በግብርና ኢንቨስትመንት የተሰማሩ ባለሀብቶች ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ያቀረቡት ቅሬታዎች ምን መነሻ አላቸው?

Wednesday, 23 August 2017 12:50

 

-    ባክኗል የተባለው የሕዝብ ሐብት ይፋ እንዲሆን እና ተጠያቂ እንዲበጅለት ጥሪ አቅርበዋል

 

ባሳለፍነው ሳምንት የቤንሻንጉል ጉምዝ የግብርና ኢንቨስተሮች ማህበር አባላት፣ የደቡብ ኦሞ ጋምጎፋና ስገን ዞኖች የግብርና ኢንቨስትመንት ህብረት፣ የሶማሌ የእርሻ ኢንቨስተሮች ህብረት አባላት፣የጋምቤላ እርሻ ኢንቨስተሮች ሁ //ማህበር አባላት እንዲሁም በሌሎች አከባቢዎች በዘርፉ የተሰማሩ አልሚዎች ለጠቅላይ ሚኒስትር ኃ/ማሪያም ደሳለኝ አጋጥሞናል ያሉትን ተግዳሮቶች እና ምላሽ የሚሹ ጥያቄዎችን በጽሁፍ አቅርበዋል፡፡

ቅሬታቸውን ያቀረቡትን መንግስት በግብርናው ዘርፍ የሰነቀውን ራዕይ ተጋሪ በመሆን የተሻለ ሥራዎችን ለመስረት መሆኑን አስፍረው፣ “በሀገራችን እየተፈጠረ ያለውን የምግብ እጠረት ለመቀነስ ብሎም በዘላቂነት የምግብ ዋስትና ለማረጋገጥ ከመንግስት ጋር እጅ ለእጅ ተያይዘን ለተግባራዊነቱ” ተደማሪ ለመሆን የቀረበ አቤቱታ ነው ሲሉ ገልጸዋል፡፡

አያይዘውም፣ የግብርና ኢንቨስትመንት በሰው ሰራሽ እና በተፈጥሮ በሚከሰቱ ችግሮች ከፍተኛ ተግዳሮቶች የሚገጥመው የሥራዘርፍ በመሆኑ አውቀን፣ የሚጠበቅብን መስዋዕትነት ጭምር ለመክፈል ወስነን ነው፤ ወደግብርና ኢንቨስትመንት የተሰማራ ነው፡፡ በዚህ ደረጃ በአእምሮ እና በቁስ እራሳችን አዘጋጅተን የመንግስትን ራዕይ  ተጋርተን ወደ ሥራ ብንገባም በመንግስት ዘርፉን እንዲደግፉ የተቀመጡት አንዳንድ ኃላፊዎች የሰነቅነውን አብሮ የማደግ ራዕይን ለማኮላሸት ከጫፍ ስለደረሱ ክብርነትዎ አቤቱታችን በቀናነት እና ኃላፊነት ባለው መልኩ እንዲመለከቱልን እና ምላሽ እንዲሰጡን እንጠይቃለን ሲሉ ተማፅነዋል፡፡

 በዚህ ጹሁፍም የማሕበራቱ ተግዳሮቶች ምን ይመስላሉ? አስተዳደራዊ እና ፖለቲካዊ ችግሮች መነሻቸው ምንድን ነው? በአማራጭነት ያነሷቸው ሃሳቦች ይዘታቸው ምን ይመስላል? ምላሽ የሚጠይቁ ጥያቄዎቻቸው የትኞቹ ናቸው? የሚሉትን ከደብዳቤው መንፈስ በወፍ በረር ለመመልከት የተዘጋጀ ነው፡፡

 

ማሕበራቱ በግብርና ኢንቨስትመንት ለምን ተሰማሩ?

መንግስት በዘላቂነት ኢኮኖሚው ያረጋጋል፤  ይደግፋል፤ ያሳድጋል ግብርናውን ዋንኛው የትኩረትና የቅድምያ የልማት ሴክተር በማድረጉም በአቋሙ በመጽናትና በማሻሻል ዘርፉን ይደግፋል በሚል የመንግሰት የልማት አቅጣጫ በመደገፍና በማመን ወደዚህ ከፍተኛ መስዋእትነት የሚጠይቅ ስራ መግባታቸውን አሻሚ ባልሆነ መንገድ አቅርበዋል፡፡

አሁን ላይ ማሕበራቱ መንግስት በግብርና ኢንቨስትመንት የሚከተለው አቋምና አቅጣጫ ከዚህ በፊት በመንግስት ላይ የነበራቸውን እምነት እየመነመነ መምጣቱን አስፍረው፤ ተጠያቂ ያደረጉት አጠቃላይ የመንግስት አሰራር ሳይሆን፣ “በመንግስት ቢሮክራሲ ውስጥ ጭምብል ለብሰው ለኪራይ ሰብሳቢ ፖለቲካ ኢኮኖሚ ልዕልና ተግተው የሚሰሩ እና በጸረ ልማት መስመር የተኮለኮሉ አንዳንድ ኃይሎች እና አሰራሮችን ነው፡፡ ስለዚህም፣ “ተገቢውን የማስተካከያ እርምጃ በእርስዎ (በጠቅላይ ሚኒስትር ኃ/ማሪያም) በኩል እንዲወሰድልን” ይህንን አቤቱታ ለመጻፍ ተገደናል ብለዋል፡፡

