የአክስስ ሪል እስቴት ውዝግብ እንደቀጠለ ነው

Wednesday, 28 June 2017 12:03

 

የአክስስ ሪል እስቴት ውዝግብ እንደቀጠለ ነው

 

አክሰስ ሪል ስቴት በመባል የሚታወቀው የአክሲዮን ማኅበር በ2001 ዓ.ም. ቁጥራቸው 634 በሆነ አባላትና በ34 ሚሊዮን ብር ካፒታል የተቋቋመ ነው።

 ከ2004 ዓ.ም. ጀምሮ በቦርዱ እና በቤት ገዢዎች መካከል በተፈጠረው አለመተማመን እና አለመግባባት ድርጅቱ ለከፍተኛ ኪሳራ እና የአሰራር ክፍተቶች መጋለጡ በስፋት ይነገራል። መንግስት የተፈጠረውን ችግር ከግምት በማስገባት የተለያዩ ኮሚቴዎችን በማዋቀር ለችግሩ እልባት ለመስጠት ላለፉት አራት አመታት ሲሰራ ከርሟል። ድርጅቱንም በተመለከተ ልዩ የሒሳብ ምርመራ በማድረግ ችግሮቹን ለመለየት ችሏል።

መንግስት ያደረገውን የሒሳብ ምርመራ ተከትሎ ሰኔ 16 ቀን 2009 ዓ.ም. የአክሰስ ሪል እስቴት አ.ም. የዳሬክተሮች ቦርድ እና የአክሰስ ሪል እስቴት የቤት ገዢዎች ዐብይ ኮሚቴ በጋራ መግለጫ በድርጅቱ ጽ/ቤት ውስጥ ሰጥተዋል። በዚህ ጋዜጣው መግለጫ ላይ የተነሱትን እና ሌሎች ከድርጅቱ ጋር የተገናኙ ጥያቄዎችን አንስተን አነጋግረናቸዋል።

እንዲሁም የአክሰስ ሪል እስቴት መስራች እና የቀድሞ የዳሬክተሮች ቦርድ ሰብሳቢ የነበሩትን አቶ ኤርሚያስ ጠቅል አለመልጋን አጠቃላይ ስለሪል እስቴቱ በተመለከተ እና ቤት ገዢዎች ተጨማሪ ክፍያ ሳይፈጽሙ ቤትሰርተው ለመስጠት እቅድ አለኝ ስላሉት ሃሳብ አነጋግረናቸዋል።

ውድ አንባቢያን፡- የሁለቱንም አካሎች የሚያነሷቸውን ነጥቦች አይታችሁ የራሳችሁን ግንዛቤ እንድትወስዱ ያስችላችሁ ዘንድ ሁለቱንም አነጋግረናቸዋል።

 

“ቤት ገዥዎች ተጨማሪ ክፍያ ሳይፈፅሙ፤ ቤታቸውን የሚያገኙበት ዕቅድ አለኝ”

አቶ ኤርሚያስ ጠቅል አመልጋ

የቀድሞ የአክሰስ ሪል እስቴት የዳይሬክተሮች ቦርድ ሰብሳቢ

 

ሰንደቅ፡- ከድርጅቱ ያገኘነው መረጃ አክሰስ ሪል እስቴት ሲቋቋም የነበርዎት የሁለት ሚሊዮን ብር የአክሲዮን ድርሻ በፍርድ ቤት በተሰጠ ውሳኔ፣ ለአቶ ሁሴን ሰዒድ መተላለፉ ተነግሮናል። በዚህም መነሻ ድርጅቱ ከእርስዎ ጋር ሕጋዊ የሆነ ግንኙነት የለኝም ብሏል። በዚህ ላይ ምን አስተያየት አልዎት?

አቶ ኤርሚያስ፡- የአክሲዮን ድርሻው ተላልፏል የተባለው ልክ ነው። መታወቅ ያለበት የአክሰስ ሪል እስቴት መስራች እና ከፍተኛ ባለአክሲዮን ድርሻ ያለው አክሰስ ካፒታል ነው። የአክሰስ ካፒታል ቦርድ ሰብሳቢና ሥራአስኪጅ እንዲሁም ከፍተኛ ባለድርሻም እኔ ነኝ። የሕግ ክፍተት አገኘን በሚል ከጨዋታ ውጪ የማድረግ አካሄድ መሆኑ ይገባኛል። ከዚህም በላይ እኔ ልወክለው የምችል የአክሲዮን ድርሻ ያለው ሰው አለ። በአንድም በሁለትም መንገድ ባለመብት ነኝ።

ሕጋዊነት ከተነሳ አይቀር የአንድ የቦርድ ዘመን ሶስት ዓመት ነው። ስለዚህም አሁን ያለው ቦርድ ጠቅላላ ጉባኤ ጠርተው ለምን አዲስ ምርጫ አይደረግም? ለዚህም ምላሽ ቢሰጡበት ጥሩ ነው።

 

ሰንደቅ፡- ቤቶቹን ሰርቶ ለማስረከብ ተጨባጭ የሆነ የእርስዎ አማራጭ ሃሳብ ምንድን ናቸው?

አቶ ኤርሚያስ፡- ከአንድም ሶስት አማራጭ አለኝ። አንደኛ፣ ሁለት ትልልቅ የውጭ ኩባንያዎች በሪል እስቴት ግንባታ ልምድ ያላቸው፣ ገንዘብ ያላቸው፣ ከአክስ ሪል እስቴት ድርሻ በመግዛት፣ የቤቶች ግንባታ በማከናወን ራሳቸውም ተጠቃሚ ሆነው፣ አሁን ያለው ቤት ገዢ ምንም ተጨማሪ ክፍያ ሳይፈጽም ወደ 2ሺ ቤቶች ሰርተው ያስረክባሉ። አሁን በአክሰስ ሪል እስቴት እጅ ያሉ መሬቶች ላይ ወደ 2ሺ አፓርትመንቶች ወይም ቤቶች ቢሸጡ፣ ወደ 4ሺ የሚጠጉ ቤቶች ያልተሸጡ አሉ። ወይም ሊኖሩ ይችላሉ። ከእነዚህ 4ሺ ቤቶች ሽያጭ የሚገኘው ትርፍ በጣም ትልቅ ስለሆነ፣ ውል ፈጽመው ቤታቸውን ለመረከብ ለሚጠባበቁ ሰዎች ቤታቸውን አሰረክበን፣ የድርጅቱን ወጪዎች ሸፍነን ትርፍ ማስገኘት የሚችል በአክሰስ ሪል እስቴት እጅ የሚገኝ ሐብት ስላለ ነው፣ እነዚህ የውጭ ኢንቨስተሮች ኢንቨስት ማድረግ የፈለጉት።

