የኦሮሚያ ክልል ፕሬዝደንት፤ ከመገንጠል እና ከአግላይ ጠቅላይ የአስተሳሰብ ሳጥን ውጪ ምን ብለዋል?

Wednesday, 04 October 2017 12:44

“ይቅርና በየመንደሩ ተከፋፍለን፤ አንድም ሆነን ዳገቱን ልንገፋው አልቻልንም”

በሳምሶን ደሣለኝ

አቶ ለማ መገርሳ ኦህዴድን የተቀላቀሉት የደርግ ስርዓት ከመውደቁ ከጥቂት ወራት በፊት ገና በለጋ የወጣትነት እድሜያቸው በ1983ዓ.ም ነበር፤ በተለያዩ ድርጅታዊ የካድሬ መዋቅር ውስጥ የተለያዩ ግዳጆችን በብቃትና በታማኝነት መወጣታቸው ይነገራል፡

አቶ ለማ መገርሳ ከሽግግር ጊዜ ጀምሮ እስከ ቅርብ ዓመታት ድረስ በተለያዩ ክልላዊ የፀጥታ እና ደህንነት መዋቅር ውስጥ በተለያዩ ደረጃዎች ላይ ከፍተኛ ልምድ አካብተዋል፤ ኦህዴድ በክልሉ ህዝባዊ መሰረቱን እንዲያሰፋ እንደ ኦነግ የመሳሰሉ ድርጅቶችን በመዋጋቱ ረገድ እጅግ ውጤታማ ስራን በሰፊው መስራታቸው ይታመናል።

አቶ ለማ መገርሳ በድርጅት ደረጃ ከተራ ታጋይ እስከ ማዕከላዊ ኮሚቴ እና ስራ አስፈፃሚ አሁን ደግሞ የድርጅቱ ሊቀመንበር እስከመሆን ደረጃ ደርሷል።

በመንግስት ኃላፊነት ደረጃ፤ የኦሮሚያ ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ሆነው ሰርቷል፣ የኦሮሚያ የፀጥታ ቢሮ ኃላፊ ሆነው ሰርቷል፣ የኦሮሚያ ንግድ ገበያ ልማት ቢሮ ኃላፊ ሆነው ሰርቷል፣ የጨፌ ኦሮሚያ ም/ቤት አፈ-ጉባዔ ሆነው ሠርተዋል፤ አሁን የኦህዴድ ሊቀመንበር በመሆናቸው የኦሮሚያ ክልል ፕሬዝዳንት በመሆን እያገለገሉ ይገኛሉ።

በትምህርት ደረጃቸውን በተመለከተ፤ በPolitical Science & International Relations የመጀመሪያ ዲግሪ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ወስደዋል። ሁለተኛ ዲግሪያቸውን በInternational Relations ከአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ወስደዋል። ሶስተኛ ዲግሪያቸውን በPeace & Security ለመቀበል በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ እየተማሩ እንደነበር ይታወቃል።

በዚህ የፖለቲካ አምድም አቶ ለማ መገርሳ ከዚህ በፊት በተለያዩ መድረኮች ያሰሟቸው ፍሬ ነገሮች ተደምረው፤ በ21/1/2010 በቢሾፍቱ ከተማ በተከበረው የኢሬቻ በዓል ላይ ሲጠበቅ የነበረውን የሰው ሕይወት እና የቁስ መጥፋት አጀንዳዎችን፤ ባዶ አድርገዋቸዋል። እንዲሁም ከፖለቲካ አመራሩ ባልተናነሰም አባገዳዎች እና ሕዝቡ የኢሬቻ በዓል በሰላም እንዲጠናቀቅ የተጫወቱት ሚና ከፍተኛ ከበሬታ የሚሰጠው ነው።  

አቶ ለማ መገርሳ፤ ከኦሮሚያ ክልል ተሻግረው በፖለቲካና በኢኮኖሚ የዳበረች ኢትዮጵያ የሁሉም ዜጋ ዋስትና መሆኗን አስምረው የተናገሩትን መለስ ብለን ማካፈል ወደናል። መልካም ንባብ ይሁንላችሁ።

 

 

ክልሎች ማንን ማባረር ይችላሉ?

የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት ማንንም ኢትዮጵያዊ ዜጋ ለማባረር ስልጣኑም ፈቃዱም የለውም። እውነት ነው ሁላችንም የተለያየ ስም አለን። ግን ሁላችንም ኢትዮጵያውያን ነን። ሁላችንም ኢትዮጵያውያን ነን። ይቅርና አንድ ኢትዮጵያዊ አንድን ኢትዮጵያዊ ከራሱ ቤት ማባረር፤ የውጭውን ዜጋ ፈረንጁንምኮ ለምነን አምጥተን እያስተናገድን ነው። ሊታሰብ የሚችል አይደለም ይሄ። ሊታሰብ የሚችል አይደለም። እኔ አንዳንዶቻችሁ በየማኪያቶ ቤትና በየአረቄ ቤቱ የሚወራውን ወሬ ሰምታችሁ እንዳትረበሹ ስለምፈልግ ነው። ስለምፈልግ ነው። ትልቁ ኢንቨስትመንት ከፊንፊኔ ቀጥሎ ኦሮሚያ ውስጥ ነው ያለው። ትልቁ ኢንቨስትመንት በኢትዮጵያ። ትልቁ ኢንዳስትሪ ያለው ኦሮሚያ ውስጥ ነው።

 

 

የጋራ መለወጥ ለምን?

ኦሮሚያ ካልተለወጠ ኢትዮጵያ አትለወጥም። ቤኒሻንጉል ካልተለወጠ ኢትዮጵያ አትለወጥም። ጋምቤላ ካልተለወጠ ኢትዮጵያ አትለወጥም። በየመንደራችን ለውጥ ስናመጣ ነው ሀገራችን ልትለወጥ የምትችለው። ያ ማለት ደግሞ እያንዳንዳችን፤ ግለሰቦች ስንለወጥ ስንቀየር ለለውጥም ስንሰራ ነው ሀገር የሚቀየረው። ስለዚህ ኢትዮጵያን ለመቀየር ኦሮሚያን መቀየር አለብን። እዚጋ ሃላፊነትና ድርሻ አለንና እኛ እንደመንግስት መሪዎች ዛሬ ያለነው። ለዚህ ደግሞ በሁሉም የኢኮኖሚ መስኮች መደረግ የሚገባቸው ማስተካከያዎች ማድረግ፤ መውሰድ፤ ማስተካከል ተገቢ ነው የሚሆነው።

 

ስደተኛው ማን ነው? ሕገወጥ ኢንቨስተሩ ምን ይደረጋል?

ይቺ ሀገር የሁላችንም ነች። ማንም ስደተኛ የለም። አንዱ ኣሳዳጅ አንዱ አባራሪ፣ አንዱ ተባራሪ የሚሆንበት ሀገር ላይ አይደለንም ያለነው። ስርዓት ባላት የሁላችንም በሆነች ሀገር ላይ ነው ያለነው። ህገ ወጡ ግን ይቀማል። ምንም ጥያቄ ለውም ይቀማል። የሚገርማችሁ ወጣቱ አምራች ኃይል ነው፤ ሰርቶ መኖር አለበት። ሰርቶ ለመኖር የእያንዳንዱ ወጣት ህይወት ለመቀየርም ብቻ አይደለም፤ አምራች ኃይል ነውኮ ይሄ። ጉልበት አለው፣ እውቀት አለው፤ አገር እናሳድግ ካልን ይሄን ወጣት ወደምርት ማስገባት አለብን። እንዲያመርት እድል ማመቻቸት አለብን። ዳቦ እንዲያገኝ ብቻ አይደለም። ሀገርን ለመለወጥ አእምሮ ያለው ብሩህ ወጣት ያስፈልጋል፤ እሱን ሜዳ ላይ አስቀምጠን ሀገር እንለውጣለን ብለን የምናስበው ነገር አይሆንም።  ከዛም ባለፈ ደግሞ እንዲሁ ዝም ብሎ ሲቀመጥ ምን ሊያደርግ እንደሚችልም ደግሞ አይተናል። ለኢንቨስተሮችችን ከለላ እንሰጣለን ብለን  ስንል እንዲህ አይነት ነገሮችን ካልሰራን፤ ካላመቻቸን፤ ካላስተካከልን፤ አደጋው ሂዶ ሂዶ ከማናችንም በላይ ባለሃብቶችችንን ነው የሚጎዳው። ጎድቶም ስላየን። እናስተካከል ብለን ወጣቱን በግብርናው፤ በኢንዳስትሪው፤ በማኑፋክቸሪንጉ፤ በምኑም አቅም በፈቀደ ሁሉ እናስገባ ብለን ስንጀምር መዓት ዘመቻ ነው የተነሳብን።

