የኤርትራ ፈተናዎችና መፃኢ ሥጋቶች

Wednesday, 17 May 2017 12:36

 

ኤርትራ እንደ ከኢትዮጵያ ተነጥላ እንደ ሀገር ከቆመች ሁለት አስርተ ዓመታት ተቆጠሩ። ሀገሪቱ በእነዚህ ዓመታት በብዙ ውጣ ውረድ ውስጥ አልፋለች። ከኢትዮጵያ ተነጥላ እንደ ሀገር በቆመች ማግስት የነበሩት ህልሞችና ውጥኖች ዛሬ እንደ ጉም ተነዋል። ዛሬ ኤርትራ ለኤርትራዊያን የምድር ላይ ሲኦል ሆናለች። ዜጎቿ በባህር፣በየብስና በአየር ጥለዋት እየኮበለሉ ነው። በነፃ አውጭነት አመራር ስኬታቸው በነፃነት ማግስት ከአምላክ በታች ፍፁም መሪ ተደርገው ይታዩ የነበሩት ፕሬዝዳንት ኢሳያስ በሰተመጨረሻ ሁሉንም ነገር እንዳይሆን እንዳይሆን አድርገውታል። በተለይ ከኢትዮጵያ ጋር የገቡበት የድንበር ይገባኛል ጦርነት፣ ኤርትራን በኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ለመገንባት የነበረውን የጥገኝነት ራዕይ ሙሉ በሙሉ አክሽፎታል። እነዚህና ሌሎች ፓለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ምክንያቶች ቀጣዩን የኤርትራ መፃኢ እድል አደጋ ውስጥ ከተውታል። ዛሬ በኤርትራ ምን እየተከናወነ እዳለ አፉን ሞልቶ መናገር የሚችል ሀገርና ድርጀት ወይም ተቋም የለም። በአስመራ ተቀማጭነትታቸው የሆኑ የውጭ አምባሳደሮች ልዩ ፈቃድ ካላገኙ በስተቀር ከአሥመራ 25 ኪሎ ሜትር ርቀው የሚጓዙበት እድል የለም። ኤርትራ ዝግ በመሆኗ በርካቶች የምስራቅ “አፍሪካዋ ሰሜን ኮሪያ” እያሉ ይጠሯትል።  በአጠቃላይ በኤርትራ ያሉ ፈተናዎች እየገዘፉና እየተውሰበሰቡ የመጡ ሲሆን እኛም ያሉትን አጠቃላይ ሁኔታዎች በተመለከተ በተወሰነ ደረጃ ለመዳሰስ ሞክረናል።

ድርቅና ረሃብ በኤርትራ

ከተወሰኑ ዓመታት ወዲህ መላ ምስራቅ አፍሪካን የመታው ድርቅ ኢትዮጵያን፣ ደቡብ ሱዳንን፣ ሱዳንን፣ ሶማሊያን፣ ሶማሌላንድን እና ኬኒያንን በከፍተኛ ደረጃ አጥቅቷል። ካለፈው ዓመት ጀምሮ አድማሱን ያሰፋው ይህ የድርቅ መጠን ምዕራብ አፍሪካዊቷን ናይጄሪያን እንደዚሁም ከቀይ ባህር ማዶ ያለችውን የመንን ሳይቀር ክፉኛ አሽመድምዷል። መንግስታቱም የችግሩን ስፋት ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ በመግለፅ የእርዳታ ተማፅኗቸውን አቅርበዋል። ሆኖም በኤርትራ ይህ ሁኔታ ለአፍታም ፈፅም ቢሆን ትንፍሽ ሲባል አልተሰማመም።

 

መንግስት ቀደም ሲል በሀገሪቱ ይሰሩ የነበሩትን መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችን ሙሉ በሙሉ ጠራርጎ በማባረሩ በኤርትራ ስላው የድርቅ ሁኔታ የገለልተኛ ወገን መረጃን ማግኘት የሚቻልበት እድል ዝግ ሆኗል። ኤርትራን የከበቡት ሀገራት እና አጠቃላይ የምስራቅ አፍሪካ ቀጠና በአደገኛ ድርቅ በተመታበት ሁኔታ ኤርትራ ደሴት ልትሆን አትችልም። ይሁንና በኤርትራ መንግስት በኩል በተዳጋጋሚ የሚገለፀው በኤርትራ የድርቅ ስጋት የሌለ መሆኑንና፤ እንደውም ገበሬዎች የተሻለ ምርትን እየሰበሰቡ መሆኑን የሚገልፅ ነው።

