የሙሴቬኒ የአቋም መዋዥቅ መነሻው ምንድን ነው?

Wednesday, 17 May 2017 12:40

 

በሳምሶን ደሣለኝ

በኡጋንዳው መሪ ዩዌሪ ሙሴቬኒ የተጠራው የናይል ካውንስል የመሪዎች ስብሳባ ከሜይ 25 ወደ ጁን አጋማሽ እንዲዘዋወር ተደርገዋል፡፡ ዘገባውን ያስነበበው የግብጹ ዴይሊኒውስ ስብሰባው የተዛወረበትን ምክንያት ሲታት፣ ግብፅ የኢንቴቤው ስምምነት ተብሎ ለሚጠራው ውይይት ቀርፃ ያቀረበችውን ሰነድ ለመመልከት የኢትዮጵያ መንግስት ጊዜ በመጠየቁ ነው ብሏል፡፡

እንደዘገበው ከሆነ፣ ግብፅ የዓለም ዓቀፉን የውሃ ስምምነት መሰረት ያደረገ ሰነድ ይዛ መቅረቧን ገልጸል፡፡ ሆኖም፣ ሶስት መሰረተዊ ነጥቦች ማካተቱን ጽፏል፡፡ ይኸውም፣ የውሃ ደህንነትን፣ ቀድሞ ማሳወቅን ይጠይቃል እና የሚሰጡ ውሳኔዎች በመስማማት እንጂ በአብዛኛው ድምፅ ብልጫ እንዳይወሰን የሚጠይቅ ነው፡፡

ግብፅ አቀረበች የተባለው አዲስ የድርድር ስምምነት ሰነድ፣ ፈረንጆቹ እንደሚሉት “An old wine in a new bottle” አይነት ነው፡፡ ሌላው ቢቀር በናይል ውሃ ላይ የሚደረጉ ማናቸውም አይነት የልማት እንቅስቃሴዎች፣ ቅድሚያ ግብፅ ማሳወቅ የሚጠይቀው 1959 የቅኝ ግዛት የናይል ውሃ አጠቃቀም ውል ዛሬም ግብፅ ይዛ ቀርባለች፡፡ የድምፅ ውሳኔ አሰጣጥን በተመለከተ በስምምነት ብቻ የሚባለው፣ ግብፅ እስካሁን ስታካሂደው በነበረው አቋም የቅኝ ግዛት ውሎችን የሚጣረስ ነጥብ አትቀበልም፡፡ ይህ ማለት በአጭሩ ለፍታዊ የውሃ ክፍፍል ዝግጁ አይደለችም፤ ከላይኛው ተፋሰስ ሃገሮች ጋር አትስማማም ማለት ነው፡፡ ስለዚህም ውሳኔ የማያሳልፍ የናይል ውሃ ካውንስል እንዲመሰረት ከተፈለገ ብቻ ነው፣ ውሳኔ በአብላጫ ድምጽ እንዳይወሰን ጥያቄ የሚቀርበው፡፡ የውሃ ደህንነትን በተመለከተ ተመሳሳይ ነው፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ኃ/ማሪያም ደሳለኝ ካምፓላን በጎበኙበት ጊዜ በሰጡት የጋራ ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ከጋዜጠኞች የናይል ውሃ ስምምነትን በተመለከተ ለቀረበላቸው ጥያቄ ሙሴቬኒ ይህንን ምላሽ ነበር የሰጡት፤ "I have not yet ratified because I want to dialogue. To get a consensus, it is better we have more dialogue, more talking." (እስካሁን አለፃደቅነውም፡፡ ምከንያቱም ከስምምነት ላይ ለመድረስ ውይይት እንፈልጋለን፡፡) የሚገርመው ኢትዮጵያ የናይል ውሃ ሃብትን አጠቃቀም የፈረመችው ኤንቴቤ በመገኝት ነበር፡፡ እዚህ ስምምነት ላይ ለመድረስ ከ1999 እስከ 2010 ድረስ ረጅም ጥረት ጠይቋል፡፡

