የባዮ-ቴክኖሎጂ እና የባዮ-ሴፍቲ ፖሊሲ አውደ ጥናት፤ እምቅ ፍላጎቶች ምንድን ናቸው?

Wednesday, 26 July 2017 13:11

 

ሐምሌ 17 ቀን 2009 ዓ.ም. ዘመናዊ ጥበብ ሕይወት እና ደህንነት ሕይወት ላይ የተዘጋጀ የፖሊሲ አውደ ጥናት በአዲስ አበባ ሒልተን ሆቴል ተደርጓል።

በዚህ የፖሊሲ አውደ-ጥናት ላይ፣ የባዮ-ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት በዶክተር ካሳሁን ተስፋዬ፤ የኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት በዶክተር እንዳለ ገብሬ፤ የኢትዮጵያ ብዝሃ ሕይወት ኢንስቲትዩት በዶክተር መለሰ ማሪዮ፤ እና የአካባቢ የደንና አየር ንብረት ለውጥ ሚኒስቴር በዶክተር አየለ ሄገና በመወከል በባለድርሻነት በፓናል ውይይቱ ተሳታፊ ነበሩ።

እንዲሁም በፖሊሲ አውደ-ጥናቱ ተሳታፊ ከነበሩት መካከል የምዕራብ አፍሪካ የኔፓድ ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ጄሬሚ ኡድራኦጎ ተገኝተዋል። የኮሜሳ የባዮ-ቴክኖሎጂ ሲኒየር የፖሊሲ አማካሪ የሆኑት ዶክተር ጌታቸው በላይ ተሳታፊ ነበሩ። በተጨማሪም ከሸማቾች ማሕበር፣ ከመንግስት አካላት፣ ተመራማሪዎች፣ የግል የጥጥ እርሻ ማሕበራት፣ መቀሌ ዩኒቨርስቲ፣ ጅማ ዩኒቨርስቲ እና ሌሎች ባለድርሻ አካላትም ተሳታፊ ነበሩ።

በዚህ ጽሁፍ የአውደ ጥናቱን እምቅ ፍላጎት ምን ይመስላል? ለምን የፓናሉ ተሳታፊዎች ላለመነካካት ወስነው ውይይቱ ላይ መቅረብ ፈለጉ? የሚሉትን ሃሳቦች በወፍ በረር ለመመልከት የቀረበ ነው። መልካም ንባብ።

የፓናሉ የፖሊሲ ውይይት ማዕከላዊ ነጥብ ተደርጎ መውሰድ የሚቻለው፣ “ጠንቅን መከላከል” ቅድሚያ መሰጠት አለበት በሚሉ አካላት እና “ቴክኖሎጂውን ለማሸጋገር” ከፍተኛ ፍላጐት ባላቸውና ማሸጋገር በቻሉ ባለሙያዎች መካከል የቀረበ ውይይት ነበር።

በዚህ የፓናል ውይይት ላይ መታዘብ የሚቻለው፣ ተሳታፊ ከነበሩ ባለድርሻ አካላት ሲደመጥ የነበረው የባዮቴክኖሎጂ ውጤቶችን ለመጠቀም ሁሉም ፈቃደኛ ናቸው፤ ወደሥራ የገቡ የባዮቴክኖሎጂ የምርምር ውጤቶች መኖራቸውን በአብነት ያቀረቡም ነበሩ። ከባለድርሻ አካላት የቀረበው የልዩነት ጥያቄ፣ በልውጥ ሕያው (Genetically modified organism) የሚዘጋጁ ዝርያዎችን በተመለከተ ሰፊና አሳማኝ ውይይት መደረግ አለበት የሚል መከራከሪያ ነው። ከባዮቴክኖሊጂ የምርምር ውጤቶች መካከል አንዱ በሆነው በልውጥ ሕያው ላይ ምርምርና አጠቃቀም ላይ ግልጽ እና የማያሻማ ምላሽ የተጠየቀበት ብቻ ነው። ውይይቱም በዚህ ላይ ማተኮር ሲገባው፣ ፖሊስ ለማውጣትና ማስፈጸሚያ መመሪያዎችን ለማዘጋጀት በሚል ሽፋን መደረግ አልነበረበትም። “ማን ያውቃል ቀደም ብሎም የተዘጋጀ የፖሊሲ ሰነድና ማስፈጸሚያ ሰነዶች ሊኖሩም ይችሉ” ይሆናል፤ ስላልቀረበ ግን ተዘጋጅቷል ተብሎ መደምደም አይቻልም።