 

ሀገሪቱ ይህ ነው ሊባል መስኖ የሌላት እንደዚሁም ከጣሊያንና ከደርግ ከተወረሱት አሮጌ ፋብሪካዎች በስተቀር በኢንዱስትሪው ዘርፍም ብዙም ልማትን ያላከናወነች በመሆኑ መንግስት ከዝናብ ውጪ ምርት የሚያገኝበት እድል እንደሌለ በግልፅ ይታወቃል።

 

 እንደ ቢቢሲ ዘገባ ከሆነ ደግሞ የዓለም አቀፉ አየር ትንበያ ሳተላይት ምስሎች የሚያሳዩት በኤርትራ ምድር በቂ ዝናብ እየጣለ አለመሆኑን ነው። ይሁንና በኤርትራ መንግስት በኩል እነዚህ የመሬት ላይ ሀቆች ተቀባይነት ሊያገኙ አልቻሉም። ድርቁ መከሰቱን አምኖ መንግስት እየተቆጣጠረው መሆኑን መግለፅም አንድ ነገር ነው። ሆኖም በመንግስት በኩል በተደጋጋሚ የሚገለፀው ኤርትራዊያን ገበሬዎች የተሻለ ምርት እያገኙ መሆኑን ነው።

ሆኖም የአካባቢው ሀገራትን ክፉኛ የመታው ኤሊኒኖ አመጣሹ ድርቅ ኤርትራንም ጭምር ክፉኛ ከመጉዳት ባለፈ ድርቁ ወደ ረሃብ የተቀየረ መሆኑን ከራሳቸው ከኤርትራዊያን የሚወጡ ድብቅ መረጃዎች ይፋ እየሆኑ ነው። መረጃዎቹ ሾልከው እየወጡ ያሉት ሀገሪቱን ጥለው ከሚወጡ ስደተኞች እንደዚሁም በድብቅ ተነስተው በማህበራዊ ሚዲያ በሚለቀቁ ፎቶች ነው። ከረሃቡ ጋር በተያያዘ በርካታ በምግብ እጥረት ለተጠቁ ህፃናትን የህክምና እርዳታን ሲሰጡ የነበሩ ኤርትራዊያን ነርሶች ከሰሞኑ በኢንተርኔት የለቀቋቸው የፎቶግራፍ ምስሎች የኤርትራን ድብቅ ረሃብ ገሃድ ያወጣ ሆኗል።

 

ኢኮኖሚው

የኤርትራ ኢኮኖሚ በምን አይነት የኢኮኖሚ ስርዓት እንደሚመራ ግልፅ አይደለም። “ነፃ ገበያ” እንዳይባል መንግስት ከገበሬው የእለት ምርት ጀምሮ እስከ መሰረተ ልማትና አገልግሎት አሰጣጥ ድረስ ኢኮኖሚውን ሙሉ በሙሉ ሲቆጣጠረው ይታያል። በሀገሪቱ መሰረታዊ ሸቀጦችን በገበያ ዋጋ ከመሸጥ ይልቅ መንግስት በወሰነው ዋጋ ብቻ ማቅረብ የግድ ነው። የሀገሪቱ የኤክስፖርትና የኢምፖርት ገቢ በግልፅ አይታወቅም። ብሄራዊ በጀቱም ለህዝብ ይፋ ተደርጎ አያውቅም። ሀገሪቱ አለም ባንክን ከመሰሉ ተቋማት ጋር በጋራ የምትሰራበት ሁኔታ ስለሌለ የኢኮኖሚው ግልፅነት ማጣት አስገዳጅነት አይታይበትም።  ያም ሆኖ ሀገሪቱ በብዙ መልኩ ፈተና ውስጥ መሆኗ ኢኮኖሚው ውጤት አልባ መሆኑን የሚያሳይ ነው።

 

