ላለመነካካት ተማምሎ የነበረው የህወሓት አመራር፤ መነካካቱ የተለያዩ ስሜቶችን እያስተናገደ ነው

Wednesday, 29 November 2017 13:01

ሕዳር 18 ቀን 2010 ዓ.ም. በትግራይ በመቀሌ ከተማ የህወሃት ማዕከላዊ ኮሚቴ በከፍተኛ አመራሮቹ ላይ ከደረጃ የማንሳት እና የእገዳ ውሳኔ ማስተላለፉን ድርጅቱ አስታውቋል።

 በማዕከላዊ ኮሚቴው ግምገማ መሰረትም፣ አቶ አባይ ወልዱን ከድርጅቱ ሊቀ መንበርነት አንስቶ፤ ከስራ አስፈጻሚነት ወደ ማዕከላዊ ኮሚቴ አባልነት ዝቅ አድርጓል።  አቶ በየነ ምክሩን ደግሞ፣ ከስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ወደ ማዕከላዊ ኮሚቴ አባልነት ደረጃ አውርዷል።

በፖለቲካው ባለድርሻ አካላት የተለየ ትኩረት የሳበው ደግሞ፣ የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ባለቤት ወይዘሮ አዜብ መስፍን ከስራ አስፈጻሚ እና ከማዕከላዊ ኮሚቴ አባልነት እንዲታገዱ ማዕከላዊ ኮሚቴው ውሳኔ አስተላልፏል።

መግለጫው ሁለት የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላት፣ ማስጠንቀቂያ ሰጥቷል። የማዕከላዊ ኮሚቴው ግምገማውና የሂስ ግለሂስ መድረኩ እንደቀጠለ መሆኑን ከሥፍራው የሚወጡ ዘገባዎች እያመላከቱ ነው።

የህወሓት ማዕከላዊ ኮሚቴ የተራዘመ የግምገማ ሒደት ያልተጠበቁ የሚመስሉ የተጠበቁ ርምጃዎችን ማሳለፉ በተለያዩ ወገኖች እና በባለድርሻ አካለት የተለያዩ ስሜቶችን እና አረዳዶችን ፈጥሯል። የስብሰባው አጠቃላይ መንፈስ በፋና ብሮድካስቲንግ ድርጅት በሸራተን አዲስ በተደረገው የፖለቲካ ምክክር መድረክ ላይ፣ “የመንግስት ስልጣን”፣ “የፓርቲ ስልጣን”፣ “የአዲሱና የነባሩ አመራር ተሳትፎ” የሚሉት በብዙ ገጽ በሚተነተኑ ሐረጎች በህወሓት ማዕከላዊ ኮሚቴ ስብሰባ ተያይዘው የተንጸባረቁ መስለዋል።

በሌሎች አረዳድ ደግሞ፣ ጠጋኝነት (reformism)፣ ከላሽነት (revisionism) እና ቀያጭነት (Eclecticism) አመለካከቶች፣ የማዕከላዊ ኮሚቴው የግምገማ ማዕከል መሆናቸውን አስቀምጠዋል።

ጠጋኝነት (reformism) ህወሓት የጀመረውን የጥገናዊ ለውጥን ውጤት እንደመጨረሻ ግባቸው አድርገው በመውሰድ ሳይሆን፣ ጥገናው በሚፈጥረው አመች ሁኔታ በመጠቀም ድርጅቱን ከሥር መሰረቱ በመለወጥ፤ የሀገራዊ ለውጥ ተደማሪ ሐይል ለማድረግ የሚንቀሳቀሱ፤

