ግንቦት ሃያ የብሔር ፖለቲካውና የኢትዮጵያ አንድነት

Friday, 26 May 2017 19:04

ሃያ ስድስተኛው የግንቦት ሃያ በዓል ሊከበር ጥቂት ቀናት ይቀሩታል። ኢህአዴግ ይህችን ሀገር በመንግስትነት ማስተዳደር ከጀመረ ሩብ ክፍለ ዘመን ያለፈ በመሆኑ ባለፉት 26 ዓመታት ምን ተከወነ? ምንስ ቀረ ብሎ ለመነጋገር የሚያስፈልግበት ጊዜ ቢኖር አሁን ነው። ኢህአዴግ ባለፉት ሁለት አስርተ ዓመታት ከሄደበት ኢትዮጵያዊነት አንፃር ጥቂት ማለት ይቻላል። በኢህአዴግ አተያይ የዛሬ ሃያ ስድስት ዓመት በፓርቲው መተዳደር የጀመረችው ኢትዮጵያ አዲሲቷ ኢትዮጵያ ናት። ከዚያ በፊት የነበረችው ኢትዮጵያ ከህዝቦች አንድነት ይልቅ በግዛት አንድነት የተዋቀረች አገር ስለነበረች የብሄረሰቦች እስር ቤት ናት የሚል ስያሜ ተሰጥቷታል። በመሆኑም የቀደመው ኢትዮጵያዊ የአንድነት ቅኝቱ በአዲሱ የብሄረሰቦችን መብት እስከ መገንጠል ድረስ በደነገገው ህገ መንግስታዊ አንቀፅ እንዲተካ ተደረገ።

 

ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ ደረጃ የመገንጠልን መብት በህገ መንግስቷ በማረጋገጥ በታሪክ ሁለተኛ ሀገር ተደርጋ የምትጠቀስ ናት። ከዚህ ቀደም የመገንጠል መብትን በህገ መንግስቷ ያረጋገጠች ብቸኛ ሀገር የስታሊኗ ሩስያ ነበረች። ስታሊን የብሄረሰቦችን ጥያቄ በሀገር ደረጃ እንዴት መፍታት ይችላል? በሚለው ቀመሩ “የራስን እድል በራስ መወሰን” በሚለው ዓለም አቀፍ የዲሞክራሲ መብት ላይ “እስከመገንጠል” የሚለውን ቃል በመጨመር ሀሳቡን ለጠጠው።


ይህች “እስከመገንጠል” የምትለው ቃል አቀላል አልነበረችምና እየዋለ እያደረ ሲሄድ የተሰጠውን መብት ተጠቅመው ከዋናው ግዛት መነጠል የሚፈልጉ ግለሰቦችንና ቡድኖችን መነቃቃት ጀመሩ። በጊዜውም ፊላንድና ፖላንድ ከዋናዋ ሩስያ ሲገነጠሉ፤ ሩስያም ቀላል በማይባል የእርስ በእርስ ጦርነት ውስጥ አልፋለች። ከዚያ በኋላም በነበረው የአዲሱ የሶቪየት ህብረት መስረታ ላይ ይህ አንቀፅ በመቀጠሉ ሀገሪቱ በቀዝቃዛው የዓለም ጦርነት ማብቂያ ሙሉ ህልውናዋ አክትሞ የሶቪየቱ አባላቱ በየራሳቸው የየግላቸውን መንግስት በመመስረት ወደ ቀድሞ ሉአላዊ ህልውናቸው ተመለሱ። በመጨረሻም የሩስያ ፌደሬሽን ብቻዋን መቅረት ግድ ሆኖባታል።