ሀገሪቱን ወደ ኋላ እየጎተተ ያለው የኤሌክትሪክ ሀይል እጥረት

 ለማህበራዊ አገልግሎትና ለኢንዱስትሪው ዋነኛ ግብዓት ተደርገው የሚወሰዱት የኤሌክትሪክ ኃይልና ውሃ በመላ ኤርትራ ከፍተኛ እጥረት የሚታይባቸው ናቸው።

 

ኤሌክትሪክን በተመለከተ በመላ ኤርትራ ለኤሌክትሪክ ኃይል ምንጭነት የሚያገለግል አቅም ያለው ወንዝ ባለመኖሩ ሀይድሮ ፓወርን የማይታሰብ አድርጎታል። ከዚህ ውጪ ይኖራል ተብሎ የሚታሰበው የኤሌክትሪክ ኃይልን ከነፋስና ከፀሀይ ኃይል የማመንጨት ተግባር ነው። ይሁንና እነዚህ ሁለት እምቅ የኃይል አማራጮች በተለይ ዘርፉ ከሚጠይቀው መዋዕለ ነዋይና ከሀገሪቱም የፋይናስ አቅም ማነስ ጋር በተያያዘ ዘርፎቹ የአዋጭነት ጥናት እንኳን ሊደረግባቸው አልቻለም።

 

ከዚህ ውጪ በአሁኑ ሰዓት ብቸኛው የኤሌክትሪክ ኃይል ምንጭ ሆኖ እያገለገለ ያለው ሂርጊጎ በመባል የሚታወቀው የዲዝል ጄኔረተር የኃይል ማመንጫ ነው። የዚህ ኃይል ማመንጫ ታሪክ ኤርትራ ከኢትዮጵያ ከመነጠሏ ቀደም ብሎ የሚመዘዝ ሲሆን እስከዛሬም ድረስ ብቸኛው የሀገሪቱ የኤሌክትሪክ ኃይል ምንጭ ሆኖ በማገልገል ላይ ነው። ማመንጫው ለዓመታት አገልግሎትን በመስጠቱ በገጠመው ከፍተኛ እርጅና ሙሉ አቅሙን መጠቀም ካለመቻሉም ባሻገር አንዳንድ ጊዜም ሙሉ በሙሉ ስራውን እስከማቋረጥ የሚደርስበት ሁኔታም አለ።

 

ችግሩ በመላ ኤርትራ እየሰፋ የመጣው ደግሞ ከማመንጫው እርጅና ጋር በተያያዘ ብቻ ሳይሆን፤ የኤሌክትሪክ ኃይል ፍላጎቱና አቅርቦቱ መጠን እየሰፋ የመሄዱ ጉዳይ ነው። በዚያው በሂርጊጎ የተተከሉት ዲዝል ጄኔረተሮች አጠቃላይ ኤሌክትሪክን የማመንጨት አቅም ቀደም ሲል 84 ሜጋ ዋት ብቻ ስለነበር፤ ዋና ከተማዋን አስመራን ጨምሮ በርካታ የሀገሪቱ ከተሞች በተደጋጋሚ የኤሌክትሪክ ኃይል መቋረጥ ሲያጋጥማቸው ቆይቷል።

 

 ችግሩን ለመፍታት ሻንጋይ ኮርፖሬሽን ፎር ፎሬይን ኢኮኖሚክ ኤንድ ቴክኖሎጂካል ኮኦፖሬሽን ከተባለ አንድ የቻይና ኩባንያ ጋር በተደረሰ የሁለትዮሽ ስምምነት እያንዳንዳቸው 23 ሜጋ ዋት የኤሌክትሪክ ሀይል የማመንጨት አቅም ያላቸው ሁለት የዲዝል ጄኔሬተሮች በተጨማሪነት በመተከላቸው አጠቃላይ የሀገሪቱን ኤሌክትሪክ ኃይል አቅም ከ84 ሜጋ ዋት ወደ 132 ሜጋ ዋት ከፍ ማድረግ ተችሏል።

 