በፓናል ውይይቱ ላይ ትኩረት ከሳበው አንዱ፣ የቀረቡት አራቱም ሳይንቲስቶች አንዱ ባቀረበው የጥናት ወረቀት ላይ ሌላኛው አስተያየት አይሰጡም። አራቱም ተጠባብቀው ሳይነካኩ ውይይት ማድረግን መምረጣቸው ገራሚም ነበር። ከመካከላቸው የኢትዮጵያ ብዝሃ ሕይወት ኢንስቲትዩት ኃላፊ ዶክተር መለሰ ማሪዮ በልውጥ ሕያው ላይ ያላቸውን አሉታዊ ግንዛቤ ለመድረኩ አቅርበው ካስረዱ በኋላ፣ ከሌሎቹ ዶክተሮች ጋር ብዙም ያልራቀ መደምደሚያ ማቅረባቸው አስገራሚ ነበር። ይህንን መሰል ክርክር አልባ ከከፍተኛ የሳይንስ ጠበብቶች የሚጠበቅ አይደለም፤ አይገባምም።

ምክንያቱም አብዛኛውን ጊዜ ሳይንቲስቶች የምርምር ውጤቶችን ያቀርባሉ ተብሎ ነው የሚታመነው። ባገኙት የምርመር ውጤት መነሻም በእውቀት ቆመው መከራከር ስለሚጠበቅባቸው ነው። ለፖሊሲ አውጪውም ቢሆን የምርምር ውጤት ነው ተብሎ ስለሚወሰድ ለመወሰን አይቸግርም። እንዲሁም ባለድርሻ አካላቱ በአንድ ልብ ለመወሰን አይቸገሩም። ከዚህ ውጪ የሚሆነው፣ በተፅዕኖ ከላይ ወደታች የሚወረወር የፖሊሲ  አቅጣጫ የውይይት መድረክ ነው። ባለድርሻ አካላት ባይቀበሉትም፣ እንዲተገብሩት ይገደዳሉ።

ለመሆኑ ልውጥ ሕያው ምንድን ነው? ለምንስ በባለድርሻ አካላት ዘንድ ልዩነት ፈጠረ? ስለደህንነት ሕይወት በወጣው አዋጅ እንዲህ ሰፍሯል፤ “ሰው ሰራሽ የሆነ ወይም ከሌላ ሕያው የተወሰደ ይሁን ከቅሪት የተወሰደ የተወለደ ወይም እንደ አዲስ የተቀመመ ባይተዋር ዘረመል ወይም ሌላ ንጥረ ነገር ስለተከተተበት የዘረመሎች ይዘቱ ወይም የባሕርዩ ክስተት የተለወጠበት ሕያው ነው” ይላል። ለዚህም ይመስላል፣ በፓናል ውይይቱ ላይ ተሳታፊ ከነበሩ ባለድርሻ አካላት የተነሳ፣ ከባዮቴክኖሎጂ የምርምር ውጤቶች አንዱ የሆነውን፣ ልውጥ ሕያውን ብቻ ገንጥለው ማብራሪያ እና መተማመኛ ይሰጠን ያሉት።