ምንም የተለየ ነገር ኖሮ አይደለም። ድርጅቶች ብዙውን ጊዜ ችግር ላይ የሚወድቁት። እዳቸው ከሃብታቸው በላይ በሚሆን ጊዜ ይከስራሉ፣ በዚህ ጊዜ ትንሽም ነገር ማግኘት አለብኝ ከሚል ስሜት ሰዎች ይጋጫሉ። ይካሰሳሉ። በአክሰስ ሪል እስቴት ውስጥ ግን የተገላቢጦሽ ነው ያለው። አክሰስ ሪል እስቴት ከሰረ አይባልም። ምክንያቱም ከሰረ ማለት insolvent የሚሉት ነው። ይህ ማለት ድርጅቱ እዳዎቹ ካለው ሃብት ይበልጣሉ። አክሰስ ሪል እስቴት ላይ ስንመጣ ግን ሃብቱ ከእዳው ይበልጣል። ችግሩ ያለው፣ liquidity ላይ ነው። ይህ ማለት ሥራውን ለተወሰነ ጊዜ ማንቀሳቀስ የሚችል የገንዘብ እጥረት ገጥሞታል። አንድ ጊዜ ለሥራው ማንቀሳቀሻ የሚሆን ገንዘብ ሲገባ ያለው ሃብት በተጨማሪ ሃብቶች ያፈራል። ከውጭ የሚመጡት ኢንቨሰተሮችም ድርጅቱ ያለውን ሃብት ተመልክተው በመሬቶቹ ላይ ግንባታ ቢካሄድ ምን ያህል ሊፈጅ እንደሚችል? ምን ያህል ቤቶች በመሬቶቹ ላይ ሊሰሩ እንደሚችሉ? በየሳይቶቹ ላይ ስንት አፓርትመንቶች ይገነባሉ? ምን ያህል ብርስ ይፈጃሉ? ቤት የተሸጠላቸው ሰዎች ተጨማሪ ብር ሳይከፍሉ ቤታቸው ተሰርቶ ቢሰጣቸው ቀሪ አፓርትመንቶች በሜትር ካሬ በስንት ብር ቢሸጡ ምን ያህል ትርፍ ሊመጣ ይችላል የሚለውን ዝርዝር ሒሳብ ሰርቼ፣ ቤት ሰሪዎቹ ካለተጨማሪ ክፍያ ቤታቸውን ተረክበው ብዙ ሚሊዮን ብሮች ማግኘት እንደሚቻል አቅርቤላቸው፣ ትክክለኛ መሆኑን አረጋግጠው ወደ ሥራ ለመግባት የተዘጋጁ የውጭ ባለሃብቶች በእጄ ላይ ይገኛሉ።

ተጨማሪም ይመጣሉ። ሁሌ የሚነሳው ጥያቄ ግን እዚህ ጫጫታ መካከል የትኛው ኢንቨስተር ነው የሚመጣው? የሚለው ነጥብ ነው። ለዚህ የማቀርበው ምላሽ ግርግር እና ጫጫታው ከወዴት ነው የሚመጣው? የሚለውን መመልከቱ በጣም ጥሩ ነው። አንደኛው የድርጅቱ ባለዕዳዎች እነማን ናቸው? ቤት ገዢዎች ናቸው። የባንክ ብድር የሚባል የለም። ቤት ገዢዎች ቤታቸውን ካገኙ ምን ይፈልጋሉ? ስለዚህ በተወሰነ የጊዜ ገደብ ውስጥ ቤቶቹ ተገንብተው ትረከባላችሁ ከተባሉ፣ ሰላም ይፈጠራል። ከእነሱ በኩል የሚነሳ ችግር አይኖርም። ሁለተኛው፣ ከኢንቨስተሮቹ የቀረበው የአክሰስ ሪል እስቴት መሬቶች ላይ ግንባታ ለመፈጸም ከመንግስት የመሬት ይዞታ ሕጋዊ ባለቤትነት ማረጋገጫ እንፈልጋለን የሚል ነው። በመሬቶቹ ቁጥር ተማምነን ወደሥራ የምንገባበት ሁኔታ ሲፈጠር፣ መንግስት ማረጋገጫ ለመስጠት ዝግጁ መሆኑን ስለነገርኳቸው ችግሩ እንደሚታለፍ አምነው ኢንቨስት ለማድረግ ተዘጋጅተዋል።

ሁለተኛ፣ ኢንቨስተሮች የሉም ተብሎ ቢታሰብ እንኳን፣ ድርጅቱ ያጣው ወደ ሥራ የሚያስገባው መንቀሳቀሻ ገንዘብ ብቻ መሆኑ ሊታወቅ ይገባል። በቢሊዮን የሚቆጠር ሃብት ያለው ድርጅት በመሆኑ፣ የብድር ውሎች ተመቻችተው ድርጅቱ እራሱን በእራሱ አንቀሳቅሶ ወደ ፍፃሜ መድረስ የሚችልበት ዕድል አለው። አሁን የጠፋው፤ ቢዝነስ ማለት ምን እንደሆነ በትክክል ገብቶት? ሥራ ማንቀሳቀስ ምን እንደሆነ ገብቶት? ይህንን ተግባራዊ ማድረግ የሚችል አመራር ነው ድርጅቱ ያጣው። ድርጅቱ አልከሰረም። ምንአልባትም ኢትዮጵያ ውስጥ ካሉት ሐብታም ድርጅቶች አንዱ አክሰስ ሪል እስቴት ነው። ሃብት ተይዞ ማንቀሳቀሻ አጣሁ ማለት ምን ማለት ነው? ድርጅቱ ላይ በኃላፊነት የተሰየሙት ሰዎች ፈጽሞ ከቢዝነስ ጋር ትውውቅ የላቸውም። ላለፉት ሃያ አመታት ቢያንስ በቢዝነስ ላይ የቆየሁ በመሆኔ እና አሁን ባቀረብኩት አማራጭ ሃሳቦች ዕድሉ ቢሰጠኝ እና ድርጅቱን ለማዳን ብሰራ ለሁሉም የተሻለ ውጤት ያስገኛል የሚል ሃሳብ ነው ያለኝ። ችግሩን ከስሩ ለመፍታት ለእኔ ፈተና አይደለም።

 

ሰንደቅ፡- እርስዎ በነበሩት አመራር ችግሮች አልነበሩም ወይ?

አቶ ኤርሚያስ፡- ቀደም ባለው ጊዜ የተሰሩ ስህተቶች ነበሩ። ድርጅቱን በአግባቡ መምራት ነበረብኝ። ሆኖም በሚፈለገው መልኩ አልመራሁትም። እኔ ጋር ጥፋት ሳይኖር፣ አሁን የተፈጠረው ችግር ሊፈጠር አይችልም። ከእኔም ቁጥጥር ውጪ በሆኑ ነገሮች የተፈጠሩ ችግሮችም ነበሩ። ድርጅቱን በተፈለገው ፍጥነት መሔድ አልቻለም። ሶስተኛ ወገኖች የሆኑ ክፍያ የተፈጸመላቸው በውላቸው መሰረት ሥራዎችን ማከናወን አልቻሉም። በተፈጠሩት አጋጣሚዎች ችግሮቹ ተደራረቡ፣ ሥራዎቻችን እንዲቆሙ ተደረጉ። ቤት ገዢውም ብሬን መልስ ማለት ጀመረ። እጄ ላይ የነበረው 80 ሚሊዮን ብር ለቤት ገዢዎች ክፍያ ውሏል። በርካታ ሰዎች ገንዘብ ስለጠየቁን መንቀሳቀሻ ገንዘባችን ተሟጦ አለቀ።

ሰንደቅ፡- አሁን በድርጅቱ ኃላፊነት ላይ ያሉ ሰዎች በማሕበር ተደራጅተው ለመስራት ጥያቄ አቅርበዋል። በዚህ ምን አስተያየት አልዎት?

