በቱርክ የተደረገው ሕዝበ ውሳኔ፤ ሕዝቡን ለሁለት ከፍሎታል

Wednesday, 19 April 2017 12:49

 

·         የአውሮፓ ሕብረት ታዛቢዎች ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ አልነበረም ብለዋል

·         ተቃዋሚ ፓርቲዎች ውጤቱን አልተቀበሉትም፤ ዳግም ቆጠራ ጠይቀዋል

·         ሬሲፕ ጣይብ ኤርዶጋን አሸናፊ መሆናቸውን አውጀዋል

 

ከ167ሺ በላይ የድምጽ መስጫ ቦታዎች ተዘጋጅተው ቀርበዋል። 55 ሚሊዮን ቱርካዊያን ድምፃቸውን ሰጥተዋል። ለሕዝበ ውሳኔ የቀረበው ፓርላሜንታዊ ሥርዓተ መንግስት ይቀጥል? ወይንስ ፕሬዝዳንታዊ ሥርዓተ መንግስት ይሁን? የሚሉ ሁለት አማራጮች ናቸው። በሕዝበ ውሳኔው ከሕገ መንግስቱ ክፍሎች በ18 አንቀፆች ላይ የሕዝብ ድምፅ ተሰጥቶባቸዋል። በተገኘው ውጤት መሰረት 51 በመቶ የጣይብ ኤርዶዋን ደጋፊዎች ማሸነፋቸውን ይፋ አድርገዋል።

ሬሲፕ ጣይብ ኤርደዋን ከሕዝበ ውሳኔው በፊት ስልሳ በመቶ የመራጩን ድምጽ እንደሚያገኙ ተስፋ አድርገው የነበረ ቢሆንም፣ በተሰጠው ውጤት 51 ለ49 በመቶ መጠናቀቁ ሕዝቡ ለሁለት የተከፈለ መሆኑ ማሳያ ተደርጎ እየተነገረ ነው። ከዚህም በላይ፣ ምርጫው ዓለም አቀፍ ደረጃውን አልጠበቀም ሲሉ የታዛቢዎች ቡድን ይፋ አድርገዋል። እንዲሁም በምርጫ ወቅት የሦስት ሰዎች ሕይወት መጥፋቱ በዴምክራሲያዊ የምርጫ ሒደት ላይ ያልተለመደ በመሆኑ፣ የምርጫው ውጤት ተጭበርብሯል የሚለው ሚዛን እያነሳ ይገኛል።

ከዚህም በላይ የቱርክ ሊሂቃን እና የንግዱ ማሕበረሰብ በብዛት የሚገኝባቸው ኢስታንቡል፣ አንካራ እና ኢዝሚር ከተሞች ለጣይብ ኤርዶዋን የሥርዓት ለውጥ ጥያቄ፣ አይሆንም የሚል ሙሉ ለሙሉ ምላሽ ሰጥተዋል። በእነዚህ ሦስት ትልልቅ ከተሞች ውስጥ ኤርዶዋንን የደገፈው የለም። ከዚህ በፊት የነበራቸውንም ማሕበራዊ መሰረት በግልፅ መናዱን የሚያሳይ ውጤትም ነው። ሕዝቡም ከፍርሃት ቆፈን ውስጥ ወጥቶ ቀደምት የነበረውን የተቃውሞ ባህሉን ሳይለቅ፣ መጥበሻ እና ማሰሮ ይዞ በግልጽ በአደባባይ እየደለቀ ተቃውሞውን አሰምቷል። አደባባዮች በፕሬዝደንቱ ደጋፊዎች እና ተቃዋሚዎች ተጥለቅልቆም ነበር። አሁንም እንደቀጠለ ነው።

