“የመደራደር አቅማችን የሚለካው እኛ ባቀረብናቸው አጀንዳዎች በሚገኙ ውጤቶች ነው”

Wednesday, 13 September 2017 12:31

“የመደራደር አቅማችን የሚለካው

እኛ ባቀረብናቸው አጀንዳዎች በሚገኙ ውጤቶች ነው”

አቶ ትዕግስቱ አወል

አንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ ሊቀመንበር

ከገዢው ፓርቲ ኢሕአዴግ ጋር በመደራደር ላይ የሚገኙት ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ አስራ ሁለቱ እንደ አንድ ተቀናጅተው ለመደራደር መወሰናቸውን ይፋ አድርገዋል።

የተቀናጁት ፓርቲዎች በሦስት ተወካዮች ለድርድሩ ይቀርባሉ። እነሱም ዶክተር ጫኔ ከበደ (ከኢዴፓ)፣ አቶ ሙሉጌታ አበበ (ከመኢአድ) እና አቶ ትዕግስቱ አወል (ከአንድነት) ናቸው።

በዚህ የፖለቲካ ዓምድ ከአቶ ትዕግስቱ አወል አንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ ሊቀመንበር ጋር ቃለ ምልልስ አድርገናል። ለአቶ ትዕግስቱ ስለፈጠሩት ጊዜያዊ የድርድር ቅንጅት እና የድርድሩ አጀንዳዎች ውጤትና ቀጣይ ዕጣፋንታቸውን በተመለከተ አነጋግረናቸዋል። መልክም ንባብ።

 

ሰንደቅ፡- የአስራ ሁለቱ ፓርቲዎች ወደ አንድ ጥምረት እንዲመጡ ተነሳሽነቱን የወሰደው አካል ማነው? 

አቶ ትዕግስቱ፡-በተናጠል ያደረግነው ውይይት ብዙ አርኪ አልነበረም። በሁላችንም ውስጥ ወደአንድ ጥምረት ብንደርስ የሚል አመለካከት ነበረን። ሆኖም ግን የመኢብን ፓርቲ ተነሳሽነቱን ወስዶ ሁሉንም ፓርቲዎች አነጋገረ። በመጀመሪያ ያነጋገሩት አንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ ሲሆን ቀጥለው ኢዴፓ እንዲህ እየተባለ አስራ ሁለት ፓርቲዎች በማነጋገር በኋላም እኛ ተሳታፊ በመሆኑ አሁን ወደደረስንብት የድርድር ጥምርት መምጣት ተችሏል።

ሰንደቅ፡- ለአጭር ጊዜ የነደፋችሁት የድርድር የስምምነት ሰነድ ምን ይመስላል?

አቶ ትዕግስቱ፡-ዋና የተጣመርንበት ድርድሩ ለሕዝብ ጥቅም እንዲውል ነው። ሌላው የተደራጀንበት ዓብይ ምክንያት፣ የተደራጀ ሃሳብ ለማፍለቅና ለድርድር ዝግጁ በሚሆነ መልኩ አጀንዳ ለማቅረብ ነው። ይህም ሲባል የመደራደር አቅማችን ወጥና አንዱ በሌላው ላይ ተደራቢ እንዳይሆን ልዩነታችን አጥብበን፣ የጠበበውን የፖለቲካ የዴምክራሲ ምህዳሩን ለማስተካከል ነው። ይህንን ፍላጎታችን ለማስፈጸም እንዲረዳን ሶስት ተደራዳሪዎች መርጠናል። እነሱም፣ አቶ ሙሉጌታ አበበ እና ዶክተር ጫኔ እና እኔ ነኝ። ሶስታችንም እኩል ኃላፊነት ነው ያለን። ከሶስት አንዳችን የማንገኝ ከሆነ ተለዋጭ አባላት ተመርጠዋል።

