“የወወክማ ጠቅላላ ጉባዔ ሕጋዊ መሆኑን የሚገልጽ ሠነድ በእጃችን ይገኛል”

Wednesday, 06 September 2017 13:55

“የወወክማ ጠቅላላ ጉባዔ

ሕጋዊ መሆኑን የሚገልጽ ሠነድ በእጃችን ይገኛል”

ኤጀንሲው

 

የኢትዮጵያ ወንዶች ወጣቶች ክርስቲን ማሕበር (ወወክማ) በሚያዚያ 29 ቀን 2009 ዓ.ም ያደረገው ጠቅላላ ጉባኤ ሕገወጥ ነው በሚል ለበጎ አድርጎት ድርጅቶችና ማሕበራት ኤጀንሲ ለለውጥና መልካም አስተዳደር ዳሬክቶሬት የቀረበ የቅሬታ ሰነድ ለዚህ ጽሁፍ መነሻ ነው።

ባለፈው እትማችን የቀድሞውን የማሕበሩን የቦርድ ሰብሳቢ ዶክተር ጸጋዬ እና የአዲሱን የማሕበሩን የቦርድ ሊቀመንበር አቶ ይርጋ ገ/እግዚአብሔር እና ሌሎች የሚመለከታቸውን አነጋግረን አቅርበን ነበር።

 ዛሬ ደግሞ በዚህ ጉዳይ ላይ የበጎ አድርጎት ድርጅቶችና ማሕበራት ኤጀንሲ የክትትልና ድጋፍ ዳይሬክቶሬት ዳሬክተር አቶ ብዛየነ ገ/እግዚአብሔር እና የክትትልና ድጋፍ ዳይሬክቶሬት ቡድን መሪ አቶ ተስፋዬ ሽፈራውን አነጋግረን በጋራ የሰጡንን ምላሽ አቅርበናል። ለስራችን መቃናት ከፍተኛ እገዛ ያደረጉልን የኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ዳሬክቶሬት ዳሬክተር አቶ መስፍን ታደሰን እናመሰግናለን።

በዚህ ጽሁፍ የኤጀንሲው ኃላፊዎች የጠቅላላ ጉባኤውን ስብሰባ ሒደት እና የምርጫ ሥርዓቱን በተመለከተ ከሰነድ ጋር አቀናጅተው ምላሽ ሰጥተዋል። መልካም ንባብ።

 

***          ***          ***

 

ሰንደቅ፡-የጠቅላላ ጉባዔውን ስብሰባ እና ውጤት በመቃወም በ25/07/2009 ዓ.ም ለቀረበላችሁ ደብዳቤ ለምን ምላሽ አልሰጣችሁም?

አቶ ተስፋዬ፡- በሕጋዊ መንገድ ለተደረገ ጠቅላላ ጉባኤ ምላሽ የምንሰጠው፣ ሕጋዊ ለሆነ አካል ነው እንጂ ተፈራርሞ ለቀረበ ወረቀት አይደለም። ስለጠቅላላ ጉባኤው መጠየቅ የሚችለው የጠቅላላ ጉባኤ አባላት ናቸው። ከዚህ ውጪ የተወሰኑ ሰዎች ተፈራመው ምላሽ ይሰጠን ቢሉም፣ ዋናው ነገር ጥያቄውን ለማንሳት ሕጋዊ መሆናቸውን ማረጋገጥ ነው። ከዚህ አንፃር ከጠቅላላ ጉባኤው አባላት ቢያንስ አንድ ሶስተኛ ድምጽ ያላቸው አባላት የጠቅላላ ጉባኤው ሂደት አስመልክተው የጠየቁት ጥያቄ የለም። ተፈራመው የቀረቡት የጠቅላላ ጉባኤ አባላት አይደሉም። ስለዚህም ሕጋዊ ላልሆኑ አካላት ምላሽ መስጠት አይጠበቅብንም።

ሰንደቅ፡- ጠቅላላ ጉባኤው የተካሄደው ሕግን በተከተለና ሰላማዊ በሆነ መልኩ ተደርጎ መውሰድ ይቻላል?