ባለፉት አስርት አመታት በጋራ በመሆን የተሳተፉት ፕሬዝደነት ሙሴቬኒ፣ ዛሬ ላይም ውይይት አጥብቀው የመሻታቸው ጉዳይ አጠያያቂ ነው፡፡ ፍትሃዊ የውሃ አጠቃቀም ላይ የሙሴቪኒ አቋም መዋዠቅ መነሻዎች ምንድን ናቸው? ተራ የፖለቲካ ቁማር ውስጥ ምን ዘፈቃቸው? ኡጋንዳና ግብፅ ምን ዓይነት ተልዕኮ አንድ አደረጋቸው? ሙሴቬኒ ለምን የተንሸዋረረ አቋም ማራመድ ፈለጉ? እና ለሌሎችም ምላሾችን ከተለያዩ ምንጮች ከተገኙ መረጃዎች ጋር በማጠናቀር በዚህ መልኩ አቅርበነዋል፡፡

 

 

ኡጋንዳ በደቡብ ሱዳን ፖለቲካ ውስጥ ከፍተኛ ጣልቃ ገብነት ያላት ሀገር ስትሆን፣ የፕሬዝደንት ሳልቫኪር መንግሥት ዋነኛ ሸሪክ ነች። ኡጋንዳ እና ኢትዮጵያ ከደቡብ ሱዳን ጋር ሰፊ ድንበር የሚጋሩ ሀገራት ናቸው። ከዚህም አንፃር ኡጋንዳ በደቡብ ሱዳን ፖለቲካ ውስጥ ግልፅ ፖለቲካዊ እና ኢኮኖሚያዊ ፍላጎት አላት።

የኡጋንዳ መንግሥትን የሚቃወሙ ተቃዋሚ ኃይሎች በደቡብ ሱዳን ድንበር ላይ በመንቀሳቀስ፣ የኡጋንዳን ውስጣዊ ፖለቲካና መረጋጋት ሲያምሱ የነበሩ ኃይሎችን  በመደምሰስ የሳልቫኪር መንግሥት በሰጠው ድጋፍ መነሻ፣ አለቅድመ ሁኔታና ሚዛናዊነት የሳልቫኪርን የፖለቲካ ቡድን እየደገፈች ትገኛለች። የተሻለ ተጠቃሚም ለጊዜው መሆን ችላለች።

ኡጋንዳ፣ በደቡብ ሱዳን ውስጥ ከፍተኛ የኢኮኖሚ ፍላጎት አላት። ለኡጋንዳ የኢኮኖሚ መነቃቃት እጅግ ሰፊ የሆነ የግብርና ምርት ገበያ በደቡብ ሱዳን መገኘቱ  አስተዋጽኦ ቀላል የሚባል አይደለም። ኡጋንዳ፣ የአትክልትና ፍራፍሬ ምርት ለደቡብ ሱዳን ታቀርባለች። በደቡብ ሱዳን ውስጥ፣ በግንባታና የግንባታ ቁሳቁስ በማቅረብ ሥራ የተሠማሩ በርካታ ኡጋዳዊያን በዱጁባ፣ እንዲሁም ከሰሜናዊ ኡጋንዳና ከካምፓላ የመጡ በንግድ ሥራ ብቻ የተሰማሩ የኡጋንዳ ዜጎች ቁጥር እስከ ሶስት ሚሊዮን እንደሚደርሱ ይገመታል።

በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለው የንግድ ሥርዓት ኢፍትሃዊነት ብዙ ጥያቄዎች ይቀርብበታል። ይህም ሲባል፣ ንግዱን የተቆጣጠሩት የፖለቲካ ሊሂቃን ናቸው። ተራው ዜጋ ከንግዱ ተጠቃሚ የሆነበት መንገድ በጣም ዝቅተኛ ነው። ከፍተኛው መጠን ያለው የንግድ እንቅስቃሴ በፖለቲካ ልሒቃን የንግድ መረብ የተተበተበ እንደሆነ በስፋት ይታመናል።

