በግጭቶች መካከል ድምፅ አልባው የጥፋት መሣሪያ - የቀበሌ መታወቂያ

Wednesday, 20 September 2017 13:40

በሳምሶን ደሳለኝ

Politicaበኢትዮጵያ ውስጥ ግጭቶች እየተበራከቱ መጥተዋል። ግጭት በየትኛውም ዓለም ውስጥ የነበረ፤ ወደፊትም ሊከሰት የሚችል የተግባር ውጤት መሆኑ አሻሚ አይደለም። ሆኖም፣ በኢትዮጵያ ውስጥ እየተከሰቱ ያሉ ግጭቶች፣ ለግጭቶቹ መነሻ ተደርገው የሚሰጡት ምክንያቶች በቅርጽም በይዘትም የሚቀየሩበት ሒደት በጣም ለየት ያለ ነው።

ራቅ ያለውን ተወት አድርገን፣ በቅርቡ በጎንደር እና በሶማሌና በኦሮሚያ ድንበር ማካለል የተነሱት ግጭቶች፣ ቅርፃቸውን እና ይዘታቸውን የቀየሩበት ፍጥነት በጣም ገራሚ ነው። የጎንደር ግጭት መነሻ ተደርጎ የተወሰደው ወይም የተነገረው የኮሎኔል በዛብህ የእስር ጥያቄ አያያዝ እንደሆነ በስፋት ይታመናል። በዚህ መነሻ ተቀሰቀሰ የተባለው ግጭት ቅርጹ እና ይዘቱን ቀይሮ በፍጥነት ወደ ፖለቲካዊ እና የድንበር ጥያቄ መሸጋገሩ የሚታወስ ነው።

በኦሮሚያ እና በሶማሌ ክልል አዋሳኝ ቦታዎች በተደረገ የድንበር ማካለል አለመግባባት የተነሳ ነው የተባለው ግጭት፤ ቅርጹ እና ይዘቱን ቀይሮ ለበርካታ ዜጎች ሕይወት መጥፋት ምክንያት ሲሆን  የሽግግሩ ፍጥነት አስገራሚ ነበር። በተለይ ደግሞ የሁለቱን ክልል ሕዝቦች የማቀራረብና በሕዝቦቹ መካካል ሰላም እንዲሰፍን ከፍተኛ ኃላፊነት የተሰጣቸው የክልሎቹ የኮሚኒኬሽን ቢሮዎች ኃላፊዎች ተግባር አብዛኛውን ሰው ያሳዘነ ነበር። ለንፁሃን ዜጎችም ሕልፈት የራሱ የሆነ ተፅዕኖ የነበረው ተግባር መሆኑ፣ አሻሚ አይደለም።

የሁለቱ ኮሚኒኬሽን ሰዎች ተግባር በይፋ ሳይወገዝ ወይም ለፈጸሙት ተግባር ኃላፊነት የወሰደ አካል በሌለበት ሁኔታ፤ የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳደር አቶ ለማ መገርሳና የኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል ርዕሰ መስተዳደር አቶ አብዲ መሐመድ፤ መስከረም 7/2010 በአዲስ አበባ በሰጡት የጋራ ጋዜጣዊ መግለጫ እንደተናገሩት በኦሮሚያና  በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልሎች አዋሳኝ አካባቢ የተፈጠረው ግጭት የሁለቱን ክልሎች ህዝብና መንግስት እንደማይወክል የሁለቱ ክልል ርዕሰ መስተዳድሮች አስረግጠው አስታውቀዋል።

አያይዘውም ድርጊቱን ያወገዙት ርዕሰ መስተዳድሮቹ፤ ግጭቱን በአፋጣኝ በማስቆም ፣በግጭቱ የተፈናቀሉ ዜጎችን  መልሶ ለማቋቋምና በግጭቱ የተሳተፉ አካላትን ለህግ ለማቅረብ በጋራ እንደሚሰሩም አስታውቀዋል። እንዲሁም፣ በተፈጠረው ግጭት ሳቢያ ሕይወታቸውን ላጡ ዜጎች የተሰማቸውን ሀዘን በመግለጽ ለቤተሰቦቻቸው መፅናናትንም ተመኝተዋል።