ከሩስያ ፌደሬሽን መቅረት በኋላ ሀገሪቱ በአዲስ ህገ መንግስት እንድትተዳደር ሲደረግ፤ ይህ ስታሊናዊ አንቀፅም ቀሪ እንዲሆን ተደርጓል። ከዚያ በኋላ ከሩስያ ግዛት ለመገንጠል የሞከረችው ቺቺኒያ በሀይልና በከባድ ደም መፋሰስ በሩስያ ስር ሆና እንድትቀጥል ተደርጓል። ከሶቪየት ህብረት ማክተም በኋላ የመገንጠል መብትን በብቸኝነት በህገ መንግስቷ ያካተተች ሀገር ኢትዮጵያ ናት። ኢትዮጵያ የመገንጠል መብትን አፅድቃ ፖለቲካዋን በአዲስ መልክ እንድትቃኝ በተደረገባቸው ዓመታት በበርካታ ውጣ ውረዶች ውስጥ አልፋለች። የኢትዮጵያ ህገ መንግስት ይህንን መብት ያለገደብ ከማስቀመጥ ባለፈ ሀገሪቱን በብሄረሰቦች ፊደራላዊ የግዛትና መንግስት አወቃቀር ሲያስቀምጣት ሁለት ወገኖች በግልፅ ነጥረው ወጥተዋል። በአንድ መልኩ የሀገሪቱ አንድነት በነበረበት እንዲቀጥል የሚፈልጉ ሲሆኑ በሌላ አቅጣጫ ደግሞ አዲሱ የብሄር ቅኝት ፖለቲካ እንዲሰርፅ የሚፈልጉ ናቸው። በሁለቱም ኃይሎች መካካል ከባድ የሀሳብና ጥላቻ የተቀላቀለበት የፖለቲካ ትግል ተካሂዷል። በዚህ በኩል ኢህአዴግን መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች፣ ፕሬሶች፣ በርካታ ዜጎችና ምሁራን አምርረው ታግለውታል። ኢህአዴግ በአንፃሩ እነዚህን ኃይሎች አምርሮ በመታገል ከፖለቲካው ሜዳ ገፍትሮ ለመጣል ብዙ ጥሯል።


አዲሲቷን ኢትዮጵያ ባስቀመጠው አቅጣጫ ለመቅረፅም ብዙ ርቀት ተጉዟል። ይህ የሄደበት ርቀትም በልዩነት ውስጥ ያለውን አንድነት ከማሳየት በላይ በአንድነት ውስጥ ያለውን ልዩነት የበለጠ አጉልቶ በማሳየቱ ላይ በማተኮሩ በመሰተመጨረሻ ከ26 ዓመታት በኋላ የታየው ውጤት የሀገሪቱን የአንድነት ምሶሶ የሚነቀንቅ ሆኖ ታይቷል። በቅርቡ በኦሮሚያና በአማራ ክልሎች የታዩት ህዝባዊ አመፆች የዚህ እውነታ በቂ መሳያዎች ተደረገው የሚወሰዱ ናቸው። ዛሬ ብሄርተኝነት የገመና መሸፈኛ የውስጥ ልብስ ተደርጎ ሲወሰድ ኢትዮጵያዊነት በአንፃሩ ሲበርድ ከላይ ጣል የሚደረግ የክት ልብስ ተደርጎ የሚታይበት ደረጃ ላይ ነው።


በተለይ ከ1993 የኢህአዴግ ተሀድሶና ከ1997 ሀገራዊ ምርጫ በኋላ በኢህአዴግ በኩል ሁሉም ነገር እየከረረ ሄደ። ቀደም ብሎ በነበሩት ዓመታትም የሥና ዜጋ ትምህርቶች በብሄህርተኝነት ላይ ባተኮረ መልኩ እንደቀረፁ ተደረገ። በከፍተኛ ተቋማት ደረጃ ይሰጥ የነበረው የታሪክ ትምህርት ቆመ። የታሪክ ዲፓርትመንቶች ሳይቀሩ ተዘጉ። ከፓርቲው አስተሳሰቦች ጋር አይሄዱም የተባሉ ምሁራን ተገለሉ፤ ቀስ በቀስም አንድ በአንድ ተሰናበቱ።


የሁሉም ነገር ማሰሪያና መፍቻ ብሄረሰብና ብሄር ብቻ ሆነ። ባንኮችና ኢንሹራንሶች ሳይቀሩ የብሄር አቅጣጫን ተከትለው መፍሰስ ጀመሩ። አደረጃጀታቸውና አገልግሎታቸውም የሰራተኛ ሹመታቸውና የሰው ሀይል ቅጥራቸውም ይሄንኑ የብሄር መሳሳብን የተከተለ ሆነ። እንኳን ሌላ ደንበኛው ገንዘቡን የሚቆጥበው የብሄረሰቡ ባለአክስዮኖች በተኮለኮሉበት ባንክ እየሆነ ሄደ። የእምነት ተቋማት ሳይቀሩ የብሄር ቡድንተኝነቱ ሰለባ ሆኑ።