አቶ ኤርሚያስ፡- በማሕበር ተደራጅተው ለመስራት የሚያስችል ተጨባጭ ማሳያዎች ቢኖራቸው እቅዳቸውን የምቀበለው ነው የሚሆነው። መታወቅ ያለበት ግን እኔ ወደ እዚህ ሀገር ተመልሼ የመጣሁት ኃላፊነት እና ግዴታ አለብኝ በማለት ነው። ድርጅቱን፤ የመሰረትኩት፣ የመራሁት፣ ችግሩ ሲፈጠር የነበርኩት እኔነኝ፣ ችግሩንም መፍታት ያለብኝ እኔነኝ፣ ለፈጠርኩት ችግር ተጠያቂ ለመሆን ዝግጁ ነኝ፣ ተጠያቂም ሆኛለሁ። ቤት ገዢው እኔ በአደባባይ ብሰቀል ቤት አያገኝም። የተወሰኑ ሃያ ሰላሳ ሰዎች በመሰቀሌ ይደሰቱ ይሆናሉ። መፍትሔ ግን አይደለም። መንግስትም በራሱ አቅም ብቻ መፍትሔ ለማስቀመጥ አይችልም።

ስለዚህም እኔ በሕግ የምጠየቅበት ጉዳይ እንደተጠበቀ ሆኖ፣ ቤት ገዢውም ሆነ የድርጅቱ ኃላፊዎች ለቤት ፈላጊው ሕዝብ ቤት ሰርተን እናስረክበዋለን እንደሚሉት አሳማኝ እቅድ ካላቸው፣ ከእኔ በላይ ደስተኛ የሚሆን ሰው አይኖርም። የሕዝብ ሸክም ይቀልልኛል። ሥራ ይቀልልኛል። ከዚህ ውጪ ምንም የማጣው ነገር የለም። ሕዝቡ ብቻ ቤቱን ያግኝ። እስከዛሬ ድረስ ግን የድርጅቱ ኃላፊዎች አማራጭ ሃሳቦች ሲያቀርቡ አልሰማሁም። በተደጋጋሚ ያቀረብኳቸው አማራጭ ሃሳቦች ወደ ተግባር እንዳይለወጡ ቦርዱ እና የድርጅቱ ሥራአስኪያጅ እንቅፋት እንደሆኑብኝ ለመንግስት በዝርዝር አሳውቄያለሁ። ይኸውም፣ ግልጽ በሆነ መልኩ የጥቅም ግጭት በድርጅቱ ውስጥ ተፈጥሯል።

 

 

ሰንደቅ፡- ምን አይነት የጥቅም ግጭት ነው የተነሳው?

አቶ ኤርሚያስ፡- የድርጅቱ ሥራአስኪያጅ ለአክሰስ ሪል እስቴት የጥበቃ አገልግሎት የሚሰጥ ድርጅት ባለቤት ነው። ገንዘብ ተከፍሎት የጥበቃ ሥራዎች ይሰራ ነበር። በስራ ስምሪት ጊዜ አሉ የሚባሉ ሠራተኞች ቁጥር እና በስራ ገበታው ላይ የሚገኙት የሠራተኞች ቁጥር በጣም የተራራቀ ነው። በሥራ ገበታ ላይ ላልተገኙ ሰዎች ክፍያ በድርጅቱ እንጠየቃለን። ወደ ሥራ አስኪያጅነት ያመጣሁት፣ ድርጅቱን ያውቀዋል፣ አብረን ሰርተናል፣ የሀገሪቱንም ተጨባጭ ሁኔታዎችን ያውቃል ከሚል መነሻ ነበር። እኔም ትልልቅ ሥራዎችን ትቼ ደንበኞችን ማስተናገድ ዋና ስራዬ ከሚሆን፣ የሕዝብ ግንኙነት ሥራዎችን እና የዕለት ዕለት ሥራዎችን እንዲሰራ የአሁን ሥራአስኪያጅ አመጣሁት።

እኔ እዚህ ሀገር ስመጣ በአንድ ወር ውስጥ ግንባታ አስጀምራለሁ ብዬ ቃል ገብቼ ነው። በአንድ ወር ውስጥ ግንባታ ለማስጀመር የምችለው የነበረው ኒያላ ሞተርስ በሚገኘው ሳይታችን ላይ ነበር። 9ሺ ካሬ ላይ የተሰሩ ስምንት ሕንፃዎች አሉ። ከስምንቱ አምስቱ ሕንፃዎች ጂ ፕላስ ሰባት ስትራክቸራቸው አልቆ ሊሾ ተደርጎ ለፊኒሺንግ የተዘጋጁ ናቸው። ሶስቱ ሕንፃዎች ሶስተኛ እና አራተኛ ፎቆች ላይ ደርሰው የቆሙ ናቸው። እነዚህን ሕንፃዎች ወደ አምስቱ ሕንፃዎች ደረጃ ለማድረስ የ40 ሚሊዮን ብር ገደማ ወጪ ነው የቀራቸው። ይህንን ሥራ ማጠናቀቅ ማለት ወደ ሁለት መቶ ሰዎች ካርታ ያለው ቤት ያገኛሉ ማለት ነበር።

ግንባታውን ከሚያካሂደው ተቋራጭ ጋር አንድ ስምምነት አደረግን። 40 ሚሊዮን ብር ወጪ ከተቋራጩ ወጪ ተደርጎ ድርጅቱ አንድም ክፍያ ሳይፈጽም ሶስቱን ሕፃዎች ለፊኒሺንግ አድርሶ ሊያስረክበን ተስማማን። ክፍያው የሚፈጸመው፣ በሳይቱ ላይ ቤት ከገዙ ሰዎች ተሰብሳቢ 45 ሚሊዮን ብር ውስጥ መሆኑን ተቋራጩ አረጋግጦ ነው የተስማማው። ክፍያውን ሰዎቹ ባይፈጽሙ እንኳን ቤቶቹ ተሽጠው ገንዘቡን ሊያገኝ እንደሚችል ተቋራጩ ሒሳብ ሰርቶ ነው የተስማማው። ይህንን ስምምነታችንን በውል ለማሰር ለቦርዱ ጥያቄ አቅርቤ አራት ዙር ስብሰባ ብንቀመጥም፣ ማሳመን አልተቻለም። በወቅቱ ለእነአቶ መኩሪያ ኃይሌ አቤት ብዬ ስለነበረ፣ ወደ ግንባታ ውስጥ ለመግባት ሥራው መጀመር አለበት የሚል መመሪያ እንዲተላለፍ ተደረገ።

የውሉን ሰነድ እንዲፈርም ለሥራ አስኪያጁ አቀረብኩለት። ሥራ አስኪያጁም፣ በመካከላችን የጥቅም ግጭት እንዳይነሳ ያቀረብከውን የውል ሰነድ የምፈርመው፣ የማራኪ የጥበቃና ምክር አገልግሎት ኃ/የተ/የግ/ማ ለአክሰስ ሪል እስቴት ለሰጠው የጥበቃ አገልግሎት ያለበትን ተከፋይ እዳ ብር 18 ሚሊዮን 534 ሺ 184 ብር በ9 በመቶ ወለድ ተጨምሮበት የተሰናዳውን የውል ሰነድ ስትፈርምልኝ ብቻ ነው አለኝ። ሒሳብ ክፍል ያላመነበት ለጥበቃ 22 ሚሊዮን ብር ክፍያ ስጠየቅ አልቀበልም ብዬ ጥያቄውን ለቦርዱ አቀረብኩ። ቦርዱ ዝምታን መርጦ ወደ ሥራ እንግባ አሉኝ። ውሉን ግን ማስፈረም አልቻልኩም። አቶ ይግዛው የተባሉት የቦርድ አባል ደውለው በወቅቱ ያሉኝ “አቶ አክሎግ ደውሎ ለምን የኮሎኔሉን ገንዘብ አትከፍሉትም” ብሎ ጠየቀኝ አሉኝ። ይህንን ከእሳቸው ስሰማ በተፈጠረው ሁኔታ በጣም አዘንኩ።

 

 

ሰንደቅ፡- የጥቅም ግጭት ተብሎ የሚነሳው ሥራአስኪያጁና አቶ አክሎግ በጋራ ከእርስዎ ጋር የተፈጠረ ነው ተደርጎ መውሰድ ይቻላል?

