ቤት ገዥው ለሥራ ማስኬጃ ያዋጣው ገንዘብ ለምን እንደዋለ ያውቀው ይሆን?

Wednesday, 05 July 2017 12:34

 -    ወደ መፍትሄው ከመሄዳችን በፊት ካለፈው ስህተታችን መማር አለብን

 

ከአክሰስ ሪል እስቴት በስማቸው ቤት የገዙ ደንበኞች

 

 

በአክሰስ ሪል እስቴት በቅርቡ በአቶ ኤርሚያስ ጠቅል አመልጋ የቀድሞ የቦርድ ሊቀመንበር በተሰጠው መግለጫ እና ከዚህ መግለጫ በኋላ የቤት ገዥ አብይ ኮሚቴ እና አሁን በሥራ ላይ ያለው የአክሰስ ሪል እስቴት የዲሬክተሮች ቦርድ በጋራ በሰጡት መግለጫ ላይ እኛ ቤት ገዥዎች የምንለው አለ። በቅድሚያ የቤት ገዥ አብይ ኮሚቴ እና የዲሬክተሮች ቦርድ በጋራ የሰጡበት መግለጫ ተመሳሳይ ባሕርያቸውን የሚያሳይ ነው።

 

ይኸውም አሁን በሥራ ላይ ያለው ቦርድ ምንጩ ከአክሰስ Share Holders ሲሆን፤ ለተመረጠበት ዓላማ በጠንካራ ጐኑ የቆመ አይመስልም። ከዚህም በመነሳት የአክሰስ ሪል እስቴት ኩባንያ መብቱንም ግዴታውንም በእኩል ለማስጠበቅ ገለልተኛ እና ጠንካራ በሕጋዊ መንገድ የተመረጠ ቦርድ እንደሚያስፈልገው አሻሚ አይደለም። አሁን ካሉት የዳሬክተሮች ቦርድ መካከል ሁለት ሦስተኛው በሚሊዮኖች በሚቆጠር ገንዘብ በስማቸው ቤት ከአክሰስ የገዙ ናቸው። በሌላ በኩል ደግሞ የአክሰስን ኩባንያ ሼር ከ25,000 እስከ 100,000 በሚደርስ ገንዘብ አክስዮን ያላቸው ሆነው እናገኛቸዋለን። ስለዚህ ከወከላቸው አብዛኛው ቤት ገዥ ላልሆነው Share Holders መብትና ጥቅም ሚዛናዊ ውሣኔ ለመወሰን ይሳናቸዋል። ሁልጊዜም በድምፅ ብልጫ በማለት ሚዛኑ ወደ ቤት ገዥ እና Share Holders በመሆን አጣምረው ለያዙት የዲሬክተሮች ቦርድ ይሆናል።

 

ሌላው ማኔጅመንትን በተመለከተ ያለንን ልዩነት ማስቀመጥ ተገቢ ነው። ይኸውም በዚህ የዲሬክተሮች ቦርድ የሚሰየመው ሥራ አስኪያጅ ገለልተኛ፣ ከዚህ ቀደም ከድርጅቱ ጋር ምንም የጥቅም ንክኪ የሌለው፣ በዕውቀት ላይ የተመሠረተ፣ በተለይም በኮንስትራክሽን ማኔጅመንት ባለሙያ መሆን ሲገባው፣ ፍጹም ተቃራኒ በሆነ መልኩ ተሰይሞ ይገኛል።

 

በአሁኑ ጊዜ ያለው የአክሰስ ሪል እስቴት ሥራ አስኪያጅ ከዚህ ቀደም በአክሰስ ኩባንያ በኃላፊነት እየሰሩ፣ በሌላ በኩል የግል ድርጅት (ማራኪ ፕሮፌሽናል የጥበቃ ድርጅት) አቋቁመው ከአክሰስ ጋር የጥቅም /Contrat/ ሥራ የነበራቸው፤ አክሰስ ሪል እስቴትን በመክሰስ በግምት ከሃያ ሁለት ሚሊዮን ብር በላይ ያስፈረዱ እና በአሁኑ ሰዓት ጥቅማ ጥቅምን ሳይጨምር በወር ብር 50,000.00 /ሃምሳ ሺህ ብር/ ደመወዝ እየተከፈላቸው ላለፉት ሁለት ዓመት ጀምሮ በአክሰስ ሪል እስቴት ሥራ አስኪያጅ ሆነው የሚገኙ እና የዚህ ቦርድ ድጋፍ ያልተለያቸው ናቸው።