አጀንዳዎች የምንቀርጸው በጋራ ውይይት በማድረግ፣ ግንዛቤ በመጨበጥ እና በደረስንበት የጋራ ስምምነት መሰረት በማድረግ ነው። በመርህና ሳይንሳዊ በሚሆን መንገድ የሚደረግ የውይይት መድረክ ነው የሚሆነው። ከውይይቱ በኋላ በጋራ ድምጽ የተሰጠበት አጀንዳ፣ የድርድር አጀንዳ በመሆን ለመደራደሪያነት ከኢሕአዴግ ጋር በሚደረገው ድርድር ላይ ይቀርባል። አጀንዳው የሚጸድቀው በተባበረ ከፍተኛ ድምጽ መሆኑን ከስምምነት ላይ ደርሰናል።

  ሰንደቅ፡- እስካሁን ባደረጋችሁት ድርድር ከገዢው ፓርቲ ጋር ትርጉም ያለው ልዩነት አልተንጸባረቀም። ይህ እንዴት ሊሆን ቻለ?

አቶ ትዕግስቱ፡-እስካሁን ባደረግነው እና በምናደርገው የምርጫ ምዝገባ፣ የምርጫ ሕግ እና የምርጫ ሥነምግባር ሕጎችን በተመለከተ ገዢው ፓርቲ እንዲሻሻሉ ፍላጎት አለው። ያቀረባቸው የድርድር አጀንዳዎችም ነበሩ። በተደረጉ ድርድሮችም፣ ገዢው ፓርቲ እና እኛም ባቀረብናቸው የድርድር አጀንዳዎች ላይ ከስምምነት ላይ ደርሰናል። የድርድር ውጥረቱም ብዙ አስጨናቂ ተብሎ የሚወሰድ አልነበረም።

በእኛ በኩል ከምርጫው ሕጉ 532 ውስጥ 28 አንቀፆች ለድርድር አስቀመጠናል። ከእነዚህ አንቀፆች ዘጠኝ አንቀፆች ሙሉ ለሙሉ እንዲሰረዙ የምንጠይቃቸው ነው። ስምንት አንቀዖች በአዲስ ሃሳቦች እንዲተኩ አቅርበናል። በአጠቃላይ 45 አንቀዖች ላይ ለመደራደር ነው ለአደራዳሪዎቹ ገቢ ያደረግነው።

ሰንደቅ፡- በቀጣይ ባሉ አጀንዳዎች ከፍተኛ ልዩነቶች ሊጋብዙ የሚችሉ ይኖሩ ይሆን?

አቶ ትዕግስቱ፡-በጣም ይኖራል። ለምሳሌ ገዢው ፓርቲ የምርጫ ሥርዓቱን ለመቀየር እንደሚፈልግ በሀገሪቷ ፕሬዝደንት በኩል አቅርቧል። ይኸውም፣ ከአብላጫ የምርጫ ሥርዓት ወደ ተመጣጣኝ ውክልና ለመቀየር ያለውን ፍላጎት ገልጿል።

ሰንደቅ፡- (ላቋርጥዎትና) ተመጣጣኝ ውክልና እንዴት ለልዩነት በር ሊከፍት ይችላል?

አቶ ትዕግስቱ፡-ተመጣጣኝ ውክልና የሚከተል የምርጫ ሥርዓት እንደግፋለን፤ ሆኖም ግን በጥናት ላይ የተመሰረተ ለውጥ እንዲመጣ መደራደራችን አይቀሬ ነው። ከዓለም ዓቀፍ ተሞክሮ የሚጨመቅ እንጂ፣ ተመጣጣኝ ውክልና በገዢ ፓርቲ አስተሳስብ ላይ የተንጠለጠለ እንዳይሆን የምንችለውን ሁሉ እናደርጋለን። ከሌላው አጀንዳ ጋር ተጨፍልቆ የሚታይ ሳይሆን፣ ጥንቃቄ የሚፈልግ ነው።