 ይህን አቅም የማሳደግ ስራ ከተሰራ በኋላም ቢሆን ዛሬም ድረስ በመላ ኤርትራ ከፍተኛ የሆነ የኤሌክትሪክ ኃይል መቆራረጥ ችግር ይታያል። ካለው የሀይል እጥረት ጋር በተያያዘ ታላላቆቹን አስመራና ምፅዋ ከተሞችን ጨምሮ በሀገሪቱ በርካታ ከተሞች ለሰዓታት ብሎም ለቀናት የኤሌክትሪክ ኃይል መቋረጥ የተለመደ ነው። በዚም የኃይል መቆራረጥ የትምህርት ተቋማት፣ ሆስፒታሎችና ኢንዱስትሪዎች ሳይቀሩ የዕለት ተዕለት ተግባራቸውን በአግባበቡ መወጣት አልቻሉም።

 

 የሀገሪቱ የግንባታ የጀርባ አጥንት እንደሆነ የሚነገርለት ብቸኛው ገደም የሲሚንቶ ፋብሪካ ከኤሌክትሪክ ሀይል እጥረት ጋር በተያያዘ ማምረት ወደማይችልበት ደረጃ እየደረሰ ነው። ኤርትራ የሀይል ማስፋፊያ ስራዋን እንደሰራች ከሁሉም በፊት ቅድሚያ የሰጠችው ይህ የሲሚንቶ ፋብሪካ በሙሉ አቅሙ እንዲሰራ ማድረግ ነበር። ኳታር የኤርትራን ኢኮኖሚ ለማገዝ ባሳየችው ፍላጎት ሀገሪቱ እ.ኤ.አ በ2022 ለምታካሂደው የዓለም ዋንጫ እየተካሄደ ባለው መጠነ ሰፊ ግንባታ ኤርትራ ሲሚንቶ አቅርባ የውጭ ምንዛሪ አቅሟን የምታሳድግበትን ሰፊ እድል ሰጥታት ነበር። ኤርትራም እድሉን በመጠቀም የሲሚንቶ ምርቷን ወደ ኳታር መላክ ጀምራ የነበረ ቢሆንም እየተባባሰ በሄደው የኤሌክትሪክ ኃይል እጥረትና በሌሎች ያልታወቁ ምክንያቶች ኤክስፖርቱ በጀመረበት ሂደት መቀጠል ሳይችል ቀርቷል።

 

የሀገሪቱ ኤሌክትሪክ ኃይልን የማመንጨት አቅም ውስንነት እንጂ በአሁኑ ሰዓት ያለው አጠቃላይ የኃይል መጠን ከበርካታ ሀገራት አጠቃላይ የኃይል ምርት መጠን አንፃር ሲታይ እዚህ ግባ የሚባል አይደለም። ደቡብ አፍሪካ በአሁኑ ሰዓት ከ30 ሺህ ሜጋ ዋት በላይ የኤሌክትሪክ ሀይልን ታመነጫለች። የግብፅ አጠቃላይ የኤልክትሪክ ሀይል የማመንጨት አቅም ወደ 27 ሺህ ሜጋ ዋት አድጓል። 1 ሺህ 780 ሜጋ ዋት የኤሌክትሪክ ኃይል የሚያመነጨውን ግልገል ጊቤ ሶስት የኃይል ማመንጫ ግድብ መጠናቀቅን ተከትሎም በአሁኑ ሰዓት ያለው የኢትዮጵያ አጠቃላይ ሀገራዊ የኤሌክትሪክ ኃይል ምርት መጠንም ወደ 5 ሺህ ሜጋ ዋት ተጠግቷል። በሂደት ላይ ያሉ ፕሮጀክቶችም ሲጠናቀቁ አሁን ያለው የኢትዮጵያ ኃይል የማምረት አቅም ቢያንስ በእጥፍ የሚያድግበት ሁኔታ ይኖራል ተብሎ ይታሰባል።

 

