የሰዎችን ሕይወት የቀጠፈው የኬኒያ ምርጫ ውዝግብ ወደየት ያመራ ይሆን?

Wednesday, 16 August 2017 12:50

 

በሳምሶን ደሣለኝ

 

ከተባበሩት መንግስታት የሕግ ወሰን ተላልፈው የሊቢያ መንግሥት አፍርሰው፤ የሊቢያ ሕዝብን ለእርስ በእርስ ጦርነት የዳረጉ እንዲሁም የሊቢያ የነዳጅ ሐብት ለአውሮፓ ኩባንያዎች እና ለአሸባሪዎች እንዲቀራመቱት ያደረጉት 44ኛው የአሜሪካ የቀድሞ ፕሬዝደንት ባራክ ኦባማ፤ ኦገስት 7 ቀን 2017 በኬኒያ መገናኛ ብዙሃን ሰላማዊ ምርጫና የምርጫ ውጤቱን እንዲቀበሉ ለተፎካካሪ የኬኒያ ፖርቲዎች መልክታቸውን አስተላልፈው ነበር።

ያልተጠበቀና ያልተገመተ መልክት በመሆኑ ብዙዎቹን አስገርሟል። ምንአልባት ከኬኒያ ዘራቸው የተመዘዘ በመሆኑ ሳይሆን አይቀርም። ምክንያቱም ኦባማ ሰላም ፈላጊ የአሜሪካ መሪ ተደርጎ የሚወሰዱ አይደለም። በአፍጋኒስታን፣ በሊቢያ፣ በዩክሬን እና በሌሎችም የንፁሃን ዜጎችን የቀጠፉ መሪ በመሆናቸው ነው። በተለይ ሰው አልባ በራሪ ሮኬት አስወንጫፊ መሣሪዎችን በመጠቀም የአለም አቀፍ ሕግን አደጋ ላይ የጣሉት መሪም በመሆናቸው ነው። ከዚህ መነሻ ለኬኒያ ምርጫ ሠላም የሚያስመኛቸው መከራከሪያ የአባታቸው ሀገር ከመሆን በዘለለ የተለየ ምክንያት አይኖራቸውም።

 

 

ከምርጫው በፊት የተከሰቱ አስፈሪ ድርጊቶች

በጁላይ 29 ቀን 2017 የኬኒያ ምክትል ፕሬዝደንት ዊሊየም ሩቶ መኖሪያ ግቢ፣ በአንድ ታጣቂ በጥይት ሩምታ ተደብድቧል። በአጋጣሚ ም/ፕሬዝዳንቱ እና ቤተሰቦቻቸው አልነበሩም። ታጣቂው፣ የግቢ ጠባቂውን ካቆሰለው በኋላ አግቶ አቆይቶ፤ ገድሎታል። እገታው ለአስራ ስምንት ሰዓት የቆየ ነበር። የኬኒያ ልዩ የፖሊስ ቡድን በአካባቢው ደርሶ በተደረገ የተኩስ ልውውጥ የታጣቂው ሕይወት አልፏል። የታጣቂው ፍለጎት እስካሁን ምን እንደሆነ አልታወቀም። 

ሌላው ጁላይ 2017 ከናይሮቢ ወጣ ባለ ሥፍራ ሁለት አስከሬን ወድቀው መገኘታቸው ነበር። አንዱ አስከሬን፤ የኬኒያ ምርጫ ኮሚሽን የመረጃ ኮሚኒኬሽንና ቴክኖሎጂ ኃላፊ የነበሩት የክሪስቶፎር ማሳንዶ ነበር። ሰውየው የኬኒያ ምርጫ የአመራረጥ ሥርዓት ወደ ዲጂታል ያሸጋገሩ ከፍተኛ ባለሙያ ነበሩ። የኮሚሽኑ ኃላፊ ከፍተኛ ድብደባ ተፈጽሞባቸው መገደላቸውን መረጃዎች ይጠቁማሉ። እንዲሁም የሃያ አንድ አመት ወጣት  አስከሬን ከሰውየው አስከሬን ጎን ወድቆ ተገኝታለች። እስካሁን ለሞታቸው የተሰጠ ምክንያት ባይኖርም፤ ከፖለቲካ ሴራ የዘለለ ምክንያት እንደማይኖረው ተጠባቂ ነው፤ ከየትኛው ወገን እንደተፈጸመ ግን ምርመራ የሚሻ ጉዳይ ናቸው።  

 