አቶ ኤርሚያስ፡- በትክክል። የሚገርመው ነገር ቢሮ ውስጥ ቁጭ ብለን ኮሎኔል አብርሃም “ኤርሚያስ የእኔን ሒሳብ አታምነውም ማለት ነው” ብሎ ጠየቀኝ። የሰጠሁት ምላሽ፣ የማመን፣ አለማመን ጉዳይ አይደለም። በጣም ትልቅ ክፍያ ነው። “ቦርዱ ያጸደቀውን ምን ይሁን ነው የምትለው” አለኝ። “ኤርሚያስ ስወድም እስከ ሞት ነው። ስጣላም እስከ ሞት ነው። ግንባርህን ብዬ በሁለተኛው ቀን ባለኝ ግንኙነት ከእስር እንደምወጣ አታውቅም ወይ?” ሲል አስጠነቀቀኝ። ይህንን ያለኝን ፖሊስ ጣቢያ ሄጄ ቃል በቃል መስክሬያለሁ። ቦርዱ ግን ሰምቶ እንዳልሰማ አለፈው። የሰጠሁት ምላሽ፣ ችግር የለውም ሒሳቡን ላጣራው አልኩት። ሁኔታውን ለአንድ ከፍተኛ መንግስት ኃላፊ ሳስረዳው፣ ክሰሰው አለኝ። ሶስተኛ ፖሊስ ጣቢያ ሄጄ ክስ መሰረትኩ። በሚገርም ሁኔታ ወ/ሮ መብራት እና አቶ አክሎግ የእሱ ምስክር ሆነው ቀረቡ። “የገጠመን ችግር የለም። ችግር ቢፈጠር እንኳን የቦርዱ ሊቀመንበር ብቻውን መክሰስ አይችልም” የሚል ምስክርነት አቀረቡ። ሥራ አስከያጁም በዋስ ወጣ። ይህ የሆነው ረቡዕ ዕለት ነበር። ቅዳሜ በተደረገው የቦርድ ስብሰባ አጀንዳው የድርጅቱን ቀጣይነት በተመለከተ ነው አሉ። በቦርድ ሊቀመንበር ላይ ድምፅ ይሰጥ የሚል አጀንዳ አመጡ። በድምጽ ብለው ተነሰትሃል አሉኝ። ማመን አልቻልኩም። አቶ ይግዛው ምን እየተሰራ ነው ብሎ ጠየቀ፤ ጆሮ የሰጠው የለም። ወ/ሮ መብራት የቦርድ ሊቀመንበር መሆናቸው ተነገረ። ከዚህ ዕለት ጀምሮ እኔን ማጥፋት ሆነ ሥራቸው።

ሰንደቅ፡- በድርጅቱ በኩል ለግጭታችሁ መንስኤ ተደርገው የቀረቡት “ከዚህ በፊት ውል ያደረጉባቸው ወደ 33 ሚሊዮን ብር የሚጠጋ በኢምፔሪያል ሆቴል ሽያጭ ለኢምፔሪያል ሆቴል ተወካይ ለአቶ ፀጋዬ ሊከፈል ይገባል። ስለዚህም የድርጅቱን ሥራ አስኪያጅ 33 ሚሊዮን ብር እዳ አለብን ብለህ ፈርም የሚል ጥያቄ በማቅረብዎ ነው?” በዚህ ላይ ምን አስተያየት አልዎት?

አቶ ኤርሚያስ፡- አንደኛ የኢፔሪያል ሆቴል ሽያጭ በሜቴክ እና በአቶ ፀጋዬ መካከል የተደረገ ሽያጭ በመሆኑ እኔን አይመለከተኝም። የሚሉት ነጭ ውሸት ነው። ያቀረብኩት ሰነድ ካላቸው ማቅረብ ይችላሉ። በተጨማሪም አቶ ፀጋዬ ወይም ሜቴክን መጠየቅ ትችላለህ። 

ሰንደቅ፡- ከውጭ ባለሃብቶች ጋር ለመሥራት ያቀዱትን ሥራዎች በተጠያቂነትና በግልጽ ለማከናወን ምን ያህል ዝግጁ ነዎት?

አቶ ኤርሚያስ፡- መቶ ፕርሰንት ፍላጎቱም ግዴታም አለብኝ። ዝም ብላችሁ አይናችሁን ጨፍናችሁ ስጡኝ አልልም። የምንሰራው ሥራም አዲስ ሳይንስ አይደለም። ለግንባታ ምን ያስፈልጋል የገንዘብ ምንጭ ነው። የገንዘብ ምንጭ የሆነው ተቋም ከመንግስት ጋር ፊት ለፊት ቀርቦ ነው የሚወያየው። የተቋሙን የመገንባት አቅም፣ ተቋሙ የሚገነባውን በየወሩ ሪፖርት ያቀርባል። በተቋሙ ላይ የመንግስት አማካሪ ድርጀት ማስቀመጥ ይቻላል። መንግስት በማንኛውም መልኩ በስራው ላይ ተሳታፊ እንዲሆን እንፈቅዳለን።

ሰንደቅ፡- በአደባባይ ከድርጅቱ “ገንዘብ መዝረፍዎ” ነው የሚነገረው። በዚህ ላይ ምን ይላሉ?

አቶ ኤርሚያስ፡- የተፈጠሩ የአሰራር ክፍተቶች ናቸው ድርጅቱ ያጋጠመው። በአንዳንድ ሰዎች “ገንዘብ ዘርፏል” በሚል ስም ለማጥፋት መሰለፋቸው ቢገባኝም፣ ገንዘብ ከድርጅቱ ዘርፌ እንዴት ከእስር ልፈታ እችላለሁ? በፌደራል ፖሊስ ምርመራ ተደርጎብኛል። የኦዲት ሪፖርቱም ተጠናቆ ቀርቧል። የተፈጸመ ወንጀል ካለ የቤት ገዢውም ሆነ የድርጅቱ ወይም የቦርድ አባላት ችግር አይደለም። ጉዳዩን የሚከታተል የመንግስት አቃቤ ሕግ አለ። ሕግ ባለበት ሀገር ውስጥ ነው ያለነው። ስለዚህም በሕግ የተያዘው ጉዳይ በሕግ ምላሽ ያገኛል። ሆን ተብሎ ከዋናው የቤት ግንባታ አጀንዳ ጋር እያነሱ ለማምታታት መሞከር ለማናችንም ጥቅም የለውም። መፍትሔም አይደለም።¾  

 

 

 

 

 

 

 

 

“ኤርሚያስ ስለተናገረ ብቻ አናምነውም፤ የእቅዱን ተግባራዊነት በመንግስት ከተረጋገጠ እኛም እንቀበላለን”

 

አቶ አክሎግ ስዩም

 

የቤት ገዢዎች ዓብይ ኮሚቴ ሰብሳቢ

 

 

 

ሰንደቅ፡- በጽ/ቤታችሁ የሰጣችሁት ጋዜጣዊ መግለጫ ከምን መነሻ ነው?