 

ለአንባቢያን እና ለባለድርሻ አካላት ግንዛቤ ይረዳ ዘንድ፣ አቶ ኤርሚያስ ከሀገር ከመውጣቱ በፊት ለማራኪ የጥበቃ ድርጅት በወር ብር 1,117,000.00 /አንድ ሚሊየን አንድ መቶ አስራ ሰባት ሺህ ብር/ ለጥበቃ ይከፈል የነበረ ሲሆን፤ ይህ የአክሰስ ንብረት አሁን ደግሞ በብር 38,812.50 /ሰላሳ ስምንት ሺህ ስምንት መቶ አስራ ሁለት ብር ከሃምሳ ሣንቲም/ በዚሁ የጥበቃ ድርጅት እየተጠበቀ መሆኑን የሚያሳይ ሠንጠረዥ ተያይዟል። ይህንን ልዩነት ሕዝብና መንግሥት ይፍረደው። በተመሳሳይ የሥራ አገልግሎት በፊት እና አሁን የሚከፈለውን ማነፃፀር ጥሩ ማሳያ ነው።

 

ከዚህም በተጨማሪ የሂሣብ ባለሙያ የሆኑት የቀድሞው የድርጅቱ የፋይናንስ መምሪያ ዋና ኃላፊ አሁንም በወር ብር 20,000.00 /ሃያ ሺህ ብር/ ደመወዝ በድርጅቱ ተቀጥረው የሚገኙ ናቸው።

 

የቤት ገዥ አብይ ኮሚቴን በተመለከተ የሚከተለውን አቅርበናል። ይህ ኮሚቴ የአቶ ኤርሚያስ ከሀገር መውጣትን ተከትሎ በግርግር ያለምንም ማጣራት የተመሠረተ ነው። በጥቂት የቤት ገዥዎች ብቻ የሚታወቀው ይህ የቤት ገዥ አብይ ኮሚቴ ሦስት አምስተኛዎቹ (3/5) ሰብሳቢውን አቶ አክሎክ ሥዩምን ጨምሮ በስማቸው ቤት የገዙ የአክሰስ ሪል እስቴት ደንበኞች አይደሉም፤ ይህን የቤት ገዥ አብይ ኮሚቴ በበላይነት እና በውሣኔ ሰጭነት የሚመሩት ከአንድ ግለሰብ ለቤት መግዣ ከብር 400,000 ሺህ ብር በላይ ያልከፈሉ ቤት ገዥ በጉዳይ አስፈጻሚነት በውልና ማስረጃ ውክልና የተሰጣቸው እንጂ በቀጥታ ቤት የገዙ የአክሰስ ደንበኛ አይደሉም።

 

ነገር ግን ከቤት ገዢው መዋጮ ላይ ብር 450,000.00 (አራት መቶ ሃምሳ ሺህ ብር) ከአክሰስ ሪል እስቴት ደግሞ በወር ከ15 እስከ 20,000 ብር ደመወዝተኛ ሆነው የአክሰስ ሪል እስቴት በጉዳይ አስፈጻሚነት እንዲሁም አቶ አለምነህ ደሴ በደመወዝ ብር 6,000 /ስድስት ሺህ ብር/ ተቀጥረው ከውልና ማስረጃ ምዝገባ ጽ/ቤት በአሁኑ ሥራ አስኪያጅ ሥልጣን ተሰጥቷቸዋል።

 

