ቻይና ልዕለኃያል ሀገር ለመሆን እየሰራች ይሆን?

Friday, 26 May 2017 19:07

በሳምሶን ደሣለኝ

 

የቻይና ኮሚኒስት ፓርቲ እና ፕሬዚደንት ዢ ጂንፒንግ የቻይናን የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ አሁን ያለውን የጂኦፖለቲካ መልካምድርን በአዲስ መልክ ለመፃፍ ያስችላል ያሉት ግዙፉ ፕሮጀክት ይፋ አድርገዋል። ዢ ይፋ ያደረጉት “New Silk Road” በሃያ አንደኛው ክፍለዘመን የባህር መርከብ ዝመና እና የኢኮኖሚ ትስስሮሽን (Economy belt) የሚያካተትተው እና አራት ቢሊዮን ሕዝብ እና አንድ ሶስተኛ የዓለምን ሃብት መጠን የሚያንቀሳቅስ ግዙፍ ፕሮጀክት ነው። ይህ የፕሮጀክት እቅድ መሰረት ያደረገው፤ የኃይል አቅርቦት፣ የደህንነት እና የገበያ ፍላጎት ላይ መሆኑ ተገልጿል።


እነዚህ የእቅዱ አንቀሳቃሽ ሞተሮች ከአንዱ ጫፍ ወደ ሌላኛው ጫፍ ሲነካኩ እንደሽመና እርስ በእርሱ የሚናበብ የትራንስፖርት መተላለፊያ እና የወደቦች አገልግሎት አቅርቦት በጣምራ የንግዱ እንቅስቃሴን ከፍ ማድረግ፣ የደህንነት ይዞታን ማጠናከር እና ስትራቴጂክ እርዳታ ለመስጠት የሚያስችል እድል ይፈጥራል ተብሎ ይጠበቃል። ይህ የሜጋ የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ ኤዢያ፣ አውሮፓ እና አፍሪካ የሚደርስ መሆኑን ሰነዶች ያሳያሉ።


የዢ ጂፒንግ ራዕይ ራሮት የበዛበት ነው ቢባልም፣ በቻይናን እና በአውሮፓ መካከል ያለውን ግንኙነት የሚያሻሽል እና ከቻይና አጎራባች ሀገሮች ጋር ከተቀረጸው የቻይና ፖሊሲ ጋር ተመጋጋቢ መሆኑ ማጣቀሻዎች ያሳያሉ። ይህ በትራንስፖርት መተላለፊያዎች ላይ የሚፈሰው የቻይና የኢንቨስትመንት እቅድ፤ አዲስ የአየርመንገድ አገልግሎት፣ የባቡር አገልግሎት እና የመንገድ መሰረተ ልማት ግንባታዎችን ያካትታል።


ዢ ይህንን የ“Silk road” እቅዳቸውን ይፋ ያደረጉት በሴፕቴምበር 7 ቀን 2013 በአስታና ከተማ፣ ካዛክስታን ነበር። በኤዢያ ማዕከላዊ ግዛቶች ጉብኝት በሚያደርጉበት ጊዜ፣ እየተንገዳገደ ያለውን የአካባቢውን ኢኮኖሚ በቻይና ኢንቨስትመንት ወደ ተሻለ ደረጃ ከፍ ለማድረግ ያለመ እቅድ መሆኑ ገልጸውም ነበር። ዢ የዚህን እቅድ ስያሜን “Economic Belt” ሲሉ ጠርተውታል። ባለሙያዎች ይህንን ስያሜ የተሰጠው፣ ሒላሪ ክሊንተን “New Silk Road” በሚል በጁላይ 20 ቀን 2011 በሕንድ ቼናይ ከተማ ካደረጉት ንግግር የተለየ መሆኑን ለማሳያት እንደሆነ ይናገራሉ። በርግጥም በእቅድ ደረጃ በጣም የተለያየ ነው። የሒላሪ እቅድ የነበረው፣ የአፍጋኒስታንን ኢኮኖሚ ለማገዝ ከሰሜን-ደቡብ ኤዢያ ሀገሮች ጋር በኢኮኖሚ ኮሪደሮች ማስተሳሰር ነበር፤ የቻይና መጠነ ሰፊ የኢኮኖሚ ትስስሮሽ ዕቅድ ነው።