 

አቶ አክሎግ፡-በአክሰስ ሪል እስቴት እና ከአክሰስ ሪል እስቴት ቤት ለመግዛት በተዋዋሉ አካሎች መካከል በተፈጠረው ውስብስብ ችግር መነሻ ላለፉት አራት አመታት ከመንግስት የተወከሉ ከፍተኛ ኃላፊዎች፣ የቤት ገዢዎች ኮሚቴ እና በአክሰስ ዳሬክተሮች ቦርድ የጋራ ጥምረት ችግሮችን ለመለየት ሥራዎች ሲሰሩ እንደነበር ይታወቃል። አሁን ላይ ልዩ የኦዲት ምርመራው ውጤት በመጠናቀቁ መንግስትም የተሻለ አቅጣጫ ይዟል። በኦዲት ምርመራው መሰረት የሕዝብ ገንዘብ በማኔጅመንት ችግር አለአግባብ ወጪ መደረጋቸው ቁልጭ ብሎ ተቀምጧል።

 

በተገኘው የኦዲት ምርመራ ውጤት መነሻ አብዛኛው የባከነው ገንዘብ በቀድሞው የአክሰስ ሪል እስቴት ዳሬክተሮች ቦርድ ሰብሳቢ እና በተደራቢነት ሥራ አስኪያጅ ሆነው ደርበው ሲሰሩ በነበሩት በአቶ ኤርሚያስ ጠቅል አመልጋ መሆኑን ማረጋገጥ ችለናል። የተለዩት ችግሮች እንዴት መፈታት አለባቸው የሚለውን መንግስት አቅጣጫ ስለሰጠበት ይህንን ለባለድርሻ አካላት ማሳወቅ የቤት ገዢዎች አብይ ኮሚቴ ኃላፊነትና ግዴታ በመሆኑ ነው መግለጫ የተሠጠው።  

 

አቶ ኤርሚያስ ከውጭ እንዲመጡ ያደረግነው መንግስት ላይ ተፅዕኖ በመፍጠር ነበር። ምክንያታችን የነበረው፣ የችግሩ ዋና ፈጣሪ የመፍትሔውም አንድ አካል ቢሆን የተሻለ ውጤት ይገኛል ከሚል መነሻ ነው። እንደሚታወቀው አቶ ኤርሚያስ 1 ነጥብ 3 ቢሊዮን ብር ሰብስቦ በመጨረሻም በድርጅቱ የሒሳብ ቋት ውስጥ 129 ብር ሲቀረው ከሀገር ኮብልሎ ወደ ውጭ ሀገር ወጥቷል።  በዱባይም ለሁለት ዓመት ተቀምጧል። በእኛ በኩል የደረሰብንን ችግር ደጋግመን ለመንግስት በማሳወቃችን፣ መንግስትም ጉዳያችንን አዳምጦ ችግሩ እንዴት እንዲፈታ ትፈልጋላችሁ? የሚል ጥያቄ ሲያቀርብልን፣ በወቅቱ የቤት ችግራችን እንዲቃለል ብቻ በማሰብ ችግሩ የሚፈታው ችግሩን በፈጠረው ሰው ነው የሚል አቋም ነበረን።

 

ስለዚህም መንግስት ላይ ጫና በማሳደራችን፣ መንግስትም ምንም እንኳን በተለያዩ ክሶች አቶ ኤርሚያስ ቢፈለግም፣ ችግር ውስጥ የገቡትን ዜጎች ለመታደግ የአቶ ኤርሚያስ ወደ ሀገር መመለስ የሚጠቅም ነው ብላችሁ እንደመፍትሄ የምታቀርቡ ከሆነ በማለት መንግስት በተለየ ፈቃድ በጊዜያዊነት በቀረበለት ጥሪ ወደ ሀገር ውስጥ ሊገባ ችሏል። መንግስት በሰጠው እድልም ለአንድ ዓመት ከቤት ገዢዎች አብይ ኮሚቴ እና በ2005 አዲስ ከተመረጠው የዳሬክተሮች ቦርድ ጋር በጋራ መፍትሔ ለማምጣት አብረን እንሰራ ነበር።

 

አብረን በጋራ ስንሰራ በነበረበት ጊዜ ከአቶ ኤርሚያስ የተገነዘብነው ወይም ያረጋገጥነው ነገር፣ ለተፈጠሩት ችግሮች መፍትሔ ከማስቀመጥ ይልቅ የበለጠ ችግሮቹን ማወሳሰብ ነው የመረጠው። ለዚህ ማሳያዎቹ አንደኛ፣ ሲመጣ ያቀረበው እቅድ ነበር። እቅዱ በአስራ አምስት ቀን ውስጥ ከ100 እስከ 300 ሚሊዮን ብር አለአግባብ ክፍያ የፈጸምኩላቸው ግለሰቦች ድርጅቶች እቃ አቅራቢዎች ኮንትራክተሮች ነበሩ። ከእነዚህ አካሎች ገንዘቡን የማስመለስ አቅም አለኝ የሚለው የመጀመሪያው እቅድ ነበር። በዚህ ወቅት ገንዘብ አግኝቶ አቅም መፍጠር ለእኛ በጣም አስፈላጊም ጠቃሚም እንዲሁም ሥራ የማስጀመር እድል ይፈጥርልናል ብለን በደስታ ተቀበልን። ሁለተኛው ያቀረበው እቅድ፣ ውጭ ሀገር በነበረበት ጊዜ 1 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር በላይ ያላቸው የውጭ አልሚዎችን አነጋግሬ ተስማምቼ ነው የመጣሁት በቀጥታ ወደ ሥራ እንገባለን የሚል ነበር ያቀረበው።

 

ከላይ የሰፈሩትን ሁለት እቅዶች ተግባራዊ ለማድረግ በርካታ ሥራዎችን ሰርተናል። ለምሳሌ ከሁለት አመት በላይ አቶ ኤርሚያስ መክፈል የነበረበትን ውዝፍ የሠራተኞች ደሞዝ ወደኋላ ከፍለን፤ በቀጣይ ለሥራው አስፈላጊ ናቸው የተባሉ የሰው ኃይል ቀጥረን ደሞዝ ከፍለናል። ከፍተኛ ወጪ ይከፈልባቸው የነበሩ ቢሮዎችን አጥፈን ወደ ድርጅቱ ግቢ ገብቶ እንዲሰራ ብዙ እገዛ አድርገናል። ይህንን ሁሉ ድጋፍ አቅርበን በአስራ አንድ ወር ውስጥ አንዳቸውም ተግባራዊ ሆነው አላየንም። ይህም በመሆኑ በኮሚቴው እና በአቶ ኤርሚያስ መካከል አለመግባባቶች ተፈጠሩ።

 

በአስራ አምስት ቀኖች ውስጥ እሰበስባቸዋለው ያላቸው ገንዘቦች ሊመለሱ ቀርቶ፤ ቀድሞ እሱ በቃልና በጽሁፍ ስምምነት በፈጸማቸው እዳዎች ወደ ድርጅቱ የሚመጡበት አዝማሚያ ነው የተፈጠረው። የድርጅቱን እዳ ሲጨምር ነበር። ይህ ሁኔታ ከድርጅቱም ከቦርዱም ከቤት ገዢዎች ኮሚቴም ጋር ሊያግባባን አልቻለም።

 

ሁለተኛ ከውጭ 1 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር ይዘው ለማልማት ይመጣሉ ያላቸው ድርጅቶች ድርድሩ ተቋማዊ ይዘት እንዲኖረው አምጣቸውና እንወያይና ወደሥራ እንግባ የሚል ጥያቄ ቀረበለት። ድርድሩን እኔው እራሴ ተደራድሬ እጨርሰዋለው እንጂ፣ ወደ ጠረጴዛ ድርድር መልሼ አላመጣውም የሚል ምላሽ ሰጠን። በእኛ በኩል ተቋሙ የህዝብ ገንዘብ ያለበት በመሆኑ ግልጽ አሰራር መከተል አለብን የሚል አቋም ወሰድን። በግል የምታደርጋቸውን ድርድሮች የዳሬክተሮች ቦርድ፣ የቤት ገዢዎች አብይ ኮሚቴም አይቀበለውም የሚል ግልጽ ምላሽ ሰጠነው። በገባው እቅድ መሰረት መፈጸም አልቻለም። አሰራሮቹን ስንፈትሻቸው ወደ ቀድሞው የተሳሳተ የማኔጅመንት መንገድ የሚመልሱን ሆነው ስላገኘናቸው፤ አንቀበልም አልን።

