ዛሬም የርሃብ ስጋት?

Wednesday, 10 May 2017 13:12

 

በይርጋ አበበ

በምስራቅ አፍሪካ የዜጎች ኑሮ አሁንም ከድጡ ወደ ማጡ እንጂ የመሻሻል ተስፋ የሚታይበት አልመሰለም። ከ25 ዓመታት በላይ መንግስት አልባ ሆና የቆየችው ሶማሊያ ባፈው ዓመት መሃመድ አብዱላሂ ፋርማጆን ፕሬዝዳንት አድርጋ ብትመርጥም አገሪቱ ግን አሁንም ከአልሻባብና ከርሃብ ስጋት ነጻ የመውጣት ተስፋ አልታየባትም። ደቡብ ሱዳን ለአራት አመታት ከዘለቀው የእርስ በእርስ ጦርነት ያልተላቀቀች በመሆኗ ዜጎቿ አሁንም በምግብ እጥረት እየተሰቃዩ መሆኑን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የዓለም ምግብ ፕሮግራም ሰሞኑን ይፋ ያደረገው መረጃ አስታውቋል። ጭር ሲል አልወድም የሚለው የኤርትራ መንግስትም ቢሆን ዜጎቹን ለስደትና ለቸነፈር በመዳረጉ የሚተች ሲሆን፤ ኬኒያም ከቀጠናው ስጋት ያጠላባቸው አገራት አንዷ መሆኗን በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የዓለም ምግብ ፕሮግራም መረጃ ያመለክታል።

ከላይ ከተጠቀሱት አገራት የበለጠ አኃዝ ያለው ህዝብ ደግሞ በኢትዮጵያ የአስቸኳይ ምግብ እርዳታ ፈላጊ መሆኑን የኢትዮጵያን መንግስት መግለጫ ዋቢ አድርጎ ዋሽንግተን ፖስት ጋዜጣ ባሳለፍነው ሳምንት አስነብቧል። የኢትዮጵያ መንግስት ‹‹5.6 ሚሊዮን ዜጎቼ የአስቸኳይ የምግብ እርዳታ ፈላጊ ናቸው›› ብሎ ባወጀ በአራተኛ ወሩ አኃዙ ላይ ከሁለት ሚሊዮን በላይ በመጨመር የተረጂዎችን ቁጥር ወደ 7.8 ገደማ አድርሶታል። ገና ከአራት ወራት በፊት በነበረው የመንግስት መግለጫ ለእርዳ ፈላጊ ዜጎች ከ948 ሚሊዮን ዶላር ያላነሰ ገንዘብ እንደሚያስፈልገው ገልጾ የነበረ ሲሆን ለጊዜው ከራሱ ካዝና አንድ ቢሊዮን ብር (47 ሚሊን ዶላር) ማጽደቁን ገልጾ ነበር። አሁን ደግሞ የተረጂዎች ቁጥር መጨመሩ ሲገለጽ የእርዳታ አቅራቢ ድርጅቶች የመመጽዎት አቅም ተዳክሞ የታየበት አጋጣሚ እንደሆነም ጋዜጣው ጨምሮ አስንብቧል። ከዚህ በባሰ መልኩ ደግሞ ድርቁ በተለይም በላይኛው ወይም ደጋማው የአገሪቱ ክፍል (አማራ ከፊል ኦሮሚያ እና ትግራይ ክልሎች) ድርቁ ተባብሶ ሊቀጥል መሆኑም ተዘግቧል።

ኢትዮጵያ በቀጣይም በድርቅ ምክንያት ተጎጂ እንደምትሆን የተነበየውን የዋሽንግተን ፖስትን ዘገባ እና በተላያዩ ጊዜያት በኢትዮጵያ መንግስት የተሰጡ ምላሾችን ከዚህ በታች ለአንባቢያን በሚመች መልኩ አቅርበነዋል።

 

 

ድርቅ፣ የርሃብ ስጋት እና ርሃብ

እ.እ.አ በ2015/16 የበልግ ወቅት በፓሲፊክ ውቅያኖስ በተፈጠረ ኤል- ኒኖ (የውቅያኖስ ታችኛው ክፍል መሞቅ) መከሰት ምክንያት በአገሪቱ የተወሰኑ አካባቢዎች ድርቅ መከሰቱ አይዘነጋም። በዚህ የተነሳም ከአስር ሚሊዮን የሚልቁ ዜጎች ለከፋ ጉስቁልና ተጋልጠው እንደነበረ የኢትዮጵያ መንግስት አስታውቆ ነበር። የድርቁን ከባድነትና የተጎጂዎችን ቁጥር የገለጸው የኢትዮጵያ መንግስት በራሱ አቅም እንደተቋቋመውም ተናገሯል። 400 ሚሊዮን ዶላር ከካዝናው አውጥቶ ለድርቅ ተጎጂዎች ድጋፍ በማድረግ መንግስታዊ ግዴታዊን የተወጣው የኢትዮጵያ መንግስት፤ በሌሎች የልማት ስራዎቹ ላይ ተጽእኖ ሳያሳርፍበት እንዳልቀረ አልደበቀም። ዓለም አቀፍ ረጅ ድርጅቶች ያደረጉለትን ድጋፍ በተመለከተም ‹‹ከተጠበቀው በታች›› ሲል ነበር የገለጸው።