 

 

ኪራይ ሰብሳቢ ኢንቨስተር

ማዕድን አሸዋ፤ ድንጋይ፤ ፑሚስ፤ አፈር ዝቆ ለፋብሪካ መስጠትን….እውነት ነው እዛ ውስጥ ገብተው ሲጠቀሙ ነበሩ ግለሰቦች አሉ። ጉዳዩ ከገባቸው አካላት ጋር ተነጋግረን ተስማምተን ፈታን። ነገር ግን 12 እና 13 ዓመታት ያመረቱ ጥሪት ያካበቱ ግለሰቦች እንለቅም፤ ትልቅ ግብግብ ነው የነበረው። ምንድነው የሚሰሩት እነኚህ ግለሰቦች? ላይሰንስ ወስደው እዚህ አደአ ላይ የሚገኝ ተራራ ፑሚስ አፈር እናወጣለን ብለው አንድም እንኳን ተጨማሪ እሴት መጨመር እንኳን አይደለም በጣታቸው ሳይነኩት 58፣ 68 ሚሊየን ሸጠው የወጡ ግለሰቦች አሉ። ተራራ፤ ተራራ እንደተፈጠረ፤ ያውም ተራራ ላይ ወጥተው ሳይሆን በሩቅ እያሳዩ ሃምሳ ስምንት ስልሳ ስምንት ሚሊየን። ይቺ ሀገር ሁላችንም ሀገር ነች። ልዩ ዜጎች ናቸው እንዴ እነሱ? ወይስ ሮያል ፋሚሊ ናቸው? እንደዚህ አይነት ክፍል የለንም በዚህ ሀገር ውስጥ። ግማሹ ዳቦ እያረረበት ግማሹ ወጣ ብሎ ሚሊየኖችን ሰብስቦ የሚመለስ ከሆነ ይሄ እብደት ነው። ወዴት ነው የሚወስደን?

 

የመሬት ካርታ እሽክርክሪት

ታጥረው የሚቀመጡ መሬቶችንም ብታዩአቸው ማነው የወሰደው መጀመሪያ አቶ ከበደ። አሁን ማን እጅ ነው ያለው? ሶስተኛ አራተኛ ወገን ተላልፎ በአምስተኛ በስድስተኛ ግለሰብ እጅ ነው ያለው ጣጥሮ የሚቀመጠው መሬት። የብዙ ሚሊዮኖች ዝውውር በአንዲት መሬት ላይ ታካሂዷል። ይሄንን ዝም ብለን ማየት አለብን? ማየት የለብንም። ሀገር እንዲለውጥ እኮ ነው እያንዳንዱን ገበሬ ከህይወቱ ላይ እትብቱ ከተቀበረበት መሬት ላይ አንስተን ወደሌላ ቦታ የወሰድነው። ግለሰቦችን ሚሊየነር ለማድረግ አይደለም። ያምኮ ዜጋ ነው። ኢትዮጵያዊኮ ነው፤ ያም። ስለዚህ የጀመርነው ስራ በልበ ቀናነት ጥሮ ግሮ ለፍቶ ሚሰራውን ኢንቨስተር መለየትና ማበረታታት ነው እንደ ኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት። በቅርበት ችግሩን እየጠየቅን ማበረታታት። በዚህ ውስጥ ደግሞ ተቀለቅሎ እንዲህ አይነት ስራ እየሰራሁ ልኑር ብሎ የሚለውን ለይተን መቅጣት። አስፈላጊውን ማስተካከያ ማድረግ። ይሄን ሰራን። ይሄን ስንሰራ ደግሞ ሁላችንም ተጋግዘን መስራቱ አስፈላጊ ነው።ተቀላቅለን በስመ ኢንቨስተር ኪራይ ሰብሳቢ በጅምል፤ እንዲህ ሆነ፤ መባባል የለብንም። ይሄ ችግር አለ ይሄን በግልጽ ልነግራችሁ እፈልጋለሁ።

 

በሶማሌ እና በኦሮሚያ ክልል ሕዝቦች መካከል የተነሳው ፀብ የማነው?