ሁለቱ ርዕሰ መስተዳድሮች የወሰዱት አቋም ተገቢ መሆኑን ማንም የሚገነዘበው ነው። ጥያቄው ያለው፣ የክልሎቹ ኮሚኒኬሽን ቢሮዎች ሲያስተጋቡት የነበረው ክስ ከርዕሰ መስተዳድሮቹ እውቅን ውጪ ተደርጎ እንዴት ሊወሰድ ይችላል? በአንድ ሕገመንግስት ጥላ ሥር ያሉ ክልሎች አንዱ ሌላውን፣ “ኦነግ” እያለ ሲከስ፤ ሌላው “የታላቋ ሱማሌ ራዕይ” አስፈፃሚዎች እያለ ሲከስ ነበር። በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አሸባሪ ተብሎ የተከሰሰ ቡድን አባላት ናችሁ ብሎ መክሰስ ከወዴት የመጣ ፍላጎት ነው? እንዲሁም “የታላቋ ሶማሌ ራዕይ” አስፈፃሚ ብሎ የሲያድ ባሬ መንግስት ቅጥያ አድርጎ መፈረጅስት ከወዴት የመጣ ፍላጎት ነው? በጣም የሚገርመው ነጥብ ደግሞ፣ የሁለቱም ኮሚኒኬሽን ቢሮዎች ውንጀላ ከድንበር ማካለሉ ጋር ተያያዥ አለመሆኑ ነው።

ከላይ የሰፈሩት አስረጅዎች፣ በኢትዮጵያ የሚነሱ ግጭቶች፣ የግጭቶቹን መነሻ ለመልቀቅ በጣም ፈጣን መሆናውቸውን ማሳያ ነው። አሁን አሁን ግጭቶች ሲነሱ በቅርብ የሚቀመቱ ምክንያችን፣ የግጭቶቹ ዋና ማሳያዎች አድርጎ መውሰድ ከባድ እየሆ ነው። በትንሽ ግጭቶች ውስጥ ትልልቅ ግጭቶች ብቅ እሉ ነው። ይህ ከሆነ ደግሞ፣ የግጭቶቹን ሥር ፈልጎ ምላሽ መስጠት እንጂ በግጭቶች መገለጫ ላይ ጊዜ ማጥፋቱ አይመከርም። ወይም ከእሳት ማጥፋት የዘለለ ግብ አይኖረውም።

 

በግጭቶች መካከል ድምፅ አልባው የጥፋት መሣሪያ -

የቀበሌ መታወቂያ

 በኢትዮጵያ ውስጥ በተከሰቱ ተደጋጋሚ ግጭቶች ንጽሃን ዜጎች እየተቀጠፉ መሆናቸው የአደባባይ እውነት ነው። በተለይ በሚከሰቱ ግጭቶች ዙሪያ ምንም አይነት አስተዋጽዖም ሆነ መረዳት የሌላቸው ዜጎች በመንጋ እንቅስቃሴዎች እየተቀጠፉ ይገኛሉ። ባሳለፍነው ሳምንት በተፈጠረው ግጭት ምንም አይነት እንቅስቃሴ ይሁን ተሳትፎ ያልነበራቸው ከ50ሺ በላይ የኦሮሚያና የሶማሌ ተወላጆች ከቀያቸው እንዲፈናቀሉ ተደርጓል። ከጎንደር በርካታ የትግራይ ተወላጆች ተፈናቅለዋል። ከጉራፈርዳ በርካታ የአማራ ተወላጆች ተፈናቅለዋል። ነገም ማን እንደሚፈናቀል ማን ያውቃል?