ዋሽንግተን ፖስት በሚያዝያ 23 ቀን 2009 ዓ.ም ዘገባው ‹‹Ethiopia longe associated with a divastating famine in the 1980s, returned to the headlines last year when it was hit by sever drought in the highland region, affecting 10.2 million people. Food aid poured in, the government spent hundreds of millions of its money, and famine was averted›› በአማርኛ አቻ ትርጉም ‹‹ኢትዮጵያ በ1980ዎቹ ከርሃብ ጋር ጠንካራ ቁርኝት ነበራት። ባለፈው ዓመት ደጋው የአገሪቱ ክፍል በተከሰተው ከፍተኛ ድርቅ ምክንያትም ወደ 10.2 ሚሊዮን ህዝቧ በድርቅ ተጎጂ ሆኖ ነበር። መንግስትም ከካዝናው በመቶ ሚሊዮኖች የሚቆጠር ገንዘብ በማውጣት ለዜጎቹ በማከፋል ርሃቡ እንዲቀንስ አድርጓል›› ሲል የነበረውን ሁኔታ አስታውሷል።

የኢትዮጵያ አደጋና ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽነር አቶ ምትኩ ካሳ በበኩላቸው ‹‹በድርቅ ለተጎዱ ዜጎች መንግስት የቻለውን ሁሉ በማድረግ ከርሃብ መታደግ ችሏል። ሆኖም በአንዳንድ አካባቢዎች የመሰረተ ልማት እጥረትና የሰው ሀይል ችግር ነበረብን›› ሲሉ ተናግረዋል። በተለይም በአማራ እና ኦሮሚያ ክልሎች የነበሩት መንገዶች ከባድ ተሸከርካሪ የማይገባባቸው ከመሆናቸውም በላይ ጉዳት የደረሰባቸው አካባቢዎች ከዋናው መንገድ በጣም የራቁ ስለነበሩ በእርዳታ አቅርቦቱ ላይ አሉታዊ ሚና ተጫውተዋል ሲሉ ነበር ከወራት በፊት የገለጹት። ሰሞኑን ደግሞ የእርዳታ ፈላጊዎችን ቁጥር ሲገልጹ 7.7 ሚሊዮን እንደሆነ ተናግረዋል።

 

 

አባባሽ ሁኔታዎች

በአራት አገራት ብቻ 20 ሚሊዮን ዜጎች የርሃብ ስጋት ያጠላባቸው መሆኑን የገለጸው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰሞኑ ዘገባ ነው። እነዚህ አራት አገራትም ናይጄሪያ፣ ደቡብ ሱዳን፣ ሶማሊያ እና የመን ሲሆኑ አገራት በአሁኑ ወቅት በእር በእርስ ጦርነት እየታማሱ መሆኑንም አስታውቋል። ከእንዚህ አራት አገራት በባሰ መልኩ ግን 7.7 ሚሊዮን ዜጎች የርሃብ ስጋት ያጠላባት አገር ኢትዮጵያ ስትሆን ይህም የችግሩን ጥልቀት ያመለክታል ሲል ዘገባው ጠቁሟል። የችግሩ ጥልቀትስ ምን ያህል ነው ለሚለው ጥያቄ መልስ የሚሰጠው የዋሽግተን ፖስት ዘገባ ‹ችግሩን ከድጡ ወደ ማጡ የሚወስዱ ምክንያች›› ሲል አራት ነጥቦችን አስቀምቷል።

ዘገባው በቅድሚያ ያስቀመጠው ‹‹መንግስት እጅ አጥሮታል›› በማለት ነው። ጋዜጣው ምክያቱን ሲያስቀምጥም ‹‹During last year’s drought,  Ethiopia came up with more than 400 million dollar of its own money to fight off famine, but this year, it has been able to commit only 47 million dollar, probably because of an exhausted budget››  ባለፈው ዓመት በነበረው ድርቅ ኢትዮጵያ ከካዝናዋ ከ400 ሚሊዮን ዶላር በላይ በማውጣት ድርቅን መመከት ችላለች። በዚህ ዓመት ግን ከ47 ሚሊዮን ዶላር ያልበለጠ ነው የመደበችው። ይህ ደግሞ ያለፈው ዓመት ወጪ የመንግስትን በጀት አዳክሞት ሊሆን ይችላል›› በማለት ነው።

ጋዜጣው ቀጣይ የችግሩ አባባሽ ምክንያት ሲያስቀምጥ ደግሞ ድርቁ ተባብሶ የሚቀጥል መሆኑን በማንሳት ነው። በተለይም ደገኛው ክፍል በድርቅ የሚጎዳ ከሆነ ያ አካባቢ በርከት ያለ ቁጥር ያለው ህዝብ የሚኖርበት በመሆኑና አካባውም ሰብል አምራች በመሆኑ ‹‹መጋቢው ተመጽዋች›› ሊሆን እንደሚችል ነው የገለጸው። እንደዘገባው ከሆነ ከ50 እስከ 60 በመቶ ድርቁ የሚቀጥል በመሆኑ ችግሩ ሊከፋ እንደሚችል ካሳባቸው መንገዶች አንዱ መሆኑን ዋሽንግተን ፖስት አመልክቷል።

