ኢትዮጵያ 150ኛ ደረጃ ላይ ሆና የዓለም የፕሬስ ቀንን ዛሬ ታከብራለች

Wednesday, 03 May 2017 12:36

 

በይርጋ አበበ

ዓለም አቀፉ የፕሬስ ቀን ዛሬ ይከበራል። በዓሉ ከመከበሩ በፊትም ያለፈውን ዓመት የአገራትን የፕሬስ ነጻነት የተመለከተ ዳሰሳ እና የአገራትን ደረጃ ይፋ ያደረገው ሪፖርት ወጥቷል። እንዳለፉት ዓመታት ሁሉ ዘንድሮም የስካንዲኒቪያን አገሮች (ኖርዌይ፣ ስዊድን፣ ፊንላንድና ዴንማርክ) ከአንደኛ እስከ አራተኛ ያለውን ደረጃ ሲቆጣጠሩ ምስራቅ አፍሪካዊያኑ ኤርትራ ጂቡቲና ሱዳን ከሩቅ ምስራቆቹ ሰሜን ኮሪያ፣ ቻይና እና ቬትናም እንዲሁም ከምስራቅ አውሮፓዋ ሀያል ሩሲያ ጋር በመጨረሻዎቹ ደረጃዎች ላይ ተካተዋል። ኢትዮጵያ ደግሞ ባለፈው ዓመት ከነበረችበት 149ኛ ደረጃ አንድ ቀንሳ 150ኛ ላይ ተቀምጣለች። የፕሬስ ቀንን አስመልክቶም ከዓለም አቀፍ ሪፖርቶችና ከተለያዩ ባለሙያዎች ያሰባሰብነውን መረጃ ከዚህ በታች አቅርበነዋል።

 

 

ኢትዮጵያ እና ፕሬስ በ2016

በአሁኑ ወቅት የኢትዮጵያ ህዝብ ወደ 100 ሚሊዮን ይደርሳል ተብሎ ይገመታል። ይህም ማለት ኢትዮጵያን ከናይጄሪያ ቀጥሎ በአፍሪካ በሕዝብ ቁጥር ሁለተኛ ያደርጋታል ማለት ነው። በአገሪቱ መንግስት የፌዴራል የስራ ቋንቋ ለንባብ የሚበቁ የግል ጋዜጦች ቁጥር ሶስት (ሰንደቅ፣ ሪፖርተር እና አዲስ አድማስ) ብቻ ሲሆኑ በእንግሊዝኛ ቋንቋ የሚታተሙ ደግሞ አራት (ሪፖርተር፣ ካፒታል፣ ፎርቹንና ዴይሊ ሞኒተር) ናቸው። የኤሌክትሮኒክስ መገናኛ ብዙሃን ደግሞ ሁሉም በሚያስብል መልኩ የግል ራዲዮ ጣቢያዎቹ መገኛቸው አዲስ አበባ ሲሆን አብዛኞቹ ትኩረታቸው መዝናኛ እና ስፖርት ላይ ብቻ ያተኮረ ነው ሲል የብሮድካስት ባለስልጣን በቅርቡ ይፋ ባደረገው ጥናት አስታውቆ ነበር። በቅርቡ የሚቀላቀሉትን አሃዱ እና ሉሲ ራዲዮኖችን ጨምሮ እስካሁን በስራ ላይ ያሉት የግል ራዲዮ ጣቢያዎች ሸገር፣ ዛሚ እና ፋና ራዲዮም ይገኛል። 

በቴሌቪዥን በኩል ደግሞ አሃዙ ከዚህ ያነሰ መሆኑን መረጃዎች ያመለክታሉ። በመጽሔት በኩል አገሪቱ ውስጥ ምን ያህል እንደሆኑ ከብሮድካስት ባለስልጣን መረጃውን ለማግኘት ያደረግነው ሙከራ ባይሳካም ከአስር የማይበልጡ መሆናቸውን አስተያየት ሰጪዎች ተናግረዋል።

