ለብሔራዊ መግባባት አስተዋጽኦ አላበረከቱም የተባሉት የግል መገናኛ ብዙሃን

Wednesday, 19 April 2017 12:46

 

በይርጋ አበበ

 

በአዋጅ ቁጥር 533/1999 መሰረት የኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለስልጣን በአገሪቱ የሚገኙ መገናኛ ብዙሃን ተቋማትን ፈቃድ ክትትልና ቁጥጥር የሚያከናውንበትነ ስልጣን ተሰጥቶታል። ይህ ተቋም ባሳለፍነው ሳምንት በሒልተን ሆቴል ከግል ብሮድካስት መገናኛ ብዙሃን (ባለስልጣኑ የንግድ መገናኛ ብዙሃን ነው የሚላቸው) ተቋማት ጋር ለአንድ ቀን ውይይት አካሂዶ ነበር። “ሕገ መንግስታዊ ኃላፊነትን በመወጣትና የዴሞክራሲ ስርዓትን በመገንባት ረገድ የንግድ ብሮድካሰት ሚዲያው የሚገኝበት ሁኔታ” በሚል ርዕስ ውይይት የተካሄደ ሲሆን ለውይይቱ መነሻ ጥናታዊ ጽሁፍ በብሮድካሰት ባለስልጣኑ የተለያዩ ኃላፊነት ያላቸው ባለሙያዎች አቅርበዋል። ጥናቱ ከቀረበ በኋላም የብሮድካስት ባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር አቶ ዘረዓይ አስገዶም ውይይቱን የመሩ ሲሆን በውይይቱ ማጠቃለያ ደግሞ የብሮደካስት ባለስለጣኑ ስራ አመራር ቦርደ ሰብሳቢ አቶ አስመላሽ ወልደስላሴ የማጠቃለያ ንግግር አቅርበዋል።

ብሮድካስት ባለስልጣኑ ባዘጋጀው የውይይት መድረክ ላይ መነሻ ጽሁፍ ያቀረቡት የባለስልጣኑ ኃላፊዎች (የመገናኛ ብዙሃን ክትትልና አቅም ግንባታ ዳይሬክሩ አቶ ዴሬሳ ተረፈ እና የህግና የማስታወቂያ ዳይሬክተሩ አቶ ግዛው ተሰፋዬ) በጥናታዊ ጽሁፋቸው የግል ብሮድካስት መገናኛ ብዙሃን ተቋማቱ ባለፉተ 12 ወራት አካባቢ ያሰራጫቸውን 150 ዜናዎችና 800 ፕሮግራሞች መሰረት አድርገው ጥናቱን እንደሰሩ ገልጸዋል። በዚህ ጥናታቸውም ከመገናኛ ብዙሃን ድርጅቶችም ሆነ ከብሮድካሰት ባለስልጣኑ አሉ ያሏቸውን ችግሮች ያቀረቡ ሲሆን በተለይ የግል ብሮድካስት መገናኛ ብዙሃን ተቋማቱ ለብሔራዊ መግባባት የሰሩት ስራ እዚህ ግባ የሚባል አይደለም ብለዋል። በአድዋ ድል ዙሪያ በተሰሩ ዘገባዎችም ድሉን ለነገስታቱ (ለአጼ ምኒልክና እቴጌ ጣይቱ) በመስጠት የብሔር ብሔረሰቦችንና ህዝቦችን ድካም በባዶ አባዝተዋል ሲሉ ትችታቸውን አቅርበዋል።

በጥናታዊ ጽሁፉና በውይይቱ ዙሪያ የተነሱ ሃሳቦችን እንዲሁም አስተያየታቸውን እንዲሰጡን ካነጋገርናቸው ባለሙያዎች ያገኘናቸውን መረጃዎች አጠናቅረን ከዚህ በታች አቅርበነዋል።

 

 

የውይይቱ ዓላማ እና የመረጃ አራጋቢነት ጉዳይ

የብሮድካስት ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ዘርዓይ አስገዶም “አገራችን ከምትገኝበት ሁኔታ አኳያ ይህ የውይይት መድረክ መካሄዱ አስፈላጊ ነው” ሲሉ ተናግረዋል። አቶ ዘርዓይ “አስፈላጊ ነው” ብለው በጠሩት የውይይት መድረክ ላይ ከተሳታፊዎች ለተነሱላቸው ጥያቄዎችም ምላሽ ሰጥተዋል። በግል ሚዲያው በኩል ማራገብ አለ ያሉት ዳይሬክተሩ “እንደኛ አይነት ኋላቀር አስተሳሰብ እና አመለካከቶች ባሉበት አገር ማራገብ በጣም አደገኛ ነው” ሲሉ ለመገናኛ ብዙሃን ተቋማቱ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል። 