አያይዘውም፤ “በግልፅ ማስፈር የምንፈልገው ፍሬነገር፣ እኛ በግብርና ኢንቨስትመንት የተሰማራን ባለሃብቶች እንደሌሎች የውጭ ዜጎች አማራጭ ሀገር ይዘን አይደለም፡፡ በአጭር ጊዜም ከኢንቨስትመንቱ ትርፍ እናገኛለን ብለን ሳይሆን ትርፍና ኪሳራችን አስልተን በረጅም ጊዜ ውጤታማ እንደምንሆን በመተማመን ነበር፡፡ ከላይ ያሰፈርነው እምነት ባይኖረን ኖሮ፣ በዚህ ከባድ የስራ ዘርፍ ተሰማርተን ሀገር እና ሕዝባችን እንጠቅማለን ብለን ፈጽሞ አንሞክረውም ነበር፤ ከቤተሰቦቻችን ርቀን ከፍተኛ የፀጥታ ሥጋት ባለባቸውና የሕይወት መስዋዕትነት በሚያስከፍሉ ሥፍራዎች አንሰማራም ነበር፤ በተቃራኒው እንደሰው ከውጭ የተመረቱ ምርቶችን በማከፋፈል ኮሚሽን ኤጀንት በመሆን ሀገራዊ ፋይዳ በሌላቸው፣ ግን በጣም አትራፊ በሆኑ ቀላል የሥራ ዘርፎች ላይ መሰማራት እንችል ነበር፡፡ የመረጥነው መስመር ምንም ያህል መስዋዕትነት የሚጠይቅ ቢሆንም የመንግስትን ረጅም የልማት ራዕይ የሚጋራ ነው፡፡ አሁንም የምንመርጠው ፋይዳው ብዙ የሆነው የልማት መስመር ነው፡፡ ዳሩግን ሥራችንን ለማከናወን፣ በእምቅ ፍላጎት የታሹ ውስብስብ ችግሮች ተጋርጠውብናል” ሲሉ ለመንግስት አቤት ብለዋል፡፡

 

 

ማሕበራቱ በዚህ ዘርፍ ያጋጠሟቸው ችግሮች ምንድን ናቸው?

ችግሮቹን ጠቅለል አድርገው ሲያስቀምጧቸው፤ “ወደስራ ከተገባ በኋላ የፖሊሲና የመመሪያ መለዋወጥና ፍትሀዊ ያልሆነ የመሬት ሊዝ ክፍያ፤ በመሰረተ ልማት እጥረት ምክንያት ለከፍተኛ ኪሣራ መዳረግ፤ የመልካም አስተዳደር መጓደል፤ የጸጥታ አለመኖርና የሦስተኛ ወገኖች የመሬት ወረራ፤ ለሚቀርቡ አቤቱታዎች ዘርፉ በሚፈልገው መልኩ አስቸኳይ መልስና መፍትሄ አለመስጠትና ድጋፍና ክትትል ደካማ መሆን ተቀራርቦ አለመስራት፤ የግብአት አቅርቦት አለመኖርና የገበያ ውጣ ውረድ እና ሌሎችም፤ ናቸው፡፡”

 

የፖሊሲና የመመሪያ መለዋወጥ እና ፍትሀዊ ያልሆነ የመሬት ሊዝ ክፍያ

አሁን አሁን የመንግስት ፖሊሲና የመመሪያ መለዋወጥ አዲስ የአሰራር ፋሽን እስከሚመስል ለሕዝብ እየተዋወቀ ነው የሚገኘው፡፡ በተለይ መንግስት የሚከሰስበት የህግ አግባብ የሌለ ይመስል የመንግስት ቢሮክራቶች ሞቅ ሲላቸው ወይም በአንድም በሌላ መልኩ ውስጣዊ የፖለቲካ መቆራቆዝ ሲገጥማቸው አንዱ ቡድን ብድግ ብሎ፤ ፖሊሲ መመሪያ ሲለውጥ ሆን ብሎም የተወሰኑ አካሎችን ለመጉዳት እንደሆነ ይስተዋላሉ፡፡ ለዚህ ጥሩ ማሳያ የሚሆነው የአዲስ አበባ ቤቶች ግንባታ ጽ/ቤት በ40/60 ቤቶች ግንባታ እና እጣ ድልድል ላይ ከገባው ውል ውጪ የፈጸመው ኃላፊነት የጎደለው ተግባር አንድ ነው፡፡ የመስተዳድሩ አስፈፃሚዎች ለፈጸሙት ስህተት እንኳን “ሕዝቡን ይቅርታ አልጠይቅም” ሲሉ ያለሃፍረት በአደባባይ ተናግረዋል፡፡

መንግስት ከህዝብ ወይም ከባለድርሻ አካላት ጋር የገባውን ውል በአንድ ጀንበር ተነስቶ ሲለውጥ ጠያቂ የለውም? ወይንስ መብቱን በሕግ የበላይነት ማስከበር የሚችል ወይም ፍላጎት የሌለው ኅብረተሰብ ተበራክቶ ይሆን? ወይንስ በመንግስት ውስጥ በተሸሸጉ ሕገወጥ አስፈፃሚዎች ሕዝቡ ተሰላችቶ ጊዜ እየገዛ ይሆን? ለእነዚህ ጥያቄዎች መልስ ለመስጠት ጥልቅ ጥናት ይፈልጋል፡፡