የቻይና ፖሊሲ አውጪዎች “Silk Road” የሚለውን መገለጫ ታሪካዊ የባለቤትነት ጥያቄን ያነሳሉ፣ “የእኛ” ነው ይላሉ። በታሪክ አንድ ሲልክ ሮድ የለም፣ በጣም በርካታ መሆናቸው ነው የሚነገረው። በቅርብ ባሉት ጊዜዎች ሲልክ ሮድ የሚለውን ቃል የተጠቀመው በዓለም ዙሪያ እየተዘዋወረ ጥናት የሚያደርገው ጀርመናዊው ፈርዲናንድ ቮን ሲሆን፣ ወቅቱም በ18ኛው ክፍለ ዘመን አጋማሽ አከባቢ ነው። ይኸውም፣ በ1868-1872 ወደ ቻይና ግዛት ጥናት ለማድረግ የተንቀሳቀሰውን ቡድን በመራበት ጊዜ፣ የተጠቀመበት መግለጫ ነው። የቀድሞ የአሜሪካ መንግስት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሒላሪ ክሊንተንም ሲልክ ሮድ የሚል ቃል መጠቀማቸው፣ የቻይና ከፍተኛ ባለስልጣናትን ግራ ማጋባቱን ይነገራል። በተለይ የወ/ሮ ሒላሪ ቃል አጠቃቀም የአሜሪካ የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ መስመር መስሏቸው ግራ የተጋቡ የቻይና ባለስልጣኖች እንደነበሩ ተዘግቧል። አንድ የቻይና ዲፕሎማት አለ የተባለው፣ ‘‘when [the] U.S. initiated this we were devastated. We had long sleepless nights. And after two years, President Xi proposed [a] strategic vision of our new concept of Silk Road.”


በተጨማሪም በኦክቶበር 2014 በኢንዶኔዢያ ዢ ጂፒንግ፣ “Maritime Silk Road of the 21st century” ግንባታ እንደሚያካሂዱ ይፋ አድርገው ነበር። በዚህ የባህር መርከብ ኢንቨስትመንት የሚሸፈኑት አካባቢዎች፤ ደቡብ ምስራቅ ኤዢያ፣ የሕንድ ውቂያኖስ፣ የፕርሺያ ገልፍ እና ሜዲቴራንያን ናቸው። ኢንቨስትመንቱ የሚያተኩረው፣ የወደብ መሰረት ልማት መዘርጋት እና የአገልግሎት አሰጣጡን ማዘመን ላይ ነው።


ቻይና በአደባባይ ይፋ ያደረገችው “One Belt One Road” የኢኮኖሚ ዲፕሎማሲ ማዕቀፍ ዋና መገለጫዎች፣ የኢኮኖሚ ትስስር የምትዘረጋበት “Economic Belt” እና የወደቦች መሰረተ ልማት በመዘርጋት ኢኮኖሚዋን የምታስተሳስርበት “Maritime Silk Road” ናቸው። በቀጣይ የቻይና ዲፕሎማሲ የማዕዘን ድንጋይ እንደሚሆን የሚጠበቅ ይኸው የሜጋ የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ መሆኑ በስፋት ይታመናል።

 

ለምን? ሲልክ ሮድ ያስፈልጋል


እንደ ዬ ዚቼንግ (author of a treatise on china grand strategy) “የቻይና ሕዝብ ሕዳሴ እና የቻይና ልዕለሃያል ሀገር የመሆን ግስጋሴ ቅርብ ቁርኝት አለው። ቻይና ልዕለሃያል ሀገር የማትሆን ከሆነ፣ የቻይና ሕዝብ ሕዳሴ የተሟላ አይሆንም። ቻይና ልዕለሃያል ሀገር ከሆነች ብቻ ነው፣ የቻይና ሕዝብ ሕዳሴ ሙሉ ለሙሉ ተሳክቷል ማለት የሚቻለው” ብሏል።


ሲልክ ሮድ፣ በቻይና እና በአውሮፓ መካከል ከክርስቶስ ልደት በፊት በሶስተኛው ክፍለ ዘመን ተዘርግቶ የነበረ ትልቅ የንግድ መስመር ነበር። ቻይና በንግድ ኃያል ከነበረችበት ዘመን ጋር የሚቆራኝ ነው። የ ዢ ዕቅድም፣ ቻይናን ከአውሮፓ ሀገሮች ማያያዝ፣ በውጤቱም ልማት ማፋጠን፤ በተያያዥነትም ዓለም ዓቀፋዊ የንግድ ትስስር በአውሮፓ እና በኤዢያ መፍጠር፤ የውጭ ኢንቨስትመንት በአካባቢው እንዲመጣ መሳብና ለግጭት ተጋላጭ የሆነውን ቀጠና ደህንነቱን ማጠናከር ናቸው። ዢ እንደሚሉት አዲስ ቅርጽ ያለው የአካባቢው የኢኮኖሚ ማሕበረሰብ መፍጠር ነው። ወይም ዢ በሌላ አገላለጽ እንዳስቀመጡት፣ ‘‘a sense of common destiny’’ among the countries concerned.”


