የአማራ እና የኦሮሞ የምክክር መድረክ እንደምታዎች

Wednesday, 08 November 2017 18:50“…ካልተባበርን አንድ ካልሆንን ከችግር ባርነት ልንላቀቅ አንችልም”

አቶ ለማ መገርሳ
የኦሮሚያ ክልል መንግሥት ፕሬዝደንት


“በሀገራችን ፖለቲካ ውስጥ የገባውን ነቀርሳ እንታገለው”

አቶ ገዱ አንዳርጋቸው
የአማራ ክልል ፕሬዝደንት

 

ለአጠቃላይ የኢትዮጵያ ሰላም ተደማሪ የሆነ በኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት ፕሬዝደንት በአቶ ለማ መገርሳ የተመራ የልዑካን ቡድን በባሕርዳር ከተማ በመገኘት፣ ከአማራ ክልል የፖለቲካ አመራሮች፣ የሐገር ሽማግሌዎች፣ ታዋቂ ግለሰቦች እና ከተለያዩ የሕብረተሰብ ክፍሎች ከተወጣጡ አካላት ጋር በሁለቱ ሕዝቦች መካከል በተፈጠረው ወቅታዊ ሁኔታ እና ቀጣይ የግንኙነት አቅጣጫዎች ላይ የምክክር ጉባኤ አድርገዋል። የጉባኤው መሪ ቃል “አብሮነታችን ለሰላማችን፣ ሰላማችን ለአብሮነታችን” ነው።


በባህርዳር ከተማ የአማራ ከልል ምክር ቤት አባይ አዳራሽ ውስጥ የተደረገው የኦሮሞ እና የአማራ ህዝቦች የምክክር መድረኩ ይዘት እና ውጤት ወደፊት ብዙ ሥራዎች የሚጠብቁት ቢሆንም በብዙ ልሒቃን የሚነገረውን ትረከት ግን ለመቦርቀስ የቀረበ ይመስላል። ይኸውም፣ አብዛኛው የፖለቲካ ልሂቃን እንደሚያስቀምጡት፣ የአማራ የፖለቲካ ኃይሎችን “የጠቅላይ ፖለቲካ ተጫዎቾች” ናቸው ሲሉ፤ የኦሮሞ የፖለቲካ ኃይሎችን “በኦሮሞ አጀንዳ የተጠለፉ” ናቸው ይላሉ። ይህንን የፖለቲካ ትንተና የተሻገረ ቀጣይነት ያለው ሥራ ከታከለበት ደግሞ፣ አስተሳሰቡን በተጨባጭ ሥራዎች ለመቅበር የባሕር ዳር ጉባኤ የመጀመሪያውን መጨረሻ እርምጃ ተራምዷል።


የኢትዮጵያ አንድነት አብሪ ኮኮብ ሆነው ብቅ ያሉት የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት ፕሬዝደንት አቶ ለማ መገርሳ በጉባኤው እንዲህ ነበር ያሉት፣ “ከኦሮሚያ ወጥተን አማራ ወንድሞቻችን ጋር ስንመጣ ለሽርሽር አይደለም። ወይም ለአንድ ሰሞን ሞቅታ አይደለም። በእውነት ከልብ እንደምታስፈልጉን ስለገባን ነው። ሌሎችም ኢትዮጲያውያኖች ብሔር ብሔረሰቦችም ያስፈልጉናል። የኦሮሞ ህዝብ ሺህ ግዜ ብቻውን ቢወራጭ አዋሽን ሊሻገር አይችልም። አማራም እንዲሁ ሺህ ግዜ ብቻውን ቢወራጭ አባይን ሊሻገር አይችልም። ካልተባበርን አንድ ካልሆንን ከችግር ባርነት ልንላቀቅ አንችልም።”


