ኢዴፓ በውዝግብ ውስጥ

Wednesday, 29 November 2017 12:54

በይርጋ አበበ

የኢትዮጵያ ፖለቲካ መገለጫ ከሆኑት አብይ ክስተቶች መካከል አንዱ የፓርቲዎች ውስጠ ዴሞክራሲ አናሳ መሆን ነው። ሁሉም ፓርቲዎች በሚያስብል መልኩ ውስጣቸው መግባባትና መደማመጥ ያልሰፈነበት በመሆኑ የምርጫ ሰሞን ድምቅ ብለው ታይተው እንደ አደይ አበባ ቶሎ ይጠፋሉ። በዚህ የተነሳም አማራጭ ሃሳብ የሚፈልገው የአገሪቱ ህዝብ በእነሱ ድርጊት ተስፋ የቆረጠ ይመስላል።

ባሳለፍነው ሶስት ሳምንት የቀድሞ አንድነት ለፍትህና ለዴሞክራሲ አመራሮች ከሰማያዊ ፓርቲ ጋር ተቀላቅለው ሰላማዊ ትግሉን እንደሚያስቀጥሉ መዘገባችን ይታወሳል። ዛሬ ደግሞ የኢትዮጵያዊያን ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኢዴፓ) በአመራሮቹ መካከል መከፋፈል እንደተፈጠረ የሚያመለክት ምልክት እየታየ ነው። ፓርቲው ለዝግጅት ክፍላችን በላከው ደብዳቤ የአመራር ለውጥ ማካሄዱን አመልክቷል። ለአለፉት አራት ዓመታት የፓርቲው ፕሬዝዳንት ሆነው የቆዩትን ዶ/ር ጫኔ ከበደን በአቶ አዳነ ታደሰ መተካቱን የፓርቲው መግለጫ አመልክቷል። እዚህ ውሳኔ ለመድረስ ያስገደደው ገፊ እና ሳቢ ምክንያቶች ምንድን ናቸው? የፓርቲው የውስጥ ደንብስ ይህን ይፈቅዳል ወይ? ጠቅላላ ጉባኤ እንዳንጠራ አስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ከለከለን ሲል የነበረው ኢዴፓ አዋጁ ከተነሳ በኋላ ለምን ጠቅላላ ጉባኤውን አልጠራም? የሚሉና ሌሎች ጉዳዮችን በተመለከተ የሚመለከታቸውን አካላት አነጋግረን ከዚህ በታች አቅርበነዋል።

 

የደብዳቤው ይዘትና አንደምታ

“ኢዴፓ በውይይት የሚያምን ፓርቲ ነው። ለዚህም ነው መንግሥት ለድርድር ሲጠራን ያለምንም ቅድመ ሁኔታ በድርድሩ ተሳታፊ የሆነው” ሲል ደብዳቤው ይጀምራል። ይህ ለመገናኛ ብዙሃን “እንዲያውቁትና እንዲያሳውቁት” ተብሎ የተላከው ደብዳቤ ፓርቲው ከድርድሩ መውጣቱን በፓርቲው ብሔራዊ ምክር ቤት የተወሰነ መሆኑን ይገልጻል። አያይዞም ከድርድሩ ለመውጣት ያቀረበው ምክንያት “በድርድሩ ፓርቲው የወከላቸውን ሰው ለመቀየር ብንፈልግ ኢህአዴግ ሊፈቅድልን አልቻለም” ሲል ያስታውቃል።

ኢዴፓ በፓርቲዎች ድርድር ሊቀመንበሩ ዶ/ር ጫኔ ከበደ እና በፓርቲው የህዝብ ግንኙነት ኃላፊው አቶ ወንድወሰን ተሾመ ተወክሏል። ከትናንት በስቲያ ለዝግጅት ክፍላችን ኢዴፓ የላከው ደብዳቤ የሚለውም በድርድሩ አንሳተፍም ሳይሆን የምንሳተፍ ከሆነ ከኢዴፓ ተወክለው በድርድሩ የሚሳተፉ የፓርቲው አባላት በሌላ ይቀየሩ የሚል ነው። ይህን ደግሞ ለድርድሩ ጋባዥ ኢህአዴግም ሆነ ለፖለቲካ ፓርቲዎች ድርድር መድረክ ደጋግሞ በደብዳቤ ማሳወቁን ገልጿል።

 

ኢዴፓ ከድርድሩ ለምን ወጣ?