ከላሾቹ (revisionism)፣ ህወሓት ከግንባር ድርጅቶች ጋር የታጠቀውን የዴሞክራቲክ ልማታዊ መንግስት ርዕዮተዓለም እና የገበያ ሥርዓት አስተሳሰቡን፤ ከተጨባጭ ሁኔታዎች ጋር ማጣጣም ማዳበር ያስፈልጋል፣ በሚሉ ሃይሎች የንድፈ ሃሳባዊ መሰረቱንና የኢኮኖሚ ንድፈ ሐሳቡን ከድርጅቱ በመንጠቅና በአዲስ አክራሪ የገበያ ሥርዓት ለመተካት የተሰለፉ ኃይሎች፤

እንዲሁም ቀያጮቹ (Eclecticism)፤ አንድን ፖለቲካዊ ወይም ኢኮኖሚያዊ ክስተትን፣ በአንድ በተወሰነ ጊዜ ከአካባቢው ጋር ያለውን መሠረታዊ ግንኙነት ፈጥኖ መለየት ማጤንና ያዳገተው ኃይል፣ በአንድ ታሪካዊ ወቅት ለሚከሰቱ ችግሮች ተገቢ መፍትሔዎችን ለማግኘት የተሳነው ኃይል የአልሞት ባይ ተጋዳይነቱን ያሳየበት መድረክ መሆኑን አስፍረዋል።

ከማዕከላዊ ኮሚቴው ግምገማ ጋር በተያያዘ፣ በትግራይ ክልል ከሚሰሩ ጋዜጠኞችና ፖለቲከኞች ጋር ያደረግነውን ቆይታ በዚህ መልኩ የርምጃውን አግባብነት እንዲሁም በድርጅቱ ችግሮች የፕሮግራም ወይስ የአመራር ችግሮች ናቸው የሚሉትን ለማየት ሞክረናል። ከተጠያቂዎቹ ሁለቱ ሥማቸው እንዲጠቀስ አልፈለጉም። ሌሎቹን በስማቸው አቅርበናል።

ሥማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ በትግራይ ክልል የሚሰሩ የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያ ከግምገማው ጋር በተያያዘ፣ “የህወሓት የራሱን የማየት ልምድ አለው የሚል ዕሳቤ ነበር የነበረኝ፤ በተግባር አሳይተውናል። ድርጅቱ በርካታ ችግሮች አሉብኝ ሲል ነበር በመሆኑ አሁን ወደ እርምጃ መግባቱ ተገቢነቱ ከፍ ያለ ነው። ጅምር በመሆኑ አጠቃላይ አስተያየትም ግንዛቤም ሊሰጥበት በሚችል ደረጃ ግን ላይ አይደለም። ሆኖም፣ በሕዝቡ ውስጥ የነበረውን አመለካከት እናውቀዋለን። ለወጣቱ የሥራ ዕድሎች መፍጠር አለመቻል፣ ኪራይ ሰብሳቢነትን መዋጋትና ፀረ-ዴሞክራሲያዊ አካሄዶች ፋፍተው መገኘታው እና የመሳሰሉትን ድርጅቱ ሊዋጋቸው ይችላል ወይስ አይችልም የሚሉ ጥያቄዎች ሲቀርቡ ነበር። በድርጅቱ ሰነዶችም ብዙ ችግሮች ተነቅሰው፣ ተለቅመው ተቀምጠዋል። በዚሁ መሰረት እርምጃ ተወስዷል። እየሰማን ያለው አሳዛኝ ነገር አሁን ተወሰደ የተባለው እርምጃ በቡድን የተሰራ አይደለም። ታቧድነዋል ከሚባሉት በላይ ሕዝቡ ብዙ ችግሮቹን ያውቃቸዋል። ሕዝቡን ማዕከል ያደረጉ ውሳኔዎች ናቸው እንጂ በተወሰነ ቡድን ተወስዷል የሚባል እርምጃ አይደለም። በኔትዎርክ የተወሰደ እርምጃ ሳይሆን፣ ይብዛም ይነስ የህዝቡን የለውጥ ስሜት ያገናዘበ ነው” ብለዋል።