ስለዚህ የአክሰስ ደንበኞች በመሆን ቤት ከገዙት ጋር የአመለካከት ልዩነት በስፋት ይታያል። የዛሬ ሁለት ዓመት ገደማ ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት በተገኙበት መንግሥት በጠራው የቤት ገዥዎች ጠቅላላ ስብሰባ ላይ የቤት ገዥው አቋም ወስዶ የወጣው በውላችን መሠረት ቤታችንን ካልሆነም በውላችን መሠረት ገንዘባችንን የሚል ነበር። መንግሥትም ይህን ለማስፈጸም ቃል የገባበት ቀን መሆኑ ይታወሳል።

 

ይህ በእንዲህ እንዳለ የቤት ገዥ ጠቅላላ ጉባዔ ሳያውቀው በኮሚቴው ፍላጐት ብቻ በማህበር ተደራጅቶ መሬት መረከብ የሚል ሃሳብ መሰራጨት ተጀመረ። ይህም ግልፅነት የሌለው አካሄድ በሦስት መደብ መከፋፈልን በቤት ገዥዎች ዘንድ ፈጥሯል። አንደኛው፤ በአብይ ኮሚቴ ሰብሳቢ የሚመራው የወኪል ቡድን አንድ ማህበር አቋቁመን መሬቱን በሙሉ በአንድ የቤት ገዥ ማህበር እናስተዳድረዋለን በማለት የተፈጠረውን የቤት ገዥዎች ችግር ለሥራ መተዳደሪያ ሊያደርገው ሲያመቻች ይታያል።

 

ሁለተኛ፤ በስሙ ቤት በመግዛት የአክሰስ ሪል እስቴት ደንበኛ የሆነው የመጨረሻ አማራጭ ከጠፋ በየራሳችን ሳይት 19 ማህበር በማቋቋም የየራሳችን ቦታ እንረከብ ይላል።

 

ሦስተኛው፤ ያልተሰባሰበው መደብ መጀመሪያውኑም ቤት ለመግዛት አስቤና ገንዘብ የከፈልኩት ቁልፍ ለመረከብ ስለሆነ በውሉ መሠረት ቤቴን ወይም ገንዘቤን ከዚህ በኋላ በማህበር ተደራጅቶ ሌላ ገንዘብ ከኪሴ ማውጣት አልፈልግም ይላል።

 

የቤት ገዥ የብር 5,000 /አምስት ሺህ ብር/ መዋጮ በተመለከተ ያለንን መረጃ በዚህ መልክ አስቀምጠነዋል። ከቤት ገዥው በአንድ ቤት 5,000.00 /አምስት ሺህ ብር/ በድምሩ ከስድስት ሚሊየን ብር በላይ ከቤት ገዥው ተሰብስቧል። ከዚህም ውስጥ ብር 3,638,311.98 /ሦስት ሚሊየን ስድስት መቶ ሰላሳ ስምንት ሺህ ሦስት መቶ አስራ አንድ ብር ከዘጠና ስምንት ሣንቲም/ ሚያዝያ 20 ቀን 2009 ዓ.ም ከአክሰስ ፋይናንስ መምሪያ ተ/ሥ/አስኪያጅ በአቶ ኃ/ሚካኤል ምሥጋናው እንዲሁም በ12 እና 15/09/2009 ዓ.ም በአቶ አክሎክ ሥዩም ፊርማ የውስጥ ማስታወሻ ልውውጥ በሠንጠረዡ እንደሚታየው /4 ገጽ ሰነድ ተያይዟል/ የአክሰስ ኩባንያ በብድር ወሰደ በማለት የአክሰስን ሠራተኞች እና የዳይሬክተሮች ቦርድ /አበል/ ደመወዝ፣ ነዳጅ፣ ስልክ እና ትራንስፖርት፣ የአዳራሽ ኪራይ እና ሌሎችም በሚል ወጪ ተደርጓል።

 