የአንድ ሀገር ኢኮኖሚ መለኪያ መሳሪያዎች ተደርገው ከሚወሰዱት ግብዓቶች መካከል አንደኛው የዚያ ሀገር የሀይል ፍጆታ መጠን ነው። ሆኖም ኤርትራ በሀገር ደረጃ እያመነጨች ያለው አጠቃላይ የኤሌክትሪክ ኃይል መጠን ሲታይ በአሁኑ ሰዓት በኢትዮጵያ እየተገነቡ ካሉት የኢንዱስትሪ ፓርኮች አንዱ ብቻ ከሚያስፈልገው የኤሌክትሪክ ኃይል መጠን በታች ሆኖ ይታያል። ሀገሪቱ በቀይ ባህር ዳርቻ የነፋስ ኃይል እምቅ አቅም እንደዚሁም በአፋር ዝቅተኛ ቦታዎች ደግሞ ከእንፋሎት ሀይል ሊመነጭ የሚችል ከፍተኛ እምቅ አቅም እንዳላት ቢገመትም፤ ካለው የአቅም ውስንነት ጋር በተያያዘ የሀይል ማመንጫ ልማትን ማከናወን ይቅርና የአዋጭነት ስራ እንኳን የተሰራበት ሁኔታ የለም።

 

 መንግስት ከሌሎች ሀገራት ጋር ካለው ደካማ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነትና የመበደር አቅም ውስንነት ጋር በተያያዘ ለትልልቅ የልማት ስራዎች የሚያስፈልግ ፋይናስን ማግኘት የሚቻልበት እድልም ጠባብ ነው። የኤርትራ መንግስት የሀገሪቱን በጀት፣የኢኮኖሚ እንቅስቃሴዋን እና አጠቃላይ ሂደቱን በተመለከተ ከዓለም አቀፍ ተቋማት ጋር በጋራ የሚሰራበት አካሄድ ስለሌለ በዚያው መጠን የዓለም አቀፍ አበዳሪዎችን ይሁንታ የሚያገኝበት እድሉ ዝግ ሆኗል። ይህም ችግር ግዙፍ የፋይናስ አቅም የሚጠይቁትን እንደ ኤሌክትሪክ ኃይል ያሉ መሰረተ ልማቶች ኤርትራ እንዳትገነባ እንቅፋት ሆኖባታል። የመሰረተ ልማት ፋይናሱ ጉዳይ ራስ ምታት የሆነበት የኤርትራ መንግስት ከግንባታው ይልቅ የአቋራጭ አማራጭ ያደረገው የኤሌክትሪክ ኃይል ከሌላ ሶስተኛ ሀገር መግዛት ነው። በዚህ ጉዳይ ወሳኝ አማራጭ ሆና የምትታየው ኢትዮጵያ ብትሆንም በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለው ባላንጣነት እድሉን ዝግ አድርጎታል። ሁለተኛዋ አማራጭ ተደርጋ አይን የተጣለባት ሀገር ሱዳን ናት።

 

ሱዳን በአካባቢው ሌላኛዋ ከፍተኛ የኤሌክትሪክ ኃይል እጥረት የሚታይባት ሀገር ናት። ከዚሁ ጋር በተያያዘ የኤሌክትሪክ ሀይልን ከኢትዮጵያ ለመግዛት ሰፊ ሁለቱ ሀገራት ሰፊ ስራዎችን ሲሰሩ ከቆዩ በኋላ 321 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያለው ከፍተኛ የኤሌክትሪክ ሀይል ማስተላለፊያ መስመር ተዘርግቶ ሱዳን ከኢትዮጵያ የኤሌክትሪክ ኃይልን በግዢ የምታገኝበት ሁኔታ ተፈጥሯል። ሆኖም ኤርትራ ከሱዳን የኤሌክትሪክ ኃይልን በመግዛት የገጠማትን እጥረት ለመፍታት ጥረት እያደረገች መሆኑን ቀደም ያሉ መረጃዎች ያመለክታሉ።

 

  እንደውም አንዳንዶች “ሱዳን ከኢትዮጵያ የኤሌክትሪክ ኃይልን በመግዛት በተጨማሪ ሂሳብ ለኤርትራ የመሸጥ ስትራቴጂን እየተከተለች ነው” በማለት አስያተየት ሲሰጡም ተሰምቷል። ኤርትራዊያን በሶስተኛ ወገን በተለይም በሱዳን በኩል ቡና እና በርበሬን የመሳሰሉ የኢትዮጰያን ምርቶች መግዛት የተለመደ ነው። ይህ በመንግስት ደረጃ በኤሌክትሪክ ኃይሉም አይደገምም ተብሎ አይታሰብም።

 