የመድረኩ ጥናት አቅራቢዎች፣ በቀጥታ በልውጥ ሕያው ላይ አትኩሮት በመስጠት ከመወያየት፣ በአዋጅ ቁጥር 655/2001 ዓ.ም. የወጣው የደህንነት ሕይወት ሕግ በማሻሻል አዲስ የደህንነት ሕይወት ሕግ በአዋጅ ቁጥር 896/2007 ዓ.ም. መውጣቱን በሕዝብ ተወካዮች ምከር ቤት ማጽደቁን በመከራከሪያነት ማቅረቡን በአማራጭነት ወስደዋል። ይህም ሲባል የአዋጁ መሻሻል አስፈላጊነት ከመድረኩ እንደቀረበው፤ የቀድሞ (አዋጅ ቁጥር 655/2001) ሕጉ ከሚፈለገው በላይ የጠበቀ በመሆኑ፤ ምርምር እና ፈጠራ የሚገድብ በመሆኑ፤ የሕጉ ምልክት ብዝሃ ሕይወትን በምርምር ላይ ተመስርቶ ለመጠበቅ የወጣ ሳይሆን ጥበቃን ብቻ እንደዋነኛ ዓላማው አድርጎ የተዘጋጀ በመሆኑ፤ የባዮቴክኖሎጂን መልካም ጎንን እና ጠቀሜታውን የማያመለክት በመሆኑ ተሻሽሏል የሚል አጠቃላይ ማሳያ አቅርበዋል።

ሕጉን ለማሻሻል ከመድረኩ የቀረበው መከራከሪያ አንድ ነገር ሆኖ፤ በፓናል ውይይት የመከራከሪያ ፍሬ ነገር የነበረው “ጥበቃን ብቻ እንደዋነኛ ዓላማው አድርጎ” የሚለው ሐረግ በተለይ ከ“ጠንቅ” ጋር ተያይዞ ከሚከሰት ጉዳት ጋር የተያያዘ በመሆኑ በድጋሚ በውይይቱ መድረክ በባለድርሻ አካላት በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ጥያቄ ቀርቧል። ይኸውም፣ “ጠንቅ” ማለት ከየትኛውም እንቅስቃሴ በቀጥታ ወይም በተዘዋዋሪ መንገድ፣ በአጭር፣ በመካከለኛ ወይም በረጅም ጊዜ በሰው ወይም በእንስሳ ጤና፣ በብዝሐ ሕይወት፣ በአካባቢ፣ በማሕበረሰቦች ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ወይም ባህላዊ ሁኔታ ወይም በአገሪቷ ኢኮኖሚ ላይ ሊከተል የሚችል አደጋ ነው።”  በሚል ይዘት በአዋጁ (655/2001) ላይ ሰፍሯል።

ነገሮችን የበለጠ ግልፅ ለማድረግ፣ የባለድርሻ አካለት ጥያቄ ከባዮቴክኖሎጂ አጠቃላይ ምርምር እና ውጤቶች አስፈላጊነት ጋር በቀጥታ የተያያዘ አይደለም። ያቀረቡት ጥያቄ አንድ እና አንድ ብቻ ነው። እሱም፤ ከልውጥ ሕያው ጋር በተያያዘ የሚደረጉ ምርምሮችና ሙከራዎች፣ በቀጥታ ወይም በተዘዋዋሪ መንገድ፣ በአጭር፣ በመካከለኛ ወይም በረጅም ጊዜ በሰው ወይም በእንስሳ ጤና፣ በብዝሐ ሕይወት፣ በአካባቢ፣ በማሕበረሰቦች ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ወይም ባህላዊ ሁኔታ ወይም በአገሪቷ ኢኮኖሚ ላይ ሊያስከትሉ የሚችሉ አሉታዊ እና አዎንታዊ ተፅዕኖዎች በግልፅ እንዲቀመጥላቸው በመፈለግ ያቀረቡት ጥያቄ መሆኑን ለመረዳት የሮኬት ሳይንስ ማጥናትን አይጠይቅም። በባለድርሻ አካላት በባዮቴክኖሎጂ ምርምር ዙሪያ የተነሳው ጥያቄ፤ ከአጠቃላይ ከፖሊሲ ማዕቀፍ አንፃር በመቶኛ ቢቀመጥ አንድ በመቶ አይሆንም።