ከዚህም በተጨማሪ ከደቡብ ሱዳን ሕዝብ የተዘረፈ የፕሬዝደነት ሳልቫኪር እና በእሳቸው ዙሪያ የተሰለፉ የፖለቲካ ኃይሎች አንጃዎች ሐብት እና ንብረት በአብዛኛው በኡጋንዳ ማከማቸታቸው በሁለቱ ሀገራት መካከል ጥልቅና ሰፊ ወዳጅነት እንዲመሰርቱ አስችሏቸዋል። በአደባባይ የኡጋንዳ መንግስት በደቡብ ሱዳን ሰላም እንዲመጣ እንደሚሰራ ይናገር እንጂ፣ ከፕሬዝደነት ሳልቫኪር ውጪ ደቡብ ሱዳን እንድትመራ አይሻም። በተቃዋሚዎች የሚመራ የፖለቲካ ኃይል ስልጣን ከያዘ የኡጋንዳ መንግስት አሁን የሚያገኘውን ጥቅም ማስጠበቅ እንዳመይችል አድርጎ ነው የሚወስደው። ስለዚህም የኡጋንዳ መንግስት ለፕሬዝደንት ሳልቫኪር የፖለቲካ ቡድን ዋነኛው የስልጣን ምንጭ ሆኗል።

ኡጋንዳዊያን፣ ደቡብ ሱዳኖች በመቶ ሚሊዮኖች የሚቆጠር ዶላር ከነዳጅ ዘይት ቢያገኙም ከማሕበራዊ ምጣኔ ሃብት አንፃር ፍታሃዊ ክፍፍል የሌለ እንዲሁም፣ ወጥነት ባለው የፖሊሲ ስርዓት እንደማይመሩ በማወቃቸው ወደ ደቡብ ሱዳን ገብተው ከትልቅ እስከ ትንሽ በምርትና አገልግሎት አቅርቦት ሥራ ላይ ተሰማርተው ይገኛሉ። ይህ መሆኑ ብዙ አስደናቂ ጉዳይ አይደለም። በዚህ መካከል ከደቡብ ሱዳን ፔትሮ ዶላር የሚያገኙት የኡጋንዳ ኢኮኖሚ ላይ ያለው ተጽዕኖ ቀላል አይደለም። ማጣቀሻዎች እንደሚያሳዩት፣ እስከ 2008 (ኤ.ኤ.አ) ድረስ ኡጋንዳ በየዓመቱ ከ50 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር ያላነሰ የውጪ ንግድ በደቡብ ሱዳን ብቻ እንዳከናወነች መረጃዎቹ ያሳያሉ።

ከኢትዮጵያ እና ኬንያ ወደ ደቡብ ሱዳን የሚገቡ ሰዎች ቁጥር እያደገ ቢመጣም፣ በደቡብ ሱዳን ከሚገኙት የውጪ ዜጐች አምስት በመቶ የሚሆኑት የኡጋንዳ ዜጎች ናቸው። ስለዚህም ከማንም በላይ የደቡብ ሱዳን የመንግሥት ሥርዓት ቢናጋ፣ ኡጋንዳን የሚያስከትልባት ሁለንተናዊ ቀውስ ቀላል አለመሆኑን ባለሙያዎች ይናገራሉ።  በተለይ ከ2013 በኋላ በተከሰተው የእርስ በእርስ ጦርነት ኡጋንዳ ወደ ደቡብ ሱዳን በምትልከው የውጪ ንግድ ላይ ከባድ ተፅዕኖ አስከትሎባታል። ከላይ ከሰፈሩት ፖለቲካዊ እና ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ አንፃር ኡጋንዳ፣ የደቡብ ሱዳን ተቃዋሚ የፖለቲካ ኃይሎችን ከሳልቫኪር እኩል እየተዋጋች ትገኛለች። ለደቡብ ሱዳን ተቃዋሚ ኃይሎችም መጠለያ ድጋፍ የሚሰጡ ሀገራትን እንደጠላት በመውሰድ በደቡ ሱዳን ሰላም ሒደት ላይ አሉታዊ ሚና እየተጫወተች ትገኛለች።