ንፁህ መጠጥ ውሃ፤ ሌላኛው የኤርትራ ፈተና

በአሁኑ ሰዓት መላ ኤርትራን እየተፈታተነ ያለው ጉዳይ የንፁህ መጠጥ ውሃ አቅርቦት እጥረት ነው። የገጠሩ ጉዳይ ፈፅሞ የሚነሳ አይደለም። የከተሞቹን ፈተና ማንሳቱ በቂ ማሳያ ሊሆን ይችላል።

 

 የዚህ ችግር ተጠቂ ከሆኑት የኤርትራ ከተሞች መካከል በዋነኝነት የምትጠቀሰው አስመራ ናት። በአስመራ ረዥም ወራፋን እየጠበቁ ውሃን በቦቴ መኪና በራሽን መልክ መውሰድ በደርግም እንደዚሁም ከኤርትራ አንደ ሀገር መቆም ማግስትም የተለመደ ተግባር ነው። ይህ ለአስመራ ነዋሪዎች አዲስ አይደለም።

 

 ለበርካቶች በከተማዋ በተቋቋሙት የውሃ ማከፋፈያ ማዕከላትና ጣቢያዎች ስማቸው የተፃፉባቸው ሴሚያዊ የፕላስቲክ በርሚሎች በየእለቱ ማሰለፍ የተለመደ ነው። ውሃ የጫኑ ቦቴዎችም በተወሰነ ቀን አንድ ቀን የማከፋፈል ስራን ይሰራሉ። ይህ አስመራን ጨምሮ የበርካታ የኤርትራ ከተሞች የየዕለት ተዕለት ተግባር ነው።

 

 Awate.com በመባል የሚጠራውን ታዋቂ የኤርትራዊያን ድረገፅ ጨምሮ በርካታ የኤርትራ ሚዲያዎች በሰፊው እየተወያዩበት ያለ አጀንዳ ቢሆንም፤ ችግሩ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ ከመሄድ ባለፈ ይህ ነው የሚባል መፍትሄ ሊገኝለት አልቻለም። መንግስት ካለበት ከባድ የገንዘብ እጥረት ጋር በተያያዘ ከጣሊያን እስከ ደርግ ዘመን ሲያገለግሉ የነበሩ ያረጁ የውሃ ቧንቧ መስመሮች እንኳን መለወጥ አልቻለም።

 

ኤርትራን እያፈረሰ ያለው የዜጎች ስደትና ኩብለላ

ከኢትዮ ኤርትራ ጦርነት ማብቂያ ማግስት ኤርትራን የገጠማት ፈተና ዜጎቿ በገፍ ሀገሪቱን ጥለው የመሰደዳቸው ጉዳይ ነው። ለዚህ የገፍ ስደት የሚጠቀሱ በርካታ ምክንያቶች አሉ። ከእነዚህ ምክንያቶች መካከል አንደኛው እስከ ዛሬም ድረስ በስራ ላይ ያለው የግዳጅ ወታደራዊ አገልግሎት ነው። በኤርትራ የሚገኝ አንድ ወጣት እድሜው ለአቅመ አዳም ከደረሰና ከሃምሳ ዓመት በታች መሆኑ ከተረጋገጠ ወታደራዊ ስልጠና መውሰድ እንደዚሁም ለተወሰኑ ዓመታት ነፃ የጉልበትና የእውቀት አገልግሎት መስጠት ብሄራዊ ግዴታው መሆኑ በህግ ተደንግጓል። ይህ ህግ በመላ ሀገሪቱ እንዲተገበር የተወሰነው እ.ኤ.አ ከ1995 ጀምሮ ነው። ፕሬዝዳንት ኢሳያስ ይህንን ህግ ተግባራዊ ሲያደርጉ ለብሄራዊ አንድነት፣ ሀገር ፍቅር ያለው ትውልድን ለመገንባትና በዲሲፒሊን የተሞላ የስራ ሀይልን በሀገር አቀፍ ደረጃ ለመገንባት መሆኑን አመልክተው ነበር። 

 