የብሄር ፖለቲካው ጉዳዩን ሲያቀነቅኑ ከነበሩት ፖለቲከኞች አልፎ በዜጎች ደም ውስጥ መፍሰስ ብሎም መንተክተክ ጀመረ። “ከህብረ ብሄር እኛነት” ይልቅ “የብሄር እኔነት” አስተሳሰብ እየዳበረ ሄደ። ሁሉም በየብሄሩ ክልል ልሁን፣ ዞን ልሁን የሚል ጥያቄን ማንሳት ጀመረ። ማንነቴ አልታወቀም፣ ደንበሬ ተነካ የሚሉትና የመሳሰሉት ከማንነት ጋር የተያያዙ ጥያቄዎች ከጊዜ ወደ ጊዜ እየበረከቱ መሄድ ጀመሩ። በአንድነት ውስጥ ልዩነት እንደዚሁም በልዩነት ውስጥ አንድነት መኖሩ ቢታወቅም ባለፉት ሁለት አስርት ዓመታት በአንድነት ውስጥ ስላለው ልዩነት እጅግ ፅንፍ በወጣ መልኩ ሲሰበክ በመቆየቱና በአሰራርም ሳይቀር ወንዜነት፣ክልላዊነትና ብሄርተኝነት በኢትዮጵያዊነት ላይ ፍፁም የበላይነት እንዲወስድ በመደረጉ ኢትዮጵያ የምንላት ሀገር መቆሚያ ምሶሶ በርዕደ መሬት የተመታ ህንፃ ያህል ክፉኛ ተናጋ።


ትላንት በተወሰኑ ፖለቲከኞች ሲቀነቀን የነበረው ብሄርተኝነት በብዘዎች ልብ ውስጥ በቂ መደላድልን ያገኘበት ደረጃ ላይ በመደረሱ ቀላል የማይባለው ዜጋ በዚህ የብሄር ፖለቲካ ገመድ ጉተታ ውስጥ እንዲገባ አደረገው። ዛሬ አንድ ዜጋ በኢትዮጵያዊነት ይቅርና ተፈጥሯዊ በሆነው በሰው ማንነቱ መመዘን ወደ ማይችልበት ደረጃ ላይ ደርሷል። የማንነት ልኬቱ ተወላጅነት፣ የሆነ ብሄር ቋንቋ ተናጋሪነትና የብሄር አባልነት ሆኖዋል።


ባለሀብት መዋዕለ ነዋዩን ሲያፈስ ኢንቨስትመንቱን የሚያካሂደው በብዙ መልኩ አዋጪ ነው ብሎ በገመተው ዘርፍና ቦታ ነው። ሆኖም ቀላል የማይባለው ባለሀብት ከዚህ የቢዝነስ መርህ ውጪ ሀብቱን የሚያፈሰው አንድም በአዲስ አበባና ዙሪያዋ፤ ከበዛም በአዲስ አበባ ጂቡቲ መስመር እስከ አዳማ አካባቢው ባለው ኮሪደር ነው። ከዚህ ውጪ ሀብቱን የግብዓት ምርትን ተከትሎ ከክልሉ ውጪ ማፍሰስ የሚፈለገው ባለሀብት እጅግ ጥቂት ነው። ክልላዊነት በከረረበት ብሄርተኝነቱም ጫፍ እየረገጠ በሄደበት ሁኔታ ክልል ዘለል በሆነ መልኩ ባለሀብቶችን ማፍራት እየከበደ እንደሚሄድ ግልፅ ነው። በኢትዮጵያዊነት ማንነታቸው ክልል ዘለል በሆነ መልኩ ሀብት ያፈሩ ዜጎች ሀብታቸው በአንድ ጀምበር ወድሞ የህግ ጥበቃና ከለላ እንኳን ሳያገኙ የቀሩባቸው አጋጣሚዎች እጅግ ብዙዎች ናቸው።


