የሙሰኞች ጉዳይ፣ “በፖለቲካና በአስተዳደር” ለምን ይዳኛል?

Wednesday, 09 August 2017 13:16

By Samson Dessalgn

 

የፌዴራል የሥነ ምግባር እና የፀረ-ሙስና ኮሚሽን በአንድ ወቅት በቢሾፍቱ ከተማ ለመገናኛ ብዙሃን ስልጠና አዘጋጅተው ነበር። በዚህ ሥልጠና ላይ አንድ የኮሚሽኑ ከፍተኛ ኃላፊ በሻይ ዕረፍት መካከል “የማትዘግቡት እውነት ልንገራችሁ” ሲሉ ቁም ነገር አነሱ። በተቋሙ ውስጥ ለረጅም ጊዜ ሰርቻለሁ የደረስኩበት አንድ መደምደሚያ አለ። ይኸውም፣ በአብዛኛው ሙሰኛ በብሔሩ እና በፓርቲው ውስጥ የተደበቀ ነው። ባለቀለት መረጃ አንድ ሙሰኛ ለመያዝ ስንቀሳቀስ፤ በሌላ በኩል የሚገጥመን አይናችሁ እኛ ላይ ይበረታል። ሌላው አይሰርቅም? እያሉ ያጣጥሉናል። ግልፅ የሆነ የፖለቲካ ድጋፍ የለንም። በአጠቃላይ ሒደቱን ስንመለከተው፤ ወንጀለኛ ከየብሔሩ በመዋጮ እንዲያዝ የሚፈልግ የፖለቲካ ኃይል ነው፤ ያለው። ወንጀል ደግሞ በብሔር ውክልና የሚፈጸም ተግባር አይደለም። በግለሰብ ወይም በተደራጁ ቡድኖች የሚፈጸም ተግባር ነው። ስለዚህም የብሔር እና የፓርቲ ፖለቲካው በሕግ የበላይነት በቀጥታ ካልተዳኘ፤ ወንጀል በብሔር እና በፓርቲው ውስጥ ይደበቃል፤ አደጋውም የከፋ ነው የሚሆነው።” ነበር ያሉት።

የኮሚሽኑ ከፍተኛ ባለስልጣን በወቅቱ በጸረ-ሙስናው ትግል በከፍተኛ የተስፋ መቁረጥ መንፈስ ውስጥ ነበሩ። በጣም ያንገበግባቸው የነበረው፤ ሕብረተሰቡ ለኮሚሽኑ ያለው አመለካከት ነበር። የኮሚሽኑ ከፍተኛ ኃላፊ፣ ኮሚሽኑ ከፍተኛ ሥራዎች እንደሰራ በአሃዝ አንድ ሁለት ብለው ዘርዝረው ያስቀምጣሉ። ኮሚሽኑ በእጁ እውነትና ጠንካራ መረጃዎች ቢኖሩትም፣ የፖለቲካ ቁርጠኝነት ላይ የደረሰ አመራር ባለመኖሩ፤ ኮሚሽኑ በሕዝቡ ቅቡል ተቋም ሳይሆን ቀርቷል። ተቋሙም በሥነ-ምግባር አስተምህሮ ብቻ እንዲወሰን ሆኗል።

ከላይ የሰፈረውን መግቢያ ለመጠቀም የተገደድነው፣ ባሳለፍነው ሳምንት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በጠራው አስቸኳይ ስብሳባ ያለመከሰስ መብታቸው የተነሳባቸው አንድ የፓርላማ ተመራጭ ያቀረቡት ምክረ ሃሳብ በጣም ትኩረት የሚስብ ሆኖ ስላገኘነው ነው። ያለመከሰስ መብታቸው የተነሳባቸው የፓርላማ ተመራጭ “የተጠረጠርኩበት የሙስና ጉዳይ በፖለቲካና በአስተዳደር” ቢታይ የተሻለ መሆኑን ለፓርላማው ምክረ ሃሳብ አቅርበዋል። ሆኖም የተቀበላቸው ባለመኖሩ፣ ያለመከሰስ መብታቸው ተነስቶ በቁጥጥር ሥር ውለዋል።

ያለመከሰስ መብታቸውን ያጡት የፓርላማ አባል ፓርቲያቸውን ወክለው የመንግስት ስልጣን የያዙ ነበሩ። የመንግስት ስልጣን የሚያዘው፣ የሕዝብ ሃብትን ለማስተዳደር ነው። የሕዝቡን ሃብት ለማስተዳደር ሥርዓተ መንግስት የመሰረተው ገዢው ፓርቲ፣ ኢሕአዴግ መሆኑ ይታወቃል። ስለዚህም ኢሕአዴግ ወክለው የመንግስት ሥልጣን የሚይዙ የገዢው ፓርቲ ከፍተኛ ኃላፊዎች በሕዝብ ሃብት ላይ ጉዳት ሲያደርሱ የሚጠየቁት በኢትዮጵያ መንግስት ሕግ እንጂ፤ በገዢው ፓርቲ ውስጠ ደንብ አይደለም። ከዚህ መነሻ ያለመከሰስ መብታቸውን ያጡት የቀድሞ ተመራጭ ጉዳያቸው፣ “በፖለቲካና በአስተዳደር” ይታይልኝ በሚል ያነሱት ጥያቄ ምን ለማስተላለፍ ፈልገው ይሆን የሚል ጥያቄ ማጫሩ አይቀርም።  ከግለሰቡ ጋር ተመሳሳይ የሙስና ሪከርድ ያላቸው “ጓዶች”፤ በፖለቲካ እና በአስተዳደር ምህረት ያገኙበት አጋጣሚ ጠቋሚ ይመስላል።

