ የሚመለከታቸውን ሁሉ አካቶ ወደ ዋናው አጀንዳ ገብተን መፍትሄዎች እንዲፋጠኑ የጋራ እድላችን በሆነች በአንዲት ኢትዮጵያ ስም እንጠይቃለን..” ብለዋል።

ኢዴፓን በመወከል አቶ ዋሲሁን ተስፋዬ እንዳስረዱት፤ “..በዚህ ውይይት ላይ አማራጮች ይዘን ቀርበናል። አንደኛ፣ ገለልተኛ አደራዳሪ ይኑር የሚለው አቋማችን የጸና ነው። …በልዩነትም እንዲሰፍርልን እንጠይቃለን። በሁለተኛ ደረጃ ድርድሩ እየተካሄደ ያለው በሞዳሊቲው መሰረት በአስራ ሁለት አጀንዳዎች ነው። አንዱ የአደራዳሪዎችን የተመለከተ ነጥብ ነው። በዚህ ነጥብ ላይ ስምምነት አልተደረሰም ተብሎ ድርድሩን አለመሳተፍ ወይም ማቋረጥ እንደኢዴፓ ተገቢ ነው ብለን አናምንም። …ድርድሩን ለመቀጠል አቋም ይዘናል።”

መኢብን በበኩሉ፤ “ከዚህ ቀድም ስድስቱ የሚል ስያሜ ነበር የሚጠቀሙት። አሁን መኢአድ እና ተባባሪዎቹ እየተባለ ነው። እኛ የምናውቀው ደግሞ እያዳንዱን ፓርቲ በተናጠል ነው። አንደኛ፣ እያንዳንዱ ፓርቲ በእያንዳንዱ ነጥብ ላይ ያለውን አቋም ማሳወቅ አለበት። ሁለተኛ ሌላ የመደራደሪያ ነጥቦች ነው ይዘው እየመጡ ያሉት። በእያንዳንዱ ነጥብ ላይ ልዩነታችን እያሰፈርን ወደ ሚቀጥለው ነጥብ እንሂድ ነው የሚሉት። ይህ ደግሞ ሞዳሊቲውን ከመጨረስ አኳያ አስቸጋሪ ነው የሚሆነው።…በምርጫ ቦርድ ያልታወቀ አንድነት ለአሰራር አስቸጋሪ ነው። በሚወሰድ አቋም ላይ በኋላ የእኔ አይደለም የሚል ጥያቄ ሊያመጣ ይችላል።” ሲሉ ሊቀመንበሩ አቶ መሳፍንት ሽፈራው ተናግረዋል።

መኢብን ላቀረበው ጥያቄ መኢአድ የሰጠው ምላሽ፤ “..እያንዳንዳቸው በሕግ አይታወቁም የሚለውን እያጠራነው መሄድ አለብን። ሃሳብ ነው አንድ ያደረገን። በሃሳብ አንድ አትሁኑ የሚል አካል ካለ ይህ ሌላ ጥያቄ ነው የሚሆነው። ለሌላውም ማሳሰቢያ የሚሆነው፣ ስድስቱ በሞዳሊቲው ላይ ሃሳባችን አንድ ነው። ተባባሪም ተባለ፣ ስድስቱም ተባለ፣ የሃሳብ ውጤት ነን። የፖርቲዎቹ ሕልውና የተጠበቀ ነው። በአጀንዳዎቹም ላይ አንድ ልንሆን እንችላለን።  ሌላ የመደራደሪያ ነጥብ ነው ይዘው የመጡት የተባለው መድረኩ ውሳኔ ይስጥበት። እንደመኢአድ ግን ገለልተኛ አደራዳሪ መኖሩ ጽኑ እምነታችን ነው። ልዩነታችንም በቃለ ጉባኤ እንዲሰፍርልን እንጠይቃለን። መፍትሄ ብለን ያቀረብነው፣ ድርድር ሰጥቶ መቀበል ነው። መኢአድ እና ስድስቱ ፓርቲዎች ነፃ ገለልተኛ አደራዳሪ ሲያነሱ፤ ኢሕአዴግ ድርድሩ በዙር የሚለውን ማንሳቱ እንዲሁም ሌሎቹ የወሰዱት አቋም እንደተጠበቀ ሆኖ፣ ሃሳባቸውንም እናከብራለን። …በድርድር ሕግ ኢሕአዴግ ግማሽ መንገድ ሄዶ፤ ሌሎቻችንም ግማሽ መንገድ ቀርበን፤ ለሀገራችን ጥቅም፣ ለሕዝቦች ጥቅም እና ለፓርቲዎቻችን ሕልውና ጥቅም የሚሰጥ ነው በሚል ገለልተኛ አደራዳሪ አንስተናል። የሁለትዮሽ ድርድር ስናነሳም ኢሕአዴግ ከስድስቱ ድርጅቶች ጋር እንዲደራደር ነው የጠየቅነው። ለዚህ ግልጽ አጭር ጥያቄ ምላሽ  የምንጠብቀው ከኢሕአዴግ ነው” ብለዋል።