ከ1983ቱ ለውጥ በኋላ ራሳቸውን በኢትዮጵያዊነት ብቻ መቁጠር የሚፈልጉ ሰዎች መቆሚያ ወለል እንዲያጡ ተደረገ። ዜጎች መታወቂያቸው ላይ የግድ የብሄር ማንነታቸው እንዲካተት ተደረገ። የብሄር ማንነት በኢትዮጵያዊ ህብረ ብሄራዊነት ላይ ሙሉ የበላይነትን እንዲወስድ ሁሉም ነገር ተመቻቸ። ስለአንድነት የሚያወሩ፣የሚናገሩና የሚሰብኩ ሁሉ “የቀደሙ ስርዓቶች ናፋቂዎች” በሚል በአንድ ቅርጫት ውስጥ ተከተው ተፈረጁ። “አዲሲቷ ኢትዮጵያ” የሚለው የብሄር ቅኝት ኢትዮጵያዊያን በዘመናት ሂደት ውስጥ የገነቧቸውን የጋራ እሴቶች ገሸሽ በማድረግ ኢትዮጵያን በብሄርና ብሄረሰቦች ድምር ቀመር ብቻ በማድረግ አስልቶ አስቀመጣት።


አሁን በክፉም በደጉም ለምንጣላባትና ለምንታረቅባት ሀገር መመስረት የጣሉ ብሎም በዘመናት የታሪክ ቅብብሎሽ ውስጥ በብዙ የወጡና የወረዱ ነገስታትና አባቶች “አንድነትን በጉልበት ጨፍልቀው ያመጡ” በሚል አፅማቸው ይወቀስና ይወገዝ ጀመር።


ማንም በዓለም ላይ ያለ በሀገር ደረጃ ሲጠነሰስ በዜጎች ስምምነት አልተመሰረተም። አሁን በዓለም ላይ ያሉ ከሁለት መቶ ያላነሱ ሀገራት የየራሳቸው ሀገራዊ የአመሰራረት ታሪክ ያላቸው ናቸው። በርካታ ሰፊ ግዛት የያዙ ሀገራት የየጊዜው ሃያላን የመስፋፋትና የኢምፓየር ውጤቶች ናቸው። ኢትዮጵያም ከእነዚህ ሀገራት የተለየ ታሪክ የላትም።


ሆኖም የየትኛውም ሀገር መንግስታት የተረከቡትን ሀገር ወይንም ከመስራቾቹ ተቀብለው ያቆዩትን ነገስታት ወደኋላ ሄደው ሲያወግዙና ሲኮንኑ አልታየም። ዛሬ በዲሞክራሲ ባህል ግንባታ ጫፍ የደረሱ ሀገራት ተደርገው የሚወሰዱት የአውሮፓ ሀገራትና አሜሪካ የዚህ ማሳያ ተደርገው ሊወሰዱ የሚችሉ ናቸው።


አሜሪካ ከእንግሊዝ ቅኝ አገዛዝ ነፃ ከወጣች በኋላ 13 ነፃ የወጡ ግዛቶች በአንድ ላይ ተስማምተው መሰረቷት። ሌሎች ግዛቶችም ነፃ እየወጡ ሲሄዱ አዲስ የተመሰረተውን ግዛት እየተቀላቀሉ ሄዱ። ዲሞክራሲያዊ ስርዓቱ ማቆጥቆጥ በጀመረበት ወቅት ግን በአሜሪካ በሁለት አቅጣጫ የጎሉ ልዩነቶች መታየት ጀመሩ። የሰሜን ግዛት የሆኑት የፌደራሉ አባል ሀገራት በኢንዱስትሪው ዘርፍ ሲበለፅጉ ደቡቦቹ በአንፃሩ ገና ግብርናው ላይ ዳዴ ነበር።


ሰሜኖቹ ከግብርና የኢኮኖሚ የበላይነት ወደ ኢንዱስትሪ የኢኮኖሚ ዘርፍ ማደጋቸውን ተከትሎ ብዙም የባሪያ ጉልበት የማያስፈልጋቸው መሆኑ በመረጋገጡ በሀገር አቀፍ ደረጃ የባሪያ ነፃነት እንዲታወጅ አጥብቀው መከራከር ጀመሩ። በአንፃሩ የደቡብ አሜሪካ ግዛት ነጮች ደግሞ ገና ከግብርናው ኢኮኖሚ መሰረት የተላቀቁበት ሁኔታ ስላልነበረ በሀገር አቀፍ ደረጃ የባሪያ ነፃነት መታወጁን በመቃወም መገንጠልን በአማራጭነት መውሰድን መረጡ።