ስለዚህም አጠቃላይ የባዮቴክኖሎጂው የፖሊሲ ማዕቀፉ ጽንሰ ሃሳብ፣ በልውጥ ሕያው ምርምር እና ለገበያ ለማቅረብ በሚደረግ አሰጥ አገባ መሸፈን አልነበረበትም። ምክንያቱም ባዮቴክኖሎጂ በእድገት እና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ውስጥ በበርካታ ዘርፎች ያለው ጠቀሜታ ከግምት ተወስዶ በተለያየ ዘርፍ ስትራቴጂክ ሰነዶች መዘጋጀቱን በዶክተር እንዳለ ገብሬ በቀረበ የጥናት ጽሁፍ ለባለድርሻ አካላት ቀርቧል፤ በቴክኖሎጂው ላይ ቅሬታ የቀረበበትም ሁኔታ አልነበረም። ዶክተሩ በገለፃቸው ባዮቴክኖሎጂ በግብርናው ዘርፍ አንዱ የልማት አቅጣጫ ተደርጎ መቀረጹን አስቀምጠዋል። የባዮቴክኖሎጂ ፍኖተ ካርታ መዘጋጀቱንም አሳውቀዋል። በተለይ የግብርና ምርምር ፍኖተ ካርታ ከባዮቴክኖሎጂ ጋር በተናበበ መልኩ መቀረጹን አስረድተዋል። የባዮቴክኖሎጂ ምርምር ከሁለት አስርት አመታት በላይ መሆኑን አስታውሰው፣ አሁን በአዲስ የልውጥ ሕያው ወይም በዘረመል(Genetically modified organism) የሚደረጉ ምርምሮች በተለያዩ ተቋማት ውስጥ እየተሞከሩ መሆናቸውን አስታውቀዋል።

ዶክተር እንዳለ ስለባዮሴፍቲ ሲያስረዳ፣ “የቀድሞ የባዮሴፍቲ ሕግ የሕጉ ምልክት ብዝሃ ሕይወትን በምርምር ላይ ተመስርቶ ለመጠበቅ የወጣ ሳይሆን ጥበቃን ብቻ እንደዋነኛ ዓላማው አድርጎ የተዘጋጀ በመሆኑ፤ የባዮቴክኖሎጂን መልካም ጎንን እና ጠቀሜታውን የማያመለክት በመሆኑ ከሁለት እስከ ሶስት አመት ድረስ ውይይት ተደርጎበት ተሻሽሏል” ብለዋል። የአሁኑ ባዮሴፍቲ ሕጋችን ግን አሉ “ሳይንሳዊ ምርምሮችን የሚጋብዝ በጣም ጥሩ የሆነ ነው” ሲሉ አወድሰውታል። “የቀድሞ ሕግ ላለፉት ስድስት ዓመታት ምርምር እዳይደረግ ገደቦ ይዞ ነበር” ሲሉ ዶክተሩ ወቀሳ ሰንዘር አድርገዋል። በዓለም ጥቅም ላይ የዋሉ የዘረመል ምህድስና ምርምር ውጤቶችን ወደ ሀገር ውስጥ በማስገባት ለመጠቀም ዝግጅት እያደረግ ነው። የማስፈጸሚያ ሰነዶች ተዘጋጅተው ጸድቀው ስላልመጡ ወደ ሥራ ለመግባት ዘግይተናል በማለት ቅሬታ አሰምተዋል።

ዶክተር እንዳለ አያይዘውም፣ “ከሃያ ዓመታት በፊት ዓለም ሲጠቀምባቸው የነበሩ ውጤታማነታቸው የተመሰከረ የባዮቴክኖሎጂ ውጤቶችን ዛሬ ላይ እና እየተከራከርንባቸው እንገኛለን። በርግጥ የምናደርገውን ነገር እናውቃለን?” የሚል ጥያቄ ለመድረኩ አቅርበዋል።