 

ምርጫው

በኬኒያ በ1992፣ በ1997 እና በ2007 በከፍተኛ ረብሻና ቀውስ መከሰቱ የሚታወቅ ነው። በተለይ እ.ኤ.አ. በ2007 ከምርጫ በኋላ በተፈጠረ ረብሻ 1ሺ 300 ሰዎች ሲገደሉ፤ ከ600ሺ በላይ ሰዎች ለስደት ተዳርገዋል።

የኬኒያ ሕገመንግስት በየአምስት አመቱ ብሔራዊ ምርጫ እንዲደረግ ይደነግጋል። የኬኒያ ፕሬዝደንታዊ ምርጫ የሚመረጠው በተሻሻለው የምርጫ ሕግ መሰረት መሆኑ ማጣቀሻዎች ያሳያሉ። ይኸውም፤ በመጀመሪያው ዙር ሃምሳ በመቶ በላይ ያገኘ እና ካሉት 47 ካውንቲስ ቢያንስ በሃያ አራቱ ከሃያ አምስት በመቶ በላይ የመራጩን ድምጽ ማግኘት ይጠበቅበታል። ተወዳዳሪዎቹ ፓርቲዎች ለፕሬዝደንት የሚወዳደሩ ዕጩዎቻቸውን ከአፕሪል 20 እስከ ሜይ 2 ቀን 2017 ለምርጫ ኮሚሽን ማሳወቅ አለባቸው። የፓርላማ ተመራጮች በሁለት መንገድ ነው የሚመረጡት። ከ337 የፓርላማ መቀመጫ 290 የመራጩን አብላጫ ድምጽ ያገኘ በቀጥታ ይመረጣል። ቀሪዎቹ 47 መቀመጫዎች፣ ለሴቶች የተተወ ሲሆን፣ የመራጩን አብዛኛውን ድምጽ ያገኙ ሴቶች በቀጥታ ይመረጣሉ።  

ኦገስት 8 ቀን 2017 በኬኒያ አጠቃላይ ብሔራዊ ምርጫ ተደርጓል። በዚህ ምርጫ፣ ኬኒያዊያን ፕሬዝደነት እና የፓርላማ ተመራጮችን መርጠዋል። 19 ሚሊዮን 745 ሺ 716 ዜጎች በምርጫው ላይ ለመሳተፍ መመዝገባቸው ይታወቃል። ድምጽ ከሰጡ መራጮች የተገኘው ውጤት፤ ኡሁሩ ኬኒያታ እና ዊሊየም ሩቶ 8 ሚሊዮን 203 ሺ 290 (Jubilee Party of Kenya 54.27) ሲያገኙ፤ ራይል ኦዲንጋ እና ካሎንዞ ሙስካ 6 ሚሊዮን 762 ሺ 334 (National Super Alliance 44.74) አግኝተዋል።  በዚሁ መሰረት ኦገስት 11 ማምሻውን የምርጫ ኮሚሽን ኃላፊው ኡሁሩ ኬኒያታ እና ዊሊየም ሩቶ ፕሬዝደንት ሆነው መመረጣቸውን ይፋ አድርገዋል። በስልጣን ላይ የሚገኙት ፕሬዝደነት ኡሁሩ ኬኒያታ ሃምሳ አራት በመቶ የመራጩን ድምጽ በማግኘት ለሁለተኛ ጊዜ ኬኒያ የሚያስተዳድሩበትን እድል ማግኘታቸውን የኬኒያ ምርጫ ኮሚሽን ይፋ ማድረጉን ተከትሎ፣ ተቀናቃኛቸው የነበሩት ራይል ኦዲንጋ የምርጫውን ውጤት እንደማይቀበሉት ይፋ አድርገዋል። ለኬኒያ ሕግ መወሰኛው ምክርቤት ለመጀመሪያ ጊዜ ሶስት ሴቶች ተመርጠዋል። የኬኒያታ ፓርቲ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እና በሕግ መወሰኛ ምክር ቤት የአብላጫውን ወንበር መቆጣጠር መቻሉም እየተዘገበ ነው።