አቶ ዘርዓይ ሀሳባቸውን ሲያጠናክሩም “አሁን ለምሳሌ በቆሼ የደረሰውን አደጋ የዘገባችሁበት መንገድ በጣም የተጋነነ ነው። በቻይና በየወሩ ተመሳሳይ ችግረ አለ ትናንትም ኮሎምቢያን ጎርፍ ወስዷታል” ሲሉ ተመሳሳይ አደጋ በየትኛውም ዓለም ይከሰታል የእኛን ለምን እንደ አዲስ ታዩታላችሁ አይነት ንግግር አቅርበዋል። አቶ ዘርዓይ በንግግራቸው አያይዘውም “ትኩረት ማድረግ ያለብን በመፍትሔዎቹና በመንስዔዎቹ ላይ በቂ ትንታኔ ማቅረብ ነው” ብለዋል።

የዛሚ ኤፍ ኤም ተወካዮች አቶ ዘሪሁን ተሾመ እና ጋዜጠኛ መስታወት ተፈራ “የመንግስት ስራ አስፈጻሚዎች መረጃን ይከለክላሉ እነሱን ያላስደሰታቸውን ፕሮገራም ስናቀርብ ደግሞ የደብዳቤ ጋጋታ ያቀርባሉ። በቅርቡ ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የተጻፈልን ደብዳቤ የአገሪቱን ህግና ስርዓት አክበሮ ለሚሰራ ለእኛ ሚዲያ ሳይሆን ለኢሳት የተጻፈ ነበር የመሰለን። እኛ ግን ቀድመን ሃሳባቸውን እንዲሰጡን ደጋግመን ጠይቀናቸው የነበረ ቢሆንም እንደ ጥፋተኛ ቆጠረው ማስተባበያ ካላወጣችሁ ብለው የማስፈራሪያ ደብዳቤ ጻፉልን” ሲሉ የግል መገናኛ ብዙሃን ድርጀቶች ያለባቸውን ጫና ጠቅሰው አቅርበው ነበር።

ለዚህ ቅሬታ መልስ የሰጡት በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የባህልና ቱሪዝም እና የመገናኛ ብዙሃን ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ወይዘሮ ፈቲያ የሱፍ “አንድ ሰራ አስፈጻሚ እምቢ አለ ተብሎ እንደዚህ ማራገብ ትክክል አይደለም። አንዳንድ ሚዲያዎች በማራገብ (ሰንሴሽናሊዝም) ተወዳጅ ለመሆን ይጥራሉ” በማለት መልስ ሰጥተዋል። በወይዘሮ ፈቲያ ላይ ተጨማሪ መልሰ የሰጡት አቶ ዘርዓይ በበኩላቸው “አንድ አስተዳደር መረጃ አልሰጥም አለ ተብሎ ሁሉንም መውቀስ ተገቢ አይደለም። ኢህአዴግ እንደሆነ እንኳንስ ለወዳጆቹ ለጠላቶቹም ቢሆን ችግር እንዳለበት ከመግለጽ አልተቆጠበም” ሲሉ ተናግረዋል።

በሁለቱ ባለስልጣናት ምላሽ ያልተደሰተችው ጋዜጠኛ መስታወት “አንድ ስራ አስፈጻሚ እምቢ አለ ተብሎ  የሚል ምላሽ ከእናንተ አልጠብቅም ነበር። በአንድ ስራ አስፈጻሚ ችግር ምክንያት የስንት ሰው ህይወት ነው የሚጎዳው? አንዲትን የ84 ዓመት አዛውንት ጎዳና ላይ ጥሎ ቁልፉን የሚሸጥ ሰራ አስፈጻሚ እኮ ነው ያለው። እኔ በግሌ ለአንድ ጉዳይ ሶስት ዓመት የተመላለስኩበት ኃላፊ አለ” ያለችው ጋዜጠኛዋ “ስለ መልካም አስተዳደር ብቻ ሳይሆን ስለ መልካም አስተዳደርም መስበክ አለብን” ስትል ተናግራለች።