ዶክተር መለሰ ማሪዮ የኢትዮጵያ ብዝሃ ሕይወት ኢንስቲትዩት ኃላፊ በበኩላቸው፣ “ባዮቴክኖሊጂ በሁለት ከፍለን ማየት እንችላለን። እነሱም፣ ባሕላዊ ወይም ነባሩ (እርሾ ጠላ ቆጮ የሚብላላበት) እና አዲሱ የዘረመል ምህንድስ ናቸው። በዘረመል ምርምር ውጤቶች የሚከሰቱ ችግሮች አሉ ለሚለው ጥያቄ፤ አዎ አሉ ብለዋል። አያይዘውም መልካም ጎኖችም አሏቸው፤ ከሚጠቀሱት መካከል ለስኳር ሕመም ኢንሱሊን፤ ለካንሰር ሕክምናዎችም፤ ቫይታሚን ኤን ወደ ሩዝ መቀላቀል፤ የጄኔቲክ ብዝሃነት መፍጠር፣ የአባለዘር ፍሬዎችን በፍሪጅ ማቆየት፣ መዳቀል የማይችሉትን ማዳቀል፣ ዝርያዎችን ለረጅም ጊዜ ማቆየት፣ የጠፉ ዝርያዎችን ለማባዛት እና ለሌሎች ነገሮችም ይጠቅማሉ” ሲሉ አዎንታዊ ጐኖችን ለማሳየት ሞክረዋል።

አያይዘውም ዶክተሩ የጂኤምኦ አሉታዊ ጎኖቹን አስቀምጠዋል፤ “ከጂ ኤም ኦ የተመረተ በቆሎን ከተመገቡ አይጦች መካከል፣ አስራ ስምንቱ በሁለት ሳምንት ውስጥ ሞተዋል። መካንነት አጋጥሟቸዋል። የሞቱ በጎችም አሉ። በጂኤምኦ የተመረተ ድንች የተመገቡ አይጦች በሽታ የመከላከል አቅማቸው ቀንሷል። በጂኤምኦ የሚመረቱ ዝርያዎች በሀገር ውስጥ ሳይንቲስቶች ቁጥጥር ውስጥ ካለሆኑ ዘሮችን ደግሞ ለመዝራት አይቻልም። ለገበሬው በጣም አስቸጋሪ ነው የሚሆነው። በውጭ ምንዛሪ የሚገዙ ናቸው። በጂኤምኦ የተመረተ ጥጥ መርዛማ ነገር ስለሚያመነጭ፣ ቢራቢሮዎችና ንቦችን ያጠቃል። ያጠፋል። ለጸረ-አረም የተመረተ ዝርያ ወደሌላ ዝርያ ከተላለፈ ጸረ-አረም መቋቋም የሚቻል አረም ማጥፋት በጣም አስቸጋሪ ያደርገዋል። በጂኤምኦ የተመረቱ ምርቶችን የማይገዙ ሀገሮች አሉ። የፓተንት መብቶች ያሉባቸው ምርቶች ናቸው” ብለዋል። በመጨረሻም ዶክተሩ መለሰ፣ የጂ ኤም ኦ ምርቶችን ከመጠቀማችን በፊት ከፍተኛ ጥንቃቄ ያስፈልጋል ብለዋል።  

በዶክተር ወልደየሱስ የቀረበው የጥናት ጽሁፍ በበኩሉ እንደሚያሳየው፣ የጂኤም ምርቶችን ከአፍሪካ ለገበያ ያቀረቡ ቡርኪናፋሶ ሱዳን እና ደቡብ አፍሪካ ብቻ ናቸው። ፈቃድ ከሀገራቸው ተቆጣጣሪ ባለስልጣን ለገበያ እንዲቀርቡ የተሰጠቻው ኬኒያ፣ ማላዊ እና ናይጄሪያ ናቸው። በተወሰኑ ቦታዎች ጂ ኤም ኦ ላይ ምርመር እያደረጉ ያሉ ሀገሮች፤ አስራት ናቸው፡፤ እነሱም፣ ካሜሩን፣ ግብፅ፣ ኢትዮጵያ፣ ጋና፣ ኬኒያ፣ ናይጄሪያ፣ ማላዊ፣ ሞዛቢክ፣ ደቡብ አፍሪካ፣ ሱዳን፣ ሲዋዚላድ፣ ታንዛኒያ እና ኡጋንዳ ናቸው።