በኬኒያ የተደረገው ምርጫ ፍትሃዊና ታማኝ እና አሳታፊ ነበር ሲሉ ምስክርነት ከሰጡት ዓለም ዓቀፍ ታዛቢዎች መካከል፤ የኮመንዌልዝ ሰብሳቢ የቀድሞ የጋና ፕሬዝደነት ጆን ማሃማ፣ የምስራቅ አፍሪካ ኮሚኒቲ ተወካይ ኤድዋርድ ሩጉማዮ፣ እና የአፍሪካ ሕብረት ታዛቢ ቡድን በመወከል ታቦ ምቤኪ ይገኙበታል። ምቤኪ፣ በተቃዋሚዎች በኩል ተቃውሞ መኖሩን ቢረዱም የተሰጣቸው ሃላፊነት ለማደራደር ኃላፊነት ስላልተሰጠው የቀረበውን ውንጀላ ለመመርመር እንደማይችሉ አሳውቀዋል። የካርተር ማዕከል በቀድሞ በአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጆን ኬሪ የተመራው በበኩሉ ችግር ቢኖር እንኳን ወደ ፍርድ ቤት ሄደው እንዲከራከሩ መክረዋል።

የዓለም ምስክርነት ያደመጡት ኬኒያታ፤ በባዕለ ሹመታው ላይ እንዲገኙላቸው በርካታ የዓለም መሪዎች ለመጋበዝ ጊዜ አላባከኑም። ግብዣ ከቀረበላቸው መሪዎች መካከል፤ የቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዝደንት ባራክ ኦባማ፣ የጀርመን ቻንስለር አጌላ መርኬል፣ የእንግሊዝ ጠቅላይ ሚኒስትር ቴሬሳ ሜይ፣ የጣሊያኑ ጠቅላይ ሚኒስትር ማቴዖ ሬንዚ፣ የቻይናው ፕሬዝደነት ዢ ጂፒንግ፣ የላይቤሪያ ፕሬዝደንት ኤሌን ጆንሶን ሰርሊፍ፣ ናይጄሪያ ፕሬዝደነት ሙሃማዱ ቡሃሪ፣ ሩዋንዳው ፕሬዝደነት ፖል ካጋሜ፣ ኡጋንዳ ፕሬዝደነት ዌሪ ሙሴቬኒ፣ ታንዛኒያ ፕሬዝደነት ጆን ማጉፉሊ፣ የደቡብ አፍሪካ ጃኮብ ዙማ እና ናይጄሪያዊ ቢሊዮነር አሊኮ ዳንጎቴ ይገኙበታል።

 

የተቃዋሚዎች ተቃውሞና መዘዙ

የኬኒያ መንግስት ከዚህ ቀደም ምርጫውን ተከትሎ የተነሳውን ረብሻና የሰው ሕይወት እንዳይጠፋ የምርጫ ሥርዓቱን በኤሌክትሮኒክስ መንገድ ለመጠቀም ይፋ ማድረጉ ይታወቃል። የምርጫ ማጭበርበር ይቀንሳል፤ አንድ ሰው ከአንድ ጊዜ በላይ ድምጽ አይሰጥም ተብሎ ተስፋም ተደርጎ ነበር። የምርጫ ታዛቢዎችም በቀላሉ ምርጫውን የመከታተል እድል ይፈጥርላቸዋል ተብሎ ተጠብቆ ነበር። ውጤቱን ተከትሎ ስጋት ያመጣል ተብሎ እንደተሰጋው፤ የምርጫው ውጤት ከፍተኛ ተቃውሞ አስተናግዷል።

ተቀናቃኙ ኦዲንጋ ምርጫው በመረጃ ቋት ሰባሪዎች መሰበሩ በመግለጽ፤ ምርጫው መጭበርበሩን ለማሳወቅ ጊዜ አልፈጀባቸውም። በዚህም ሳያበቁ፣ ውጤቱ እንደማይቀበሉት ይፋ አድርገዋል። በኬኒያ የምርጫ ታሪክም ከፍተኛው የማጭበርበር ድርጊት የተፈጸመበት ሲሉ የነበረውን የምርጫ ሒደት ተችተዋል። የምርጫ ኮሚሽኑ ሰብሳቢ ዋፉላ ቼቡካቲ በበኩላቸው፣ ውንጀላውን መሰረተ ቢስ ክስ ነው ሲሉ ውድቅ አድርገዋል።

ኦዲንጋ በቲወተር ገፃቸው፣ “ገዢው ፓርቲ ደጋፊዎችን የመግደል መብት ተሰጥቶታል” ሲሉ በመሳለቅ፤ ውንጀላቸውን የኬኒያታ ፓርቲ ላይ አድርገዋል። አንዱ የተገደለው ሰው፣ በተቃዋሚዎች ጠንካራ ይዞታ በመሆነው ኪሱሙ ካውንቲ ውስጥ ነው። ይህ አካባቢ ከዚህ በፊት 1ሺ 200 ሰዎች የተገደሉበት ሥፍራ ነው።