በኢትዮጵያ ውስጥ በሚከሰቱ ግጭቶች የሚፈናቀለው ሕዝብ ቁጥር በርካታ ነው። እንዲሁም እየተቀጠፉ ያሉ ንጹሃን ዜጎች ቁጥር በርካታ ነው። በተለይ ተቃውሞ በሚደረግባቸው አካባቢዎች የሚኖሩ ሰዎች ቀደም ብለው በወሰዱት የቀበሌ መታወቂያ ብሔራቸውን የሚገልጽ በመሆኑ በቀላሉ ለጥቃት እየተጋለጡ መሆናቸው ለዝግጅት ክፍላችን በግንባር ቀርበው ያስረዱን ሰዎች ቁጥር ቀላል አይደለም። ለምሳሌ ባሳለፍነው ሳምንት ከፍተኛ ቁጥር ያለው ሕዝብ ከቀየው የተፈናቀለው ቀበሌ በሰጠው መታወቂያ ላይ በሰፈረው የብሔር ማንነቱ መነሻ በማድረግ መሆኑ ምንጮቻችን ነግረውናል። “የአካባቢውን ሕዝብ ለመለየት በጣም አስቸጋሪ ነው። ኦሮሞው ከሶማሌ ጋር የተጋባ በመሆኑ ለመለየት የሚያስቸግር ነው። በእምነትም አብዛኛው ተመሳሳይ እምነት ውስጥ ነው ያለነው። ልዩነቱ ያለው በቀበሌ መታወቂያ ላይ በሰፈረው የብሔር ማንነት ላይ ብቻ ነው፤ ችግሩን ግን አሁን ቀመስነው” ብለዋል።

እማኝ ሆነው ከነገሩ መካከል “ከትራንስፖርት መኪና ውረዱ እያሉ በመታወቂያችን ላይ በሰፈረው ብሔር ማንነት ይሰበስቡናል። ከጉዳዩ ቅርበት ይኑረን አይኑረን የሚጠይቀን የለም። ብቻ ይመቱናል፣ ደስ ካላቸው ይገሉናል። በጣም አስቸጋሪ የሆነ ጉዞ ነው እያደረግን ያለነው። መታወቂያ ላይ በተፃፈ ማንነት መነሻ ብቻ ተጠያቂ የምንሆንበት ጊዜ ላይ ደርሰናል። በጣም ያሳዝናል። መታወቂያው ላይ ባይሰፍር ማን እንደሆን እንኳን ግንዛቤ በሌላቸው ሰዎች እየተገደልን፣ እየተደበደብን እስከመቼ ነው የምንዘልቀው?” ሲሉ ጠይቀዋል።

በዚህ ጉዳይ ያነጋገርናቸው የደህንነት ባለሙያ እንደገለጹልን፣ “ለዚህ አይነት አደጋ በቅርብ በሩዋንዳ የተደረገውን ማስታወስ በቂ ነው። ያሁሉ ሰው ያለቀው በመታወቂያው ላይ በሰፈረው ማንነቱ ብቻ ነው። ነገ በኢትዮጵያ ተመሳሳይ ጥፋት እንደማይደገም ማንም ማረጋገጫ ማቅረብ አይችልም። የብሔር ማንነት መመዝገብ የሚያስፈልገው ከሕዝብ ቆጠራ አንፃር ወይም ከዲሞግራፊ አንፃር ነው። ወይም ለበጀት አያይዝ እንዲመች ፖለቲካዊ መብቶችን በቁጥሩ መሰረት ለመመለስ ነው። ይህንን ለማድረግ ደግሞ መታወቂያ በሚዘጋጀው ዳታ ቤዝ ላይ ተገቢውን መረጃ አስቀምጦ መስጠት ይቻላል። ብሔር የሚለውን በዳታ ቤዝ መዝግቦ ሌላ መገለጫዎቹን ሞልቶ መስጠት ይቻላል። በጣም ቀላል ሥራ ነው። ከዚህ ውጪ የፖለቲካ አመራሩ ሲያጠፋ ወይም በማንኛውም ዋጋ ሥልጣን የሚፈልገው ኃይል አመጽ ባስነሳ ቁጥር ንፁሃን ዜጎች በመታወቂያ መነሻ መገደል መሰደድ የለባቸው” ሲሉ መክረዋል።

 

 

አቶ አብዲ መሀሙድ ኡመር የሶማሌ ክልላዊ መንግስት ርዕሰ መስተዳደር

ቀብር ስነስርዓት ላይ ያስተላለፉት መልእክት

የተከበራችሁ በሀገር ውስጥም በውጭም የምትገኙ የኢትዮ. ሶማሌ ክልል ተወላጆች በሙሉ መስከረም 2 ቀን 2010 አ.ም በአወዳይ ከተማ ምንም ባላጠፉ እና የሶማሌ ተወላጅ በመሆናቸው ብቻ በሀገራችን በየትኛውም ቦታ ታይቶና ተሰምቶ በማይታወቅ መልኩ በአሰቃቂ ሁኔታ በስለት ተጨፍጭፈው የተገደሉ ህዝባችን የደረሰባቸው የህይወት መጥፋት በክልሉ መንግስትና በራሴ ስም የተሰማኝን ሀዘን ለመግለጽ እወዳለሁ::