 

ከዚህ በኋላ አቶ ኤርሚያስ ያቀረበው እቅድ ተፈፃሚ ማድረግ ባለመቻሉ መንግስት የተለየ አቅጣጫ ይስጠን የሚል አዲስ አቤቱታ አቀረብን። መንግስት ይህንን አቤቱታ ሲመረምር ቆይቶ ጥር 2 ቀን 2008 ዓ.ም. የጠቅላላ ጉባኤ ስብሰባ ጠራ። በዚህ ጠቅላላ ጉባኤ የባለአክሲዮኖችን አቋም ገመገመ። ከ1ሺ 500 በላይ የቤት ገዢዎችን አቋምም ገመገመ። አስራ አንድ ወር ሙሉ የተሰሩትን ሥራዎች ከቴክኒክ ኮሚቴውም ተቀበለ። በመጨረሻም አብይ ኮሚቴው የራሱን ውሳኔ ወሰነ። የመጀመሪያ እርምጃ ያደረገው፣ በጊዜያዊነት የተሰጠውን የህግ ከለላ ማንሳት ነበር። በቀጣይ በሰጠው ደረቅ ቼኮች እንዲታሰር ተደረገ። በሕግ የተያዘ ጉዳይ ነው፣ ወደፊት አብረን የምናየው ነው የሚሆነው። በአቶ ኤርሚያስ ላይ ተጥሎ የነበረው የመፍትሔ ፍለጋ በዚሁ አበቃ።

 

መንግስት ሁለተኛ የመፍትሔ አቅጣጫ ሰጠ። ይኸውም፣ በምን አቅጣጫ ችግሮቹ ሊፈቱ እንደሚችሉ ፕሮፖዛል አቅርቡ አለ። በዚህ መሰረት ቤት ገዢው ፕሮፖዛል ሰርቶ አቀረበ። የቀረበው ፕሮፖዛል የሚያሳየው ያለው ሃብት መሬት ነው። አክሰስ ሪል እስቴት አብዛኛውን ገንዘባችን አባክኖ በጣም ጥቂት በሆነው ገንዘብ መሬት ገዝቷል። ስለዚህም በቤት ገዢው የተገዙት መሬቶችን ለማስተዳደር ሕጋዊ ተቋም መንግስት ፈጥሮልን፣ በሕብረት ሥራ ማሕበር ተደራጅተን ቤት እንድንሰራ ይፍቀድልን። በዚህ ፕሮፖዛል መነሻ መንግስት ጉዳዩን ሲመረምር ቆየ። በዚህ ምርመራ ውስጥ መጀመሪያ ማለቅ ያለበት እኛን በሕብረት ስራ ለማደራጀት የድርጅቱ ሕልውና መወሰን አለበት። ይህንን ለማወቅ የድርጅቱ የሒሳብ ቋት በመንግስት የኦዲት ኮርፖሬሽን ተመርምሮ መታወቅ ነበረበት። በርግጥ ምርመራው ከሚጠበቀው በላይ የዘገየ ነው። መጋቢት 2009 ዓ.ም. የኦዲት ምርመራው ተጠናቆ ለአብይ ኮሚቴው ደርሷል።

 

መንግስት የኦዲት ምርመራውን መነሻ በማድረግ የሰጠው ውሳኔ፣ ቤት ገዢዎቹ የሚደራጁበትን አግባብ መርምሮ እንዲደራጁ ማድረግ፤ በቀረበው የኦዲት ሪፖርት የድርጅቱን ሕልውና መወሰን እና መጠየቅ ያለባቸው ግለሰቦችና ድርጅቶች ተጣርተው ለሕግ እንዲቀርቡ ማድረግ ናቸው።

 

 

 

ሰንደቅ፡- በአደባባይ የሚነገረው አቶ ኤርሚያስ “ከድርጅቱ ገንዘብ መዝረፋቸው” ነው። ለአብይ ኮሚቴው የደረሰው የኦዲት የምርመራ ውጤት ላይ ከድርጅቱ ገንዘብ የዘረፉ ሰዎች በስም የተጠቀሱ አሉ?

 

አቶ አክሎግ፡- ከድርጅቱ ገንዘብ የባከነበትን መንገድ በግልፅ የሚያሳይ የኦዲት ሪፖርት ደርሶናል። እኛ ያየነው የኦዲት ሪፖርት ተጠያቂዎቹን ለመለየት ተጨማሪ ምርመራ በባለሙያ መደረግ ይፈልጋል። እኛ እገሌ ብድር ወስዷል …እገሌ ገንዘብ ወስዷል…እገሌ ድርጅት ከአክሰስ ሪል እስቴት ገንዘብ ወስደዋል የሚለውን አረጋግጠናል። የተሰጠበት አግባብን የሚያጣራው ማጣራት ባለበት አካል ነው።

 

ሰንደቅ፡- ገንዘብ በጥሬው መዘረፉን የሚያሳይ የኦዲት ሪፖርት ደርሷችኋል?

 

አቶ አክሎግ፡- የተወሰደ ገንዘብ እንዳለ ሪፖርቱ ያሳያል። ሆኖም በኦዲት ሪፖርት ገንዘብ ተዘርፏል ተብሎ አይቀመጥም።

 

ሰንደቅ፡- የድርጅቱ ገንዘብ በመሬት ግዢ ላይ የዋለ ነው? ወይንስ በጥሬው የተመዘበረ ነው?

 

አቶ አክሎግ፡- ለምሳሌ ኦዲት ሪፖርቱ ለሌሎች ድርጅቶች አለአግባብ ብድር ተሰጥቷል ይላል፤ ለግለሰቦች አለአግባብ ክፍያ ተፈጽሟል ይላል፤ ማኔጅመንቱና ሠራተኞች የማይገባቸውን ጥቅም አለአግባብ ወስደዋል ይላል፤ ገንዘቡ በዚህ መልኩ ነው የባከነው ብሏል። በተራ አነጋገር “ተዘርፏል” ብሎ ማስቀመጥ ይቻል ይሆናል። ለአሰራር ክፍተቱ ግን የሒሳብ ባለሙያዎች ትርጉም ቢሰጡት የተሻለ ይሆናል። ቁምነገሩ ያለው፣ ለቤት መስሪያ ከተከፈለው ክፍያ አለአግባብ ወጪ መደረጉ ነው።

 

ሰንደቅ፡- ከላይ እንደገለጹልን አቶ ኤርሚያስ ያቀረቡትን እቅድ መፈጸም ባለመቻላቸው በመንግስት አዲስ አቅጣጫ መቀመጡ ነው። አቶ ኤርሚያስ በበኩላቸው “ወደሥራ መግባት ያልቻልኩት ከድርጅቱ ዋና ሥራአስኪያጅ ጋር በተፈጠረ የጥቅም ግጭት ነው። ይኸውም የድርጅቱ ሥራአስኪያጅ ንብረት ለሆነው ማራኪ ሴኪዩሪቲ ሰርቪስ ለጥበቃ የሚከፈል 18 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር ክፍያ እስካልተፈጸመ ድረስ ምንም አይነት ሥራዎች ለመፈጸም ዝግጁ አይደለሁም በማለቱ ነው” ብለዋል። በዚህ ነጥብ ላይ እርስዎ ምን ይላሉ?