ሁኔታው የበለጠ እየከረረ የሄደው የባሪያ ነፃነትን አጥብቀው የሚደግፉት 16ኛው የአሜሪካ ፕሬዝዳንት አብራሃም ሊንከን ተመርጠው ወደ ስልጣን ማምራታቸውን ተከትሎ ነበር። የሪፖብሊካን ወኪል የነበሩት አብራሃም ሊንከን ፕሬዝዳንታዊ ምርጫውን አሸንፈው ገና ስልጣን ሳይረከቡ በጊዜው ከነበሩት 34 የአሜሪካ ግዛቶች ውስጥ ሰባቱ የደቡብ ግዛቶች ከአሜሪካ ህብረት መገንጠላቸውን አስታወቁ።


በዚህም ወቅት በተገንጣዮቹና በአንደነት አቀንቃኞች መሃል ጦርነት ተከፈተ። ይህም ከ1861 እስከ 1865 የቆየ የእርስ በእርስ ጦርነት በታሪክ የአሜሪካ የእርስ በእርስ ጦርነት (American Civil War) በመባል የሚታወቅ ሲሆን፤ በዚህ የእርስ በእርስ ጦርነትም ከ620 ሺህ እስከ 750 ሺህ የሚሆን ህዝብ እንዳለቀ ይገመታል። ጦርነቱም በአብርሃም ሊንኮሎን የሚመራው የአንድነት ሀይል በአሸናፊነት በመጠናቀቁ የመገንጠል ጥያቄ ያነሱ ኃይሎች ታሪክ በዚያው አክትሟል።


አስራስድስተኛው የአሜሪካ ፕሬዝዳንት አብራሃም ሊኒኮሎን ታሪክ በዚህ የአንድነትና መገንጠል ግብግብና ደም መቃባት አክትሟል። ፕሬዝዳንቱ በጊዜው በመሰላቸው መንገድ የአሜሪካንን አንድነት አስጠብቀዋል። ዛሬ አሜሪካዊያን ወደ ኋላ ሄደው ፕሬዝዳንት አብራሃም ሊንከንን ሲያወግዙ አልታየም። ወይንም ደግሞ በታሪክ አጋጣሚ በተፈጠረው ጦርት ሰማዕት ለሆኑ ዜጎች አብራሃም ሊንከንን በማውገዝ ሀውልት ሲያቆሙም አልታዩም።


ይልቁንም የሊንከንን በበጎነት የሚያስታውሱ በርካታ መታሰቢያዎች በስማቸው የተሰየሙ መሆኑን የዛሬው የአሜሪካ እውነታ ይነግረናል። ከእነዚህ የሊንከንን መታሰቢያዎች መካከልም አንደኛው በዋሽንግተን ዲሲ የሚገኘው ግዙፉ የፕሬዝዳንቱ መታሰቢያ ሀውልት (Lincoln Memorial Monument) ይገኝበታል። እንደውም ፕሬዝዳንቱ የአሜሪካንን የመገነጣጠል አደጋ ታድገዋል በሚል ከአሜሪካ መስራች አባቶች (Founding Fathers) ተርታ የሚመድቧቸውም አሉ።


የጀርመን የጣሊያንም ሆነ የበርካታ የአውሮፓ ሀገራት ታሪክ ከዚህ የተለየ አይደለም። ታሪክን ዘወር ብሎ ማገላበጡ መልካም ነው። አሜሪካኖች አብርሃም ሊኒኮለንን እንደዚሁም ጀርመኖች ቢስማርክን ሲከሱና የታሪክ ተወቃሽ አድርገው ያወጉበትበት ሁኔታ የለም። በኢትዮጵያ የፖለቲካ አውድ ግን ይህ ሊታይ አልቻለም።


ለህትመት የሚበቁት መፃህፈት፣ በየጊዜው ለስርጭት የሚበቁት የመገናኛ ብዙኋን ውጤቶች መቶ ዓመታትን ወደኋላ ሄደው የታሪክ ቁርሾን የሚያጠነጥኑ ናቸው። እነዚህም የታሪክ እንኪያ ሰላንታዎች አዲሱ ትውልድ ከትውልዶች በፊት በተፈፀመ ድርጊት አዲሱ ትውልድ ቂም ቋጥሮ ጎራ በመለየት በጥላቻ እንዲፋለም አድርጎታል። ቂም ሰንቆም ለመጪው ትውልድ የማስቀመጥ አዝማሚያም ይታይበታል። ይህ እንደ ሀገር የኢትዮጵያን ህልውና የሚፈታተን ነው።