ልብ ያለው ልብ ይላል እንዲሉ፤ “በእውነት ከልብ እንደምታስፈልጉን ስለገባን ነው።…ካልተባበርን አንድ ካልሆንን ከችግር ባርነት ልንላቀቅ አንችልም።” የዚህች ሀገር እጣፈንታ በመፈላለግ እና በመተባበር ላይ የወደቀ መሆኑ ፕሬዝደንቱ በማያሻማ መንገድ አስቀምጠውታል። የኦሮሞ አጀንዳ ከሌላው ኢትዮጵያዊ ተደማሪ እንጂ ብቻውን መቆም እንደማይችል፤ ለማ መገርሳ አስምረውበታል። አዋሽ እና አባይን ለማሻገር የሚቻለው ሁለቱን ሕዝቦች በሚጠቅም እንዲሁም ሌላውን የኢትዮጵያ ሕዝብ ተጠቃሚ በሚያደርግ የጋራ አጀንዳ መተሳስር ሲቻል ብቻ መሆኑን፣ በገዢው ፓርቲ መስመር ብቅ ያሉት አዲሱ የአንድነት አብሪ ኮኮብ ለማ መገርሳ ለጉባኤው አስረድተዋል።


የአማራ ክልል ፕሬዝደነት አቶ ገዱ አንዳርጋቸው በበኩላቸው አብዛኛው ሰው የሚጠይቀውን ጥያቄ አንስተው ምላሽ አቅርበዋል። አቶ ገዱ ጥያቄ እና ምላሽ አዳምረው እንዲህ ነበር ያሉት፣ “ይሄ መፈናቀል አምና እኛም ክልል ተከስቶ ነበር፤ አሁን ኦሮሚያ ውስጥ የሆነውን ያህል ባይሆንም። “ማነው ያፈናቀላችሁ ህዝቡ ነው?” (ተብሎ በኦሮሚያ ክልል ውስጥ የሚገኙ ሲጠየቁ) የሚሰጡት ምላሽ፤ “ህዝቡማ አዳነን እንጂ ጠበቀን እንጂ ንብረታችንን ሽክፍ አድርጎ ያዘልን እንጂ' ምንም አላደረገንም ነው፤ የተባለው። እኔ በዚህ ጉዳይ ላይ በሀገራችን እንዲህ ህዝብን በማፈናቀል ግለሰብ ተጠያቂ ማድረግ ቡድን ተጠያቂ ማድረግ አንዱ አንዱን ሲካሰስ ቢውል የሚያመጣው ጥቅም የለም። እንዲህ እያደረገን ያለው በሀገራችን ፖለቲካ ውስጥ የገባ ህዝብን የሚከፋፍል ነቀርሳ የሆነ አስተሳሰብ ስላለ እርሱን ብንታገለው ነው ውጤት የምናመጣው።”


አቶ ገዱ የኦሮሞ ሕዝብ ከደረሰው መፈናቀልም ሆነ ሌላ እርምጃ እጅ እንደሌለበት በግልጽ አስቀምጠዋል። በሁለቱ ሕዝቦች መካከል ልዩነትን እንዲፈጠር የሰረገ “ህዝብን የሚከፋፍል ነቀርሳ የሆነ አስተሳሰብ” አለ ብለዋል። ይህንን መሰል የአቶ ገዱ አቀራረብ ፋይዳው በሕዝቦቹ መካከል የመተማመን የመደጋገፍ አብሮነት መኖሩን የሚያሳ ነው። የመከፋፈል ነቀርሳ የሆነው አስተሳሰብ ከሕዝቡ ጋር ቁርኝት እንደሌለው አስፍረዋል። ቀጣዩ ሥራ የከፋፋይ አስተሳሰብ ነቀርሳ ተሸካሚውን ማፈላለግ ይሆናል።