ፓርቲው ለዝግጅት ክፍላችን በፃፈው ደብዳቤ ከድርድሩ ለመውጣትና በድርድሩ ለመቆየት ያቀረበው ቅድመ ሁኔታ አለ። ኢዴፓ ድርድሩን በተመለከተ የወሰደውን አቋም ሲያስታውቅ “ባለፈው ዓመት ጥር ወር በኢህአዴግ ጋባዥነት በተጀመረው የድርድር መድረክ ላይ ፓርቲያችን ተሳትፎ ማድረግ ጀምሮ ነበር። ሆኖም ፓርቲው በድርድሩ ጠንካራ ተሳትፎ እንዲኖረው በማሰብ በግንቦት 23 ቀን 2009 ዓ.ም፣ በነሐሴ 11 ቀን 2009 ዓ.ም እና በጥቅምት 13 ቀን 2010 ዓ.ም በተፃፉ ደብዳቤዎች በተደጋጋሚ በድርድሩ ተሳታፊ የሆኑ ተወካዮችን መቀየሩን ቢያሳውቅም ተቀባይነት ሳያገኝ ቀርቷል። እኛ በማናውቀው ምክንያት የድርድር መድረኩ ፓርቲው የወከላቸውን ተወካዮች ከመቀበል ይልቅ የፓርቲው ውክልና የሌላቸውን ሰዎች የድርድሩ አካል አድርጎ መቀጠሉን መርጧል። በዚህ ምክንያት በድርድሩ ላይ እየተወሰኑ ያሉ ውሳኔዎች ፓርቲው የማያውቃቸው ሲሆን ከዚህም በኋላ በ13/02/2010 ዓ.ም ፓርቲው በደብዳቤ ያሳወቃቸውን ተወካዮች ተቀብላችሁ ድርድሩ ላይ ተሳትፎ እንድናደርግ ካላደረጋችሁ ኢዴፓ ከዛሬ ህዳር 18 ቀን 2010 ዓ.ም ጀምሮ የድርድሩ አካል እንዳልሆነ እንገልፃለን” ሲል በአቶ አዳነ ታደሰ ፊርማ በወጣ ደብዳቤ ገልጿል።

ኢህአዴግ ከተቃዋሚ ፓርቲዎች ጋር እያካሄድኩ ነው ሲል በሚጠራው ድርድር ላይ ኢዴፓ የተወከለው በሊቀመንበሩ ዶ/ር ጫኔ ከበደ እና በህዝብ ግንኙነት ኃላፊው አቶ ወንድወሰን ተሻለ ሆኖ እያለ ከትናንት በስትያ ለመገናኛ ብዙሃን የተላከው ደብዳቤ ግን የፓርቲው ፕሬዚዳንት አቶ አዳነ ታደሰ መሆናቸውን ያበስራል።

ፓርቲው በድርድሩ ላይ እየተሳተፉ ያሉት ሁለቱ ተደራዳሪዎችና አንዱ አደራዳሪ (የፓርቲው ጥናትና ምርምር ኃላፊው አቶ ዋሲሁን አሰፋ) አይወክሉንም ሲል ለድርድሩ መሪዎች ደብዳቤ የፃፈው ለምንድን ነው? እነማንንስ ነው የወከላችሁት? ስንል ለአቶ አዳነ ታደሰ ጥያቄ አቅርበንላቸው ነበር። አቶ አዳነ ሲመልሱም “በሶስቱ ሰዎች ምትክ የተወከሉት አቶ ኤርሚያስ ጋሻ፣ ወይዘሪት ጽጌ ጥበበ እና እኔ (አቶ አዳነ ታደሰ) ነን። ይህን ያደረግንበት ምክንያት በፓርቲያችን ብሔራዊ ምክር ቤት ውሳኔ መሠረት ነው” ብለዋል።