ይህ እያየነው ያለው ጉዳይ (ወቅታዊ ግጭት) የኦሮሞ ህዝብ እና የሶማሌ ህዝብ መካከል የተፈጠረ ጉዳይ አይደለም። የኦሮሞ ህዝብ እና የሶማሌ ህዝብ ግጭት አይደለም። በፍፁም አልነበረምም። ለዚህ ማሳያ ይሀን በመሰለ ከባድ ነገር ውስጥ በየቤታቸው እየደበቁ የብዙ ኦሮሞዎችን ህይወት ከአደጋ የታደጉት ሶማሌዎች መሆኑ እንዲሁም የብዙ ሶማሌዎች ህይወት የታደጉትም ኦሮሞዎች መሆኑ ነው።

በዚህ አደጋ አንድ ቤተሰብ ለሁለት ተከፍሏል። ባልና ሚስት ተለያይቷል። ህዝቡ የፈራውን ንብረት ትቶ ለመፈናቀል ተገዷል። ይህ ጉዳይ አስከፊ እና አደገኛ ነው። የደረሰው አደጋን የተፈናቀሉትን ለመደገፍ መንግስትና ህዝባችንም የተቻለውን ርብርብ እያደረገ ይገኛል። ለዚህም የኦሮሞ ህዝብን ለማመስገን እፈልጋለሁ።

ታይቶ በማይታወቅ መልኩ ህዝባችን ከምስራቅ እስከ ምእራብ፡ ከደቡብ እስከ ሰሜን በአንድነት ወገኑን ለመደገፍ እየተረባረበ ይገኛል።

ይህ ድጋፍ በአጭር ጊዜ ድጋፍ የሚቆም አይደለም። የሚበላና የሚጠጣ ማቅረብ ብቻ በቂ አይደለም። የመንግስት ውሳኔ እና የህዝብ ድጋፍን ይጠይቃል። የተፈናቀለውን ህዝብ በዘላቂነት መልሶ ማቋቋምና ወደ ቀድሞ ኑሮው እንዲመለስ ታቅዶ መሰራት አለብን። የተፈናቀለው ህዝብ ለተለያዩ በሽታ አንዳይጋለጥ እየሰራን ነው።

የኦሮሞ ህዝብ የሀገሪቱ ግንድ ነው።የክልሉ መንግስትና የህዝባችን አቋም ለህዝባችን እና ለሀገራችን ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች አንድነት መቆም ነው። ለሰላማችን እና ለህዝቦች ወንድማማችነት በጋራ መቆም አለብን።

 

ሁለታችንም ጋር ችግሮች አሉ?

አሁን ባለው ደረጃ፤ እውነት ነው መንግስትን መውቀስ ትችላላችሁ፤ እኛም እናንተን መውቀስ እንችላለን ሁለታችንም ጋር ችግር አለ። ይህን የኢኮኖሚ ፖሊሲ፤ ኢኮኖሚ ስርዓት የጀመርነው ቅርብ ጊዜ ነው። ሙሉ እውቀት ሙሉ ብቃት ኖሮን አይደለም፤ እናንተም ወደ ኢንቨስትምንቱ ስትገቡ ይሔው  ነው። ብዙ በስራ ውስጥ ተግዳሮት ውስጥ እየተማርን እየተለወጥን የምናስተካክላቸው በርካታ ነገሮች በወዲያም በወዲህም አሉ። ኢንቨስተሩ የሚቸገርባቸው በርካታ ነገሮች አሉ። ሁላችንም የምንቀበላቸው ነገሮች አሉ። ሁላችሁም እየሰራችሁ ያላችሁበት ሁኔታ የተመቻቸ ሁኔታ ላይ ሆናችሁ አይደለም እየሰራችሁ ያላችሁት። የቢሮክራሲው ችግር ውጣ ውረዱ ከባድ ነው። እናውቃለን። እዉነት ነው ፓወር አለ ምናለ ግማሹ ህንፃ ገንብቶ ማሽን አስገብቶ ሰራተኛ ቀጥሮ ፓወር በማጣቱ ብቻ በኪሳራ ለወራት የሚቆም ስንት ፋብሪካ አለ። ቆጣሪ ባለመግባቱ ብቻ የሚቸገር ኢንቨስተር አለ። የመሬት… ለማስፋፋት ኢንቨስትመንት መስፋፋት አለበት። በሆነች ቦታ፤ ካሬሜትር ወይም ሄክታር ላይ ሊገደብ የሚችል አይደለም።