የቻይና ብሔራዊ መከላከያ ዩኒቨርስቲ ፕሮፌሰር ጂ ሚንግኩኪ በበኩላቸው፣ አዲሱ የሲልክ ሮድ እቅድ ለኢኮኖሚ ካሮት ዲፕሎማሲ ብዙ ጠቃሚ ነገሮች አለው። ይህም ሲባል፣ ቻይና ከጎረቤት ሀገሮች ጋር የሚገጥማትን የደህንነት ችግሮች ለመፍታት መደራደሪያ እንዲሆናት ፕሮጀክቱ ከፍተኛ ጠቀሜታ አለው። ይህ የኢኮኖሚ ካርድ በተጨማሪም፣ በቻይና ስትራቴጂካዊ ጥቅሞች ላይ ተፎካካሪ ወይም ፈተናዎች በሚሆኑት አሜሪካ እና ጃፓን ላይ ተፅዕኖ ለማሳረፍ ጠቃሜታው የጎላ ነው ብለዋል።


የቻይና ሲልክ ሮድ ኢኮኖሚ ትስስሮሽ ለሀገር ውስጥ ኢኮኖሚያቸውም ከፍተኛ መነቃቃት እንደሚፈጥር ተነግሯል። ባለሙያዎቹ እንዳስቀመጡት፣ የሲልክ ሮዱ የኢኮኖሚ መቀነት የሚጀምረው ከቻይና ምዕራብ ድንበር ወደ ማዕከላዊ ኤዢ አይደለም። ከቻይና ምስራቅ ክልሎች ነው። ይህም በመሆኑ ለፖሊሲ አውጪዎቹ፣ ዝቅተኛ የእድገት ደረጃ ላይ የሚገኙት የማዕከላዊ እና የምዕራበ የቻይና አውራጃዎችን ልማት ለመደገፍ እድል ይፈጥራል። በቀጠናው ካሉ አጎራባች ሀገሮች ጋር የንግድ ትስስር እንዲፈጥሩ ያግዛቸዋል፤ በመንግስት ቁጥጥር ሥር የሚገኙ ኩባንያዎችም ከፍተኛ ኢንቨስትመንት የሚያፈሱበት እድል ይፈጠራል።


በቻይና አመለካከት፣ የኢኮኖሚ ልማት ፅንፈኛ የእስልምና እምነት አክራሪዎችን ለመታገል ያግዛል። በምዕራብ ቻይና እና በማዕከላዊ ኤዢ አካባቢ ያለውን ደህንነት የበለጠ ለማጠናከር ይረዳል። ሆኖም ይህ የቻይና አተያየት ጥያቄ ይነሳበታል፤ ይኸውም ቻይና ሶስቱ ሰይጣኖች ብላ የምትጠራቸው መገንጠል፣ ፅንፈኝነት እና አሸባሪነት ናቸው። እነዚህ “የሰይጣን ምልክቶች” በቻይና ግዛት ዢንጂያንግ እና ቲቤት ግዛቶች ውስጥ የሚስተዋሉ ከመሆናቸው አንፃር፣ ችግሮቹን በኢኮኖሚ ልማት ብቻ መፍታት ይቻላል ወይ? የሚሉ ጥያቄዎች ያስነሳሉ።
የቻይና ብሔራዊ መከላከያ ዩንቨርስቲ ፕሮፌሰር ሜጀር ጀነራል ጂ ሚንከይ፣ የማሪታይም ሲልክ ሮድ እይታውን ጠቀሜታ እንዳስቀመጡት ከሆኑ “የማሪታይም ሲልክ ሮድ እቅድ የቀጠናውን ደህንነት እና ትብብር ከፍ ያደርጋል። የደብቡ ቻይና የባሕር ይገባኛል ጭቅጭቆችን ያቀዘቅዛል። ሁሉንም ተጠቃሚ በማድረግ የኤዢ ሕልሞችን ያሳካል።” ብለዋል።