ኦዲንጋ 4ሺ ደጋፊዎቻቸው በተሰበሰቡበት አክለው እንደተናገሩት፣ “ይህ የወደቀ አገዛዝነው፣ ለትክክለኛው ጉዳዩ ምላሽ ከመስጠት ሕዝቡን መግደል ወደ ነበረበት የመለሰው። ድምጽ ተሰርቋል። ይህ ስለመሆኑ ምንም ሚስጥር አይደለም።” ቀደም ብለን እንደገመትነው፣ ምርጫውን ይሰርቃሉ፤ አድርገውታል። እስካሁን ምንም አላደረግንም። እጃችን አንሰጥም። ቀጣዩን እርምጃ አሳውቃለሁ።

ኦዲንጋ፣ “በድጋሚ ፕሬዝደንታዊ ዕጩ መሆን አልፈልግም። ኬኒያዎች ስለተፈጠረው ጉዳይ ማወቅ አለባቸው፤ ዓለም ያልተረዳው ነገር ነው የተከሰተው።” ኦዲንጋ እና አጋሮቻቸው እንዳስቀመጡት፣ ለምርጫ ቆጠራ የተዘጋጀው የኮምፒውተር ፕሮግራም አልጐሪዝም አስር በመቶ ኡሁሩ ኬንያታ እንዲያሸንፉ ተደማሪ ተደርጐ የተሳናዳ ነው ሲሉ ኮሚሽኑን ወንጅለዋል።

በተጨማሪም በሰዎች እጅ ሕይወታቸው በጠፋው በቀድሞው የኮሚሽኑ የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂው ኃላፊ በሚስተር ክርስቶፎር ማሳንዳ የይለፍ ቃል በመስበር የመራጮች የዳታ ቋት ተዘርፏል ሲሉ ከሰዋል።

የኦዲንጋ ደጋፊዎች ጐዳና ላይ በውጣት ኡሁሩ ስልጣናቸውን እንዲለቁ ጠይቀዋል። በተፈጠረው እረብሻ 24 የኬንያ ዜጎች በጥይት በፖሊስ ተደብድበው ተገለዋል። ይህ በእንዲህ እንዳለ ኦዲንጋ ሕገ-መንግስቱ ከሚደነግገው ውጪ ስልጣን ለመውሰድ ሌሎች አማራጮችን እንደማይጠቀሙ ይፋ አድርገዋል።  

በሌላ በኩል፤ የአውሮፓ ሕብረት የውጭ ጉዳይ ኃላፊ ፌዴሪካ ሞግሄሪኒ እና የቀድሞ የተባበሩት መንግስት ፀሐፊ ኮፊ አናን ኦዲንጋ የምርጫውን ውጤት እንዲቀበሉ ጫና እያደረጉ ይገኛሉ።

 

 

በቀንዱ ሀገሮች ደህንነት ላይ ይፈጥራል የተባለው ሥጋት

የኬኒያ ምርጫ በቀንዱ ሀገሮች ሊያስከትል ይችላል የተባለው ሥጋት ካቀረቡት መካከል ተመራማሪው ያሲን አህመድ ኢስማኤል አንዱ ሲሆኑ፣ “Kenya's election: What is at stake for the region?” በሚለው ጽሁፋው በርካታ ፍሬ ነገሮች አስፍረዋል።

ኬኒያታ እና ኦዲንጋ በቀንዱ ሀገሮች እንከተለዋለን የሚሉት አካሄድ በጣም የተራራቀ ከመሆኑም በላይ ሊያስከትል የሚችለው ውጤትም እጅግ አደገኛ አድርገው የሚወስዱ አሉ። ከዚህም መነሻ የአካባቢው ሀገሮች የኬኒያን የምርጫ ውጤት በአይነ ቁራኛ ነበር ሲጠባበቁ የነበሩ። ምክንያታቸው “በሁለቱ መሪዎች መካከል ያለው የደህንነት እና የትብብር ፖሊሲ ልዩነት ስለሚያስፈራቸው ነው” ብለዋል ተመራማሪው።

 

 