ከዚህ ጋር በተያያዘ አቶ አዳነ ታደሰን ወደ ፕሬዝዳንትነት የመጡበት መንገድ አግባብነት አለው ወይ? ምርጫ ቦርድስ የሰጣችሁ ምላሽ ምንድን ነው? ለሚለው ጥያቄ አቶ አዳነ ሲመልሱ “የፓርቲያችን መተዳደሪያ ደንብ አንቀጽ 4 ቁጥር 17 ብሔራዊ ምክር ቤት በፈለገው ጊዜ አመራሮቹ ላይ እርምጃ ሊወስድ ይችላል ይላል። ለምርጫ ቦርድም በደብዳቤ አሳውቀናቸው እስካሁን ደብዳቤውን ባይቀበሉም ከዋና ፀሐፊው ጋር ባደረግነው የቃል ውይይት ጥያቄያችንን እንደሚቀበሉን ቃል ገብተውልናል” ብለዋል።

በሌላ በኩል የአቶ አዳነ ታደሰን ምላሽ ተቃውመው አስተያየታቸውን ለሰንደቅ የሰጡና ስማቸው እንዲገለፅ ያልፈለጉ የፓርቲው ሥራ አሥፈፃሚዎች “ድርጊቱ ህግን ያልተከተለ እና ሕገ ወጥ ስለሆነ ተቀባይነት ሊኖረው አይገባም። የተደረገውን ሕገ-ወጥ ስራም ለምርጫ ቦርድ አሳውቀናል። በህግም እየተከታተልነው ነው” ሲሉ ተናግረዋል።

 

 

የፓርቲው ሌላ ገፅታ

25 አባላት ያሉት የኢዴፓ ብሔራዊ ምክር ቤት የፓርቲው መተዳደሪያ ደንብ በተፈቀደለት ሥልጣን መሠረት ሶስት ሥራ አስፈፃሚዎችን ከኃላፊነት ዝቅ አድርጓል ሲሉ አቶ አዳነ ይናገራሉ። ለዚህ ንግግራቸው ያቀረቡት አስረጅ ሃሳብ ደግሞ ፓርቲውን ላለፉት አራት ዓመታት በሊቀመንበርነት የመሩትን ዶ/ር ጫኔ ከበደን ከኃላፊነታቸው በማንሳት አቶ አዳነን በምትካቸው ሾሟል። የጥናትና ምርምር ኃላፊ የነበሩትን አቶ ዋሲሁን አሰፋን ከኃላፊነትና ከሥራ አስፈፃሚነት በማንሳት የጥናትና ምርመር ቦታውን ደግሞ ለዶ/ር ጫኔ ከበደ ሰጥቷል። አቶ ዋሲሁንን ወደ ብሔራዊ ምክር ቤት ዝቅ ብለው እንዲሰሩ ተደርጓል ብለዋል።

ይህን የአቶ አዳነ ምላሽ የማይቀበሉት የፓርቲው አመራሮች ግን የተካሄደውን አሰራር እንደሚቃወሙት ገልጸው ጉዳዩንም በህግ እየተከታተሉት እንደሆነ ተናግረዋል። አሁን በኢዴፓ ውስጥ እየተካሄደ ያለውን አሰራርም ፓርቲውን ችግር ላይ የሚጥል መከፋፈል እንደተፈጠረ የሚናገሩት የሰንደቅ ምንጮች፤ ጠቅላላ ጉባኤ ሳይካሄድ የቆየውም ለዚህ ሲባል ነው ብለዋል። “ጠቅላላ ጉባኤ ቢካሄድ አሁን ያለው የአንጃ ቡድን የሚጠብቀውን ስለሚያውቅ የተለያዩ ሰበቦችን እየፈጠረ ጠቅላላ ጉባኤው እንዳይካሄድ ሲያደርግ ቆይቷል” ሲሉ ለሰንደቅ አስተያየታቸውን የሰጡ የኢዴፓ አመራሮች ተናግረዋል።