አቶ ብዛየነ፡- የኤጀንሲው ስልጣን መታወቅ አለበት። እነዚህ የጠቅላላ ጉባኤ አባላት ከሰባት ቀናት በፊት ጠቅላላ ጉባኤ እንደሚያካሂዱ አስታውቀዋል። የጠቅላላ ጉባኤው ደንቦች የውስጥ አሰራር ደንባቸውን ተከትለው ነው ያደረጉት። ይህ በሚሆንበት ጊዜ፣ እኛ ጣልቃ አንገባም። እኛ የምናስፈልገው፣ ጠቅላላ ጉባኤው በሰላም ተካሂዷል፣ አልተካሄደም? ተስማምተው ነው የጨረሱት ወይንስ አይደለም? የሚሉትን ከፈተሽን በኋላ ነው። ችግር ካላ በጠቅላላ ጉባኤ አባላት ፊርማ ለኤጀንሲው ይደርሰዋል። ይህን ጊዜ፣ ምርጫ ቢደረግም፣ ባይደረግም ሕጋዊነቱን እናያለን። ሕገወጥ ከሆነ ይሰረዛል። ለሁለተኛ ጊዜ እንዲጠራ እናደርጋለን። ይህም ካልተሳካ፣ ለሶስተኛ ጊዜ ጠቅላላ ጉባኤ ይጠራል፤ በተገኙት ጠቅላላ ጉባኤ በኤጀንሲው ሊቀመንበርነት ስብሰባው ይካሄዳል።

በወወክማ ጠቅላላ ጉባኤ ችግሮች ስላልቀረቡ ጠቅላላ ጉባኤው ላይ ጣልቃ መግባት አስፈላጊም አልነበረም። አይገባምም። ምርጫው ካለቀ በኋላ ነበር የጠቅላላ ጉባኤ አባላት ያልሆኑ ሰዎች ተፈራርመው ወደ እኛ ቢሮ የመጡት። የጠቅላላ ጉባኤውን ዶክተር ጸጋዬ አስጀምሮ ነው በሰላም የተጠናቀቀው። ስብሰባ መጠናቀቂያው ላይ ከክፍለ ሀገር የሚመጡ ሰዎች ከፋይናንስና ከቦታው ርቀት አንፃር መመረጣቸው ተገቢ አይደለም የሚል ክርክር ያነሱት። ዶክተር ጸጋዬን ችግሮች ከነበሩ ምርጫው ሳይደረግ ቀደም ብለህ ለምን አላነሳህም፣ ብለን ጠይቀነዋል። ዶክተር ጸጋዬ ከአቶ ስብሃት ጋር አብረው ቢሯችን ቀርበው፣ ላቀረቡት አቤቱታ በሕገ ደንባችሁ ተነጋግራችሁ አሳውቁን ብለን መልስ ሰጥተናል። ከአንድ ወር በላይ ቢጠበቁም ለቅሬታቸው በሕገ ደንባቸው መሰረት ይዘውት የቀረቡት ነገር የለም። ይህም በመሆኑ፣ ማሕበሩ ያለበትን ኃላፊነት እንዲወጣ ለአዲሱ ሥራ አመራር ቦርድ እውቅና በመስጠት ወደሥራ እንዲገቡ ተደርጓል።

 

ሰንደቅ፡- ችግሩ ሳይፈታ፤ ማሕበሩን ለማገዝ ብላችሁ ነው እውቅና የሰጣችሁት?

አቶ ብዛየነ፡- ከላይ ያስቀመጥኩት መሰለኝ። የጠቅላላ ጉባኤው ሒደት ችግር አለበት ተብሎ ከጠቅላላ ጉባኤ አባላት የመጣ ቅሬታ የለም፤ ችግርም የቀረበ የለም።

ሰንደቅ፡- ዶክተር ፀጋዬ ይመሩት የነበረው ቦርድ ጊዜው ካበቃ ቆየት ብሏል። በወቅቱ ጊዚያቸውን ጨርሰው በቦርድ አመራርነት እንዲቀጥሉ እንዴት ፈቀዳችሁ? ጣልቃ በመግባት ጠቅላላ ጉባኤ እንዲጠራ ለምን አላደረጋችሁም? በወቅቱ በመካከላቸው አለመግባባት እንደነበረ አውቃለሁ።

አቶ ብዛየነ፡- እንደጋዜጠኛ ዳኛ መሆን ነው የሚጠበቅብህ። “ጠብ መኖሩ አውቃለሁ ካልክ” ድጋፍ እያደረክ ነው። ነገሩን ከደገፍክ ሌላ ነገር ነው።

ሰንደቅ፡- በመካከላቸው ችግር መኖሩን አውቃለሁ። ይህማ እውነት ነው።

አቶ ብዛየነ፡- ታዲያ በጊዜው እኛን ጠየከን?