እነዚህ በዲሞክራሲ ሂደት በብዙ እጥፍ ወደፊት የተራመዱ ሀገራት የየዘመኑን የሀገራቸውን ውጣ ውረድ የሚለኩት በዚያው በዘመኑ መለኪያ እንጂ እነሱ ባሉበት ዘመን አይደለም። አውሮፓ ሰውን ከአንበሳ ጋር ታግሎ ሲበላና ሲቦጫጨቅ በሰገነታቸው ላይ ቁጭ ብለው ይዝናኑ የነበሩ ነገስታትን ያፈራ አህጉር ነው። ሆኖም ያ የብዙ ዘመናት የጨለማው ዘመን ታሪክ ግን በ21ኛው መቶ ክፍለ ዘመን መነፅር እየታየ የእነዚያ ሰዎች አፅም አልተወገዘም። ያ ዘመን ያንን ፈቅዷልና። በሁለተኛው የዓለም ጦርነት በሄሮሽማና ነጋሳኪ በአሜሪካ የአቶሚክ ቦምብ ጥቃት ደርሶባቸው በመቶ ሺዎች የሚቆጠር ህዝብ ያለቀባቸው ጃፓናዊያን በጦርነቱ ማግስት ደም ከተቃቧቸው ጋር የሰላም ስምምነት በመፈራረም ለበርካታ አስርተ ዓመታት በአለም ሁለተኛ ሆኖ ሲመራ የቆየውን ግዙፍ ኢኮኖሚ መገንባት የቻሉት በአሜሪካ እገዛ ነበር።


ጃፓናዊያን የኋላውን ረስተው ከአሜሪካ ጋር ስለመጪው ጊዜ ለማሰብ ጊዜ አልፈጀባቸውም። የዚያን ጊዜዎቹ ትውልዶች የኋላውን እያስታወሱ በአሜሪካዊያን ላይ በቂማቸው ቢቀጥሉ ኖሩ ዛሬ የደረሱበት ደረጃ ባልደረሱ ነበር። አሜሪካ ለጃፓን የኢኮኖሚ እድገት እንዴት መስፈንጠሪያ ማማ ሆና እንዳገለገለች ታሪክን ወደ ኋላ ሄዶ ማገላበጥን ይጠይቃል። መጪውን ጊዜ በጋራ ብሩህ ለማድረግ ሲባል በጋራ ታሪክ ክፉንም ደጉንም ያሳላፉ ብሎም በደምና በዘር ሀረግ የተሳሰሩ ህዝቦች ይቅርና ባዕዳን ሳይቀሩ በጎ በጎውን እንደሚያስቡ አሜሪካና ጃፓን በጎ ማሳያ ናቸው። ስድስት ሚሊዮን የሚሆን ዜጋ በናዚ ጭፍጨፋ ያለቀባቸው እስራኤላዊያን የዛሬውን ጀርመኖች በጥላቻ አይን አያዩም።