የኢራፓ ሊቀመንበር አቶ ተሻለ ሰብሮ በበኩላቸው፤ “የአቶ መሳፍንትን አስተያየት እደግፋለሁ። በሌላ በኩል ደግሞ ማብራሪያም ያሻዋል። እርግጥነው ስድስቱ ተብለን ስንጠራ ነበር፤ አሁንም ስድስቱ ነን። መኢአድ እና ተባባሪዎቹ የሚለው አገላለጽ ትክክል አይደለም። ስድስቱ የሚለው በሃሳብ ስድስት ነን። …ወደ አጀንዳዎች እንግባ የሚባለው ነገር ፈቃዳችሁ ከሆነ ባንቸኩል ጥሩ ነው። መንጠባጠብ የኢትዮጵያን ሕዝብ ጥያቄ አያፋጥነውም፤ ያዳክመዋል፣ ያቀጭጨዋል። በዴሞክራሲ አሰራር እና ድርድር አጣብቂኝ ውስጥ ያስገቡ አጀንዳዎች ትዕግስትን፣ ጥበብን፣ ብልሃትን፣ መቻቻልን እና መከባበርን የሚጠይቁ ናቸው። ይህ ለእኛ አዲስ ሊሆን አይገባም። እነዚህን ዴሞክራሲያዊ መርሆችን ተጠቅመን ባለፉት በስድስተኛ እና በሰባተኛ ላይ “አደራዳሪ” እና “ያላደራዳሪ” የሚሉት ናቸው። ወደመሃል መምጣት ያለብን ይመስለኛል። ምንግዜም መፍትሄ ይኖራቸዋል።…ስድስቱ ያቀረቡት ሃሳብ እንደተጠበቀ ሆኖ፣ ከኢራፓ መፍትሄ አቅርበናል። ይኸውም፣ ከመሰረቱ የደፈረሰ አይጠራም። አጀንዳዎቹ መፈተሽ አለባቸው። …አጀንዳዎች ዙሪያ ላይ መፈራራትና መጠራጠር አለ። …ኢሕአዴግ አጀንዳዎችን በተመለከተ ማንኛውም አጀንዳ መቅረብ ይችላል ሲል ደጋግሞ ሲናገር ሰምተናል፤ እያረጋገጠልን ከሆነ እሰየው። …ሕዝባችንም እየጠበቀ ያለው የአለም ሕብረተሰብ እየተመለከተን ያለው፣ የሚቀርቡት ብሔራዊ አጀንዳዎች ምንድን ናቸው? ምን አይነት መፍትሄዎች ይሰጣሉ ከማለ ነው።” ብለዋል።  