ከዚሁ ከቤት ገዥ መዋጮ ላይ ብር 450,000.00 /አራት መቶ ሃምሣ ሺህ ብር/ ሌሎች የመኪና የነዳጅ፣ የሻይ፣ የጽዳት ጥቅማ ጥቅሞችን ሳይጨምር ለቤት ገዥ አብይ ኮሚቴ ሰብሳቢ በአቶ አክሎክ የተከፈለ በሚል ተይዟል። ከዚህም በተጓዳኝ አቶ አክሎክ በአክሰስ የወቅቱ ሥራ አስኪያጅ በውልና ማስረጃ የተመዘገበ የአክሰስ ሪል እስቴት የጉዳይ ማስፈጸም ሥልጣን ተሰጥቷቸዋል። የድርጅቱን መኪና ነዳጅና ደመወዝ ይጠቀማሉ። ይህ የተዋጣ ገንዘብ በምን ላይ እንደዋለ አብዛኛውን የቤት ገዥው አያውቀውም። የቤት ገዥውም ለጠቅላላ ጉባዔ ሪፖርት ተደርጐ አያውቅም።

 

አቶ ኤርሚያስ የሰጡትን መግለጫ በተመለከተ ሃሳባችን ይህንን ይመስላል። አቶ ኤርሚያስ ጠ/አመልጋ ተዝቆ የማያልቅ ስህተት መፈጸሙ የሚካድ አይደለም። ሕዝብ በነበረው አመኔታ ከ1 ነጥብ 4 ቢሊዮን ብር በላይ በመክፈል በአንድ ወረቀት /ደረሰኝ/ ብቻ ተረክቧል፤ ይህ ገንዘብ ወደ አክሰስ ሪል እስቴት መግባቱን ያዩ የብዙ ሰዎችን፣ ድርጅቶችን፣ ኪራይ ሰብሳቢዎችን ቀልብ ስቧል። በዚህም የተነሳ ሕጋዊና ሕጋዊ ባልሆነ መልኩ ከአክሰስ ሪል እስቴት ጋር በሚደረጉ ስምምነቶች ድርጅቱ በውስጥም በውጭም ተመዝብሯል።

 

አቶ ኤርሚያስ አስተካክላለሁ፣ ሕዝቡንም እክሳለሁ በማለት የሥራ አፈጻጸም ፕሮፖዛል ይዘው ወደ ሀገር ውስጥ በመግባት በድጋሚ የቦርድ ሰብሳቢ መሆናቸው አይዘነጋም። በድምፅ ብልጫ ተሸንፈው እስከተወገዱ ድረስ። አሁን ያቀረቡት እክሳለሁ አለምንም ተጨማሪ ወጪ በአጭር ጊዜ ውስጥ ወደ ሥራ በመግባት አስረክባለሁ፣ ለቤት ገዥው ዋስትና እሰጣለሁ፣ ከውጭ ኩባንያ ጋር በጋራ እሰራለሁ የሚሉት ጉዳይ አዋጭነቱን እና የጋራ ጥቅምን የሚያስከብር መሆኑን ለዜጐች የቆመው መንግሥት አጥንቶ ውሣኔ እንዲሰጥበት ለመንግሥት የምንተወው ጉዳይ ነው።

 

ይህንን የተፈጠረውን የአክሰስ ሪል እስቴት ጉዳይ ለመፍታት በማንኛውም ግለሰብ፣ ድርጅት ወይም መንግሥት መፍትሔ በማግኘት የሚቀርብ የአፈጻጸም ፕሮግራም ወደ ተግባር ከመግባቱ በፊት መንግሥት /የቴክኒክ ኮሚቴ/ ካለፈው ስህተት ተምሮ መወሰድ የሚገባቸው ገንቢ አስተያየቶችን ማስቀመጥ እንፈልጋለን።

 

1ኛ. ገለልተኛ ነፃ መብት እና ግዴታውን የሚያውቅ የጥቅም ግጭት የሌለበት ሕጋዊ ሥርዓትን የተከተለ የዳይሬክተሮች ቦርድ አባላት በጠ/ጉባዔ ማስመረጥ፣

 