ወደዋናው ነጥብ ስንመለስ በግብርና ኢንቨስትመንት የተሰማሩ ማሕበራት ከፖሊሲና የመመሪያ መለዋወጥ ጋር በተያያዘ ያሰፈሩት ፍሬ ነገር፤ “የኢትዮጵያ ልማት ባንክ በተለይም በሰፋፊ እርሻዎች ለሚሰማሩ ባለሃብቶች ብድር በመስጠት የግብርና ኢንቨስትመንትን ለመደገፍ የሚሰራ የፖሊሲ ባንክ ሆኖ ሳለ፣ አሁን ላይ ኃላፊነቱን መወጣት በማይችልበት አግባብ ተቀምጦ ይገኛል፡፡በመንግስት ፖሊሲና የማበረታቻ ማዕቀፎች መነሻ፣ ወደዘርፉ የሚገቡ ባለሃብቶች ቁጥራቸው በየጊዜው እየጨመረ መምጣቱ ቢታወቅም፣ ዛሬ ላይ የልማት ባንክ ያወጣቸው የብድር ፖሊሲዎች፤ መመሪያዎችና የአፈቃቀድ ሒደቶች ግን ልማቱን ውርዴ እንደሚያደርጉት ለመገመት የተለየ እውቀት አይፈልግም፡፡ ካስቀመጡት ጸረ-ልማት አቅጣጫም በመነሳት የባንኩ አመራሮች በየጊዜው የሚያጋጥሙ ችግሮች ለመፍታትና ለማለፍ ፍላጎት፣ ቅንነትና ቁርጠኝነት የተላበሱ አለመሆናቸውን ማሳያ አድርጎ መውሰድ ይቻላል፡፡” ብለዋል፡፡

ከላይ ላሰፈሩት አጠቃላይ መገለጫ በመከራከሪያነት ያስቀመጡት፣ በማሕበራት ውስጥ የታቀፉ ባለሃብቶች ቀድሞ በነበረው የልማት ባንክ ውል መሠረት ብድር ወስደው ወደ ሥራ ከገቡ በኋላ፣ ባለሃብቶቹን ባንኩ ሳያማክር እና ምንም ዓይነት ቅድመ ማስጠንቀቂያም ሆነ መረጃ ሳይሰጥ፣ ባንኩ የፖሊሲ እና የመመሪያ ለውጥ በማድረግ የባለሃብቶቹን መብትና ልፋት ሳያስገባ ተግባራዊ ማድረጉ በአብይ ማሳያነት አቅርበዋል፡፡ በተመሳሳይ መልኩ በ40/60 ኮንዶሚኒየም ግንባታ ላይ ንግድ ባንክ የ40/60 የቁጠባ ፖሊሲ አሰራር በማን አለብኝት ጥሶ፤ መቶ በመቶ ለከፈሉኝ ብቻ ነው ኮንዶሚኒየም የማስተላልፈው የሚል አዲስ ፖሊስና መመሪያ አውጥቶ በአደባባይ ለሕዝብ ያቀረበውን ፖሊሲ ሽሯል፡፡ የጠየቃቸው አካል የለም፤ ምክንያቱም “የመንግስት አስፈፃሚዎች” ናቸው፡፡ እውነቱ ግን፤ በባንኩ ቢሮክራሲ ውስጥ እንዲቀመጡ የተደረጉት ኃላፊዎች እምቅ ፍላጎት ምን እንደሆነ ፈልጎ ማግኘት ላይ የተንጠለጠለ ነው፡፡ በሰለጠነው ዓለም የደንበኞቹን ውል የሚበላ ባንክ፤ አንድም ደንበኛ አይኖረውም፤ አንድም በፍርድ ቤት ቀርቦ ተገቢውን ቅጣት ይቀበል ነበር፡፡ በዚህች ሀገርም የሕግ የበላይነት “በመንግስት አስፈፃሚዎች” ላይ መተግበሩ የቅርብ ሩቅ መሆኑ የአደባባይ እውነት እየሆነ መምጣቱ እንደ በጎ እርምጃ የሚታይ ነው፡፡

ወደ ዋናው ጉዳያችን ስንመለስ፤ ልማት ባንክ በግብርና ኢንቨስትመንት በተሰማሩ ማሕበራት ላይ የፈጸመው የፖሊስና የአሰራር ውስልትና ባለሃብቶቹ እንዳስቀመጡት፣ “ወደ እርሻ ዘርፍ ለሚሰማሩ ባለሀብቶች የ25 በመቶ የገንዘብ መዋጮ ካፒታል ከ7 ነጥብ 5 ሚልዮን ብር በላይ እንዲሆን የሚል ገዳቢ ፖሊሲ በማውጣት ከዚህ በታች ካፒታል ያላቸው በተለይም ቀደም ብለው ስራ የጀመሩት በአማካይ በአመታዊ ሰብሎች ላይ ከ900 ሔክታር በታች የእርሻ መሬት ያላቸው ብድር አግኝተው ወደልማት እንዳይገቡ የሚገድብ ከሥራ ውጪ የሚያደርግ መመርያ በማውጣቱ፤ ይህም አነስተኛ የእርሻ መሬት ባላቸው ክልሎች ባለሀብቶች ከባንክ ብድር አግኝተው በዘመናዊ መልኩ እንዳያለሙ የሚያደርግ ኢፍትሀዊ መመርያ ነው፡፡” ብለውታል፡፡

ከላይ የሰፈረው የልማት ባንክ አዲስ ፖሊሲ አይሉት ቀጭን መመሪያ መሰረታዊ ስህተቱ ከደንበኞቹ ጋር የገባውን ብድር አሰጣጥ ውል በአንድ ጀምበር ብድግ ብሎ ማፍረሱ ሲሆን፤ የአንድ ባንክ ዋና እሴት ተብለው ከሚወሰዱት አንዱ ለደንበኞቹ ያለው ታማኝነት መሆኑን የባንኩ ኃላፊዎች ጠፍቶች ግን አይደለም፡፡ እንደዚህ ዓይነት ግብታዊ የፖለቲካ እርምጃዎች የሚወሰዱት፣ በኢትዮጵያ ውስጥ በፖሊሲ ባንክ ደረጃ ተወዳዳሪ የግል ባንኮች ባለመኖራቸው ነው፡፡ ባለሃብቱም የመንግስት ፖሊሲ ባንክ ጥገኛ በመሆኑ መሄጃ የለውም በሚል የሚፈልጉትን ለመቅጣት ግብ አድርገው አለማንቀሳቀሱ ነው፡፡