“የህወሓት ችግር የአመራር ነው ወይንስ የፕሮግራም ችግር ነው” ተብሎ ለቀረበላቸው ጥያቄ የሰጡት ምላሽ፣ “የአንድ ሕዝብ ኢኮኖሚያዊና ማሕበራዊ ለውጦችን ለማምጣት ፕሮግራም መገምገም ያስፈልጋል። ስምምነት በተሰጠው ፕሮግራም ግን መመዘኛው አገልግሎት ለመስጠት በተቀመጡ መለኪያዎች ነው የሚመዘነው። ድርጅቱ የፕሮግራም ችግር አለበት የሚል መደምደሚያ የለኝም። ቢያንስ ግን የተቀመጠውን ፕሮግራም አመራር በመስጠት ማስፈጸም የሚችሉ አመራሮች አለመኖራቸው አከራካሪ አይደለም። ስለዚህም አመራሩን መፈተሽና ማስተካከያ መውሰድ ስጠብቀው የነበረ ነው።”

አቶ አስራት አብረሃም ፖለቲከኛና ፀሀፊ ግምገማውን አስመልክተው እንደገለጹት፣ “አዲስ አበባ ላይ ያለው የህወሓት ቡድን የበላይነቱን እንደያዘ ነው የምረዳው። አዲስ የተለወጠ ነገር የለም። ከዚህ በፊት ተሸናፊ የነበረው ቡድን አሸንፎ መውጣት ችሏል።  ይህ መሆኑ ደግሞ በፌደራል መንግስት ላይ ህወሓት ጠንክሮ ለመውጣት መፈለጉን ያሳያል። ያሸነፈው ቡድን የበላይነትን ለማስቀጠል የፈለገ ቡድን ነው። ለመታደስ የተዘጋጀ አይደለም” ብለዋል።

“ከሃላፊነት የተነሱት ለትግራይ ክልል ልዩ ትኩረት ሲሰጡ የነበሩ ናቸው ብሎ መውሰድ ይቻላል” ተብለው ለቀረበላቸው ጥያቄ “አይቻልም። በአንድ ስብሰባ ላይ አቶ አባይ ወልዱ ሲናገሩ ስለአዲስ አበባ አያገባንም። ህወሓት ለፌደራል መንግስት መመደብ ያለባትን የሰው ኃይል መድባለች። ስለዚህም የፌደራል ጉዳይ የተመደቡት አባላት ችግር ነው። እና ተጠያቂነታችን ለትግራይ ሕዝብ ነው። ይህን በማለታቸውም የተለያዩ ቡድኖች እያደራጀ የራሱን ዝና እየገነባ ነበር። ከዚህም መነሻ የምትወስደው፣ የአርከበ፣ የስብሃት እና የደብረፂዮን ቡድን አሸንፎ መውጣቱን ነው የምትመለከተው። በፌደራል ደረጃ ተሸናፊ አለመሆናቸውን ያሳዩበት መድረክ ነው” ሲሉ አቶ አስራት አረዳዳቸውን አካፍለዋል።