 

አቶ አክሎግ፡- በመጀመሪያ ደረጃ ዋና ሥራአስኪያጁን ወደ ድርጅቱ እንዲመጡ ያደረጉት አቶ ኤርሚያስ ከውጭ ከተመለሱ በኋላ ነው። ሥራአስኪያጁ ወደ ድርጅቱ ሲገቡ ከድርጅቱ ጋር የጥቅም ግጭት እንዳይኖር ጥንቃቄ ይደረግ ያለው ቦርዱ ነው። ቦርዱ ይህንን ጥያቄ ያነሳው፣ ቀድሞው ሥራአስኪያጁ አክሰስ ሪል እስቴት ይገባኛል የሚላቸውን መሬቶች የሚጠብቁ የጥበቃው ተቋም ባለቤት ናቸው። በሰጡት የጥበቃ አገልግሎት ያልተከፈላቸው 11 ሚሊዮን ብር በፍርድ ቤት ከሰው አስፈርደዋል። ከጥበቃው ተቋም ጋር ውሎቹን የፈረመው ኤርሚያስ ራሱ ነው። በ2005 ዓ.ም. ከሀገር ኮብልሎ ሲወጣ ፍርድ ቤት ከሰው አስፈርደዋል።

 

አዲሱ ቦርድ ያደረገው ጥበቃውን ከመልቀቅ በፍርድ ቤት ያስወሰንከውን ከሌሎች የእዳ ባለመብቶች ጋር አብሮ የሚታይ ስለሆነ በእዳነት ተይዞ ጥበቃውን ግን ቀጥልልን ተብሎ አዲስ ውል ቦርዱ ፈጽሟል። በዚህ ወቅት ነው ኤርሚያስ የመጣው። ኤርሚያስ ከመጣ በኋላ “የእኔን ችግር የምታውቀው አንተነህ። ከማንም በላይ የምታግዘኝ አንተነህ። የተፈጠረውን ችግር ለመፍታት ታስፈልገኛለህ” ብሏቸው አሳምኖ ያመጣቸው። ቦርዱ ግን አንተ በፈጸምከው ስምምነት መነሻ በፍርድ ቤት ያስወሰነብን ገንዘብ አለ። ይህንን ምንድን ነው የምናደርገው የሚል ጥያቄ ቀረበለት። ኤርሚያስ የሰጠው ምላሽ “በፍርድ ቤት የተሰጠው ውሳኔ የፍርድ ባለመብቶች መብት ሲጠበቅ ተግባራዊ ይደረጋል። አሁን ባለን ግንኙነት ግን በሕግ መከተል፣ በማኔጅመንት እውቀት፣ ችግሩን ከእኔ ጋር ተባብሮ ከመፍታት አኳያ እሱን የመረጥኩበትን መንገድ ብትቀበሉኝ የተሻለ ውጤት አመጣለሁ” አለ። ቦርዱም አቶ ኤርሚያስ ከመጣበት አላማ አንፃር ፍላጎቱን ጠብቆ አጸደቀ።

 

ዋናው ሥራአስኪያጅ ሥራ ከጀመሩ በኋላ አቶ ኤርሚያስ በአደባባይ የማይናገረው ጥያቄ ይዞ ቀረበ። ይኸውም፣ ከዚህ በፊት ውል ያደረኩባቸው ወደ 33 ሚሊዮን ብር የሚጠጋ በኢምፔሪያል ሆቴል ሽያጭ ለኢምፔሪያል ሆቴል ተወካይ ለአቶ ፀጋዬ ሊከፈል ይገባል። ስለዚህም የድርጅቱን ሥራአስኪያጅ 33 ሚሊዮን ብር እዳ አለብን ብለህ ፈርም አላቸው። የብድር ውሉን ከመፈረሜ በፊት ውሉ በቦርድ ተወስኖ ይምጣ የሚል አቋም ሥራ አስኪያጁ ያዙ። የዳሬክተሮች ቦርድ በመሆንህ ብቻ በግል በምትሰጠኝ ትዕዛዝ የብድር ውል አልፈርምም በማለት ተቃውሟቸውን አሰምተዋል። ቦርዱ በሁለቱ መካከል ችግር መኖሩን አውቆ ስብሰባ ተቀምጦ ውሳኔ አስተላልፏል።

 

ቦርዱ የሰጠው ውሳኔ፣ ቦርዱን ሳታስፈቅድ ሥራአስኪያጁን እዳ ፈረም ማለት አግባብ አይደለም። ሁለተኛ፣ ቦርዱ ሳያውቅ እዳ ተቀብያለሁ ብለህ መፃፍህ ትክክል አይደለም ሲል ለአቶ ኤርሚያስ በግልጽ ተነግሮታል። አቶ ኤርሚያስ ግን ሥራ አስኪያጅን መፈረም ፈቃደኛ ካልሆንክ ሥራውን ልቀቅ እና ቦርዱ እኔን ሥራ አስኪያጅ እንዲያደርገኝ ጥያቄ ላቅርብ ይላቸዋል። ሥራ አስኪያጁ በበኩላቸው፣ የሾመኝ ቦርዱ ስለሆነ ቦርዱ ሥራ ልቀቅ ካለኝ እለቃለሁ፤ በራሴ ግን አላደርገውም አሉ። አቶ ኤርሚያስ ግን ለቦርዱ ሥራ አስኪያጁ ሥራ መልቀቅ ስለሚፈልግ መልቀቂያውን አጽድቁለት የሚል ጥያቄ ያቀርባል። ቦርዱ የመልቀቂያውን ጥያቄ ካደመጠ በኋላ፣ አንድ ሥራ አስኪያጅ ከመልቀቁ በፊት “exit report” ማቅረብ አለበት። መልቀቅ የሚፈልግ ከሆነ ሪፖርቱን ያቅርብ አለ። አቶ ኤርሚያስ የሰጡት መልስ “ሥራ አስኪያጁ ሪፖርት ማቅረብ አይፈልግም” የሚል ነበር።

 

ቦርዱ በበኩሉ፣ ሥራአስኪያጅ በቀጥታ አስጠርቶ ለምን ድርጅቱን እንደሚለቅ ይጠይቀዋል። ሥራአስኪያጁ የሰጡት ምላሽ፣ “ለአቶ ጸጋዬ 33 ሚሊዮን ብር እዳ ፈርም አለኝ። ለጋቢ ኢንቨሰትመንት 46 ሚሊዮን ብር እዳ ፈርም አለኝ። ይህንን መፈጸም የምትችል ከሆነ አብረን መቀጠል እንችላለኝ አለኝ። የእኔ መልስ ደግሞ፣ ቦርዱ በአጀንዳነት ተነጋግሮበት በጽሁፍ ውሳኔ ካስተላለፈ እፈርማለሁ አልኩት። ከዚህ ውጪ አልፈርም ብያለሁ። በሁለተኛው ቀን የማትፈርም ከሆነ ሥራ ልቀቅ አለኝ። ቦርዱ ከወሰነ እለቃለሁ። ከዚህ ውጪ ሥራዬን ለመልቀቅ ያቀረብኩት ጥያቄ የለም” አሉ። ይህ ኤርሚያስ ባለበት በቃለ ጉባኤ የተያዘ ነው።

 