በኢትዮጵያ ስላለው የፕሬስ ደረጃ መንግስት ምን ይላል? ለሚለው ጥያቄ መልስ የሰጡት በመንግስት ኮምዩኒኬሽን ጉዳዮች ጸ/ቤት የሚዲያ ዳይሬክተሩ አቶ መሃመድ ሰይድ “የህትመት ቁጥር አነሰ ለሚባለው ነገር በህግ የተቀመጠ ገደብ የለም። ሆኖም ሚዲያዎች የውስጥ አቅማቸውን እንዲያጎለብቱ በመንግስት በኩል ሊሰሩ የሚገባቸው ነገሮች እንዳሉ ተገንዝበናል” ሲሉ ለሰንደቅ ጋዜጣ ተናግረዋል። ነገ በሚከበረው የፕሬስ ቀን ላይም ከአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የጋዜጠኝነት ትምህርት ቤት አስተማሪዎች በአገሪቱ ውስጥ ያለውን ተስፋና ፈተናዎች የሚዳስሱ የጥናት ውጤቶች እንደሚያቀርቡ አቶ መሃመድ ጨምረው ተናግረዋል። በውይይት መድረኩም የግልና የመንግስት መገናኛ ብዙሃን አባላት ተሳታፊ እንዲሆኑ ጥሪ ተደርጎላቸዋል ብለዋል።

 

 

የጋዜጠኞች ፍልሰትና እስር በኢትዮጵያ

አቶ መሃመድ ሰይድ ከሰንደቅ ጋዜጣ ጋር ባካሄዱት የስልክ ቃለ ምልልስ “እንደ ፍሪደም ሃውስ ያሉ ዓለም አቀፍ ተቋማቱ የሚያወጧቸው መረጃዎች በሀገራችን ካለው እውነታ ጋር አይገናኝም” ሲሉ ተናግረዋል። በአገሪቱ ያለውን የፕሬስ ደረጃ ሲገልጹም “ቅድመ ምርመራ መቅረቱን እና ማንኛውም ሰው ሃሳቡን የማራማድ እንዲሁም የማስተላለፍ መብት በህገ መንግስት መሰረታዊ እውቅና የተሰጠው ነው። መሬት ላይ ያለው እውነታም ቢሆን የሚያሳየው በአገሪቱ ሃሳብን የመግለጽና የማስተላለፍ መብት ያልተገደበ መሆኑን ነው” ብለዋል።

ዓለም አቀፉ የጥናት ውጤት ደግሞ በአገሪቱ ያለው የጋዜጠኝነት አፈና ያልተቀረፈ መሆኑን ገልጾ ለዚህ ማስረጃነትም እንደ ዞን ዘጠኝ (ZONE NINE) መንግስት መክሰሱን፣ የተወሰኑትን ከጥፋተኝነት ነጻ ቢላቸውም የተቀሩትን ግን እስካሁንም በፍርድ ሂደት ላይ መሆናቸውን ያነሳል። በድንበር የለሽ የጋዜጠኞች ቡድን ዓመታዊ ሽልማት ለመቀበል ወደ ስፍራው የሚያቀኑ የዞን ዘጠኝ አባላትንም እንዳይሄዱ መታገዳቸውን የሚገልጸው የዓለም አቀፉ የጥናት ቡድን በእስር ላይ ካሉት ጋዜጠኞች መካከልም በሽብርተኝነት ወንጀል ተከሶ የ18 ዓመት እስር የተፈረደበት እስክንድር ነጋ ዓመታዊ ሽልማት የተበረከተለት መሆኑንም ያነሳል። ጥናቱ የእስክንድርን ሽልማት ሲገልጽም ለዴሞክራሲና ነጻነት ሲባል ዋጋ እየከፈሉ ያሉ ጋዜጠኞች ሽልማት መሆኑን ነው የገለጸው።

በሌላ በኩል ደግሞ በ2016 ብቻ ወደ 20 የሚጠጉ ጋዜጠኞች በተለያዩ መንገድ ከአገር ወጥተው መጥፋታቸው ታውቋል። ከእነዚህም መካከል አብዛኞቹ የስፖርት ጋዜጠኞች ሲሆኑ ለዘገባ ሂደው ያልተመለሱ ናቸው። አንዳንዶቹን በስልክም ሆነ በማንኛውም የዘመኑ መገናኛ ዘዴ አግኝተን ለማናገር ያደረግነው ጥረት አልተሳካም፡፡ እንዲገለጽ ያልፈለጉ የተወሰኑ ጋዜጠኞች ግን በአገሪቱ ያለውን ፖለቲካዊ አለመረጋጋትና አፈናን ለመሸሽ የስፖርት ጋዜጠኝነትን መርጠው ሲሰሩ መቆየታቸውን ተናግረዋል። ወደ ውጭ አገር ለመሄድ ሲያስቡም ላለመመለስ ቀድመው እንዳሰቡበት ነው የተናገሩት። ከዚህ አስተያየተ ጋር የሚስማማ አሰተያየት የሚሰጡት ደግሞ “በአገሪቱ አብዛኛው ሰው ከመንግስት ጋር በፖለቲካ ዘገባ ምክንያት እንካ ስላንትያ ላለመግጠም ሲል በመዝናኛ እና በስፖርት ዘገባዎች ላይ ብቻ ያተኩራል” ሲሉ አቶ ሰውነት የተባሉ የአዲስ አበባ ነዋሪ ለሰንደቅ ጋዜጣ ተናግረዋል። አቶ ሰውነት አከለውም “ያም ሆኖ የስፖርት ጋዜጠኞች እንኳን ሳይቀሩ አገሪቱን ለቀው የሚሰደዱባት አገር ሆናለች” ሲሉ የችግሩን ጥልቀት ተናግረዋል።