ወይም ሊሒቁ ሩሶ እንደሚለው የፖለቲካ ሙስና ለሥልጣን በሚደረገው ፍትጊያ አይቀሬና አስፈላጊ ክትያ ነው። (political corruption is a necessary consequence of the struggle for power.) እንዲህም ሲል ይሞግታል፣ ሰው በማሕበራዊ እና በፖለቲካ ሕይወቱ ሊሞስን ይችላል። የሰው መሞሰን ግን የፖለቲካ ሲስተሙን አያጠፋውም። ነገር ግን በሙስና የተበላሸ የፖለቲካ ሲስተም፤ ሰውን ሞሳኝ እና ጠፊ ያደርገዋል። (Then he argued "that man had been corrupted by social and political life. It is not the corruption of man which destroyed the political system but the political system which corrupts and destroys man.)

ከዚህም መረዳት የሚቻለው ያለመከሰስ መብት የተነፈጋቸው የቀድሞው የፓርላማ ተመራጭ ከዚህ በፊት “የይርጋለም የፋይናንስ እና ኢኮኖሚ የቢሮ ኃላፊ” ሆነው፤ ሞስነው ሊሆን ይችላል። የሰውዬው መሞሰን የፖለቲካ ሲስተሙን ሊያጠፋው አይችልም። ሆኖም ግን በሙስና የተበላሸው የፖለቲካ ሲስተም፣ ሰውዬውን ሞሳኝ እና ጠፊ አደረጋቸው። ለዚህም ነበር፣ በሙስና በተበላሸው የፖለቲካ ሲስተም በኩል “በፖለቲካና በአስተዳደር” ፍትህ ይሰጠኝ ሲሉ የቀድሞው ተመራጭ ጥያቄ ያቀረቡት፤ ጥያቄያቸው ተቀባይነት አግኝቶ ቢሆን ኖሮ በርግጠኝነት ለእስር አይዳረጉም፤ ምክንያቱም የተበላሸው የፖለቲካ ሲስተም ነፃ ያወጣቸው ነበር።

ሌላው ያለመከሰስ መብታቸውን ያጡት የቀድሞ የፓርላማ ተመራጭ “በፖለቲካና በአስተዳደር ፍትህ ይሰጠኝ” የሚል ጥያቄ ማቅረባቸው የፖለቲካ ሙስናን ለማጋለጥ ይመስላል። በዚህ አውድ ማስቀመጥ የሚቻለው በሙስና ያደፈ የዘቀጠ የፖለቲከ ሲስተም ሄዶ ሄዶ፣ ተቀራማች የፖለቲካ ሲስተም (patronage political system) ይፈጥራል። ይህ ማለት፣ የሚሞሰነውን ንዋይ ወይም ቁስ በየደረጃው እየበለቱ መከፋፋል ሲሆን፣ ክፍፍሉ ግን ሙስናውን ለመፈጸም ባበረከቱት ድርሻ መጠን የሚወሰን ነው የሚሆነው። ሰውዬውም የፖለቲካና የአስተዳደር ፍትህን ሲጠይቁ፤ “ጉዳዩ ይታይልኝ፤ ብቻዬን የፈጸምኩት አይደለም” እያሉ ሊሆን ይችላል።

ይህ ተቀራማች ሲስተም አሁን ባለው ገዢ ፓርቲ ውስጥ መገለጫው በርካታ ነው። በተቀራማች ፖለቲካ ሲስተም ውስጥ አሰላለፋቸው፣ በብሔር፣ በድርጅት፣ በአካባቢ ልጅ፣ በቤተሰብ፣ በጓደኛ እና በሙያ የተቧደኑ ናቸው። ሌላው አደገኛ የሆነው ቡድን ደግሞ፣ ፓርቲውን የመሰረተው የግንባር አደረጃጀትን የዘለለ፣ በአራቱም ፓርቲ ውስጥ እንደግንባር አባላት ሆነው ከመተጋገል ይልቅ፤ ወደ ኔትዎርክ ዝርጋታ የተሸጋገሩ ተቀራማች ኃይሎች አሉ።