አቶ ገዱ ጠቆም ያደረጉት ሃሳብም አላቸው። ይኸውም፣ “ከሁሉም በላይ የሚገርመው የኦሮሞና የአማራ ህዝብን ግንኙነት የሚያሻክሩ ቅስቀሳዎችና ታሪክን በፕሮፖጋንዳ መሳሪያነት በመጠቀም የሁለቱን ህዝቦች አንድነት ለማዳከም ለአመታት የተሰራ ቢሆንም የሁለቱ ህዝቦች አሁንም ጠንካራ አንድነት ይዘው መቀጠላቸው ነው። ይልቁንም በአሁኑ ወቅት ይህ ግንኙነት በአዲስ መልክ እንዲጎለብት ከፍተኛ ግፊት እየተፈጠረ ነው። በቅርብ ጊዜ የኦሮምያ ወጣቶች በጣና ላይ የታየውን መጤ አረም ለማጥፋት ያደረጉት ዘመቻ መልዕክቱ ከአረም መንቀል ያለፈ ነው። የሁለቱን ህዝቦች የወደፊት አብሮነትና ብሩህ ተስፋ አሻግሮ የሚያሳይ እና እስከ ማዶ የሚያስተጋባ ሚሊዮኖች እየተቀባበሉ የሚዘምሩት ጣና ኬኛ፡ አባይ ኬኛ፡ ኦሮሞ ኬኛ፡ አማራ ኬኛ፡ ኢትዮጵያ ኬኛ የሚል የአንድነት ድምጽ ነው።”


አቶ ገዱ አያይዘውም፣ “ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ የኢትዮጵያን አንድነትና መጠናከር የማይፈልጉ ሃይሎች በማህበራዊ ሚዲያ ሳይቀር ጎላ ባለ ደረጃ ሁለቱን ህዝቦች ለማጋጨት ሆን ተብሎ፣ ሌት ተቀን በሚቀነባበር ሴራና የጥፋት ዘመቻ ያላሰለሱ ጥረቶች እየተደረጉ ቢሆንም በአስተዋዩ እና ሰላም ወዳዱ በአገራችን ህዝቦች እንቢተኝነት የእለት ተእለት ትንኮሳዎቻቸው እየመከኑ ናቸው። በቀጣይነትም ቢሆን ይኸው ህዝባዊ አርቆ አሳቢነት፣ ጠላትን አጋልጦ ራቆቱን የማስቀረት አኩሪ ተግባር ተጠናክሮ እንደሚቀጥል እምነቴ ነው።” ብለዋል።


አቶ ለማ መገርሳ ከትልቋ ኢትዮጵያ ታሪክ ተነስተው ለጉባኤው ጥያቄ አቅርበዋል፣ “ሕይወትን ብቻ አይደለም፣ ሞትንም የተጋራን ህዝቦች ነን። አድዋ ላይ ሞትን ተጋርተናል፤ አፅማችን አንድ ላይ ተቀብሯል። ሶማሊያ ሲወረን ደማችን አንድ ላይ ፈሷል። ተቀጥረን አይደለም፤ተከፍሎን አይደለም፤ ደማችንን ያፈሰስነው፤ ለዚህች ሀገር ሉአላዊነት ለዚህች ሀገር ክብር ሲባል ነው። ይህንን ለምንድን ነው በዋዛ የምንሸረሽረው? ሲበላሽ፣ ሲጠፋ፣ ሲናድ ዝም ብለን የምናየው? ይሄ ሄዶ ሄዶ ማናችንን ነው የሚጠቅመው? ይሄ ሁላችንም ልናስብበት የሚገባ ጉዳይ ነው።”


አቶ ገዱም የአቶ ለማን ሃሳብ አጠናክረውታል። እንዲህም አሉ አቶ ገዱ፤ “ኢትዮጵያዊነት የራሱና የጋራው በሆኑ ባህሎች፣ ወጎች፣ ሃይማኖቶች፣ ቋንቋዎች፣ ትውፊቶችና ጠንካራ የአብሮነት እሴቶች ጥምረት ድርና ማግ ሆኖ የተሠራ የከበረ ማንነት ነው። ይህ ለዘመናት በአንድ የተገመደ አብሮነት እና ውህደት ታይቶ እንደሚጠፋ እንፋሎት በንፋስ ተወዛውዞ የሚወድቅ ወይም የሚሰበር ሳይሆን ይበልጥ ሥር እየሰደደ፣ እየጠበቀና እየጠለቀ የሚሄድ ታላቅ ኃይል ያለው ማንነት ነው። ታሪኩን ጠብቀውና አዳብረው ያቆዩን አባቶቻችንም ቢሆኑ ምንም አይነት የማንነት ልዩነት ሳይገድባቸውና ሳያደናቅፋቸው የሁላችን የሆነችውን ውብ ኢትዮጵያን በደምና ባጥንታቸው መስዋእትነት ጭምር አጥር ሆነው ከጠላት ወረራ በመጠበቅ ከልዩነት ይልቅ አብሮ የመቆም፣ አብሮ የማሸነፍ፣ አብሮ የመድመቅ፣ አብሮ የማደግና የመለወጥ ታሪኩንም ሁሉ ጠቅለው ለሁላችንም አስረክበውናል።”