ከላይ ከፍተኛ ልዩነት የሚፈጥሩ አጀንዳዎች አላችሁ ላልከው፤ ድርድሩ ከፍተኛ ደረጃ የሚደርሰው ከምርጫ ሕግ ጋር የተያያዙትን ከጨረስን በኋላ ነው። ምክንያቱም ከሶስቱ የምርጫ ሕጎች በኋላ ያለው ዘጠኝ አጀንዳዎች በተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲዎች ፍላጎት ብቻ የቀረቡ ናቸው። ኢሕአዴግ ለመደራደር ፍላጎት ከማሳየት ውጪ፣ ባቀረብናቸው ነጥቦች ዙሪያ ለውጥ እንዲደረግባቸው ያቀረበውም የማሻሻያ ነጥቦች የሉም። በእኛ በኩል ከቀረበ ግን ለመደራደር ፈቃደኛ መሆኑን አስቀምጧል።

ሰንደቅ፡- ለምሳሌ የትኞቹ አጀንዳዎች ናቸው?

አቶ ትዕግስቱ፡- የፀረ-ሽብር አዋጁን መሻሻል በተመለከተ እኛ የተቃዋሚ ፓርቲዎች ብቻ ነው ያቀረብነው። በዚህና መሰል አጀንዳዎች ዙሪያ ነው የድርድር አቅማችን የሚለካው። በጋራ ሆነን ላቀረብነው አጀንዳ የሃሳብ የበላይነት በመያዝ አዋጆቹ እንዲሻሻሉ፣ አንዳንዶቹ ደግሞ እንዲሰረዙ ማድረግ መቻል፣ አለመቻላችን የሚለካው በቀጣይ ባሉ አጀንዳዎች ነው። አቅማችን የሚለካው እራሳችን ባቀረብነው አጀንዳ ላይ በሚደረግ ድርድር ነው። ምክንያቱም በምርጫ ሕግ ዙሪያ ከገዢው ፓርቲ ጋራ የጋራ ግንዛቤ አለን። ከዚያ ውጪ ባሉት አጀንዳዎች ላይ ግን ልዩነታችን ሰፊ ነው። ይህ ማለት የአንድ ወገን ጥያቄ ነው፤ ለዚህም ነው ቀጣይ ድርድሮች በጣም ፈታኝ የሚሆኑት።   

ሰንደቅ፡- በፀረ-ሽብር ሕጉ ላይ ያላችሁ ልዩነቶች ምንድን ናቸው?

አቶ ትዕግስቱ፡-ተመጣጣኝ ያልሆነ ኃይል ያስቀምጣል። ለምሳሌ ለጸጥታ ኃይሉ ከፍተኛ ስልጣን ይሰጣል። ምንም ላልታጠቀው ሲቨል ማሕበረሰብ ግን የሚተወው መብት የለም። በተግባር ካየነው ለማስቀመጥ፣ በሃሳብ ነፃነታቸው ብቻ ፖለቲከኞች ጋዜጠኞች በዚህ አዋጅ መነሻ ታስረዋል። በሌላው ዓለም ፀረ-ሽብር በተቋም ደረጃ የሚመራ ሲሆን ኢትዮጵያ ውስጥ ግን በሃሳብ ነፃነት ብቻ የሚታሰሩበት አሠራር ነው ያለው።

የፀረ-ሽብር ሕግ የፖለቲካ ምህዳሩ እንዲጠብ ከፍተኛ ሚና አለው። አንድ ነገር ሲፈጠር የሚጠቀሰው የፀረ-ሽብር ሕግ ነው። ፖለቲከኛው ጋዜጠኛው የሚታሰረው በዚህ ሕግ መነሻ ነው። ጋዜጠኞች እነሱን በሚመለከት በወጣው የመረጃ ሕግ መነሻ ሲጠየቁም ሆነ፤ ሲታሰሩ አይታይም። ፖለቲከኛውም በፖለቲካ ፓርቲዎች ሕግ ሳይሆን፣ በፀረ-ሽብር ሕግ ተጠቅሶ ሲጠየቁ ሲታሰሩ ነው፣ በተግባር ያየነው። ከታሰሩት መካከል እስታስቲክ ብትወሰድ፣ ከፖለቲካ ምሕዳሩ መጥበብ ጋር በተያያዘ የታሰሩት በቁጥር ይበዛሉ።

ሰንደቅ፡- ሌሎች ፈታኝ ሁኔታ የሚፈጥሩ አጀንዳዎች ካሉ ቢጠቅሱልን?