ሌላው በችግሩ ላይ ቤንዚን አቅራቢ ምክንያቶች አንዱ ደግሞ ቀድሞውንም የአገሪቱ ሸክም የሆኑት ሶማሊያ እና ደቡብ ሱዳን አሁንም ለኢትዮጵያ ሸክም እንደሆኑ የሚቀጥሉበት እድል ሰፊ መሆኑ ነው። የምስራቅ አፍሪካ ሁሉንም አገራት በር የሚያንኳኳው ድርቅ በኢትዮጵያ ላይ የራሱን ጥቁር ነጥብ ጥሎ ከማለፉም በላይ እንደ ሶማሊያ እና ደቡብ ሱዳን አይነት ዘርፈ ብዙ ችግር ያለባቸው አገራት በኢትዮጵያ ጥገኝነታቸው የሚቀጥልበት ሰፊ በመሆኑ በኢትዮጵያ ላይ የድርቁ ተጽእኖ የከፋ እንዲሆን ያደርገዋል ማለት ነው።

እንደ ዋሽግተን ፖስት ዘገባ አራተኛው ችግር ሆኖ የቀረበው የፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ አስተዳደር ለኢትዮጵያ ከሚያርገው የቆየ ድጋፍ ውስጥ የ100 ሚሊን ዶላር (2.4 ቢሊዮን ብር ገደማ) ተቀናሽ ማድረጉ የኢትዮጵያ መንግስት ለድርቁ የሚያደረገውን ድጋፍ አነስተኛ እንዲሆን ያደርገዋል ሲል ስጋቱን ያስቀምጣል። ጋዜጣው አያይዞም የተባሩት መንግስታት ድርጅት በኢትዮጵያ በደረሰው ድርቅ ምክንያት ጉዳት ከደረሰባቸው ክልሎች መካከል የሶማሌን ክልል ድጋፍ ሲያደርግ ቢቆይም በገጠመው ችግር ምክንያት 80 በመቶውን መቀነሱን ዘግቧል። በዚህ ከቀጠለም በመጪው ክረምት እርዳታው ሙሉ በሙሉ የሚቋረጥበት እድል ሰፊ መሆኑን ዘግቧል።

 

 

የመንግስት ምላሽ

የኢትዮጵያ መንግስት አገሪቷን በገጠማት ድርቅ ጉዳት የደረሰባቸውን ዜጎች የመታደግ ስራ እየሰራ መሆኑን አስታውቋል። ለዚህም ለእንስሳት መኖ ከማቅረቡም በዘለለ በራሱ ወጪ እህል በመግዛት ወደ አገር ወስጥ እያስገባ በማከፋፋል ላይ መሆኑን ይገልጻል። በተለይም ወደብ ላይ በሚደርስ መጨናነቅ እርዳታ ፈላጊው ህዝብ ጉዳቱ ሳይጠናበት አስፈላጊው ምግብ እንዲደርስ ሲባል ቅድሚያ ለእርዳታ እህልና ለማዳበሪያ ተሰጥቶ ወደ አገር ቤት እየገባ መሆኑን አቶ ምትኩ ካሳ ገልጸዋል።

ከአራት ወራት በፊት የእርዳታ ፈላጊው ቁጥር 5.2 እንደሆነ መንግስት ይፋ ባደረገበት ወቅት ለድጋፍ የሚስፈልገው ገንዘብ መጠን ከአንድ ቢሊዮን ዶላር በታች ነበር። ከዚህ ገንዘብ ውስጥ 715 ሚሊዮን ዶላሩ ከምግብና ለአስቸኳይ እርዳታ እንደሆነ ነበር የተገለጸው። በአሁኑ ወቅት የተረጂዎች ቁጥር መጨመሩን ተከትሎ እና ወደፊትም የሰብል አምራቹ የአገራችን ክፍል በድርቅ የሚጠቃ መሆኑ ከተገለጸ መንግስት የሚወስደም ምላሽ ምንድን ነው? የሚለው ጥያቄ ጊዜ ሳይሰጥ ሊመለስ የሚገባው ነጥብ ነው።

‹‹ባለፈው ዓመት በአገሪቱ ከተከሰተው ድርቅ በማገገም ላይ በነበረችበት ሰዓት ለተጨማሪ ድርቅ ተዳርጋለች›› ያለው የዋሽንግተን ፖስት ዘጋቢው፤ በተባበሩት መንግስታት የምግብ ድርጅት የኮሚኒኬሽን ዳይሬክተሯን ጠቅሶ ባሰራጫ ዘገባ፤ ዓለም ኢትዮጵያን እንዳይዘነጋት መልዕክቱን አስተላልፏል።¾

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
430 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 939 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us