ኡጋንዳ፣ በደቡብ ሱዳን ያላት ፍላጎት ኢኮኖሚያዊ ብቻ ሳይሆን ረጅም ድንበር ከደቡብ ሱዳን ጋር የምትዋሰን መሆኑን በሁለቱ ሀገራት ድንበሮች አካባቢ የሚኖሩት ጎሳዎች ደግሞ በማንነት እጅግ ልዩ ልዩ መሆናቸው አካባቢውን ለውክልና ጦርነትና ለድንበር ግጭት ተጋላጭ አድርጎባታል። ይህን እንቅስቀሴ ለመመከት ከደቡብ ሱዳን መንግሥት ጋር በመተባበር እየሰራች ትገኛለች።

በደቡብ ሱዳን በተከሰተው የእርስ በእርስ ግጭት የኡጋንዳ ሚና ፍላጎቷን በግልፅ የሚያሳይ ነው። የደቡብ ሱዳን መንግሥት በበኩሉ ከኡጋንዳ የጠየቀው እገዛ በራሱ የሁለቱን ሀገራት ፍላጎት በግልፅ የሚጠቁም ነበር። ይኸውም፣ የኡጋንዳ አየር ኃይል የተቃዋሚ ኃይሎች ግስጋሴ ለመግታት የአየር ጥቃት እስከ መፈፀም መድረሱ የሚታወስ ነው። የኡጋንዳ ዜጎች በመከላከል ሽፋን፣ የአየር ማረፊያዎችንም በመቆጣጠር ያስገባውን የጦር ኃይል የመንግሥቱን ኃይሎችን ከመደገፍ በላይም ለሳልቫኪር መንግሥት መቆም ከለላ አቅርቧል። እስካሁንም መጠናቸው ቢቀንስም በደቡብ ሱዳን ውስጥ የሚንቀሳቀሱ የኡጋዳ ወታደሮች አሉ።

በአንፃራዊነት የኡጋንዳ ጣልቃ ገብነት መገታት፣ የሳልቫኪር መንግስትን የሚቃወሙ ኃይሎች እንቅስቃሴ እየበረታ መምጣቱ የኡጋዳን መንግስት ተስፋ መቁረጥ ውስጥ ከመክተቱም በላይ ቀጠናውን ወደ ማተራመስ እንቅስቃሴ ውስጥ እንዲገባ አድርጐታል። የተፈጠረባቸውን ጫና ለማቃለል በሚል ትልቁን የቀጠናውን ስዕል ማየት አቅቷቸው ቀጠናው እንዲታመስ ከሚፈልጉ ኃይሎች ጋር፣ ፕሬዝደንት ሙሴቬኒ የፖለቲካ ሽርሙጥና ውስጥ ገብተዋል።

ኡጋንዳ፣ የቀጠናውን ትልቁን ሰላም ከማየት ይልቅ የመረጠችው መንገድ፣ የደቡብ ሱዳን ፖለቲከኞች ሐብትና ፍላጎት ጠባቂና በመሆኑን ፍላጎቷን ማሟላት ነው። በተለይ ለሳልቫኪር የምትሰጠው ጭፍን ድጋፍ ለደቡብ ሱዳን ሰላም ማጣት ከፍተኛውን ድርሻ ወስዷል። ኡጋንዳ ፍላጎቷን በመለጠጥ፣ የኢትዮጵያ መንግሥት እና ሌሎቹም የቀንዱ ሀገራት የደቡብ ሱዳን ተቃዋሚዎችን ለማጥፋት ትብብር እንዲያደርጉላት ትሻለች።