በመንግስት ኮምዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት የሚዲያ ዳይሬክተሩ አቶ መሃመድ ሰይድ ግን በዚህ አይስማሙም። አቶ መሃመድ ሃሳባቸውን ሲያቀርቡም በአገሪቱ ያለው ሁኔታ ሙሉ በሙሉ ምቹ እና አስተማማኝ ባይሆንም የተባለውን ያህል የከፋ ሁኔታ እንደለሌ ተናግረዋል። በአገር ውስጥ ያሉት መገናኛ ብዙሃንም እስካሁን ያላቸው እንቅስቃሴ መልካም የሚባል አይነት እንደሆነ የገለጹት አቶ መሃመድ “ከውጭ በሳተላይት የሚለቀቁ መገናኛ ብዙሃን ግን አፍራሽ፣ ግጭትን ፈጣሪ እና ሁከት ቀስቃሽ ናቸው” ብለዋል።

 

 

የመንግስት ክፍተቶች

በሰብአዊ መብት አያያዝና በመገናኛ ብዙሃን ነጻነት ዙሪያ ከዓለም አቀፍ ተቋማት ጋር ተስማምቶ የማያውቀው የኢትዮጵያ መንግስት ሰሞኑን የወጣውንና የፕሬስን ነጻነት የሚያመለክተውን ሪፖርትም የወደደው አይመስልም። አቶ መሃመድም በጥናቱ ላይ የመንግስት አቋምን ሲያንፀባርቁ፤ ሲናገሩ “ጥናት አቅራቢዎቹ ያለ በቂ መረጃ ነው ጥናቱን ሰራን የሚሉት” በማለት ተናግረዋል። ‘በእርግጥ’ ይላሉ አቶ መሃመድ “መንግስት የመረጃ ምንጭ በመሆኑና የግል መገናኛ ብዙሃኑን በመረጃ አሰጣጥ ላይ በስፋት የሚያሳትፍ አሰራርን በተመለከተ ድክመት እንዳለብን ተመልክተናል። በመሆኑም በቀጣይ መንግስት ትኩረት ሰጥቶ የሚሰራው የመንግስትን መረጃ ለሁሉም መገናኛ ብዙሃን በበቂ ሁኔታ ማዳረስ ይሆናል” በማለት ገልጸዋል።

ከሁለት ሳምንት በፊት የብሮድካስት ባለስልጣን ባዘጋጀው የውይይት መድረክ ላይ በአገሪቱ ውስጥ የሚገኙ የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች የስነ ምግባርና የእውቀት ክፍተት አለባቸው ሲል ገልጾ ነበር። የብሮድካሰት ባለስልጣኑን ሃሳብ የሚጋሩት አቶ መሃመድም “በሁሉም የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የጋዜጠኝነትና የኮምዩኒኬሽን ትምህርት በስፋት እንዲሰጥ ሁኔታዎች ተመቻችተዋል። በመሆኑም በሙያውና በስነ ምግባሩ ብቁ የሆነ ባለሙያ ማፍራት ያስችለናል” በማለት ለችግሩ የተዘየደውን መፍትሔ ገልጸዋል።

