ሳዑዲ ዓረቢያ በአካባቢና በዓለም አቀፍ ጂኦ ፖለቲካ ፍጥጫ ውስጥ?!

Wednesday, 15 November 2017 13:13

 

በሳምሶን ደሳለኝ

 

የቅዳሜ ጥቅምት 25 ቀን 2010 ዓ.ም. የሳዑዲ ንጉሳዊ አገዛዝ አሥራ አንድ ልዑላን፣ በሥራ ላይ የነበሩ አራት ሚኒስትሮች፣ የቀድሞ ሚኒስትሮች እና ባለሀብቶች “በጸረ-ሙስና ዘመቻ” ሽፋን ጠራርጎ ባለአምስት ኮከብ ሆቴል ውስጥ ለጥያቄ በሚል በቁም እስር ውስጥ ካስቀመጣቸው ሳምንት አልፎታል።


ወጣቱ አልጋ ወራሽ መሐመድ ቢን ሰልማን በሳዑዲ ዓረቢያ በፖለቲካ በንግድ ተፅዕኖ ፈጣሪ የሆኑትን እና በውሃቢዝም አስተምህሮ ከፍተኛ ሊሂቃን የሆኑ መንፈሳዊ ሰዎችን ለቀጣይ የንግስና መንገዱ ላይ እንቅፋት ይሆናሉ ብሎ በመስጋት እየጠረጋቸው ይገኛል። የ32 ዓመቱ አልጋ ወራሽ ልዑል ሰልማን የራሱን የፖለቲካ ምኅዳር ለማጠናከር የወሰደው እርምጃ ምን ያህል ርቀት እንደሚወስደው አሁን ላይ ማንም መገመት አይችልም።


መረጃዎች እንደሚያሳዩት የሳዑዲ ንጉሳዊ ቤተሰቦች ወይም የሳዑድ ቤተሰቦች በቁጥር 15ሺ ይደርሳሉ። አብዛኛው የንጉሳዊ ቤተሰቦቹ ሃብት የሚገኘው 2ሺ በሚሆኑ ግለሰቦች እጅ ነው። ከ15ሺዎቹ የሳዑድ ቤተሰቦች 4ሺ ልዑላን ናቸው። የአልጋ ወራሽ ልዑል ሰልማን የጸረ ሙስና ዘመቻ በከፍተኛ ፍጥነት በመጓዝ አጠቃላይ ታሳሪዎቹን ከሳዑዲ ቤተሰቦች የታሰሩትን ጨምሮ 1ሺ 700 አድርሶታል። ከጸረ-ሙስናው ዘመቻ ጋር በተያያዘም የመካከለኛው ምስራቅ ጂዖ-ፖለቲካ በከፍተኛ ፍጥነት እየተለዋወጠ ይገኛል።


የመካከለኛው ምስራቅ ጂዖ-ፖለቲካ በፍጥነት ለመቀያየር ዋና ዋና ምክንያቶችን ከሳዑዲ አንፃር ተይለር ዱርደን ሲዘረዝሩ፤ ያልተጠበቀ እና ከፍተኛ የውስጥ የፖለቲካ ተቀናቃኞችን የማጥፋት እርምጃ መወሰዱ፣ ትልቅ ውስጣዊ የፖሊሲ እና የስትራቴጂ ለውጥ መደረጉ፣ ከአሜሪካ በፖለቲካ በፋይናንስ እና በሚሊተሪ ጥገኛ ከመሆን መሸሽ፣ ከቻይና ጋር በጥልቅ ግንኙነት መተሳሰር፣ አስገራሚ በመሆነ መልኩ ከሩሲያ ጋር በኢኮኖሚ እና በሚሊታሪ ግንኙነት መመስረት እና ከእስራኤል ጋር የትብብር እና የወዳጅነት ግንኙነቶች መጠናከር ናቸው።