አቶ ገዱ በኦሮማ እና በአማራ ሕዝቦች መካከል ያለውን ግንኙነትንም በአሳማኝ መገለጫዎች አስቀምጠዋል። ይኸውም፣ “የአማራ እና የኦሮሞ ህዝብ በባህል፣ በወግና በአኗኗር በእጅጉ ከመተሳሰራቸው በላይ በበርካታ አካባቢዎች በጋብቻ፣ በጉዲፈቻና በጡት መጣበት ጭምር ተዋህደው እየኖሩ ያሉ አንድ ህዝብ ናቸው። አሁን በዚህ ሰዓት ያለውን እውነታ እንኳን ለአብነት ብናነሳ የአማራ ክልል ህዝቦች በመላው ኢትዮጵያ በስፋት ተሠራጭተው የሚኖሩ መሆኑ እንዳለ ሆኖ ከቁጥር አኳያ ብንወስደው የአማራው ተወላጅ ከአማራ ክልል ቀጥሎ በብዛት እየኖረ ያለው በኦሮሚያ ክልል ውስጥ ነው። ይህ በሚሊዮኖች የሚቆጠር የአማራህ ዝብ በኦሮሚያ ክልል ከኦሮሞ ወንድሞቹና እህቶቹ ጋር ተዋልዶ፣ ተዛምዶ እና ተዋዶ ለዘመናት ኖሯል። ይህ ህዝብ በኦሮሞ ህዝቦች መካካል ማንነቱ ታውቆና ተከብሮ ይኖራል። በዚህ መሃል ልብ ልንል የሚገባው ከላይ በገለጽናቸው ምክንያቶች ግፊት አልፎ አልፎ ግጨቶች ሲከሰቱና አዝማሚያዎች ሲደፈርሱ የኦሮሞ ህዝብ አጥፊውን ሲኮንንና ለህግ ሲያቀርብ፣ የአማራ ወገኑን ህይወትና ንብረት ከጥፋት ሲያድንና ራሱንም ጭምር ለወገኑ አሳልፎ ሲሠጥ፣ የተጎዳውን ደግሞ ባለው ሁሉ ሲደግፈና ሲያረጋጋ ፣ መልሶም ሲያቋቁም አያሌ ጊዜያት አይተናል። በዚህም የኦሮሞ ህዝብ አንዳንዶች እንደሚሉት አግላይ ሳይሆን ሁሉንም አቃፊ የሆነ የተከበረ ባህል ባለቤት መሆኑን እያስመሰከረ ይገኛል። በሌላ በኩል ደግሞ በአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ውስጥ ግማሽ ሚሊየን የሚጠጋ የኦሮሞ ህዝብ ከአማራ ህዝብ ጋር ተሳስሮ በወንድማማችንት እየኖረ ይገኛል።” ብለዋል።