ሰንደቅ፡- በራሳቸው ጊዜ ይፈቱታል በሚል ወደ እናንተ ዘንድ ጥያቄውን ይዘን አልቀረብንም።

አቶ ተስፋዬ፡- በመጀመሪያ ደረጃ እነዚህ ቅሬታ አቅራቢዎች እነማን ናቸው የሚለውን መመልከት ተገቢ ነው። በርግጥ ቅሬታ ማቅረብ የሚችሉ ናቸው? ለምሳሌ አቶ ስብሃት ታደሰ የሚባለው፣ የዑራኤል ተወካይ ነኝ የሚሉት፤ ከወወክማ ከታገዱ አምስት አመታቸው ነው። የታገደ ሰው በማሕበሩ ውስጥ ቅሬታ ማቅረብ አይችልም፤ አባልነት የለውም። ሁለተኛ ዶክተር ተካልኝ፣ የጠቅላላ ጉባኤ አባል አይደሉም። አቶ ስብሃት ከዑራኤል ተውክያለሁ በሚሉበት ቦታ፤ በእኛ እጅ በሚገኘው ሰነድ የተወከሉት አቶ ኤፍሬም ለማ ናቸው። በጠቅላላ ጉባኤው ስብሰባ አቶ ኤፍሬም ለማ ድምጽ ሰጥተዋል። አቶ ይልማ ኃ/ማሪያም ከአራት ኪሎ ተሳትፈዋል። አቶ ስብሃት አቶ ሽመልስ እና ዶክተር ተካልኝ የወወክማ እድር በሚል አራት ኪሎ አቋቁመዋል። ከዚህ መነሻ ወወክማ የሚመለከተው “እኛ” ነው የሚሉት፤ እውነቱም ይህ ነው። የወወክማ እድር ነው፤ የኢትዮጵያን ወወክማ ይዞ መንቀሳቀስ የሚል አቋም ይዘው ነው እያራመዱ ያሉት።

ለዚህም ነው፣ መረጃ ስጠኝ ብለው ቢሮ ሲመጡ፤ በመጀመሪያ ሕጋዊ ሰውነት ያለው አካል መሆን ይጠበቅባችኋል የሚል ምላሽ የሰጠነው። አቶ ስብሃት ከታገደ አምስት አመቱ ነው፣ ሌሎቹ ደግሞ የጠቅላላ ጉባኤ አባላት አይደሉም። ወወክማ አስር ቅርጫፎች አሉት። ሁለት ሁለት ተወካዮች ጠቅላላ ጉባኤውን ይመሰርታሉ፤ በብዛት ሃያ ናቸው። ዘጠኝ የሥራ አስፈፃሚዎች ቦርድ አባላት አሉ። እነዚህ ሰዎች ሲመረጡ አጀንዳ ቀርቦ ቃለ ጉባኤ ተይዞ ነው የተመረጡት። ይህንን የምርጫ ሒደት ዶክተር ፀጋዬ ገለልተኛ ሰዎች አሰይሞ ነው ምርጫው የተካሄደው። ለዚህም ነው የጠቅላላ ጉባኤ አባል ያልሆነ ሰው ምርጫው ሕጋዊ አይደለም ማለት የማይችለው፣ ምክንያቱም በምርጫው ቦታ አልነበረም፤ አላየም። የጠቅላላ ጉባኤውን ቃለ ጉባኤ ማየት ትችላለህ። ለሕዝብም ይፋ ማድረግ ትችላለህ። የቦርዱ ሊቀመንበር ተደርጎ የተመረጠው ግለሰብ ከፍተኛ ድምጽ ከቀረቡ ተወዳዳሪዎች፣ ከፍተኛ ቁጥር በማግኘት ነው። ጠቅላላ ጉባኤም እንደሚያደርጉ ከሰባት ቀን በፊት አሳውቀዋል።

 

 

ሰንደቅ፡- ኤጀንሲው በምርጫው ጊዜ ተሳታፊ ነበር?