“የፖለቲካ ምሕዳሩን ከማስፋት አንፃር ግምገማው ምን ፋይዳ አለው” ለሚለው በሰጡት ምላሽ፣ “የፖለቲካ ምሕዳሩን ከማስፋት አንፃር ምንም ለውጥ አያመጣም፤ የወረደውም የሚወጣውም ህወሓት ነው። ህወሓት ዴሞክራሲን በሚያይበት አቅጣጫ ነው፣ አዲሶቹ ተሸሚዎች የሚመለከቱት። ከድርጅቱ አሰራር ውጪ ዝንፍ አይሉም። ባለፈው የአድዋ ልጆች ተገፋን የሚል ስሞታ አቅርበው ነበር። አሁን በአዲስ መልክ አሸናፊ ሆነው ወጥተዋል። ቀድሞውም ቢሆን የህወሓት ፖለቲካ የአድዋ ፖለቲካ ነው፣ የተለየ ነገር የለውም።  በአድዋ ቤተሰቦች የሚሽከረከር ፖለቲካ ነው። ከበፊትም ቢሆን ተንቤን፣ እንደርታ፣ ሽሬና ራያ ከፖለቲካ ስልጣኑ የተገለሉ ናቸው። አባይ ወልዱ የእነስብሃትን ኔትዎርክ እበጣጥሳለሁ ብሎ እየሰራ ነበር፤ አልተሳካለትም፤ አልቻለም። ቀድመው በጠሱት። የዴሞክራሲ ጥያቄ ሳይሆን፣ የቤተሰቡ ጠብ ገዝፎ ወጥቷል። አሸናፊው የሆነው ኃይል የትግራይን ሕዝብ አስይዞ ቁማር ሊጫወት ይችላል። ከኤርትራ ጋር ባድመን ሰጥቶ ሊታረቅ ይችላል። ከብአዴንና ከኦሕዴድ ጋር የገባውን ሹኩቻ ለማብረድ የትግራይን ሕዝብ ዳግም ዋጋ ሊያስከፍል ይችላል። ከልማት አንፃር ትግራይን መስዋዕት አድርገው ስልጣናቸውን የማስቀጠል ሥራዎች ሊሰሩ ይችላሉ። ለኦሕዴድ መጪው ጊዜ ፈታኝ ነው። ለብአዴን ግን አብረው መስራት የሚችሉ ሃይሎች ናቸው፣ ህወሓትን የተቆጣጠሩት” ሲሉ አቶ አስራት ተናግረዋል።

ሌላው ስሜ አይጠቀስ ያሉ የመገናኛ ብዙሃና ባለሙያ በበኩላቸው፣ “የተወሰደው እርምጃ ደግፈዋል። ምክንያቱም የእርምጃው መነሻ በተቀመጠው አጀንዳ የመጣ በመሆኑ ነው። የውይይቱ አጀንዳዎች ሁሉም የትግራይ ሕዝብ ያውቃቸዋል። ከአቅም ማነስ እስከ ከፀረ ዴሞክራሲ አካሄድ ድረስ የተዘረጉ ናቸው። በጥልቅ ውይይት ተደርጎባቸዋል። ውሳኔውም የሚጠበቅ ነበር። ወጣቱ ላይ እምነት የሌለው አመራር ነው። ወጣቱ በግሎባላይዜሽን እና በተለያዩ የእግር ኳስ፣ የፊልም እና የተለያዩ ሱሶች የተጠመደ ነው የሚል ንቀት አዘል ድምዳሜ የሚሰጥ አመራር ነው። ወጣቱ ወደ ፖለቲካው መግባቱን ለማመን የተቸገሩ ናቸው። አሁንም በማሕራዊ ሚዲያዎች በሚደረግባቸው ጫናዎች ወጣቱን ለመቀበል ምልክቶች አሉ። የሚገርመው በዩኒቨርስቲዎች የሚያስተምሩ የተለያዩ ምርምሮች የሚያደርጉ ወጣቶችን እንኳን ለማየት አይናቸው ያልተገለጠ፣ የፖለቲካ አመራሮች ናቸው ያሉት። ይህንን አመለካት ይዘውት እንዴት ሊዘልቁ ይችላሉ ምላሽ ካልሰጡበት ቀጣይ ግዜው ቀላል አይሆንም። ከዚህ አንፃር የተወሰደው እርምጃ ተገቢ ነው። የነበረው አመራር ወጣቱን በመምራት ውጤታማ ሥራዎች አልሰራም፤ መነሳቱ ተገቢ ነው” ብለዋል።