በተለይ ኢትዮጵያ ለዚህ ለኡጋንዳ ፍላጎት የማትተባበር ከሆነ፣ የኢትዮጵያን ተቃዋሚ ኃይሎችን ወደ ደቡብ ሱዳን በመሳብ እና ከናይል ውሃ አጠቃቀም ጋር በተያያዘ ከግብፅ ጋር በማበር ብሔራዊ ጥቅሟን ለመጉዳት እንደሚንቀሳቀሱ ምልክት እየሰጡ ይገኛሉ። ይህም ሲባል፣ በሕዳሴው ግድብ ግንባታ ሒደት ላይ እና በኢትዮጵያ ፖለቲካ ነፍጥ ላነሱ ቡድኖች ከለላና ድጋፍ በደቡብ ሱዳን ግዛት ውስጥ እንዲያገኙ እየተንቀሳቀሱ ናቸው።

ለዚህም ነው ፕሬዝደነት ሙሴቬኒ በደቡብ ሱዳን ፕሬዝደንት ሳልቫኪር እና ከግብፁ አቻቸው ፕሬዝደነት አልሲሲ ጋር በማገናኘት የተለያዩ ምሥጢራዊ ስምምነቶች እንዲኖሩ ለማድረግ የፖለቲካ ሽርሙጥና ውስጥ የተዘፈቁት። ሙሴቬኒ፣ ፕሬዝደንት አልሲሲ ኡጋንዳን በ2016 በጎበኙበት ወቅት ዲፕማሲያዊ አቅማቸውን ለማሳየት ሞክረዋል። ሙሴቬኒ፣ ከግብፁ ፕሬዚዳንት ጉብኝት በኋላ ወደ ጁባ አቅንተው ከሳልቫኪር ጋር በዝግ መምከራቸው ይታወሳል። የፖለቲካ ተንታኞች፣ ለደቡብ ሱዳን ተቃዋሚ ኃይሎች ድጋፍ ይሰጣሉ ተብለው በሁለቱ መንግስታት የሚከሰሱት ኢትዮጵያ እና ሱዳን ላይ ያነጣጠረ ስብሰባ መሆኑ በወቅቱ ገልጸዋል።

ኡጋንዳ ፍላጎቷን ለማሟላት፣ ግብፅን በቀንዱ ሀገራት ፖለቲካ ውስጥ እንድታምስ ያደረገችው ኢትዮጵያን ለማስፈራራት እንደሆነ ይታወቃል። ግብፅም ኢትዮጵያ ከጀመረችው የህዳሴው ግድብ የኃይል ማመንጫ ግንባታ የሚያጓትት ማንኛውም ነገር ከማድረግ እንደማትቦዝን ይታወቃል። ሙሴቬኒ፣ ከምን መነሻ የኢትዮጵያ መንግስት ግብፅን በመፍራት የኡጋንዳን ፍላጎት ያስፈጽማል ብለው እንዳሰቡ ለመገመትም አስቸጋሪ ነው።

የሙሴቬኒ ፍላጎት ከዚያም በላይ የተሻገረ ነው፣ ግብጽ ለኡጋንዳ ድጋፍ የምትሰጥበት አሰራር እንዲኖር እና ኡጋንዳ በበኩሏ ደቡብ ሱዳንን እንደመተላለፊያ በመጠቀም ለሱዳን እና ለኢትዮጵያ መንግሥት ተቃዋሚዎች የጦር መሣሪያና የገንዘብ ድጋፍ ማድረግ፤ እንዲሁም በደቡብ ሱዳን፣ በኡጋንዳ እና በኮንጎ አዋሳኝ አካባቢዎች ወታደራዊ ሥልጠና እስከመስጠት የሚደርስ ድጋፍ ለማቅረብ መወጠናቸውን ከተለያዩ የደህንነት ተቋማት የወጡ መረጃዎች ያሳያሉ።