 

 

በኢንቨስትመንት ስም የሚወሰደው መሬት

አሁን በእጃችን ላይ ያለው ዳታ፤ ይሄም ኢንቨስተር ብለን ስንል ጥቃቅኑን ሳይሆን ትልልቆቹ። ከዚህ ውስጥ ስራ ውስጥ ገብቶ እየሰራ ያለው 46 ከመቶ ብቻ ነው። 46 ከመቶ። ይህስ ራሱ ምን እየሰራ ነው? አንዳንዱ ባለአምስት ኮከብ ሆቴል እሰራለሁ ብሎ መጋዘን ሰርቶ በ100ና 150 ሺህ ብር የሚያከራይ ነው። የመኪና መለማመጃ ያደረገ፤ ግማሹ አጥሮ አስቀምጦ ሌላ ስራ የሚሰራበት፤ ይሄም ራሱ ኢንቨስትመንት ከተባለ እንተወው። አንድም ቆርቆሮ አለበት እንተወው። 46 ከመቶው እነኚህን አካቶ ነው። የተቀረው 60 ምናምን ከመቶው እንዲሁ ታጥሮ የሚቀመጥ ነው። አስራ ምናምን፣ ሰባት፣ ስምንት፣ ዘጠኝ ዓመት፤ በዓመት እየሄደ ሳር እያጨደ የሚሸጥ፤ ይሄ ነው ኢንቨስተር የሚባለው። እናንተም እነኛ አይነት ሰዎችም ኢንቨስተር ነው ስማችሁ። ሳር እያጨደ የሚሸጥ፤ ከዚህ መሬት ላይ 200፤ 300፤ 400 ገበሬ ነው የተፈናቀለው። አጥሮ ከሚያስቀምጥ ገበሬው አስር ዓመት ምንም ይሁን ምን ምርት ቢያመርትበት ህይወቱንም ይቀይርበታል፤ ሀገርንም ይጠቅማል። አስር ዓመት። በዚች ደሃ ሀገር ውስጥ መሬትን እንዲህ ጦም ማሳደር ምን ያህል ከባድ እንደሆነ ሁላችንም መገመት የሚያዳግተን አይመስለኝም።

 

 

የመሬት ነገር?

የመሬት ጉዳይ ከባድ ነው። የሀብት ምንጭ መሬት ነው እዚህ ሀገር ላይ። የሃብት ምንጭ መሬት ነው። ኢትዮጵያ እንደ ሀገር ከተመሰረተችበት ጊዜ ጀምሮ ሲካሄዱ የነበሩ አብዮቶችን መለስ ብለን ካየን መነሻውም መድረሻውም፤ መሬት ነው። ሌሎቹ ተቀጥላዎች ናቸው። የመሬት ጉዳይ ቀላል አይደለም። የማንነት ጉዳይ ነው። የኢኮኖሚ መሰረት ነው። እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ከመሬት ጋር ያለውን ቁርኝት ሁላችንም እናውቀዋለን። ይሄን ጉዳይ በሚገባ አጢነነው፤ በሚገባ ሁላችንም የምንጠቀምበት፤ ይህች ሀገር ይህች ምድር ሁላችንንም የአቅማችንን ያህል የምትጠቅመን አድርገን ካሁኑ መስራት ካልጀመርን ሄደን ሄደን ብንወጣም፤ ብንወርድም፤ ብንለፋም ውጤቱ ዜሮ ነው የሚሆነው። አጥሮ አስቀምጦ ኢንቨስተር ነኝ የሚለውን እየነጠቅን ነው። የግድ ነው ይሄ። ይሰራል አይቆምም። ለሚሰራው አሳልፈን መስጠት አለብን። ያን ስናደርግ የሚያኮርፈን በየከተማው፤ በየጠላ ቤቱ፤ ማኪያቶ ቤቱና ውስኪ ቤቱ ስም ሲያጠፋ የሚውል መዓት ነው። መዓት ፕሮፖጋንዳ ነው ያለው። ኦሮሚያ ኢንቨስተር እያፈናቀለ ነው፤ ኦሮሚያ ኢንቨስተርን እያሳደደ ነው፤ መዓት ነው ፊንፊኔ ውስጥኮ የሚወራው። ከሚዲያ በላይ ነው በነዚህ ቦታዎች ላይ የሚወሩት ስንቱን እያስበረገጉ፤ እያስደነገጡ የሚውሉት። ኢንቨስትመንትን ስንመራ እንዲሁ ዝም ብለን በጨቅላ አእምሮ የምንመራ ሰዎች ስብስቦች አይደለንም። ገብቶን በእውቀትና በእውቀት የምንመራ ሰዎች ነን።