2ኛ. በዳይሬክተሮች ቦርድ የሚመረጠው የድርጅቱ ሥራ አስኪያጅ ገለልተኛ ነፃ የሆነ ከዚህ ቀደም ከአክሰስ ሪል እስቴት ጋር ምንም ዓይነት የጥቅም ንክኪ የሌለበት እና በዕውቀት ላይ የተመሠረተ ይህንንም መንግሥት /የቴክኒክ ኮሚቴ/ አጣርቶ የሥራ አስኪያጅ ሥልጣኑን ሲያጸድቅለት፣

 

3ኛ. ምንም እንኳን ጠንካራ የቤት ገዥ ኮሚቴ አስፈላጊ መሆኑ ቢታመንም የቤት ገዥ ኮሚቴ ትልቅ ሥልጣን ቤቱን ለመረከብ ሲባል ለመንግሥት አቤቱታ ማሰማት እንጂ ወደ ግንባታ ሙያ ገብቶ አንድ ብሎኬት እንደማያስቀምጥ የሚታመን ስለሆነ የአክሰስ ሪል እስቴት የቤት ገዥ ደንበኞች ኮሚቴ በአዲስ መልክ በስማቸው ቤት በገዙ ደንበኞች መዋቀር ይኖርበታል፣

 

4ኛ. እስካሁን ጉዳዩን በማወሳሰብ አክሰስን ሪል እስቴትን የተቆጣጠረውን ገፍቶ በማውጣት በሕጋዊ መንገድ ሜዳውን ለሥራ የተመቻቸና እንዲሁም ለመንግሥት ቁጥጥር የተመቸ ግልጽ እና ከሙስና የፀዳ መሆን ይኖርበታል፤

 

5ኛ. ከዚህ በኋላ የሚደረጉ ማንኛውም አፈጻጸም ለቤት ገዥው ዋስትና ወይም ኢንሹራንስ ቅድሚያ የሚሰጠው ጉዳይ ሊሆን ይገባል።

 

6ኛ. የቤት ገዥውም ሆነ ሼር ሆልደሩ እምነቱ በመንግሥት ላይ ብቻ የተንጠለጠለ በመሆኑ መንግሥት ቤት ገዥው ቤቱን እስኪያገኝ ድረስ ቦርዱንና ማኔጅመንቱን በቅርብ የሚከታተል አፈጻጸሙን የሚገመግም ተቆጣጣሪ የመንግሥት አካል ሊኖር ወይም ሊመደብለት ይገባል።

 

7ኛ. በሙስና እና በኪራይ ሰብሳቢነት እንዲሁም ሕግን ባልተከተለ ኮንትራት በአክሰስ ሪል እስቴት ውስጥ እጃቸውን ያስገቡ በሕግ ሊጠየቁ ይገባል።

 

8ኛ. በመንግሥት የተቋቋመው የችግር ፈቺ አብይ ኮሚቴ የጉዳዩን መጓተት እና የቤት ገዢውን ችግር ከዚህ ወደ ባሰ ውስብስብ ነገር እንዳይገባ በጥልቀት ተገንዝቦ ሁሉንም ወገን በሚያረካ መልኩ ውሣኔ ሊያስተላልፍ ይገባል።

 

 

 

 

 

 