የኢትዮጵያ መንግሥት በበኩሉ እንደዚህ አይነት ስጋት እንደሌለ በአደባባይ ይክዳል። ይልቁንም፣ ሙሴቬኒ በግብፅ የፖለቲካ ቀውስ በገባችበት ጊዜ ቃል ስለገቡ ነው፣ ከግብፅ ጋር እየመከሩ ያሉት ሲል አስተበብሏል። መሬት ላይ ያለው እውነት ግን፣ ኡጋንዳና ግብፅ ደቡብ ሱዳንን በመጠቀም በኢትዮጵያ እና በሱዳን ላይ ፖለቲካዊ እና ወታደራዊ ሴራዎች እየቀመሩ መሆናቸው ነው።

ግብጽ የደቡብ ሱዳንን ሰላም እንድታጣ በማድረግ የኢትዮጵያን የህዳሴ ግድብ እርምጃ ለመግታት ቢያቅታት እንኳን፣ የቀጠናው ሰላም የኢኮኖሚ ኮሬደር እንዳይሆን ለማድረግ እየሰራች ነው። ይህን የምታደርገው ከሕዳሴው ግድብ የሚመነጨው ኃይል ለማስተላለፍ መሰረተልማት ለመዘርጋት አመቺ እንዳይሆን ነው። ይህን ማድረግ ኢትዮጵያ ካቀደችው የኢኮኖሚ ግብ አንፃር አሉታዊ ውጤት ይኖረዋል። ይህንን ተግባር ለማስፈጸም ተራ የፖለቲካ ድለላ የሚሰሩት፣ ፕሬዝደንት ሙሴቬኒ ናቸው።

የግብጽ እና የኡጋንዳ ጋብቻ መገለጫ ተደርጎ የሚነገረው፤ ግብፅ የኢትዮጵያ ግድብ ፕሮጀክት ለማስቆም ያደረገችው ዓለም አቀፍ የዲፕሎማሲ ጥረት ባለመሳካቱ ነው፤ በተመሳሳይ ኡጋንዳ የደቡብ ሱዳን ተቃዋሚዎችን ለማዳከምና ለማጥፋት ያደረገችው ጥረት በተፈለገው ውጤት ባለመደምደሙ ነው። ሁለቱ ሀገራት ስትራቴጂክ ወዳጅነት እንዳላቸው ለማሳየት እየሞከሩ ያሉት በእነዚህ ነጥቦች ነው። ፍላጎታቸውም የትም አይደርስም ተብሎ የሚተው አይደለም። የኢትዮጵያ መንግስት በአደባባይ ሊሸፍነው የሚሞክረው ችግር ተደርጎም የሚወሰድ አይደለም። በግልፅ ለሕዝብ ሊነገር የሚገባ ፖለቲካዊ ቀውስ መሆኑን መገንዘብ ተገቢ ነው።

የሙሴቬኒ ሴራ አንድ እርምጃ ተደርጎ የሚወሰደው፣ ግብጽ የደቡብ ሱዳኑን ፕሬዚዳንት ወደ ሀገሯ በመጋበዝ ለማግባባትና ዘርፈ ብዙ ግንኙነት ለማድረግ መስማማታቸው ይፋ ማድረጉን ተከትሎ ነው። ግብፅም ታማኝ ወዳጅ መሆኗን ለመግለጽ ጊዜ ሳታባክን፣ ተቃዋሚዎቻቸውን በአየር ጥቃት ደብድባለች። ሳልቫኪርም፣ በቀላሉ ድጋፍ የሰመረላቸው ይመስላል። ግብፅ በኡጋንዳ ሴራ ጦር መሳሪያ በማቅረብ ሳልቫኪርን እየረዳች ነው።