እስካሁን ባለው የመንግስት አሰራር በኩል ለግል መገናኛ ብዙሃኑ መጠናከር ምን የሰራችሁት ስራ አለ? ተብለው ከሰንደቅ ጋዜጣ የተጠየቁት አቶ መሃመድ ሲመልሱ “የመንግስት መረጃዎችን ከጠቅላይ ሚኒስትሩ መግለጫ ጀምሮ እስከ ሳምንታዊው የመንግስትን አቋም የሚተነትነው የጽ/ቤታችን መግለጫ ድረስ ሁሉም የመገናኛ ብዙሃን ተቋማት እንዲያገኙ እናደርጋለን። በሁሉም የአገሪቱ ክፍሎች ተንቀሳቅሰው እንዲዘግቡ ጥበቃና ከለላ እንሰጣለን። ነገር ግን ይህን ስናደርግ በበቂ መጠን ነው እያልኩ አይደለም። ብዙ ልንሰራቸው የሚገባን ነገሮች አሉ” ብለዋል።

ዓለም አቀፉ የፕሬስ ተሟጋች ድርጅት በበኩሉ ከአቶ መሃመድ በተለየ መልኩ ነው የኢትዮጵያን መንግስት የፕሬስ አያያዝ የሚገልጸው። “ቀይዋን መስመር እስካላለፋችሁ ድረስ የፈለጋችሁትን ያህል ዝለሉ ይላል” የሚለው የተቋሙ ሪፖርት በአገሪቱ ውስጥ ከሚንቀሳቀሱ የግል የፕሬስ ውጤቶች መካከል የመንግስትን ድክመት በስፋት የሚገልጽ እንደሌለ ይህም የሆነበት ምክንያት የመንግስት አፋኝነት እንደሆነ ገልጿል።

 

 

የፕሬስ እስር ቤቶች

የዓለም አቀፉ የፕሬስ ተሟጋች ድርጅት ይፋ ባደረገው የዚህ ዓመት የአገራት ደረጃ የጋዜጠኞች “የምድር ገነት” ተብላ ኖርዌይ በቀዳሚነት የተገለጸች ሲሆን የኢሳያስ አፈወርቂ የግል ንብረት የሆነችው ኤርትራ ደግሞ “የምድር ሲዖል” ሆና ተመርጣለች። ለተወሰኑ የዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃን ተቋማት ብቻ በሩን ገርበብ አድርጎ የሚከፈተው የኤርትራ መንግስት ከሌላው አምሳያው የሰሜን ኮሪያው ኪም ጁንግ ኡን በአንድ ደረጃ ብቻ ነው ያነሰው። ድሮውንም በሰብአዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች አያያዝ ተስማሚ አይደለችም ተብላ በምዕራባዊያን የምትነቀፈው ቻይና ዘንድሮም በርካታ ጋዜጠኞችን በማሰርና በማሳደድ ተወንጅላለች። የመጨረሻዎቹን ደረጃም ለመያዝ ተገድዳለች።

በእርስር በእርስ ጦርነትና እና አሜሪካና ሶሪያ የበላይነት ለማሳየት የጦር አውድማ ያደረጓት ሶሪያ ጋዜጠኞች ከሚማረሩባቸው አገራት አንዷ ናት ያለው ሪፖርቱ የእኛ ጎረቤት ደቡብ ሱዳን ደግሞ በየጊዜው ደረጃዋ እያሽቆለቆለ ይገኛል ሲል ይፋ አድርጓል። የቪላድሚር ፑቲን አገር ሩሲያም ጋዜጠኞችን የምታሰቃይ አገር እንደሆነች ተገልጿል።

ካለፉት ዓመታት የተቋሙ ሪፖርት በተለየ መልኩ ለጋዜጠኞች የከፋች አገር ሆና የቀረበችው የጣሂር ኤርዶዋን አገር ቱርክ ነች። ከነሃሴው መፈንቅለ መንግስት በኋላ ያልተረጋጋው የኤርዶዋን መንግስት ጋዜጠኞችን በማሳደድ፣ በመወንጀልና በማፈን ተግባሩ የከፋ ሆኖ ተገኝቷል። ምንም እንኳ በጥናቱ ባይካተትም የዶናልድ ትራምፕ መንግስት ለአሜሪካ ጋዜጠኞች የማይመች ነው ያለው ሪፖርቱ በተለይ ፕሬዝዳንት ትራምፕ መገናኛ ብዙሃንን በአደባባይ በመዝለፍ ጋዜጠኞች ስራቸውን ተረጋግተው እንዳይሰሩ አድርገዋል ብሏል።¾

ይምረጡ
(1 ሰው መርጠዋል)
364 ጊዜ ተነበዋል

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us