እንዲሁም ከመላው ኦሮሞ አቶ ተሰማ ሁንዴሳ እንዳሉት፤ “በዚህ ነጠብ ዙሪያ ከበቂ በላይ ውይይት አድርገናል፤ መቋጨት አለበት። አብዛኛው የድርድሩ ተሳታፊ ፓርቲዎች አደራዳሪ እንደማያስፈልግ ከስምምነት ደርሰዋል። የተወሰኑ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጊዜ ተሰጥቷቸው አቋማቸውን ይዘው ቀርበዋል። እንደተገነዘብኩት ኢዴፓ በአብዛኛው ድምጽ የተገዛ መስሎኛል። ይኸውም፣ ልዩነታቸውን አስመዝግበው፣ በድርድሩ ለመቀጠል ወስነዋል። በጣም የሰለጠነ መንገድ ነው። በሰጥቶ መቀበል ማመን ነው። በጣም የምቀበለው አቋም ነው። ሌላውም መድረክ ረግጦ ወጥቷል፣ መብቱ ነው፤ እቀበለዋለሁ። ሌሎቹም ቢሆኑ አቋማቸውን አሳወቁ እንጂ ከድርድሩ እንወጣለን አላሉም። ስለዚህም ልዩነታችን እንደተጠበቀ ሆኖ፣ ድርድሩን መቀጠል እንችላለን። …በዚህ ጉዳይ ላይ ከዚህ በላይ ጊዜ ማጥፋቱ ተገቢ አይመስለኝም።” ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ አንድነት ንቅናቄ ሊቀመንበር አቶ ገብሩ በርሄ እንደገለፁት፤ “በመድረኩ ላይ እየቀረበ ያለው ሁለት አይነት ሃሳብ ነው። አንደኛው፣ ኢሕአዴግ ያወያየን የሚል ነው። ይህ ኢሕአዴግን የሚመለከት ነው። ሁለተኛው፣ ያለአደራዳሪ ድርድሩ ይቀጥል የሚል ነው። ሶስተኛው፣ ኢራፓ አማራጭ አለኝ ሲሉ ሰምቻለሁ ሆኖም ማቅረባቸውን አላስታውስም። እዚህ ላይ ያለአደራዳሪ ሲባል፣ ዝም ተብሎ መድረኩ የሚንሸራሸር አይደለም። ሁላችንም አምነንበት እንዴት መደራደር እንዳለብን ጨምቀን በውይይት እንዴት እንደምንመራ የምናስቀምጠው መርህ ይኖራል። ለዚህም ነው ገለልተኛ የሚባል ከሚመጣ በራሳችን እንደራደር ያልነው። …ስለዚህ ነጥቦችን ስናጸድቃቸው አሰራሩ አብሮ ይመጣል። ሰጥቶ መቀበል መጀመር ያለበት ከዚሁ ነው። አቋማቸውን እናከብራለን፤ ሀገር የሚጎዳ ቢሆን በእሳት አንጫወትም። የሚያስረዳንም ስላጣን ነው። በራሳችን መደራደራችን የሚጎዳ ቢሆንና በታሪካችን ላይ ጠባሳ የሚጥል ከሆነ እኛም አንቀበለውም። በዚህ መልኩ ያስረዳንም የለም። እንደማይጎዳ ግን እናምናለን። ስለዚህ እንደእኔ የተከበሩ የመኢአድ ተወካይ በስፋት ነው የገለፁት። እሳቸው ያቀረቡትን እንደአጠቃላይ መርህ ወስደነው ውይይታችን ቢቀጥል ጥሩ ይመስለኛል።…ልዩነታቸው መመዝገቡ የስብሰባ አካሄድ ነው። ወደፊትም በድርድሩ ልዩነታችን እያስመዘገብን ነው የምንሰራው።

ኢዴፓ ከስድስቱ ፓርቲዎች ጋር መክሬበታለሁ ያለውን አማራጭ ሲያስቀምጥ፤ “አማራጭ የማቅረብ አጀንዳ ውስጥ ስለተገባ በእኛ በኩል ያለውንም እናቀርባለን። ይኸውም፣ በዙር መደራደር የሚለውን በመርህ ደረጃ እንቀበላለን። ሆኖም በዙር የሚለው ሃሳብ ላይ አማራጭ አለን። ይህም ሲባል፣ በዙር ሲሆን ኢሕአዴግም ጨምሮ ሃያ ሁለቱ ፓርቲዎች እያደራደሩ እየተደራደሩ የሚኬድበት ሁኔታ ወጥነት የጎደለው የድርድር ሥርዓት ያስከትላል። የአጀንዳ መቆራረጥ፣ መዘበራረቅ ያስከትላል። ሁለተኛ፣ ሃያ አንዱ ፓርቲዎች በዙር ይድረሳቸው ቢባል እንኳን ሃያ አንድ አጀንዳ ሊኖር አይችልም። እስካሁን ካስቀመጥነው እንኳን ስምንት ዘጠኝ ናቸው። ስለዚህም ድርድሩ በዙር ሆኖ፣ በሁሉም ፖርቲዎች ፈቃድ የሚመረጡ ሶስት ወይም አምስት ቋሚ አደራዳሪዎች ተሰይመው ድርድሩ መካሄድ አለበት የሚል አንድ አማራጭ እናቀርባለን።”