ዶክተር ወልደየሱስ በኢትጵዮያ ውስጥ ከዘረመል ምህንድስና ጋር የተያያዙ ወቅታዊ የምርምር ሥራዎችን ለባለድርሻ አካላት ይፋ አድርገዋል። በተለየ ፈቃድ ምርምር እየተደረገባቸው የሚገኙት፣ Bt-cotton (Bollgard I- Cry1Ac) ሲሆን፣ ማምረት እና ምርቱን መሞከር ያጠቃልላል። በስምንት ቦታዎች የሙከራ ሥራዎች እየተሰሩ እንደሚገኝ ገልፀዋል። ሁለተኛው፣ Enset (Hrap and pflp genes) ማምረት እና ምርቱን መሞከር ያጠቃልላል ብለዋል።

ዶክተሩ ሲያስረዱ፣ “እንሰትን የሚያጠቃ አርሶ አደሩን ስጋት ውስጥ የሚጨምር ባክትሪየም ቢትስ የሚባል አለ። ይህ ባክቴሪያ ከኢትዮጵያ ወደ ኡጋንዳ፣ ታንዛኒያ፣ ሩዋንዳ ኮንጉ፣ ብሩንዲ ተዛምቷል። በእነዚህ አካባቢዎች ደግሞ የሙዝ ተክልን በስፋት እያጠቃ ነው። ያሳደረውን ስጋት ለመቀነስ፣ በኡጋንዳ የዘረመል ምርምር እየተደረገበት ይገኛል። ተስፋ ሰጪ ውጤቶች ተገኝተዋል። ቴክኖሎጂውን ተመራማሪዎቻችን ቢጠቀሙት በአማራጭነት ጥሩ ነው” ብለዋል።

ለማጠቃለል የፖሊሲ አውደ ጥናት ተብሎ የተዘጋጀው መድረክ ዋና ዓላማው በዶክተር ጌታቸው በላይ በግልፅ የተቀመጠው ነጥብ ነው። ይኸውም፣ የውይይቱ ዋና ዓላማ BT-Cotton ን በኢትዮጵያ ውስጥ ለማልማት ከባለድርሻ አካላት ጋር በሳይንሳው መረጃዎች እና ተሞክሮዎች የጋራ ግንዛቤ በመፍጠር ስምምነት ላይ መድረስ ነው።

ስምምነት ላይ ከተደረሰ ወደ ተግባር ለመሄድ፣ ኢትዮጵያ የባዮቴክኖለጂ እና የባዮሴፍቲ ፖሊሲ ሊኖራት ይገባል። ይህም ሲባል፣  ከአመራረቱ እስከ ገበያ አቅርቦት በተመለከተ ፖሊሲ ማውጣት እና የማስፈፀሚያ ሰነዶችን ማዘጋጀት የግድ ይላል።

በሸማቾች ጥበቃ ማሕበር ሊቀመንበር በሻምበል ገብረመድህን ቢረጋ የቀረበው ግልፅ ጥያቄ በፖሊሲው ሊመለስ ይገባል። ይኸውም፤ የBT-Cotton ጥጥ ፍሬ ወደ ምግብ ሥርዓት ውስጥ እንደማይገባ ማረጋገጫ ማቅረብ። ለዚህ ጥያቄ ምላሽ የሚሰጠው ደግሞ፣ ለባዮቴክኖለጂ እና ለባዮሴፍቲ የሚወጣው ፖሊሲ ብቻ መሆኑ አሻሚ አይደለም።

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
295 ጊዜ ተነበዋል

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us