በግጭቱ ግዜ እስከ 300 የሚደርሱ የክልሉ ተወላጆች በአንዳንድ ሰላም ወዳድና ሰብአዊነት በሚሰማቸው የኦሮሞ ተወላጆች የሶማሌን ተወላጆች በመደበቅና ለሀገር መከላከያ ሰራዊት በሰላም ያስረከቡ በመሆኑ የ300 ዜጎች ህይወት የታደጉ ሲሆን በተቃራኒው የክልሉ ና የአከባቢው ጸጥታ ሀይልና አመራሮች ዝምታና ተሳታፊነት የሌሎቹ በአሰቃቂ ሁኔታ ህይወታቸው ሊያልፍ ችሏል::

በአጠቃላይ ይህንን ነገር ለማርገብና የመንግስት አቅቋማችንን ለማንጸባረቅ የሚከተሉትን መርህ አስተላልፈናል:-

መላው የክልላችን ህዝብ ሊያውቀው የሚገባ ዋንኛው ነገር ይህንን ጥቃት የፈጸሙትና በማህበራዊ ድረ ገጽ የሚያስተጋቡት ማንኛውም አካል አሁን ያለውን ስርአት የሚቃወሙና ህዝባችንን የሚጠሉ አካላት መሆናቸውን፤

 

 • አብረውን የሚኖሩ ምንም በማያውቁ ኦሮሞ ተወላጆች ላይ ምንም አይነት ጥቃት እንዳይፈጸምባቸው::
 • የሞቱት ሞተዋል ፈጣሪ ነፍስ ይማር አሁን ማተኮር ያለብን ሰላማችንና ልማታችን ላይ ነው:: ለሞቱት ዜጎች አብረውን የሚኖሩትን ኦሮሞ ተወላጆች ላይ የበቀል እርምጃ መውሰድ ክብርም አይደለም፣ ጀግንነትም፣ አይደለም ትርፍም የለውም:: ስለዚህ ማንኛውም የሶማሌ ተወላጅ ምንም አይነት የጥፋት እርምጃ በኦሮሞ ተወላጆች ላይ እንዳይወሰድ::
 • ትልቅነት ማለት ችሎ ማለፍና ከበቀል በጸዳ አመለካከት ህዝባዊነትን በማጎልበት በመቻቻል መንፈስ ሰላማችንን በማስቀጠል ልማታችንን ማፋጠን ነው::
 • ሰላም የህልውናችንና የልማታችን ቁልፍ መሆኑን መረዳት፤
 • በማንኛውም መልኩ በኦሮሞና በሶማሌ ህዝብ መካከል የሚፈጠር የብሄር ግጭት በምንም መልኩ እንዳይከሰትና መቼም እንዳይፈጠር ማድረግ፣
 • ከሰብአዊ መብት ተሟጋች የተውጣጡ አካላት ጥቃቱን በአካል አሳይተናል በአይናቸውም ተመልክተዋል፣ ይህም ማስረጃ ሆኖልናል::
 • እንደ መንግስትም እንደ ህዝብም የፌደራል መንግስታችን  ይህንን ጥፋት ያደረሱ አካላት ለህግ እንድታቀርቡልን እንጠይቃለን::
 • በግጭቱ ጉዳት የደረሰባቸውን የምንረዳበትና መልሰው የሚቋቋሙበት ሁኔታ እንፈጥራለን ወደተግባርም በፍጥነት እንገባለን::
 • ይህንን የሚያከናውንና ፈንድ የሚያሰባስብ በሀገር ውስጥም ከሀገር ውጭም ኮሚቴ ይቋቋማል፣
 • ከፌደራል መንግስት ጋርም ከኦሮሚያ ክልል መንግስት ጋርም ግጭቱ በዘላቂነት የሚፈታበትን መንገድ በጋራ  እንሰራለን::
 •  በመጨረሻም በአሰቃቂ ሁኔታ ህይወታቸውን ላጡ ወገኖቻችን ነፍስ ይማር እያልኩኝ ለቤተሰቦቻቸውም መጽናናትን እመኛለሁ::