በተለይ በአሜሪካ ኒክሰን አስተዳደር እና በቀድሞ በሳዑዲ ንጉስ ፋይሰል መካከል ከ41 ዓመታት በፊት በሚስጥራዊ የተደረገውን ስምምነት ብሎምበርግ ወደኋላ መለስ ብሎ ሲገልጸው፣ አሜሪካ ከሳዑዲ ዓረቢያ ነዳጅ ትገዛለች በምላሹ ወታደራዊ እርዳታ እና ወታደራዊ ቁሶች ታቀርባለች፤ ሳዑዲ በበኩሏ ከነዳጅ ሽያጭ የምታገኘውን ቢሊዮን ዶላር ገቢን የአሜሪካን የግምጃ ቤት ሰነድ መግዛት እና ለአሜሪካ ኢኮኖሚ ፈሰስ ታደርጋለች።


በዋሽንግተን የመካከለኛው ምስራቅ የውድሮ ዊልሰን ዓለም ዓቀፍ ማዕከል ተመራማሪ ዴቪድ ኦታዌ በሁለቱ ሀገሮች መካከል ከ41 ዓመት በፊት የተፈረመውን ሚስጥራዊ ስምምነት አስመልክቶ እንደተናገረው፣ የግምጃ ቤት ሰነድ መግዛት ዋናው ስትራቴጂው የሳዑዲ የነዳጅ ገንዘብ ወደ አሜሪካ በምልሰት አዙሪት ውስጥ በመክተት ከአሜሪካ ገበያ እንዳይወጣ ማድረግ ነው ብሎታል። ከሳዑዲ ዓረቢያ የግምጃ ቤት ግዢ የሚገኘው ገንዘብ ለአሜሪካ ጦር መሳሪያ አምራች ኩባንያዎች ለማምረቻነት የሚቀርብ ነው።


ሌላው የሳዑዲ ውስጣዊ የፖለቲካ ጡዘት የሚጀምረው ንጉስ ሳልማን እ.ኤ.አ. በ2015 ወደ ንግስና ሲመጡ ነው። በተለይ ደግሞ ልዑል አልጋ ወራሽ ሰልማን መሐመድ ቢን መሾማቸውን ተከትሎ ነው። ሰልማን የመጀመሪያው ሥራ አድርጐ የወሰነው በየመን የእርስ በእርስ ጦርነት ውስጥ በቀጥታ ተሳታፊ መሆን ነው። ይህም ሲባል፤ ሳዑዲ በሱኒ ተጽዕኖ ይመራ የነበረውን መንግስት ስትደግፍ፤ ኢራን በበኩሏ በመንግስት ላይ ጦር መሳሪያ ያነሱትን የሁዚ አማፂያንን ደግፋ ቆመች። በግልጽ ሳዑዲ እና ኢራን የውክልና ጦርነት ውስጥ ገቡ።


እ.ኤ.አ. በ2017 ሳዑዲ ዓረቢያ ኳታርን አሸባሪዎችን በመደገፍ እና ሰይጣናዊ ሥራዎችን በመፈጸም ድርጊት ከሰሰች። ኳታር በበኩሏ ለዓለም አቀፉ ሕብረተሰብ ሳዑዲ ዓረቢያ በኳታር ንጉሳዊ ቤተሰቦች ላይ የሥርዓት ለውጥ ለማድረግ እየሰራች መሆኗን በመጥቀስ ከሰሰች። ከዚህ ጋር በተያያዘ ባልተጠበቀ ፍጥነት እና አጋጣሚ ኢራን ከኳታር መንግስት ጎን በመቆም የሳዑዲን እንቅስቃሴ ለመቀልበስ ተሰለፈች። ይህም በመሆኑ ሳዑዲና ኢራን በአዲስ መልኩ ወደ ውክልና ጦርነት ውስጥ ገቡ።