 በርግጥ ልማት ባንክ እና ንግድ ባንክ በሀገር ደረጃ የብድር ስርዓቱን ለመቀየር ወይም የተሰጡ ብድሮች ሳይበላሹ ለማስመለስ ፍላጎት ኖሯቸው አዲስ ፖሊሲ ለማውጣት ተገደው ቢሆን ኖሮ፤ የመጀመሪያ ሥራቸው የሚሆነው ከሁለቱ ባንኮች 3 ነጥብ 1 ቢሊዮን ብር ለአምስት የውጭ ሀገር ኩባንያዎች ያበደሩትን ገንዘብ ተመላሽ አድርገው ወደ ሥራ ይገቡ ነበር፡፡ ቁም ነገሩ ያለው ግን፣ በውስጣዊ የፓርቲ ፖለቲካ ሽኩቻ በታሸ እምቅ ፍላጎት ውስጥ የተጸነሰ የተወለደ ፖሊሲና መመሪያ በመሆኑ ዋነኛ ግቡ ልማት ሳይሆን፤ ጭቃ ውስጥ ገብተው ለመውጣት መራጨት ላይ ባሉ አስፈፃሚዎች ፍላጎት ላይ የተመሰረተ፤ ግብ መሆኑ ላይ ነው፡፡

ልማት ባንክ ምክንያቱ አጥጋቢ ባልሆነ መልኩ ያወጣውን ተጨማሪ መመሪያዎች ማሕበራቱ ሲያስቀምጡ፤ “ባለሃብቱ ለማልማት ባለው ጉጉት በራሱ አቅም ቀድሞ ያለማውን መሬትና የገዛው ንብረት ተገምቶ በኮላተራል /equity/ አይያዝም፡፡ ለመሬት ልማት የሚሰጠው የብድር መጠን እያንዳንዱ አልሚ ባቀረበው የአዋጭነት ጥናት ሳይሆን የማያሰራና በጥናት ያልተደገፈ በጅምላ በሄክታር 11,000 እስከ 25,000.00 ብር ብቻ እንዲሆን ተደርጓል፤ የአክስዮን ማህበር ድርጅቶች ለግብርና ልማት በማህበሩ ስም ለሚጠይቁት ብድር ያቀረቡት የፕሮጀክት ጥናት በመገምገም ሳይሆን ከኃላፊነታቸውና ከንግድ ሕጉ ውጪ የግል ንብረታቸውን (personal guarantee) እንዲፈርሙ የሚጠይቅ ገዳቢ ፖሊሲ ማውጣቱ፤ የእርሻ ባህሪ የማይመጥን የተንዛዛ የብድር አለቃቀቅ /ከ6 ጊዜ በላይ/ አሰራር መኖር፤ ባንኩ ለግብርና ልማት ለሰጠው ብድር በተበዳሪዎች ባልሆነ ምክንያት በሚቀርብለት አሳማኝ ምክንያትና ለልማቱ በሚኖረው ፋይዳ አፋጣኝ መፍትሄ በመስጠት ኢንቨስትመንቱ የሚቀጥልበት መንገድ ከማመቻቸት ይልቅ ከስረው ወደ ታማሚ ጎራ /NPL/ እና ሓራጅ እንዲገቡ ማመቻቸትና እንደአማራጭ የመውሰድ ችግሮች እንደዳረጋቸው” ለጠቅላይ ሚኒስትሩ በፃፉት ደብዳቤ ጠቅሰዋል፡፡

ማሕበራቱ በአስረጅነት ከጠቀሷቸው ሥጋቶች መካከል፣ በአሁኑ ሰዓት አሳማኝ ባልሆኑና አብዛኛውን በማይወክል “በመንግስት ታዘናል” በሚል ምክንያት ባንኩ ህጋዊ በሆነ መልኩ በውል የተፈደቀላቸው በጋምቤላ የሥራ ማስኬጃ ገንዘብ በሙሉና በከፊል የኢትዮጵያ ልማት ባንክ በመከልከሉ ከ100 በላይ ፕሮጀክቶች ታማሚ ጎራ እንዲገቡ፤ የተቀሩት 92 ፕሮጀክቶች አደጋ ውስጥ እንዲገቡ መደረጋቸው አስታውሰዋል፡፡ እንዲሁም፤ የብድር ማራዘሚያ ለሚጠይቁ ድርጅቶች አስቸኳይ ምላሽ ያለመስጠት፤ ለብድሮች በቂ የእፎይታ ጊዜ ያለመስጠት ሁኔታዎች መኖራቸውን ለጠቅላይ ሚኒስትሩ በፃፉት ደብዳቤ ላይ አስፍረውታል፡፡