አቶ ትዕግስቱ፡-ዝርዝር ነገር ማቅረብ አልችልም። ለምሳሌ በግብር አዋጅ፣ የበጎ አድራጎት ድርጅቶችና ማህበራት አዋጅ የመሳሰሉት ከፍተኛ ድርድር የሚፈልጉ እንደሚሆን ይጠበቃል።

ሰንደቅ፡- በግብር አዋጁ ላይ የምታቀርቡት የመደራደሪያ ሃሳቦች ይኖራሉ?

አቶ ትዕግስቱ፡-አዎ። የምሰጥህ ዝርዝር መረጃ ግን የለኝም። በአጠቃላይ ግን የፖለቲካ ምህዳሩን ባጠበቡት አዋጆች ዙሪያ ድርድር ይደረጋል።

ሰንደቅ፡- ሀገር ውስጥ አሁን ካለው ተጨባጭ የፖለቲካ ከባባዊ ሁኔታ በድርድሩ ሒደት የምታነሷቸው ነጥቦች አሉ?

አቶ ትዕግስቱ፡-አሁን ካለው ተጨባጭ ሁኔታ ቀደም ብለን በፌደራል ሥርዓቱ እና በሕገ-መንግስቱ ዙሪያ ድርድር እንዲደረግ ጥያቄ ያቀረብን ቢሆንም፣ ገዢው ፓርቲ አልተቀበለውም። አሁን የተፈጠረው አለመረጋጋት፣ ከፌደራሊዝም ሥርዓት አፈፃፀም ጋር የተያያዘ ሰለመሆኑ በርካታ ምክንያቶች ማንሳት ይቻላል። የድንበሮች ግጭት ሥሩ፣ አንቀጽ 39 መሆኑ አሻሚ አይደለም። 

ሰንደቅ፡- እንዴት?

አቶ ትዕግስቱ፡-አንቀጽ 39፣ ለክልሎች እስከመገንጠል ነው የሚያዘው። አሁን ላይ እያየነው ያለውም፤ የለማ መሬት፤ በተፈጥሮ የበለጸ ንጥረ ነገር ያለበትን ቦታ ለመያዝ ሽሚያ  ነው። የኢትዮጵያ መልከዓምድር በአንድነትና በመተባበር የሚለማ ለመጠቀምም ቢሆን በጋራ ተጠቃሚነት መሰረት ያደረገ መሆን አለበት። እንደሚታወቀው በክልሎች መካከል የድንበር መካለል አልተደረገም። ስለዚህም አንዱ እየተነሳ የወገኑን መሬት እየተቀራመተ፤ “የእኛ” ክልል ነው የሚባልበት ሁኔታ፣ ለመገንጠል ጥያቄ ከማንሳት በፊት መስፋፋትን ያስቀደመ እርምጃ እየተተገበረ ያለ ነው የሚመስለው። ዛሬም ላይ ለደረሰው የፖለቲካ አለመረጋጋት፣ ከጽንሰ ሃሳብ እስከ ፌደራሊዝም ትግበራው ትልቁን ድርሻ ይወስዳል የሚል እምነት ነው፤ ያለኝ።

ሰንደቅ፡- አንዳንድ ባለድርሻ አካላት ገዢው ፓርቲ ስለፈለገ የተደረገ ድርድር እንጂ፤ ተቃዋሚ ፓርዎች በፈጠሩት ማሕበራዊ መሰረት አስገድደውት የተደረገ አይደለም፤ የሚል መከራከሪያ ያነሳሉ። በዚህ ላይ የእርስዎ ምላሽ ምንድን ነው?