“ፓርቲው ውስጥ መከፋፈል ነግሷል። ከዚህ መከፋፈል ጀርባ ደግሞ የቀድሞው ሊቀመንበር አቶ ልደቱ አያሉው አሉ” ሲሉ የሰንደቅ ምንጮች ይገልጻሉ። አቶ አዳነ ታደሰ ግን በዚህ ሃሳብ አይስማሙም። ፓርቲው በተለመደው የተረጋጋ መንገድ እየተጓዘ መሆኑን ገልፀው “ይህን ወሬ የሚያወሩት በብሄራዊ ምክር ቤት ውሳኔ የተከፉ አመራሮች ናቸው” ሲሉ መልሰዋል።

አቶ አዳነ ለመገናኛ ብዙሃን በፊርማቸው የላኩት ደብዳቤ ላይ የፓርቲው ፕሬዝዳንት መሆናቸውን በተዘዋዋሪ የሚገልፅ ቢሆንም ሕትመት እስከገባንበት ትላንት ከሰዓት በኃላ ድረስ ፕሬዚዳንትነታቸው በምርጫ ቦርድ ዕውቅና አላገኘም።  በዚህ ጉዳይ ምርጫ ቦርድ ያለውን አስተያየት እንዲሰጠን ያደረግነው ሙከራ ባይሳካም ከፓርቲው ባገኘነው መረጃ ለማወቅ እንደተቻለው ግን ምርጫ ቦርድ አዲሱን የኢዴፓ ካቢኔ ሹም ሽር ላይ ገና ውሳኔ አላሳረፈም።። ለአንድ ዓመት ከስድስት ወር የተራዘመው የፓርቲው ጠቅላላ ጉባኤ የፊታችን የካቲት 27 ቀን እንደሚካሄድ አቶ አዳነ ተናግረዋል። አቶ አዳነ አያይዘውም ለረዥም ጊዜ ጉባኤ ሳይካሄድ የቆየው እንደሚባለው በውስጣችን ችግር ስላለ ሳይሆን በአገሪቱ ተጥሎ የቆየው አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እንዳንሰበሰብ እና መግለጫ እንዳንሰጥ ስለከለከለን ነው። አሁን ግን የጠቅላላ ጉባኤ አመቻች ኮሚቴ ተዋቅሮ ለጉባኤው ዝግጅት እያደረግን ነው” ብለዋል።

 

 

ማስተካከያ

 

13ኛ ዓመት ቁጥር 637 በወጣው ሰንደቅ ጋዜጣ ከሜጀር ጄኔራል አበበ ተክለሃይማኖት ጋር ባደረግነው ቃለ ምልልስ “ከአየር ኃይል አዛዥነታቸውና ከህወሓት/ኢህአዴግ አባልነታቸው ራሳቸውን ካገለሉ…” የሚለው፤ “በጡረታ እንዲያገሉ ከተደረጉ በኋላ” በሚል ይታረም።

“ኢህአዴግ ስልጣን መልቀቅ የነበረበት በ1987 ዓ.ም ነበር” የሚለው “ከ1987 ዓ.ም በኋላ ወጣቱና የተማረው ኃይል ስልጣኑን እንዲረከብ ሁኔታዎችን ማመቻቸት ነበረበት” በሚል ይስተካከል።

ለተፈጠረው ስህተት አንባቢያንን እና ሜጀር ጄኔራል አበበ ተክለሃይማኖትን ይቅርታ እንጠይቃለን።¾

   

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
297 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 62 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us