ወጣቶች በሚገቡባቸው ማሰልጠኛ ተቋማት ወታደራዊ ስልጠናን ጭምር መውሰድ ግዴታቸው ነው። ከዚያ በኋላም ከእርከን ሥራ እስከ ተፈጥሮ ጥበቃ ድረስ እንደዚሁም ከመንገድ ግንባታ እስከ መስኖ ስራ የሚዘልቅ ግንባታን በአነስተኛ የኪስ ገንዘብ ማከናወን ይጠበቅባቸዋል። ይህ የኤርትራ መንግስት ህግና አሰራር ከተጀመረ በኋላ ለጥቂት ዓመታት ያህል እንደቆየ ከበድያለ ተቃውሞ እየገጠመው ሄዷል።  ብሄራዊ ግዴታው የበለጠ እየከፋ የሄደው ደግሞ የአገልግሎት ቆይታው ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መሄዱ ነው። የኤርትራ ባለስልጣናት የዜጎችን ብሄራዊ ግዴታ በተመለከተ የሚሰጧቸው መግለጫዎች ከድንበር ጦርነቱ ጋር በተያያዘ የኢትዮጵያን ወረራ በስጋትነት በማየትም ጭምር መሆኑን ይገልፃሉ።

 

 ከዚሁ ጋር በተያያዘም በወታደራዊ ስልጠናው እንደዚሁም በጉልበት ስራው የተማረሩ ኤርትራዊያን ሀገሪቱን ጥለው መሰደድ ግድ እየሆነባቸው ሄዷል።  እንደ ኦፕን ማይግሬሽን ድረገፅ ዘገባ ከሆነ ኤርትራን በየወሩ ለቀው የሚወጡ የሀገሪቱ ዜጎች ቁጥር ከአራት ሺህ እስከ አምስት ሺህ ደርሷል። መንግስት ሀገሪቱን ጥለው የሚሄዱ ዜጎቹን አድኖ ለመያዝ ያቆማቸው በርካታ ኬላዎች ሊሰሩ አልቻሉም። ኬላ ጠባቂ ወታደሮች ሳይቀሩ መሳሪያቸውን እየጣሉ ስደቱን በመቀላለቀል ላይ ናቸው። ሀገር ጥለው ለመኮብለል ሲሞክሩ የተደረሰባቸው በርካታ ዜጎችም ለእስርና ድብደባ እንደዚሁም ለጥይት ሰለባ እስከመሆን ደርሰዋል።

 

 ከዚህም አልፎ በአፋር በረሃ የቀሩ፣ በሰሃራ በረሃ ተውጠው የጠፉና በሜድትራኒያን ባህር ሰምጠው ህይወታቸው ያለፉ በርካቶች ናቸው። በኢትዮጵያ፣በየመንና በሱዳንም በርካታ ስደተኞች ይገኛሉ። በርካቶችም የወጣትነት ጊዜያቸውና እድሜያቸውን በስደተኝነት ካምፕ ውስጥ ማሳለፍ ግድ ሆኖባቸዋል። አንዳንዶች በየካምፑ ወልደው ቤተሰብ የመሰረቱም አሉ። ኤርትራ በአለም አቀፍ ደረጃ ከሶርያና ከአፍጋኒስታን በመቀጠል በሚሰደድ ዜጎች ቁጥር የሶስተኝነት ደረጃን የያዘች መሆኑን የአልጀዚራ ዘገባ ያመለክታል። ኢትዮጵያም በአሁኑ ሰዓት ከአንድ መቶ ሺህ በላይ ኤርትራዊያን ስደተኞችን በማስተናገድ ላይ ስትሆን ይህ ቁጥርም ለጊዜ ወደ ጊዜ በመጨመር ላይ ይገኛል።

 

 የሀገሪቱ ሰራተኛ ሀይል ኤርትራን ለቆ የመውጣቱም ጉዳይ ሌላኛው ፈተና ነው። በርካታ በአውሮፓና በአሜሪካ የሚኖሩ ኤርትራዊያን በተለያዩ ሀገራት የሚገኙ ስደተኞች ዘመዶቻቸውን ወዳሉበት ሀገር ለማሻገር በሚያደርጉት ጥረት  ገንዘባቸውን የሚልኩት ስደተኞቹ ወደ ተጠለሉባቸው ሀገራት መሆኑ የኤርትራ መንግስት የሚተማመንበት የሀዋላ የገንዘብ ምንጭ በከፍተኛ ደረጃ እየወረደ እንዲሄድ አድርጎታል።

 