በኢፌዴሪ የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት

ግጭቱን አስመልክቶ የተሰጠ መግለጫ

አገራችን ኢትዮጵያ እየገነባችው ያለው ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ገና ጨቅላ ዕድሜ ያስቆጠረ ቢሆንም ከተመሰረተበት ጊዜ አንስቶ ባለፈባቸው ጥቂት ዓመታት ውስጥ በርካታ አንጸባራቂ ድሎችን ማስመዝገብ የቻለ ነው። ከአሁኑ ለሌሎች ሃገራት ልምዶችን እያካፈለ የሚገኝም ስርዓት ሆኗል።

አገራችን ሰላም በራቀው የምስራቅ አፍሪካ አካባቢ እየኖረች፣ የራሷን ሰላም አስተማማኝ ከማድረግ አልፋ ለአካባቢውና ለሌሎች የአፍሪካ አገራት የሰላም ዘብ ለመሆን የበቃችውም የኢትዮጵያ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ወደውና ፈቅደው በመሰረቱት ፌዴራላዊ ስርዓት አማካኝነት ውስጣዊ ሰላሟን በአስተማማኝ መልኩ ለማረጋገጥ በመቻላቸው ነው። ኢትዮጵያውያን እነዚህና ሌሎች በርካታ አንፀባራዊ ድሎችን ማስመዝገብ የቻሉት ግን መንገዳቸው ሁሉ አልጋ በአልጋ ስለሆነላቸው አልነበረም። በየወቅቱ የሚያጋጥሟቸውን ፈተናዎች ሁሉ በፌዴራል ሥርዓታቸው ማዕቀፍ ውስጥ ሆነው በፅናት እየፈቱ በማለፋቸው እንጅ! 

በቅርቡ ካጋጠሙን ፈተናዎች መካከል አንዱ በአንዳንድ አካባቢዎች ከወሰን ጋር ተያይዞ ይነሱ የነበሩ ችግሮች ይጠቀሳሉ። እነዚህን ችግሮች ለመፍታት የፌዴራሉና የሚመለከታቸው የክልል አመራሮች እና ወንድማማች ህዝቦች በጋራ ሲሰሩ ቆይተዋል። በኦሮሚያና በኢትዮጵያ ሶማሊ፣  በኦሮሚያና በደቡብ ብሄር፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች፣ በኦሮሚያና በቤንሻንጉል እንዲሁም በትግራይና በአማራ ክልሎች መካከል ከወሰን ጋር ተያይዞ ተፈጥረው የነበሩትን ችግሮች በመፍታት ረገድ አበረታች ስራዎች ተሰርተዋል።

በኦሮሚያና በኢትዮጵያ ሶማሊ ክልሎች መካከል ከወሰን ጋር ተያይዞ የተፈጠረውን ችግር ለመፍታት በተካሄደው እንቅስቃሴ አበረታች ሥራዎች ቢከናወኑም አሁንም ቀሪ ስራዎች መኖራቸው ይታወቃል። በዚህ መሃል ግን ለዘመናት አብረው የኖሩትን የኦሮሚያና የኢትዮጵያ ሶማሊ ወንድማማች ህዝቦችን ፈጽሞ ሊወክል የማይችል ግጭት ሰሞኑን በአንዳንድ አካባቢዎች ተከስቶ ለወገኖቻችን ሞትና መፈናቀል ምክንያት ሆኗል። በዚህ አጋጣሚ በዚህ ግጭት ሳቢያ ህይወታቸውን ላጡና ጉዳት ለደረሰባቸው ወገኖቻችን ሁሉ የኢፌዴሪ መንግስት የተሰማውን ጥልቅ ሀዘን እየገለጸ፣ ለቤተሰቦቻቸውም መጽናናትን ይመኛል።