ከበሮ ሲያዩት ያምር ሲይዙት ያደናግር

ከኤርሚያስ ጠቅል አመልጋ

ባለፈው ሳምንት የአክሰስ ሬል እስቴት ቤት ገዢዎች ኮሚቴ ስብሳቢ እና የዲሬክተሮች ቦርድ ሰብሳቢ  በሰጡት የፕሬስ መግለጫዎች እንዳየነው ምንም አይነት መሬት ወርዶ ተግባራዊ ሊሆን የሚችል የመፍትሄ እቅድ የላቸውም። የሰንደቅ ጋዜጣ አዘጋጅ በቀጥታ “የናንተ የመፍትሄ እቅድ ምንድን ነው?’’ ብሎ ለጠየቃቸው ጥያቄ የተሰጠው መልስ የተጨበጠ እቅድ እንደሌላቸው የሚያሳይ ነው። ቃል በቃል እቅዳቸው የሚከተለው ነው። “መሬቶቹ ለቤት ገዢዎቹ እንዲያለሙዎቸው በመብትነት ከተሰጡ፤ እንዴት መልማት እንዳለባቸው እቅድ ይወጣላቸዎል። መጀመርያ መሬቶቹን ማግኘት ነው’’። ቀጥሎ ለቀረበላቸው የእቅዳቸው የግንባታ ፋይናንስ ምንጭ ምን እንደሆነ ጥያቄ፤ የሰጡት መልስ የሚከተለው ነው “ህዝብን አማክረን ነው ለመንግስት ፕሮፖዛል ያቀረብነው። መንግስት መሬቱን ከሰጠን ተጨማሪ ገንዘብ አውጥተን ለመገንባት አብዛኛው ህዝብ ጋር ተወያይተንበታል፤ በፊርማም የተረጋገጠ ሰነድ ለመንግስት አቅርበናል። በዋስትናነት ግን ከመንግስት የምንጠብቀው ሙሉ ገንዘባችንን እንዲያስመልስልን ነው። አለአግባብ የበለፀጉትን ሰዎች በህግ አግባብ እንዲጠየቁ ነው’’ ብለዋል።

ቀጥሎም አሁን ባለው የመኖሪያ ቤቶች ግንባታ ዋጋ በተለይ ከአስር እና ከአስራ አምስት ፎቆች በላይ ለመገንባት ከፍተኛ የገንዘብ አቅም ይጠይቃል። ከቤት ገዢዎች መካከል ምን ያህሉ ተጨማሪ ወጪ መክፈል ይችላሉ@ ተብለው ሲጠየቁ የሚከተለውን መልስ ሰጥቶታል፤ “ለምሳሌ በአንድ ሳይት ያሉ ሰባ ሰዎች አሉ። ገንዘባቸው ሙሉ ለሙሉ ተበልቶ አልቋል። በዚህ ሁኔታ ውስጥ እያሉ መሬት ተሰጣቸው እንበል፤ መጀመሪያ ያላቸው አማራጭ ባላቸው አቅም መሬቱን ወደ ቤት ግንባታ ለመለወጥ መንቀሳቀስ ነው። በእንቅስቃሴያቸው ወቅት የገንዘብ እጥረት ይገጥማቸዋል ወይንስ አቅም ኖሯቸው ይጨርሳሉ? በጊዜው የሚታወቅ ነው የሚሆነው። ዛሬ ላይ ሆኜ መተንበይ አልችልም። ሕዝቡ ግን ሙሉ ለሙሉ ያልከፈለው ክፍያ በመኖሩ መሬቱ ሲሰጠው ክፍያውን አጠናቆ ቢያንስ መስረት ማውጣት ይችላል። መሰረት ማውጣት ከተቻለ በሀገሪŸ ሕግ መስረት ብድር በማፈላለግ ገንብቶ ሊጨርስ የሚችልበት እድልም አለ።

እስቲ ይሄን “እቅድ’’ እንደው በትንሹ እንˆን ወደ ተራ ሂሳብ እናውርደው፤ ሁለት ሺህ ቤት ገዢዎች አሉ እንበል። እያንዳንዱ ቤት በአማካይ 125 ሜትር ካሬ ይሆናል ብለን እናስብ። በአሁኑ ግዜ ግንባታው በትንሹ በሜትር ካሬ10,000 ብር ይፈጃል። ይህ ማለት ግንባታው ቢያንስ 2.5 ቢልዮን ብር ይፈጃል ማለት ነው።