የኬኒያን ጦር ከአፍሪካ ጥምር ኃይል ማስወጣት

የኬኒያ ጦር ሰራዊት በአፍሪካ አንድነት ተልዕኮ ተሰጥቶ በሶማሌ ሀገር ሰላም አስከባሪ ኃይል መሰማራቱ የሚታወቅ ነው። የኬኒያ ጦር ሰራዊት በዚህ በአፍሪካ አንድነት ጥምር ሰላም አስከባሪ ኃይል ተሳታፊ ነው። ይህ ጦር ሰራዊት ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ሶማሌ ሲላክ፣ ኦዲንጋ ጠቅላይ ሚኒስትር ነበሩ። በምዕራብ እና በደቡብ ምዕራብ ሶማሌ የተሰማራው የኬኒያ ጦር ሰራዊት ወደ 3ሺ 600 የሚጠጋ ነው። በዚህ አካባቢ ያለው የአል-ሸባብ አሸባሪ ቡድን ለመመንጠር እና ለማሸነፍ አይነተኛ ሚና እየተጫወተ ያለ ኃይል ነው። አሁን ላይ አል- ሸባብ ትርጉም ባለው መልኩ ስጋት የሚያመጣበት ሁኔታ ባይኖርም ቅሉ።

አሚሶም፣ ከሶማሌ ጦር ሰራዊቱን ማውጣት የሚጀምረው፣ በኦክቶበር 2018 ሲሆን ጠቅልሎ የሚወጣው በ2020 መሆኑ በአፍሪካ ሕብረት የተወሰነ ነው። ሆኖም ተጨባጭ የሶማሌ ሁኔታ ሊወስነው እንደሚችልም ተቀምጧል። ከዚህ በተጨማሪ አሁን ያለው ተልዕኮ አሚሶም እንዲያሳካ በተለይ በሶማሌ ደቡብ ማዕከላዊ አካባቢዎች ያለውን የአልሸባብ ኃይል ለማምከን፤ ከ28ሺ ጦር ሰራዊት በላይ ያስፈልገዋል እየተባለ ነው።

ተመራማሪው ያሲን አህመድ እንደሚሉት፣ “ኦዲንጋ የኬኒያን ጦር ሰራዊት ከአሚሶም አስወጣለሁ ማለታቸው አሳሳቢ የነበረው ከዚህ አንፃር ነበር። ይህንን አድርገው፣ አልሸባብ እራሱን ዳግም እንዲያደራጅ ከማድረጉም በላይ ለኬኒያ ሰላም ተመልሶ ስጋት እንደሚሆነው፣ እንዲሁም ለአጠቃላይ ለቀጠናው ሰላም አደገኛ ነበር።” መሆኑን አስፍረዋል። “የኬኒያታ መንግስት በበኩሉ የቀንዱ ሀገሮች ተጨማሪ ጦር ሠራዊት እንዲያዋጡ ከመጎትጎት በላይ ዓለም ዓቀፉ ማሕበረሰብ ተጨማሪ ጦር ሰራዊት እንዲያሰፍሩ ጠይቀዋል።” ሲሉ በአንፃሪዊነት አስቀምጠዋል።

ኦዲንጋ ቢያሸንፉ፣ በቀንዱ ሀገሮች ከፍተኛ የዲፕሎማሲ ቀውስ ይፈጥሩ ነበር። ምክንያቱም፣ ከሶማሌ በራስ ገዝ ደረጃ ለተገነጠለችው ሶማሌላንድ ሙሉ እውቅና እሰጣለሁ፤ ማለታቸው ነበር። በዚህ አቋማቸው ከሶማሌ መንግስት ከፍተኛ ውግዘት ደርሶባቸዋል። ከአፍሪካ ሕብረት ቻርተር አንፃርም ተቀባይነት የሌለው ተግባር ተደርጎ ተወስዶባቸዋል። በሌሎች የአፍሪካ ሀገሮችም ተመሳሳይ እርምጃዎች እንዲወሰዱ ከማነሳሳቱም በላይ፣ ሊያስከትል የሚችለው የደህንነት ስጋት ከፍተኛ መሆኑ በስፋት እንደሚታመን አስረድተዋል።

ኦገስት 13 ቀን 2017 አዲሱ የኬንያ ፓርላማ ሥራውን ይጀምራል ተብሎ ይጠበቃል። በኦገስት 22 ቀን 2017 ኡሁሩ ኬኒያታ ለሁለተኛ የሥልጣን ዘመናቸው ቃለ መሃላ ይፈጽማሉ።¾

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
235 ጊዜ ተነበዋል

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us