በመጨረሻም ኢሕአዴግ በአቶ አስመላሽ ወልደስላሴ በኩል አቋሙን አንፀባርቋል። ይኸውም፤ “በመጀመሪያ ስድስቱ ፓርቲዎች በሕገደንባቸው መሰረት ተወያይተው ዛሬ ላቀረቡት ሃሰብ አክብሮት አለን። የኢትዮጵያ ዴሞክራሲ ባሕል በዚህ መልኩ ነው ማደግ ያለበት። በሁሉም ጉዳዮች ላንስማማ እንችላለን…በሒደት በምናደርገው ግን ለዴሞክራሲ መጎልበት የራሱ አስተዋፅዖ አለው። …አደራዳሪ ይኑር፣ አይኑር የሚለውን ተወያይተንበታል፣ ሆኖም ልዩነቶቹ እንደተጠበቁ ሆነው ድርድሩ ለመቀጠል የመጣው ሃሳብ በአዎንታዊ የሚወሰድ ነው። …ባለፈው ስንወያይም ያነሳነው የትኞቹ ፓርቲዎች በድርድሩ ይሳተፉ የሚሉ ናቸው። አንደኛው፣ የመሪ ተደራዳሪ ፓርቲ፣ የተወሰኑ ፓርቲዎች ድርድሩን ይወክሉ እና ሃያ ሁለቱ ፓርቲዎች በድርድር ይሳተፉ የሚሉ ናቸው። መሪ ተደራዳሪ እና የተወሰኑ ፓርቲዎች ይወክሉ የሚለው ሃሳብ ተቀባይነት አላገኘም። …በዙር የሚለውን ስናቀርብ መድረክ የሚመሩ ሰዎች ድርድሩን ከማመቻቸት ውጪ የተለየ ሚና የላቸውም። ሌላው ቢቀር የሚነሱ ሃሳቦች ላይ ፖለቲካዊ አስተያየት ማቅረብ አይችሉም። ለተደራዳሪዎች እድል የመስጠት ነገር ብቻ ነው።… ከዚህ የዘለለ ሚና የለውም። በእኛ በኩል መድረኩን ተቃዋሚ ፓርቲዎች ቢመሩትም ምንም ችግር የለብንም። በድርድሩ ተሳትፈን ሃሳባችን የመግለጽ መብት እስካገኘን ድረስ በድርድሩ መድረክ ላይ እድል መስጠት፣ አለመስጠት አንፈልገውም። በስድስቱ ፓርቲዎች የቀረበው በቋሚነት የሚመሩ ከዚህ መድረክ የሚመረጡ ሰዎች በመሰየም ድርድሩ እንዲካሄድ የቀረበውን ሃሳብ ሌሎች ፓርቲዎችም ከተስማሙ፣ በእኛ በኩል አማራጩን ለመመልከት ችግር የለብንም። …በጋራ አጀንዳዎች በጋራ መወያየቱ ተገቢ ነው። የጋራ አጀንዳ ባልሆኑትም ላይ በተናጠልም ሆነ በሁለትዮሽ መንገድ እንወያያለን። …ዋናው ግን አቶ አሰፋ እንዳስቀመጡት ይህንን ታሪካዊ መድረክ በጋራ ብንጠቀምበት። …ፖለቲካ ፓርቲዎች የዲሞክራሲ ተቋም ብቸኛ እና ብቸኛ ተቋም አይደሉም።” ብለዋል።

ከላይ በሰፈሩት ሃሳቦች ከፍተኛ የሃሳብ መንሸራሸሮች ከተደረጉ በኋላ በሁለት አማራጮች ዙሪያ ዳግም ውይይት ፓርቲዎቹ አድርገዋል። አንደኛው፣ ድርድሩ በዙር ይመራ የሚለው ሲሆን፤ ሁለተኛው ድርድሩ በፓርቲዎቹ ከመድረኩ በሚመረጡ ቋሚ የመድረክ መሪዎች ተሰይመው ድርድሩ ይካሄድ የሚለው ነው።

በማጠቃለልም፤ መድረኩን ሲያስተባብሩና ሲመሩ የነበሩት አቶ ሽፈራው ሽጉጤ፤ ተሳታፊ የፖለቲካ ፓርቲዎቹ ልዩነታቸውን እንዲያጠቡ ሃሳቦችን በማደራጀት ወደ አንድ ነጥብ እንዲደርሱ ያደረጉት አስተዋፅዖ በጣም የሚደነቅ ነው። በተለይ አቶ ሽፈራው፣ ከዚህ በፊት በፖለቲካ ፓርቲዎች ምክር ቤት ለመሳተፍ እንደጋሬጣ የሚነሳ ፈርሙ፣ አትፈርሙ የሚባለውን አጨቃጫቂ ነጥብ በማስታወስ፣ ውይይቱ ወደዚያ እንዳያመራ የመድረኩን ሚዛን በመጠበቅ ሁሉም ፓርቲዎች በበቂ ስምምነት ላይ እንዲደርሱ በማድረግ፤ በድርድሩ በሚሳተፉ የፖለቲካ ፓርቲዎች ፈቃድ በተመረጡ ቋሚ አደራዳሪ ሰዎች ድርድሩ እንዲመራ ተስማምተዋል።

በፖለቲካ ፓርቲዎች ድርድር የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ አንድነት መድረክ (መድረክ) እና ሰማያዊ ፓርቲ ራሳቸውን በማግለላቸው የቅድመ ድርድር ጉባኤ ላይ አልተሳተፉም።¾

ይምረጡ
(1 ሰው መርጠዋል)
379 ጊዜ ተነበዋል

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us