ጂኦፖለቲክስ


የቻይናው ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዋንግ ዪ እንደገለጹት፣ “Belt and Road” ፕሮጀክት የጂዖፖለቲካ መሣሪያ አይደለም። የኢኮኖሚ ትብብር በመስተመጨረሻው የፖለቲካ ተፅዕኖ መሣሪያ ካልሆነ፣ አስገራሚ ነው ሲሉ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩን አቀራረብ የሸነቆጡም አሉ። መሬት ላይ ባለው እውነት ከሆነ፣ የቻይና ፖሊሲ አውጭዎች ከጂዖፖለቲካ አንፃር ጉዳዩን እንዳዩት ምልክቶች አሉ። የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ዋንግ እራሳቸው እንደተናገሩት፣ “Belt and Road” የ“ዩሬዢያ ሀገሮች ሕዳሴ ነው” ያሉት። የጂዖፖለቲካ አባት የሚባሉት ሃልፎርድ ማክኢንደር የዩሬዢያ መነቃቃት “የዓለም ደሴት” ይፈጥራል ብለዋል። እድሜ ለቻይና፤ አሜሪካን ያገለለ የኢኮኖሚ ትብብር እና የማሪታይም መሰረተ ልማት ዝርጋታ በዩሬዢያ መፈጠሩ፣ በፓስፊክ እና በአትላንቲክ ሀገሮች መካከል ያለውን የንግድ ሥርዓት ወደሚዛናዊነት ይመልሰዋል ሲሉ ግምታቸውን አስቀምጠዋል።


የጂዖፖለቲካ መሣሪያነቱን አግዝፈው የሚያሳዩ መከራከሪያዎችም አሉ። በተለይ የማክኢንደር ቲዎሪ ተብሎ የሚጠራው “Heartland Theory” በጣም ተጠቃሽ ነው። as a vital springboards for the attainment of continental domination. (በአንድ አካባቢ ተፈላጊ የሆነ ማዕከላዊ ቦታን በተመለከተ የቀረበ ፅንሰ ሃሳብ ነው። ቦታው ለሁሉም ሕልውና አስፈላጊ ተደርጎ የሚወሰድ ነው። ቦታውን መቆጣጠር በዓለም ላይ ተፅዕኖ ለመፍጠር የመወናጨፊያ ቦርድ በመሆኑ ከፍተኛ እድልን ይፈጥራል።) ማክኢንደር ከጂዖፖለቲካ ጋር በተያያዘ የሚጠቀስላቸው ዝነኛ ጥቅስ አላቸው። ይኸውም፣ ‘‘Who rules East Europe commands the Heartland; who rules the Heartland commands the World Island; who rules the World Island commands the World.’’

 

የኢኮኖሚ እና ፖለቲካ አንደምታዎች


ባለሙያዎች እንደሚሉት የቻይና የረጅም ጊዜ እቅዷ የኤዢ ተፅዕኖ ፈጣሪ ሃይል መሆን ነው። ይህንን እቅዷን ለማሳካት መገንዘብ ያለበታ፣ ባገኘችው ልክ ለመስጠት ዝግጁ መሆን ነው፡፤ የውጭ ግንኙነቷ ፖሊሲ ሚዛናዊ እና ከብዝበዛም የጸዳ መሆንን ይጠበቅበታል ሲሉ አሳስበዋል።


እንዲሁም መካከለኛው ኤዢያ በተለምዶ በሩሲያ ተፅዕኖስር የቆየ ነበር። በሂደት ግን የቻይና እቅድ አንድ አካል ሆኗል። “Belt and Road” ፕሮጀክት የሌሎች ግዛቶችን ያቋርጣል። ሕንድንም ጨምሮ። በዘረጋችው እቅድ በፓኪስታን እና በቻይና የኢኮኖሚ ትብብር ማዕቀፍ የኢኮኖሚ ኮሪደሮች ለመስራት ወስናለች። ይህ ሕንድን ያሰጋታል። ሌላው ቻይና አዲሱ ፕሮጀክቷን ከሻንጋይ የትብብር ድርጅት ዓላማ ጋር ማጣጣም ይጠበቅባታል። በሻንጋይ ስምምነት መሰረት፣ ወታደራዊ የሰጥታ ትብብር እና የኢኮኖሚና ሶሻል ዴቬሎብመንት ግዴታዎችን ይጥላል። በዚህ ስምምነት የታቀፉት ሀገሮች፣ ቻይና፣ ካዛክስታን፣ ኪርጊዝታን፣ ሩሲያ፣ ታጃኪስታን፣ ኡዝቤኪስታን፣ ሕንድ እና ፓኪስታን ሲሆን፤ ቻይና ቀደም ብላ ከገባችበት ስምምነት የተቃረኑ ሥራዎች ከመስራት መቆጠብ አለባት።