ሌላው “የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ለእርሻው ዘርፍ ሲሰጥ የነበረው ብድር እንዲቆም ተደርጓል፡፡” በመህር ደረጃ የልማት ባንክ የፖሊሲ ባንክ ከመሆኑ አንፃር የመንግስት ፖሊሲን እየተከተለ ብድር ማቅረቡ ተገቢ ስለሚሆን እንደአሰራር ተገቢነት አለው፡፡ ሆኖም ግን የንግድ ባንክ በቢሊዮኖች የሚቆጠር ገንዘብ በግብርና ኢንቨስትመንት ለተሰማሩ የውጭ ሀገር ባለሃብቶች ማበደሩ የሚታወቅ ነው፡፡ የተሰጠው ብድር ከካራቱሪ ኩባንያ ጀምሮ የተዘረፈ መሆኑ የአደባባይ ወሬ ነው፤ እካሁን ግን በዚህ “የተበላሸ” ተብሎ በተቀመጠ የብድር ቋት ተጠያቂ የሆነ የንግድ ባንክ ኃላፊ የለም፡፡ ወይም ባንኩ እንዲያበድር አቅጣጫ የሰጠ የፖለቲካ ኃላፊ ካለም ተጠያቂ የሆነበት ሁኔታ የለም፡፡ በዚህ ሁኔታ ውስጥ የሚገኘው ንግድ ባንክ ከዚህ በፊት የሰጠውን የግብርና ኢንቨስትመንት ብድር “የተበላሸ” ብሎ ስያሜ ከመስጠት ውጪ፤ አለተጠያቂነት እንዴት ወደ ልማት ባንክ “የተበላሸው” ብድር ሊዘዋወር ይችላል፡፡ ንግድ ባንክ የሰጠውን ብድር መከታተል ተፈጻሚነቱን ማረጋገጥ እንደሚጠበቅበት እየታወቀ፤ በፖለቲካ ሽፋን አለተጠያቂነት ወደ ልማት ባንክ በድፍኑ ለማስተላለፍ መሞከር፣ የጊዜ ጉዳይ እንጂ ለውጭ ባለሃብቶች በተሰጠው ብድር ሰንሰለት ውስጥ የተሰለፉት ኪራይ ሰብሳቢ የአስፈፃሚ አካላት ተጠያቂ የመሆናቸው ጉዳይ አይቀሬ ነው፡፡

“በአጠቃላይ የአገሪቱ የፋይናንስ ተቋማት ግብርናው ባለው ከፍተኛ ፋይዳ ውጤታማ ለማድረግ የአገሪቱ መልክዐ ምድርና የአየር ሁኔታ፤ የመሬት አቀማመጥ፤ እርሻው የሚለማበት መንገድ (በመስኖ፣ በከርሰ ምድር በዝናብ ውይም በሁሉም) የሚያስፈልገው በቂ ካፒታል የሰው ኃይል፤ ለማገናዘብ በሚችሉበት ሁኔታ በእውቀት ስለማይመሩት ስማይደግፉት በሚቀረበላቸው የአዋጭነት ጥናት ተቀብለው በአግባቡ በመገምገምና የግብርና ባህሪ በማወቅ በወቅት በመለየት በፍጥነት የብደር አገልግሎት ስለማይሰጡ በዘርፉ አመርቂ ውጤት እየመጣ አይደለም፡፡” ሲሉ ማሕበራቱ ያላቸውን ልዩነት በደብዳቤቻው ላይ አስፍረዋል፡፡

 

የኢንቨስትመነትና የመሬት አስተዳደር ሥርዓት እና ሥልጣን መለዋወጥ

በግብርና ኢንቨስትመንት የሚሰማሩ ባለሀብቶች በሚያቀርቡት የአዋጭነት ጥናት እና የማልማት አቅም፤ በሚጠይቁት የመሬት መጠንና የአልሚው ዜግነት ወይም የተመሰረተበት ድርጅት ምክንያት ከዞን እና የክልል ኢንቨስትመንት ፈቃድ በማውጣት የእርሻ መሬቱም ህጋዊ ፎርማሊቲ ካሟላ በኃላ ባላው አሰራር መሰረት ከክልሎችና የኢትዮጵያ የግብርና ኢንቨስትመንት መሬት አስተዳደር ኤጀንሲበሚል ስያሜ በሚኒስትሮች ምክርቤት ደንብ ቁጥር 283/2005 የተቋቋመ የመንግስት መ/ቤት አማካኝነት ሲሰጥ ቆይቷል፡፡

“በፌደራል መንግሥትና በክልሎች የተሰጠው የኢንቨስትመንት መሬት የሚተዳደረው በየክልሉ ዞንና በወረዳ በመሆኑ ባለሀብቶችም ለሚፈጠርባቸው የመልካም አስተዳደር መጓደል፣ የጸጥታ መደፍረስ፣ የፋይናንስና የመሰረተ ልማት እጥረት፣ የመሬት መደራረብ እና ሌሎችም መፍትሄ የሚሹ ችግሮች ከወረዳ እስከ ፌደራል በተቀመጡት ባለድርሻ አካላት አለመናበብ የተፈጠሩ ናቸው፡፡”

“አሁን በግብርና ኢንቨስትመንት ለተፈጠረው እጅግ ከፍተኛ ችግር ዋንኛ ምክንያትም ነበሩ፡፡ አሁን ላይም ለከፍተኛ ውጣ ውረድና ጣልቃገብነት በመዳረጋችን ኢንቨስትመንት እንዲደግፍ የተቀመጠው አካል በፖሊሲው መሰረት ባለመደገፉ መንግስት በማመን ገንዘቡን፤ ጉልበቱ እና ሕይወቱን እየገበረ ያለው አልሚ፣ እየተጉላላ እና ብዙ የተባለለት የግብርና ኢንቨስትመንት በተፈለገው መልኩ ያልተጓዘና አልሚውም ለከፍተኛ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ችግሮች እንዲሁም አላስፈላጊና ፍትሃዊ ላልሆኑ ውሳኔዎች ተዳርጎ ይገኛል” ብለዋል፡፡

 

ፍትሀዊ ያልሆነ የሊዝ ክፍያ

መንግስት የእርሻ መሬት እንዲለማ የተለያዩ ማበረታቻዎች ያደርጋል፡፡ ከእዚህም ውስጥ የእርሻ መጠቀሚያ ዓመታዊ የመሬት የሊዝ ክፍያ የማበረታቻ አካል ዝቅ የተደረገ መሆኑ የሚታወቅ ቢሆንም፣ መመዘኛው በማይታወቅ መልኩ ደረጃ እየተሰጠው ፍትሃዊ ያልሆነ የሊዝ ክፍያ በፌደራልና በክልሎች በተሰጡ የእርሻ መሬቶች በመኖራቸው በዚህም ምክንያትም ፍትሃዊ የልማትና የንግድ ውድድር እንዳይኖር አድርጓል፡፡ ለምሳሌ በደቡብ አሞ ዞን ብቻ ለተለያዩ ባለሀብቶች ከ30 እስከ 600 ብር አመታዊ የሊዝ መጠቀምያ የአከፋፈል ሥርዓት መኖሩ ማሳያ አድርገው አቅርበዋል፡፡