አቶ ተስፋዬ፡- አልነበረም። እንደክፍተት ሊወሰድ ይችል ይሆናል፤ ከሦስት ሺ በላይ ማሕበራት ስለሚገኙ ለሁሉም ምርጫ ኤጀንሲው ሊገኝ አይችልም። ማሕበሩ ግን በሕጉ መሰረት ጥሪ አቅርቧል። ሰላማዊ ምርጫም አድርጓል። ይህንን የምልህ የማሕበሩ ሰነድ በምስክርነት ስለተቀመጠ ነው። በቅሬታ አቅራቢዎች በኩል የሚቀርበው “የቦርድ አመራሩ ከአዲስ አበባ መሆን አለበት” የሚል ሲሆን፣ ይህንን ቅሬታቸውን አሁን ካለው አደረጃጀት አንፃር ማየት ጠቃሚ ነው የሚሆነው። በመላው ሀገሪቷ የተቋቋመ ማሕበር፣ የአደረጃጀት ይዘቱም ሀገር አቀፍ ነው መሆን ያለበት። ሀገር አቀፍ ይዘት አይኑረው የሚለው ጥያቄ፤ ተቀባይነት የለውም። ከአዲስ አበባ ብቻ ሊመረጥ አይችልም። ክልሎች አባል የመሆን እንጂ አመራር አይሆኑም የሚለው አሰራር ከእኛ አዋጅ ጋር ይጋጫል። የማሕበራቸውም ደንብ ክልሎች አመራር አይሆኑም፣ የሚል የሰፈረበት ሰነድ የለም።

ሰንደቅ፡- ነባሩ ቦርድ ለአዲሱ ቦርድ ያስረከበው ሰነድ የለም። ምክንያቱ ደግሞ ሰላማዊ ሽግግር ባለማድረጋቸው ነው የሚሉ አሉ። ለዚህ የእናንተ ምላሽ ምንድን ነው?

አቶ ተስፋዬ፡- ማሕበሩ ጽ/ቤት አለው። ማሕበሩ ድርጅቱን የሚመራ ዳሬክተር አለው። ቋሚ ሆነ ተንቀሳቃሽ ንብረት ከቦርዱ ጋር የሚያገናኘው ነገር የለም። ጽ/ቤት አለው፣ የሒሳብ ባለሙያ አለው። በወላይታ በባሕር ዳር ማዕከሎች እየተገነቡ ነው። የቦርዱ ኃላፊነት በሶስት ወር አንዴ አፈፃጸሞችን መገምገም ነው፤ በውጤቱም አቅጣጫ ማስቀመጥ ነው። ገንዘብ ውስጥ እጁን አያስገባም። ቦርዱ ከጽ/ቤቱ አንድ እስኪርቢቶ ይዞ መውጣት አይችልም፤ ጽ/ቤት አለ። በየአመቱ የባንክ ሪፖርት የሰራተኛ ዝርዝር እንዲያቀርቡ እናደርጋለን። የእነሱ ቅሬታም፣ ከንብረት ጋር የተያያዘ ነው። ጥያቄያቸው ከንብረት ጋር ሳይሆን ከስልጣን ጋር የተያያዘ ነው፤ “እኛ” መመረጥ አለብን ከማለት የቀረበ ነው። 

አቶ ተስፋዬ፡- ዶክተር ፀጋዬ ስለ አዲስ አበባ ተመራጭነት ያነሳው ምርጫው ከተደረገ በኋላ ነው። እነዶክተር ፀጋዬ ተመራጮቹ ከአዲስ አበባ ነው የሚሆኑት የሚል እሳቤ ስለነበራቸው በምርጫው ጊዜ ያቀረቡት ጥያቄ አልነበረም። በተሰጠው ድምጽ የክልል ተመራጮች ድምጽ ማግኘታቸውን ሲመለከቱ ጥያቄ ማንሳት ውስጥ ገቡ። በመጀመሪያ እራሱ ዶክተር ጸጋዬ ማንሳት ይችል ነበር፤ ቢያነሳም በሕግ የተደገፈ የክልል ተመራጮች ወደአመራር አይመጡም የሚል መከራከሪያ ሊያቀርብ አይችልም። ሆኖም ቢያነሳው ጥያቄው በአሰራር ተገቢ ይሆን ነበር። ውጤቱም በመተማመን ላይ የተመሰረተ እንጂ የህግ መሰረት ግን የለውም። ዶክተር ጸጋዬ ለሥራ አመቺ እንዲሆን ከአዲስ አበባ ቢመረጡ ብሎ ቅስቀሳ አድርጓል፤ በውስጡ ለነበረው ቅሬታ አመቺ ሁኔታ አድርጎ ነው የተጠቀመበት።

ሰንደቅ፡- 1943 ዓ.ም. የወንዶች ወጣቶች ክርስቲያን ማሕበር እንዲቋቋም በወጣው አዋጅ፣ አመራሮቹ ከአዲስ አበባ እንዲሆኑ ይደነግጋል። ይህንን አዋጅ ተቋማችሁ እንዴት ነው የሚተረጉመው?  