 

የፌዴራሊዝም የስልጣን ክፍፍል ማሳያ

አንዳንዴ የሚያስቁ ነገሮች ናቸው ያሉት።

.

የሚገርማችሁ እንዲሁ  ላምጣና፤...  አንዳንድ ጊዜ እንዲህ የሚል ደብዳቤ  በግልባጭ ይደርሰኛል። ለሰነድ ለታሪክ አስቀምጠናል።

...አንድ የተጨማለቀ እንዲህ እንዲያ የሚባል ኦሮሚያ መዋቅር እንዲህ እያስቸገረ ሰለሆነ ክቡርነትዎ ባስቸኳይ መመሪያ ሰጥተው እንዲያስተካክሉልኝ።

.

ግልባጭ ለኦሮሚያ ክልል ፕሬዝዳንት።

.

.

.

በግልባጭ ነው እኔ የማውቀው? ማነው ሚኒስትሩ? የስራ ድርሻ አለን ሁላችንም። የምንወስንባቸውን፣ ልንወስንባቸው የማንችላቸው ስልጣኖች አሉን። የተገደበ ስልጣን ነው ያለን። ማናችንም እንደፈለገን ልንጋልብበት የምንችልበት ሜዳ የለም። ኃላፊነቱን ከወሰድኩ በሚመለከተኝ ጉዳይ ላይ እኔና እኔ ነኝ የምወስነው። በግልባጭ አልወስንም። ወደ መዝገብ ቤትም አልመራም። ቀድጄ ነው መጣያ ውስጥ የምጥለው። ለምን መዝገብ ቤት እናጣብባለን። ይሄ ችግር አለ። ጎድ ፋዘርስ/ንስሃ አባቶች/ ሲስተም ሲበላሽ፤ ኮራፕትድ ሲሆን እንዲህ ነው የሚያደርገው። ኔትዎርክ ፍለጋ ይሄዳል። ሬሽን መስፈር ይፈልጋል። ተቆራጭ። ተቆራጭ ድሮ ለአባቶቻችን ላሳደጉን ተቆራጭ ይቆርጣል ልጅ ደሞዝ ሲያገኝ። አሁን ብዙ ተቆራጭ የሚፈልግ አለ። ይሄንን ማቆም አለብን፣ ማስተካከል አለብን። ሄዶ ሄዶ እናንተንም ያከስራል። ያው ሳንቲም ካልቆጠራችሁ ትርፍና ኪሳራችሁን ካላያችሁ ያከስራችኋል።

 

 