ኢትዮጵያዊያን ነገስታትም ቢሆኑ ጊዜው በፈቀደውና እነሱ በመሰላቸው መንገድ አሁን የተረከብናትን ሀገር ፈጥረዋል። ይህች ሀገር ባለችበት ለቀጣይ ትውልድ እንድትተላለፍም ከወራሪዎችና ከቅኝ ገዢዎች ጋር ተፋልመዋል። በጊዜው ዙሪያዋን ከከበቧት ሃያላን የአውሮፓ ቅኝ ገዢዎችን በመቋቋም የታወቀ የደንበር ችካል እንዲተከል አድርገዋል። በውስጥ የተነሱባውን የዙፋን ባላንጣዎች በሀይል ጨፍልቀዋል። አቅማቸው በፈቀደ ግዛታቸውን አስፋፍተዋል። በጊዜው በቀሪው አለም ሲደረግ የነበረውን ሀሉ አድርገዋል። ከዚህ የተለየ ታሪክ የላቸውም። ጥፋተኛ ሊባሉ ቢችሉ እንኳን የጥፋተኝነት መለኪያቸው ሊሆን የሚገባው በነበሩበት ዘመን መለኪያ እንጂ በ21ኛው መቶ ክፍለ ዘመን የስልጣኔ ደረጃ አይደለም። በ18ኛውና በ19ኛው መቶ ክፍለ ዘመን የህዝብ ሉአላዊነት፣ የህግ የበላይነት፣ ሰብአዊና ዲሞክራሲያዊ መብቶች የመንግስትና የሀይማኖት መለያየትና የመሳሰሉት በኢትዮጵያ አይደለም በአውሮፓም የሚጠበቅ አልነበረም። አለም አቀፍ ሰብአዊ መብት ድንጋጌዎችና ቃልኪዳኖች ሳይቀር በሰነድ ተደግፈው ተግባራዊ መሆን የጀመሩት እኮ የሁለተኛውን የዓለም ጦርነት መጠናቀቅ ተከትሎ የዛሬ ስልሳና ሰባ ዓመት አካባቢ ነው። ከዚያ በፊት የዓለም ታሪክ የነገስታት ታሪክ ነው። ከአሜሪካ ውጪ ባሉ ሀገራት ህዝብ ተገዢ ከዚህ ያለፈ እድል ፈንታ አልነበረውም። ኢትዮጵያም ከአለም የተለየ ታሪክ ሊኖራት አይችልም። በአለም የነበረው በኢትዮጵያ ነበር።


እነዚያ ባለፉት ሁለት አስርት ዓመታት ልዩነትን ትኩረት አድርገው የተዘሩት ዘሮች ዛሬ በሚገባ ፍሬ አፍርተው ኢህአዴግን እንደ ፓርቲ ሳይቀር መፈተን ጀምረዋል። ከሀገራቸው ጥቅም ይልቅ የፓርቲያቸውን ጥቅም ያስቀድማሉ እየተባሉ የሚታሙት ጥቂት የማይባሉ የአህአዴግ አመራሮችና አባላት የብሄር ጠቀስ ጎራው እየከረረ ሲመጣ ታማኝነታቸውን ከፓርቲነት ወደ ብሄር ማንነት አዙረውታል። ይህም ሁኔታ በውስጥ የፓርቲ ሚስጥር ዝግነት የሚታወቀውን ኢህአዴግ ሚስጥሮቹ ቀድመው እያፈተለኩ አደባባይ ላይ እንዲውሉ አድርጓቸዋል። ይህም በብሄር የአባል ድርጅቶቹ መካከል የእርስ በእርስ መጠራጠር ውስጥ እንዲገቡ ያደረጋቸው መሆኑን የራሱ የኢህአዴግ ሰነድና የቅርቡ የጠቅላይ ሚኒስቴር ኃይለማርያም ደሳለኝ ጋዜጣዊ መግለጫ አመላካች ነው። የአባላቱ ፓርቲያዊ ታማኝነቱ በብሄር ገመድ ጉተታ ውስጥ መግባቱ ኢህአዴግ እንደ ፓርቲ በራሱ የብሄር ፍልስፍና መጠለፉ አይቀሬ መሆኑን የሚያሳይ ምልክት ሆኗል።


ዛሬ የፓርቲው አባላት በማናቸውም አኳኋን በህግ ሲጠየቁ በብሔረሰባቸው ማንነት ጥቃት እንደደረሰባቸው አድርጎ ለማቅረብ የመሞከሩ ጉዳይ ብሔረሰባዊ አስተሳሰቡ የት ድረስ በርቀት ተጉዞ የአስተሳሰቡ አቀንቃኝ የሆነውን ፓርቲ ሳይቀር በቀጣይ ቀላል በማይባል መጠላለፍ ውስጥ እንደሚከተው ግልፅ ማሳያ ሆኗል። እነዚህ ሁሉ ማሳያዎች ከሀገር ወደ ፓርቲ የወረደው ቡድናዊ ብሄርተኝነት አንድ ቦታ መፍትሄ ካልተበጀለት በስተቀር ቀጣይ ሂደቱን ፈታኝ የሚያደርገው ይሆናል። ኢህአዴግ ግን ይሄንን የብሄር ፖለቲካ መጠላለፍ በትምክህትና በጠባብነት ጎራ በመፈረጅ ነገሩን ቀለል አድርጎ ማየቱን የመረጠ ይመስላል።

ይምረጡ
(1 ሰው መርጠዋል)
405 ጊዜ ተነበዋል

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us