እነዚህ ኃይሎች የድርጅቱ የትኩረት አቅጣጫ ላይ ተፅዕኖ በማሳረፍ፤ በማይረባ አጀንዳ ድርጅቱ እንዲጠመድ እና ትኩረቱን ወደ እነሱ እንዳያደርግ የሚሰሩ ናቸው። ከአራቱም ፓርቲዎች የሚነሱ የፖለቲካ ውሳኔዎችን ቀድመው የመስማት እድላቸው ሰፊ በመሆኑ፣ አጀንዳው ለኢሕአዴግ ሥራ አስፈፃሚ ከመቅረቡ በፊት ኢ-መደበኛ ቡድን አደራጅተው ቀድመው ይማታሉ። ለዚህም ነው የፖለቲካ ሲስተሙን የተቀራማች ኃይሎች ስለተቆጣጠሩት፤ የፖለቲካ ሙስናውን በቀላሉ መቆጣጠር ያልቻለው። ያለመከሰስ መብታቸው የተነሳባቸው የቀድሞ ተመራጭ በድርጅቱ ውስጥ ለመዳኘት አንድ እድል ቢሰጣቸው፤ በብሔር ወይም በድርጅት ወይም በአካባቢ ልጅ ወይም በቤተሰብ ወይም በጓደኛቸው ወይም በአራቱ ፓርቲዎች ውስጥ ኔትዎርካቸውን በዘረጉት ኃይሎች ነፃ እንደሚወጡ አሻሚ አይደለም።

ሌላው፣ ያለመከሰስ መብታቸው የተነሳባቸው ተመራጭ ሕዝብ እንኳን እንዳይዳኛቸው፤ ሕዝቡ ስለሳቸው ሃብት የሚያውቀው የለም። ይህም ሲባል፣ የከፍተኛ ባለስልጣናት ሃብት መመዝገቢያ አዋጅ ከወጣ የቆየ ቢሆንም ሕዝቡ የሚያውቀው አንዳች ነገር የለም። በአዋጁ አንቀጽ 12 ቁጥር 1 እንደሰፈረው፤ በኮሚሽኑ የሚገኙ ማንኛውም የተመራጭ ወይም የመንግስት ሥራ ኃላፊዎች ሃብት ተመዝግቦ ለሕዝብ ክፍት እንደሚሆን ይደነግጋል። ሆኖም ግን የአንዱም ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣን ሃበት ለሕዝብ ይፋ አልሆነም። ሕዝብ በሚወሰዱ እርምጃዎች ላይ ተጠራጣሪ ከሚያደርጉት አንዱ፤ የተመዘገበው የከፍተኛ ኃላፊዎች ሃብት ባለመታወቁ ነው። ሕዝቡ ተጨማሪ ጥቆማዎች እንኳን እንዳይሰጥ፤ ስለተመዘገቡት ሃብቶች የሚያውቀው አንዳች መረጃ፤ የለም።

የተመዘገበው ሃብት ይፋ ቢደረግ፤ የትኛውም ከፍተኛ የመንግስት ተሿሚ “በፖለቲካና በአስተዳደር” እንዲዳኝ ጥያቄ አያቀርብም። ምክንያቱም ለሕዝብ ይፋ በሆነ የሃብት መጠን ላይ፤ ተጨማሪ ምንጫቸው የማይታወቁ ሃብቶችን መደመር ስለማይቻል ነው። ተደርጎ ቢገኝም፤ ገዢው ፓርቲ በሕዝብ ዘንድ የሚከፍለው ዋጋ መኖሩ አሻሚ አይደለም። መንግስት እና ገዢው ፓርቲ የተመዘገቡ የሃብት መጠኖች ይፋ እንዲሆን ካደረጉ፤ በሚወሰዱ የሙስና እርምጃዎች ቅቡልነት ያገኛል።

የመከሰስ መብታቸው የተነጠቁት የቀድሞ የፓርላማ ተመራጭ “በፖለቲካና አስተዳደር” ጉዳያቸው እንዲታይ መጠየቃቸው በአጠቃላይ የሚሰጠው ትርጉም፤ ብቻቸውን መጠርጠራውን እንዳልተቀበሉት እና በሕግ የበላይነት መዳኘት ያለባቸው ሰዎች እንዳሉ አመላካች ነው። ፍሬ ነገሩ ግን፤ የገዢው ፓርቲ የመንግስት ከፍተኛ አመራሮች ሆኑ፣ ተራው ዜጋ፤ በሕግ የበላይነት በመደበኛ ፍርድ ቤቶች መዳኘት እንዳለባቸው ለድርድር የሚቀርብ ነጥብ መሆን የለበትም። በቀጣይም ሁሉም ተጠርጣሪ በሕግ የበላይነት እንጂ በፓርቲ ውስጠ ደንብ መዳኘት እንደሌለበት የጋራ ግንዛቤ መውሰዱ ተገቢ ነው።¾       

ይምረጡ
(1 ሰው መርጠዋል)
416 ጊዜ ተነበዋል

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us