አቶ ገዱ የጉባኤውን ተሞክሮ ወደሌሎች ክልል በመውሰድ ሥራዎች መሰራት እንዳለባቸው ሲያስቀምጡ፣ “ዛሬ እዚህ አዳራሽ የተገኘነው አመራሮች፣ አባገዳዎች፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ ምሁራን እና ወጣቶች እንዲሁም መላው የአማራ እና የኦሮሞ ህዝቦች ዋናው ተልዕኮአችን ይህን ታላቅ ቁምነገር ለትውልዱ ሁሉ ማስተላለፍ ነው። እኛ ኦሮሞ እና የአማራ ህዝቦች በዚህ መድረክ የምናካሄደው ምክክር አንድነትና ትስስራችንን የሚያሳይ ከመሆኑ በላይ ለሌሎች የሀገራችን ወንድም ህዝቦችም የሚያስተላልፈው መልእክት የጐላ ከመሆኑም በላይ ከመላው የሀገራችን ህዝቦች በተለይም ከአጐራባች ክልሎቻችን ህዝቦች ጋር ያለንን ጠንካራ ትስስር ይበልጥ የምናጠናክርበትና ተሞክሮውን የምናስፋፋበት አጋጣሚም ነው።ይህን መሠሉን የህዝብ ለህዝብ ትስስር በማጠናከር በብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች እኩልነት ላይ የተመሰረተችውን አዲሲቷን ኢትዮጵያ በፅኑ መሠረት ላይ የመገንባት ሃላፊነታችንን አጠናክረን ለመሄድ ቆርጠን የተነሳን መሆኑንም ማረጋገጥ እፈልጋለሁ።” ብለዋል።


የኦሮሚያ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ለማ መገርሳ የጉባኤውን አጠቃላይ መንፈስ ሲገልጹት፤ “ኢትዮጵያዊነት ምን እንደሆነ ዛሬ ባየነው ትዕይንት ትርጉሙ ገብቶኛል። ኢትዮጵያዊነት ልዩ ነው። አትዮጵያዊነት ሱስ ነው። ከደም አልፎ ልቡ ውስጥ እንዳለ ዛሬ አይተነዋል። ማንኛውም ኢትዮጵያዊ የትም ይሁን የት፣ ምን ያህል የኢትዮጵያዊነት ርሀብ እንዳለበት በመላው ዓለም የሚገኙ ሁሉ መምጣታችንን ሲሰሙ ምን ያህል በውስጣቸው እንዳደረ አይተናል። ችግሮቻችንን በጋራ እየፈታን ለእድገታችን የምንሰራበት ጊዜም ነው። ለዚች ሀገር ህይወቱን አሳልፎ የሰጠው ይህ ህዝብ ለሀገሩ ፣ለአንድነቱ ነው። ትናንት በተለያዩ አውደ ውጊያዎች ደሙን የገበረው ለኢትዮጵያ ነው። ለሀገራችን አሁንም መስራት ይጠበቅብናል። ወደ ኋላ እያየን ወደፊት ልንጓዝ አንችልም። ያለፈውን እንርሳው ።ለሀገራችን አንድነት በጋራ እንቁም ሲሉ” ጥሪያቸውን አቅርበዋል።


በመጨረሻም አቶ ለማ “ለኢትዮጵያችን ሁሉም ብሄሮች ብሄረሰቦች እና ህዝቦች ያስፈልጓታል። ፍቅር ያሸንፋል። ብሄሮች በጋራ ሊቆሙላት ይገባል። የምስራቅ አፍሪካ ቀጠና ላይ ነው ያለነው። በጎረቤቶቻችን ላይ ያለውን መመልከት ያስፈልጋል። ለምናደርጋቸው ነገሮች ኃላፊነት ሊሰማን ይገባል።” ካሉ በኋላ ለወላጆች ምርክ ለግሰዋል፣ “ትውልዱን ለመቅረጽ ደግሞ ቅድሚያ የሚወስደው ቤተሰብ ነው። በመቀጠልም ማህበረሰብ፤ ስለሆነም ለስነ-ምግባር ጉዳይ ቅድሚያ ልንሰጥ ይገባል። አባቶች፣ አባ ገዳዎች፣ የሀገር ሽማግሌዎችና የሀይማኖት አባቶች ስነ-ምግባርን በተመለከተ ትኩረት ልትሰጡት ይገባል” ሲሉ አሳስበዋል።