እንዲሁም በሶሪያ ምድር ለአምስት አመት በተደረገው ጦርነት ኢራን የበሽር አላሳድ መንግስትን ወግና ስትቆም፤ ሳዑዲ አረቢያ በበኩሏ የአል-አሳድን መንግስት ከሚቀናቀኑ ሃይሎች ጋር አበረች። በተያያዘም የሶሪያ ሕጋዊ መንግስት የሆነውን የበሽር አላሳድ መንግስትን ሩሲያ በቀረበላት ጥሪ መሰረት ድጋፍ ማድረጓን ተከትሎ፤ የበሽር አላሳድ መንግስት ከመወድቅ ተረፈ። ሶሪያም እንደመንግስት ከመንግስታዊ ውደቀት ተረፈች። ኢራንም በገባችው የውክልና ጦርነት በሳዑዲ አረቢያ ላይ ድል ተቀዳጀች። ከፍተኛው እገዛ የሩሲያ ቢሆንም።


ሳዑዲ አረቢያ ከላይ በተዘረዘሩት ዓለም አቀፍና አካባቢያዊ ሁኔታዎች መነሻ ውጥረትና ውድቀት ላይ እየተገኘች፣ ቅዳሜ ጥቅምት 25 ቀን 2010 ዓ.ም. ማምሻውን በልዑል አልጋ ወራሽ ሰልማን መሐመድ ቢን የተመራው “የጸረ-ሙስና ዘመቻ” በፖለቲካ በንግድ ተፅዕኖ ፈጣሪ የሆኑትን እና በውሃቢዝም አስተምህሮት ከፍተኛ ሊሂቃን የሆኑ መንፈሳዊ ሰዎችን በቁጥጥር ስር በማዋል ቀድሞ በተፈጠረው ውጥረት ላይ አዲስ ነዳጅ አፈሰሰበት። ከፀረ-ሙስና ዘመቻው አንድ ቀን ቀደም ብሎም በየመን የሚገኙት የሁዚ አማፃያን የባልስቲክ ሚሳኤል ወደ ሳዑዲ ዋና ከተማ ሪያድ አወናጭፈዋል፤ ሆኖም ግን በአሜሪካ እርዳታ ከሽፏል። ሳዑዲ ዓረቢያ በበኩሏ ድርጊቱን ተከትሎ፣ የተተኮሰው ሚሳኤል ኢራን ሰራሽ በመሆኑ ኢራን ጦርነት ከፍታብኛለች ስትል ከሳለች።


 

ከላይ ባስቀመጥናቸው ነጥቦች መነሻ የመካከለኛው ምስራቅ ጂኦ-ፖለቲካን ለመቆጣጠር በሳዑዲ አረቢያ እና በኢራን መካከል እየተደረገ ባለው ትግል፣ በኢራን የበላይነት እየተጓዘ ይመስላል። ምክንያቱም ሳዑዲ አረቢያ በየመን ያዋቀረችው የሱኒ ፖለቲካ ኃይል ጥምረት ከሽፏል፤ ኳታር ባልተጠበቀ መልኩ ወደ ኢራን ሄዳለች፤ ኢራን በኢራቅ ፖለቲካ ከፍተኛ ተፅዕኖ ፈጣሪ ሆናለች። ሳዑዲ አረቢያ ውስጣዊ የፖለቲካ ሽኩቻ ውስጥ በመግባት ያልተረጋጋ መንግስት ባለቤት ስትሆን፣ ኢራን በምርጫ መንግስት መመስረቷን ቀጥላለች።


በዚህ ሒደት ተስፋ የቆረጡት የሳዑዲ ንጉስ እና አልጋ ወራሽ ዓለምን ባደናገጠ መልኩ የሊባኖስ ጠቅላይ ሚኒስትር ሳድ ሃሪሪን አግተው በሪያድ መያዛቸው በስፋት እየተወራ ነው። በጉዳዩ ላይ ሳዑዲ አረቢያ እና ጠቅላይ ሚኒስትር ሳድ ሃሪሪ ማስተባበያ ከመስጠታቸውም በላይ ውንጀላውን ውድቅ አድርገውታል። በአንፃሩ የሊባኖስ ፓርላማ እና ፕሬዝደንቱ ሳድ ሃሪሪ አሁንም ጠቅላይ ሚኒስትራችን ናቸው ሲሉ ገልጸዋል። የሂዝቦላ መሪው ሃሰን ነስረላ በበኩላቸው ሳዑዲ ዓረቢያ ሊባኖስ ላይ ጦርነት አውጃለች ሲሉ ከሰዋል።