ከዚህ በተቃራኒ ደግሞ ጥናቱን ያቀረቡት የብሮድካስተ ባልስልጣኑ የስራ ኃላፊ “አንዳንድ የመንግስት ተቋማትና የስራ ኃላፊዎች መረጃ ሲጠየቁ አለመስጠት በንግድ መገናኛ ብዙሃኑ በኩል ያሉ ተግዳሮቶች ናቸው” ብለዋል። የባለስልጣኑ ስራ አመራረ ቦርድ ሰብሳቢ አቶ አስመላሽ ወልደስላሴ በበኩላቸው “ባለስልጣን መረጃ ተጠይቆ አልመልስም ካለ እገሌ የተባሉት ኃላፊ ደውለን መልሰ ለመስጠት ፈቃደኛ አልሆኑም ብለን እንናገራለን ብትሉ ይህ ባለስልጣኑን ለማሳጣት ጥሩ አጋጣሚ ነው። ይህን እስካደረጋችሁ ድረስ ሰራ አስፈጻሚ እምቢ አለ ብሎ መጮኽ አይጠቅምም። ዋናው ቁልፉ ነገር ከጋዜጠኞች የሚጠበቀው በአራቱ የዴሞክራሲ እሴቶች መገንቢያ (የህግ የበላይነት ምክንያታዊ መሆን መቻቻልና መፍጠርና ሰጠቶ መቀበል) ተጠቅሞ ችግሮችን ፈልፍሎ ማውጣትና ማቅረብ ነው” ሲሉ ተናግረዋል።

 

 

ብሔራዊ መግባባትን አልሰበካችሁም

በብሮደካስት ባለስልጣን የህግና ማስታወቂያ ዳይሬክተሩ አቶ ግዛው ተስፋዬ “የንግድ ብሮድካስት መገናኛ ብዙሃን አጀንዳ ቀርጸው በአበይት አገራዊ ጉዳዮች ላይ ብሔራዊ መግባባትን በሚያጎለብቱ ፕሮገራሞችን ከማሰራጨት እና በብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች እኩልነትና መፈቃቀድ ላይ የተመሰረተ ዴሞክራሲያዊ አንድነትን የሚያጠናክር ተከታታይነት ያላቸው ፕሮግራሞችን ከማቅረብ አኳያ እጥረት ይታይባቸዋል” ሲሉ የጥናታቸውን ወጤት አቅርበዋል። አቶ ግዛው አያይዘውም “የብሮድካስት ፈቃድ ሲሰጣቸው ከገቡት ውል ውጪ በመሆን አብዛኛውን ጊዜያቸውን በስፖርትና በመዝናኛ ፕሮግራሞች ላይ ያተኩራሉ” ሲሉ የገለጹ ሲሆን “በህዝብ አየር ሰዓት ላይ የልጅን ሰርግ የቀጥታ ስርጭት በመስጠት ለግል ጥቅማቸው እስከማዋለ የደረሱ መገናኛ ብዙሃንም አሉ” በማለት ተናግረዋል።

የብሔር ብሔረሰብ ሙዚቃዎችን በእኩልነት አለማስታገድ በግል ብሮድካስት ሚዲያዎች ላይ እንደሚታይ በጥናት አቅራቢው ከቀረቡ የግል መገናኛ ብዙሃን ተቋማት ችግሮች አንዱ ነው። በአጠቃላይም የብሔር ብሔረሰብ ሙዚቃን አለማስተላለፍን ጨምሮ የመገናኛ ብዙሃኑ ለብሔራዊ መግባባት ያደረጉት አስተዋጽኦ ዝቅተኛ መሆኑ ተገልጿል። 

ብሔራዊ መግባባትን በተመለከተ መልሰ የሰጡት በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግስት ተጠሪ ሚኒስትርና የብሮድካስት ባለስልጣን ስራ አመራር ቦርድ ሰብሳቢ አቶ አስመላሸ ወልደስላሴ “ብሔራዊ መግባባት ሲባል በህገ መንግስቱ የተቀመጠ መሰረታዊ መርህ በህዝቡ ዘንድ ተቀባይነት እንዲኖረው በምን መልክ ሊጠቀምባቸው እንደሚችል ለህብረተሰቡ ማስረዳትና የማስረጽ ስራ እንጂ የገዥውን ፓርቲ ፖሊሲና ስትራቴጂ ትክክል ነው አይደለም መናገር አይደለም” ሲሉ ተናግረዋል።