  ከኢትዮጵያ መነጠል ማግስት በኤርትራ የነበረው ህልም ዛሬ የለም። ሀገሪቱ በየትኛውም አቅጣጫ የመፍረስ አደጋ ውስጥ ገብታለች። በሀገሪቱ የበረራ መስመር የነበራቸው ዓለም አቀፍ አየር መንገዶች ሳይቀሩ የኤርትራ በረራ አዋጪ ሆኖ ባለማግኘታቸው ሙሉ በሙሉ እስከመሰረዝም ደርሰዋል። በማዕቀብ ውስጥ ያለው የኤርትራ መንግስት በአሁኑ ሰዓት ዋነኛ ገቢው እንደሆነ የሚታሰበው በወታደራዊ ቤዝነት ለአካባቢው ዓረብ ሀገራት ያከራያቸው የጦር ሰፈሮች፤ እንደዚሁም ቢሻ የወርቅ ማዕድንና መልካም ተስፋ እየታየበት ያለው የአፋር ዙሪያ የፖታሽ ማድን ነው። ይህ ገቢም ቢሆን ሀገራዊ ፋይዳው በግልፅ አይታወቅም። ኤርትራ ብዙም በተፈጥሮ ሀብት የታደለች ሀገር አትሁን እንጂ የቀይ ባህር ዳርቻ የቱሪስት መዝናኛዎቿ ቢለሙ፤ የዳህላክ ደሴቶች ለመዝናኛነት መዋዕለ ነዋይ ቢፈስባቸው፣የቀይ ባህር የጨው ሀብቱ በኢንዱስትሪ ቢቀነባበር፣ የዚያው የቀይ ባህር የአሳ ሀብት በዘመናዊ መልኩ ጥቅም ላይ ቢውል፤ ለሀገሬው ዜጋ በቂ ሀብት መሆን ይችል ነበር። ይህ ብቻ ሳይሆን በአፋር ዝቅተኛ ቦታ ያለው የፖታሽና የሌሎች ማዕድናት ሀብትም ከፍተኛ እንደሆነ ይታመናል። ሆኖም እስከዛሬ የጠፋው ጊዜ ከዚህ በኋላ እነዚህን ሀብቶች የማልማቱን አቅም ሩቅ እያደረገው ሄዷል።

 

 ሀገሪቱም ወደለየለት የእርስ በእርስ ጦርነት የምትገባበት አጋጣሚ፤ እንደዚሁም የፕሬዝዳንት ኢሳያስ መንግስትም ቢሆን በወታደራዊ መፈንቅለ መንግስት የሚወድቅበት ዕድል ሰፊ መሆኑ ይነገራል። እነዚህ ሁኔታዎች የሚከሰቱ ከሆነ ደግሞ የአካባቢው የፖለቲካ መልክዓ ምድር ያልተጠበቀ አቅጣጫን እንዲይዝ የሚያደርገው ይሆናል። በስልጣን ላይ ረዘም ላለ ጊዜ የቆዩ አምባገነን መሪዎች በተለይም በአፍሪካ ምድር የመጨረሻው ዕጣ ፈንታ መፈንቅለ መንግስት መሆኑ የሚታወቅ ነው። በተለይም ከምዕራባዊያኑ ሀገራት ጋር ሆድና ጀርባ የሆነ መንግስት፤ እንደዚሁም ለአጭር ጊዜ ፍላጎት የበርካታ የውጭ ኃይሎች ፖለቲካዊ ፍላጎት ለማሳካት የሚጥር መንግስት መጨረሻው ተጠልፎ መውድቅ መሆኑ እሙን ነው።

 

ከአንድ አምባገነን መንግሰት መውደቅ በኋላ ምን ሊከሰት ይችላል? የሚለውን ጉዳይ በተመለከተ ደግሞ ከሳዳም ሁሴን በኋላ ያለችውን ኢራቅ፣ ከሞአመር ጋዳፊ ህልፈተ ህይወት ማግስት የተፈጠረችውን ሊቢያ እንደዚሁም ከአምባገነኑ ዚያድባሪ መንግስት ማክተም በኋላ የታየችውን ሶማሌ በማሳያነት መመልከቱ ብቻ በቂ ማስረጃ ነው።     

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
468 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 1040 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us