ፕሬዝደንት ኤርዶዋን ግን በአንካራ ከተማ የመጨረሻ ገዳብ ዳርቻ ላይ በከፍታ ቦታ በ615 ሚሊዮን ዶላር ባስገነቡት 1ሺ ክፍሎች ባለው ፕሬዝደንታዊ ፓላስ ውስጥ ተቀምጠው፣ እ.ኤ.አ. 2029 ድረስ ቱርክን ለመግዛት የቆረጡ መስለዋል። ከሕዝበ ውሳኔው ውጤት በኋላ በሰጡት አስተያየት፣ ተቃዋሚ ኃይሎች ውጤቱን እንዲቀበሉ አሳስበዋል። በቀጣይም ችግር እንደማይገጥመኝ ተስፋ አደርጋለሁ ብለዋል። ተቃዋሚዎች በበኩላቸው ውጤቱ በድጋሚ እንዲቆጠር እየወተወቱ ናቸው። ውጤቱን የማይቀበሉ ከሆነ፣ ጣይብ ኤርዶዋን ምን አይነት እርምጃ ሊወስዱ እንደሚችሉ? ወደፊት የምናየው ነው የሚሆነው። 

በዚህ ጽሁፍ ሕዝበ ውሳኔ የተሰጠባቸው ፍሬ ነገሮች፤ የቱርክ የመንግስት ስርዓት ለውጥና ክርክሮች መቼ ተጀመሩ? የቱርክ ሕገመንግስት ሕዝበ ውሳኔ ሲሰጥበት እና ፖለቲካ ፓርቲዎች ማሻሻያ ያቀረቡባቸው ጉዳዮች የሚያሳይ ከ1808 እስከ 2016 ድረስ ቀርበዋል። በዚህ መልኩም ተዘጋጅቷል።

 

***    ***    ***

 

በዘመናዊ የቱርክ ፖለቲካ፣ ወሳኝ የተባለ የፖለቲካ ሥርዓት ለውጥ በሕዝበ ውሳኔ መሰጠቱ ተነግሯል። በገዢው ፓርቲ የሕገ መንግስት ማሻሻያ ጥያቄ መነሻ አስራ ስምንት አንቀፆች ላይ እሁድ ዕለት ሕዝቡ ሕዘበ-ውሳኔ አድርጓል። ለሕዝበ ውሳኔ የቀረበው ሕገ መንግስት እ.ኤ.አ. በ1980 ከተደረገው መፈንቅለ መንግስት በኋላ የተረቀቀ መሆኑ ተነግሯል።

ቱርክ ከፓርላመንታዊ የመንግስት ስርዓት ወደ ፕሬዝደንታዊ የመንግስት ሥርዓት ለመሸጋገር ያስችላል ለተባለው የፖለቲካ ሥርዓት ድምጽ ለመስጠት 55 ሚሊዮን ቱርካዊያን ተሳትፈዋል። እንደሚታወቀው የፕሬዝደንት የፖለቲካ ሚና በአስፈፃሚነት ደረጃ የተቀየረው እ.ኤ.አ. 2014 ነበር። ይኸውም ለመጀመሪያ ጊዜ በቀጥታ በሕዝብ ድምጽ የተመረጡ ፕሬዝደንት ስልጣን ሊጨብጡ ነበር። በኦገሰት 10 ቀን 2014 ለመጀመሪያ ጊዜ በቀጥታ በሕዝብ በተሰጠ ድምጽ ከመራጩ 51 ነጥብ 79 በመቶ በማግኘት የተመረጡት ሬሲፕ ጣይብ ኦርዶዋን ናቸው። ይህንን ምርጫ ተከትሎ በፓርላማው እና በፕሬዝደንቱ መካከል የስልጣን መሻኮት ማስከተሉን ይነገራል። አሁን ላይ በሕገ መንግስቱ አንቀፆች ላይ ሕዝበ ውሳኔ እንዲሰጥ የጠየቁት የፖለቲካ ኃይሎች፣ ለፕሬዝደንቱ የአስፈፃሚነት ስልጣን ቢጨመርላቸው ከፓርላማው ጋር ያለውን ፖለቲካዊ ውጥረት ይቀንሳል ባይ ናቸው። የዚህን ሃሳብ የሚሞግቱ ኃይሎች በበኩላቸው፣ ለፕሬዝደንቱ የአስፈፃሚነት ሚና እንዲኖረው ማድረግ ሀገሪቷን ወደ አንድ ግለሰብ አገዛዝ ይቀይራታል ሲሉ ስጋታቸውን አስቀምጠዋል።