በሌላ በኩል ደግሞ አስተያየታቸውን ለሰንደቅ ጋዜጣ የሰጡ የአንድ መገናኛ ብዙሃን ድርጅት ተወካይ “ብሔራዊ መግባባት ማለት በዚህ መልኩ ስራ ይህን አትስራ እያሉ ማስፈራራት አይደለም። ህዝቡ ያመነበትን እና የተቀበለውን ጉዳይ ማቅረብ ነው። ለዚህም የህዳሴውን ግድብ በተመለከተ የእኛን ሚዲያ ጨምሮ በሌሎች ሚዲያዎችም ህዝባዊ ተቀባይነት እንዲኖረው የበኩላችንን ጥረት አድርገናል” ሲሉ ተናግረዋል። አስተያየት ሰጪው አያይዘውም “የብሔር ብሔረሰብ ሙዚቃ በተመጣጣኝ መልኩ አላቀረባችሁም ብሎ ብሔራዊ መግባባትን አልሰበካችሁም ማለት ለእኔ ቀልድ ነው የሚሆንብኝ” ብለዋል።

ሌላው አስተያየት ሰጪ በበኩላቸው “የመንግስትን ህግና ስርዓት አክብረን ፈቃድ ከወሰድን በኋላ በየዓመቱ የሚጠበቅብንን ግብር እየከፈልን አገራዊ ግዴታችንን የምንወጣ ተቋማት ነን። የመንግስት ድርጅቶችን ማስታወቂያዎች ግን በመመሪያ ለተወሰኑ የግል መገናኛ ብዙሃን እና ለመንግስተ መገናኛ ብዙሃን ብቻ እየሰጡ እኛን ወሬ አራጋቢ ለብሔራዊ መግባባት ደንታ የሌላቸው ብሎ መጥራት ከውንጀላ አሳንሼ አላየውም። እኛም እንደ አገሪቱ ባለቤትና ግብር ከፋይነታችን ልናገኘው የሚገባንን ጥቅም እና መረጃን እየከለከሉ የማግለል ስራ የሚሰሩት እነሱ (ብሮድካስት ባለስልጣኑን) ሆነው ሳለ ለምን የራሳቸውን ድክመት ትተው በሰው ላይ ያሳብባሉ?” በማለት ጥያቄያዊ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።

 

እኔም ደካማ ነኝ

ሚያዝያ 4 ቀን 2009 ዓ.ም በሒልተን ሆቴል የተካሄደው የውይይት መድረክ የተዘጋጀው በብሮድካስት ባለስልጣን ሲሆን ጥናት አቅራቢዎቹም ሆኑ አጥኚዎቹ የብሮድካስቱ ከፍተኛ አመራሮች ናቸው። በውይይቱ ላይ ለሚነሱ ጥያቄዎች መልሰ የሰጡትና መደረኩን የመሩት የብሮድካስት ባለስልጣኑ ዋና ዳይሬከተር ሲሆኑ በክብር እንግድነት ተገኝተው ለተሳታፊዎች ተጨማሪ መልሰ የሰጡት የባለስለጣኑ የስራ አመራረ ቦርድ ሰብሳቢው አቶ አስመላሽ ወልደስላሴ ናቸው።

ብሮድካስት ባለስልጣኑ ራሱ አዘጋጅቶ ራሱ ባቀረበውና ራሱ ባወያየው እንዲሁም ራሱ መልሰ ሰጪ በሆነበት የውይይት መድረክ ላይ የብሮድካስት ባለስልጣኑ “ድክመት” ተብለው በጥናት የተገኙ እንዳሉ ተገልጿል። ጥናት አቅራቢዎቹ የብሮድካስት ባለስልጣኑን ድክመቶች ሲያስቀምጡም “በአገሪቱ ውስጥ አንደ ወጥ የሆነ አንቴና አለመኖር ለግል መገናኛ ብዙሃኑ መርጃ መሳሪያዎች የሚከፈለው ቀረጥ ከፍተኛ መሆን የአቅም ግንባታ ስልጠናዎችን አለማዘጋጀት እና ተከታታይነት ያላቸውን ውይይቶች በየጊዜው አለማካሄድ የሚሉት ይገኙበታል።

የመንግስት ማስታወቂያዎችን ለሁሉም የመገናኛ ብዙሃን ተቋማት ፍትሃዊ በሆነ መልኩ የማዳረስ ህጉ መሆኑ ይታወቃል። ሆኖም ይህ ደንብ በስራ ላይ ሳይውል የቆየ ሲሆን ለዚህም ገና ባለመጽደቁ እንደሆነ በውይይት መድረኩ ላይ አቶ ዘርዓይ ተናግረዋል። ይህም የባለስልጣኑ ድክመት መሆኑን አቶ ዘርዓይን ጨምሮ በጥናቱም ተገልጿል።

ብሮድካስት ባለስልጣኑ ድክመት እንዳለበት በጥናት የተገለጸ ቢሆንም ለጥናቱ ግኝት ምን ያህል ራሱን አዘጋጅቷል ለሚለው ጥያቄ ግን የተሰጠ ምላሽ የለም። በደፈናው ድክመት አለብኝ እሻሻላለሁ በማለት ታልፏል።