አቶ ትዕግስቱ፡-በነገራችን ላይ እኛን የሚተቹ አካሎች ጥያቄያቸው ሲደመር፤ “ከገዢው ፓርቲ ጋር አደራድሩን” ነው የሚሉት። ልዩነታችን፤ እነሱ ሲደራደሩ “ተራማጅ” አድርገው ራሳቸውን ያቀርባሉ፤ ሌላው ከገዢው ፓርቲ ጋር ሲደራደር “አደርባይ” ናቸው የሚል የቅጥያ ፕሮፖጋንዳ ያሰራጫሉ።

ለዚህም ነው ሁሉም ነገር በገዢው ፓርቲ በጎ ፈቃድ ብቻ የሚወሰን አስመስለው የሚያቀርቡት። ገዢው ፓርቲ በቀና ልብ መደራደር እፈልጋለሁ ቢል፣ ክፋቱ ምኑ ላይ ነው? ገዢው ፓርቲ ተጨባጭ ሁኔታዎችን ተንትኖ ያልተወከሉ ድምጾች አሉ፤ ሊወከሉ ይገባል ቢል እንኳን ሁላችንም እናተርፍ ይሆናል እንጂ፤ ኪሳራው ምኑ ላይ ነው? ወይንስ ከገዢው ፓርቲ ጋር ስምምነት ቢደረስ የአንዳንዱን ፖለቲከኛ የገቢ ምንጭ ሊደርቅ ይችላል ከሚል ስጋት የሚቀርብ፣ መከራከሪያ ይሆን እንዴ?

የፖለቲካ ድርድር የግድ ከቀውስ ወይም ከጦርነት በኋላ የሚደረግ አይደለም። የሚደረጉ ድርድሮች ሰላማዊ በመሆነ መልኩ መሄድ እስከሚችሉ ድረስ ማስቀጠል መሰልጠን እንጂ፣ ጀብደኝነት አይደለም። ሰላማዊ ድርድር ቢያንስ የዜጎችን ሕይወት፤ የሀገር ቁሶችን፣ የመታደግ እድል ይፈጥራል።

ሰንደቅ፡- በሶስቱ የምርጫ ሕጎች ላይ ገዢውን ፓርቲ ጨምሮ ሁላችንም እንዲሻሻል እንፈልጋለን ብለዋል። ዘጠኝ አጀንዳዎች በተቃዋሚ ፖለቲከኞች ፍላጎት ብቻ የቀረቡ መሆናቸውንም ገልጸዋል። ከዚህ አንፃር በዘጠኙ አጀንዳዎች ባትስማሙ፣ በምርጫ ሕጎቹ ላይ ያሰፈራችሁት ስምምነት ሕጋዊ ሰነድ ሆኖ ይቀጥላል?  

አቶ ትዕግስቱ፡-አዎ። በስምምነታችን መሰረት የተስማማንበት አጀንዳ በተናጠል ውሳኔ የሚያርፍበት በመሆኑ፤ ሁሉም አጀንዳዎች በተናጠል ራሳቸውን የቻሉ ውሳኔዎች የሚሰጣቸው  በመሆኑ፤ ሕጋዊ ሰነድ ይሆናል። እንዲሁም አንደኛው አጀንዳ ከሁለተኛው አጀንዳ ጋር የሚገናኙበት ቅድመ ሁኔታዎች አልተቀመጠም።

ሰንደቅ፡- የታዛቢዎች ስብጥር ምን ይመስላል?

አቶ ትዕግስቱ፡-ከሀገር ውስጥ፣ የኤምባሲዎች ተወካዮች እና ተቋማት (ለምሳሌ ዩኤስአይዲ) አሉ።

ሰንደቅ፡- እስካሁን ያደረጋችሁት ድርድር ፖለቲካዊ ትርፉ እንዴት የሚገለጽ ነው?

አቶ ትዕግስቱ፡-ተስማምተን ነው፤ ውሳኔ ያሳለፍነው። የእኛን ጥቅም፤ ታሳቢ ያደረገ በመሆኑ ነው። ድርድሩም ለሕዝብ ተብሎ የተደረገ በመሆኑ፣ በፖለቲካ ትርፍ ብቻ ሊመዘን የሚገባው አይመስለኝም።

ሰንደቅ፡- አሁን ላይ በሶስት የፖለቲካ አመራሮች በድርድሩ የምትወከሉ ከሆነ፤ ቀድሞውኑ በመድረክ የፖለቲካ ጥምረት መወከል አትችሉም ነበር?