ለሕዝበ ውሳኔ የቀረበው ሕገ መንግስት በ18 አንቀፆች ላይ መሰረታዊ ለውጦችን የሚጠይቅ ነው። ይኸውም፣ የጠቅላይ ሚኒስትሩን ስልጣን ሙሉ ለሙሉ ይሽራል፤ የፓርላማ የመቀመጫ ወንበር ከ550 ወደ 600 ከፍ ይላል፤ የፓርላማ ተመራጮች እና የፕሬዝደንት ምርጫ በየአምስት አመቱ በተመሳሳይ ሁኔታ ይደረጋል፤ ፕሬዝደንቱ ሚኒስትሮችን፣ ከፍተኛ የመንግስት አስፈጻሚ አካሎችን እና ምክትል ፕሬዝደንትን እንዲሾሙ ስልጣን ይሰጣቸዋል፤ አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ፕሬዝደንቱ ያወጃሉ፤ ቀርበው በፓርላማ ያጸድቃሉ፤ ፕሬዝደንቱ ከፖለቲካ ፓርቲው ራሱን እንዲያርቅ አይገድም፤ ለዳኞችና ለአቃቤ ሕግ ቦርድ ከሚሰየሙት አባላት መካከል ሰባቱ በፓርላማው የሚሰየሙ ሲሆን፣ አራቱ በቀጥታ በፕሬዝደንቱ ይሰየማሉ፤  ለፓርላማ ተመራጭነት 25 ዓመት ዕድሜ በዝቅተኛ ጣሪያ የነበረውን ወደ 18 ዝቅ ይላል፤ የሕግ አውጪው የተለየ መብት ጥቅም ባለበት ይቀጥላል፤ ፕሬዝደንቱን ለመመርመር ከፓርላማው የ360 መቀመጫ ድጋፍ ያስፈልጋል፤ ፕሬዝደንቱ እና ፓርላማው ዳግም ምርጫ መጠየቅ ይችላሉ፤ ፕሬዝደንቱ የሚያወጣውን ዓመታዊ በጀት በፓርላማው እንዲያጸድቅ ግዴታ ይጥላል፤ ወታደራዊ ፍርድ ቤት ለወታደራዊ ሥነሥርዓት ጥፋቶች ብቻ ይውላል፤ የፍርድ ቤት ሥርዓቱ ነፃ ብቻ ሳይሆን ገለልተኛ እንዲሆን ይጠይቃል።

በቱርክ ፖለቲካ ውስጥ ፕሬዝደንታዊ የመንግስት ሥርዓት እንዲዘረጋ ጥያቄ ሲቀርብ፣ ክርክር ሲደረግ፣ የመጀመሪያው አይደለም፤ ከ1970ዎቹ ጀምሮ እንደነበር ማጣቀሻዎች ያሳያሉ። በ1970ዎቹ ናሽናል ኦርደር ፓርቲ እና ናሽናል ሳሊቬሽን ፓርቲ በጋራ የመንግስት ያልተሟላ ቢሮክራሲን ውጤታማ ለማድረግ ፕሬዝደንታዊ የመንግስት ሥርዓት አስፈላጊ መሆኑ ሃሳብ አቅርበው ተከራክረዋል። በ1979 የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መሪ የነበሩት አልፓረስላን፣ ፕሬዝደንታዊ ሥርዓት ጠንካራና ፈጣን ማስተካከያዎች ለማምጣት አስፈላጊ መሆኑ አምነው ተከራክረዋል። 1980ዎች ከ1983 እስከ 1989 ድረስ ጠቅላይ ሚኒስትር የነበሩት ኦዛል፣ ፓርላሜንታዊ ሥርዓት ተቋማዊ ለውጦች ላይ አዝጋሚ ነው ከሚል መነሻ ይከራከሩ ነበር። 1990ዎቹ ከ1964 እስከ 1993 ድረስ ሰባት ጊዜ ጠቅላይ ሚኒስትር የነበሩት ሱሌይማን፤ ፕሬዝደንታዊ ሥርዓት ለፖለቲካ መረጋጋት፣ ሥርዓት መንግስቱን ለማስተዳደር እና ዴሞክራሲን ለማጠናከር አስፈላጊ ነው ሲሉ መከራከራቸው ማጣቀሻዎች ያሳያሉ።