በመጨረሻም ኤርሚያስ ለቦርዱ አንድ ጥያቄ አቀረበ። ይኸውም፣ ከእኔ ወይም ከሥራአስኪያጁ ምረጡ? የሚል ሀሳብ አቀረበ። ቦርዱ በሰጠው ምላሽ የሰጠነው ውሳኔ ከግለሰብ መረጣ ጋር የሚያያዝ ሳይሆን፣ ከአሰራር ግድፈት ጋር የሚገናኝ ነው። የተከተልከው መንገድ ስህተት ነው፤ እዳም ለመቀበል አልተወያየንም፣ ሥራአስኪያጁም ሥራ ለመልቅቅ አልጠየቀም። ከዚህ በኋላ ተመሳሳይ ሥራዎች የምትፈጽም ከሆነ ከዳሬክተሮች ቦርድ ኃላፊነት እናነሳሃለን የሚል ማስጠንቀቂያ ተሰጠው። ከዚህ የቦርዱ ውሳኔ በኋላ ኤርሚያስ ከቦርዱም ሆነ ከቤት ገዢዎች ኮሚቴዎች አብሮ መስራት አቆመ። ለተለያዩ ኃላፊዎችም አላሰራ አሉኝ የሚል ደብዳቤ አስገብቷል።

 

 

ሰንደቅ፡- የድርጅቱ ሃብቶች የተገዙት መሬቶች ናቸው። መሬት የመንግስት ነው። ድርጅቱ ካዝና ውስጥ ገንዘብ የለም። ከዚህ አንፃር ለቤት ገዢዎች አለተጨማሪ ክፍያ ቤት ተደራጅታችሁ ለመስራት የቀረበው ፕሮፖዛል ምን ያህል ተግባራዊ የሚሆን ነው?

 

አቶ አክሎግ፡-ድርጅቱ ሃብት አለው፣ እሱም መሬት ነው። መሬት ደግሞ አይሸጥም፣ አይለወጥም የህዝብ ነው። መሬቱ የተገኘው በሕዝብ ገንዘብ ነው። እኛ ያቀረብነው ጥያቄ ግልጽ ነው። የባከኑት ገንዘቦች ወደ ድርጅቶች የሄዱት በመንግስት ኃይል የሚሰበሰቡ ከሆነ ለድርጅታችን ሀብት ናቸው። ሁለተኛው፣ በሕዝብ ገንዘብ የተገዙት መሬቶች ላይ መንግስት ውሳኔ መስጠት ይችላል። መሬቶቹ የቤት ገዢዎቹ እንዲያለሟቸው በመብትነት ከተሰጡ፣ እንዴት መልማት እንዳለባቸው እቅድ ይወጣላቸዋል። መጀመሪያ መሬቶቹን ማግኘት ነው። 

  

 

ሰንደቅ፡- የድርጅቱ ሃብት መሬት ከሆነ፤ መሬት የመንግስት ይዞታ መሆኑ እንዴት ይታያል?

 

አቶ አክሎግ፡- እነዚህን መሬቶች መንግስት የእኔነው ማለት አይችልም።

 

ሰንደቅ፡- መሬት የመንግስት መሆኑ በሕገመንግስት የሰፈረ እውነታ አይደል? ለምሳሌ መሬቱን አስይዞ ገንዘብ የመበደር አሰራር የለም። እንዴት ብላችሁ ነው ግንባታ የምትገቡት?

 

አቶ አክሎግ፡-ሕዝቡን አማክረን ነው ለመንግስት ፕሮፖዛል ያቀረብነው። መንግስት መሬቱን ከሰጠን ተጨማሪ ገንዘብ አውጥተን ለመገንባት ከአብዛኛው ሕዝብ ጋር ተወያይተንበታል፤ በፊርማም የተረጋገጠ ሰነድ ለመንግስት አቅርበናል። በዋናነት ግን ከመንግስት የምንጠብቀው ሙሉ ገንዘባችንን እንዲያስመልስልን ነው። አለአግባብ የበለጸጉትን ሰዎች በሕግ አግባብ እንዲጠየቁ ነው።

 

ሰንደቅ፡- አሁን ባለው የመኖሪያ ቤቶች ግንባታ ዋጋ በተለይ ከአስር እና ከአስራ አምሰት ፎቆች በላይ ለመገንባት ከፍተኛ የገንዘብ አቅም ይጠይቃል። ከቤት ገዢዎቹ መካከል ምን ያህሉ ተጨማሪ ወጪ መክፈል ይችላል?

 

አቶ አክሎግ፡- ለምሳሌ በአንድ ሳይት ያሉ ሰባ ሰዎች አሉ። ገንዘባቸው ሙሉ ለሙሉ ተበልቶ አልቋል። በዚህ ሁኔታ ውስጥ እያሉ መሬት ተሰጣቸው እንበል፤ መጀመሪያ ያላቸው አማራጭ ባላቸው አቅም መሬቱን ወደ ቤት ግንባታ ለመለወጥ መንቀሳቀስ ነው። በእንቅስቃሴያቸው ወቅት የገንዘብ እጥረት ይገጥማቸዋል ወይንስ አቅም ኖሯቸው ይጨርሳሉ? በጊዜው የሚታወቅ ነው የሚሆነው። ዛሬ ላይ ሆኜ መተንበይ አልችልም። ሕዝቡ ግን ሙሉ ለሙሉ ያልከፈለው ክፍያ በመኖሩ መሬቱ ሲሰጠው ክፍያውን አጠናቆ ቢያንስ መሰረት ማውጣት ይችላል። መሰረት ማውጣት ከተቻለ በሀገሪቷ ሕግ መሰረት ብድር በማፈላለግ ገንብቶ ሊጨርስ የሚችልበት እድልም አለ። 

     

 

ሰንደቅ፡- መንግስት መሬቱን ሊያስረክባችሁ ከውሳኔ የደረሰበት ሁኔታ አለ እንዴ?

 

አቶ አክሎግ፡-መሬቶቹን በአደራ ተረክቧል። ነገሮቹን እያጣራ ነው የሚገኘው። አጣርቶ ከጨረሰ በኋላ ያስረክበናል የሚል እምነት አለን።   

 

ሰንደቅ፡- ከአቶ ኤርሚያስ ጋራ በጋራ ለመስራት ያደረጋችሁት ጥረት እንደተጠበቀ ሆኖ፤ አቶ ኤርሚያስ “ቤት ገዢዎች ተጨማሪ ክፍያ ሳያወጡ ከአውሮፓና ከቻይና ኩባንያዎች ጋር በሽርክና በመስራት ቤት ገንብቼ ማስረከብ እችላለሁ። እቅዴንም ለጠቅላይ ሚኒስትሩ አስገብቻለሁ” እያሉ ነው። በርግጥ የአቶ ኤርሚያስ እቅድ ተጨባጭና መሬት ላይ የሚወርድ ሆኖ ካገኛችሁት ለመቀበል ዝግጅ ናችሁ?

 

አቶ አክሎግ፡-አቶ ኤርሚያስ ስለተናገረ ብቻ አናምነውም። ከዚህ በፊትም ተመሳሳይ እቅድ አለኝ ብሎን ብዙ ርቀት ሔደን አንዳችም የፈጸመው ነገር የለም። አሁንም አዲስ እቅድ አለኝ የሚለውን፣ በመንግስት ከተረጋገጠ ብቻ እንቀበላለን። ምክንያቱም የእኛ አላማ መኖሪያ ቤት ማግኘት ብቻ ስለሆነ ነው። በድጋሚ ሕዝብን ለማጭበርበር የተቀየሰ ዘዴ ከሆነ ግን አንሞክረውም።¾         

 

ይምረጡ
(1 ሰው መርጠዋል)
757 ጊዜ ተነበዋል

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us