አቶ ትዕግስቱ፡- ከመድረክ በኩል የቀረበው ፀረ-ዲሞክራቲክ የሆነ ጥያቄ በመሆኑ ነበር ያልተቀበልነው። በነገራችን ላይ ገዢው ፓርቲ መድረክ ድርድሩን አቋርጦ እንዲወጣ ያደረገው አንዳችም ግፊት አልነበረም። በዚህ አጋጣሚ መታወቅ ያለበት፤ የትኛውም ፓርቲ፤ ከፓርቲዎች ፈቃድ ውጪ ሕልውናቸውን ሊወክል ወይም ሊያጠፋ አይችልም። የአንድ ፓርቲ ሕልውናው፤ በማንም የሚገረሰስ አይደለም።

መድረክ ያደረገው፤ እንደውጫሌ ውል ኢሕአዴግ “በእኔ” በኩል አግኙት ነበር ያለው። ይህ እንዴት ይሆናል? ሁላችንም ሕጋዊ ሰውነት ያለን ፖለቲካ ፓርቲዎች ሆነን፤ ከእኛ ስምምነት እና ፈቃድ ውጪ በሌላ ሶስተኛ ወገን እንድንወከል የሚያስገድደን፤ ለዚህም ነው ፀረ-ዲሞክራቲክ አካሄድ በመሆኑ ውድቅ ያደረግነው።

አሁን የተስማማነው አስራ ሁለት ፓርቲዎች በፈቃዳችን የሚወክሉንን መረጥን እንጂ፤ ከፖለቲካ ፓርቲዎቹ ፈቃድ ውጪ ውክልና የወሰደ የለም። መድረክም ዲሞክራቲክ በመሆነ አግባብ እና ውይይት ፍላጎቱን ለተቃዋሚ ፓርቲዎች ቢያቀርብ፣ ሃሳቡ ውሃ የሚያነሰ ከሆነ ሁሉም ሊቀበለው ይችል ይሆናል።  

ሰንደቅ፡- በቀጣይ በአዲስ አበባ አስተዳደር የምክር ቤት ምርጫ ላይ ትሳተፋላችሁ? የምትሳተፉ ከሆነ፤ ዝግጅታችሁ የገንዘብ አቅማችሁ እንዴት ነው?

አቶ ትዕግስቱ፡-እንሳተፋለን። በነገራችን ላይ ከዚህ ድርድር አንዱ የተገኘው ለተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲዎች ቋሚ የሥራ ማስኬጃ ገንዘብ በመንግስት እንዲመደብ ከስምምነት ላይ ደርሰናል። ከዚህ በፊት በአቅም ማነስ ፖለቲካ የዕለት ተዕለት ሥራችን ለማድረግ ከፍተኛ ውስንነት ነበረብን። በአዲሱ ስምምነት ቋሚ የሥራ ማስኬጃ በጀት ከመንግስት ስለምናገኝ፤ በቋሚነት ከሕዝባችን ጋር ዓመቱን ሙሉ መገናኘት እና የጋራ ግብ ለመያዝ ያስችለናል።

ሰንደቅ፡- በፓርላማው ከሚተዳደር የዴሞክራሲ ፈንድ ተጠቃሚ አልነበራችሁም? ምርጫ ቦርድ የሚሰጣችሁ የበጀት ድጎማ አልነበረም?

አቶ ትዕግስቱ፡-የዴሞክራሲ ፈንድ አይተነውም አናውቅም። ምርጫ ቦርድ፣ በምርጫ ጊዜ ከሚያደርገው የገንዘብ ድጋፍ ውጪ ምንም የገንዘብ ድጋፍ አያደርግልንም። የፓርላማ ወንበር ለያዙ የሚደረግ ድጋፍ ነበር፤ አሁን ገዢው ፓርቲ ሙሉ ለሙሉ የፓርላማ ወንበሩን በመቆጣጠሩ ድጋፍ የሚያገኝ የተቃዋሚ ፓርቲ የለም።¾

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
284 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 871 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us