እንዲሁም የቱርክ ሕገ መንግስታዊ የለውጥ ዳራዎች እንደሚያሳዩት፣ ለበርካታ ጊዜ በተለያዩ ሥርዓተ-መንግስታት ማሻሻያ አቅራቢነት የለውጥ ሒደቶችን ማስተናገዳቸውን ያሳያሉ። እ.ኤ.አ. ከ1808 እስከ 2015 ድረስ በሕገ መንግስታቸው ላይ የተለያዩ ለውጦች አድርገዋል። እንዲሁም መፈንቅለ መንግስት በራሱ የቱርክ የፖለቲካ መገለጫ ተደርጎም የሚወሰድ ነው። ከዚህ በታች በቱርክ ሕገ-መንግስት ላይ መሰረታዊ ለውጦች ተብለው የተጠቀሱትን አቅርበነዋል።

 

1808

ሕገ መንግስታዊ ኅብረት ስምምነት ተደርጓል። ማዕከላዊ መንግስቱን የሚያስተዳድረው የኦቶማን መንግስት እና የአካባቢ አስተዳደሮች፣ በሱልጣን የሚመሩ ግዛቶችን ላይ ስልጣን የሚገድብ ስምምነት አድርገዋል።

1876

የኦቶማን ሕገ መንግስት ሥራ ላይ ውሏል። ይህ ቱርክ ሕገ መንግስታዊ ሥርዓት ለመጀመሪያ ጊዜ ሥራ ላይ ያዋለችበት ጊዜ ነው።

1909

ሕገ መንግስታዊ ክለሳ አድርገዋል

1921

የመጀመሪያ የቱርክ ሪፐብሊክ ሕገ መንግስት ሥራ ላይ ውሏል

1924

አዲስ ሕገመንግስት ተብሎ የቀረበው ከበፊቱ ያነሰ ዴሞክራሲያዊ እሴቶች ነበሩት። የስልጣን ክፍፍል የለውም፤ አስፈጻሚውና ሕግ ተርጓሚው አካል በፓርላማው ቁጥጥር ስር ናቸው፤ የመድብለ ፓርቲ ስርዓት የለም።

1934

የሕዝቡ የመምረጥ መብት ተጠበቀ

1937

የሪፐብሊክ ፒፐል ፓርቲ መርሆችን በማሻሻያ ሥርዓት፣ በሕገ መንግስቱ እንዲካተቱ ተደርገዋል።

1960

ግንቦት 27 መፈንቅለ መንግስት ተደረገ።

1961

አዲስ ሕገ መንግስት ሥራ ላይ ዋለ። አስፈጻሚው እና ሕግ አውጪ የተለዩበት የመወሰኛ ምክር ቤት አሰራር ተዘረጋ። የአስፈጻሚ ስልጣን ለፕሬዝደንቱና ለሚኒስትሮች ምክር ቤት ተሰጠ። የዳኞች ስልጣን ለገለልተኛ ፍርድ ቤቶች ተተወ። የዳኞች እና የአቃቤ ሕግ ከፍተኛ ቦርድ ተመሰረተ። የሰበር ችሎት ተቋቋመ። የአሰሪና ሰራተኞች ሕብርት ስምምነቶች እና ሰላማዊ ሰልፎች እንዲያደርጉ ተፈቀ።

1971

ማርች 12 የመግባቢያ ሰነድ ተፈረመ።

1972

የሚኒስትሮች ምክር ቤት ድንጋጌዎችን እንዲያወጣ ስልጣን ተሰጠው። የሲቪል ሰራተኞች የመደረጃት መብት ተነፈገ። የዩኒቨርስቲዎች ራስን የማስተዳደር ስልጣን እንዲደክም ተደረገ። የመንግስት ደህንነት ፍርድ ቤቶች ተስፋፉ፣ የስልጣን ድንበራቸውም ተለየ።