ከመሰረተ ልማት መጓደል ጋር በተያያዘ ለከፍተኛ ኪሳራ መጋለጣቸውን ገልጸው፤ ለአብነት “በደቡብ አሞ ዞን የኦሞ የወደቀው ድልድይ መሬቱ ለባለሀብቱ ከተረከበ በኃላ ለስድስት አመታት ሳይሰራ በመቆየቱ፤ በሳላማጎ ልዩ ወረዳ፤ በደቡብ አሪ ወረዳ፤ በጋምጎፋ ዞን አልግሪን ኃ.የተ.የግ.. ለሰባት ዓመታት መንገድ ያልነበረው በመሆኑ በቤንሻንጉል ጉምዝ ክልል የተለያዩ ወረዳ እንዲሁም ሌሎች አከባቢ የመሰረተ ልማት ችግር ያለባቸው በግብርና ኢንቨስትመት የተሰማሩ አልሚዎች ለከፍተኛ ኪሳራ” መዳረጋቸውን ገልፀዋል፡፡

ከመልካም አስተዳደር መጓደል ጋር በተያያዘ ያስቀመጡት ማሳያ ተፈጽሞ ከሆነ አፋጣኝ እርምት የሚፈልግ ጉዳይ ነው፡፡ ይኸውም፣ “በሀገር ውስጥ እና በውጭ ሀገራት በሚገኙ ሓይሎች በጋራ ተጣምረው ከመንግስት ቢሮዎች በሚላክላቸው የተመረጡ የባለሃብቶች ስም ዝርዝር መነሻ የባለሃብቶች ዘር እየተቆጠረ ለማሸማቀቅ ከፍተኛ ሥራዎች ተሰርተዋል፤ እየተሰሩም ይገኛሉ፡፡ የመንግስት ከፍተኛ ኃላፊዎችም ይህንን መሰል ኃላፊነት የጎደለው ተግባር ሲፈጸም ከማስተባበል ይልቅ ተዘፈቀው ልማቱ ሲጎዳ እያዩ ማስተባበያ እንኳን ለመስጠት ፈቃደኛ አይደለሙ፤ አልፈው ተርፈውም የሸቀጥ አራጋፊው አጋር በመሆን አልቧልታዎች ሲነዙ ይገኛሉ፡፡” ሲሉ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ክስ አቅርበዋል፡፡

እንዲሁም፤ “ባንኮች የደምበኛቸውን የሒሳብ ቋት ሚስጥር የመጠበቅ ግዴታ በአዋጅ የተጣለባቸው ቢሆንም፣ ከተፈቀደለት አካል ወይም ከፍርድ ቤት ትዕዛዝ ውጪ ሆን ብለው አሳልፈው በመስጠትና በዝርክርክ አሰራሮች ሽፋን የደንበኛቸውን ሕጋዊ መብቶች ሲጥሱ ተገኝተዋል፤ ሕግም እንዲጣስ ተባባሪ ሆነዋል፤ የእርሻ መሬት ተረክቦ ከድርሻው በላይ በራሱ በማሟላት ብድር ቢጠይቅም፣ በፖሊሲ መቀያየር እና ኃላፊነት በጎደላቸው የባለድርሻ አካላት ጫና ብድር እንዲቆም በመደረጉ፣ ባለሃብቱ ወደልማቱ እንዲገባ ሲደረግ የተገባለት ቃል ተፈፃሚ እንዳይሆን በመከልከላቸው አብዛኛው አመታዊ ሰብሎችን ለማምረት የእርሻ መሬት የተረከቡ አልሚዎች፣ በተለይም በደቡብ አሞ ዞን በቤንሻንጉል እና በሶማሌ ክልል ውስጥ የሚገኙ ባለሃብቶች ለከፍተኛ ኪሳራ ተዳርገው ይገኛሉ፤ ኢንቨስትመንቱን እንዲደግፉ የተቀመጡት ባለድርሻዎች ከማስተዋወቅና መሬቱ ከማስረከብ ውጪ እንዲሁም በኢንቨስትመንት አዋጅ የተሰጣቸው ስልጣን መሠረት ባለሀብቱን ተክተው የመሰረተ ልማትና የፋይናንስ አቅርቦት፤ የመልካም አስተዳደርና የጸጥታ ችግር እንዲሁም ሌሎች ማበረታቻዎች በተመለከተ መስራት ሲገባቸው ወደስራ ከገባን በኋላ በተግባር ስለማይደግፉና ይልቁንም ውላቸውን ስለሚቀያይሩ ህጋዊነቱ ፈተና ላይ በመጣል ጉዳት እየደረሰ ይገኛል” ብለዋል፡፡

ከላይ ለሰፈረው አስረጂ አድርገው ያስቀመጡት፤ “በጋምቤላ ክልል ባለሀብቱ በውል ሰጪና ውል ተቀባይ መካከል የተቀመጠው አስገዳጅ ውል ወደጎን በመተው የመሬት የመጠቀምያ የሊዝ ጭማሪ መደረጉ፡፡ በደቡብ ኦሞ ዞን ከፌደራል መሬት የተረከቡ ባለሀብቶች ለአቤቱታቸው መፍትሄ ሳይሰጥበት እየተጠባበቁ እያለ ከውል ውጪ አለአግባብ ይዞታቸው በዞንና በወረዳ መቀነሱን” በደብዳቤያቸው አስፍረውታል፡፡