በላቲን አሜሪካም ቻይና ብዙ ነገሮች ከግምት ሳታስገባ ትልልቅ ፕሮጀክቶችን ለመስራት መግባቷን አስታውሰዋል። ቢያንስ የሀገሮችን የውስጥ ፖለቲካ ሳትገነዘብ ነው የገባችው። በአሁን ሰዓት የቻይና ኢኮኖሚ እየተቀዛቀዘ ነው፤ ውጤቱም በቻይና ኢኮኖሚ ላይ በጣም ጥገኛ በሆኑት ሀገሮች ላይ ጫና እያሳደረ ነው። ለምሳሌ የታቀዱ ፕሮጀክቶች በኮሎምቢያ፣ በሜክሲኮ፣ በኒካራጓዋ እና ቬኑዜላ ተሰርዘዋል። ለምሳሌ፣ የባቡር ዝርጋታ ፕሮጀክት ከፓስፊክ ወደ አትላንቲክ ወጥነው ነበር፣ ይኸውም በፔሩ አድርገው በብራዚል ለመዘርጋት ያለዕቅድና ጥናት ባለመሆኑ ተሰርዟል።


አዲሱ ዕቅድ ከፍተኛ ተግዳሮት በየሀገሩ ይጠብቀዋል። የአሰሪና ሠራተኞች ሕጎች በተለይ የውጭ ሠራተኞችን ቀጥሮ ማሰራት ፈቃድ ማግኘቱ ከባድ ነው። ሙስና፣ በተፈጥሮ የሚገጥሙ ጋሬጣዎች፣ የአካባቢ ደህንነት ሥራዎች እና ሌሎችም ተግዳሮቶች ይሆናሉ ተብሎ ይጠበቃል።

ቻይና ዓለም ዓቀፍ ተፅዕኖ ፈጣሪ ለመሆን


በባለሙያዎች ከፍተኛ ራሮት አለው የተባለው፣ “Belt and Road” ፕሮጀክት በዓለም ዓቀፍ ደረጃ ተቀባይነት ባለው መልኩ መፈጸም አለበት። ለዓለም ዓቀፉ ሕብረተሰብ እና ለአሜሪካ፤ ቻይና ይፋ ያደረገችውን ፕሮጀክት ዕቅድ መሰረታዊ አስተሳሰቡ እና ፍላጎቱን ጭምር ማስረዳት አለባት። ቻይና የቀጥታ ኢንቨስትመንት እና ንግድ ለመቀበል ከአጎራባች ሀገሮች መጀመር አለባት።


እንደሚታወቀው አሜሪካ የኤዢ ባንክ ሲቋቋም ሃሳቡን ውድቅ አድርጋለች። በአይ.ኤም.ኤፍ የመዋቅር ማስተካከያ ለመቀበል አምስት አመታት ወስዶባታል። ይኸውም፣ ቻይናን ጨምሮ ሌሎች በማደግ ላይ ያሉ ሀገሮች ከፍ ያለ ድምጽ እንዲኖራቸው የሚጠይቅ ነበር። አውሮፓዎችም ቻይና በዓለም የንግድ ድርጅት ውስጥ የማርኬት ኢኮኖሚ ደረጃ እንዳይሰጣት ግፊት ሲያደርጉ ነበር። አሜሪካም በTrade in Services Agreement (TiSA) ድርድር ውስጥ ቻይና እንዳትሳተፉ ተከላክላለች። ሆኖም ስልሳ ሀገሮች ያቀፈ የኤዢያ ባንክ ቻይና ማቋቋም በመቻሏ፤ አሜሪካን ቀዝቀዛ በቀል በፈጠረችው ዓለም አቀፍ ሶፍት ፖዎር አቅምሳታለች።


አሜሪካ አሁንም “Belt and Road” ፕሮጀክትን በጥንቃቄ ነው የምትመለከተው። በተለይ ቻይና በዘረጋውችው ፕሮጀክት በምትፈጥረው የኢኮኖሚ ተፅዕኖ፣ ዩዋን ዋናው የኢኮኖሚው ማንቀሳቀሻ የመገበያያ ገንዘብ እንዳይሆን ከፍተኛ ስጋት አላት። ስለዚህም ቻይና ከአሜሪካ እና ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር ፕሮጀክቱን በተመለከተ ተደጋጋሚ ውይይት ማድረግ ይጠበቅበታል ሲሉ ባለሙያዎች ያሳስባሉ።

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
433 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 922 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us