አስተያየታቸውን ለሰንደቅ ጋዜጣ የሰጡት የሌላ ሚዲያ ተወካይ በበኩላቸው “ራሱ አዘጋጅቶ ራሱ በመራው የውይይት መድረክ ላይ ድክመት አለብኝ ብሎ መናገር ምን ይባላል? እንደምታየው መድረኩን ሙሉ በሙሉ የያዙት የባለስልጣኑ ኃላፊዎች ናቸው። ድክመት አለብኝ ሲባል ማን ባጠናው የጥናት ግኝት ለጥናት ግኝቱ የሚሰጥ ምላሽስ ምንድ ነው? የሚሉትን መልስ መስጠት ያልቻለ እና ምንም ሳልለ እንዳልቀር ተብሎ የቀረበ ነው የሚመስለው” ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።

 

 

ለምን ለምኒልክ ብቻ?

አቶ ግዛው ተስፋዬ የግል መገናኛ ብዙሃን ድክመት ነው ብለው ያቀረቡት አንዱ ነጥብ “የታሪካችንን ድሎች በተዛባ መልኩ ማቅረብ ነው” ያሉ ሲሆን ለአብነት ያህልም “በቅርቡ ባከበርነው አገራዊ ድል ላይ የድሉ ባለቤት ህዝቡ ሆኖ ሳለ የድሉ ባለቤት ነገሰታቱ እንደሆኑ ተደርጎ ነበር ይቀርብ የነበረው” ሲሉ አቅርበዋል።

በቅርቡ ያከበርነው አገራዊ የድል በዓል “የአድዋ ድል” መሆኑ ይታወቃል። የአድዋ ጦርነት በተነሳበት ወቅት አገሪቱን የመሩ የነበሩት ዳግማዊ አጼ ምንሊክ ሲሆኑ ከአድዋ ድል ጋር በተያያዘ የእሳቸው እና የባለቤታቸው እቴጌ ጣይቱ ስም ተደጋግሞ መነሳቱ አይቀርም። የብሮድካስት ባለስልጣን ግን ከግል ብሮድካስት መገናኛ ብዙሃን አገኘሁት ያለው ችግር “ድሉን ለንጉሱ ጠቅልሎ የመስጠት ችግር አለባችሁ” የሚል ነው። 

በዚህ ላይ አስተያየቱን የሰጠን በቅርቡ ስራ የሚጀምረው የአሃዱ ኤፍ ኤም ስራ አስኪያጅ ጋዜጠኛ ጥበቡ በለጠ፣ “አንድ ጦርነት ሲነሳ መሪው አብሮ ይነሳል። ይህ የትም አገር ያለ እውነታ ነው። የአድዋን ጦርነት በተለይም ለአጼ ምንሊክ ለየት ያለ አክብሮት እንዲሰጣቸው የሚያደርገው ወደ ጦር ግንባር በዘመቱበት ወቅት የተናገሩትን ስንመለከት ነው” የሚለው ጋዜጠኛው “አገር የሚያጠፋ ሀይማኖት የሚለውጥ ጠላት እግዚያብሔር የወሰነልንን የባህር በር አልፎ መጥቷል .... ጉልበት ያለህ በጉልበትህ እርዳኝ ጉልበተ የሌለህ ደግሞ ለልጅህ ለሚስትህ ለሀይማኖትህ ስትል በሃዘን እርዳኝ። ወስልተህ የቀረህ ግን ኋላ ትጣላኛለህ አልተውህም። ማሪያምነ ለዚህ አማላጅ የለኝም። ዘመቻዬ በጥቅምት ነውና የሸዋ ሰው እስከ ጥቅምት እኩሌታ ወረኢሉ ከተህ ላግኝህ” ሲሉ ነበር የአገር አድን ጥሪ ያቀረቡት። በዚህ ጥሪያቸው ላይ የምንመለከተው አንደኛ እንደሚያሸንፉ አምነዋል። በሌላ በኩል ደግሞ በትግሉ ራሳቸውና ባለቤታቸው ተሳታፊ ሲሆኑ ልጆቻቸውም አልቀሩም ነበር።  ታዲያ በዚህ ላይ የእሳቸውን ስም እያነሱና እያወደሱ ድሉን መዘከሩ ምን ላይ ነው ጥፋቱ?” ሲል ተናግሯል።¾

ይምረጡ
(1 ሰው መርጠዋል)
431 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 124 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us