ከጸጥታ ጋር በተያያዘ የሶስተኛ ወገኖች የመሬት ወረራ በማሳያነት አቅርበዋል፡፡ ይኸውም፣ “በደቡብ አሞ ዞን በናጸማይ ወረዳ የሳግላ ኃላፊነቱ የተ.የግ. ማህበር ለስምንት ዓመታት በሁሉም የሚመለከታቸው የመንግስት ቢሮዎች የሚታወቅና ያልተፈታ የመሬት ወረራ፣ ዝርፍያ፣ አካል ጉዳትና የፍትህ እጦት፤ በኦልግሪን ኃ.የተ. ማህበር ንብረት መያዝና፤ በሉሲ እርሻ ልማት፣ በጸጋዬ ደሞዝ፣ ሲሳይ ተስፋዬ፣ አማኑኤል ገ/መድህን፣ በሀይረዲን እርሻ፤ ልማት የተፈጸመው የመሬት ወረራ አና የምርት ውድመት እንዲሁም የሰራተኞች ሞት፤ በጋምቤላ የተፈጠረው የሙርሌ ጥቃትና የጎሳ ግጭት እንዲሁም የብዙ ሠራተኛና ባለሀብት ሞትን” ጠቅሰው ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ጽፈዋል፡፡

ከግብአት አቅርቦት አለመኖር እና የገበያ ውጣ ውረዶችን በተመለከተ የሚከተሉትን አስፍረዋል፡፡ ይኸውም፣ “ከምርምር ተቋማት ምንም አይነት የተሻሻሉ ምርታማ፣ በሽታና ድርቅ የሚቋቋም የዘር እና የግብአት አቅርቦት በሀገር አቀፍ ደረጃ ስለሌላ በዘርፉ አመርቂ ውጤት ለማምጣት የማይታሰብ ጉዳይ እየሆነ ይገኛል፡፡ በተለይም የተሻሻሉ የጥጥና የቅባት አዝርእት እጦት፣ በቂ የኬሚካል እና የማዳበሪያ አቅርቦት ያለመኖር ዘርፉን እየጎዳው ይገኛል” ብለዋል፡፡

ከገበያ ጋር በተያያዘ አስተማማኝና ዘለቄታዊ አይደለም፡፡ ይህም ሲባል፣ “የገበያው ሁኔታ ዓለም አቀፋዊ ባልሆነ መልኩ ሲዋዠቅ፣ የግብርና ምርቶቻችን ዋጋ ሆን ተብሎ በገበያ ተዋናዮች ሲበላሽ (በወቅቱ ያለመግዛት፣ በክፍያ መዘግየት፣ የምርት ማከማቻ እጥረት እና በመሳሰሉት) ለከፍተኛ ኪሳራ እየተዳረግን” እንገኛለን ሲሉ ከሰዋል፡፡

ማሕበራቱ ከመንግስት ምን ይጠብቃሉ?

“በኢፌድሪ መንግስትና በክልሎች የግብርና ኢንቨስትመንት ለመደገፍ በተለያዩ ግዚያት የወጡት የድጋፍ ማእቀፎች (አዋጆች፣ መመርያዎችና ደንቦች) እና የፋይናናስ አቅርቦት፣ የመሰረተ ልማት አቅርቦት፣ የመልካም አስተዳደርና የጸጥታ መጓደል ባጠቃላይ በዘርፉ፤ በየክልሉና በያንዳንዱ አልሚ በፍትሃዊነት የሚሟላበት ሁኔታ እንዲፈጠርና ይህ ባልተሟላበት ሁኔታ በአፈጻጸም ችግር ምክንያት ባለሀብቱ ላይ ጉዳት እንዳይደርስበት ጥንቃቄ እንዲደረግልን፤

በመንግስታዊ የግብርና ኢንቨስትመንት ባለድርሻና ተዋናዮች ዘርፉና አልሚው በሚጎዳ መልኩ ነባራዊ ሁኔታ ያላገናዘበ ወደ ኢትዮጵያ ህዝብ የተሰራጨው ወሬ እንዲታረም በዚሁ መሠረትም መንግስት በጀመረው መልኩ፤ በዘርፉ ለሀገር ውስጥ እና ለውጭ ባለሃብቶች የተሰጠው የብድርና መጠን በውስጡም ለአመታዊ፣ ቋሚ እና አበባና አትክልት የተሰጠው የብድር መጠን ከየትኛው (የኢትዮጵያ ልማትና ንግድ ባንክ) እንደተሰጠና ያሉበት ሁኔታ ተገናዝቦ መንግስት እና ህዝብ እንዲያውቁት ቢደረግ፤ ለሀገር ውስጥ ትውልድ ኢትዮጵያውያን ጨምሮ እና ለውጭ ባለ ሀብቶች የተሰጠ የእርሻ መጠንና የለማ የመሬት መጠን የተሰጠ ብድር በማነጻጸር እንዲገለጽ፤ በማልማት አቅም እና ፍላጎት ሳይሆን በፋይናንስ አቅርቦትና መልካም አስተዳደር አድልዎ ማበላለጥ በመኖሩና በዚሁ ምክንያትም መተማማትና በመካከላችን አለመግባባት እየተፈጠረ በመሆኑ በዘርፉ የተሰማራን በፍትሀዊነት እኩል እንድንስተናገድ ቢደረግ፤

እኛ ለዘርፉ በተለይም በፋይናንስ አቅርቦት የተሰጠው ትኩረት አናሳ እንደሆነ ስለምናምን ከሌሎች ዘርፎች አንጻር በማነጻጸር መንግሥት ብድር ከማቆሙ እና ስራ ማስኬጃ እንዳይሰጥና ከመከልከሉ በፊት የባከነ የመንግሥት እና የህዝብ ገንዘብ ካለ በተለመደው መልኩ እንዲያሳውቅ፤ በተፈጠረው ችግር እና በፋይናንስ አቅርቦት ምክንያት መልማት የነበረበት የመሬት መጠን፣ የታጣው የምርት መጠን፣ ይፈጠር የነበረው የሥራ እድል እንዲሁም በአጠቃላይ በባለሀብቱ እና በመንግስት የደረሰው ጉዳት ተጣርቶ እንዲገለጽ፤