የጂኦ-ፖለቲካ ውጥረቶቹ እንደተጠበቁ ሆነው፤ አልጋ ወራሽ ልዑል ቢን ሰልማን የ2030 ዕቅድ አውጥተው ኢኮኖሚውን ማጠናከርና ኢንቨስትመንትን ማስፋፋት፣ በነዳጅ ምርት ላይ ያለውን ጥገኝነት መቀነስ፣ ከሶስተኛ አገሮች የሚኖሩ የንግድ ልውውጦች በነዳጅ ምርት ላይ ከሚያተኩሩ ይልቅ በሌሎች ዘርፎች ለመሰማራት 500 ቢሊዮን ዶላር እያፈላለጉ ይገኛሉ። አንዱ ማስፈጸሚያ መንገዳቸው አድርገው የወሰዱት ለእስር ከዳረጓቸው ሰዎች 800 ቢሊዮን ዶለር የሚገመት ሃብት እንዳይንቀሳቀስ እገዳ መጣል ነው። በነዳጅ ምርት ላይ ተሰማርተው ቱጃር ለሆኑት ባለሀብቶች የአልጋ ወራሹ እቅድ ተቀባይነት ባለማግኘቱ በአፀፋው ለእስር መዳረጋቸው ይነገራል።


ሴቶች መኪና እንዲያሽከረክሩ መፍቀድን ጨምሮ በተለይ ለምዕራቡ ዓለም የቀረቡ አስተምህሮቶችን ወደ ሳዑዲ በመሳብ (Modern Muslim)፣ ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ለማምጣት የሚተጉት ንጉሡና አልጋ ወራሹ እየተሞካሹ፣ እንዲሁም በሳዑዲ ዓረቢያ ዘመናዊነትንና አዲስ ዓይነት ምልከታ የማምጣቱ አካሄዳቸው በወጣቱ ክፍል ድጋፍ አግኝተዋል። ይሁንታን ያስገኘላቸው ቢሆንም፣ በአንፃሩ ግን በወግ አጥባቂዎቹና ለዓመታት ንግዳቸውን እየተቀባበሉ በቆዩት የሳዑድ ቤተሰቦች ዘንድ በቀላሉ ተቀባይነት ለማግኘት ተቸግረዋል።


የብሔራዊ ዘቡንና የባህር ኃይሉን አዛዥ ቀይረዋል። ይህም ከንጉሡ ጀርባ የልዑል አልጋ ወራሹ ጡንቻ አለ አስብሏል። በሳዑዲ የአሲር ግዛት ምክትል ገዢ ልዑል መንሱር ቢን ሙክሪን ከብዙ ባለሥልጣናት ጋር የቅኝት ሥራ ጨርሰው ወደ ሳዑዲ በመመለስ ላይ እያሉ ሔሊኮፕተራቸው በሳዑዲና በየመን ድንበር ተከስክሶ መሞታቸው የሚታወስ ነው። ሔሊኮፕተሩ የተከሰከሰበት ምክንያት አልታወቀም። ከመሬት በተተኮሰ ሚሳኤል መመታቱን የሚገልፁ ሪፖርቶች ወጥተዋል። ይህም አልጋ ወራሹ ሥልጣኑን ለማራዘም የሚያደርገው ጥረት አንድ አካል ተደርጎ ተጠርጥሯል።