1980

ሴፐቴምበር 12 መፈንቅለ መንግስት ተደረገ።

1982

አዲስ ሕገ መንግስት ተግባራዊ ሆነ። አስፈፃሚው አካል ስልጣን ጠቅሎ ወሰደ። ስልጣን ከሕዝቡ ወደ መንግስት ተወሰደ።

1987

የመራጮች እድሜ ወደ 19 ዓመት ዝቅ አለ። የፓርላማ መቀመጫ ከ400 ወደ 450 ከፍ ተደረገ። አንዳንድ የፖለቲካ መሪዎች ታገዱ።

1993

በቴሌቪዥ እና በሬዲዮ ማቋቋም ላይ የተጣለው እገዳ ረገብ አለ።

1995

ሲቪል ሰራተኞች የመደራጀት መብታቸው ተከበረ። የሕብርት ስምምነት እንዲፈጽሙ ተፈቀደ። የመራጮች እድሜ ወደ 18 ዓመት ዝቅ አለ። ፖለቲካ ፓርቲዎች የሴቶች እና የወጣቶች ክንፍ እንዳያደራጁ የሚከለክለው ድንጋጌ ተነሳ። የዩኒቨርስቲ መምህራን እና ተማሪዎች የፖለቲካ ፓርቲ አባል መሆን እንዲችሉ ተፈቀደ። የፓርላማ መቀመጫ ወንበር ወደ 550 ከፍ ተደረገ።

1997

መፈንቅለ መንግስት ተደረገ።

1999

የመንግስት ደህንነት ፍርድ ቤቶች ሃላፊዎች የነበሩት ወታደሮች በሲቪል ተተኩ። በመንግስት ይዞታ ሥር የነበሩ ድርጅቶች ወደ ግል ይዞታ እንዲዘዋወሩ ተፈቀደ።

2001

የአውሮፓ የሰብዓዊ መብቶች ፍርድ ቤት አሰራር ተቀባይነት ተሰጠው። የኮሚኒኬሽን ነፃነት ተፈቀደ። መልክት የመለዋወጥ መብት ተሰጠ። የፆታ እኩልነት መብት ተጠናከረ። ፖለቲካ ፓርቲዎችን ማገድ አስቸጋሪ ሆነ።

2005

በሬዲዮና በቴሌቪዥን ከፍተኛ ካውንስል ላይ መዋቅራዊ ለውጥ ተደረገ።

2006

ለፓርላማ ተመራጭነት ከ30 ወደ 25 ዓመት ዝቅ ተደረገ።

2007

የምርጫ የመግባቢያ ሰነድ ጸደቀ። ምርጫ በየአምስት አመቱ መሆኑ ቀርቶ በአራት አመት እንዲሆን ተወሰነ፤ ፕሬዝደንቱ በቀጥታ በሕዝብ ተሳትፎ እንዲመረጡ ተወሰነ፤ ፕሬዝደንታዊ ምርጫ በሰባት ዓመት መሆኑ ቀርቶ፣ በአምስት አመት አንዴ እንዲሆን ተወሰነ።

2010

ሕዝበ ውሳኔ ተሰጠ። በዳኞች እና በፍርድ ቤቶች ላይ መዋቅራዊ ለውጥ ተደረገ።

2014

በሕዝብ በቀጥታ በተደረገ ምርጫ የመጀመሪያው አሸናፊ ፕሬዝደንት በመሆን ራይብ ጣይብ ኤርዶዋን ተመረጡ።

2016

ጁላይ 15 የመፈንቅለ መንግስት ሙከራ መደረጉ ተነገረ።

2017

አፕሪል 16 ቀን 2017 በአስራ ስምንት አንቀፆች ላይ ሕዝበ ውሳኔ ተሰጠ።¾

  

ይምረጡ
(1 ሰው መርጠዋል)
397 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 949 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us