ችግሩ ወደከፋ አደጋ እንዳይሸጋገር ለመቆጣጠር ሲባል የአገር መከላከያ እና የፌዴራል ፖሊስ ሰራዊቶቻችን ግጭቱ ወደ ተከሰተባቸው አካባቢዎች በመንቀሳቀስ ከክልሎቹ የፀጥታ ኃይሎች ጋር በትብብር በመሥራት ሁኔታውን በመቆጣጠር እና በማረጋጋት ላይ ይገኛሉ። ግጭቱን በማነሳሳትና በማባባስ የተሳተፉ ወገኖችን በህግ ተጠያቂ ለማድረግ በሚከናወነው የቁጥጥር ስራም በዜጎች ላይ የሰብዓዊ መብት ጥሰት እንዳይፈጸም አስቀድሞ ለመከላከል ሲባል የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ተወካዮች በሥፍራው ተገኝተው ሁኔታውን በቅርበት እየተከታተሉ ናቸው። በግጭቱ ሳቢያ ከመኖሪያ ቀያቸው የተፈናቀሉ ወገኖቻችንን በጊዜያዊ ማረፊያ ቦታዎች በማቆየት አስፈላጊውን ድጋፍ እንዲያገኙ በመደረግ ላይ ሲሆን በቀጣይም ወደቀድሞ መኖሪያ አካባቢዎቻቸው ተመልሰው የተረጋጋ ሕይወታቸውን እንዲቀጥሉ የሚደረግ ይሆናል።

ችግሩን ከማረጋጋት ባለፈ በዘላቂነት ይፈታ ዘንድ መንግስት ከክልሎቹ አመራሮች፣ የአገር ሽማግሌዎች፣ የሃይማኖት አባቶችና ህዝቦች ጋር በጋራ በመሆን ከአሁን በፊት የጀመራቸውን ስራዎች አጠናክሮ የሚቀጥል ይሆናል። በዚህ አጋጣሚ የሁለቱ ክልሎች ወንድማማች ሕዝቦች፣ የአገር ሽማግሌዎችና የሃይማኖት አባቶች በጊዜያዊ ግጭት ሳይረበሹ ችግሩን በሰላማዊ እና ዴሞክራሲያዊ አግባብ ለዘለቄታው ለመፍታት ሲያካሂዱት የነበረውን ጥረት አጠናክረው በመቀጠል ለችግሩ ዘላቂ ዕልባት በመስጠት ላይ አተኩረው እንዲሰሩ መንግስት ጥሪውን ያቀርብላቸዋል። የአገራችንን ሰላም፣ ልማትና ብልጽግና የማይወዱ አንዳንድ ኃይሎች ጊዜያዊ ግጭቶችን በመቆስቆስና በማፋፋም አገራችንን ወደ ጥፋትና ውድመት ለመክተት እያደረጉት ያለው ማንኛውም እንቅስቃሴ ከሕዝቦቻችን ዕይታ የተሰወረ ባለመሆኑ የአገራችንን ሰላም በመጠበቅ ረገድ ስትጫወቱት የነበረውን የመሪነት ሚና አጠናክራችሁ እንድትቀጥሉም መንግሥት ጥሪውን ያቀርብላችኋል።

የአንዱ ወይም የሌላኛው ሕዝብ ተቆርቋሪ በመምሰል፣ በሶሻል ሚዲያና በሌሎች የመገናኛ አውታሮች አማካኝነት ችግሩን በማራገብና በማጋነን፣ በሽብር እና የጥላቻ ቅስቀሳ እኩይ ተግባር ላይ የተሰማራችሁ አካላት ሁሉ ከድርጊታችሁ እንድትቆጠቡ መንግሥት ያስጠነቅቃል። አንዳንድ አካላትም፣ በተፈጠረው ጊዜያዊ ችግር በመደናገጥ በደመ ነፍስ እየሰጡት ያለው መረጃ እና እርስ በርስ የመወነጃጀል ተግባር ችግሩን ከማባባስ ያለፈ ፋይዳ የሌለው በመሆኑ ከዚህ መሰሉ አድራጎት እንዲታቀቡ መንግስት ማሳሰብ ይወዳል። በዚህ መሰሉ ተግባር ላይ መሳተፍ የሕግ ተጠያቂነትን የሚያስከትል ከባድ ወንጀል እንደሆነም መንግሥት ማስገንዘብ ይወዳል።¾

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
345 ጊዜ ተነበዋል

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us