በተጨማሪም በሳዑዲው አልጋ ወራሽ መሐመድ ቢን ሰልማን የሚመራው የፀረ ሙስና ኮሚቴ በቁጥጥር ሥር ካዋላቸው መካከል ቢልየነሩ ልዑል አልዋሊድ ቢን ታላል፣ የቀድሞ የገንዘብ ሚኒስትር ኢብራሒም አል አሳፍ፣ የሳዑዲ ባህር ኃይል ኮማንደር አብዱላህ አል ሱልጣን፣ የኤምቢሲ ቴሌቪዥን ኔትወርክ ባለቤት አልዋሊድ አል ኢብራሒም፣ ባለሀብቱ ሼክ መሐመድ ሁሴን ዓሊ አል አሙዲ፣ እንዲሁም የሳዑዲ ኢንቨስትመንት ባለሥልጣን የቀድሞ ገዥ አሚር አል ዳባጋ፣ ቢሊየነሩ ልዑል አዋሊድ ቢን ታላል፣ የብሔራዊ ዘብ ሚኒስትሩ ልዑል ሚተብ ቢን አብዱላህ፣ የኢኮኖሚና ፕላኒንግ ሚኒስትሩ ልዑል አደል ፋኪ፣ የኦሳማ ቢን ላደን ወንድምና የቢን ላደን ግሩፕ ሊቀመንበር ባክር ቢን ላደን በሪያድ ባለ አምስት ኮከብ ሆቴል ሪትዝ ካርልተን በእስር ላይ ይገኛሉ።

 

ቻይና አዲሷ አስፈላጊ ሀገር


በማርች 2012 የቀድሞ የአሜሪካ ፕሬዝደንት ባራክ ኦባማ ሳዑዲን ይጎበኛሉ ተብለው ቢጠበቁም ሳይጎበኙ ቀርተዋል። ይህንን ተከትሎ ከ41 ዓመት በፊት በአሜሪካ እና በሳዑዲ ዓረቢያ መካከል የነበረውን ሚስጥራዊ ግንኙነት በሚጥስ መልኩ ንጉስ ሰልማን በማርች 16 ቀን 2017 ከፍተኛ ቁጥር ያለው ልዑካን በመምረት ወደ ቤጂንግ ተጉዘው ጉብኝት አድርገዋል። ከቻይና መንግስት ጋርም የ60 ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር የንግድ ስምምነት ሰነድ ተፈራርመዋል። በስምምነት ሰነዱ ከታቀፉት መካከል የሳዑዲ አረቢያ ነዳጅ ኩባንያ “Aramco” እና “China North Industries Group Corp (Norinco)” ይገኙበታል። እንዲሁም ይህ ስምምነት ሳዑዲ ኢኮኖሚዋን ከአሜሪካ ጥገኝነት ለማላቀቅ የተደረገ ተደርጎ ተወስዷል።


ንጉስ ሰልማን በቻይና ቆይታቸው፣ ቻይና በመካከለኛው ምስራቅ ፖለቲካ ብዙ ሚና መጫወት እንደምትችል በማንሳት ተሳታፊ እንድትሆን ጋብዘዋል። በዚህም ሳያበቁ እ.ኤ.አ. በኦገስት 2017 አዲስ የ70 ቢሊዮን ዶላር በኢንቨስትመንት፣ በንግድ፣ በኃይል አቅርቦት፣ በፖስታ አገልግሎት በኮሚኒኬሽን እና በሚዲያ ዙሪያ አብረው ለመስራት ስምምነት ፈጽመዋል።


ንጉስ ሰልማን ሩሲያን በጎበኙ ጊዜ ከሩሲያ ፌዴሬሽን ጋር የጦር መሳሪያ ግዢ እና በሃይል አቅርቦት ዙሪያ ከመፈራረማቸውም በላይ S-400 የተባለ ዘመናዊ የአየር መቃወሚያ መሣሪያ ገዝተዋል።


ሳዑዲ አረቢያ በመካከለኛው ምስራቅ የኢራንን ተፅዕኖ ለመቋቋም እየሰራች ሲሆን፤ በሌላ መልኩ ለ41 ዓመት ከአሜሪካ ጋር የነበራትን ሚስጥራዊ ግንኙነት በቻይናና በሩሲያ ለመተካት እየተጋች ነው። በአካባቢው እና በዓለም አቀፉ የጂኦ-ፖለቲካ አጣብቂኝ ውስጥ የገባችው ሳዑዲ አረቢያ ቀጣይ ጉዞዋ ምን ሊሆን እንደሚችል መገመት ከባድ ሆኗል። 

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
251 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 64 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us