የጥናት ወረቀቶች ምክረ ሃሳቦች


ለጉባኤው የቀረቡ የጥናት ወረቀቶች በረዳት ፕሮፌሰር ዶክተር ብርሀኑ ለሜሶ እና በረዳት ፕሮፊሰር አበባው አያሌው ቀርበዋል።


የታሪክ ምሁር በሆኑት በረዳት ፕሮፌሰር ዶክተር ብርሀኑ ለሜሶ “‹የአማራና የኦሮሞ ህዝቦች ትስስርና በኢትዮጵያ ግንባታ ያላቸው ሚና” የተነሱ ጭብጡም በሚከተሉት ናቸው፤ የኢትዮጵያ ታሪክ ሲነሳ የኦሮሞው ታሪክ የመገንጠል ሆኖ በውሸት ተቀርጿል። ኦሮሞ መገለጫው አብሮነት እና አንድነት ነው። ሞጋሳ እና ጉድፊቻ ለዚህ ማሳያ ናቸው። አማራውም አንድነት ወዳጅ ህዝብ ነው። ስለዚህ ተመሳሳይ ስነ ልቦና አላቸው። ስለዚህ የሁለቱ አንድነት ለኢትዮጵያ ትንሳኤ ልዮ ምዕራፍ ይከፍታል ብለዋል።


አያይዘውም ዶክተር ብርሃኑ ለሜሶ፣ የሁለቱን ህዝቦች አንድነት ለማጠናከር በመሰረተ ልማት ማገናኘት የሁለቱም የጋራ ታሪካቸውን ማጥናት የሁለቱን ህዝቦች ባህላዊ ፣ማህበራዊ ግንኙነታቸውን የሚያጠናክር ፌስቲባል ማዘጋጀት፤ የሁለቱን ህዝቦች ሊሂቃን በማገናኘት ማወያየት ይገባል በማለት ምልከታቸውን አቅርበዋል።


በረዳት ፕሮፊሰር አበባው አያሌው የቀረበ ጥናት የአማራ እና የኦሮሞ የታሪክ ክፍተቶች እና ወደፊት አቅጣጫዎች ... የኦሮሞ የአማራ 19ኛው እና 20 ኛው ክፍለ ዘመን በትክክል አለመፃፉ በታሪክ ላይ የፈጠረው ክፍተት የአማራው ገዥ መደብ እና የአማራውን ህዝብ አንድ ማድረግ፣እንደጨቋኝ መቁጠር የህዝቡን መስተጋብር መሰረት ያላደረገ የልሂቃን ፖለቲካም የሁለቱን ህዝቦች አንድነት ሸርሽሮት ቆይቷል። ያለፈውን መሰረት አድርጎ የብሄር ጭቆና አለ ብሎ ማሰብ የሁለቱን ብሄሮች አንድነት አሳስቷል።


አቶ አበባው የወደፊት አቅጣጫ ብለው ያቀረቡት ምክር ሃሳብ፤ ቋሚ የባህል ልውውጥ ማድረግ፣ በየክልሉ ሚዲያዎች የአማራ እና የኦሮሞ አብሮነትን የሚያጎለብቱ የጋርዮሽ ጊዜ መመደብና የህዝብ ለህዝብ ግንኙነቱን ማጠንከር፤ የቋንቋ ትምህርት በሁለቱም ክልሎች ቢካሄድ። አማርኛን በኦሮሚያ ማጠናከር። በአማራም ኦሮመኛን ማስተማር፤ ጠባብ እና ትምክህተኛ የሚሉ የፖለቲካ ቃላት ቃላት የሁለቱን ህዝቦች ማንነት ላይ የወደቁ መስለዋል። ግለሰባዊ መሆን ነበረባቸው።


በተጨማም አቶ አበባው ያስቀመጡት፣ የሊሂቃን እና የፖለቲከኞች የአንድነት ሚና መጫዎት እና የፖለቲካ ምህዳሩን ማስፋት፤ የመሰረተ ልማት ትስስር መፍጠር፣ የኢኮኖሚ ህብረት በመፍጠር የሁለቱን ህዝቦች አንድነት ማጠናከር ተገቢነት አለው። 

ይምረጡ
(1 ሰው መርጠዋል)
413 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 1009 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us