አቶ ብዛየነ፡- በሀገሪቱ የነበሩ ከወንጀለኛ እና ከንግድ ሕጉ ውጪ ያሉ በሙሉ በአዲሱ በሕገ መንግስቱ ተሸረዋል። ከ1950ዎቹ የወጡ ሕጎች አይሰሩም። የነበሩ የማሕበራት ማቋቋሚያ አዎጆችን ሽሮታል። አዋጅ 621 ሲወጣ የመመዝገብ እና ፍቃድ የመስጠት የመቆጣጠርና የመደገፍ እርምጃ የመውሰድና የመሰረዝ ለዚህ ተቋም ሰጥቷታል። ወወክማም በአዲስ መልክ በአዋጅ 621 ተመዝግቦ ተቋቁሟል።

ሰንደቅ፡- የስብሰባው አጠራር ሕጉን ያልተከተለ ነው የሚል ቅሬታ በተደጋጋሚ የሚያነሱ አሉ። የጠቅላላ ጉባኤው አጠራር ሕግ መከተሉን አረጋግጣችኋል?

አቶ ብዛየነ፡- በማሕበሩ ውስጥ ችግር መበጣበጥ ካለ የጠቅላላ ጉባኤው ሰብሳቢ ስብሰባ ይጠራል። ካልተገኙ፣ ለሁለተኛ ጊዜ የስብሰባ ጥሪ ያደርጋል። በሶስተኛው፣ ለኤጀንሲው በደብዳቤ ያሳውቃል። ኤጀንሲው በተገኘበት ስብሰባ ይጠራል። ቦርድ ያዋቅርና ከጉዳዩ ይወጣል። በዚህ መልኩ የቀረበ ችግር የለም። በጠቅላላ ጉባኤያቸው በተነሱ አጀንዳዎች ላይ አብዛኛው ተስማምቶባቸው ያለፉ ናቸው። ሃምሳ ሲደመር አንድ የሚለውን የምርጫ ሕጋቸውን አሟልተዋል። አብላጫው ድምጽ ሰጥቷል። በውይይት ውሳኔ ያገኙ አጀነዳዎች አሉ። ሃምሳ ከመቶ በላይ በሆነ መልኩ ቅሬታ ይዞ የቀረበ የለም። ስለዚህም የአጠራሩም የምርጫው ሒደት ትክክል ነው ተብሎ የሚወሰደው። በአብላጫው ተሰብሳቢ የጸደቁ በመሆናቸው ነው።

ከምርጫ በኋላ ምርጫው አጀዳውም ትክክል አይደለም ብለው መጡ። ኤጀንሲው ባጠራው መንገድ ግን ሕጋዊ ምርጫ ነው የተደረገው።  ሕጋዊ ውክልና በጠቅላላ ጉባኤ ያላቸው አካላት ቅሬታ ባላቀረቡበት ሁኔታ፣ ማሕበሩ ጉዳይ ውስጥ ጣልቃ የመግባት ሕጋዊ መሰረት የለንም። እኛ ጋር ባለው የማሕበሩ ሰነድ፣ በሕጋዊ መንገድ የተመረጡ መሆናቸውን የሚያሳይ ነው።

አቶ ተስፋዬ፡- በጠቅላላ ጉባኤ የተሳተፉ የጠቅላላ ጉባኤ አባላት አንድ ሶስተኛ ድምጽ ያላቸው የምርጫው ሒደትም ሆነ የስብሰባው አጀንዳዎችና አጠራሮች ስህተት ነበረባቸው የሚል ቅሬታ ካቀረቡ፤ በሕጉ መሰረት ድጋሚ ጠቅላላ ጉባኤ ይጠራል። ቅሬታ አቅራቢዎቹ የጠቅላላ ጉባኤው አባላት አይደሉም።¾

        

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
199 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 1011 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us