ግብጽ በበኩሏ እየጎተጎተች ያለችው፣ የደቡብ ሱዳን መንግሥት በኢትዮጵያ ፖለቲካ ነፍጥ ላነሱ ኃይሎች የሽምቅ ውጊያ የሚያደርጉበት ቦታዎች እንዲሰጣቸው ነው። ሳልቪኪር በአደባባይ ባያደርጉትም፣ ባለፈው ሳምንት ስድስት የአርበኞች ግንባር አባላት ጦር መሣሪያ ሲገዙ ጁባ ላይ መያዛቸው መዘገቡ የሚዘነጋ አይደለም።

የግብፅ ፖለቲከኞች በአደባባይ የቆመውን የህዳሴው ግድብን ሥራዎች ለማስተጓጓል፣ ቀጠናውን ማመስ እንዴት እንደመፍትሄ እንደወሰዱት ግልጽ አይደለም። ምክንያቱም ወደፊት ነፍጥ አንስቶ ኢትዮጵያን የሚስተዳድረው የፖለቲካ ኃይል ቀርቶ፣ አሁን ኢትዮጵያ የሚያስተዳድረው ገዢው ፓርቲ እንኳን ከግብፅ ጋር ቢሻረክ የህዳሴው ግድብ ግንባታን መቀልበስ አይችልም። ደግነቱ፣ ሕዝባዊነት ያላቸው ትውልዶች በመሆናቸው በሀገራቸው ላይ አያሴሩም። ግንባር ቀድም ሆነው የተራመዱትም ለዚሁ ነበር። በርግጥስ፣ በቀጠናው ራሷን ለመለኮስ የምትፈልገው እሳት፣ ግብፅ ተመልሶ እንደማያቃጥላት እንዴት እርግጠኛ እንደሆኑ ሌላው ጥያቄ የሚያስነሳ ጉዳይ ነው።

ግብፅ፣ ከናይል ውሃ ጋር በተያያዘ ከዚህ በፊት ጅቡቲን እና ሶማሌን አረቦች ሳይሆኑ ዓረብ ሊግ እንዲገቡ አድርጋለች። የኤርትራ ጉዳይ አልተሳካለትም። ዛሬ ላይ ደግሞ ደቡብ ሱዳን የአረብ ሊግ ለማድረግ የማትሰራበት አጋጣሚ አይኖርም።  ሳልቨኪር በበኩላቸው ከአረብ ሊግ ጋር ለመስራት ዝግጁ መሆናቸው አስታውቀዋል።

የደቡብ ሱዳን ሰላም መናጋት ከማንም በላይ የሚጎዳው ኢትዮጵያ እና ኡጋንዳን ነው። ይህም በመሆኑ ሁለቱም ሀገራት ትልቁን የደቡብ ሱዳን ሰላም በመመልከት ሁሉነም አሳታፊ የሆነ መንግስት በደቡብ ሱዳን እንዲመሰረት መስራት ላይ ቢያተኩሩ ተመራጭ ነው።

ሙሴቬኒ በኢትዮጵያ ላይ የተንሸዋረረ አመለካከት ሊፈጠርባቸው የቻለው ምንአልባት፣ የኢትዮጵያ ውስጣዊ ፖለቲካ በከፍተኛ አለመረጋጋት ውስጥ ይገኛል የሚል ትንታኔ ይዘው፤ ወይም በቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ጊዜ የነበረው የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ ተፅዕኖ አሁን ላይ የለም ከሚል ሊሆን ይችላል። ይህንን የሙሴቬኒን ሸውራራ አመለካከት የወለደውን የፖለቲካ ሽርሙጥና አካሄድ በፈጣን ተግባር ማምከን ከአመራሩ የሚጠበቅ ነው ተብሎ ይወሰዳል።¾

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
412 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 830 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us