ሌላው ያነጋገርናቸው አቶ ጌታቸው አረጋዊ የወራይና መጽሔት ማኔጂንግ ዳይሬክተር ሲሆኑ ስለግምገማው እንዲህ ነበር ያሉን፣ “ጥልቀት ያለው ግምገማ እንዳደረጉ መረዳት ይቻላል። ከዚህም በላይ ወደ ግለሂስ ገብተዋል። የተገኘውም ውጤት ጥሩ ነው። የፓርቲውን ደንብ የተከተለ በመሆኑ ተቀባይነቱም ከፍ ያለ ነው። ለውጡም መሰረታዊ ነው። በተለይ በትግራይ ውስጥ ችግሮች እንዲፈጠሩ ዋና ተዋናኝ ሆነው ሲሰሩ የነበሩ ጸረ ዴሞክራሲ የነበሩ አመራሮችን በግልጽ ግምገማ ተገምግመው መውረዳቸው አስደሳች ተደርጎ የሚወሰድ ነው። በግሌ እንደአንድ ክልል ውስጥ የሚኖር ሰው ስመኘው የነበረውን ነው፣ ፓርቲው የፈጸመው። ከዚህ እርምጃ መገመት የሚቻለው ለውጥ የሚፈልግ ኃይል ይመጣል፤ የነበሩት ሁኔታዎች በሙሉ ይቀየራሉ የሚል ተስፋ አለኝ” ብለዋል።

“የህወሓት ችግር የፕሮግራም ወይስ የአመራሩ ነው” ተብሎ ለቀረበላቸው ጥያቄ የሰጡት ምላሽ፣ “የህወሓት ችግር በዋናነት ከአመራሩ የሚመነጭ ነው። ምክንያቱም የህወሓት ፕሮግራም የሁሉም ግንባር ድርጅቶች ፕሮግራም በመሆኑ፣ በትግራይ ውስጥ የተለየ የሚያደርገው ነገር የለም። በክልሎች መካከል ያለው ልዩነት የአመራር ልዩነት እንጂ፣ የፕሮግራም አይደለም። የፕሮግራም ከሆነ ሁሉም አባል ድርጅቶች ተነጋግረው የሚለውጡት ነው የሚሆነው። ስለዚህም በትግራይ ክልል ያለው ግልፅ የአመራር ችግር ነው። ከልማት አጀንዳ አንፃር ለገበያ ከቀረቡ አስተሳሰቦች መካከል አንዱ መሆኑ ብቻ ሳይሆን፣ ልማትም ማምጣት የቻለ ፕሮግራም ድርጅቱ ይዟል። በርግጥ ድርጅቱ የያዘው ፕሮግራም ግኡዝ ተደርጎ የሚወሰድ አይደለም። ከተጨባጭ ሁኔታዎች ጋር የሚከለስ ነው የሚሆነው። ከተጨባጭ ሁኔታዎችና ከተለዋዋጭ ሁኔታዎች ጋር መጓዝ የሚችል አመራር ህወሓት የላትም። ሥራ ከመስራት በኔትዎርክ የታጠረ፣ በሃሜትና አልቧልታ የደነዘዘ፣ በማጥቃትና በመከላከል ዙሪያ የተጠመደ፣ የተወጠረ በመሆኑ፣ ከልማትና ከዴሞክራሲ ራሱን ያራቀ አመራር ነበር የነበረው። መቆረጡ ቢዘገይም፣ እርምጃው ግን ተገቢ ነው። የሚመጣውም አመራር ከላይ የሰፈሩትን ችግሮች የሚቀርፍ ይሆናል። አመራር መቀየር የአፈፃጸም አሰራሮች ስለሚቀይራቸው የተሻለ ነገር ይጠበቃል። ከዚህ ውጪ ያለው አማራጭ እንደድርጅት መፍረስ ብቻ ነው። ስለዚህም ፈጣን የፕሮግራም ለውጥ ሳይሆን ቢያንስ ያለውን በተገቢው መንገድ ለሕዝቡ ተደራሽ ማድረግ ከቀጣዩ አመራር የሚጠበቅ ነው” ሲሉ አቶ ጌታቸው ተስፋቸውን አስቀምጠዋል።¾ 

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
448 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 56 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us