ቤት ገዢዊች ከVAT ውጭ ለአክሰስ ሬል እስቴት የከፈሉት ብር 1.2 ቢልዮን ብር ነው። በሁለት ሺህ ቤት ገዢ ሲካፈል በአማካይ እያንዳንዱ ቤት ገዢ የከፈለው 600.000 ብር ይሆናል። በትንሹ ለግንባታ የሚያስፈልገው ተጨማሪ 2.5 ቢልዮን ብር ለ2000 ሰዎች ሲካፈል ከየአንዳንዱ ቤት ገዢ የሚፈለገው ተጨማሬ ክፍያ 1,250.000 ብር ይሆናል ማለት ነው። የአቶ አክሎግ “እቅድ’’ ይሄ ነው። ይሄን ሂሳብ እንˆን የሰሩት አይመስለኝም። ቤት ገዢው እንˆን ይሄን ብር ሊያዋጣ አምስት አምስት ሺህ ብር ለጊዜያዊ ስራ ማስኪያጃ ካዋጣ በኋላ ቦርዱና ኮሚቴው ብሩን ጨርሶ ቤት ገዢው ተጨማሬ አምስት ሺህ ብር አልከፈልም ስላላቸው፣ የድርጅቱ ሰራተኞች ተሰናብተው ፅ/ቤቱ ራሱ ተዘገቶ ይገኛል።

 “መንግስት የተበተነውን ብር ይሰብስብልን እና ግንባታውን እንናካሄድበታለን’’ የሚለውም “እቅድ’’ እንዲሁ ከተራ ሂሳብ ውጭ የሆነና ግንዛቤ የጎደለው አሳሳች “እቅድ’’ ነው። ከዚህ በፊት በተደጋጋሚ እንደገለፅኩት የድርጅቱ ግርድፍ ሂሳብ እንደሚከተለው ነው።

 

 

· የተሰበሰበው ብር 1.4 ቢልዮን ነው።

· ለVAT ለመንግስት የተከፈለው 200 ሚልዮን ብር ነው።

· ለኮንትራክተሮች የተከፈለው 500 ሚልዮን ብር ነው።

· ለመሬት የተከፈለው 350 ሚልዮን ብር ነው።

· ከውጭ ለግንባታ ብረት ማስመጫ የተከፈለው ብር 70 ሚልዮን ብር ነው።

· ለቤት ገዢዎች ተመላሽ የተደረገው ብር 80 ሚልዮን ብር ነው።

· ለአማካሪዎች ለደሞዝ ለሽያጭ ኮሚሽን ለቤት ክራይ ለጥበቃ ወዘተ የተከፈለው ወደ 70 ሚልየን ብር ነው።

· ሲደመር አንድ ቢልዮን ሁለት መቶ ሰባ ሚልዮን ይሆናል። ቀሪው ተሰብሳቢ ብድሮችና እዳዎች ወደ 150 ሚልዮን ብር ይሆናሉ። ከሚያስፈልገው የገንባታ ሂሳብ ጋር ሲተያይ የትም አይደርስም።

እንዲህ አይነት እቅድ፣ እቅድ አይደለም። በእነዚህ ሰዎች አቅም ቤት ገዢው መቼም ቤቱን አያገኝም። መንግስትም ችግሩን ለመፍታት ለህዝብ ቃል የገባውን አደራ አይወጣውም። ነገሩን ከጭቃው ወደ ማጡ መክተት ማለት ነው። ከበሮ ሲያዩት ያምር ሲይዙት ያደናግር ማለት ይሄ ነው። በእኔ በኩል ሂሳቤን በደንብ ሰርቸዋለሁ። ፋይናንስ ምን እንደሆነ እና እንዴት እንደሚገኝ በተግባር አውቃለሁ። ይሄ የማይገፋ ተራራ የሆነባቸው ፈተና፣ ለእኔ መደበኛ ስራዬ ነው። የማያጠራጥርና የማያዳጋም ቤት ገዢውን ለተጨማሬ ክፍያ የማይጋርድ መንግስትንም ከዚህ ውዝግብ የሚገላግል ተጨባጭና አስተማማኝ እቅድ ይዜ ቆምያለሁ። ወደ አይምሮአችን እንመለስና፣ ይሄን ነገር መልክ እናስይዘው። በግለሰቦች የግል ጥላቻ፤ የግል የጥቅም ፍላጎቶችና ግጭቶች ምክንያት ህዝብ መተራመስ አይገባውም። መንግስት እንደ መንግስት ለአንዴና ለመጨረሻ ግዜ ሊዳኝን ይገባል።

ይምረጡ
(2 ሰዎች መርጠዋል)
545 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 879 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us