የኬኒያዎች የሙስና አረዳድ፤ በኢትዮጵያ አይሠራም

ቅድም ስለ ኬንያ ሲያነሱ አንድ ነገር ነው ትዝ ያለኝ። ኬንያውያን ጋር ቁጭ ብለን ስለሙስና (Corruption) ስናወራ፤ ስለኮራፕሽን አልገባችሁም ይሉናል።ጽንሰ ሃሳብ ምንድነው ኮራፕሽን ማለት? ቅድም አትሸነፉም እናንተ ኢትዮጵያውያን እንዳሏችሁ ስለኮራፕሽን አልገባችሁም ይሉናል። ምን ማለት ነው? ኮራፕሽን ማለት ይላሉ እነሱ፤ ሙስና ከመንግስት ገንዘብ ላይ መውሰድ ነው እንጂ ሌላው ኮራፕሽን አይደለም። አንድ ባለሃብት እኔ ውሳኔ ወይም አገልግሎት ሰጪ ሆኜ አንድ ባለሃብት እኔጋ መጥቶ ያን ጉዳይ ለመጨረስ ሶስት አራት ቀን የሚፈጅበትን እኔ ዛሬውኑ በግማሽ ቀን ብሰራለትና አመሰግናለሁ ቢለኝ ምን ችግር አለው? አመሰግናለሁ ብሎ የሆነ ነገር ቢያስጨብጠኝ’ኮ አመሰግናለሁ ማለት ነው። አመሰግናለሁ ብቻ አይደለም እሱ ሃብታም ነው እኔ ደሃ ነኝ በረዥም ጊዜ ውስጥም የሃብቱ ፍሰት ከሃብታም ወደ ደሃ ሲሆን ያመጣጥናል። እሱ ብቻ ሳይሆን ሁለት ሶስት ቀን የሚፈጀውን ስራ በግማሽ ቀን እኔ ብጨርስ የስራ ውጤት ይጨምራል ሁሉም እንዲህ ቢሰራ ይላሉ። በእንዲህ አይነት መልኩ ሌብነትን ሊገልጹ ይፈልጋሉ። ይህ ለኛ አያዋጣንም። ስለዚህ ቢሮ ቁጭ ብሎ እጅህን ሰብስብ ማለት አለብን ሁላችንም። ለመብታችን ደግሞ አንዳንዴ እያስለመድን አስቸጋሪ ነው። የለመደ አመል ከባድ ነው፣ አስቸጋሪ ነው። ዛሬ ስትሉት ነገም ያያችኋል አይተውም። ትናንት እንትን ብሎኛል ብሎ አይተውም። ሄዶ ሄዶ ሁላችንም ይጎዳናል። ሄዶ ሄዶ የግፊትና የስኳር በሽተኛ ነው የሚያደርጋችሁ የባንክ ብድር ብቻ አይደለም። ስለዚህ ይሄ የሁላችን ትግል የሚያስፈልገው ነቀርሳ ነው።

 

ለአዲስ ታሪክ እንነሳ!!

የኋላውን ጥሩም ይሁን መጥፎ ለታሪክ እንተወው። ዛሬ ያለን ትውልድ የራሳችንን አዲስ ታሪክ እንስራ። እኛም የማናፍርበት የነገውም ትውልድ እኛ የሰራነውን እንደ ጥሩ ተምሳሌት ወስዶ የሚሰራውን የሚያስቀጥለውን የራሳችንን ታሪክ እንስራ። የሚጠቅመን ይሄ ነው። በየመንደሩ መናቆሩ፤ ታሪክ ወደኋላ እየቆጠሩ አንዳንዱ የተፈበረከ፤ እውነት ይሁን ውሸት ይሁን እውነት ባላየነው ባልጨበጥበነው ማረጋገጫ መናቆሩ አይጠቅመንም። ይበትነናል። ይጎዳናል። ነቀርሳ ነው። አያስፈልግም። ስለዚህ ከምንም በላይ ለትውልድ ጥለን የምናልፈው በተለይ ደግሞ አንድ ለኛ ለልጆቻችን ዋስትና የሆነች ሀገራችንን፤ አንድ ሆና ተጠናክራ የምትወጣበትን ለዚህ አስበን ነው መስራት ያለብን። ይሄ በጣም ያስፈልገናል። ከኢንቨስትምንትም በላይ ነው ይሄ። ዋስትናችን የኛም የልጅ ልጆቻችን ዋስትና ይሄ ነው። ይቅርና በየመንደሩ ተከፋፍለን አንድም ሆነን ዳገቱን ልንገፋው አልቻልንም። ዓለም ወዶ አይደለም ወደ አንድ መንደር ሳይፈላለግም መፈላለግ የጀመረው። ሳይፈላለግም መተቃቀፍን የመረጠው ወዶ አይደለም። ያ ሊታየን ካልቻል፤ ያ ካልተገለጠልን በጨለማ ውስጥ ተጉዘን ልንለወጥ፣ ልናድግ አንችልም። ምን ጊዜም ሁላችንም መርሳት የሌለብን ለዚች ሀገር አንድነት፤ ለሀገራችን ለውጥ፤ በየቤትም እንሰማራ፤ በየትም እንሂድ፣ በየትም እንግባ፣ እንውጣ ለዚህ ሀገር አንድነት ለዚህ ሀገር ለውጥ ማሰብ መስራት መትጋት አለብን።¾

ይምረጡ
(12 ሰዎች መርጠዋል)
822 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 190 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us