ልማት ባንክ የአሰራር፣ የፖሊሲና የክትትል ችግር፣ በድርቅ፤ በመሬት መደራረብ፤ በፀጥታ ችግር፣ በመሰረተ ልማት፣ በገበያ ችግር እንዲሁም በመሰል ፈተናዎች ምክንያት የልማት ሥራዎቻቸውን ተረጋግተው ማከናወን ያልቻሉ ባለሃብቶች፣ ብድሮቻቸውን ለመክፈል አቅም በማጣታቸው የተነሳ፣ የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ችግሮቻቸውን ከግምት ባለማስገባት ወደታማሚ /NPL/ ጎራ አስገብቷቸዋል፡፡ ይህ ሁኔታ አግባብነት የጎደለው በመሆኑ ለእነዚህ ፕሮጀክቶች አስቸኳይ የብድር ማራዘሚያ እርምጃ በመውሰድ ፕሮጀክቶቹንና ባንኩን የማዳን ሥራዎች እንዲሰሩ እንጠይቃለን፤

የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ባለው መመሪያና የብድር ውል መሰረት መመዘን፣ የፖሊሲ ባንክ በመሆናቸው ልማቱ ባለው ፋይዳ መሰረት ብድር ማስተዳደርና መምራት ሲገባቸው ከፋይናንስ አሰራር ውጪ ተፈቅዶ መለቀቅ የተጀመረውን የስራ ማስኬጃ ገንዘብ ከእርሻ ባህሪ ውጪ እንዲቆም በማድረግ ልማቱን በማሰቆም ለኪሳራ በመዳረጋቸው የደረሰው ጉዳት በሚያካክስ መልኩ እንዲታረምልን፤

ልማት ባንክ በሁሉም ቅርንጫፎቹ አማካኝነት አስቸኳይ የብድር አገልግሎት እንዲጀምር በማድረግ ከቀን ወደ ቀን እየተዳከሙ ያሉ ሌሎች ፕሮጀክቶችን በመታደግ ዘርፉን የማነቃቃት ስራ እንዲከናወን እንጠይቃለን፤

በመሰረተ ልማት ያለመሟላት፤ በብድር አቅርቦት ችግር፤ በጸጥታና መሬት ወረራ፤ በመልካም አስተዳደር አለመኖር ምክንያት ልማቱ የተጓተቱባቸው አካባቢዎችና ለከፍተኛ ኪሳራ የተዳረጉ አልሚዎች በመለየት የጋራና የተናጠል መፍትሄ እንዲሰጥባቸው (ውል ማሻሻል፤ የእፎይታ ግዜ መጨመር፤ የመሳሰሉት) በማድረግ መፍትሄ በመስጠት ሙሉ ለሙሉ ወደ ስራ የሚገቡበት መንገድ እንዲያመቻች፤

መሬት የሚሰጠውና የሚያስተዳድረው (በአስቸኳይ ወደ ልማት ግቡ የሚለው) አካል እና የፋይናንስ ተቋማት (ብድር ቆሟል ወይም ቆዩ እሰኪገመት እስኪፈቀድ) የሚለው አካል ተናበው የሚሰሩበት መንገድ እንዲፈጠር፤

ቀደም ሲል በልማት ባንክ ሲሰጥ የነበረው ብድር ከሁለት ዓመት በላይ በመቆሙ የሥራ ማስኬጃ እጥረት ለገጠማቸው ፕሮጀክቶች ሥራቸውን እንዲያከናውኑ በአስቸኳይ ተጨማሪ የሥራ ማስኬጃ ብድር እንዲፈቀድላቸውና ባለሃብቶቹን ከውድቀት የማዳን እርምጃ እንዲወሰድ፤

ኢንቨስትመንት በራሱ ዘርና እምነት የሌለው ከፖለቲካ ነፃ ሆኖ ሳለ በማወቅና ባለማወቅ ወይም በሌላ ተልዕኮ በተላላኪነት ለችግሩ መፈጠር ምክንያቶች የሆኑ ኢንቨስትመንቱን በፍትሃዊነት እንዲደግፉ ከላይ እስከ ይዞታው የተቀመጡት አንዳንድ የመንግስት አመራሮች እና ባለሞያዎች እንዲሁም ሌሎች ተዋናዮች ኢንቨስትመንቱ ላይ የከፋ ጉዳት ያደረሱና እኛንም ለከፍተኛ ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊና የቤተሰብ ቀውስ የፈጠሩ እና ይልቁንም መንግስት ከመነሻው አንድ አይነት የኢኮኖሚ ማህበረሰብ ለመገንባት እያደረገ ያለው ጥረት ወደጎን በመተው የዘርፉ ፋይዳዎች እንዲጎዱ እያደረጉ፣ የተዛባ ጥናት በማቅረብ መንግስትና ህዘቡን እያሳሳቱ የሚገኙት ግለሰቦችና ቡድኖች በጥፋታቸው ልክ ህጋዊና አስተዳደራዊ እርምት እንዲሰጥልን” እንጠይቃለን ሲሉ ለጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሣለኝ የድረሱልን ጥያቄ አቅርበዋል፡፡

የጠቅላይ ሚኒስትሩ ጽ/ቤት በዚህ ጽሁፍ ላይ የሚሰጠው ምላሽ ካለ ለማስተናገድ ዝግጁ መሆናችንን እንገልፃለን፡፡¾

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
387 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 946 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us